-
ትዕቢት ውርደትን ያስከትላልመጠበቂያ ግንብ—2000 | ነሐሴ 1
-
-
ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል
“ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 11:2
1, 2. ትዕቢት ምንድን ነው? ለውድቀት ሊዳርግ የሚችለውስ እንዴት ነው?
አንድ ምቀኛ ሌዋዊ ይሖዋ በሾማቸው ላይ ለማመፅ የተነሱ ሰዎች አስተባባሪ ሆነ። የሥልጣን ጥም ያሰከረው አንድ ልዑል የአባቱን ዙፋን ለመቀማት በተንኮል አሴረ። ትዕግሥት የሌለው አንድ ንጉሥ የአምላክ ነቢይ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ናቀ። እነዚህን ሦስት እስራኤላውያን የሚያመሳስላቸው አንድ ባሕርይ አለ። ይኸውም ትዕቢት ነው።
2 ትዕቢት እገሌ ከገሌ ሳይል ሁሉንም ሰው ለችግር ሊዳርግ የሚችል የልብ ዝንባሌ ነው። (መዝሙር 19:13) ትዕቢተኛ የሆነ ሰው አንድን ነገር የማድረግ ሥልጣን ሳይኖረው በማን አለብኝነት ይሠራል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው አካሄድ ለውድቀት ይዳርጋል። እንዲያውም፣ ትዕቢት ነገሥታትን ጥሏል፣ ግዛቶችን አፍርሷል። (ኤርምያስ 50:29, 31, 32፤ ዳንኤል 5:20) አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮችንም እንኳ ሳይቀር አጥምዶ ለጥፋት ዳርጓቸዋል።
3.ትዕቢት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል እንዴት ማወቅ እንችላለን?
3 መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ብሎ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 11:2) መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ምሳሌ እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ምሳሌዎች ይዞልናል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን መመርመራችን ገደብን አልፎ መሄድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ስለዚህ ምቀኝነት፣ የሥልጣን ጥመኝነትና ትዕግሥት ማጣት በመግቢያው ላይ የተጠቀሱትን ሰዎች በትዕቢት እርምጃ እንዲወስዱ እንዴት እንዳነሳሳቸውና ለጥፋት እንዴት እንደዳረጋቸው እንመርምር።
ቆሬ—ቅናት ያደረበት ዓመፀኛ
4. (ሀ) ቆሬ ማን ነው? በየትኛው ታሪካዊ ክንውን ውስጥ ተካፋይ ሳይሆን አይቀርም? (ለ) ቆሬ ወደኋላ ላይ ምን መጥፎ ድርጊት ፈጸመ?
4 ቆሬ ከቀዓት ወገን የሆነ ሌዋዊ ሲሆን የሙሴና የአሮን የአጎት ልጅ ነው። ለአሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግል እንደነበረ ግልጽ ነው። ቆሬ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ቀይ ባሕርን በሕይወት የመሻገር መብት ካገኙት ሰዎች መካከል አንዱ ከመሆኑም በላይ በሲና ተራራ በጥጃ አምልኮ በተካፈሉ እስራኤላውያን ላይ የይሖዋን ፍርድ ካስፈጸሙት ሰዎች መካከል አንዱ ሳይሆን አይቀርም። (ዘጸአት 32:26) ዳሩ ምን ያደርጋል በመጨረሻ የሮቤልን ልጆች ዳታንን፣ አቤሮንን እና አንን ጨምሮ 250 የእስራኤል አለቆች በሙሴና በአሮን ላይ እንዲያምፁ በማድረግ ረገድ ቀንደኛ የዓመፁ መሪ ሆነ።a “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ተናገሩ።—ዘኁልቁ 16:1-3
5, 6. (ሀ) ቆሬ በሙሴና በአሮን ላይ ያመፀው ለምንድን ነው? (ለ) ቆሬ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የተሰጠውን ቦታ አቅልሎ ተመልክቶታል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
5 ቆሬ ለዓመታት ታማኝ ሆኖ ከቆየ በኋላ ዓመፀኛ የሆነው ለምንድን ነው? ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” ስለነበር እስራኤልን በጭቆና እንዳልመራ የተረጋገጠ ነው። (ዘኁልቁ 12:3) ቆሬ በሙሴና በአሮን ላይ ባደረበት ቅናት ሥልጣናቸውን ለመቀበል ሳይፈልግ የቀረ ይመስላል፤ ይህም በማን አለብኝነትና በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ ራሳቸውን ከጉባኤው በላይ ከፍ አድርገዋል ብሎ በተሳሳተ መንገድ እንዲናገር አደረገው።—መዝሙር 106:16
6 ቆሬ ከነበሩበት ችግሮች መካከል አንደኛው በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የነበረውን ቦታ ከፍ አድርጎ ለመመልከት ሳይችል መቅረቱ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሌዋዊ የነበሩት ቀዓታውያን ካህናት ሆነው አያገልግሉ እንጂ የአምላክ ሕግ አስተማሪዎች ነበሩ። እንዲሁም የመገናኛ ድንኳኑ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚጓጓዝበት ጊዜ ዕቃዎቹንና ቁሳቁሶቹን ተሸክመው ይወስዱ ነበር። ዕቃዎቹን ተሸክመው ከሚያጓጉዙት ሰዎች ሃይማኖታዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ይጠበቅ ስለነበር ይህ ዓይነቱ ሥራ እንደ ተራ የሚታይ አልነበረም። (ኢሳይያስ 52:11) ስለዚህም ሙሴ ቆሬን የተሰጠህን የአገልግሎት ሥራ ንቀህ ነው የክህነት አገልግሎት ለመያዝ የፈለግኸው? ብሎ የጠየቀው ያህል ነበር። (ዘኁልቁ 16:9, 10) ቆሬ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ በተመደቡበት ቦታ በታማኝነት ማገልገል ልዩ ሥልጣን ወይም ደረጃ ከማግኘት የበለጠ ነገር መሆኑን ሳይገነዘብ ቀርቷል።—መዝሙር 84:10
7. (ሀ) ሙሴ የቆሬንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ጉዳይ በተመለከተ ምን አደረገ? (ለ) የቆሬ ዓመፅ መጨረሻው ጥፋት የሆነው እንዴት ነው?
7 ሙሴ በቀጣዩ ቀን ጠዋት የእሳት ጥና እና ዕጣን ይዘው በመገናኛው ድንኳን አጠገብ እንዲሰበሰቡ ቆሬንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ጋበዛቸው። ቆሬና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ካህናት ስላልሆኑ ዕጣን የማቅረብ ሥልጣን አልነበራቸውም። ጉዳዩን በጥሞና እንዲያስቡበት የሚያስችል አንድ ሙሉ ሌሊት ካገኙ በኋላም እንኳ የእሳት ጥና እና ዕጣን ይዘው ከመጡ እነዚህ ሰዎች በክህነት የማገልገል መብት እንዳላቸው ሆኖ የሚሰማቸው መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ይሆናል። በቀጣዩ ቀን ራሳቸውን ሲያቀርቡ ይሖዋ በቀጥታ ቁጣውን ገለጸ። “መሬት ተሰነጠቀ፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ” የሮቤልን ልጆች ዋጠች። ቆሬን ጨምሮ የቀሩት ከአምላክ እሳት መጥቶ በላቸው። (ዘዳግም 11:6፤ ዘኁልቁ 16:16-35፤ 26:10) ቆሬ ትዕቢተኛ መሆኑ ለከፋ ውርደት ዳርጎታል ማለትም የአምላክን ሞገስ አሳጥቶታል!
‘የቅንዓትን ዝንባሌ’ መዋጋት
8. ‘የቅንዓት ዝንባሌ’ በክርስቲያኖች መካከልም ሊንጸባረቅ የሚችለው እንዴት ነው?
8 ስለ ቆሬ የሚናገረው ዘገባ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ነው። ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች ውስጥ ‘የቅንዓት ዝንባሌ’ የሚገኝ በመሆኑ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንኳ ሳይቀር ይህ ባሕርይ ሊንጸባረቅ ይችላል። (ያዕቆብ 4:5) ለምሳሌ ያህል ሥልጣን ፈላጊዎች ልንሆን እንችላለን። እኛ የተመኘነውን መብት ሌሎች ሲያገኙት ስናይ እንደ ቆሬ የቅናት ስሜት ሊያድርብን ይችላል። ወይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው እንደ ዲዮጥራጢስ ልንሆን እንችላለን። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደምንችለው የሐዋርያነትን ሥልጣን ይመኝ ስለነበር ይህን ቦታ አብዝቶ ይነቅፍ ነበር። እንዲያውም ዮሐንስ “ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ” በማለት ጽፏል።—3 ዮሐንስ 9
9. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ኃላፊነቶችን በተመለከተ የትኛውን አመለካከት ማስወገድ ይኖርብናል? (ለ) በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ስላለን ቦታ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?
9 እርግጥ ነው፣ አንድ ክርስቲያን ለጉባኤ ኃላፊነቶች ለመብቃት ቢጣጣር ምንም ስህተት የለበትም። እንዲያውም ጳውሎስ እንዲህ ማድረግን አበረታቷል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁን እንጂ የአገልግሎት መብቶችን ማግኘት ከሌሎች በላይ የሚያደርግ ልዩ ሥልጣን እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይገባንም። ኢየሱስ “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” በማለት የተናገረውን አስታውስ። (ማቴዎስ 20:26, 27) በአምላክ ፊት ያለን ዋጋ የሚለካው በድርጅቱ ውስጥ ባለን “ቦታ” እንደሆነ አድርገን በማሰብ ከፍተኛ ኃላፊነት ባላቸው ሰዎች ላይ መቅናት ተገቢ አይደለም። ኢየሱስ “እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:8) አዎን፣ አስፋፊም ሆኑ አቅኚዎች፣ በቅርቡ የተጠመቁም ሆኑ ለረዥም ጊዜያት ጽኑ አቋማቸውን የጠበቁ፣ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የሚያገለግሉ ሁሉ በእርሱ ዝግጅት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ አላቸው። (ሉቃስ 10:27፤ 12:6, 7፤ ገላትያ 3:28፤ ዕብራውያን 6:10) “እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ከሚጣጣሩ በሚልዮን ከሚቆጠሩ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት በእርግጥም በረከት ነው።—1 ጴጥሮስ 5:5
አቤሴሎም—የሥልጣን ጥም የተጠናወተው አድርባይ ሰው
10. አቤሴሎም ማን ነበር? ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጡ ሰዎችን ልብ ለመማረክ የሞከረውስ እንዴት ነበር?
10 የንጉሥ ዳዊት ሦስተኛ ልጅ የነበረው አቤሴሎም ከተከተለው የሕይወት ጎዳና ለሥልጣን መቋመጥን በተመለከተ ተግባራዊ የሆነ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ይህ መሠሪና አድርባይ የሆነ ሰው ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጡት ሰዎችን ልብ ለመማረክ ሙከራ አድርጓል። በመጀመሪያ ዳዊት ለእነርሱ ችግር ምንም ደንታ እንደሌለው በረቀቀ መንገድ ተናገረ። ከዚያም ዙሪያ ጥምጥም መናገሩን አቆመና በቀጥታ ድብቅ ምኞቱን ይፋ አወጣ። አቤሴሎም “ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?” በማለት ተናገረ። የአቤሴሎም ተንኮል በዚህ ብቻ አላበቃም። “ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር። እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር።” ውጤቱስ ምን ሆነ “አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።”—2 ሳሙኤል 15:1-6
11. አቤሴሎም የዳዊትን ዙፋን ለመቀማት ሙከራ ያደረገው እንዴት ነው?
11 አቤሴሎም የአባቱን ዙፋን ለመቀማት ቆርጦ ተነስቶ ነበር። ከአምስት ዓመት በፊት የአቤሴሎምን እህት ትዕማርን በመድፈሩ ምክንያት የተበቀለው በማስመሰል አምኖን የተባለውን የዳዊትን የመጀመሪያ ልጅ ገደለ። (2 ሳሙኤል 13:28, 29) ይሁን እንጂ የአምኖን መገደል የሚቀናቀነው እንዳይኖር እንደሚያደርግለት ስለሚያውቅ በዚያን ጊዜም ቢሆን ቀልቡ ያረፈው በዙፋኑ ላይ ሊሆን ይችላል።b ያም ሆነ ይህ አቤሴሎም ምቹ ነው ብሎ ያሰበው ጊዜ ሲደርስ ሌላ እርምጃ ወሰደ። ንግሥናው በአገሩ ሁሉ እንዲታወጅ አደረገ።—2 ሳሙኤል 15:10
12. አቤሴሎም ትዕቢተኛ መሆኑ ለውርደት የዳረገው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
12 አቤሴሎም ጊዜያዊ ስኬት በማግኘቱ “ሴራውም ጽኑ ሆነ ከአቤሴሎምም ጋር ያለው ሕዝብ እየበዛ ሄደ።” በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ሲል ለመሸሽ ተገደደ። (2 ሳሙኤል 15:12-17) ብዙም ሳይቆይ ኢዮአብ አቤሴሎምን ገድሎና ጉድጓድ ውስጥ ጥሎ ድንጋይ በከመረበት ጊዜ የሕይወት ታሪኩ በዚያው አከተመ። እስቲ አስበው ንጉሥ ለመሆን ይቋምጥ የነበረው ይህ ሰው በሞተ ጊዜ በሥርዓት እንኳ አልተቀበረም!c በእርግጥም ትዕቢት በአቤሴሎም ላይ ውርደት አስከትሎበታል።—2 ሳሙኤል 18:9-17
በራስ ወዳድነት ላይ ከተመሠረተ የሥልጣን ምኞት ራቅ
13. የሥልጣን ምኞት በአንድ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ሥር ሊሰድ የሚችለው እንዴት ነው?
13 አቤሴሎም ለሥልጣን ከነበረው ምኞትና በኋላም ከደረሰበት ውድቀት እኛም ትምህርት እናገኛለን። ስለ ሌላው ምንም ደንታ በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሰዎች አንድ ዓይነት ስሜት ለማሳደር ምናልባትም አንድ ዓይነት ጥቅም ወይም ሹመት ለማግኘትና ተወዳጅነት ለማትረፍ ሲሉ አለቆቻቸውን መሸንገላቸው የተለመደ ነገር ነው። በተመሳሳይም የበታቾቻቸውን ትኩረትና ድጋፍ ለማግኘት ሲሉም በጉራ ሊናገሩ ይችላሉ። እኛም ካልተጠነቀቅን እንዲህ ያለው የሥልጣን ምኞት በልባችን ውስጥ ሥር ሊሰድ ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ የመሰለ ነገር በአንዳንዶች ላይ ተከስቶ ስለነበር ሐዋርያት ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ስለመራቅ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈልጓቸው ነበር።—ገላትያ 4:17፤ 3 ዮሐንስ 9, 10
14. በሥልጣን ጥም ራስን ከፍ ከፍ ከማድረግ መንፈስ መራቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ ‘የራሳቸውን ክብር በመፈለግ’ ከሌሎች ልቀው ለመታየት የሚሞክሩ ሰዎች በድርጅቱ ውስጥ እንዲኖሩ አይፈቅድም። (ምሳሌ 25:27) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፣ ታላቅ ነገርን የምትናገረውንም ምላስ” በማለት ያስጠነቅቃል። (መዝሙር 12:3) አቤሴሎም ልዝብ ከንፈሮች ነበሩት። የቋመጠለትን ሥልጣን ለማግኘት ሲል ትኩረት እንዲሰጡት የሚፈልጋቸውን ሰዎች ይሸነግላቸው ነበር። ከዚህ በተቃራኒ “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር” የሚለውን የጳውሎስ ምክር በሚከተል የወንድማማች ማኅበር መካከል መገኘታችን ምንኛ በረከት ነው!—ፊልጵስዩስ 2:3
ሳኦል—ትዕግሥት የለሹ ንጉሥ
15. በአንድ ወቅት ሳኦል ልኩን ያውቅ እንደነበረ ያሳየው እንዴት ነው?
15 ከጊዜ በኋላ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ሳኦል በአንድ ወቅት ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል ወጣት በነበረበት ጊዜ የሆነውን ተመልከት። የአምላክ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል ስለ እርሱ መልካም ወሬ በተናገረ ጊዜ ሳኦል “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ?” በማለት በትሕትና መልሷል።—1 ሳሙኤል 9:21
16. ሳኦል ትዕግሥት እንደሌለው ያሳየው እንዴት ነው?
16 ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሳኦል የነበረው ልክን የማወቅ ባሕርይ እልም ብሎ ጠፋ። ከፍልስጤማውያን ጋር ውጊያ ገጥሞ በነበረበት ጊዜ ሳሙኤል እስኪመጣና መሥዋዕት አቅርቦ አምላክን እስኪለምን ድረስ መጠበቅ ስለነበረበት ወደ ጌልገላ ሄደ። ሳሙኤል በተባለው ሰዓት ሳይመጣ በዘገየ ጊዜ ሳኦል በትዕቢት ተነሳስቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ራሱ አቀረበ። መሥዋዕቱን አቅርቦ እንደጨረሰ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም “ያደረግኸው ምንድር ነው?” በማለት ጠየቀው። ሳኦልም “ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፣ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ . . . አየሁ፤ . . . ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ።”—1 ሳሙኤል 13:8-12
17. (ሀ) እንዲሁ ከላይ ሲታይ ሳኦል የፈጸመው ድርጊት ትክክል ሊመስል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ትዕግሥት የማጣት እርምጃ የወሰደውን ሳኦልን ያወገዘው ለምንድን ነው?
17 እንዲሁ ከላይ ሲታይ ሳኦል ያደረገው ነገር ትክክል ሊመስል ይችላል። ደግሞም የአምላክ ሕዝቦች በነበሩበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የተነሳ “ተጨንቀው” ይንቀጠቀጡ ነበር። (1 ሳሙኤል 13:6, 7) እርግጥ ነው፣ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ በራስ ተነሳሽነት አንድ ነገር ማድረጉ ምንም ስህተት የለበትም።d ሆኖም ይሖዋ ልብን ማንበብና የተነሳሳንበትን ውስጣዊ ግፊት ማወቅ እንደሚችል አትዘንጋ። (1 ሳሙኤል 16:7) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስም ሳኦልን በሚመለከት አንድ ያየው ነገር መኖር አለበት። ለምሳሌ ያህል ሳኦል ትዕግሥት ያጣው በውስጡ ባደረበት ትዕቢት እንደሆነ ይሖዋ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ምናልባት የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሳኦል ዕድሜው ከመግፋቱ የተነሳ እያዘገመ እንደሚመጣ አድርጎ የተመለከተውን ነቢይ መጠበቁ አበሳጭቶት ሊሆን ይችላል! ያም ሆነ ይህ የሳሙኤል መዘግየት ነገሮችን በራሱ መንገድ ማከናወንና የተሰጠውን ጥብቅ መመሪያም ችላ ብሎ ማለፍ እንደሚያስችለው ሆኖ ተሰምቶት ይሆናል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሳሙኤል ጎሽ አበጀህ አላለውም። ከዚያ ይልቅ “መንግሥትህ አይጸናም . . . እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና” በማለት በቁጣ ተናግሮታል። (1 ሳሙኤል 13:13, 14) አሁንም ቢሆን ትዕቢት ውርደትን አስከትሏል።
ትዕግሥት ከማጣት ተጠበቁ
18, 19. (ሀ) ትዕግሥት ማጣት በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችን ወደ ትዕቢት ሊመራቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ። (ለ) የክርስቲያን ጉባኤን እንቅስቃሴ በተመለከተ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?
18 ሳኦል በትዕቢት ተነሳስቶ ስለፈጸመው ነገር የሚናገረው ታሪክ ለእኛ ጥቅም ሲባል በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቧል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) በወንድሞቻችን አለፍጽምና በቀላሉ ልንበሳጭ እንችላለን። ማንኛውንም ነገር እኔው ራሴ ካልሠራሁት በስተቀር በትክክል አይሠራም ብለን የምናስብ ከሆነ እንደ ሳኦል ትዕግሥት የለሽ ልንሆን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም አንዳንድ ነገሮችን በማደራጀት ረገድ የላቀ ችሎታ አለው እንበል። ሰዓት አክባሪ፣ ከጉባኤ የአሠራር ሥርዓቶች ጋር እኩል የሚራመድና የመናገርና የማስተማር ተሰጥዖ ያለው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ወንድም ሌሎች የእርሱን ጥብቅ የአቋም ደረጃዎች እንደማያሟሉና እርሱ የሚፈልገውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆኑ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ታዲያ ይህ ትዕግሥት የለሽ እንዲሆን ሰበብ ሊሆነው ይችላልን? ምናልባትም እርሱ ባይኖር ኖሮ ምንም ነገር ሊሠራ እንደማይችልና ጭራሹኑ ጉባኤው ሊዳከም እንደሚችል በተዘዋዋሪ መንገድ በመናገር ወንድሞቹን መንቀፍ ይኖርበታልን? እንዲህ ቢያደርግ ትዕቢት ይሆንበታል!
19 ለመሆኑ የክርስቲያን ጉባኤን አንድ አድርጎ የሚያቆመው ምንድን ነው? የአስተዳደር ብቃት? ቅልጥፍና? የጠለቀ እውቀት? እርግጥ ነው፣ ጉባኤው ያለ ችግር መንቀሳቀስ ይችል ዘንድ እነዚህ ነገሮች የሚያበረክቱት የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንዳላቸው እሙን ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:40፤ ፊልጵስዩስ 3:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:18) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተከታዮቹ በዋነኝነት ተለይተው የሚታወቁት በመካከላቸው ባለው ፍቅር እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) ከዚህም የተነሳ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ሥርዓታማ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ቢያውቁም ጉባኤው ምንም የማያፈናፍን አመራር የሚያስፈልገው የንግድ ተቋም እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ከዚያ ይልቅ ጉባኤው በርኅራኄ መያዝ የሚፈልግ መንጋ ያለበት እንደሆነ ያውቃሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 40:11) በትዕቢት እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ማለት ብዙውን ጊዜ ወደ ብጥብጥ ይመራል። በተቃራኒው ደግሞ አምላካዊ ሥርዓትን መከተል ሰላምን ያሰፍናል።—1 ቆሮንቶስ 14:33፤ ገላትያ 6:16
20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን ነገሮች ይብራራሉ?
20 ስለ ቆሬ፣ አቤሴሎም እና ሳኦል የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በምሳሌ 11:2 ላይ እንደሰፈረው ትዕቢት ለውርደት እንደሚዳርግ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ ያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ጨምሮ ይናገራል። ልክን ማወቅ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለዚህ ባሕርይ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቁ ምን ምሳሌዎች ይገኛሉ? እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ልክን የማወቅ ባሕርይ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ጥናት ላይ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሮቤል የያዕቆብ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ የእርሱ ዘሮች ከቆሬ ጋር አብረው ያመፁት ሌዋዊው ሙሴ በእነርሱ ላይ ያለውን የማስተዳደር ሥልጣን ለመቀበል ፈቃደኞች ስላልነበሩ ሊሆን ይችላል።
b የዳዊት ሁለተኛ ልጅ የነበረው ዶሎሕያ ከተወለደ በኋላ ዳግመኛ በስም አልተጠቀሰም። ምናልባት አቤሴሎም ከማመፁ በፊት ሞቶ ሊሆን ይችላል።
c በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው አስከሬኑ የቀብር ሥርዓት ማግኘቱ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነበር። በዚህም የተነሳ አንድ ሰው የቀብር ሥርዓት ሳይደረግለት መቅረቱ እንደ ትልቅ ውርደት የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ የአምላክን ሞገስ ማጣቱን ያመለክት ነበር።—ኤርምያስ 25:32, 33
d ለምሳሌ ያህል ፊንሐስ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው መቅሰፍት እንዲገታ ለማድረግ ፈጣን እርምጃ ወስዷል። እንዲሁም ዳዊት ከእርሱ ጋር ያሉ እርቧቸው የነበሩ ሰዎች ‘በእግዚአብሔር ቤት’ የሚገኘውን የተቀደሰ እንጀራ አብረውት እንዲበሉ ጋብዟቸዋል። አምላክ የሁለቱንም ድርጊት እንደ ትዕቢት ቆጥሮ አላወገዘውም።—ማቴዎስ 12:2-4፤ ዘኁልቁ 25:7-9፤ 1 ሳሙኤል 21:1-6
-
-
“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”መጠበቂያ ግንብ—2000 | ነሐሴ 1
-
-
“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”
“እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? . . . ከአምላክህም ጋር በትሕትና [“ልክህን አውቀህ፣” NW ] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8
1, 2. ልክን ማወቅ ምንድን ነው? ከትዕቢት የሚለየውስ እንዴት ነው?
አንድ የታወቀ ሐዋርያ የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሱ መሳብ አልፈለገም። አንድ ደፋር እስራኤላዊ መስፍን በአባቱ ቤት የሁሉ ታናሽ እንደሆነ ተናገረ። እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን እንደሌለው ገለጸ። ሦስቱም ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይተዋል።
2 ልክን የማወቅ ባሕርይ የትዕቢት ተቃራኒ ነው። ልኩን የሚያውቅ ሰው ለችሎታዎቹና ለማንነቱ ያለው አመለካከት ሚዛኑን የጠበቀ ነው። እንዲሁም ከዕብሪትና ከግብዝነት የራቀ ነው። ልኩን የሚያውቅ ሰው ኩራተኛ፣ ጉረኛ ወይም የሥልጣን ጥመኛ ከመሆን ይልቅ አቅሙ ውስን መሆኑን በሚገባ ያውቃል። ከዚህም የተነሳ ለሌሎች ሰዎች ስሜትና አመለካከት ተገቢውን አክብሮትና አሳቢነት ያሳያል።
3. ጥበብ ‘ልካቸውን በሚያውቁ ሰዎች’ ዘንድ የሚገኘው እንዴት ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ብሎ መናገሩ አለምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 11:2) ልኩን የሚያውቅ ሰው አምላክ የሚቀበለውን ጎዳና ስለሚከተል ጥበበኛ ነው፤ እንዲሁም ውርደት ከሚያስከትለው ከትዕቢት መንፈስ ይርቃል። (ምሳሌ 8:13፤ 1 ጴጥሮስ 5:5) ልክን የማወቅ ባሕርይ ጥበብ መሆኑ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች በተከተሉት የሕይወት ጎዳና ተረጋግጧል። እስቲ ለአብነት ያክል በመግቢያው አንቀጽ ላይ የተጠቀሱትን ሦስት ሰዎች ምሳሌ እንመርምር።
‘ሎሌና’ ‘መጋቢ’ የነበረው ጳውሎስ
4. ጳውሎስ ምን ልዩ መብቶች ነበሩት?
4 ጳውሎስ በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ጉልህ ቦታ ነበረው፤ ደግሞም እንደዚያ መሆኑ አያስገርምም። በአገልግሎት በተካፈለባቸው ጊዜያት በባሕር፣ በየብስ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል፤ በርካታ ጉባኤዎችንም አቋቁሟል። በተጨማሪም ራእይ እንዲያይና በልሳን እንዲናገር በማድረግ ይሖዋ ባርኮታል። (1 ቆሮንቶስ 14:18፤ 2 ቆሮንቶስ 12:1-5) እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑትን 14 ደብዳቤዎች እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ጳውሎስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ደክሟል ተብሎ ሊነገርለት ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:10
5. ጳውሎስ ስለ ራሱ የነበረው አመለካከት ልክን የማወቅ ባሕርይ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
5 ጳውሎስ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ስለነበር አንዳንዶች የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት እንዲያውም ሥልጣኑን ለማሳወቅ የሚፈልግ ሰው እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ጳውሎስ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ አልነበረውም። “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” በማለት ራሱን ከመጥራቱም በላይ “የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” ነኝ በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:9) ጳውሎስ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ እንደመሆኑ ልዩ የአገልግሎት መብት ማግኘት ይቅርና ወደ አምላክ መቅረብ የቻለው ይገባኛል በማይለው ደግነቱ እንደሆነ ፈጽሞ አልረሳም። (ዮሐንስ 6:44፤ ኤፌሶን 2:8) በመሆኑም ጳውሎስ በአገልግሎቱ ብዙ ማከናወን መቻሉ ከሌሎች የላቀ ሆኖ እንዲሰማው አላደረገውም።—1 ቆሮንቶስ 9:16
6. ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር በነበረው ግንኙነት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር የነበረው ግንኙነት ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። አንዳንዶች አጵሎስን፣ ኬፋንና ራሱን ጳውሎስን ጨምሮ ዋነኛ ብለው ላሰቧቸው አንዳንድ የበላይ ተመልካቾች ከፍተኛ ግምት ሰጥተው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:11-15) ሆኖም ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን በማግባባት የእነርሱን ውዳሴም ሆነ አድናቆት ለማግኘት አልሞከረም። በሚጎበኛቸው ጊዜ “በቃልና በጥበብ ብልጫ” ራሱን አላቀረበም። ከዚያ ይልቅ ጳውሎስ ስለ ራሱም ሆነ ስለ ባልንጀሮቹ ሲናገር “እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን” በማለት ተናግሯል።a—1 ቆሮንቶስ 2:1-5፤ 4:1
7. ጳውሎስ ምክር በሚሰጥበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ልክን የማወቅ ባሕርይ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?
7 ጳውሎስ ሌላው ቀርቶ ጠንካራ ምክርና መመሪያ እንዲሰጥ በተገደደበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይቷል። ክርስቲያን ባልንጀሮቹን በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ሳይሆን “በእግዚአብሔር ርኅራኄ” እና “ስለ ፍቅር” ለምኗቸዋል። (ሮሜ 12:1, 2፤ ፊልሞና 8, 9) ጳውሎስ እንደዚህ ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘በእምነታቸው ላይ እንደሚገዛ’ ሳይሆን የእነርሱ ‘የሥራ ባልደረባ’ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ይቆጥር ስለነበር ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:24) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤዎች ዘንድ እንዲወደድ ያደረገው ይኸው ልክን የማወቅ ባሕርይ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።—ሥራ 20:36-38
ላገኘናቸው መብቶች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
8, 9. (ሀ) ስለ ራሳችን ባለን አመለካከት ረገድ ልክን የማወቅ ባሕርይ ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ልክን የማወቅ ባሕርይ ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ ዛሬ ለምንኖረው ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ምንም ዓይነት መብት ይኑረን ከሌሎች እንደምንበልጥ ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ጳውሎስ “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 6:3) ለምን? ምክንያቱም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:23፤ 5:12) አዎን፣ ሁላችንም ከአዳም ኃጢአትንና ሞትን እንደወረስን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። ልዩ መብቶችን ማግኘት ከወደቅንበት የኃጢአተኝነት ሁኔታ ቅንጣት ታክል እንኳ ከፍ አያደርገንም። (መክብብ 9:2) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም አንዳንድ መብቶችን ማግኘት ይቅርና ወደ አምላክ መቅረብ የቻልነው ይገባናል በማንለው ደግነቱ ነው።—ሮሜ 3:12, 24
9 ልኩን የሚያውቅ ሰው ይህንን ከተገነዘበ ባገኘው መብት አይመጻደቅም እንዲሁም ባከናወነው ነገር አይኩራራም። (1 ቆሮንቶስ 4:7) ምክር ወይም መመሪያ በሚሰጥበት ጊዜ እንደ ጌታ ሳይሆን እንደ ሥራ ባልደረባ ሆኖ ይሰጣል። በአንድ ዓይነት ሥራ ከሌሎች የተሻለ ብቃት ያለው አንድ ሰው የእምነት ባልደረቦቹን በማግባባት የእነርሱን ውዳሴም ሆነ አድናቆት ለማግኘት ቢጥር በእርግጥም ስህተት ይሆንበታል። (ምሳሌ 25:27፤ ማቴዎስ 6:2-4) ውዳሴ ዋጋ የሚኖረው ከሌላ ወገን ሲመጣ ነው። ያም ደግሞ እኛ ጎትጉተን መሆን የለበትም። ሌሎች ቢያወድሱን እንኳ ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን እንድናስብ ሊያደርገን አይገባም።—ምሳሌ 27:2፤ ሮሜ 12:3
10. ብዙም ጉልህ ቦታ የሌላቸው መስለው የሚታዩ ሰዎች “በእምነት ባለ ጠጎች” ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አብራራ።
10 ልክን የማወቅ ባሕርይ አንድ ዓይነት ኃላፊነት በሚሰጠን ጊዜ የእኛ ጥረትና ችሎታ ባይኖር ኖሮ ጉባኤው በሁለት እግሩ ሊቆም እንደማይችል ሌሎች እንዲሰማቸው በማድረግ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ወደ ራሳችን ከመሳብ እንድንቆጠብ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል ጥሩ የማስተማር ችሎታ ይኖረን ይሆናል። (ኤፌሶን 4:11, 12) ይሁን እንጂ ልክን የማወቅ ባሕርይ ካለን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከምንማራቸው ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ያወቅነው ከመድረክ በሚቀርብ ትምህርት እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ለምሳሌ ያህል ልጆቻቸውን ይዘው አዘውትረው ወደ መንግሥት አዳራሽ የሚመጡ ነጠላ ወላጆች ወይም ምንም ዋጋ እንደሌለው ቢሰማውም እንኳ በታማኝነት ስብሰባ የሚመጣ የተጨነቀ ነፍስ ወይም በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ቦታ የሚደርሱበትን መጥፎ ተጽዕኖዎች ተቋቁሞ በመንፈሳዊ እድገት እያደረገ የሚሄድ ወጣት ስትመለከት አትበረታታም? (መዝሙር 84:10) እነዚህ ሰዎች ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ምን ዓይነት የአቋም ጽናትን የሚጠይቁ ፈተናዎችን እየተቋቋሙ እንዳሉ በአብዛኛው ሌሎች አያውቁላቸውም። ሆኖም በኃላፊነት ቦታ ላይ ካሉት ያላነሰ “በእምነት ባለ ጠጎች” ሊሆኑ ይችላሉ። (ያዕቆብ 2:5) ደግሞም መጨረሻ ላይ የይሖዋን ሞገስ የሚያስገኘው ታማኝነት ነው።—ማቴዎስ 10:22፤ 1 ቆሮንቶስ 4:2
በአባቱ ቤት “ታናሽ” የነበረው ጌዴዎን
11. ጌዴዎን ከአምላክ መልአክ ጋር ባደረገው ውይይት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው?
11 ከምናሴ ነገድ የተነሳውና ኃያል ሰው የነበረው ወጣቱ ጌዴዎን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ሁከት በነገሠበት ዘመን ይኖር ነበር። የአምላክ ሕዝቦች ለሰባት ዓመታት በምድያማውያን ጭቆና ሥር ሲማቅቁ ኖረዋል። ይሁን እንጂ አሁን ይሖዋ ሕዝቡን የሚያድንበት ጊዜ ደረሰ። ስለሆነም አንድ መልአክ ለጌዴዎን ተገለጠና “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፣ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።” ጌዴዎን ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለነበር ይህን ያልጠበቀውን ሙገሳ ሲሰማ ኩራት አልተሰማውም። ከዚያ ይልቅ በአክብሮት መልአኩን “ጌታዬ ሆይ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን?” አለው። መልአኩ ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ካደረገለት በኋላ ‘እስራኤልን በእርግጥ ከምድያም እጅ ታድናለህ’ በማለት ነገረው። ታዲያ ጌዴዎን ምን ተሰማው? ይህንን አጋጣሚ ራሱን ስመ ጥር ጀግና አድርጎ ለማስጠራት የሚያስችለው አጋጣሚ እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር የተሰጠውን የሥራ ኃላፊነት ተቻኩሎ ከመቀበል ይልቅ “ጌታ ሆይ፣ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” በማለት መለሰ። እንዴት ያለ ልክን የማወቅ ባሕርይ ነው!—መሳፍንት 6:11-15
12. ጌዴዎን የተሰጠውን ተልእኮ በሚወጣበት ጊዜ ብልህነትን ያሳየው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ ጌዴዎንን ወደ ጦርነት ከመላኩ በፊት ፈተና አቀረበለት። እንዴት? ጌዴዎን አባቱ ያሠራውን የበኣል መሠዊያ እንዲያፈርስና ከመሠዊያው አጠገብ ተተክሎ የነበረውን የማምለኪያ ዐፀድ እንዲቆርጥ ተነገረው። ይህን ማድረግ ድፍረት የሚጠይቅ ነበር። ሆኖም ጌዴዎን የተሰጠውን ተልእኮ በሚያከናውንበት ጊዜ ልክን የማወቅንና የብልህነትን ባሕርይ አሳይቷል። ጌዴዎን ተልእኮውን በገሃድ ከመፈጸም ይልቅ የማንንም ትኩረት ሳይስብ ጨለማን ተገን በማድረግ የተባለውን አከናወነ። በተጨማሪም ጌዴዎን የተሰጠውን ተልእኮ በሚፈጽምበት ጊዜ ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጓል። መሠዊያውንና የማምለኪያ ዐፀዱን በሚያፈርስበት ጊዜ ግማሾቹ እንዲረዱት ሌሎቹ ደግሞ ፈንጠር ብለው አካባቢውን መቃኘት እንዲችሉ ሳይሆን አይቀርም ከእርሱ ጋር አሥር አገልጋዮችን ወሰደ።b ያም ሆነ ይህ ጌዴዎን በይሖዋ ድጋፍ የተሰጠውን ተልዕኮ ያከናወነ ሲሆን በኋላም አምላክ እስራኤልን ከምድያማውያን ነፃ እንዲያወጣ ተጠቅሞበታል።—መሳፍንት 6:25-27
ልክን የማወቅን ባሕርይና ብልህነትን ማሳየት
13, 14. (ሀ) አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ሲሰጠን ልካችንን የምናውቅ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ልክን የማወቅ ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?
13 ጌዴዎን ካሳየው ልክን የማወቅ ባሕርይ ብዙ የምንማረው ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት በሚሰጠን ጊዜ የምንሰጠው ምላሽ ምን ዓይነት ነው? በመጀመሪያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው መብቱ ስለሚያስገኝልን እውቅና ወይም ክብር ነው? ወይስ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ መወጣት እችል ይሆን ብለን ልክን የማወቅ ባሕርይ በማንጸባረቅ በጸሎት እናስብበታለን? በ1966 ምድራዊ ሕይወቱን የጨረሰው ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ሲ ቲ ራስል በአንድ ወቅት እርሱ በማይኖርበት ጊዜ ሥራውን ማን ተክቶ ሊሠራ እንደሚችል ወንድም ማክሚላንን ጠይቆት ነበር። ከዚያም በኋላ ስለ ጉዳዩ ባደረጉት ውይይት አጋጣሚው የነበረው ቢሆንም አንድም ጊዜ እርሱ ሊተካው እንደሚችል አልተናገረም። መጨረሻ ላይ ወንድም ራስል ሥራውን ስለመቀበል እንዲያስብበት ለወንድም ማክሚላን ነገረው። “በድንጋጤ ፈዝዤ ቀረሁ” በማለት ወንድም ማክሚላን ከብዙ ዓመት በኋላ ጽፏል። “በቁም ነገር ካሰብኩበትና ጊዜ ወስጄ ጉዳዩን በጸሎት ከመረመርኩ በኋላ እርሱን ለመርዳት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኔን ነገርኩት።”
14 ወንድም ራስል የሞተው ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በዚህ ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንትነቱ ቦታ ክፍት ሆነ። ወንድም ራስል የመጨረሻውን የስብከት ጉዞ ባደረገበት ወቅት ቦታውን ተክቶ ይሠራ የነበረው ወንድም ማክሚላን ስለነበር አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ነገረው:- “ማክ፣ ፕሬዚዳንት የመሆን አጋጣሚው ተከፍቶልሃል። ወንድም ራስል በማይኖርበት ጊዜ እርሱን ተክተህ ትሠራ የነበረው አንተ ነህ፤ ሁላችንም አንተ ያልከንን ሁሉ እንድንሠራ ነግሮን ነበር። አሁን ደግሞ እርሱ አንዴ ላይመለስ ሄዷል። በእርሱ እግር መተካት የሚኖርብህ አንተ ትመስለኛለህ።” ወንድም ማክሚላን እንዲህ በማለት መለሰ:- “ወንድም፣ ይህን ጉዳይ መመልከት የሚኖርብን በዚህ መንገድ አይደለም። ይህ የጌታ ሥራ ነው። በጌታ ድርጅት ውስጥ የሚኖርህ ማንኛውም ቦታ ጌታ ለአንተ የሚሰጥህ ተስማሚ ሆኖ ያገኘውን ነው። እኔ ደግሞ ለዚህ ሥራ የምበቃ አይደለሁም።” ከዚያም ወንድም ማክሚላን በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሌላ ሰው እንዲቀመጥ ሐሳብ አቀረበ። ልክ እንደ ጌዴዎን ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን አሳይቷል። እኛም እንዲህ የመሰለው አመለካከት ሊኖረን ይገባል።
15. ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ ማስተዋል ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ የሆኑ መንገዶች ምንድን ናቸው?
15 እኛም የተሰጠንን ሥራ በምንፈጽምበት ጊዜ ልካችንን የምናውቅ መሆን አለብን። ጌዴዎን ጠንቃቃ በመሆን ሳያስፈልግ ተቃዋሚዎቹን ላለማስቆጣት ጥረት አድርጓል። እኛም በተመሳሳይ መንገድ በስብከቱ ሥራችን ላይ ተሠማርተን ሌሎችን ስናነጋግር ልካችንን የምናውቅና ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ ‘ምሽግን’ እና ‘አሳብን’ ለማፍረስ በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ እንገኛለን። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) ይሁን እንጂ ሌሎችን ማንኳሰስ ወይም በመልእክታችን ቅር እንዲሰኙ ማድረግ አይኖርብንም። ከዚያ ይልቅ በጋራ በምንስማማበት ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ የእነርሱን አመለካከት ማክበርና መልእክታችን ግሩም በሆኑት ተስፋዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል።—ሥራ 22:1-3፤ 1 ቆሮንቶስ 9:22፤ ራእይ 21:4
ኢየሱስ—ልክን የማወቅን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ
16. ኢየሱስ ስለ ራሱ ልከኛ አመለካከት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?
16 ልክን በማወቅ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።c ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ያለው ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጉዳዮች ከእርሱ ሥልጣን በላይ እንደሆኑ ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ዮሐንስ 1:14) ለምሳሌ ያህል የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ሁለቱ ልጆቿ በመንግሥቱ ከእርሱ አጠገብ እንዲቀመጡ በጠየቀችው ጊዜ ኢየሱስ “በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን . . . እኔ የምሰጥ አይደለሁም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:20-23) በሌላ ወቅትም ኢየሱስ “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም . . . የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:30፤ 14:28፤ ፊልጵስዩስ 2:5, 6
17. ኢየሱስ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ ፍጽምና ከጎደላቸው ሰዎች በሁሉም አቅጣጫ የሚበልጥ ሲሆን አባቱ ይሖዋም ከማንም የበለጠ ሥልጣን ሰጥቶታል። ሆኖም ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር በነበረው ግንኙነት ሁሉ ልክን የማወቅ ባሕርይ አንጸባርቋል። የሚያውቃቸውን ነገሮች ሁሉ በመናገር እንዲጨነቁ አላደረጋቸውም። ሰብዓዊ ፍላጎቶቻቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሐዘኔታንና ርኅራኄን አሳይቷቸዋል። (ማቴዎስ 15:32፤ 26:40, 41፤ ማርቆስ 6:31) ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም እንኳ ከሌሎች ፍጽምናን የሚጠብቅ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ ከአቅማቸው በላይ እንዲያደርጉ አልጠበቀባቸውም፤ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይም አልጫነባቸውም። (ዮሐንስ 16:12) ብዙዎች ኢየሱስን ዕረፍት የሚሰጥ ሆኖ ማግኘታቸው ምንም አያስደንቅም።—ማቴዎስ 11:29
ኢየሱስ ያሳየውን ልክን የማወቅ ባሕርይ ኮርጁ
18, 19. (ሀ) ራሳችንን በምንመለከትበት መንገድ (ለ) ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ኢየሱስ ያሳየውን ልክን የማወቅ ባሕርይ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
18 እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ልክን የማወቅ ባሕርይ ካሳየ እኛ ደግሞ ይህን ባሕርይ ይበልጥ ማሳየት እንዳለብን የታወቀ ነው። ብዙውን ጊዜ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ሥልጣናቸው ገደብ ያለው መሆኑን አምኖ መቀበል ይከብዳቸዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ የልከኝነትን ባሕርይ ለማሳየት ይጥራሉ። ብቃቱ ላላቸው ሰዎች ኃላፊነት ለመስጠት እስኪያዳግታቸው ድረስ ኩራተኞች አይደሉም፤ ወይም ደግሞ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች የሚሰጡትን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረን በማለት ትዕቢተኛና እንቢተኛም አይደሉም። የትብብር መንፈስ በማሳየት በጉባኤ ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ “በአገባብና በሥርዓት” እንዲከናወኑ ይፈቅዳሉ።—1 ቆሮንቶስ 14:40
19 ልክን የማወቅ ባሕርይ ከሌሎች በምንጠብቀው ረገድ ምክንያታዊ እንድንሆንና ለሚያስፈልጋቸው ነገር ደግሞ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ሌሎች ሰዎች የሌሏቸው አንዳንድ ችሎታዎችና ጠንካራ ጎኖች ሊኖሩን ይችላሉ። ሆኖም ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ሌሎች ሁልጊዜ እኛ እንደምንፈልገው እንዲያደርጉ አንጠብቅባቸውም። እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ የአቅም ገደብ እንዳለበት ማወቃችን የሌሎችን ስህተት በትህትና እንድናልፍ ይረዳናል። ጴጥሮስ “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 4:8
20. ያለብንን ማንኛውንም ዓይነት ልክን ያለማወቅ ዝንባሌ ለማሸነፍ ምን ልናደርግ እንችላለን?
20 እስካሁን እንደተማርነው በእርግጥም ጥበብ ልካቸውን በሚያውቁ ሰዎች ዘንድ ይገኛል። ይሁን እንጂ ልክን ያለማወቅ ወይም የትዕቢተኝነት ዝንባሌ እንዳለብህ ብትገነዘብስ? ተስፋ አትቁረጥ። ከዚያ ይልቅ “የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ [“በትዕቢት ኃጢአት እንዳልሠራ፣” NW ] ባሪያህን ጠብቅ” ብሎ የጸለየውን የዳዊትን ምሳሌ ተከተል። (መዝሙር 19:13) ጳውሎስ፣ ጌዴዎንና ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰሉ ሰዎችን እምነት በመኮረጅ “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” የሚሉት ቃላት ምን ያህል እውነት መሆናቸውን በራሳችን ሕይወት ልናጣጥም እንችላለን።—ምሳሌ 11:2
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ሎሌ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአንድ ትልቅ መርከብ ላይ ለመቅዘፍ የተመደበን ባሪያ ሊያመለክት ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ አንድ “መጋቢ” ርስትን እስከ ማስተዳደር ድረስ ብዙ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል። የሆነ ሆኖ፣ መጋቢም ሆነ መርከብ የሚቀዝፍ ባሪያ በአብዛኞቹ ጌቶች ዓይን ልዩነት የላቸውም።
b ጌዴዎን ያሳየው ጥንቃቄና ብልህነት የፈሪነት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ በስህተት ሊወሰድ አይገባውም። ከዚህ ይልቅ ደፋር መሆኑን በዕብራውያን 11:32-38 ላይ የተረጋገጠ ሲሆን እዚያም ላይ “ከድካማቸው በረቱ” እንዲሁም “በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ” ከተባለላቸው ሰዎች መካከል ጌዴዎንም አብሮ ተጠቅሷል።
c ልክን ማወቅ አንድ ሰው አቅሙ ውስን መሆኑን እንዲገነዘብ የሚጠይቅ ባሕርይ በመሆኑ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ እንደሆነ ተደርጎ ሊነገር አይችልም። ይሁን እንጂ ትሑት ነው።—መዝሙር 18:35 NW
-