የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “አምላክን እንዲፈልጉትና . . . እንዲያገኙት”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • ምዕራፍ 18

      “አምላክን እንዲፈልጉትና . . . እንዲያገኙት”

      ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር የሚያግባባውን ርዕሰ ጉዳይ መርጧል፤ የሚሰብክበትን መንገድ እንደ ሁኔታው አስተካክሏል

      በሐዋርያት ሥራ 17:16-34 ላይ የተመሠረተ

      1-3. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ሳለ በጣም የተረበሸው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

      ጳውሎስ በጣም ተረብሿል። የትምህርት ማዕከል በሆነችው አቴንስ፣ ግሪክ እየተዘዋወረ ነው፤ በአንድ ወቅት ሶቅራጥስ፣ ፕላቶና አርስቶትል በዚህች ከተማ አስተምረዋል። የአቴንስ ነዋሪዎች ሃይማኖተኛ ናቸው። ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር፤ ጳውሎስ በሄደበት ሁሉ፣ በየቤተ መቅደሱ፣ በየአደባባዩም ሆነ በየጎዳናው ጣዖት የሌለበት የለም። ጳውሎስ፣ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ስለ ጣዖት አምልኮ ምን አመለካከት እንዳለው ያውቃል። (ዘፀ. 20:4, 5) ይህ ታማኝ ሐዋርያ ልክ እንደ ይሖዋ ጣዖታትን ይጸየፋል!

      2 ጳውሎስ በተለይ ወደ ገበያ ስፍራው ሲገባ ያየው ነገር በጣም የሚያስደነግጥ ነው። በስተ ሰሜን ምዕራብ በሚገኘው ማዕዘን ላይ በዋናው በር አጠገብ፣ ሄርሜስ የተባለው አምላክ አስጸያፊ ሐውልቶች ተደርድረዋል። የገበያ ስፍራው በአምልኮ ቦታዎች የተሞላ ነው። ይህ ቀናተኛ ሐዋርያ የጣዖት አምልኮ በተስፋፋበት በዚህ ቦታ መስበክ የሚችለው እንዴት ነው? ስሜቱን ተቆጣጥሮ፣ ከአድማጮቹ ጋር በሚያግባባው ርዕስ ላይ መወያየት ይችል ይሆን? አድማጮቹ እውነተኛውን አምላክ እንዲፈልጉና እንዲያገኙት ለመርዳት የሚያደርገው ጥረትስ ይሳካለት ይሆን?

      3 ጳውሎስ በአቴንስ ለሚኖሩ የተማሩ ሰዎች የሰጠው ግሩም ንግግር በሐዋርያት ሥራ 17:22-31 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ግሩም የንግግር ጥበብ፣ ብልሃትና ማስተዋል የተንጸባረቀበት በመሆኑ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ በመመርመር፣ ከሌሎች ጋር የሚያግባባንን ርዕሰ ጉዳይ መምረጥና ነጥቡን እንዲያገናዝቡ መርዳት ስለምንችልበት መንገድ ብዙ እንማራለን።

      “በገበያ ስፍራ” ማስተማር (የሐዋርያት ሥራ 17:16-21)

      4, 5. ጳውሎስ አቴንስ ውስጥ በየትኞቹ ቦታዎች ሰበከ? በዚያስ ምን ዓይነት ሰዎች አጋጠሙት?

      4 ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን እያደረገ ነው፤ በ50 ዓ.ም. ገደማ ወደ አቴንስ ሄደ።a ሲላስና ጢሞቴዎስ ከቤርያ እስኪመጡ እየጠበቀ ሳለ እንደ ልማዱ “በምኩራብ ከአይሁዳውያን . . . ጋር ይወያይ ጀመር።” በተጨማሪም አይሁዳውያን ያልሆኑ የአቴንስ ነዋሪዎችን ለማግኘት ወደ “ገበያ ስፍራ” ሄደ። (ሥራ 17:17) ከአክሮፖሊስ በስተ ሰሜን ምዕራብ የሚገኘው የአቴንስ የገበያ ስፍራ 5 ሄክታር ገደማ ይሸፍናል። ይህ የገበያ ቦታ የንግድ አካባቢ ብቻ አልነበረም፤ ሰዎች የሚሰባሰቡበት የከተማዋ አደባባይ ነበር። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ ይህ ቦታ “የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ማዕከል” እንደነበር ገልጿል። የአቴንስ ነዋሪዎች እዚያ ተሰባስበው ጥልቅ እውቀት በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ መወያየት ያስደስታቸው ነበር።

      አቴንስ—የጥንቱ ዓለም የባሕል ማዕከል

      የአቴንስ ታሪክ በጽሑፍ መስፈር የጀመረው በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነው፤ የከተማዋ አክሮፖሊስ ግን ከዚያም በፊት ለረጅም ጊዜ የኖረ አስተማማኝ ምሽግ ነበር። አቴንስ በተራሮችና በባሕር የተከበበች ከተማ ስትሆን 2,500 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ በሚገኘው በአቲካ አውራጃ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት ከተማ ነበረች። ስያሜዋ፣ የከተማዪቱ ጠባቂ አምላክ ተደርጋ ከምትታየው ከአቴና ጋር ተዛማጅነት ያለው ይመስላል።

      በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ሶሎን የተባለ የአቴንስ ተወላጅ የሆነ ሕግ አውጪ በከተማዋ የማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ፣ የሕግና የኢኮኖሚ መዋቅሮች ላይ ለውጥ አካሄደ። ይህም የድሆች ኑሮ እንዲሻሻል አደረገ፤ የዲሞክራሲ አገዛዝ መሠረቱ የተጣለውም በዚሁ ወቅት ነው። ይሁንና ዲሞክራሲው የሚሠራው ነፃ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ነበር፤ አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ ባሪያዎች ነበሩ።

      በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ግሪካውያን በፋርሳውያን ላይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ አቴንስ የንጉሣዊው መንግሥት ዋና ከተማ ሆነች፤ ይህ መንግሥት የባሕር ላይ ንግዱን አስፋፋ፤ በስተ ምዕራብ ከሚገኙት ከጣሊያንና ከሲሲሊ አንስቶ በስተ ምሥራቅ እስካሉት እስከ ቆጵሮስና ሶርያ ድረስ መነገድ ጀመረ። ከተማዋ በገናናነቷ ዘመን የጥንቱ ዓለም የባሕል ማዕከል ሆናለች፤ በኪነ ጥበብ፣ በድራማ፣ በፍልስፍና፣ በንግግር ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍና በሳይንስ ስመ ጥር ነበረች። ለከተማዋ ድምቀት የሚሰጡ በርካታ ሕንፃዎችና ቤተ መቅደሶችም ነበሩ። በአክሮፖሊስ ኮረብታ ላይ ጎልቶ የሚታይ አንድ ቤተ መቅደስ አለ፤ በዚህ ግዙፍ የፓርተኖን ቤተ መቅደስ ውስጥ ደግሞ 12 ሜትር ርዝማኔ ያለው ከወርቅና ከዝሆን ጥርስ የተሠራ የአቴና ሐውልት ቆሟል።

      አቴንስ በመጀመሪያ በስፓርታውያን ከዚያም በመቄዶናውያን ቁጥጥር ሥር ውላለች፤ በመጨረሻም ሮማውያን ከተማዋን ድል አድርገው ሀብቷን ጠራርገው ወሰዱ። ያም ሆኖ አቴንስ በቀድሞ ዝናዋ የተነሳ በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመንም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣት ከተማ ነበረች። እንዲያውም ከተማዋ በየትኛውም የሮም ግዛት ሥር እንድትጠቃለል አልተደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ዜጎቿን ራሷ እንድታስተዳድር ሥልጣን የተሰጣት ከመሆኑም ሌላ ከሮም ቀረጥ ነፃ ነበረች። አቴንስ የቀድሞ ክብሯን ብታጣም የሀብታም ልጆች ለትምህርት የሚላኩባት የዩኒቨርሲቲ ከተማ ሆና ቀጥላለች።

      5 ጳውሎስ በዚህ የገበያ ቦታ ያገኛቸው ሰዎች በቀላሉ ሊያሳምናቸው የሚችል አልነበሩም። ከአድማጮቹ መካከል ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦይኮች ይገኙበታል፤ ሁለቱ ቡድኖች በጣም የተለያዩ ፍልስፍናዎችን ያራምዳሉ።b ኤፊቆሮሳውያን ‘ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ነው’ የሚል አመለካከት ነበራቸው። ስለ ሕይወት ያላቸውን አመለካከት በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል፦ “አምላክን ለመፍራት ምክንያት የለም፤ የሞተ ምንም አይሰማውም፤ ጥሩን ማግኘት ይቻላል፤ ክፋትንም ችሎ ማሳለፍ ይቻላል።” ኢስጦይኮች በምክንያትና በአመክንዮ (ሎጂክ) ማመንን በጣም ያበረታታሉ፤ አምላክ የራሱ ሕልውና ያለው አካል እንደሆነ አያምኑም። ኤፊቆሮሳውያንም ሆኑ ኢስጦይኮች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚያስተምሩትን የትንሣኤ ትምህርት አይቀበሉም። እነዚህ ሁለት ቡድኖች የሚያራምዱት ፍልስፍና፣ ጳውሎስ ከሚያስተምራቸው የላቁ የክርስትና እውነቶች ጋር ፈጽሞ እንደማይጣጣም ግልጽ ነው።

      6, 7. በግሪክ የነበሩ አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ለጳውሎስ ትምህርት ምን ምላሽ ሰጡ? በዛሬው ጊዜስ ምን ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል?

      6 ታዲያ እነዚህ የግሪክ ምሁራን ለጳውሎስ ትምህርት ምን ምላሽ ሰጡ? አንዳንዶቹ “ለፍላፊ” ብለውታል፤ ግሪክኛው ቃል ”ጥሬ ለቃሚ” የሚል ትርጉምም አለው። (የ⁠ሥራ 17:18⁠ን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፣ nwtsty-E) ይህን ግሪክኛ ቃል በተመለከተ አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “መጀመሪያ ላይ ቃሉ፣ ወዲያ ወዲህ እያለች ጥሬ የምትለቅምን ትንሽ ወፍ ለማመልከት ይሠራበት ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ በገበያ ስፍራ የምግብ ፍርፋሪና የወዳደቁ ነገሮች የሚለቃቅሙ ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ቆየት ብሎ ደግሞ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ቃል ሆነ፤ ምንም ተዛማጅነት የሌላቸውን ወሬዎች ከዚያም ከዚህም የሚለቃቅም በተለይ ደግሞ የሰማውን ነገር ምንም ሳይረዳ ለሌሎች የሚቀባጥርን ሰው ያመለክት ጀመር።” እነዚህ ምሁራን፣ ጳውሎስ የሰማውን ሳያመዛዝን የሚደግም ቀባጣሪ እንደሆነ እየተናገሩ ነበር። ይሁንና ቀጥሎ እንደምንመለከተው ጳውሎስ፣ በዚህ የንቀት ቃል አልተሸማቀቀም።

      7 ዛሬ ያለው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው እምነታችን የተነሳ ብዙውን ጊዜ መጥፎ ስም ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ምሁራን ዝግመተ ለውጥ ተጨባጭ ማስረጃ ያለው እውነታ እንደሆነ ያስተምራሉ፤ አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው ሊቀበለው እንደሚገባም ይናገራሉ። ይህን ሲሉ፣ ‘በዝግመተ ለውጥ የማያምኑ ሰዎች መሃይም ናቸው’ ማለታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር ማስተማራችንና በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን ንድፍ ማስረጃ አድርገን ማቅረባችን ተማርን ለሚሉት ለእነዚህ ሰዎች ሞኝነት ነው፤ ‘ጥሬ ለቃሚዎች’ የማለት ያህል በሰዎች ፊት ሊያብጠለጥሉን ይሞክራሉ። እኛ ግን በዚህ አንሸማቀቅም። ከዚህ ይልቅ በልበ ሙሉነት መናገራችንን እንቀጥላለን፤ በምድር ላይ ያለው ሕይወት የላቀ ንድፍ አውጪ እንዳለው፣ እሱም ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ከመናገር ወደኋላ አንልም።—ራእይ 4:11

      8. (ሀ) ጳውሎስ ሲሰብክ የሰሙ አንዳንድ ሰዎች ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) ጳውሎስ ወደ አርዮስፋጎስ ተወሰደ ሲባል ምን ማለት ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

      8 ጳውሎስ በገበያ ስፍራ ሲሰብክ አንዳንዶች ደግሞ ምላሻቸው ከዚህ የተለየ ነበር። “ስለ ባዕዳን አማልክት የሚያውጅ ይመስላል” አሉ። (ሥራ 17:18) በእርግጥ ጳውሎስ ለአቴንስ ነዋሪዎች አዳዲስ አማልክትን እያስተዋወቀ ነበር? ይህ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ክስ ነው፤ ከተወሰኑ መቶ ዘመናት በፊት ሶቅራጥስ ከተከሰሰባቸውና ለሞት ፍርድ ካበቁት ክሶች አንዱ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ጳውሎስ ወደ አርዮስፋጎስ ተወስዶ ለአቴንስ ነዋሪዎች እንግዳ የሆኑባቸውን ትምህርቶች እንዲያብራራ መጠየቁ ምንም አያስገርምም።c ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማያውቁ ሰዎች መልእክቱን እንዴት ያስረዳ ይሆን?

      ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦይኮች

      ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦይኮች ሁለት የተለያዩ ፍልስፍናዎችን የሚያራምዱ ቡድኖች ናቸው። ሁለቱም ቡድኖች በትንሣኤ አያምኑም።

      ኤፊቆሮሳውያን በአማልክት መኖር ቢያምኑም ስለ ሰዎች ግድ እንደማይሰጣቸው ይሰማቸዋል፤ አማልክት ሰዎችን ‘አይባርኩምም፣ አይቀጡምም’ የሚል አመለካከት ነበራቸው፤ በመሆኑም ወደ እነሱ መጸለይም ሆነ ለእነሱ መሥዋዕት ማቅረብ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ያምኑ ነበር። ኤፊቆሮሳውያን፣ በሕይወት ውስጥ ትልቁ ነገር ደስታ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አስተሳሰባቸውም ሆነ ድርጊታቸው ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር መመሪያ እንደሌላቸው ያሳያል። ሆኖም መረን የለቀቀ አኗኗር የሚያስከትላቸውን መዘዞች ለመከላከል ሲባል ልከኛ መሆንን ያበረታታሉ። የእውቀት ሚና ሰዎችን ከሃይማኖታዊ ፍርሃትና ከአጉል እምነት ማላቀቅ ብቻ እንደሆነ ያምኑ ነበር።

      ኢስጦይኮች ደግሞ አምላክ፣ የራሱ አስተሳሰብም ሆነ ስሜት የሌለው ኃይል እንደሆነ ያምናሉ፤ የሰውን ነፍስ ጨምሮ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ የዚህ አምላክ ወይም ኃይል ክፍል እንደሆኑ ይናገራሉ። አንዳንድ ኢስጦይኮች ነፍስ ከጊዜ በኋላ ከጽንፈ ዓለም ጋር ትጠፋለች የሚል አመለካከት አላቸው። ሌሎች ኢስጦይኮች ደግሞ በስተ መጨረሻ ነፍስ ተመልሳ ወደዚህ አምላክ ትገባለች ብለው ያምናሉ። የኢስጦይክ ፈላስፎች እንደሚሉት ከሆነ ደስታ የሚገኘው የተፈጥሮን ሕግ በመከተል ነው።

      “የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ . . . አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ” (የሐዋርያት ሥራ 17:22, 23)

      9-11. (ሀ) ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር ሊያግባባው የሚችል ርዕስ በማንሳት ውይይቱን የጀመረው እንዴት ነው? (ለ) በአገልግሎታችን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

      9 ጳውሎስ በዚያ ስፍራ የጣዖት አምልኮ ተስፋፍቶ በማየቱ በጣም ተረብሾ እንደነበር አስታውስ። ይሁንና የጣዖት አምልኮን በቀጥታ አላወገዘም፤ ከዚህ ይልቅ ስሜቱን ተቆጣጥሮ ከአድማጮቹ ጋር ሊያግባባው የሚችል ርዕስ በዘዴ በማንሳት ልባቸውን ለመንካት ጥረት አድርጓል። ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው “የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ” በማለት ነው። (ሥራ 17:22) በሌላ አነጋገር ‘ሃይማኖተኛ ሰዎች እንደሆናችሁ አስተውያለሁ’ ማለቱ ነበር። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች በሃይማኖታዊ ዝንባሌያቸው ማመስገኑ ጥበብ ነው። በሐሰት እምነት ከታወሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ መልእክቱን ሊቀበሉ እንደሚችሉ ተገንዝቦ ነበር። እሱ ራሱም ቢሆን በአንድ ወቅት “ባለማወቅና ባለማመን” ይመላለስ እንደነበር ያውቃል።—1 ጢሞ. 1:13

      10 ጳውሎስ የአቴንስ ሰዎች ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንዳላቸው የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ይኸውም “ለማይታወቅ አምላክ” ተብሎ የተሠራ መሠዊያ እንዳየ ጠቀሰ። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው “ግሪካውያንም ሆኑ ሌሎች ሕዝቦች ‘ለማይታወቁ አማልክት’ መሠዊያ የመሥራት ልማድ ነበራቸው፤ ምናልባት የተረሳ አምላክ ካለ ሊቀየመን ይችላል ብለው ይፈሩ ነበር።” የአቴንስ ሰዎች እንዲህ ያለ መሠዊያ መሥራታቸው፣ እነሱ የማያውቁት አምላክ መኖሩን አምነው መቀበላቸውን ያሳያል። ጳውሎስ ይህን መሠዊያ እንደ መሸጋገሪያ አድርጎ በመጠቀም የሚሰብከውን ምሥራች አስተዋወቀ። “ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ አሳውቃችኋለሁ” አላቸው። (ሥራ 17:23) ጳውሎስ መልእክቱን ያቀረበው በዘዴ ሆኖም አሳማኝ በሆነ መንገድ ነበር። አንዳንዶች እንደወነጀሉት ስለ አንድ አዲስ ወይም እንግዳ የሆነ አምላክ እየሰበከ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እነሱ ‘የማይታወቅ አምላክ’ ብለው ስለሰየሙት አምላክ ይኸውም ስለ እውነተኛው አምላክ እያብራራላቸው ነበር።

      11 በአገልግሎታችን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? አስተዋዮች ከሆን የምናነጋግረው ሰው ሃይማኖተኛ መሆኑን የሚጠቁም ማስረጃ ልናይ እንችላለን፤ ምናልባትም የለበሰው ወይም ያደረገው አሊያም ቤቱ ወይም ግቢው ውስጥ የሚታየው ነገር ይህን ሊጠቁመን ይችላል። ከዚያም እንዲህ ልንለው እንችላለን፦ ‘ሃይማኖተኛ ሰው እንደሆንክ አስተውያለሁ። እንደ አንተ ካሉ ሰዎች ጋር መወያየት ደስ ይለኛል።’ የሰውየውን ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንደምናከብር በመጥቀስ ከግለሰቡ ጋር የሚያግባባንን መሠረት መጣል እንችላለን። በሃይማኖታዊ እምነታቸው የተነሳ በሰዎች ላይ መፍረድ እንደሌለብን አስታውስ። ከእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ብዙዎች በአንድ ወቅት የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን አጥብቀው ይከተሉ ነበር።

      አንድ ወጣት በሳይንስ ክፍለ ጊዜ በአስተማሪውና በክፍሉ ልጆች ፊት ሲናገር።

      ከሌሎች ጋር ሊያግባባህ የሚችል ርዕሰ ጉዳይ ምረጥ

      አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” (የሐዋርያት ሥራ 17:24-28)

      12. ጳውሎስ መልእክቱን ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ያቀረበው እንዴት ነው?

      12 ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር የሚያግባባውን ርዕሰ ጉዳይ በመጠቀም ውይይቱን ጀምሯል፤ ሆኖም ይህንኑ መሠረት ሳይለቅ ውይይቱን መቀጠል ይችል ይሆን? አድማጮቹ የተማሩት የግሪክን ፍልስፍና እንደሆነ ያውቃል፤ ቅዱሳን መጻሕፍትን አያውቁም፤ በመሆኑም መልእክቱን ከእነሱ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ለማቅረብ የተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅሟል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ ሳይጠቅስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን አስተምሯቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ራሱን ከእነሱ የተለየ አድርጎ እንደማይመለከት ሊጠቁማቸው ሞክሯል፤ አልፎ አልፎ “እኛ” እያለ ራሱንም አካትቶ መናገሩ ይህን ያሳያል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የሚያስተምራቸው አንዳንድ ትምህርቶች በራሳቸው ጽሑፎች ላይም እንደሚገኙ ለማሳየት ከግሪክ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ጠቅሷል። ጳውሎስ የሰጠውን ግሩም ንግግር እስቲ እንመርምር። የአቴንስ ሰዎች የማያውቁትን አምላክ በተመለከተ የትኞቹን አስፈላጊ እውነቶች አስተምሯል?

      13. ጳውሎስ ጽንፈ ዓለም የተገኘበትን መንገድ በተመለከተ ምን ብሏል? ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክትስ ምንድን ነው?

      13 አምላክ ጽንፈ ዓለምን ፈጥሯል። ጳውሎስ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ እሱ የሰማይና የምድር ጌታ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም” ሲል ተናግሯል።d (ሥራ 17:24) ጽንፈ ዓለም የተገኘው እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም። ሁሉንም ነገር የፈጠረው እውነተኛው አምላክ ነው። (መዝ. 146:6) አቴናም ሆነች ሌሎች ጣዖታት ክብራቸው የተመካው ሰዎች በሚሠሩላቸው ቤተ መቅደሶችና መሠዊያዎች ላይ ነው፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ሉዓላዊ ጌታ ግን በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሊኖር አይችልም። (1 ነገ. 8:27) ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ግልጽ ነው፦ እውነተኛው አምላክ፣ ሰዎች በሠሯቸው ቤተ መቅደሶች ውስጥ ከሚገኙት ሰው ሠራሽ ጣዖታት እጅግ የላቀ ነው።—ኢሳ. 40:18-26

      14. ጳውሎስ፣ አምላክ የሰዎች ጥገኛ እንዳልሆነ የገለጸው እንዴት ነው?

      14 አምላክ የሰዎች ጥገኛ አይደለም። ጣዖት አምላኪዎች፣ ለአምልኮ የሚጠቀሙባቸውን ምስሎች የተንቆጠቆጡ ልብሶችን ያለብሷቸው፣ በርካታ ውድ ስጦታዎችን ይሰጧቸው ወይም ምግብና መጠጥ ያቀርቡላቸው ነበር! አማልክቱ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው የሚያስቡ ይመስላል። ጳውሎስን የሚያዳምጡት አንዳንድ የግሪክ ፈላስፎች ግን አምላክ ከሰዎች የሚፈልገው ነገር አለ ብለው የሚያምኑ አይመስልም። ይህ ከሆነ ደግሞ “[አምላክ] የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም” በሚለው የጳውሎስ ሐሳብ እንደሚስማሙ ግልጽ ነው። አዎ፣ ፈጣሪ የሚያስፈልገውና ሰዎች ሊሰጡት የሚችሉት ቁሳዊ ነገር የለም! እንዲያውም ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያገኙት ከእሱ ነው፤ “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር” ለምሳሌ ፀሐይን፣ ዝናብንና ለም አፈርን ለሰው ልጆች የሚሰጠው እሱ ነው። (ሥራ 17:25፤ ዘፍ. 2:7) ስለዚህ ሰጪ የሆነው አምላክ ተቀባይ የሆኑት የሰው ልጆች ጥገኛ አይደለም።

      15. ጳውሎስ፣ ግሪካውያን ካልሆኑ ሰዎች እንደሚበልጡ የሚያስቡትን የአቴንስ ሰዎች አመለካከት ያረመው እንዴት ነው? እኛስ እሱ ከተወው ምሳሌ ምን ትልቅ ቁም ነገር እንማራለን?

      15 ሰውን የፈጠረው አምላክ ነው። የአቴንስ ሰዎች፣ ግሪካውያን ካልሆኑ ሰዎች እንደሚበልጡ ያስቡ ነበር። ሆኖም በብሔርም ሆነ በዘር መኩራት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ይቃረናል። (ዘዳ. 10:17) ጳውሎስ ጥንቃቄ የሚያሻውን ይህን ጉዳይ ያብራራው በዘዴና በጥበብ ነው። “[አምላክ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” አላቸው፤ ይህ ሐሳብ አድማጮቹ ቆም ብለው እንዲያስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም። (ሥራ 17:26) እዚህ ላይ ጳውሎስ የሰው ዘር አባት ስለሆነው ስለ አዳም የሚገልጸውን የዘፍጥረት ዘገባ መጥቀሱ ነበር። (ዘፍ. 1:26-28) ሁሉም የሰው ዘር ከአንድ አባት የተገኘ በመሆኑ የትኛውም ዘር ወይም ብሔር ከሌላው አይበልጥም። ከጳውሎስ አድማጮች መካከል ይህን ነጥብ መረዳት የሚሳነው ሊኖር አይችልም። እኛም እሱ ከተወው ምሳሌ አንድ ትልቅ ቁም ነገር እንማራለን። በምሥክርነቱ ሥራችን ዘዴኛና ምክንያታዊ መሆን ቢኖርብንም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲቀበሉ ስንል አለዝበን ማቅረብ አይኖርብንም።

      16. ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

      16 የአምላክ ዓላማ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ነው። በጳውሎስ አድማጮች መካከል የነበሩት ፈላስፎች፣ ሰው ወደ ሕልውና የመጣበትን ዓላማ በተመለከተ ለብዙ ዓመታት ሲከራከሩ ኖረዋል፤ ያም ሆኖ አጥጋቢ ማብራሪያ ሊሰጡ አልቻሉም። ጳውሎስ ግን ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ቁልጭ አድርጎ አስቀመጠ፤ ዓላማው “ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት” መሆኑን ተናገረ፤ አክሎም “እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም” አላቸው። (ሥራ 17:27) የአቴንስ ሰዎች ያላወቁት አምላክ፣ ጨርሶ ሊታወቅ የማይችል አምላክ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እሱን ለማግኘትና ስለ እሱ ለመማር ልባዊ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች የራቀ አይደለም። (መዝ. 145:18) ጳውሎስ “ከእያንዳንዳችን” ብሎ እንደተናገረ ልብ በል፤ ይህን ሲል አምላክን ‘መፈለግና አጥብቀው መሻት’ ከሚጠበቅባቸው ሰዎች መካከል ራሱንም ማካተቱ ነው።

      17, 18. ሰዎች ወደ አምላክ ለመቅረብ ሊነሳሱ የሚገባው ለምንድን ነው? ጳውሎስ የአድማጮቹን ትኩረት ለመሳብ ካደረገው ጥረት ምን መማር እንችላለን?

      17 ሰዎች ወደ አምላክ የመቅረብ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ጳውሎስ “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው” ሲል ተናግሯል። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ይህን ሲል፣ በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ኤፒሜንዲዝ የተናገረውን ሐሳብ መጥቀሱ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይህ ቀርጤሳዊ ገጣሚ “በአቴናውያን ሃይማኖታዊ ወግና ልማድ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው” ሰው ነበር። ጳውሎስ ሰዎች ወደ አምላክ ለመቅረብ እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸውን ሌላም ምክንያት ገልጿል፤ “ከእናንተ ባለቅኔዎች አንዳንዶቹ ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው [ተናግረዋል]” ብሏል። (ሥራ 17:28) ሰዎች ከአምላክ ጋር ቤተሰባዊ ዝምድና እንዳላቸው ሊሰማቸው ይገባል፤ ምክንያቱም የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነውን የመጀመሪያውን ሰው የፈጠረው አምላክ ነው። ጳውሎስ የአድማጮቹን ትኩረት ለመሳብ ሲል ትልቅ ቦታ ከሚሰጧቸው የግሪክ ጽሑፎች ላይ በቀጥታ ጠቅሷል።e እኛም የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ከዓለም የታሪክ መጻሕፍት፣ ከኢንሳይክሎፒዲያዎች ወይም ተቀባይነት ካላቸው ሌሎች የማመሣከሪያ ጽሑፎች አልፎ አልፎ መጥቀስ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክር ላልሆነ ሰው የሐሰት ሃይማኖት ልማዶችን ወይም በዓላትን አመጣጥ ለማስረዳት ተቀባይነት ካላቸው ጽሑፎች ላይ መጥቀስ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

      18 ጳውሎስ እስከዚህ ነጥብ ድረስ ንግግሩን ከአድማጮቹ ሁኔታ ጋር እያስማማ በማቅረብ ስለ አምላክ መሠረታዊ እውነቶችን ተናግሯል። ሐዋርያው ይህን ጠቃሚ ሐሳብ ለአድማጮቹ የተናገረው ምን እንዲያደርጉ ፈልጎ ነው? እዚያው ንግግሩን በመቀጠል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነገራቸው።

      ‘በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ መግባት አለባቸው’ (የሐዋርያት ሥራ 17:29-31)

      19, 20. (ሀ) ጳውሎስ ሰው ሠራሽ ጣዖታትን ማምለክ ምን ያህል ሞኝነት እንደሆነ በዘዴ ያጋለጠው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች ምን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸው ነበር?

      19 አሁን ጳውሎስ አድማጮቹ እርምጃ እንዲወስዱ ለማበረታታት ተዘጋጅቷል። ከግሪካውያን መጣጥፎች ላይ የጠቀሰውን ሐሳብ መልሶ በማንሳት እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ እኛ የአምላክ ልጆች ከሆንን አምላክ በሰው ጥበብና ንድፍ ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም።” (ሥራ 17:29) በእርግጥም ሰዎች የአምላክ የእጅ ሥራ ከሆኑ አምላክ እንዴት የሰው እጅ ሥራ የሆኑትን ጣዖታት ሊመስል ይችላል? ጳውሎስ በዘዴ ያቀረበው አሳማኝ ማስረጃ፣ ሰው ሠራሽ ጣዖታትን ማምለክ ሞኝነት መሆኑን አጋልጧል። (መዝ. 115:4-8፤ ኢሳ. 44:9-20) ጳውሎስ “እኛ” በማለት ራሱን ጨምሮ መናገሩ ምክሩን ትንሽ ለማለዘብ ረድቶታል።

      20 ሐዋርያው እርምጃ መውሰድ የግድ እንደሆነ ግልጽ አደረገ፤ እንዲህ አለ፦ “አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ [ጣዖታትን በሚያመልኩ ሰዎች ደስ ይሰኛል ብለው በማሰብ የኖሩበትን ዘመን] ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ እያሳሰበ ነው።” (ሥራ 17:30) ከጳውሎስ አድማጮች አንዳንዶቹ፣ ይህን የንስሐ ጥሪ ሲሰሙ ደንግጠው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ያቀረበው አሳማኝ ንግግር፣ ሕይወት ያገኙት ከአምላክ በመሆኑ የእሱ ባለዕዳዎች እንደሆኑ አስገንዝቧቸዋል፤ በመሆኑም በእሱ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። አምላክን መፈለግ፣ ስለ እሱ እውነቱን መማርና ሕይወታቸውን ከዚህ እውነት ጋር ሙሉ በሙሉ ማስማማት ያስፈልጋቸው ነበር። የአቴንስ ሰዎች ይህን ለማድረግ፣ ጣዖት አምልኮ ኃጢአት መሆኑን መገንዘብና ከዚህ ልማድ መራቅ ነበረባቸው።

      21, 22. ጳውሎስ ንግግሩን የደመደመው የትኛውን ጠንከር ያለ መልእክት በመናገር ነው? ጳውሎስ የተናገረው ነገር ዛሬ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

      21 ጳውሎስ ንግግሩን የደመደመው የሚከተለውን ጠንከር ያለ መልእክት በመናገር ነበር፦ “[አምላክ] በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል፤ እሱንም ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።” (ሥራ 17:31) አዎ፣ የፍርድ ቀን ይመጣል! ይህን ማወቅ እውነተኛውን አምላክ ለመሻትና ለማግኘት የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት ነው! ጳውሎስ፣ የተሾመውን ፈራጅ በስም አልጠቀሰም። ከዚህ ይልቅ ይህን ፈራጅ በተመለከተ አስገራሚ የሆነ ነገር ጠቅሷል፤ ሰው ሆኖ እንደኖረና እንደሞተ እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው ገለጸ።

      22 ይህ ስሜት ቀስቃሽ መደምደሚያ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። አምላክ የሾመው ፈራጅ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናውቃለን። (ዮሐ. 5:22) በተጨማሪም የፍርድ ቀን የአንድ ሺህ ዓመት ርዝማኔ እንዳለውና በጣም እየቀረበ እንዳለ እናውቃለን። (ራእይ 20:4, 6) ይህን የፍርድ ቀን የምንፈራበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም ታማኞች እንደሆኑ ለተፈረደላቸው ሰዎች እጅግ አስደናቂ በረከት እንደሚያመጣላቸው እናውቃለን። ከፊታችን የምንጠብቀው አስደሳች ተስፋ እንደሚፈጸም ዋስትና የሚሆነን ወደር የሌለው ታላቅ ተአምር ተፈጽሟል፤ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው።

      “አንዳንድ ሰዎች . . . አማኞች ሆኑ” (የሐዋርያት ሥራ 17:32-34)

      23. የጳውሎስ አድማጮች ምን የተለያየ ምላሽ ሰጥተዋል?

      23 የጳውሎስ አድማጮች የሰጡት ምላሽ የተለያየ ነው። “ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር።” ሌሎቹ ደግሞ አክብሮት ቢኖራቸውም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አልነበሩም፤ “ስለዚሁ ጉዳይ በድጋሚ መስማት እንፈልጋለን” አሉት። (ሥራ 17:32) ይሁንና ጥቂቶች መልእክቱን ተቀበሉት፤ ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ሰዎች ግን ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ። ከእነሱም መካከል የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነው ዲዮናስዮስና ደማሪስ የተባለች ሴት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል።” (ሥራ 17:34) እኛም በአገልግሎታችን ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥመናል። አንዳንዶች ሊያሾፉብን ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ለእኛ አክብሮት ቢኖራቸውም ለመልእክቱ ግድየለሽ ይሆናሉ። ሆኖም አንዳንዶች የመንግሥቱን መልእክት ተቀብለው አማኞች ሲሆኑ እጅግ እንደሰታለን።

      24. ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ቆሞ ከሰጠው ንግግር ምን ትምህርት እናገኛለን?

      24 ጳውሎስ በሰጠው ንግግር ላይ ስናሰላስል፣ ምክንያታዊና አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንዲሁም እንደ አድማጮቻችን ሁኔታ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ብዙ እንማራለን። በተጨማሪም በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች የታወሩ ሰዎችን በትዕግሥትና በዘዴ መያዝ አስፈላጊ እንደሆነ እንማራለን። ሌላም የምናገኘው ትልቅ ቁም ነገር አለ፤ ይኸውም አድማጮቻችንን ለማስደሰት ብለን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አለዝበን ማቅረብ እንደሌለብን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ በመከተል በመስክ አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ አስተማሪዎች መሆን እንችላለን። የበላይ ተመልካቾች ደግሞ ጉባኤ ውስጥ የተሻለ ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች መሆን ይችላሉ። በውጤቱም “ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና . . . እንዲያገኙት” ለመርዳት የተሻለ ብቃት ይኖረናል።—ሥራ 17:27

      a “አቴንስ—የጥንቱ ዓለም የባሕል ማዕከል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      b “ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦይኮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      c አርዮስፋጎስ ከአክሮፖሊስ በስተ ሰሜን ምዕራብ የሚገኝ ቦታ ነው፤ የአቴንስ አስተዳዳሪዎች ሸንጎ የሚሰበሰበው እዚያ ነበር። “አርዮስፋጎስ” የሚለው ቃል ሸንጎውን አሊያም ራሱን ኮረብታውን ሊያመለክት ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ የተወሰደው ወደዚህ ኮረብታ ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ ስፍራ ነው? ወይስ ይህ አገላለጽ በሌላ ቦታ ምናልባትም በገበያ ስፍራው በተሰየመ ሸንጎ ፊት እንደቀረበ የሚጠቁም ነው? ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምሁራን የተለያየ አመለካከት አላቸው።

      d “ዓለም” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ኮስሞስ ሲሆን ግሪካውያን ይህን ቃል ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ለማመልከት ይጠቀሙበት ነበር። ጳውሎስም ከግሪካውያን አድማጮቹ ጋር ሊያግባባው በሚችል መንገድ ለመናገር ጥረት እያደረገ ስለነበር ይህን ቃል የተጠቀመበት ከዚህ አገባቡ አንጻር ሊሆን ይችላል።

      e ጳውሎስ የጠቀሰው፣ የኢስጦይክ ገጣሚ ኧራተስ ካዘጋጀው ፊኖሚና የተባለ የሥነ ፈለክ ግጥም ላይ ነው። በሌሎች ግሪካውያን መጣጥፎች ውስጥም ተመሳሳይ አገላለጾች ይገኛሉ፤ የኢስጦይክ ደራሲ የሆነው ክሊያንቲዝ ያዘጋጀውን ሂም ቱ ዙስ የተባለውን ጽሑፍ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

  • “መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • ምዕራፍ 19

      “መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል”

      ጳውሎስ መተዳደሪያ ለማግኘት ቢሠራም ቅድሚያ የሚሰጠው ለአገልግሎቱ ነው

      በሐዋርያት ሥራ 18:1-22 ላይ የተመሠረተ

      1-3. ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የመጣው ለምንድን ነው? ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችስ ገጥመውታል?

      ጊዜው በ50 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አሁን ያለው ቆሮንቶስ ውስጥ ነው፤ ይህች ከተማ በርካታ ግሪካውያን፣ ሮማውያንና አይሁዳውያን የሚኖሩባት የበለጸገች የንግድ ማዕከል ነች።a ጳውሎስ ወደዚህች ከተማ የመጣው ለመገበያየት ወይም ሥራ ለመፈለግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን ሥራ ለማከናወን ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት ለመመሥከር ነው። ያም ሆኖ ጳውሎስ የሚያርፍበት ቦታ ያስፈልገዋል፤ ደግሞም በቁሳዊ ነገሮች ረገድ በሌሎች ላይ ሸክም ላለመሆን ቆርጧል። አገልግሎቱን ቁሳዊ ጥቅም ማግኛ አድርጎ እንደሚጠቀምበት የሚያስመስል ነገር ማድረግ አልፈለገም። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን?

      2 ጳውሎስ ድንኳን የመስፋት ሙያ ነበረው። ድንኳን መስፋት አድካሚ ሥራ ቢሆንም መተዳደሪያ ለማግኘት ሲል ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነው። ታዲያ ሰዎች በሚተራመሱባት በዚህች ከተማ ውስጥ ሥራ ያገኝ ይሆን? የሚያርፍበት አመቺ ቦታስ? እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ዋነኛ ሥራውን ይኸውም አገልግሎቱን አልዘነጋም።

      3 ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለተወሰነ ጊዜ መሰንበቱ አልቀረም፤ በዚያ ያከናወነው አገልግሎትም ብዙ ፍሬ አፍርቷል። እንግዲያው በቆሮንቶስ ያከናወናቸውን ነገሮች በመመርመር በክልላችን ውስጥ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ ስለ መመሥከር የምናገኘውን ትምህርት እንመልከት።

      ቆሮንቶስ—የሁለት ባሕሮች እመቤት

      የጥንቷ ቆሮንቶስ የምትገኘው በዋናው የግሪክ ምድርና በስተ ደቡብ በሚገኘው የፔሎፖኒስ ባሕረ ገብ መሬት መካከል ባለ እንደ ድልድይ ያለ ሰርጥ ላይ ነው። ይህ ሰርጥ ጠባብ በሆነው ቦታ ላይ ስፋቱ ስድስት ኪሎ ሜትር እንኳ አይሞላም፤ በመሆኑም ቆሮንቶስ ሁለት ወደቦች ነበሯት። በስተ ምዕራብ ያለው የሌካኦን ወደብ ወደ ጣሊያን፣ ሲሲሊና ስፔን ለሚሄዱና ከዚያ ለሚመጡ መርከቦች የባሕር በር ነበር። በስተ ምሥራቅ በሰሮኒክ ባሕረ ሰላጤ ላይ ያለው የክንክራኦስ ወደብ ደግሞ ከኤጅያን አካባቢ፣ ከትንሿ እስያ፣ ከሶርያና ከግብፅ ለሚመጡና ወደዚያ ለሚሄዱ መርከቦች የባሕር በር ነበር።

      በፔሎፖኒስ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚገኘው አካባቢ ነፋስ የሚበዛበትና ለመርከብ ጉዞ አደገኛ ነበር፤ በመሆኑም መርከበኞች ብዙውን ጊዜ የሚመርጡት ወደ ቆሮንቶስ መሄድ ነው። ከቆሮንቶስ ሁለት ወደቦች በአንዱ ላይ መልሕቃቸውን ይጥሉና ጭነታቸውን ወደ ሌላኛው ወደብ በየብስ ያጓጉዛሉ፤ ከዚያኛው ወደብ ላይ ደግሞ በሌላ መርከብ እንዲጫን ያደርጋሉ። መርከቦቹ ቀለል ያሉ ከሆኑ ደግሞ ከአንዱ ወደብ ወደ ሌላው ወደብ እየገፉ በየብስ ያሻግሯቸዋል፤ ለዚህ ዓላማ ተብሎ ጎድጎድ ተደርጎ የተሠራ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተዘርግቶ ነበር። ከተማዋ እንዲህ ያለ ልዩ አቀማመጥ ስለነበራት ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚካሄደውን የባሕር ላይ ንግድ እንዲሁም ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚደረገውን የየብስ ላይ ንግድ መቆጣጠር ችላለች። ይህ የደራ ንግድ የቆሮንቶስ ከተማን አበልጽጓታል፤ በሌላ በኩል ግን እንደ አብዛኞቹ ወደቦች ሁሉ ለብዙ ነውረኛ ነገሮች አጋልጧታል።

      በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ቆሮንቶስ፣ የሮም ግዛት የሆነችው የአካይያ ዋና ከተማና የአስተዳደር ማዕከል ነበረች። በከተማዋ ውስጥ የተለያዩ ሃይማኖቶች ነበሩ፤ ለንጉሠ ነገሥት አምልኮ የተሠራው ቤተ መቅደስ፣ ለግሪክና ለግብፅ በርካታ አማልክት የተሠሩት ቤተ መቅደሶችና የአምልኮ ስፍራዎች እንዲሁም የአይሁዳውያን ምኩራብ ለዚህ ማስረጃ ይሆናሉ።—ሥራ 18:4

      በቆሮንቶስ አቅራቢያ ባለችው በኢስሚያ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአትሌቲክስ ውድድር፣ ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውድድር ነበር። በ51 ዓ.ም. ይህ ውድድር በተካሄደበት ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ቆሮንቶስ የነበረ ይመስላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ብሏል፦ “ጳውሎስ ከአትሌቲክስ ጋር የተያያዘ ምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ለቆሮንቶስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ነው፤ ይህ በአጋጣሚ ሊሆን አይችልም።”—1 ቆሮ. 9:24-27

      “ሙያቸው . . . ድንኳን መሥራት ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 18:1-4)

      4, 5. (ሀ) ጳውሎስ ቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ያረፈው የት ነው? መተዳደሪያ ለማግኘት ምን ይሠራ ነበር? (ለ) ጳውሎስ ድንኳን የመሥራት ሙያ የተማረው እንዴት ሊሆን ይችላል?

      4 ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ከሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቂላ ከተባለ አይሁዳዊና ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ተገናኘ፤ እነዚህ ሰዎች በእንግዳ ተቀባይነታቸው የሚታወቁ ነበሩ። ባልና ሚስቱ ወደ ቆሮንቶስ የሄዱት ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ “አይሁዳውያን ሁሉ ከሮም እንዲወጡ” ስላዘዘ ነው። (ሥራ 18:1, 2) አቂላና ጵርስቅላ፣ ጳውሎስ አብሯቸው እንዲኖር ብቻ ሳይሆን ከእነሱ ጋር እንዲሠራም አድርገዋል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ሙያቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ እነሱ ቤት ተቀምጦ አብሯቸው ይሠራ ነበር፤ ሙያቸውም ድንኳን መሥራት ነበር።” (ሥራ 18:3) ጳውሎስ በቆሮንቶስ ባገለገለበት ወቅት ያረፈው፣ ደግና እንግዳ ተቀባይ በሆኑት በእነዚህ ባልና ሚስት ቤት ነው። ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን አንዳንዶቹን ደብዳቤዎች የጻፈው ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ይኖር በነበረበት ጊዜ ሊሆን ይችላል።b

      5 “በገማልያል እግር ሥር” ተቀምጦ የተማረው ጳውሎስ የድንኳን ሥራ ሙያም ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? (ሥራ 22:3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ለልጆቻቸው የእጅ ሙያ ማስተማር የሚያሳፍራቸው አይመስልም፤ በእርግጥ ልጆቹ ተጨማሪ ትምህርት እንዲከታተሉም ያደርጉ ነበር። ጳውሎስ በኪልቅያ የምትገኘው የጠርሴስ ሰው ነው፤ ለድንኳን ሥራ የሚያገለግለው ሰለሲየም የተባለው ጨርቅ በብዛት የሚመረተው እዚህ አካባቢ ነው፤ በመሆኑም የድንኳን ሥራን በልጅነቱ ተምሮ ሊሆን ይችላል። ድንኳን መሥራት ምን ነገሮችን ይጨምራል? የድንኳኑን ጨርቅ መሸመንን ወይም ሸካራና ጠንካራ የሆነውን ይህን ጨርቅ መቁረጥና መስፋትን ሊጨምር ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሥራው በጣም አድካሚ ነው።

      6, 7. (ሀ) ጳውሎስ ድንኳን የመሥራት ሙያውን እንዴት ይመለከተው ነበር? አቂላና ጵርስቅላም ተመሳሳይ አመለካከት እንደነበራቸው የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች የጳውሎስን፣ የአቂላንና የጵርስቅላን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

      6 ጳውሎስ ይህን ሙያውን እንደ ዋነኛ ሥራው አድርጎ አልተመለከተውም። ይህን ሥራ የሚሠራው፣ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማሟላትና ምሥራቹን “ያለዋጋ” ለመስበክ ነው። (2 ቆሮ. 11:7) አቂላና ጵርስቅላስ ለዚህ ሙያቸው ምን አመለካከት ነበራቸው? ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ለሰብዓዊ ሥራቸው የጳውሎስ ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው ግልጽ ነው። እንዲያውም ጳውሎስ በ52 ዓ.ም. ቆሮንቶስን ለቅቆ ወደ ኤፌሶን ሲሄድ አቂላና ጵርስቅላ ንግዳቸውን ትተው ተከትለውታል፤ ኤፌሶን ከሄዱ በኋላም ቤታቸው ለጉባኤው መሰብሰቢያ ሆኖ አገልግሏል። (1 ቆሮ. 16:19) ከጊዜ በኋላ ወደ ሮም የተመለሱ ሲሆን ከዚያም እንደገና ወደ ኤፌሶን ሄደዋል። እነዚህ ቀናተኛ ባልና ሚስት መንግሥቱን ያስቀደሙ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ሌሎችን አገልግለዋል፤ በዚህም ምክንያት “በአሕዛብ መካከል የሚገኙ ጉባኤዎች” ሁሉ አመስግነዋቸዋል።—ሮም 16:3-5፤ 2 ጢሞ. 4:19

      7 በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖችም የጳውሎስን፣ የአቂላንና የጵርስቅላን ምሳሌ ይከተላሉ። እነዚህ ቀናተኛ አገልጋዮች ሌሎችን “ብዙ ወጪ በማስወጣት ሸክም [ላለመሆን]” ሲሉ ተግተው ይሠራሉ። (1 ተሰ. 2:9) በርካታ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ሲሉ በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ወይም በዓመት ለተወሰኑ ወራት ይሠራሉ፤ ሆኖም ቅድሚያውን የሚሰጡት ለክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው በመሆኑ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። እንደ አቂላና ጵርስቅላ እንግዳ ተቀባይ የሆኑ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችም አሉ፤ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን ቤታቸው ተቀብለው ያስተናግዳሉ። በዚህ መንገድ “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” ያዳበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረግ ምን ያህል እንደሚያበረታታና እንደሚያንጽ ያውቃሉ።—ሮም 12:13

      በመንፈስ መሪነት የተጻፉ የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች

      ሐዋርያው ጳውሎስ ከ50-52 ዓ.ም. ገደማ በቆሮንቶስ በቆየበት የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ሁለት ደብዳቤዎችን ጽፏል፤ እነዚህ ደብዳቤዎች ከጊዜ በኋላ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑት አንደኛና ሁለተኛ ተሰሎንቄ ናቸው። ለገላትያ ሰዎችም ደብዳቤ የጻፈው በዚያው ጊዜ ወይም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ነው።

      አንደኛ ተሰሎንቄ ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች መካከል የመጀመሪያው ነው። ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ የሄደው ሁለተኛ የስብከት ጉዞውን ባደረገበት ወቅት በ50 ዓ.ም. ገደማ ነው። በዚያ የተቋቋመው ጉባኤ ወዲያው ተቃውሞ ገጠመው፤ ጳውሎስና ሲላስ ከተማዋን ለቀው ለመሄድ የተገደዱት በዚሁ ምክንያት ነው። (ሥራ 17:1-10, 13) ጳውሎስ ገና ጨቅላ የነበረው ጉባኤ ሁኔታ ስላሳሰበው ሁለት ጊዜ ወደዚያ ለመመለስ ሞክሮ ነበር፤ ሆኖም ‘ሰይጣን መንገድ ዘግቶበታል።’ በመሆኑም ጳውሎስ ወንድሞችን እንዲያጽናና እና እንዲያበረታታ ጢሞቴዎስን ላከው። በ50 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም ጢሞቴዎስ ወደ ቆሮንቶስ ተመልሶ ከጳውሎስ ጋር ተገናኘ፤ በተሰሎንቄ ስላለው ጉባኤም መልካም ዜና ነገረው። ከዚያም ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ ጻፈ።—1 ተሰ. 2:17 እስከ 3:7

      ሁለተኛ ተሰሎንቄ የተጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤ ከተጻፈ ብዙም ሳይቆይ ምናልባትም በ51 ዓ.ም. ሳይሆን አይቀርም። በሁለቱም ደብዳቤዎች ላይ ጢሞቴዎስና ስልዋኖስ (በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ሲላስ ተብሎ ተጠርቷል) ከጳውሎስ ጋር ሰላምታ ልከዋል፤ ይሁንና ጳውሎስ ቆሮንቶስን ለቆ ከሄደ በኋላ ሦስቱ አብረው ስለመቀጠላቸው የሚገልጽ ምንም ዘገባ አናገኝም። (ሥራ 18:5, 18፤ 1 ተሰ. 1:1፤ 2 ተሰ. 1:1) ጳውሎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ የጻፈው ለምንድን ነው? የመጀመሪያውን ደብዳቤ ያደረሰለት ሰው ስለ ጉባኤው ተጨማሪ ሪፖርት ይዞለት የመጣ ይመስላል። ጳውሎስ ስለ እነሱ የሰማው ነገር ላሳዩት ፍቅርና ጽናት እንዲያመሰግናቸው አነሳስቶታል፤ ከዚህም ሌላ የጌታ መገኘት እንደቀረበ የሚናገሩ አንዳንድ የተሰሎንቄ ወንድሞች እንዳሉ ስለሰማ ይህን አመለካከታቸውን ማረም አስፈልጎታል።—2 ተሰ. 1:3-12፤ 2:1, 2

      ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ እንደሚጠቁመው ደብዳቤውን ከመጻፉ በፊት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ጎብኝቷቸዋል። ከ47-48 ዓ.ም. ጳውሎስና በርናባስ ወደ ጵስድያዋ አንጾኪያ፣ ኢቆንዮን፣ ልስጥራና ደርቤ ሄደው ነበር፤ እነዚህ ከተሞች የሚገኙት የሮም ግዛት በነበረችው በገላትያ አውራጃ ነው። በ49 ዓ.ም. ጳውሎስ ከሲላስ ጋር ወደዚህ አካባቢ ተመልሶ መጣ። (ሥራ 13:1 እስከ 14:23፤ 16:1-6) ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው፣ እግሩን ጠብቀው ወደዚያ በመጡት ሐሰተኛ ወንድሞች የተነሳ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ‘ክርስቲያኖች መገረዝና የሙሴን ሕግ መጠበቅ አለባቸው’ ብለው ያስተምሩ ነበር። ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ደብዳቤ የጻፈው ስለዚህ የሐሰት ትምህርት እንደሰማ መሆን አለበት። ደብዳቤውን የጻፈው ቆሮንቶስ ሳለ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ እየተመለሰ ሳለ በኤፌሶን አጭር ቆይታ ባደረገበት ጊዜ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ እዚያው አንጾኪያ ከተመለሰ በኋላ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 18:18-23

      “በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር” (የሐዋርያት ሥራ 18:5-8)

      8, 9. ጳውሎስ ለአይሁዳውያን በትጋት መስበኩ የመረረ ተቃውሞ ሲያስከትልበት ምን አደረገ? ከዚያ በኋላስ ለመስበክ ወዴት ሄደ?

      8 ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ የተለያዩ ስጦታዎችን ይዘው መጡ፤ ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ያደረገው ነገር በግልጽ እንደሚያሳየው ሰብዓዊ ሥራ ይሠራ የነበረው አገልግሎቱን ሲያከናውን ኑሮውን ለመደጎም እንዲያግዘው ብቻ ነው። (2 ቆሮ. 11:9) ዘገባው እንደሚገልጸው ጳውሎስ ወዲያውኑ “ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ [“በማስተማር ጊዜውን ሁሉ ያሳልፍ ነበር፣” የ1980 ትርጉም]።” (ሥራ 18:5) ይሁን እንጂ ይህ የስብከት እንቅስቃሴ ከአይሁዳውያን ዘንድ የመረረ ተቃውሞ ገጠመው። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ሕይወት አድን መልእክት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ከዚያ በኋላ በኃላፊነት እንደማይጠየቅ ለማሳየት ልብሱን አራገፈ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን። እኔ ንጹሕ ነኝ። ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ።”—ሥራ 18:6፤ ሕዝ. 3:18, 19

      9 ታዲያ ጳውሎስ ከዚህ በኋላ የት ይሰብክ ይሆን? ቲቶስ ኢዮስጦስ የተባለ አንድ ሰው ቤቱን ከፈተለት፤ ይህ ሰው ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሳይሆን አይቀርም፤ በምኩራቡ አጠገብ የሚገኘውን ቤቱን እንዲጠቀምበት ለጳውሎስ ፈቀደለት። ስለዚህ ጳውሎስ ምኩራቡን ለቅቆ ወደ ኢዮስጦስ ቤት ገባ። (ሥራ 18:7) ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሳለ የሚኖረው በአቂላና በጵርስቅላ ቤት ነው፤ የስብከት ሥራውን የሚያከናውነው ግን በኢዮስጦስ ቤት ነበር።

      10. ጳውሎስ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ለመስበክ ወስኖ እንዳልነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

      10 ጳውሎስ “ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” ማለቱ አይሁዳውያንንም ሆነ ወደ ይሁዲነት የተለወጡትን ሰዎች ጨርሶ እንደተዋቸው የሚያሳይ ነው? መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ለሚሆኑት እንኳ ትኩረት አይሰጥም ማለት ነው? ይህ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣ “የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ” የሚል ዘገባ እናነባለን። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በምኩራቡ ይሰበሰቡ ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎች ቀርስጶስ የወሰደው ዓይነት እርምጃ ወስደዋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር” ይላል። (ሥራ 18:8) በመሆኑም በቆሮንቶስ የተቋቋመው አዲስ ጉባኤ በቲቶስ ኢዮስጦስ ቤት መሰብሰብ ጀመረ። ሉቃስ ይህን ዘገባ የጻፈው እንደተለመደው በጊዜ ቅደም ተከተል ከሆነ እነዚህ አይሁዳውያንም ሆኑ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ክርስትናን የተቀበሉት ጳውሎስ ልብሱን ካራገፈ በኋላ ነው። ይህም ስለ ሐዋርያው የሚነግረን ቁም ነገር አለ፤ ጳውሎስ ምሥራቹን ሲሰብክ እንደ ሁኔታው ማስተካከያ የሚያደርግ ሰው ነበር።

      11. ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ላሉ ሰዎች በሚሰብኩበት ጊዜ የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

      11 በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በብዙ አገሮች ውስጥ ረጅም ዘመን አስቆጥረዋል፤ በአባሎቻቸው ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በአንዳንድ አገሮችና ደሴቶች ላይ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖታቸው ማምጣት ችለዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ እንደነበሩት አይሁዳውያን ሁሉ ዛሬም ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች በወግ የተተበተቡ ናቸው። ያም ቢሆን እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ልክ እንደ ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች በቅንዓት እንሰብካለን፤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካላቸው መጠነኛ እውቀት ተነስተን ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንሞክራለን። ቢቃወሙን ወይም የሃይማኖት መሪዎቻቸው ስደት ቢያደርሱብንም ተስፋ አንቆርጥም። እነዚህ ሰዎች “ለአምላክ ቅንዓት [ቢኖራቸውም] ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም”፤ ከእነሱ መካከል ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ የሚፈልጉ ብዙ ቅኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ እነሱን ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል።—ሮም 10:2

      “በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝ” (የሐዋርያት ሥራ 18:9-17)

      12. ጳውሎስ በራእይ ምን ማረጋገጫ ተሰጠው?

      12 ጳውሎስ በቆሮንቶስ አገልግሎቱን መቀጠል ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ ጥያቄ ተፈጥሮበት ይሆን? ከሆነም ጌታ ኢየሱስ ሌሊት በራእይ ሲገለጥለት መልሱን ሊያገኝ ነው፤ እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ ማንም አንተን ሊያጠቃና ሊጎዳህ አይችልም፤ በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና።” (ሥራ 18:9, 10) እንዴት የሚያበረታታ ራእይ ነው! ጳውሎስ ምንም ጉዳት እንደማይደርስበት እንዲሁም ምሥራቹን መስማት የሚገባቸው ብዙ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ እንዳሉ ጌታ ራሱ ማረጋገጫ ሰጠው። ታዲያ ጳውሎስ ለዚህ ራእይ ምን ምላሽ ሰጥቶ ይሆን? ዘገባው “በመካከላቸው የአምላክን ቃል እያስተማረ ለአንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቆየ” ይላል።—ሥራ 18:11

      13. ጳውሎስ ወደ ፍርድ ወንበሩ ሲቃረብ ምን ትዝ ብሎት ሊሆን ይችላል? ሆኖም እሱ ይህ ሁኔታ እንደማይገጥመው እርግጠኛ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

      13 ጳውሎስ በቆሮንቶስ አንድ ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ፣ የጌታ ድጋፍ እንደማይለየው ተጨማሪ ማረጋገጫ አግኝቷል። ዘገባው እንደሚነግረን “አይሁዳውያን ግንባር ፈጥረው በጳውሎስ ላይ ተነሱበት”፤ ከዚያም ቪማ ተብሎ በሚጠራው ‘የፍርድ ወንበር ፊት አቀረቡት።’ (ሥራ 18:12) አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ቪማ በሰማያዊና በነጭ እብነ በረድ የተሠራና በተለያዩ ቅርጾች ያጌጠ ከፍ ያለ መድረክ ነው፤ ቪማ የሚገኘው በቆሮንቶስ የገበያ ስፍራ መሃል አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ከፊት ለፊቱ ያለው ክፍት ቦታ ሰፊ በመሆኑ ብዙ ሕዝብ ሊሰበሰብበት ይችል ነበር። የአርኪኦሎጂ ግኝቶች እንደሚጠቁሙት የፍርድ ወንበሩ የሚገኘው ከምኩራቡ ብዙም ሳይርቅ ይመስላል፤ የኢዮስጦስ ቤት ደግሞ ከምኩራቡ አጠገብ ነበር። ጳውሎስ ወደ ቪማው ሲቃረብ፣ የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት እንደሆነ የሚነገርለት እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ የተገደለበት ሁኔታ ትዝ ብሎት ይሆን? በዚያን ጊዜ ሳኦል ተብሎ ይጠራ የነበረው ጳውሎስ “በእሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።” (ሥራ 8:1) ታዲያ እሱም ተመሳሳይ ነገር ይገጥመው ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም “ማንም . . . ሊጎዳህ አይችልም” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።—ሥራ 18:10

      ጋልዮስ በቁጣ የተሞሉትን የጳውሎስ ከሳሾች፣ በጳውሎስ ጉዳይ ላይ ፍርድ እንደማይሰጥ ተናግሮ ሲያባርራቸው። የሮም ወታደሮች፣ የተናደደውን ሕዝብ ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው።

      “ከዚያም ከፍርድ ወንበሩ ፊት አስወጣቸው።”—የሐዋርያት ሥራ 18:16

      14, 15. (ሀ) አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ ምን ክስ ሰነዘሩ? ጋልዮስ ክሱን ውድቅ ያደረገውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሶስቴንስ ምን ደረሰበት? የደረሰበት ሁኔታስ ምን ውጤት አስገኝቶ ሊሆን ይችላል?

      14 ጳውሎስ በፍርድ ወንበሩ ፊት ሲቀርብ ምን ተከሰተ? የሮማዊው ፈላስፋ የሴኔካ ታላቅ ወንድምና የአካይያ አገረ ገዢ የሆነው ጋልዮስ በፍርድ ወንበሩ ላይ ተሰይሟል። አይሁዳውያኑ “ይህ ሰው ሕጉን በሚጻረር መንገድ ሰዎች አምላክን እንዲያመልኩ እያሳመነ ነው” ሲሉ ጳውሎስን ከሰሱት። (ሥራ 18:13) አይሁዳውያኑ፣ ሃይማኖት በማስቀየር ሕግ እየጣሰ ነው ብለው ጳውሎስን እየወነጀሉት ነው። ይሁንና ጋልዮስ፣ ጳውሎስ ምንም “በደል” እንዳልፈጸመና በየትኛውም “ከባድ ወንጀል” ተጠያቂ እንዳልሆነ አውቆ ነበር። (ሥራ 18:14) ጋልዮስ በአይሁዳውያን ውዝግብ ውስጥ እጁን ማስገባት አልፈለገም። ጳውሎስ አንድ የመከላከያ ቃል እንኳ ከአፉ ሳይወጣ ጋልዮስ ክሱን ውድቅ አደረገው! በዚህ ጊዜ ከሳሾቹ በጣም ተበሳጩ። ከዚያም በሶስቴንስ ላይ ንዴታቸውን ተወጡ፤ ሶስቴንስ የምኩራብ አለቃ የሆነው ቀርስጶስን ተክቶ ሳይሆን አይቀርም። አይሁዳውያኑ “ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ወንበሩ ፊት ይደበድቡት ጀመር።”—ሥራ 18:17

      15 ጋልዮስ ሕዝቡ ሶስቴንስን እንዳይደበድበው ያልተከላከለው ለምንድን ነው? በጳውሎስ ላይ የተነሳው ዓመፅ መሪ ሶስቴንስ እንደሆነ አስቦ ዋጋውን እንዳገኘ ተሰምቶት ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ይህ ገጠመኝ በመጨረሻ ጥሩ ውጤት ሳያስገኝ አይቀርም። ጳውሎስ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ሶስቴንስ ስለተባለ ወንድም ጠቅሷል። (1 ቆሮ. 1:1, 2) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሶስቴንስ በቆሮንቶስ ተደብድቦ የነበረው ይሆን? ከሆነ ሶስቴንስ የደረሰበት መከራ ክርስትናን እንዲቀበል አድርጎት ሊሆን ይችላል።

      16. ጌታ “መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር [ነኝ]” በማለት የተናገረው ሐሳብ በአገልግሎታችን እንድንቀጥል የሚያበረታታን እንዴት ነው?

      16 ጌታ ኢየሱስ ለጳውሎስ “አትፍራ፤ መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር [ነኝ]” የሚል ማረጋገጫ የሰጠው አይሁዳውያን መልእክቱን አንቀበልም ካሉ በኋላ እንደነበር አስታውስ። (ሥራ 18:9, 10) እኛም በተለይ ሰዎች መልእክታችንን አልቀበል ሲሉን ይህን ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ይሖዋ ልብን እንደሚያነብና ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሚስብ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። (1 ሳሙ. 16:7፤ ዮሐ. 6:44) ይህ አገልግሎታችንን በትጋት ማከናወናችንን እንድንቀጥል የሚያበረታታ አይደለም? በየዓመቱ መቶ ሺዎች ይጠመቃሉ፤ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይጠመቃሉ ማለት ነው። “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ላሉ ሁሉ ኢየሱስ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚል ዋስትና ሰጥቷል።—ማቴ. 28:19, 20

      “ይሖዋ ከፈቀደ” (የሐዋርያት ሥራ 18:18-22)

      17, 18. ጳውሎስ በመርከብ ወደ ኤፌሶን ሲጓዝ ስለ ምን ነገር አስቦ ሊሆን ይችላል?

      17 በቆሮንቶስ የሚገኘው ጨቅላ የክርስቲያን ጉባኤ ሰላም እንዲያገኝ ያደረገው ጋልዮስ ከጳውሎስ ከሳሾች ጋር በተያያዘ የወሰደው እርምጃ ይሆን? ይህን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሆኖም ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኙትን ወንድሞቹን ተሰናብቶ ከመሄዱ በፊት “በዚያ ለተወሰኑ ቀናት” ቆይቷል። አሁን ጊዜው 52 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት ነው፤ ጳውሎስ ከቆሮንቶስ በስተ ምሥራቅ 11 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው ከክንክራኦስ ወደብ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ሶርያ ለመሄድ አቀደ። ከክንክራኦስ ከመነሳቱ በፊት ግን “ስእለት ስለነበረበት . . . ፀጉሩን በአጭሩ ተቆረጠ።”c (ሥራ 18:18) ከዚያም ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር የኤጅያንን ባሕር አቋርጦ በትንሿ እስያ ወደምትገኘው ወደ ኤፌሶን ሄደ።

      18 ጳውሎስ ከክንክራኦስ ተነስቶ በመርከብ ሲጓዝ በቆሮንቶስ ስላሳለፈው ጊዜ መለስ ብሎ አስቦ ይሆን? ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ብዙ ጥሩ ትዝታዎችና ልቡን በደስታ የሚሞሉ ነገሮች አሉት። ለአንድ ዓመት ተኩል በዚያ ያከናወነው አገልግሎት ፍሬ አፍርቷል። በቆሮንቶስ የመጀመሪያው ጉባኤ ተቋቁሞ በኢዮስጦስ ቤት መሰብሰብ ጀምሯል። አማኞች ከሆኑት መካከል ኢዮስጦስ፣ ቀርስጶስና ቤተሰቡ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ አዳዲስ አማኞች ለጳውሎስ ውድ ናቸው፤ ምክንያቱም ክርስቲያኖች እንዲሆኑ የረዳቸው እሱ ነው። ከጊዜ በኋላ ደብዳቤ የጻፈላቸው ሲሆን ለእሱ በልቡ ላይ የተጻፈ የምሥክር ወረቀት እንደሆኑ ነግሯቸዋል። እኛም እውነተኛውን አምልኮ እንዲቀበሉ ለረዳናቸው ሰዎች ልዩ የሆነ ፍቅር አለን። እነሱን ስናይ ጥልቅ የእርካታ ስሜት ይሰማናል፤ አዎ፣ ለእኛ ሕያው “የምሥክር ወረቀት” ናቸው!—2 ቆሮ. 3:1-3

      19, 20. ጳውሎስ ኤፌሶን እንደደረሰ ምን አደረገ? መንፈሳዊ ግቦች ላይ ከመድረስ ጋር በተያያዘ ከእሱ ምን እንማራለን?

      19 ጳውሎስ ኤፌሶን እንደደረሰ ወደ ሥራ ገባ። ዘገባው “ወደ ምኩራብ ገብቶ ከአይሁዳውያን ጋር ይወያይ ነበር” ይላል። (ሥራ 18:19) በዚህ ወቅት ጳውሎስ በኤፌሶን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነው። ወንድሞች ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሰነብት ቢጠይቁትም “ፈቃደኛ አልሆነም።” የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ተሰናብቷቸው ሲሄድ “ይሖዋ ከፈቀደ ተመልሼ እመጣለሁ” ብሏቸዋል። (ሥራ 18:20, 21) ጳውሎስ በኤፌሶን ገና ብዙ መሰበክ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው ተመልሶ ለመምጣት አቅዷል፤ ሆኖም ጉዳዩን በይሖዋ እጅ መተው መርጧል። ይህ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ አይደለም? መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ የእኛ የራሳችን ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ምንጊዜም ይሖዋ በሚሰጠን አመራር መታመንና ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።—ያዕ. 4:15

      20 ጳውሎስ አቂላንና ጵርስቅላን በኤፌሶን ተዋቸው፤ መርከብ ተሳፍሮም ወደ ቂሳርያ ወረደ። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም “ወጥቶ” በዚያ ለሚገኘው ጉባኤ ሰላምታ አቀረበ። (ሥራ 18:22 ግርጌ) በመጨረሻም ጳውሎስ ወደ ማረፊያው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ ሄደ። ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው በዚህ መንገድ በተሳካ ሁኔታ ተደመደመ። በመጨረሻው ሚስዮናዊ ጉዞው ደግሞ ምን ይጠብቀው ይሆን?

      የጳውሎስ ስእለት

      የሐዋርያት ሥራ 18:18 ጳውሎስ “ስእለት ስለነበረበት” በክንክራኦስ ‘ፀጉሩን በአጭሩ እንደተቆረጠ’ ይናገራል። ይህ ስእለት ምን ነበር?

      ስእለት፣ አንድ ሰው በፈቃደኝነት ለአምላክ የሚገባው ቃል ነው፤ ግለሰቡ አንድ ተግባር ለማከናወን፣ መባ ለማቅረብ ወይም አንድ ዓይነት ግዴታ ውስጥ ለመግባት ቃል ይገባል። አንዳንዶች ጳውሎስ ፀጉሩን የተቆረጠው የናዝራዊነት ስእለት ለመፈጸም እንደሆነ ይናገራሉ። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚገልጹት አንድ ናዝራዊ ለይሖዋ ልዩ አገልግሎት የሚያቀርብበትን ጊዜ ሲያጠናቅቅ ፀጉሩን መላጨት አለበት፤ ሆኖም ይህን የሚያደርገው “በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ” ላይ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በኢየሩሳሌም ብቻ ነው፤ ጳውሎስ ግን ፀጉሩን የተቆረጠው በክንክራኦስ ስለሆነ ስእለቱ የናዝራዊነት አይመስልም።—ዘኁ. 6:5, 18

      የሐዋርያት ሥራ ዘገባ፣ ጳውሎስ ስእለቱን የተሳለው መቼ እንደሆነ አይገልጽም። ምናልባትም ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት የተሳለው ስእለት ሊሆን ይችላል። ዘገባው ጳውሎስ ይሖዋን የጠየቀው ነገር ስለመኖሩም የሚገልጸው ነገር የለም። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚጠቁመው ጳውሎስ ፀጉሩን በአጭሩ የተቆረጠው “በቆሮንቶስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ አምላክ ላደረገለት ጥበቃ ምስጋናውን ለመግለጽ” ሊሆን ይችላል።

      a “ቆሮንቶስ—የሁለት ባሕሮች እመቤት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      b “በመንፈስ መሪነት የተጻፉ የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      c “የጳውሎስ ስእለት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

  • ተቃውሞ ቢኖርም “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • ምዕራፍ 20

      ተቃውሞ ቢኖርም “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ”

      አጵሎስና ጳውሎስ ምሥራቹ እየተስፋፋ እንዲሄድ አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው?

      በሐዋርያት ሥራ 18:23 እስከ 19:41 ላይ የተመሠረተ

      1, 2. (ሀ) ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ በኤፌሶን ምን አደገኛ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

      በኤፌሶን አውራ ጎዳናዎች ላይ ጫጫታና ሁካታ በዝቷል፤ ሰዎች ወዲያ ወዲህ እየተራወጡ ነው። በቁጣ የተሞላ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነስቷል፤ ከፍተኛ የሕዝብ ዓመፅ ሊቀሰቀስ እንደሆነ ያስታውቃል! ሰዎቹ ከሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ጓደኞች መካከል ሁለቱን ይዘው እየጎተቱ ወሰዷቸው። ሱቆቹ የሚገኙበት ሰፊ ጎዳና ጭር ብሏል፤ በቁጣ የገነፈለው ሕዝብ ንቅል ብሎ በመውጣት ወደ ከተማዋ አምፊቲያትር ግር ብሎ ገባ፤ ግዙፉ አምፊቲያትር 25,000 ተመልካች የማስተናገድ አቅም አለው። አብዛኞቹ ሰዎች ለረብሻ ምክንያት የሆነውን ነገር እንኳ አያውቁም፤ ቤተ መቅደሳቸውንና ተወዳጅ አምላካቸውን አርጤምስን የሚያሰጋ ነገር እንደተፈጠረ ግን ጠርጥረዋል። ስለዚህ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ያለማቋረጥ መጮኹ ጀመሩ።—ሥራ 19:34

      2 ሰይጣን አሁንም የሕዝብ ዓመፅ በመቀስቀስ፣ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እንዳይስፋፋ ለማገድ እየሞከረ ነው። እርግጥ ነው፣ ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት የሚሞክረው ዓመፅ በማስነሳት ብቻ አይደለም። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሰይጣን የተጠቀመባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች እንመረምራለን፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ሥራ ለማዳከምና አንድነታቸውን ለማናጋት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። ደስ የሚለው ግን፣ ቀጥለን እንደምንመለከተው የሰይጣን ዘዴዎች በሙሉ ከሽፈዋል፤ ምክንያቱም “የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ [ሄዷል]።” (ሥራ 19:20) እነዚያ ክርስቲያኖች ድል እንዲያደርጉ የረዳቸው ምንድን ነው? ዛሬም እኛን ለድል ያበቁን ምክንያቶች ናቸው። በእርግጥ ድሉ የእኛ ሳይሆን የይሖዋ ነው። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚረዱንን ባሕርያት በይሖዋ መንፈስ እርዳታ ማዳበር እንችላለን። እስቲ በቅድሚያ የአጵሎስን ምሳሌ እንመልከት።

      “ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 18:24-28)

      3, 4. አቂላና ጵርስቅላ አጵሎስ ምን እንደጎደለው አስተዋሉ? ምንስ አደረጉ?

      3 ጳውሎስ በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ወደ ኤፌሶን ለመሄድ ተነስቷል፤ በዚሁ ጊዜ ላይ አጵሎስ የተባለ አይሁዳዊ ወደዚህች ከተማ መጣ። አጵሎስ ታዋቂ የሆነችው የግብጿ እስክንድርያ ተወላጅ ነው። ይህ ሰው በርካታ ግሩም ባሕርያት አሉት። ጥሩ የመናገር ችሎታ አለው። አንደበተ ርቱዕ ከመሆኑም ሌላ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር።” በተጨማሪም “በመንፈስ እየተቃጠለ . . . ያስተምር ነበር።” በቅንዓት የተሞላው አጵሎስ በምኩራብ ለተሰበሰቡት አይሁዳውያን በድፍረት ይናገር ነበር።—ሥራ 18:24, 25

      4 አጵሎስ በዚህ መንገድ ሲናገር አቂላና ጵርስቅላ ሰሙት። “ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል [ሲያስተምር]” በመስማታቸው በጣም ተደስተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። አጵሎስ ስለ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ምንም ስህተት የለውም። ብዙም ሳይቆይ ግን እነዚህ ክርስቲያን ባልና ሚስት አንድ ነገር አስተዋሉ፤ አጵሎስ ያልተረዳው አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር አለ። “እሱ የሚያውቀው ዮሐንስ ይሰብከው ስለነበረው ጥምቀት ብቻ ነበር።” ድንኳን በመሥራት ሙያ የሚተዳደሩት እነዚህ ባልና ሚስት የአጵሎስን የመናገር ችሎታ ወይም የትምህርት ደረጃ በማየት ተሸማቅቀው ወደኋላ አላሉም። ከዚህ ይልቅ “ይዘውት በመሄድ የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት።” (ሥራ 18:25, 26) ታዲያ አንደበተ ርቱዕና ምሁር የሆነው ይህ ሰው ምን ምላሽ ሰጠ? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ እንደ ክርስቲያን መጠን እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ባሕርያት አንዱን ይኸውም ትሕትናን አሳይቷል።

      5, 6. አጵሎስን ይበልጥ ውጤታማ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው? እኛስ እሱ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?

      5 አጵሎስ፣ አቂላና ጵርስቅላ ያደረጉለትን እርዳታ በመቀበሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ መሆን ችሏል። ወደ አካይያ በመጓዝ በዚያ ያሉትን አማኞች “በእጅጉ ረዳቸው።” በተጨማሪም ‘አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ኢየሱስ አይደለም’ ብለው ለሚከራከሩት በዚያ ክልል የነበሩ አይሁዳውያን ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል። ሉቃስ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ከአይሁዳውያን ጋር በይፋ በመወያየት ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እያሳያቸው ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ በመግለጽ ትክክል እንዳልሆኑ በጋለ ስሜት ያስረዳቸው ነበር።” (ሥራ 18:27, 28) አጵሎስ ለክርስቲያን ጉባኤ እንዴት ያለ በረከት ነበር! እሱ ያከናወነው አገልግሎት “የይሖዋ ቃል” እያሸነፈ እንዲሄድ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አጵሎስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?

      6 ትሕትና ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ባሕርይ ነው። እያንዳንዳችን በተፈጥሮ ወይም በትምህርት ያገኘናቸው አሊያም በተሞክሮ ያዳበርናቸው የተለያዩ ስጦታዎች አሉን። ሆኖም ካሉን ስጦታዎች ይልቅ ጎልቶ መታየት ያለበት ትሕትናችን ነው። አለዚያ ጥሩ ጎናችን ደካማ ጎን ሊሆንብን ይችላል። አደገኛ የሆነው የትዕቢት ባሕርይ በውስጣችን እንዲያቆጠቁጥ ምቹ ሁኔታ ልንፈጥርለት እንችላለን። (1 ቆሮ. 4:7፤ ያዕ. 4:6) ከልባችን ትሑቶች ከሆንን ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ ለማሰብ እንጥራለን። (ፊልጵ. 2:3) ሌሎች እርማት ሲሰጡንም ሆነ ሲያስተምሩን በደስታ እንቀበላለን። አመለካከታችን መንፈስ ቅዱስ በወቅቱ ከሚሰጠው አመራር ጋር እንደማይጣጣም ከተገነዘብን ለውጥ ለማድረግ እንጥራለን፤ በያዝነው አቋም ድርቅ በማለት የኩራት ዝንባሌ አናሳይም። ይሖዋም ሆነ ልጁ የሚጠቀሙብን ምንጊዜም ትሑቶች ከሆንን ነው።—ሉቃስ 1:51, 52

      7. ጳውሎስና አጵሎስ ምን የትሕትና ምሳሌ ትተዋል?

      7 ትሕትና ለፉክክር መንፈስም ፍቱን መድኃኒት ነው። ሰይጣን በጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል ክፍፍል ለመፍጠር ምን ያህል ቋምጦ እንደነበር አስበው። አጵሎስም ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ የተጨበጨበላቸው አስተማሪዎች ናቸው፤ ቅናት በልባቸው አድሮ በጉባኤ ውስጥ የበላይ ለመሆን መፎካከር ቢጀምሩ ሰይጣን የልቡ ደረሰ ማለት ነው! ደግሞም እንዲፎካከሩ ሊያደርጋቸው የሚችል ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። በቆሮንቶስ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ “እኔ ግን የአጵሎስ ነኝ” ይሉ ነበር። ጳውሎስና አጵሎስ እንዲህ ያለውን የሚከፋፍል አመለካከት ለማስተናገድ ፈቃደኞች ነበሩ? በፍጹም! አጵሎስ ለሥራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጳውሎስ በትሕትና አምኖ ተቀብሏል፤ እንዲያውም ተጨማሪ የአገልግሎት መብት ሰጥቶታል። አጵሎስም ቢሆን ጳውሎስ የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ አድርጓል። (1 ቆሮ. 1:10-12፤ 3:6, 9፤ ቲቶ 3:12, 13) በትሕትና ተባብሮ በመሥራት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል!

      “ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ . . . ማስረዳት” (የሐዋርያት ሥራ 18:23፤ 19:1-10)

      8. ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን የተመለሰው በየት አድርጎ ነው? ለምንስ?

      8 ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል ገብቶ ነበር፤ ቃሉንም ጠብቋል።a (ሥራ 18:20, 21) ይሁንና ወደ ኤፌሶን የተመለሰው እንዴት ነበር? ጉዞውን የጀመረው ከሶርያዋ አንጾኪያ ነው። ወደ ኤፌሶን ለመሄድ አጭሩ መንገድ በአቅራቢያው ወዳለችው ሴሌውቅያ መጓዝ፣ ከዚያም መርከብ ተሳፍሮ በቀጥታ መሄድ ነው። ጳውሎስ ግን “በመሃል አገር አቋርጦ” ተጓዘ። በሐዋርያት ሥራ 18:23 እና 19:1 ላይ የተገለጸው የጳውሎስ ጉዞ በግምት አንድ ሺህ ስድስት መቶ ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል! ጳውሎስ እንዲህ ያለ አድካሚ ጉዞ ለማድረግ የመረጠው ለምንድን ነው? ‘ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ማበረታታት’ ስለፈለገ ነው። (ሥራ 18:23) ሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው እንደ ቀድሞዎቹ ሁለት ጉዞዎች ሁሉ አድካሚ መሆኑ አይቀርም፤ ለወንድሞቹ ሲል ግን ምንም ያህል ቢደክም አይቆጨውም። በዛሬው ጊዜም የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ተመሳሳይ መንፈስ አላቸው። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚያሳዩትን ፍቅር እናደንቃለን!

      ኤፌሶን—የእስያ ዋና ከተማ

      በትንሿ እስያ ምዕራባዊ ክፍል ከሚገኙት ከተሞች ሁሉ ትልቋ ኤፌሶን ነበረች። በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን የከተማዋ የሕዝብ ብዛት ከ250,000 በላይ ሳይሆን አይቀርም። ኤፌሶን የሮም ግዛት የሆነው የእስያ አውራጃ ዋና ከተማ ነች፤ በዚህም “የመጀመሪያዋና ታላቋ የእስያ ከተማ” የሚል የክብር ስያሜ ተሰጥቷት ነበር።

      ኤፌሶን ንግድና ሃይማኖት ያበለጸጋት ከተማ ነች። ለጀልባዎች እንቅስቃሴ አመቺ በሆነ አንድ ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገኘው ወደቧ የተለያዩ የንግድ መስመሮች የሚገናኙበት ቁልፍ ቦታ ነበር። ኤፌሶን የታዋቂው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ከተማ ነች፤ ሆኖም የግሪክና የሮም፣ የግብፅ እንዲሁም የአናቶሊያ በርካታ ጣዖታት ቤተ መቅደሶችም ይገኙባት ነበር።

      የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ከጥንቱ ዓለም ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል፤ የቤተ መቅደሱ ስፋት 105 ሜትር በ50 ሜትር ገደማ ይሆናል። መቶ ያህል የእብነ በረድ ዓምዶች ነበሩት፤ እያንዳንዱ ዓምድ ከታች በኩል 1.8 ሜትር ገደማ ዳያሜትር አለው፤ ቁመቱ ደግሞ 17 ሜትር ገደማ ይሆናል። ይህ ቤተ መቅደስ በጥንቱ የሜድትራንያን አካባቢ እጅግ ቅዱስ ስፍራ ተደርጎ ይታይ ነበር፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብም በአደራ ይቀመጥበት ነበር፤ በመሆኑም ቤተ መቅደሱ እስያ ውስጥ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ቁልፍ ማዕከል ነበር።

      በኤፌሶን ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሌሎች ሕንፃዎችም ነበሩ፤ ከእነዚህም መካከል ለአትሌቲክስ ውድድሮችና ምናልባትም ለግላዲያተር ግጥሚያዎች የሚያገለግል ስታዲየም፣ ቲያትር ቤት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የንግድ ማዕከሎች እንዲሁም ባለመጠለያ መተላለፊያ ያላቸው ሱቆች ይገኙበታል።

      ስትራቦ የተባለው ግሪካዊ የጂኦግራፊ ምሁር፣ የኤፌሶን ወደብ ደለል ይከማችበት እንደነበር ጽፏል። በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ከተማዋ የወደብ አገልግሎት መስጠቷን አቆመች፤ ውሎ አድሮም ወና ሆነች። በአሁኑ ጊዜ በዚያ ቦታ ላይ የተገነባ ዘመናዊ ከተማ የለም፤ በመሆኑም የኤፌሶንን ከተማ ፍርስራሽ በመጎብኘት የጥንቱ ዓለም ምን እንደሚመስል የኋሊት መቃኘት ይቻላል።

      9. አንዳንድ ደቀ መዛሙርት እንደገና መጠመቅ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ከእነሱስ ምን እንማራለን?

      9 ጳውሎስ ኤፌሶን ሲደርስ የአጥማቂው ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ አሥራ ሁለት ገደማ ሰዎች አገኘ። እነዚህ ሰዎች የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበር፤ ሆኖም ይህ ጥምቀት በወቅቱ ተቀባይነት አልነበረውም። ከዚህም ሌላ ስለ መንፈስ ቅዱስ እምብዛም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ስለዚህ ጳውሎስ ግንዛቤያቸውን ወቅታዊ እንዲያደርጉ ረዳቸው፤ ልክ እንደ አጵሎስ እነሱም ትሑቶችና ለመማር ፈቃደኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። በኢየሱስ ስም ከተጠመቁ በኋላ መንፈስ ቅዱስንና አንዳንድ ተአምራዊ ስጦታዎችን ተቀብለዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ወደፊት እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ቲኦክራሲያዊ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ በረከት ያስገኛል።—ሥራ 19:1-7

      10. ጳውሎስ ከምኩራቡ ወጥቶ ወደ አንድ የትምህርት ቤት አዳራሽ የሄደው ለምንድን ነው? እኛስ በአገልግሎታችን እሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

      10 ብዙም ሳይቆይ ሌላ ነገር ደግሞ ተከናወነ። ጳውሎስ ምኩራብ ውስጥ ለሦስት ወር በድፍረት ሰበከ። “ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ” ቢያስረዳም አንዳንዶች ልባቸውን በማደንደን ኃይለኛ ተቃዋሚዎች ሆኑ። ጳውሎስ ‘የጌታን መንገድ ከሚያጥላሉ’ ሰዎች ጋር ጊዜውን ማጥፋት አልፈለገም፤ በመሆኑም በአንድ የትምህርት ቤት አዳራሽ ንግግር ለመስጠት ዝግጅት አደረገ። (ሥራ 19:8, 9) መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ከምኩራቡ ወጥተው ወደ ትምህርት ቤቱ አዳራሽ መሄድ ነበረባቸው። ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም የምናነጋግረው ሰው ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ወይም እንዲሁ መከራከር ብቻ እንደሚፈልግ ከተገነዘብን ትተነው መሄድ እንችላለን። የምንሰብከውን የሚያጽናና መልእክት መስማት የሚያስፈልጋቸው ብዙ በግ መሰል ሰዎች አሉ!

      11, 12. (ሀ) ጳውሎስ በትጋት በመሥራትና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ በማድረግ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው በትጋት ለመሥራትና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ ለማድረግ የሚጥሩት እንዴት ነው?

      11 ጳውሎስ በዚያ የትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያስተምር ነበር፤ ምናልባትም ይህን የሚያደርገው ከቀኑ 5:00 እስከ 10:00 ሳይሆን አይቀርም። (ለ⁠ሥራ 19:9 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት፣ nwtsty-E) ይህ ሰዓት ከተማው ጭር የሚልበትና ሙቀቱ የሚያይልበት ጊዜ ነው፤ ብዙዎች ሥራቸውን አቁመው ምግብ የሚበሉበትና የሚያርፉበት ሰዓት ነው። ጳውሎስ ሁለት ዓመት ሙሉ ይህን ፕሮግራም ተከትሎ ከነበረ በማስተማር ሥራው ከ3,000 ሰዓት በላይ አሳልፏል ማለት ነው።b የይሖዋ ቃል እየተስፋፋና እያሸነፈ የሄደበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው። ጳውሎስ ትጉና እንደ ሁኔታው ማስተካከያ የሚያደርግ ሰው ነበር። ብዙ ሰዎችን ለማግኘት ሲል ፕሮግራሙን እንደ ሁኔታው አስተካክሏል። ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? “በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ።” (ሥራ 19:10) በእርግጥም ጳውሎስ በሚገባ መሥክሯል!

      ሁለት እህቶች በስልክ ሲመሠክሩ።

      ሰዎችን ለማግኘት የሚያስችሉንን ዘዴዎች ሁሉ በመጠቀም ለመስበክ እንጥራለን

      12 በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በትጋት ይሠራሉ እንዲሁም ሰዎችን ለመርዳት ሲሉ እንደ ሁኔታው ማስተካከያ ያደርጋሉ። ሰዎች ሊገኙ በሚችሉበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ምሥራቹን ለመስበክ እንጥራለን። በመንገድ ላይ፣ በገበያ ቦታዎችና በመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እንሰብካለን። በስልክም ሆነ በደብዳቤ ለሰዎች እንመሠክራለን። ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜም ሰዎችን ቤታቸው ልናገኛቸው በምንችልበት ሰዓት ላይ ለመሄድ ጥረት እናደርጋለን።

      የርኩሳን መናፍስት ተጽዕኖ ቢኖርም “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ” (የሐዋርያት ሥራ 19:11-22)

      13, 14. (ሀ) ይሖዋ ጳውሎስን ምን እንዲፈጽም አስችሎታል? (ለ) የአስቄዋ ልጆች ምን ስህተት ሠሩ? በዛሬው ጊዜስ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙዎች ተመሳሳይ ስህተት የሚሠሩት እንዴት ነው?

      13 ቀጣዩ የሉቃስ ዘገባ፣ ጳውሎስ በይሖዋ ኃይል “በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን” እንደፈጸመ ይገልጻል። ሰዎች የጳውሎስን ጨርቆችና ሽርጦች እንኳ ወደ ሕመምተኞች በመውሰድ እንዲፈወሱ ያደርጉ ነበር። ርኩሳን መናፍስትም በዚሁ መንገድ ይወጡ ነበር።c (ሥራ 19:11, 12) በሰይጣን ኃይሎች ላይ የተገኘው ይህ አስደናቂ ድል የብዙዎችን ትኩረት ሳበ፤ በዚህ የተደሰተው ግን ሁሉም ሰው አይደለም።

      14 “እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁዳውያን አንዳንዶቹ” ጳውሎስ የፈጸማቸውን ተአምራት ለማስመሰል ሞከሩ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የኢየሱስንና የጳውሎስን ስም በመጥራት አጋንንትን ለማስወጣት ተነሱ። የሉቃስ ዘገባ የካህናት ቤተሰብ የሆነው የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህን ለማድረግ ሞክረው እንደነበር ይገልጻል። ጋኔኑ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው። ከዚያም ክፉው መንፈስ ያደረበት ሰው እነዚህ አስመሳዮች ላይ እንደ አውሬ ዘሎ ጉብ አለባቸው፤ ስለዚህ ቆሳስለው ራቁታቸውን ሸሹ። (ሥራ 19:13-16) ጳውሎስ የተሰጠው ታላቅ ኃይል የእነዚያን የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች አቅመ ቢስነት አጋለጠ፤ በዚህም “የይሖዋ ቃል” አስደናቂ ድል አገኘ። በዛሬው ጊዜም የኢየሱስን ስም መጥራት ወይም “ክርስቲያን” ተብሎ መጠራት ብቻ በቂ እንደሆነ የሚያስቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ሆኖም ኢየሱስ እንደተናገረው እውነተኛ የወደፊት ተስፋ ያላቸው የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉ ብቻ ናቸው።—ማቴ. 7:21-23

      15. መናፍስታዊ ድርጊትንና ከዚህ ልማድ ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በተመለከተ የኤፌሶን ነዋሪዎች ምን ምሳሌ ትተውልናል?

      15 በአስቄዋ ልጆች ላይ የደረሰው ውርደት ብዙዎች አምላክን እንዲፈሩ አደረገ፤ በዚህም የተነሳ መናፍስታዊ ድርጊታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው አማኞች ሆኑ። በኤፌሶን አስማታዊ ድርጊቶች ተስፋፍተው ነበር። መተት መሥራትና ክታብ ማሰር የተለመዱ ነገሮች ነበሩ፤ ድግምትም እንዲሁ፤ ብዙ የድግምት መጻሕፍትም ነበሩ። በአምላክ ያመኑ ብዙ የኤፌሶን ነዋሪዎች ለአስማታዊ ድርጊቶች የሚጠቀሙባቸውን መጻሕፍት አምጥተው በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ እነዚህ መጻሕፍት አሁን ባለው የዋጋ ተመን መሠረት በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሳያወጡ አይቀሩም።d ሉቃስ “በዚህ መንገድ የይሖዋ ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ” በማለት ዘግቧል። (ሥራ 19:17-20) አዎ፣ እውነት በሐሰት ትምህርትና በአጋንንታዊ ድርጊት ላይ ታላቅ ድል ተቀዳጀ! እነዚያ ታማኝ ሰዎች ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። እኛም የምንኖረው በመናፍስታዊ ድርጊት በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያለው ነገር ካለን የኤፌሶን ነዋሪዎች እንዳደረጉት ወዲያውኑ ማስወገድ ይኖርብናል! ምንም ያህል ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለን ቢሆን እንዲህ ካለው አስጸያፊ ድርጊት መራቅ አለብን።

      “ታላቅ ሁከት ተፈጠረ” (የሐዋርያት ሥራ 19:23-41)

      ድሜጥሮስ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ የብር ምስል ይዟል፤ በኤፌሶን ባለ የብር አንጥረኞች ሱቅ ለሚሠሩ ባልደረቦቹ በቁጣ ተሞልቶ እየተናገረ ነው። ማዶ ላይ ጳውሎስ በገበያ ቦታ ለተሰበሰቡ ሰዎች ሲሰብክ ይታያል።

      “እናንተ ሰዎች፣ መቼም ብልጽግናችን የተመካው በዚህ ሥራ ላይ እንደሆነ ታውቃላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 19:25

      16, 17. (ሀ) ድሜጥሮስ በኤፌሶን ረብሻ እንዲቀሰቀስ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) የኤፌሶን ነዋሪዎች ጽንፈኛ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

      16 አሁን ደግሞ ሰይጣን የተጠቀመበትን ሌላ ዘዴ እንመልከት፤ ሉቃስ “የጌታን መንገድ በተመለከተ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ” ብሏል። ሉቃስ ይህን ሲል እያጋነነ አልነበረም።e (ሥራ 19:23) ሁከቱን የቀሰቀሰው ድሜጥሮስ የተባለ የብር አንጥረኛ ነው። በመጀመሪያ፣ የሙያ ባልደረቦቹን ትኩረት ለመሳብ ብልጽግናቸው የተመካው የጣዖት ምስሎችን በመሸጥ ላይ እንደሆነ ጠቀሰላቸው። ቀጥሎም ክርስቲያኖች ጣዖታትን ስለማያመልኩ ጳውሎስ የሚሰብከው መልእክት የገቢ ምንጫቸውን እንደሚያደርቅባቸው ገለጸ። ከዚያም የአገር ፍቅር ስሜታቸውን ለመቀስቀስ ሞከረ፤ ድሜጥሮስ፣ የኤፌሶን ሰዎች በከተማቸውና በዜግነታቸው እንደሚኮሩ ያውቃል፤ በመሆኑም አምላካቸው አርጤምስም ሆነች በዓለም ሁሉ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ቤተ መቅደሷ ‘ዋጋ ቢስ ሆነው እንደሚቀሩ’ በመግለጽ ክብራቸው እንደተነካ እንዲሰማቸው አደረገ።—ሥራ 19:24-27

      17 ድሜጥሮስ የተናገረው ነገር የፈለገውን ውጤት አስገኝቶለታል። የብር አንጥረኞቹ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር፤ በዚህም ምክንያት ከተማዋ በረብሻ ተናወጠች፤ በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ ለተገለጸው የሕዝብ ዓመፅ ምክንያት የሆነው ይህ ነበር።f ለወንድሞቹ ሲል ራሱን አሳልፎ የሚሰጠው ጳውሎስ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ገብቶ ሕዝቡን ማነጋገር ፈለገ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን አደጋ እንዳይደርስበት ስለፈሩ ወደዚያ እንዳይሄድ ከለከሉት። እስክንድር የሚባል ሰው ሕዝቡ ፊት ቆሞ ሊናገር ሞከረ። ይህ ሰው አይሁዳዊ ስለሆነ በአይሁዳውያንና በእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ልዩነት ሊያብራራ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ማብራሪያ ግን ለእነዚህ ሰዎች ምንም ፋይዳ አልነበረውም። አይሁዳዊ መሆኑን ሲያውቁ ጩኸታቸውን ቀጠሉ፤ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ለሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ዛሬም ተመሳሳይ ባሕርይ አለው። ሰዎች ጨርሶ እንዳያመዛዝኑ ያደርጋል።—ሥራ 19:28-34

      18, 19. (ሀ) የከተማዋ ዋና ጸሐፊ በኤፌሶን የተቀሰቀሰውን የሕዝብ ረብሻ ጸጥ ያሰኘው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ ባለሥልጣናት ለይሖዋ ሕዝቦች ከለላ የሆኑት እንዴት ነው? እኛስ በዚህ ረገድ ምን ሚና መጫወት እንችላለን?

      18 በመጨረሻ የከተማዋ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኘ። ይህ ባለሥልጣን ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለውና ምክንያታዊ ሰው ነው፤ ክርስቲያኖች፣ በቤተ መቅደሳቸውም ሆነ በአምላካቸው ላይ የሚያስከትሉት አደጋ እንደሌለ በመግለጽ ሕዝቡን አረጋጋ፤ ጳውሎስና ባልደረቦቹ በአርጤምስ ቤተ መቅደስ ላይ ምንም ወንጀል እንዳልፈጸሙም ገለጸ። የሚያቀርቡት ክስ ካላቸው ደግሞ ጉዳዩ የሚታይበት የራሱ የሆነ ሥርዓት እንዳለ ተናገረ። ከዚያ ግን ሕገወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ መሰባሰባቸው በሮም ሕግ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል አስታወሳቸው፤ ሰዎቹ አደብ እንዲገዙ ያደረጋቸው ይህ አባባሉ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ከተናገረ በኋላ ሕዝቡ እንዲበተን አደረገ። በድንገት የገነፈለው የሕዝቡ ቁጣ በዋና ጸሐፊው ምክንያታዊና አሳማኝ ቃላት የተነሳ ወዲያውኑ በረደ።—ሥራ 19:35-41

      19 ረጋ ያለና አስተዋይ ባለሥልጣን፣ የኢየሱስን ተከታዮች ከአደጋ ለመጠበቅ እርምጃ ሲወስድ ይህ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ አይደለም። እንዲያውም ሐዋርያው ዮሐንስ፣ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ይህ እንደሚሆን በራእይ ተመልክቶ ነበር፤ ምድሪቱ ሰይጣን በኢየሱስ ተከታዮች ላይ የለቀቀውን የስደት ጎርፍ ስትውጥ አይቷል፤ በምድሪቱ የተመሰሉት የተሻለ ምክንያታዊነት ያላቸው የዚህ ዓለም ክፍሎች ለአምላክ ሕዝቦች እንደሚደርሱላቸው ራእዩ ይጠቁማል። (ራእይ 12:15, 16) የሆነውም ይህ ነው። ፍትሐዊ አመለካከት ያላቸው ዳኞች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ የመሰብሰብና ምሥራቹን የመስበክ መብታቸው እንዲከበር ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። እርግጥ ነው፣ እኛ የምናሳየው ምግባርም ለእነዚህ ድሎች የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይችላል። ጳውሎስ ያሳየው ምግባር በኤፌሶን የሚገኙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አክብሮት ሳያተርፍለት አልቀረም፤ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች አደጋ እንዳይደርስበት ለማድረግ ጥረዋል። (ሥራ 19:31) እኛም ሐቀኛና ሰው አክባሪ መሆናችን በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም እንዲያተርፍልን እንመኛለን። ይህ ምግባራችን የኋላ ኋላ ምን በጎ ውጤት እንደሚያስገኝ አናውቅም።

      20. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ቃል በኃይል እያሸነፈ መሄዱን ስታስብ ምን ይሰማሃል? (ለ) በዘመናችን ይሖዋ እየተቀዳጀ ካለው ድል ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

      20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋና እያሸነፈ” የሄደው እንዴት እንደሆነ መለስ ብለን መቃኘታችን በእርግጥም የሚያስደስት ነው! በዘመናችን ይሖዋ ተመሳሳይ ድሎች እንዲገኙ ያደረገበትን መንገድ ስናስብም ተመሳሳይ ስሜት ይሰማናል። ለዚህ ድል ትንሽም እንኳ ቢሆን አስተዋጽኦ የማድረግ መብት ማግኘት ትፈልጋለህ? እንግዲያው ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች የተዉትን ምሳሌ ተከተል። ምንጊዜም ትሑት ሁን፤ ወደፊት እየገሰገሰ ካለው የይሖዋ ድርጅት እኩል ተራመድ፤ በትጋት መሥራትህን ቀጥል፤ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ራቅ እንዲሁም ሐቀኛ በመሆንና የሚያስከብር ምግባር በማሳየት ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የተቻለህን አድርግ።

      a “ኤፌሶን—የእስያ ዋና ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      b ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስን የጻፈውም በኤፌሶን ሳለ ነበር።

      c እዚህ ላይ የተጠቀሱት ጨርቆች ጳውሎስ ላቡ ዓይኑ ውስጥ እንዳይገባ ግንባሩ ላይ የሚያስራቸው መሐረቦች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ስለ ሽርጦቹ ከሚገልጸው ሐሳብ እንደምንረዳው ጳውሎስ በወቅቱ ነፃ በሚሆንበት ሰዓት ምናልባትም ማለዳ ላይ ድንኳን ይሠራ የነበረ ይመስላል።—ሥራ 20:34, 35

      d ሉቃስ እነዚህ መጻሕፍት 50,000 የብር ሳንቲሞች እንደሚያወጡ ጠቅሷል። እነዚህ የብር ሳንቲሞች ዲናር ከሆኑ ዋጋቸው በጣም ብዙ ነው፤ በዚያ ዘመን አንድ ሠራተኛ ይህን የሚያህል ገንዘብ ለማግኘት በሳምንት ሰባቱንም ቀን ቢሠራ እንኳ 50,000 ቀናት ማለትም 137 ዓመታት ገደማ ይፈጅበታል።

      e አንዳንዶች፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ “በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር” ያለው ይህን ገጠመኝ አስቦ እንደሆነ ይናገራሉ። (2 ቆሮ. 1:8) ይሁን እንጂ ከዚህም የከፋ አደገኛ ሁኔታ ያጋጠመውን ጊዜ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ “በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር [እንደታገለ]” ሲጽፍ በመወዳደሪያ ቦታዎች ከጨካኝ አራዊት ጋር መታገሉን መግለጹ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ከሰዎች ኃይለኛ ተቃውሞ እንዳጋጠመው እየተናገረ ይሆናል። (1 ቆሮ. 15:32) ሐሳቡ ቃል በቃል አሊያም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሊወሰድ ይችላል።

      f እንዲህ ያሉ የእጅ ሙያ ማኅበራት ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ የዳቦ ጋጋሪዎች ማኅበር በኤፌሶን ተመሳሳይ ዓመፅ አስነስቶ ነበር።

  • ‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • ምዕራፍ 21

      ‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’

      የጳውሎስ የአገልግሎት ቅንዓትና ለሽማግሌዎች የሰጠው ምክር

      በሐዋርያት ሥራ 20:1-38 ላይ የተመሠረተ

      1-3. (ሀ) ከአውጤኪስ ሞት ጋር በተያያዘ የነበረውን ሁኔታ ግለጽ። (ለ) ጳውሎስ ምን አደረገ? ይህ አጋጣሚስ ስለ እሱ ምን ያስገነዝበናል?

      ጳውሎስ አሁን ያለው ጥሮአስ ነው፤ ፎቅ ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰው ተሰብስቧል። ጳውሎስ ለተሰብሳቢዎቹ ንግግር እየሰጠ ረጅም ሰዓት ቆየ፤ ምክንያቱም ይህ ከእነሱ ጋር የሚያሳልፈው የመጨረሻ ምሽት ነው። ጊዜው እኩለ ሌሊት ሆነ። ጭል ጭል የሚሉ ኩራዞች እዚያም እዚህም በርተዋል፤ ለዚያ ሳይሆን አይቀርም ክፍሉ ይሞቃል፣ ጭሱም እፍን ያደረገው ይመስላል። አንደኛው መስኮት ላይ አውጤኪስ የሚባል ወጣት ተቀምጧል። ጳውሎስ እየተናገረ ሳለ አውጤኪስ እንቅልፍ ጣለውና ከሁለተኛ ፎቅ ወደ ታች ወደቀ!

      2 አውጤኪስን ለማንሳት እየተንደረደሩ ከወረዱት አንዱ ሐኪሙ ሉቃስ ሳይሆን አይቀርም። የሚያሳዝነው ግን ምንም ሊያደርጉለት አልቻሉም። ወጣቱን ‘ሲያነሱት ሞቶ ነበር።’ (ሥራ 20:9) ከዚያ ግን አንድ ተአምር ተፈጸመ። ጳውሎስ ወጣቱ ላይ ተኛ፤ ከዚያም ሰዎቹን “በሕይወት ስላለ አትንጫጩ” አላቸው። አውጤኪስን ከሞት አስነሳው!—ሥራ 20:10

      3 ይህ አጋጣሚ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያሳያል። እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ለአውጤኪስ ሞት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ይሁንና የወጣቱ ሞት፣ በዚህ ልዩ ፕሮግራም ላይ መጥፎ ትዝታ እንዲተው ወይም ለወንድሞች መሰናክል እንዲሆን አልፈለገም። ጳውሎስ አውጤኪስን ከሞት ማስነሳቱ የጉባኤውን አባላት አጽናንቷቸዋል፤ በአገልግሎታቸው እንዲገፉም ብርታት ሰጥቷቸዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ለሕይወት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር። በዚህ ወቅት ያደረገው ነገር “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [እንደሆነ]” የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (ሥራ 20:26) ጳውሎስ የተወው ምሳሌ እኛም ለሕይወት አክብሮት እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።

      “ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ” (የሐዋርያት ሥራ 20:1, 2)

      4. ጳውሎስ ምን ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ አሳልፏል?

      4 ባለፈው ምዕራፍ ላይ እንደተብራራው ጳውሎስ አስጨናቂ ሁኔታ አሳልፏል። በኤፌሶን ያከናወነው አገልግሎት ከፍተኛ ሁከት አስነስቶ ነበር። አዎ፣ መተዳደሪያቸው በአርጤምስ አምልኮ ላይ የተመሠረተው የብር አንጥረኞች ሆ ብለው ተነስተውበታል! የሐዋርያት ሥራ 20:1 “ሁከቱ ከበረደ በኋላ” ምን እንደተፈጸመ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠራቸው፤ ካበረታታቸውና ከተሰናበታቸው በኋላ ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ።”

      5, 6. (ሀ) ጳውሎስ በመቄዶንያ ምን ያህል ጊዜ ቆይቶ ሊሆን ይችላል? በዚያ ለሚገኙ ወንድሞችስ ምን አድርጎላቸዋል? (ለ) ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

      5 ጳውሎስ ወደ መቄዶንያ ሲጓዝ እግረ መንገዱን ጥሮአስ ወደብ ላይ አረፍ አለ፤ በዚያም የተወሰነ ጊዜ አሳለፈ። ቲቶን እዚህ እንደሚያገኘው ተስፋ አድርጎ ነበር። (2 ቆሮ. 2:12, 13) ቲቶ ወደ ቆሮንቶስ ተልኮ ነበር፤ ይሁንና ጳውሎስ ቲቶ እንደማይመጣ ሲያውቅ ወደ መቄዶንያ ጉዞውን ቀጠለ፤ በዚያም “የሚያገኛቸውን ደቀ መዛሙርት በብዙ ቃል እያበረታታ” አንድ ዓመት አካባቢ ሳይቆይ አልቀረም።a (ሥራ 20:2) በመጨረሻም ቲቶ በመቄዶንያ ከጳውሎስ ጋር ተገናኘ፤ የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ ለላከላቸው የመጀመሪያ ደብዳቤ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተም መልካም ዜና ይዞለት መጥቷል። (2 ቆሮ. 7:5-7) ጳውሎስ ይህን ሲሰማ ሌላ ደብዳቤ ሊጽፍላቸው ተነሳ፤ ይህ ደብዳቤ በአሁኑ ጊዜ 2 ቆሮንቶስ ተብሎ ይጠራል።

      6 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶንም ሆነ በመቄዶንያ የሚገኙ ወንድሞችን ሲጎበኝ ‘እንዳበረታታቸው’ ሉቃስ ጠቅሷል። ይህ አገላለጽ ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ያለውን አመለካከት ጥሩ አድርጎ ያሳያል! ፈሪሳውያን ሌሎችን ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ነበር፤ በተቃራኒው ግን ጳውሎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን አብረውት የሚያገለግሉ የሥራ ባልደረቦች አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። (ዮሐ. 7:47-49፤ 1 ቆሮ. 3:9) ጠንከር ያለ ምክር መስጠት ባስፈለገው ጊዜ እንኳ ለእነሱ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበረው።—2 ቆሮ. 2:4

      7. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

      7 በዛሬው ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ተግሣጽ በሚሰጡበት ጊዜም እንኳ ዓላማቸው እርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው ማበረታታት ነው። የበላይ ተመልካቾች ወንድሞቻቸውን ከመኮነን ይልቅ ስሜታቸውን በመረዳት እነሱን ለማበረታታት ይጥራሉ። ተሞክሮ ያካበተ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ፤ ብዙውን ጊዜ ግን ነገሮች እንዳሰቡት አለመሆናቸው ከሚፈጥረው ስሜት ጋር ይታገላሉ፤ አሊያም ስጋት የሚያሳድሩባቸው ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል፤ ወይም ደግሞ ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል።” የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ላሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸው የብርታት ምንጭ መሆን ይችላሉ።—ዕብ. 12:12, 13

      ጳውሎስ ከመቄዶንያ የጻፋቸው ደብዳቤዎች

      ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው መቄዶንያ ሲደርስ ቆሮንቶስ ያሉት ወንድሞቹ ጉዳይ አስጨንቆት ነበር። ይሁን እንጂ ቲቶ ከቆሮንቶስ ሲመለስ መልካም ዜና ይዞለት በመምጣቱ ተጽናንቷል። ይህን እንደሰማ ማለትም በ55 ዓ.ም. ገደማ ጳውሎስ 2 ቆሮንቶስን ጻፈ፤ ደብዳቤው ላይ እንደጠቀሰው ያኔም ገና በመቄዶንያ ነበር። (2 ቆሮ. 7:5-7፤ 9:2-4) በዚህ ወቅት ጳውሎስን ካሳሰቡት ነገሮች አንዱ በይሁዳ ለሚገኙ ቅዱሳን መዋጮ የማሰባሰቡን ሥራ ማጠናቀቅ ነበር። (2 ቆሮ. 8:18-21) በተጨማሪም በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ “ሐሰተኛ ሐዋርያትና አታላይ ሠራተኞች” መኖራቸው አሳስቦታል።—2 ቆሮ. 11:5, 13, 14

      ጳውሎስ ለቲቶ የላከውን ደብዳቤ የጻፈው ከመቄዶንያ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሮም ውስጥ ታስሮ ከተፈታ በኋላ የቀርጤስን ደሴት ጎብኝቶ ነበር፤ ይህን ያደረገው ከ61 እስከ 64 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ የሆነ ጊዜ ላይ ነው። በቀርጤስ የተፈጠሩ አንዳንድ ችግሮችን እንዲያስተካክልና የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲሾም ቲቶን በዚያ ተወው። (ቲቶ 1:5) ጳውሎስ፣ እሱ ወዳለበት ወደ ኒቆጶሊስ እንዲመጣ ለቲቶ ጽፎለታል። በጥንቱ የሜድትራንያን አካባቢ በዚህ ስም የሚጠሩ በርካታ ከተሞች ነበሩ፤ ጳውሎስ የጠቀሰው ግን በግሪክ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል የምትገኘውን ኒቆጶሊስ ሳይሆን አይቀርም። ሐዋርያው ለቲቶ በጻፈለት ጊዜ በዚያ አካባቢ የነበረ ይመስላል።—ቲቶ 3:12

      ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የመጀመሪያውን ደብዳቤ የጻፈውም ከ61 እስከ 64 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው፤ ሮም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ ከተፈታ ሆኖም ለሁለተኛ ጊዜ ከመታሰሩ በፊት ማለት ነው። ጳውሎስ በደብዳቤው መግቢያ ላይ እንደጠቀሰው ጢሞቴዎስን በኤፌሶን እንዲቆይ ጠይቆት ነበር፤ ጳውሎስ ግን ወደ መቄዶንያ አምርቷል። (1 ጢሞ. 1:3) ስለዚህ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈው ከመቄዶንያ ሳይሆን አይቀርም፤ በደብዳቤው ላይ ለጢሞቴዎስ አባታዊ ምክርና ማበረታቻ እንዲሁም አንዳንድ የጉባኤ አሠራሮችን በተመለከተ መመሪያ ሰጥቶታል።

      ‘ሴራ ጠነሰሱበት’ (የሐዋርያት ሥራ 20:3, 4)

      8, 9. (ሀ) ጳውሎስ በመርከብ ወደ ሶርያ ለመሄድ የነበረውን ዕቅድ ያስተጓጎለበት ምንድን ነው? (ለ) አይሁዳውያን ለጳውሎስ ጥላቻ ያደረባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

      8 ጳውሎስ ከመቄዶንያ ተነስቶ ወደ ቆሮንቶስ ተጓዘ።b በዚያ ሦስት ወር ከቆየ በኋላ ወደ ክንክራኦስ መሄድ ፈለገ፤ ከዚያ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ሶርያ የማምራት ዕቅድ ነበረው። ከሶርያ ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ እዚያ ላሉ የተቸገሩ ወንድሞች የተሰበሰበውን መዋጮ ያስረክባል።c (ሥራ 24:17፤ ሮም 15:25, 26) ይሁን እንጂ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ዕቅዱን አስቀየሩት። የሐዋርያት ሥራ 20:3 “አይሁዳውያን ሴራ [እንደጠነሰሱበት]” ይናገራል።

      9 አይሁዳውያን ጳውሎስን በጥላቻ ዓይን ማየታቸው አያስገርምም፤ በእነሱ ዓይን ከሃዲ ነበር። ከዚህ ቀደም ባከናወነው አገልግሎት በቆሮንቶስ ምኩራብ ትልቅ ቦታ የነበረው ቀርስጶስ ክርስትናን ተቀብሏል። (ሥራ 18:7, 8፤ 1 ቆሮ. 1:14) በሌላ ወቅት ደግሞ እነዚህ የቆሮንቶስ አይሁዳውያን ጳውሎስን በአካይያ አገረ ገዢ በጋልዮስ ፊት ከስሰውት ነበር። ጋልዮስ ግን ክሱን መሠረት ቢስ እንደሆነ ቆጥሮ ውድቅ አደረገው፤ ይህ የጳውሎስን ጠላቶች በጣም አበሳጭቷቸው ነበር። (ሥራ 18:12-17) እነዚህ አይሁዳውያን፣ ጳውሎስ በአቅራቢያቸው ከምትገኘው ከክንክራኦስ መርከብ እንደሚሳፈር ሰምተው አሊያም ጠርጥረው ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ በዚያ አድብተው በእሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አሴሩ። ታዲያ ጳውሎስ ምን ያደርግ ይሆን?

      10. ጳውሎስ በክንክራኦስ ማለፍ አለመፈለጉ ፈሪ ያስብለዋል? አብራራ።

      10 ጳውሎስ በክንክራኦስ በኩል ከመጓዝ ይልቅ በመጣበት መንገድ ተመልሶ በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ወሰነ፤ ይህን ያደረገው ለደህንነቱ ሲል ብቻ ሳይሆን በአደራ የተሰጠውን ገንዘብ ለመጠበቅም ነው። እርግጥ ነው፣ በየብስ መጓዝ የራሱ የሆኑ አደጋዎች አሉት። በጥንት ዘመን መንገድ ላይ አድፍጠው የሚዘርፉ ወንበዴዎች አይጠፉም ነበር። የእንግዳ ማረፊያዎቹ እንኳ ለአደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ። ያም ሆኖ ጳውሎስ በክንክራኦስ ከሚጠብቀው ጥቃት ይልቅ በእግር መጓዝ የሚያስከትለውን አደጋ ለመጋፈጥ መረጠ። ደግነቱ የሚጓዘው ብቻውን አልነበረም። በዚህ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ሲኮንዱስ፣ ሶጳጥሮስ፣ ቲኪቆስ፣ አርስጥሮኮስ፣ ጋይዮስ፣ ጢሞቴዎስና ጢሮፊሞስ ከእሱ ጋር ነበሩ።—ሥራ 20:3, 4

      11. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ጥንቃቄ የሚያደርጉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?

      11 ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ክርስቲያኖች በአገልግሎት ላይ ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ብቻቸውን ከመሆን ይልቅ በቡድን አሊያም ሁለት ሁለት ሆነው ያገለግላሉ። ስደት ሲደርስባቸውስ? ክርስቲያኖች ስደት አይቀሬ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ዮሐ. 15:20፤ 2 ጢሞ. 3:12) ይሁንና እያወቁ ራሳቸውን ለአደጋ አያጋልጡም። የኢየሱስን ምሳሌ ተመልከት። በአንድ ወቅት ኢየሩሳሌም ውስጥ ተቃዋሚዎች እሱን ለመውገር ድንጋይ ሲያነሱ “ተሰወረና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ።” (ዮሐ. 8:59) በሌላ ጊዜም አይሁዳውያኑ እሱን ለመግደል አሲረው ነበር፤ በመሆኑም “ኢየሱስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በአይሁዳውያን መካከል በይፋ መንቀሳቀስ አቆመ፤ ከዚህ ይልቅ በምድረ በዳ አቅራቢያ ወዳለ ስፍራ ሄደ።” (ዮሐ. 11:54) ኢየሱስ፣ አምላክ ለእሱ ካለው ፈቃድ ጋር የሚጋጭ እስካልሆነ ድረስ ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርግ ነበር። ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ።—ማቴ. 10:16

      ጳውሎስ ለእርዳታ የተዋጣውን ገንዘብ አደረሰ

      በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ ባሉት ዓመታት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ብዙ ችግሮች አሳልፈዋል፤ ስደት ደርሶባቸዋል፣ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል እንዲሁም ረሃብ ተከስቷል። በዚህ የተነሳ አንዳንዶቹ ችግር ላይ ወድቀው ነበር። (ሥራ 11:27 እስከ 12:1፤ ዕብ. 10:32-34) በመሆኑም በ49 ዓ.ም. ገደማ በኢየሩሳሌም ያሉት ሽማግሌዎች፣ ጳውሎስ ምሥራቹን ለአሕዛብ በመስበክ ላይ እንዲያተኩር መመሪያ በሰጡት ጊዜ ‘ድሆችን ማሰቡን እንዳያቋርጥ’ አበረታቱት። ጳውሎስም ጉባኤዎች የሚያዋጡትን የእርዳታ ገንዘብ በማስተባበር የተሰጠውን ሥራ ዳር አድርሷል።—ገላ. 2:10

      በ55 ዓ.ም. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በገላትያ ለሚገኙ ጉባኤዎች የሰጠሁትን መመሪያ መከተል ትችላላችሁ። መዋጮ የሚሰባሰበው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጥ። ስመጣም የመረጣችኋቸውንና የድጋፍ ደብዳቤ የጻፋችሁላቸውን ሰዎች የልግስና ስጦታችሁን ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ።” (1 ቆሮ. 16:1-3) ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሁለተኛውን ደብዳቤ ሲጽፍ ስጦታቸውን አዘጋጅተው እንዲቆዩ አሳስቧቸዋል፤ የመቄዶንያ ሰዎችም መዋጮ እያሰባሰቡ እንደሆነም ነግሯቸዋል።—2 ቆሮ. 8:1 እስከ 9:15

      በመጨረሻም በ56 ዓ.ም. ከተለያዩ ጉባኤዎች የተወከሉት ወንድሞች ከጳውሎስ ጋር ተገናኙ፤ የተዋጣውን ገንዘብ ለማድረስም ጉዞ ጀመሩ። ዘጠኝ ሆነው አብረው መጓዛቸው ለደህንነታቸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይረዳቸዋል፤ ከዚህም ሌላ ጳውሎስ የተዋጣውን ገንዘብ በአግባቡ አልያዘም የሚል ክስ እንዳይሰነዘርበት ያደርጋል። (2 ቆሮ. 8:20) ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘበት ዋና ዓላማ ይህን መዋጮ ማድረስ ነው። (ሮም 15:25, 26) ከጊዜ በኋላ ለአገረ ገዢው ለፊሊክስ “ከብዙ ዓመታት [በኋላ] ለወገኖቼ ምጽዋት ለመስጠትና ለአምላክ መባ ለማቅረብ መጣሁ” ብሎታል።—ሥራ 24:17

      “እጅግ ተጽናኑ” (የሐዋርያት ሥራ 20:5-12)

      12, 13. (ሀ) የአውጤኪስ ትንሣኤ በጉባኤው ላይ ምን ስሜት አሳድሯል? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይጽናናሉ?

      12 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ መቄዶንያን አቋርጠው የተጓዙት አብረው ነው፤ ከዚያ ግን ለተወሰነ ጊዜ የተለያዩ ይመስላል። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ የጉዞ ቡድኑ እንደገና የተሰባሰበው ጥሮአስ ላይ ነው።d ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በአምስት ቀን ጊዜ ውስጥም እነሱ ወዳሉበት ወደ ጥሮአስ ደረስን።”e (ሥራ 20:6) በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ወጣቱ አውጤኪስ ከሞት የተነሳው በጥሮአስ ነበር። በዚያ የነበሩት ክርስቲያኖች፣ የእምነት አጋራቸው አውጤኪስ ከሞት በመነሳቱ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን አስበው! ዘገባው “እጅግ ተጽናኑ” ይላል።—ሥራ 20:12

      13 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተአምራት አይፈጸሙም። ይሁንና የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ በያዘው የትንሣኤ ተስፋ ‘እጅግ ተጽናንተዋል።’ (ዮሐ. 5:28, 29) እስቲ አስበው፤ አውጤኪስ ፍጹም ስላልሆነ ውሎ አድሮ በድጋሚ ሞቷል። (ሮም 6:23) በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ግን ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው! ከዚህ በተጨማሪ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት የሚነሱ ሰዎች የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ። (1 ቆሮ. 15:51-53) በእርግጥም ቅቡዓንም ሆኑ “ሌሎች በጎች” ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ‘እጅግ እንዲጽናኑ’ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት አላቸው።—ዮሐ. 10:16

      “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” (የሐዋርያት ሥራ 20:13-24)

      14. ጳውሎስ ሚሊጢን ላይ ከኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ሲገናኝ ምን አላቸው?

      14 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ከጥሮአስ ወደ አሶስ አቀኑ፤ ከዚያም ወደ ሚጢሊኒ፣ ኪዮስ፣ ሳሞስና ሚሊጢን ተጓዙ። የጳውሎስ ዕቅድ ለጴንጤቆስጤ በዓል ኢየሩሳሌም መድረስ ነው። በዚህ የመልስ ጉዞ፣ ኤፌሶን ላይ የማይቆም መርከብ ለመሳፈር የመረጠው ለጴንጤቆስጤ በዓል ኢየሩሳሌም ለመድረስ በጣም ስለቸኮለ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች ማነጋገር ስለፈለገ ወደ ሚሊጢን እንዲመጡ መልእክት ላከባቸው። (ሥራ 20:13-17) እዚያ በደረሱ ጊዜም እንዲህ አላቸው፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በመካከላችሁ እንዴት እንደተመላለስኩ ታውቃላችሁ፤ በአይሁዳውያን ሴራ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስብኝም እንኳ በታላቅ ትሕትናና በእንባ ጌታን አገለግል ነበር፤ ደግሞም የሚጠቅማችሁን ማንኛውንም ነገር ከመንገርም ሆነ በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ወደኋላ ብዬ አላውቅም። ከዚህ ይልቅ አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ንስሐ እንዲገቡና ወደ አምላክ እንዲመለሱ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ በተሟላ ሁኔታ መሥክሬላቸዋለሁ።”—ሥራ 20:18-21

      15. ከቤት ወደ ቤት መመሥከር ያሉት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

      15 በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን ለሰዎች ለማድረስ የምንጠቀምባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ሰዎች ወደሚገኙበት ቦታ ሁሉ እንሄዳለን፤ በአውቶቡስ ፌርማታ፣ መንገደኛ በሚበዛባቸው ጎዳናዎች ወይም በገበያ ስፍራዎች እንሰብካለን። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ለመስበክ የሚጠቀሙበት ዋነኛው ዘዴ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ነው። ለምን? አንደኛ ነገር፣ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ፣ ሁሉም ሰው በየተወሰነ ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ አምላክ እንደማያዳላ በተጨባጭ ያሳያል። በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንደየሁኔታቸው የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በግል እንዲያገኙ ያስችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከቤት ወደ ቤት የምናገለግለው እኛም እምነታችን ይጠናከራል፤ ጽናትም እናዳብራለን። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” በቅንዓት መመሥከር ነው።

      16, 17. ጳውሎስ ፍርሃት እንደማይበግረው ያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችስ የእሱን ምሳሌ የሚከተሉት በምን መንገድ ነው?

      16 ጳውሎስ፣ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የሚጠብቀውን ነገር እንደማያውቅ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ነገራቸው። “ይሁንና ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ ምንም አያሳሳኝም” አላቸው። (ሥራ 20:24) ጳውሎስ በፍርሃት አልተበገረም፤ ማንኛውም ነገር፣ የጤና እክልም ሆነ የከረረ ተቃውሞ ተልእኮውን ዳር ከማድረስ እንዲያግደው አልፈቀደም።

      17 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እየጸኑ ነው። አንዳንዶች መንግሥት የጣለውን እገዳና የሚያደርስባቸውን ስደት ይጋፈጣሉ። ሌሎች ደግሞ ከከባድ የጤና እክል ወይም ከመንፈስ ጭንቀት ጋር ይታገላሉ፤ ሆኖም እጅ አይሰጡም። ክርስቲያን ወጣቶች ትምህርት ቤት ውስጥ የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ መቋቋም ያስፈልጋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥማቸው እንደ ጳውሎስ ከአቋማቸው ፍንክች አይሉም። ‘ምሥራቹን በሚገባ ለመመሥከር’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።

      ‘ለራሳችሁም ሆነ ለመንጋው ሁሉ ትኩረት ስጡ’ (የሐዋርያት ሥራ 20:25-38)

      18. ጳውሎስ ከደም ዕዳ ነፃ ለመሆን ምን አድርጓል? የኤፌሶን ሽማግሌዎችስ የእሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

      18 በመቀጠል ጳውሎስ የራሱን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እየጠቀሰ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ቀጥተኛ ምክር ሰጣቸው። በቅድሚያ ግን፣ ምናልባት እሱን በአካል የሚያዩት ለመጨረሻ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል ነገራቸው። ከዚያም “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [ነኝ] . . .፤ ምክንያቱም የአምላክን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመንገር ወደኋላ አላልኩም” አላቸው። ታዲያ የኤፌሶን ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ከደም ዕዳ ነፃ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ጳውሎስ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ እንድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ።” (ሥራ 20:26-28) ጳውሎስ “ጨካኝ ተኩላዎች” ወደ መንጋው ሰርገው እንደሚገቡና “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር” እንደሚናገሩ አስጠነቀቃቸው። ታዲያ ሽማግሌዎቹ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ጳውሎስ እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን እያንዳንዳችሁን በእንባ ከማሳሰብ ወደኋላ እንዳላልኩ አስታውሱ።”—ሥራ 20:29-31

      19. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የተፈጠረው ክህደት ምንድን ነው? ይህስ በቀጣዮቹ መቶ ዘመናት ምን እንዲከሰት አድርጓል?

      19 “ጨካኝ ተኩላዎች” በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ብቅ አሉ። በ98 ዓ.ም. ገደማ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አሁንም እንኳ ብዙ ፀረ ክርስቶሶች መጥተዋል፤ . . . በእኛ መካከል ነበሩ፤ ሆኖም ከእኛ ወገን ስላልነበሩ ትተውን ሄደዋል። ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር።” (1 ዮሐ. 2:18, 19) በሦስተኛው መቶ ዘመን፣ በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው አንዳንዶች የክህደት ጎዳና ተከትለው ነበር፤ ይህም የሕዝበ ክርስትና የቀሳውስት ክፍል እንዲፈጠር አደረገ፤ በአራተኛው መቶ ዘመን ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ፣ በክህደት ለተበከለው “ክርስትና” ይፋዊ እውቅና ሰጠ። የሃይማኖት መሪዎች አረማዊ የአምልኮ ሥርዓቶችን ከክርስትና ጋር በመቀላቀልና “የክርስትና” ገጽታ በማላበስ “ጠማማ ነገር የሚናገሩ” መሆናቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል። ይህ ክህደት ያሳደረው ተጽዕኖ ዛሬም በሕዝበ ክርስትና ትምህርቶችና ልማዶች ላይ ይንጸባረቃል።

      20, 21. ጳውሎስ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ያሳየው እንዴት ነው? ዛሬ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችስ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

      20 የጳውሎስ የሕይወት ጎዳና በኋለኞቹ ዘመናት መንጋውን መጠቀሚያ ካደረጉት ሰዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። ጳውሎስ በጉባኤው ላይ ሸክም ላለመሆን ሲል የሚያስፈልገውን ለማሟላት እየሠራ ነበር። የእምነት ባልንጀሮቹን ለመርዳት ቢለፋም ይህን ያደረገው ከእነሱ ጥቅም ለማግኘት ብሎ አይደለም። ጳውሎስ፣ የኤፌሶን ሽማግሌዎች የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዲያሳዩ አበረታቷል። “ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ]፤ ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል” ብሏቸዋል።—ሥራ 20:35

      21 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ልክ እንደ ጳውሎስ የራሳቸውን ጥቅም ይሠዋሉ። እንደ ሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት መንጎቻቸውን አይበዘብዙም፤ ከዚህ በተቃራኒ ‘ጉባኤውን እረኛ ሆነው የመጠበቅ’ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው በመገንዘብ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ኩራትና ለሥልጣን መቋመጥ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ የላቸውም፤ ምክንያቱም ‘የራስን ክብር መሻት’ የኋላ ኋላ ለውድቀት ይዳርጋል። (ምሳሌ 25:27) እብሪት ከመጣ ውርደት መከተሉ አይቀርም።—ምሳሌ 11:2

      ጳውሎስና ጓደኞቹ መርከብ ሲሳፈሩ። የኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች ጳውሎስ ላይ ጥምጥም ብለው እያለቀሱ ነው።

      “ሁሉም እጅግ አለቀሱ።”—የሐዋርያት ሥራ 20:37

      22. የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጳውሎስን እንዲወዱት ያደረጋቸው ምንድን ነው?

      22 ጳውሎስ ለወንድሞቹ ያለው ልባዊ ፍቅር በእነሱ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል። ከእነሱ ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም እቅፍ አድርገው ሳሙት።” (ሥራ 20:37, 38) እንደ ጳውሎስ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ መንጋውን የሚያገለግሉ እረኞችም በእምነት ባልንጀሮቻቸው ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው። ጳውሎስ የተወውን ግሩም ምሳሌ ተመልክተናል፤ ታዲያ ‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’ ብሎ ሲናገር እየተኩራራ ወይም እያጋነነ አልነበረም ቢባል አትስማማም?—ሥራ 20:26

      a “ጳውሎስ ከመቄዶንያ የጻፋቸው ደብዳቤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      b ጳውሎስ ለሮም ሰዎች የላከውን ደብዳቤ የጻፈው በዚህ ወቅት ቆሮንቶስን ሲጎበኝ ሊሆን ይችላል።

      c “ጳውሎስ ለእርዳታ የተዋጣውን ገንዘብ አደረሰ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      d ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ 20:5, 6 ላይ ያለውን ዘገባ ሲጽፍ በአንደኛ መደብ ተውላጠ ስም በመጠቀም ራሱንም ታሪኩ ውስጥ አካትቷል፤ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ ቀደም ሲል ፊልጵስዩስ ላይ የተወውን ሉቃስን እዚያው ዳግም ያገኘው ይመስላል፤ ከዚያም አብረው ወደ ጥሮአስ ሄደዋል።—ሥራ 16:10-17, 40

      e ከፊልጵስዩስ ወደ ጥሮአስ ያደረጉት ጉዞ አምስት ቀን ፈጅቶባቸዋል። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጉዞ በሁለት ቀን ውስጥ አድርገው ነበር፤ ምናልባትም በዚህ ወቅት ለጉዞ የማይመች ነፋስ አጋጥሟቸው ሊሆን ይችላል።—ሥራ 16:11

  • “የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
    • ምዕራፍ 22

      “የይሖዋ ፈቃድ ይሁን”

      ጳውሎስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቆርጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ

      በሐዋርያት ሥራ 21:1-17 ላይ የተመሠረተ

      1-4. ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዘው ለምንድን ነው? እዚያስ ምን ይጠብቀዋል?

      ጳውሎስና ሉቃስ ከሚሊጢን በሚነሳው መርከብ ላይ ቆመዋል፤ ስንብቱ በጣም ከባድ ነበር። ከሚወዷቸው የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር የተለያዩት በግድ ነው! አሁን ሁለቱ ሚስዮናውያን ጉዞ ሊጀምሩ ነው። ለጉዞ የሚያስፈልጓቸውን በርካታ ነገሮች ሸክፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ በይሁዳ ላሉ ችግረኛ ክርስቲያኖች የተሰባሰበውን ገንዘብ ይዘዋል፤ ይህን ስጦታ በማስረከብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቸኩለዋል።

      2 ነፋሱ የመርከቡን ሸራዎች ወጠራቸው፤ መርከቡም በጫጫታ የተሞላውን ወደብ ተሰናብቶ መንቀሳቀስ ጀመረ። እነዚህ ሁለት ሰዎችና ሰባቱ የጉዞ ጓደኞቻቸው፣ ዓይናቸው ከባሕሩ ዳርቻ አልተነቀለም፤ በሐዘን የተዋጡት ወንድሞቻቸው አሁንም እዚያው ናቸው። (ሥራ 20:4, 14, 15) መርከቡ ርቆ ወዳጆቻቸው ከዓይናቸው እስኪሰወሩ ድረስ መንገደኞቹ እጃቸውን ማውለብለባቸውን አላቆሙም።

      3 ጳውሎስ ለሦስት ዓመት ያህል በኤፌሶን ካሉ ሽማግሌዎች ጋር በቅርብ ሲሠራ ቆይቷል። አሁን ግን የመንፈስ ቅዱስን አመራር በመከተል ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ነው። በዚያ ምን እንደሚጠብቀው በተወሰነ መጠን ያውቃል። ቀደም ሲል እነዚህን ሽማግሌዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እዚያ ምን እንደሚደርስብኝ ባላውቅም መንፈስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው፤ እርግጥ ነው፣ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ በደረስኩበት ከተማ ሁሉ በተደጋጋሚ ያሳስበኛል።” (ሥራ 20:22, 23) ጳውሎስ አደጋ ቢደቀንበትም ‘መንፈስ ግድ ብሎታል’፤ ሐዋርያው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ መንፈስ የሰጠውን መመሪያ ለመከተል የውዴታ ግዴታ ተሰምቶታል። ጳውሎስ መከራ እንዲደርስበት ባይፈልግም በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ነው።

      4 አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን፣ በሕይወታችን ውስጥ ከምንም ነገር በላይ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም ቃል ገብተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን የታማኝነት ምሳሌ በመመርመር የምናገኘው ትምህርት አለ።

      ‘የቆጵሮስን ደሴት’ አልፈው ሄዱ (የሐዋርያት ሥራ 21:1-3)

      5. ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ወደ ጢሮስ የተጓዙት እንዴት ነው?

      5 ጳውሎስና ጓደኞቹ የተሳፈሩበት መርከብ በዚያው ቀን ቆስ ደረሰ፤ ‘የተጓዘው በቀጥታ’ ነው። ተስማሚ ነፋስ ስለነበረ በዚያ እየተነዱ በፍጥነት መጓዝ ችለው ነበር። (ሥራ 21:1) መርከቡ ቆስ ላይ መልሕቁን ጥሎ ያደረ ይመስላል፤ በማግስቱ ወደ ሮድስ ከዚያም ወደ ጳጥራ ጉዞውን ቀጠለ። በትንሿ እስያ ደቡባዊ ዳርቻ ላይ ወደምትገኘው ጳጥራ ሲደርሱ ወንድሞች በአንድ ትልቅ የዕቃ ማጓጓዣ መርከብ ተሳፍረው በፊንቄ ወደምትገኘው ጢሮስ አመሩ። በጉዟቸው ላይ ‘የቆጵሮስን ደሴት በስተ ግራ ትተው’ አለፉ። (ሥራ 21:3) የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሉቃስ ይህን ጉዳይ ለይቶ የጠቀሰው ለምንድን ነው?

      6. (ሀ) ጳውሎስ ቆጵሮስን ማየቱ ሊያበረታታው የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ያህል እንደባረከህና እንደረዳህ ማሰብህ ምን መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ያደርግሃል?

      6 ምናልባት ጳውሎስ ደሴቷን እያሳያቸው በዚያ ያጋጠሙትን ነገሮች ነግሯቸው ሊሆን ይችላል። ከዘጠኝ ዓመት በፊት በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ከበርናባስና ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር ወደዚህች ደሴት ሄዶ ነበር፤ በዚያ ሲያገለግሉ ኤልማስ የተባለ ጠንቋይ የስብከቱን ሥራ ለመቃወም ሞክሮ ነበር። (ሥራ 13:4-12) ጳውሎስ ደሴቲቱን ሲያይ በዚያ ያሳለፈው ትዝታ ወደ አእምሮው መጥቶ ይሆናል፤ ያን ጊዜ መለስ ብሎ ማሰቡ ሳያበረታታው አይቀርም፤ ከፊቱ ለሚጠብቀው ነገርም አጠናክሮት ሊሆን ይችላል። እኛም አምላክ ምን ያህል እንደባረከንና ፈተናዎችን በጽናት እንድንወጣ እንደረዳን መለስ ብለን ማሰባችን ይጠቅመናል። እንዲህ ማድረጋችን የዳዊት ዓይነት ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል፤ ዳዊት “የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል” በማለት ጽፏል።—መዝ. 34:19

      ‘ደቀ መዛሙርቱን ፈልገን አገኘናቸው’ (የሐዋርያት ሥራ 21:4-9)

      7. መንገደኞቹ ጢሮስ ሲደርሱ ምን አደረጉ?

      7 ጳውሎስ ከክርስቲያን ባልንጀሮቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያለውን ጠቀሜታ ያውቃል፤ ስለዚህ በእምነት ከሚዛመዱት ሰዎች ጋር ለመገናኘት ጓጉቶ ነበር። ጢሮስ በደረሱ ጊዜ ‘ደቀ መዛሙርቱን ፈልገው እንዳገኟቸው’ ሉቃስ ጽፏል። (ሥራ 21:4) እነዚህ መንገደኞች በጢሮስ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው እንዳሉ ስለሚያውቁ ፈልገው አገኟቸው፤ ያረፉትም እነሱ ጋ ሳይሆን አይቀርም። እውነትን ማወቅ ከሚያስገኛቸው ታላላቅ በረከቶች አንዱ፣ የትም ብንሄድ በደስታ የሚቀበሉን የእምነት ባልንጀሮች ማግኘታችን ነው። አምላክን የሚወዱና እውነተኛውን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎች በመላው ዓለም ወዳጆች አሏቸው።

      8. በሐዋርያት ሥራ 21:4 ላይ ያለውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል?

      8 መንገደኞቹ በጢሮስ ሰባት ቀናት አሳለፉ፤ በዚያ ስለሆነው ነገር ሉቃስ የጻፈው ዘገባ ላይ ላዩን ሲታይ ግራ ሊያጋባ ይችላል፤ ሉቃስ “[በጢሮስ ያሉት ወንድሞች] በመንፈስ ተመርተው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ደጋግመው ነገሩት” ብሏል። (ሥራ 21:4) ይሖዋ፣ ሐሳቡን ለውጦ ይሆን? ቀድሞውንም ቢሆን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የመራው እሱ ነው፤ ታዲያ አሁን እንዳይሄድ መመሪያ እየሰጠው ነው? አይደለም። መንፈስ የጠቆመው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም እንግልት እንደሚደርስበት ነው፤ ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ አላለውም። መንፈስ ቅዱስ ለጢሮስ ወንድሞች ያሳወቃቸው ነገር አለ፤ ከዚህ በመነሳት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ችግር እንደሚያጋጥመው የተገነዘቡ ይመስላል። በመሆኑም ለጳውሎስ ደህንነት ስላሳሰባቸው ወደዚያ እንዳይሄድ ጎተጎቱት። ጳውሎስን ከአደጋ ለማዳን መፈለጋቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ጳውሎስ ግን የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ስለቆረጠ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዙን ቀጠለ።—ሥራ 21:12

      9, 10. (ሀ) ጳውሎስ በጢሮስ ያሉ ወንድሞች ያሳሰባቸውን ጉዳይ ሲገልጹ ሲሰማ የትኛው ተመሳሳይ ሁኔታ ትዝ ሳይለው አልቀረም? (ለ) በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚታየው አመለካከት ምንድን ነው? ይህስ ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ የሚለየው እንዴት ነው?

      9 ጳውሎስ የወንድሞችን ልመና ሲሰማ፣ ኢየሱስ የገጠመውን ነገር ሳያስታውስ አይቀርም፤ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ፣ ብዙ መከራ እንደሚደርስበትና እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ጴጥሮስ በስሜታዊነት “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” ብሎት ነበር። ኢየሱስ ግን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” ብሎታል። (ማቴ. 16:21-23) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸምና ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለመስጠት ቆርጦ ነበር። ጳውሎስም የሚሰማው እንዲሁ ነው። ልክ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁሉ የጢሮስ ወንድሞችም ጳውሎስን የለመኑት በአሳቢነት እንደሆነ አያጠያይቅም፤ ይሁን እንጂ የአምላክን ፈቃድ አልተገነዘቡም ነበር።

      አገልግሎት ላይ ያለ አንድ ወንድም በመሰላቸት መንፈስ ሰዓቱን ሲመለከት። አብሮት የሚያገለግለው ወንድም ዞር ብሎ እያየው ነው።

      የኢየሱስ ተከታይ መሆን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይጠይቃል

      10 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በራሳቸው ላይ መጨከን ወይም ምንም ዓይነት መሥዋዕት መክፈል አይፈልጉም። በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች የሚመርጡት፣ ለራሳቸው የሚመቻቸውና ከአባላቱ ብዙ የማይጠብቅ ሃይማኖት መከተል ነው። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ከዚህ ፍጹም የተለየ አመለካከት እንዲኖረን አበረታቷል። ደቀ መዛሙርቱን “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 16:24) ኢየሱስን መከተል ትክክለኛና የጥበብ ጎዳና ነው፤ ቀላሉ ጎዳና ነው ማለት ግን አይደለም።

      11. በጢሮስ ያሉ ደቀ መዛሙርት ለጳውሎስ ያላቸውን ፍቅርና ድጋፍ የገለጹት እንዴት ነው?

      11 ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ፣ ሉቃስና አብረዋቸው ያሉት ሌሎች ወንድሞች ጉዟቸውን የሚቀጥሉበት ጊዜ ደረሰ። ከጢሮስ ሲነሱ ስለነበረው ሁኔታ የሚገልጸው ዘገባ ስሜት የሚነካ ነው። የጢሮስ ወንድሞች ለጳውሎስ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና በአገልግሎቱ እንዲጸና ለማበረታታት ያላቸውን ፍላጎት በግልጽ አሳይተዋል። በዚያ የነበሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ጳውሎስንና ጓደኞቹን እስከ ባሕሩ ዳርቻ ድረስ ሸኟቸው። ሁሉም አንድ ላይ ተንበርክከው ከጸለዩ በኋላ ተሰነባበቱ። ከዚያም ጳውሎስ፣ ሉቃስና አብረዋቸው የሚጓዙት ወንድሞች ሌላ መርከብ ተሳፍረው ወደ ጴጤሌማይስ ተጓዙ፤ እዚያም ከወንድሞች ጋር አንድ ቀን ዋሉ።—ሥራ 21:5-7

      12, 13. (ሀ) ፊልጶስ ምን የአገልግሎት ታሪክ አስመዝግቧል? (ለ) ፊልጶስ ዛሬ ላሉ ክርስቲያን አባቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

      12 በመቀጠል ጳውሎስና አብረውት የሚጓዙት ወንድሞች ወደ ቂሳርያ ማምራታቸውን ሉቃስ ዘግቧል። እዚያ ሲደርሱም “ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት [ገቡ]።”a (ሥራ 21:8) ፊልጶስን በማግኘታቸው እጅግ ተደስተው መሆን አለበት። ፊልጶስ ከ20 ዓመት ገደማ በፊት የክርስቲያን ጉባኤ ጨቅላ በነበረበት ወቅት ምግብ በማከፋፈሉ ሥራ እንዲረዳ በሐዋርያት ተሹሞ ነበር። ፊልጶስ ለብዙ ዓመታት በቅንዓት ባከናወነው የስብከት ሥራ መልካም ስም አትርፏል። ደቀ መዛሙርቱ በስደት የተነሳ ወደተለያዩ ቦታዎች ሲበታተኑ ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ በዚያ መስበክ እንደጀመረ አስታውስ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሰበከለት ከመሆኑም ሌላ አጥምቆታል። (ሥራ 6:2-6፤ 8:4-13, 26-38) በእርግጥም አገልግሎቱን በታማኝነት በመወጣት ረገድ ብዙ ታሪክ አስመዝግቧል!

      13 ፊልጶስ ለአገልግሎት ያለው ቅንዓት አልቀዘቀዘም። መኖሪያውን በቂሳርያ ያደረገው ፊልጶስ አሁንም በስብከቱ ሥራ በትጋት እየተሳተፈ ነው፤ ሉቃስ “ወንጌላዊው” ብሎ የጠራው መሆኑ ይህን ያሳያል። በተጨማሪም ትንቢት የሚናገሩ አራት ሴቶች ልጆች አፍርቷል፤ ይህም ልጆቹ የአባታቸውን ፈለግ እንደተከተሉ ያሳያል።b (ሥራ 21:9) በመሆኑም ፊልጶስ የቤተሰቡን መንፈሳዊነት ለመገንባት ብዙ ጥረት አድርጎ መሆን አለበት። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን አባቶች የፊልጶስን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው፤ በአገልግሎት ግንባር ቀደም በመሆን ልጆቻቸው የወንጌላዊነቱን ሥራ እንዲወዱት መርዳት ይችላሉ።

      14. ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን መጎብኘቱ ምን በጎ ውጤት አስገኝቶ መሆን አለበት? ዛሬስ ምን ተመሳሳይ አጋጣሚዎች አሉ?

      14 ጳውሎስ በደረሰበት ቦታ ሁሉ የእምነት ባልንጀሮቹን ለማግኘት ጥረት ያደርጋል፤ ከዚያም አብሯቸው ጊዜ ያሳልፋል። በየቦታው የሚያገኛቸው ወንድሞችም ይህን ሚስዮናዊና የጉዞ ባልደረቦቹን በእንግድነት ለመቀበል እንደሚጓጉ ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ጉብኝት ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ እንዳስቻላቸው ምንም ጥያቄ የለውም። (ሮም 1:11, 12) ዛሬም ቢሆን እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች አሉ። ቤትህ ትንሽ ቢሆንም እንኳ የወረዳ የበላይ ተመልካቹንና ሚስቱን በእንግድነት መቀበልህ ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል።—ሮም 12:13

      ቂሳርያ—የሮም ግዛት የሆነው የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማ

      የሐዋርያት ሥራ ዘገባዎች በተከናወኑበት ወቅት፣ ቂሳርያ በሮም የሚተዳደረው የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማ ነበረች፤ የአገረ ገዢው መቀመጫና የሠራዊቱ ዋና መምሪያ የሚገኘውም እዚያ ነበር። ከተማዋን የገነባት ታላቁ ሄሮድስ ሲሆን ለአውግስጦስ ቄሳር መታሰቢያ እንድትሆን በእሱ ስም ሰየማት። ቂሳርያ በዘመኑ የነበሩ አረማውያን የግሪክ ከተሞች ያሏቸው ነገሮች ሁሉ ነበሯት፤ ለቄሳር አምልኮ የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ፣ ቲያትር ቤት፣ የፈረስና የሠረገላ መወዳደሪያ ስታዲየም እንዲሁም አምፊቲያትር ነበራት። አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች አሕዛብ ነበሩ።

      ቂሳርያ በቅጥር የተከበበች የወደብ ከተማ ነበረች። አዲስ የተገነባው ወደብ ሰቫስቶስ (በግሪክኛ አውግስጦስ ማለት ነው) ተብሎ ተሰየመ፤ ወደቡን ከኃይለኛ ማዕበል ለመጠበቅ ግዙፍ የመከላከያ ግንብ የተሠራለት ሲሆን ይህም ለመርከቦች እንቅስቃሴ አመቺ አድርጎታል። የሄሮድስ ምኞት እሱ የገነባው ወደብ፣ በምሥራቃዊ ሜድትራንያን አካባቢ እስክንድርያን የሚያስንቅ የንግድ ማዕከል እንዲሆን ነበር። በእርግጥ ቂሳርያ፣ እስክንድርያን አልበለጠችም፤ ይሁንና ታላላቅ የንግድ መስመሮች በሚገናኙበት ስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ ስለነበረች በዓለም የታወቀች ከተማ ለመሆን በቅታለች።

      ወንጌላዊው ፊልጶስ ምሥራቹን በቂሳርያ ሰብኳል፤ ቤተሰብ መሥርቶ ልጆቹን ያሳደገውም በዚህች ከተማ ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 8:40፤ 21:8, 9) ሮማዊው መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስም የሚኖረውና ክርስትናን የተቀበለው እዚሁ ነበር።—ሥራ 10:1

      ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቂሳርያ በተለያዩ አጋጣሚዎች መጥቷል። ክርስትናን ከተቀበለ ብዙም ሳይቆይ ጠላቶቹ ሊገድሉት ሲያሴሩ ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም 90 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ቂሳርያ በፍጥነት ወሰዱት፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ጠርሴስ ላኩት። ጳውሎስ ሁለተኛና ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን አጠናቅቆ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድም በቂሳርያ ወደብ በኩል አልፏል። (ሥራ 9:28-30፤ 18:21, 22፤ 21:7, 8) በተጨማሪም ቂሳርያ ባለው የሄሮድስ ቤተ መንግሥት ለሁለት ዓመት ታስሯል። በዚህ ወቅት ከፊሊክስ፣ ከፊስጦስና ከአግሪጳ ጋር ተነጋግሯል፤ በመጨረሻም በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ሮም የተጓዘው ከዚሁ ቦታ ተነስቶ ነው።—ሥራ 23:33-35፤ 24:27 እስከ 25:4፤ 27:1

      ሴቶች፣ ክርስቲያን አገልጋዮች መሆን ይችላሉ?

      በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሴቶች ሚና ምን ነበር? ሴቶች፣ አገልጋዮች መሆን ይችላሉ?

      ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ምሥራቹን እንዲሰብኩና ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑ የሰጠው ይህ ተልእኮ፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች ይኸውም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ወንዶችንና ሴቶችን የሚመለከት ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ፍጻሜውን እንዳገኘ የተናገረው የኢዩኤል 2:28, 29 ትንቢት ይህን ያሳያል። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘በመጨረሻው ቀን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ።’” (ሥራ 2:17, 18) ቀደም ሲል እንዳየነው ወንጌላዊው ፊልጶስ ትንቢት የሚናገሩ አራት ሴቶች ልጆች ነበሩት።—ሥራ 21:8, 9

      በጉባኤ ውስጥ ከማስተማር ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው ይለያል፤ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው መሾም ያለባቸው ወንዶች ብቻ እንደሆኑ የአምላክ ቃል ይናገራል። (1 ጢሞ. 3:1-13፤ ቲቶ 1:5-9) እንዲያውም ጳውሎስ “ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም” በማለት ተናግሯል።—1 ጢሞ. 2:12

      “ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ” (የሐዋርያት ሥራ 21:10-14)

      15, 16. አጋቦስ ያመጣው መልእክት ምንድን ነው? ወንድሞች መልእክቱን ሲሰሙ ምን ተሰማቸው?

      15 ጳውሎስ ፊልጶስ ቤት እያለ፣ አጋቦስ የሚባል ሌላ የተከበረ እንግዳ መጣ። በፊልጶስ ቤት የተሰበሰቡት ሰዎች አጋቦስ ነቢይ መሆኑን ያውቃሉ፤ ደግሞም በቀላውዴዎስ ዘመን ታላቅ ረሃብ እንደሚከሰት ተንብዮ ነበር። (ሥራ 11:27, 28) ሰዎቹ አጋቦስ የመጣበት ምክንያት ጥያቄ ፈጥሮባቸው ይሆናል፤ ‘ምን መልእክት ይዞ ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ሁሉም በትኩረት እየተመለከቱት ሳለ የጳውሎስን ቀበቶ ወሰደ፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቀበቶ ገንዘብና ሌሎች ነገሮች ለመያዝ የሚያገለግል ወገብ ላይ የሚታሰር ረጅም መቀነት ነው። አጋቦስ በቀበቶው የራሱን እግሮችና እጆች አሰረ። ከዚያም ይህን አስደንጋጭ መልእክት ተናገረ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን ቀበቶ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’”—ሥራ 21:11

      16 ትንቢቱ፣ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ የማይቀር መሆኑን ያረጋግጣል። በተጨማሪም በዚያ የሚገኙት አይሁዳውያን ‘ለአሕዛብ አሳልፈው’ እንደሚሰጡት ይጠቁማል። ይህ ትንቢት በዚያ የነበሩትን ሁሉ ረበሻቸው። ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘እያለቀሳችሁ ልቤን ለምን ታባባላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ’ ሲል መለሰ።”—ሥራ 21:12, 13

      17, 18. ጳውሎስ ከአቋሙ ፍንክች እንደማይል ያሳየው እንዴት ነው? የወንድሞችስ ምላሽ ምን ነበር?

      17 እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሉቃስን ጨምሮ ወንድሞች፣ ጳውሎስ ጉዞውን እንዳይቀጥል እየለመኑት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ያለቅሳሉ። ጳውሎስ፣ የወንድሞቹን ፍቅርና ስስት ሲያይ “ልቤን ለምን ታባባላችሁ?” አላቸው፤ አንዳንድ ትርጉሞች “ልቤን እየሰበራችሁት ነው” በማለት አስቀምጠውታል። ያም ቢሆን ጳውሎስ ከአቋሙ ፍንክች አላለም፤ በጢሮስም ሆነ እዚህ ያገኛቸው ወንድሞች ለቅሶና ልመና ልቡን እንዲከፍለው አልፈቀደም። ይልቁንም ጉዞውን መቀጠል ያለበት ለምን እንደሆነ አስረዳቸው። ድፍረቱና ቆራጥነቱ እጅግ ይደንቃል! ከእሱ በፊት ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ ጳውሎስም ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቆርጦ ተነስቷል። (ዕብ 12:2) ጳውሎስ ሰማዕት የመሆን ፍላጎት የለውም፤ ሆኖም ይህ የማይቀር ከሆነ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ ሆኖ መሞቱን እንደ ክብር ይቆጥረዋል።

      18 የወንድሞች ምላሽ ምን ነበር? በአጭሩ፣ ሐሳቡን አክብረውለታል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እሱን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ ‘እንግዲህ የይሖዋ ፈቃድ ይሁን’ ብለን ዝም አልን።” (ሥራ 21:14) ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለማሳመን የጣሩት ወንድሞች ሐሳባቸውን እንዲቀበል አላስገደዱትም። የጳውሎስን ሐሳብ ሰምተው እሱ ባለው ተስማሙ፤ ነገሩ ቢከብዳቸውም የይሖዋን ፈቃድ መቀበል እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። ጳውሎስ የጀመረው ጎዳና የኋላ ኋላ ለሞት ሊዳርገው ይችላል። ወዳጆቹ ሁኔታውን ለመቀበል የሚያቀሉለት ይህን እንዳያደርግ ለማግባባት ጥረት ማድረጋቸውን ካቆሙ ነው።

      19. ጳውሎስ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

      19 ጳውሎስ ካጋጠመው ሁኔታ የምናገኘው ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ አምላክን ለማገልገል ሲሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ክርስቲያኖች የያዙትን ጎዳና እንዲተዉ ለማግባባት ፈጽሞ መሞከር የለብንም። የሞትና የሕይወት ጉዳይ በሆኑ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮችም ይህን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ ብዙ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን ለማገልገል ሩቅ ወደሆነ አካባቢ ሲሄዱ ሁኔታው እንደሚከብዳቸው የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን እነሱን ተስፋ ላለማስቆረጥ ይጠነቀቃሉ። በእንግሊዝ የምትኖረው ፊሊስ አንድ ልጇ ሚስዮናዊት ሆና ለማገልገል ወደ አፍሪካ ስትሄድ ምን እንደተሰማት አትረሳውም። እንዲህ ብላለች፦ “ስሜቴ እጅግ ተረብሾ ነበር። ከእኔ በጣም ርቃ እንደምትሄድ መቀበል ከበደኝ። በአንድ በኩል አዘንኩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኩራት ተሰማኝ። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ጸለይኩ። ሆኖም ውሳኔውን ለእሷ ተውኩት፤ ሐሳቧን ለማስቀየር አልሞከርኩም። ደግሞም እኮ ያስተማርኳት የአምላክን መንግሥት እንድታስቀድም ነው! ላለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ አገሮች አገልግላለች፤ በታማኝነት በመጽናቷም ይሖዋን በየቀኑ አመሰግነዋለሁ።” የራሳቸውን ጥቅም የሚሠዉ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማበረታታት በእርግጥም ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው!

      ፎቶግራፎች፦ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት እና ወላጆቻቸው። 1. ወላጆች ለልጆቻቸው ሲደውሉ። 2. ሚስዮናውያኑ ከተመደቡበት አገር ሆነው ወላጆቻቸውን በስልክ ሲያነጋግሩ። ወላጆችም ሆኑ ልጆች በስልክ በመገናኘታቸው ተደስተዋል።

      መሥዋዕትነት የሚከፍሉ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማበረታታት አስፈላጊ ነው

      “ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን” (የሐዋርያት ሥራ 21:15-17)

      20, 21. ጳውሎስ ከወንድሞች ጋር የመሆን ፍላጎት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው? ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መሆን የፈለገውስ ለምንድን ነው?

      20 አስፈላጊው ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ጳውሎስ ጉዞውን ቀጠለ፤ አንዳንድ የቂሳርያ ወንድሞችም አብረውት ናቸው፤ እነዚህ ታማኝ ወንድሞች በዚህ መንገድ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም ባደረጉት ጉዞ በደረሱበት ሁሉ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። በጢሮስ ደቀ መዛሙርቱን አግኝተው ከእነሱ ጋር ለሰባት ቀናት ቆይተዋል። በጴጤሌማይስ እህቶችንና ወንድሞችን ሰላም ካሉ በኋላ አብረዋቸው ውለዋል። በቂሳርያ በፊልጶስ ቤት ለበርካታ ቀናት ተቀምጠዋል። ቀጥሎ ደግሞ በቂሳርያ ያሉ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ጳውሎስንና ጓደኞቹን እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ሸኟቸው፤ እዚያ ሲደርሱም ከቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ በሆነው በምናሶን ቤት አረፉ። ሉቃስ እንደዘገበው በኢየሩሳሌም “ወንድሞች በደስታ [ተቀበሏቸው]።”—ሥራ 21:17

      21 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መሆን ያስደስተው ነበር። ዛሬ ወንድሞቻችን የብርታት ምንጭ እንደሚሆኑን ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስም ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ጋር ጊዜ ሲያሳልፍ ይበረታታል። ይህ ማበረታቻ፣ ጳውሎስ ሊገድሉት የሚፈልጉ ኃይለኛ ተቃዋሚዎቹን ለመጋፈጥ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሰጠው ምንም አያጠያይቅም።

      a “ቂሳርያ—የሮም ግዛት የሆነው የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      b “ሴቶች፣ ክርስቲያን አገልጋዮች መሆን ይችላሉ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ