ረቡዕ፣ ሐምሌ 30
ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።—ሥራ 4:20
የመንግሥት ባለሥልጣናት መስበካችንን እንድናቆም ቢያዝዙንም መስበካችንን በመቀጠል የደቀ መዛሙርቱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይሖዋ አገልግሎታችንን ለመፈጸም እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን። ስለዚህ ይሖዋ ድፍረትና ጥበብ እንዲሰጠን እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም እንዲረዳን እንጠይቀው። ብዙዎቻችን አካላዊ ሕመም፣ ስሜታዊ ቀውስ፣ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት፣ የቤተሰብ ችግር፣ ስደት ወይም ሌላ ዓይነት ፈተና ያጋጥመናል። እንደ ጦርነትና ወረርሽኝ ያሉት ነገሮች ደግሞ የሚያጋጥመንን ችግር መቋቋም ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋሉ። እንግዲያው በይሖዋ ፊት ልብህን አፍስስ። ለአንድ የቅርብ ጓደኛህ እንደምታደርገው፣ የሚሰማህን ነገር ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። ይሖዋ “ለአንተ ሲል እርምጃ” እንደሚወስድ እርግጠኛ ሁን። (መዝ. 37:3, 5) ሳንታክት መጸለያችን ‘መከራን በጽናት ለመቋቋም’ ይረዳናል። (ሮም 12:12) ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚደርስባቸውን መከራ ያውቃል፤ “እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል።”—መዝ. 145:18, 19፤ w23.05 5-6 አን. 12-15
ሐሙስ፣ ሐምሌ 31
በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።—ኤፌ. 5:10
ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ስናደርግ “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ” ማስተዋልና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:17) ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ስንፈልግ አምላክ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት እያደረግን ነው። ከዚያም የእሱን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን። “ክፉው” የተባለው ጠላታችን ሰይጣን በዚህ ዓለም ጉዳዮች ከመጠመዳችን የተነሳ ለአምላክ አገልግሎት ጊዜ እንድናጣ ማድረግ ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 5:19) አንድ ክርስቲያን ካልተጠነቀቀ አምላክን ለማገልገል ከሚያስችሉት አጋጣሚዎች ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች፣ ለትምህርት ወይም ለሙያው ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮበታል ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት እንዳልሆኑ አይካድም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ ሊይዙ አይገባም። w24.03 24 አን. 16-17
ዓርብ፣ ነሐሴ 1
የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።—መዝ. 34:19
በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ልብ በል። (1) ጻድቅ የሆኑ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። (2) ይሖዋ ከሚያጋጥመን መከራ ይታደገናል። ይሖዋ የሚታደገን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለንን ሕይወት በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን በመርዳት ነው። ይሖዋ እሱን በማገልገል ደስታ እንደምናገኝ ቃል ቢገባልንም በአሁኑ ዘመን ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምንመራ ዋስትና አልሰጠንም። (ኢሳ. 66:14) እሱ እንድንኖር የሚፈልገውን ሕይወት ለዘላለም በምናጣጥምበት በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) እስከዚያው ግን ለእያንዳንዱ ቀን የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። (ሰቆ. 3:22-24) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ በዘመናችን የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሁላችንም ያልተጠበቁ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ ከታመንን እሱ ምንጊዜም ይደግፈናል።—መዝ. 55:22፤ w23.04 14-15 አን. 3-4