አቅኚነት—ጊዜያችንን በጥበብ የምንጠቀምበት መንገድ!
1 ‘አሁንም እንኳ ብዙ የምሠራቸው ነገሮች አሉ! ታዲያ በዚህ ጊዜ አቅኚነት ብጀምር በእርግጥ ጥበብ ይሆናል?’ አንዲት እህት፣ አቅኚ የሆነ ሽማግሌ በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ “በአቅኚነት አገልግሎት ወደፊት መግፋት” በሚል ጭብጥ ያቀረበውን ንግግር በምታዳምጥበት ጊዜ ከላይ እንደተጠቀሰው ብላ አስባለች። በዚያው ስብሰባ ላይ የተገኘ አንድ ወጣት ወንድም ‘አቅኚ ሆኖ ማገልገል የቻለው እንዴት ነው? እኔ ሽማግሌ አይደለሁም፤ ሆኖም አሁንም ቢሆን ሕይወቴ በሥራ ተይዟል!’ ሲል አስቧል።
2 ሽማግሌው አቅኚነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ማብራራቱን ሲቀጥል አቅኚ ለመሆን ሲሉ ያደረጓቸውን ማስተካከያዎችና ይሖዋ ጥረታቸውን በምን መንገድ አትረፍርፎ እንደባረከላቸው እንዲናገሩ በወረዳው ከሚገኙ ጥቂት አቅኚዎች ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። ከእነርሱ መካከል የአካል ጉዳተኛ የሆነ፣ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላት እንዲሁም ዓለማዊ ሥራውን የተወና መሠረታዊ ለሆኑ ነገሮች የሚበቃ ገቢ ብቻ ያለው ወንድም ይገኙበታል። ስብሰባው ላይ የነበሩት ወንድምና እህት አቅኚዎቹ በይሖዋ እርዳታ እንዴት እንደተሳካላቸው የሚናገሩትን ሲያዳምጡ የራሳቸውን አመለካከትና ሁኔታ እንደገና መመርመር ጀመሩ። በተለይ ደግሞ አቅኚዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው ሰዓት በመቀነሱ አሁን በርካታ ቁጥር ያላቸው የምሥራቹ አስፋፊዎች ሊደርሱበት የሚችሉ ግብ ስለሆነ እናንተም ሁኔታችሁን እንድትመረምሩ እናበረታታችኋለን።
3 ይሖዋ ፈጣሪና የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ እንደሆነና ሕይወት ሰጪያችንም እርሱ መሆኑን እናውቃለን። (ዳን. 4:17፤ ሥራ 17:28) ይሖዋ በአንድ ድርጅት ብቻ እንደሚጠቀም ግልጽ ነው። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የመንግሥቱን ምሥክርነት እየሰጠን ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ በመደገፍ ከዚህ ድርጅት ጋር በታማኝነት የማገልገል መብት አግኝተናል። (ማቴ. 24:45፤ 25:40፤ 1 ጴጥ. 2:9) ወደ ‘መጨረሻው ቀን’ ዘልቀን ስለገባን መስበክ የምንችልበት ጊዜ እየተገባደደ መሆኑን እንገነዘባለን። (2 ጢሞ. 3:1) ከዚህ በተጨማሪ ቤተሰቦቻችን የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 5:8) አንድ ሰው የሚያገኘው ገቢ እንደ በፊቱ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ላይብቃቃለት ይችላል። ምናልባትም እንደ ቀድሞው ጤና ላይኖረን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ራሳችንን የምናዝናናበት ጥቂት ጊዜና ገንዘብ እንዲኖረንም እንፈልጋለን። (መክ. 3:12, 13) በመሆኑም አቅኚ እንድንሆን ለቀረበልን ጥሪ ምላሽ መስጠታችን በእርግጥ ጥበብ ይሆናል ወይ ብለን እናስብ ይሆናል።
4 የግል ሁኔታዎቻችንን በጥንቃቄ መገምገሙና አቅኚ ለመሆን መቻል አለመቻላችንን መወሰኑ ለእያንዳንዳችን የተተወ ነው። (ሮሜ 14:12፤ ገላ. 6:5) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አቅኚ እንድንሆን ለቀረበው ጥሪ ምላሽ መስጠታቸውን ማወቁ ያበረታታል። የመጨረሻው ቀን የሚያስከትላቸው ጫናዎችና ችግሮች ቢኖሩም በ1999 የዓመት መጽሐፍ ላይ የወጣው የአገልግሎት ሪፖርት በዓለም ዙሪያ ወደ 700,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች በአቅኚነት አገልግሎት በትጋት መቀጠላቸውን ያሳያል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች፣ የትራንስፖርት እጦት፣ የጤና እክል ወይም ሌሎች ችግሮችና መከራዎችን እየተጋፈጡ ቢሆንም መልካም የሆነውን ነገር ለመሥራት አለመታከታቸው የሚያስመሰግን ነው። (ገላ. 6:9) ይሖዋ ፈትኑኝ ሲል ያቀረበውን ግብዣ ተቀብለዋል። (ሚል. 3:10) አቅኚነት ውስን የሆነ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን የሚጠቀሙበት የተሻለ የጥበብ መንገድ እንደሆነና አቅኚነትን ለመጀመርና በዚያው ለመቀጠል አስፈላጊ ማስተካከያዎችን በማድረጋቸውም ይሖዋ እንደባረካቸው ይሰማቸዋል።
5 አቅኚዎች እየተባረኩ ነው፦ በካሜሩን የምትኖር አንዲት ሕፃን ልጅ ያለቻት እህት እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ልጄን ከተወለደችበት ጊዜ አንስቶ ሁልጊዜ ወደ አገልግሎት ይዣት እወጣ ነበር። መራመድ ከመቻሏ በፊት እንኳ በጨርቅ አዝያት እሄድ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት መንገድ ዳር በሚገኝ ሱቅ አጠገብ ቆሜ ሳለ ከቦርሳዬ ውስጥ በርከት ያሉ መጽሔቶች ወሰደችና ከአጠገቤ ተነስታ በአቅራቢያው ወዳለ ሌላ ሱቅ ድክ ድክ እያለች ሄደች። ብዙ የምትለው ነገር ባይኖራትም የአንዲትን ሴት ትኩረት የሳበች ከመሆኑም በላይ አንድ መጽሔት አበረከተችላት። ሴትዮዋ አንዲት ሕፃን ልጅ በዚህ ሥራ ስትካፈል ማየቷ ራሱ አስደነቃት። መጽሔቱን ከመውሰዷም በላይ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተስማማች!”
6 ተጨማሪ ረዳት አቅኚዎች እንደሚያስፈልጉ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ በመስጠት በዛምቢያ የሚኖር የሙሉ ቀን ዓለማዊ ሥራ ያለው አንድ ሽማግሌና የቤተሰብ ራስ ፕሮግራሙ የተጣበበ ቢሆንም እንኳ በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ወሰነ። ለጉባኤውም ሆነ ለቤተሰቡ ምሳሌ መሆን ፈልጎ ነበር። አንዳንድ ጊዜ መኪናውን መንገድ ዳር አቁሞ በቴፕ ክር የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ይከፍትና በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች ገብተው የሚነበበውን እንዲያዳምጡ ይጋብዛቸዋል። በዚህ መንገድ 16 የቤተሰብ ደስታ እና 13 የእውቀት መጻሕፍት ማበርከት የቻለ ሲሆን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም አስጀምሯል።
7 አጎራባች አገር በሆነችው በዚምባብዌም ጥሩ የአቅኚነት መንፈስ ታይቷል። በሚያዝያ 1998፣ 117 አስፋፊዎች ያሉት አንድ ጉባኤ 70 ረዳት አቅኚዎችና 9 የዘወትር አቅኚዎች ሪፖርት አድርጓል። ዘጠና አራት አስፋፊዎች ያሉት ሌላ ጉባኤ ደግሞ ሪፖርት የመለሱ 58 ረዳት አቅኚዎች ነበሩት። እንዲሁም 126 አስፋፊዎች ያሉት ሌላ ጉባኤ በጉባኤው ካሉት 4 የዘወትር አቅኚዎች ጋር ለማገልገል የወሰኑ 58 ረዳት አቅኚዎችን ሪፖርት አድርጓል። ያለፈው የአገልግሎት ዓመት በዚምባብዌ ጉልህ ስፍራ ነበረው። ምንም እንኳ በዚያ የሚኖሩ ወንድሞች በቤተሰብ ጉዳዮች፣ በጉባኤ እንቅስቃሴዎችና በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ምክንያት ከፍተኛ የሥራ ጫና የነበረባቸው ቢሆንም ጊዜያቸውን ጥበብ በተሞላበት መንገድ በአገልግሎት ለማሳለፉ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተውት ነበር።
8 አቅኚዎች አቅኚነትን መጀመርና በዚያው መጽናት በራሳቸው ብርታት ላይ የተመካ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። አቅኚዎች የትኛውም ነገር ሊሳካላቸው የቻለው ‘አምላክ በሚሰጣቸው ኃይል’ መሆኑን ለማመን ቀዳሚዎች ናቸው። (1 ጴጥ. 4:11) እምነታቸው ከቀን ወደ ቀን በአገልግሎት እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል። ስኬታማ የሆኑ አቅኚዎች የራሳቸውን ምቾትና ደስታ ከማሳደድ ይልቅ በጽናት መቀጠል ‘ብዙ ገድል’ ሊጠይቅ እንደሚችል ይገነዘባሉ፤ ሆኖም እንዲህ በማድረጋቸው ብዙ በረከቶች ያገኛሉ።—1 ተሰ. 2:2
9 ጳውሎስ ልንኮርጀው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል፦ መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በአገልግሎቱ ያከናወነውን ነገርና ለብዙ ሰዎች ያበረከተውን ጠቃሚ እርዳታ መዝግቦ ይዞልናል። ሥራ ይበዛብናል የምንል ከሆነ ጳውሎስም ሥራ የበዛበት ሰው ነበር። ምሥራቹን ለመስበክና ጉባኤዎችን ለማነጽ ሲል የደረሰበትን ስደትና እንግልት በጽናት አሳልፏል። እንዲሁም የነበረበትን ከፍተኛ የጤና እክል ችሎ መኖር ነበረበት። (2 ቆሮ. 11:21-29፤ 12:7-10) ጊዜውን ጥበብ በተሞላበት መንገድ ለመጠቀም ቆርጦ ነበር። ሥራውን ሁሉ ሊያከናውን የቻለው በይሖዋ እርዳታ መሆኑን ገልጿል። (ፊልጵ. 4:13) ጳውሎስ ከረዳቸው ሰዎች መካከል ማናቸውም ቢሆኑ ይሖዋን በማገልገል ያዋለው ጊዜና ጉልበት እንዲሁ ባክኗል ወይም በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት ይችል ነበር የሚሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እንዲያውም እኛም ጳውሎስ ጊዜውን በጥበብ በመጠቀሙ የተገኘው ውጤት ተቋዳሽ ሆነናል! ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ምክር በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ማስቀደም ያለብንን ነገሮች ለይተን እንድናውቅና እውነትን አጥብቀን እንድንይዝ ለመርዳት ምንኛ ጠቅሞናል!
10 ዛሬ ‘ምሥራቹን መስበክ የምንችልበት ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጭር ሆኖአል።’ (1 ቆሮ. 7:29፤ ማቴ. 24:14) ስለዚህ ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘ድንገት በነገው ዕለት ሕይወቴ ቢቀጭ፣ ዛሬ ጊዜዬን በጥበብ ተጠቅሜበታለሁ ብዬ ለይሖዋ መናገር እችላለሁ?’ (ያዕ. 4:14) ከምሥክሮቹ አንዱ እንደመሆንህ መጠን ጊዜህን በጥበብ ልትጠቀምበት እንደምትፈልግ በመግለጽ ለምን አሁኑኑ ለይሖዋ በጸሎት አትነግረውም? (መዝ. 90:12 NW) ሕይወትህን ቀላል ለማድረግ የይሖዋን እርዳታ በጸሎት ጠይቅ። ከዚህ በፊት አቅኚ መሆን አልችልም ብለህ ወስነህ ይሆናል። አሁንስ አቅኚነት በሕይወትህ ውስጥ ቦታ ሊኖረው ይችል ይሆን?
11 ያለህን አጋጣሚ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት፦ የዘወትር አቅኚ ለመሆን ፍላጎት ቢኖራቸውም ከሁኔታቸው አንጻር በወር 70 ሰዓት መመደብ የሚችሉ ሁሉም እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በርካታ አስፋፊዎች በሚያመቻቸው ጊዜ ሁሉ ወይም ሳያቋርጡ ረዳት አቅኚ ሆነው በአገልግሎት በወር 50 ሰዓት ለማሳለፍ ዝግጅት ያደርጋሉ። በአሁኑ ጊዜ ሁኔታህ ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ እንድትሆን የማይፈቅድልህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ያለህበት ሁኔታ እንዲሻሻል መጸለይህን አታቋርጥ። ለውጥ ማድረግ እስክትችል ድረስ ግን ይሖዋ እርሱን በሙሉ ነፍስ ለማገልገል በምታደርገው ጥረት እንደሚደሰት ማወቁ ሊያጽናናህ ይገባል። (ማቴ. 13:23) ከእርሱ ጎን በጽናት እንደቆምክና አንድም ወር ቢሆን ለመመስከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች እንዲያመልጡህ የማትፈቅድ ታማኝ አስፋፊ ለመሆን በትጋት እንደምትጥር ይመለከታል። ምናልባትም የምሥራቹ ሰባኪና አስተማሪ እንደመሆንህ መጠን ችሎታህን ለማሻሻል በመጣር ባለህ የመመስከር ጥበብ ረገድ እድገት ማድረግ ትችላለህ።—1 ጢሞ. 4:16
12 ‘ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ እጅግ በቀረበበት በአሁኑ ጊዜ እንድንሠራው የተሰጠንን ተልዕኮ ማጠናቀቅ እንችል ዘንድ ቀሪውን ጊዜ በጥበብ መጠቀም ይኖርብናል። (ኢዩ. 2:31) ሰይጣን አጭር ጊዜ እንደቀረው ያውቃል። በመሆኑም ሕይወታችንን ለማወሳሰብና በእርግጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ ትኩረታችን እንዳያርፍ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አቅሙ የሚፈቅድለትን ሁሉ ለማድረግ እየተፍጨረጨረ ነው። (ፊልጵ. 1:10፤ ራእይ 12:12) አምላክ ለአንተ የሚሰጠውን ትኩረት አቅልለህ አትመልከት። ይሖዋ ቀላል ሕይወት እንድትመራና በአገልግሎቱ በሙሉ ኃይልህ እንድትሠራ ሊረዳህ ይችላል። (መዝ. 145:16) ብዙዎች ሁኔታቸውን እንደገና በመገምገም ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚዎች መሆን እንደሚችሉ መገንዘባቸው ያስደስታል። በእርግጥም አቅኚዎች ጊዜያቸውን በጥበብ በመጠቀማቸው ጥልቅ እርካታ ያገኛሉ። አንተስ ከእነርሱ አንዱ ትሆናለህ?