የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ማንን ማመን ይኖርብሃል?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • ማንን ማመን ይኖርብሃል?

      “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው።”—ዕብራውያን 3:4

      ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከገለጸው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር አትስማማም? ይህ ጥቅስ ከተጻፈ ወዲህ የሰው ልጅ ሳይንሳዊ እድገት የታየባቸው 2,000 የሚያህሉ ዓመታት አሳልፏል። ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በዚህ ዘመን ‘በተፈጥሮ ውስጥ የሚታየው የረቀቀ ጥበብ አንድ ንድፍ አውጪ ወይም ፈጣሪ አለ ብለን እንድናምን ግድ ይለናል’ ብሎ የሚያምን ሰው ይኖራል?

      በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች እንኳ ሳይቀር አዎ ብለው የሚመልሱ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኒውስዊክ መጽሔት በ2005 ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው 80 በመቶ የሚያህሉ ሰዎች “አምላክ ጽንፈ ዓለሙን እንደፈጠረ ያምናሉ።” እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ እምነት ሊኖራቸው የቻለው በቂ ትምህርት ሳያገኙ በመቅረታቸው ይሆን? እስቲ በአምላክ የሚያምን ሳይንቲስት ይኖር እንደሆነ እንመልከት። ኔቸር የተባለው ሳይንሳዊ መጽሔት በ1997 እንዳመለከተው በአንድ ጥናት ውስጥ ከተካተቱ የባዮሎጂ፣ የፊዚክስና የሒሣብ ሊቃውንት መካከል 40 በመቶ የሚያህሉት አምላክ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ይህ አምላክ ጸሎት ሰምቶ መልስ እንደሚሰጥ ጭምር ያምናሉ።

      ይሁን እንጂ ይህን አጥብቀው የሚቃወሙ ሌሎች ሳይንቲስቶች አሉ። የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ዶክተር ኸርበርት ሃውፕትማን በቅርቡ በአንድ ሳይንሳዊ ስብሰባ ላይ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ታላቅ ኃይል፣ በተለይ ደግሞ በአምላክ ማመን ከትክክለኛ ሳይንስ ጋር ሊጣጣም እንደማይችል ተናግረዋል። አክለውም “እንዲህ ያለው እምነት የሰውን ዘር ደኅንነት በእጅጉ ይጎዳል” ብለዋል። በአምላክ የሚያምኑ ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ በዕፅዋትና በእንስሳት ላይ የሚታየው የረቀቀ ንድፍ በፈጣሪ መኖር እንድናምን ያስገድደናል ብለው ለማስተማር አይደፍሩም። ለምን? በስሚዝሶንያን ተቋም ፓሊዮባዮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ዳግላስ ኧርዊን ይህ የሆነበትን አንደኛውን ምክንያት ሲያስረዱ “ከሳይንስ ሕግጋት አንዱ ተአምር በሚባል ነገር አለማመን ነው” ብለዋል።

      አንተም ሌሎች በምታስበውና በምታምንበት ነገር ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብህ ልትፈቅድ አሊያም አንዳንድ መረጃዎችን ራስህ በሚገባ መርምረህ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ። በሚቀጥሉት ገጾች ላይ የሠፈሩትን የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶች በምታነብበት ጊዜ “ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው?” እያልክ ራስህን ጠይቅ።

      [በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ማስረጃዎቹን ራስህ መርምር

      [በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      የይሖዋ ምሥክሮች ክሪኤሽኒስት ናቸው?

      የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ሠፍሮ በሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ከክሪኤሽኒስቶች (የፍጥረት አማኞች) ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ብዙ ክሪኤሽኒስቶች ምድርንና በምድር ላይ የሚኖሩትን ሕያዋን ፍጥረታት ጨምሮ መላው ጽንፈ ዓለም የተፈጠረው የዛሬ 10,000 ዓመት ገደማ እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም።a በተጨማሪም ክሪኤሽኒስቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ በሌላቸው በርካታ መሠረተ ትምህርቶች ያምናሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ግን ሙሉ በሙሉ የተመሠረቱት በአምላክ ቃል ላይ ነው።

      ከዚህም በላይ በአንዳንድ አገሮች “ክሪኤሽኒስት” የሚለው ቃል በፖለቲካ ጉዳዮች በንቃት የሚካፈሉ አክራሪ ቡድኖችን ያመለክታል። እነዚህ ቡድኖች ፖለቲከኞች፣ ዳኞችና የትምህርት ባለሞያዎች ከክሪኤሽኒስቶች ሃይማኖታዊ ሕግጋት ጋር የሚስማሙ ሕጎችንና ትምህርቶችን እንዲከተሉ ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ።

      የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ናቸው። መንግሥት ያለውን ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም መብት ያከብራሉ። (ሮሜ 13:1-7) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ የተናገረውን ቃል አክብደው ይመለከታሉ። (ዮሐንስ 17:14-16) በሕዝባዊ አገልግሎታቸው አማካኝነት ሰዎች የአምላክን ሕግጋት አክብሮ መኖር የሚያስገኘውን ጥቅም የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግጋት እንዲከተሉ የሚያስገድድ መንግሥታዊ ሕግ እንዲወጣ ለሚጥሩ አክራሪ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን አያላሉም።—ዮሐንስ 18:36

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a እባክህ በዚህ እትም ገጽ 18 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት—ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

  • ተፈጥሮ ምን ያስተምረናል?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • ተፈጥሮ ምን ያስተምረናል?

      “እስቲ እንስሶችን ጠይቁ፤ ያስተምሯችኋል፤ የሰማይ ወፎችንም ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤ ለምድር ተናገሩ፤ ታስተምራችኋለች፤ የባሕርም ዓሣ ይነግራችኋል።”—ኢዮብ 12:7, 8

      ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሳይንስና የምሕንድስና ሊቃውንት ከዕፅዋትና ከእንስሳት ቃል በቃል ተምረዋል ለማለት ይቻላል። አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመፍጠርም ሆነ በሥራ ላይ የሚገኙ መሣሪያዎችን ጥራት ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት እንዲያግዛቸው የተለያዩ ፍጥረታትን ንድፍ እያጠኑና እየኮረጁ ሲሆን ይህ የጥናት መስክ ባዮሚሜቲክስ ይባላል። ቀጥሎ የቀረቡትን ምሳሌዎች በምትመለከትበት ጊዜ ‘እንዲህ ላለው የረቀቀ ንድፍ ሊመሰገን የሚገባው ማነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

      ከዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ ክንፎች ትምህርት ማግኘት

      የአውሮፕላን ንድፍ አውጪዎች ሃምፕባክ ከሚባለው ዓሣ ነባሪ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ? በርካታ ትምህርቶችን ማግኘት የሚችሉ ይመስላል። በዕድሜ ትልቅ የሆነ አንድ ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ ክብደቱ 300 ኩንታል የሚደርስ ሲሆን ሙሉ ጭነት ከተጫነ ከባድ መኪና ጋር ይተካከላል። መላ ሰውነቱ እንደልብ የማይተጣጠፈው ይህ ዓሣ ነባሪ በጣም ትላልቅ ክንፍ መሰል መቅዘፊያዎች አሉት። ይህ 12 ሜትር ርዝመት ያለው እንስሳ ውኃ ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴው በጣም ቀልጣፋ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የባሕር እንስሳት ወይም አንድ ዓሣ ለመብላት በሚፈልግበት ጊዜ ከዓሣው በታች ሆኖ ቀጥ ብሎ በመቆም በፍጥነት እየሾረ አረፋ በማውጣት መረብ ይሠራል። መሃል ለመሃል ከ1.5 ሜትር የማይበልጥ ርዝመት ያለው ይህ የአረፋ መረብ ከላይ ያሉትን ፍጥረታት በሙሉ እየሳበ አንድ ላይ ይሰበስብለታል። ከዚያም ዓሣ ነባሪው በቀላሉ ይውጣቸዋል።

      ተመራማሪዎቹን በእጅጉ ያስደነቃቸው፣ እንደልቡ ሊተጣጠፍ የማይችለው ይህ ፍጡር ጠባብ ስፋት ያለው ክብ ነገር የሚሠራበት መንገድ ነው። ተመራማሪዎቹ ምሥጢሩ ያለው በዓሣ ነባሪው መቅዘፊያ ክንፎች ቅርጽ ላይ እንደሆነ ደርሰውበታል። የፊተኛው ጠርዝ እንደ አውሮፕላን ክንፍ የተስተካከለ ሳይሆን በርካታ አባጣ ጎርባጣዎች አሉት።

      ዓሣ ነባሪው ውኃውን እየሰነጠቀ በፍጥነት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እነዚህ አባጣ ጎርባጣዎች የውኃውን ግፊት በመቀነስ ወደፊት የመወንጨፍ ኃይል ይጨምሩለታል። እንዴት? ናቹራል ሂስትሪ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው አባጣ ጎርባጣዎቹ ዓሣ ነባሪው ቀጥ ብሎ ሽቅብ በሚወጣበት ጊዜም እንኳ ከፊቱ ያለው ውኃ ሥርዓት ባለው መንገድ በክብ ቅርጽ መልክ እየተሽከረከረ እንዲያልፍ ያስችሉታል። የክንፎቹ ፊተኛ ጠርዝ የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ ከክንፉ አልፎ የሚሄደው ውኃ ሞገድ እንዲፈጠር ስለሚያደርግ በቀላሉ ሽቅብ ሊወጣ አይችልም ነበር።

      ታዲያ ይህ ግኝት ምን ተግባራዊ ጠቀሜታ ያስገኛል? በዚህ መንገድ የተሠራ የአውሮፕላን ክንፍ በርካታ የነፋስ አቅጣጫ ማስቀየሪያዎች ወይም አየር መቅዘፊያ መሣሪያዎች አያስፈልጉትም። በተጨማሪም ይበልጥ አስተማማኝ ከመሆኑም በላይ ለመጠገንም ከባድ አይደለም። የባዮሜካኒክስ ሊቅ የሆኑት ጆን ሎንግ አንድ ቀን “እያንዳንዱ አውሮፕላን የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ ዓይነት አባጣ ጎርባጣ ክንፍ ተገጥሞለት ማየታችን አይቀርም” ብለዋል።

      ሲጋል የተባለውን ወፍ ክንፍ መቅዳት

      አሁንም ቢሆን የአውሮፕላን ክንፍ ቅርጽ የተሠራው ከወፎች ክንፍ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። ይሁን እንጂ መሐንዲሶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ጥበብ ይበልጥ አሻሽለውታል። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደ ሲጋል በአየር ላይ ቀጥ ብሎ የመቆም፣ ቁልቁል የመወርወርና ሽቅብ የመውጣት ችሎታ ያለው ያለአብራሪ የሚንቀሳቀስ አውሮፕላን ሠርተዋል።”

      ሲጋል የተባለው ወፍ ይህን የመሰለ አስደናቂ እንቅስቃሴ የሚያደርገው በክንፎቹ ላይ ያሉትን የተለያዩ መገጣጠሚያዎች እንደሁኔታው በማንቀሳቀስ ነው። መጽሔቱ እንደገለጸው “ሁለት ጫማ ርዝመት ያለው ይህ የሙከራ አውሮፕላን” እንደልብ ከሚተጣጠፈው የሲጋል ወፍ ክንፍ ጋር በሚመሳሰል መልኩ “በክንፎቹ ላይ ያሉትን የብረት ዘንጎች ለመቆጣጠር የሚያስችል ትንሽ ሞተር አለው።” እነዚህ በከፍተኛ ጥበብ የተሠሩ ክንፎች ትንሿ አውሮፕላን በረጃጅም ሕንጻዎች መካከል ቀጥ ብላ እንድትቆምና ቁልቁል እንድትወርድ ያስችሏታል። የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል እንዲህ ያለውን እንደልብ የሚተጣጠፍና የሚንቀሳቀስ አውሮፕላን በትላልቅ ከተሞች ኬሚካላዊና ባዮሎጂያዊ መሣሪያዎችን አስሶ ለማግኘት ሊጠቀምበት ይፈልጋል።

      የእንሽላሊት እግሮችን አፈጣጠር መቅዳት

      ሰዎች ከየብስ እንስሳትም ብዙ የሚማሩት ነገር አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ጌኮ የምትባለው ትንሽ እንሽላሊት ቀጥ ያለ ግድግዳ ላይ መውጣትና ኮርኒስ ላይ ተገልብጣ መሄድ ትችላለች። ይህች ፍጥረት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሳይቀር በዚህ አስደናቂ ችሎታዋ ትታወቃለች። (ምሳሌ 30:28 NW) ጌኮ የስበትን ኃይል እንድትቋቋም ያስቻላት ምንድን ነው?

      ጌኮን እንደመስታወት ባለ ልሙጥ ነገር ላይ ሳይቀር እንድትለጠፍ ያስቻሏት እግሮቿን የሸፈኑት ሴታ የሚባሉ ጥቃቅን ጸጉር መሰል ነገሮች ናቸው። እግሮቿ እንደሙጫ የማጣበቅ ችሎታ ያለው ፈሳሽ አያመነጩም። ከዚህ ይልቅ በሞለኪውሎች መሳሳብ ምክንያት በሚፈጠርና በጣም ረቂቅ በሆነ ኃይል ትጠቀማለች። በሁለት ነገሮች ላይ የሚገኙ ሞለኪውሎች በመካከላቸው ባለ ቫን ደር ዋልስ ተብሎ በሚጠራ በጣም ደካማ ኃይል እርስ በርስ ይያያዛሉ። አብዛኛውን ጊዜ ይህ የመሳሳብ ኃይል ከመሬት ስበት በእጅጉ ያነሰ ነው። እጃችንን እየለጠፍን ግድግዳ መውጣት የማንችለው በዚህ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ ሴታ የሚባሉት የጌኮ ጥቃቅን ጸጉር መሰል ነገሮች በግድግዳው ላይ የሚያርፈውን የእግሯን ስፋት በጣም እንዲጨምር ያደርጉታል። የቫን ደር ዋልስ ኃይል በጌኮ እግር ላይ በሚገኙት በሺዎች በሚቆጠሩት ሴታዎች ሲባዛ አነስተኛ የሆነውን የጌኮዎች ክብደት ሊሸከም የሚያስችል ኃይል ያስገኛል።

      ታዲያ ይህ ግኝት ምን ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል? በጌኮ እግሮች አምሳል የተሠራ ሰው ሠራሽ ጨርቅ ቬልክሮ ለሚባል ማያያዣ ምትክ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፤ ለነገሩ ቬልክሮም ቢሆን የተሠራው ተፈጥሮን በመኮረጅ ነው።a ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት አንድ ተመራማሪ በጌኮ እግር ላይ ካሉ ፀጉር መሰል ነገሮች የተሠራ ጨርቅ በተለይ “በሕክምናው መስክ ኬሚካላዊ ማያያዣዎችን መጠቀም በማይቻልባቸው ወቅቶች” ልዩ ጠቀሜታ እንደሚኖረው መናገራቸውን ጠቅሷል።

      ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ማነው?

      በሌላ በኩል ብሔራዊ የበረራና ሕዋ አስተዳደር (NASA) እንደ ጊንጥ የሚራመድ ባለ ብዙ እግር ሮቦት በመሥራት ላይ ነው። የፊንላንድ መሐንዲሶች ደግሞ እንደ አንዳንድ ነፍሳት በትላልቅ እንቅፋቶች ላይ ተረማምዶ ሊያልፍ የሚችል ባለ ስድስት እግር ትራክተር ሠርተዋል። ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ ልክ እንደ ፈረንጅ ጥድ የዘር መያዣዎች አየሩ ሞቃት ሲሆን የሚከፈቱና እርጥበት ሲኖር የሚዘጉ ትናንሽ ተካፋቾች ያሉት ልብስ ሠርተዋል። አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ቦክስፊሽ በሚባል የዓሣ ዝርያ አምሳል የአየሩን ግፊት በቀላሉ ጥሶ ማለፍ የሚችል መኪና በመሥራት ላይ ነው። ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ አባሎኒ የሚባሉት የባሕር ፍጥረታት ያላቸውን ንቅናቄ የማብረድ ችሎታ በመቅዳት ይበልጥ ቀላልና ጠንካራ የሆነ የጥይት መከላከያ ለመሥራት እየሞከሩ ነው።

      ከተፈጥሮ የሚገኙት ሐሳቦች በጣም ብዙ በመሆናቸው ተመራማሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ባዮሎጂያዊ አሠራሮችን ያካተተ የመረጃ ዝርዝር አዘጋጅተዋል። ዚ ኢኮኖሚስት እንደገለጸው ሳይንቲስቶች “ለዲዛይን ችግሮቻቸው ከተፈጥሮ መፍትሔ” ለማግኘት እነዚህን ዝርዝሮች መመርመር ይችላሉ። በእነዚህ የመረጃ ስብስቦች ውስጥ የሚገኙት የተፈጥሮ አሠራሮች “ባዮሎጂካል ፓተንትስ” ወይም ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት ይባላሉ። እንደሚታወቀው የፈጠራ ባለቤት የሚሆነው አንድን አዲስ ሐሳብ ወይም መሣሪያ በሕግ ያስመዘገበ ሰው ወይም ኩባንያ ነው። ዚ ኢኮኖሚስት ስለ ባዮሎጂያው የፈጠራ ባለቤትነት የመረጃ ስብስብ ሲያብራራ “ተመራማሪዎች በተፈጥሮ ያሉ ነገሮችን አስመስሎ የመሥራት ዘዴዎችን ‘ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት’ ብለው ሲጠሩ የፈጠራው ባለ መብት ተፈጥሮ ራሷ መሆኗን ማጉላታቸው ነው” ይላል።

      ታዲያ ተፈጥሮ እነዚህን ድንቅ ሐሳቦች ልታፈልቅ የቻለችው እንዴት ነው? ብዙ ተመራማሪዎች በተፈጥሮ ውስጥ የሚታዩት አስደናቂ ንድፎች በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በሙከራ የተገኙ የዝግመተ ለውጥ ውጤቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። ሌሎች ተመራማሪዎች ግን ከዚህ የተለየ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ማይክል ቢሂ የተባሉ ማይክሮባዮሎጂስት በ2005 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በተባለ መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[በተፈጥሮ ውስጥ] የሚታየው አስደናቂ ንድፍ ማንም በቀላሉ ሊረዳው የሚችል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባል:- አንድ ነገር ዳክዬ የሚመስል፣ እንደ ዳክዬ የሚራመድና እንደ ዳክዬ የሚጮህ ከሆነ ዳክዬ ላለመሆኑ በቂ መረጃ እስካልተገኘ ድረስ ዳክዬ ነው ብለን ለመደምደም እንገደዳለን።” ታዲያ እርሳቸው የደረሱበት መደምደሚያ ምንድን ነው? “በግልጽ የሚታይ ንድፍ እንደ አልባሌ ነገር በቸልታ መታለፍ የለበትም።”

      ይበልጥ አስተማማኝና የተቀላጠፈ በረራ ለማድረግ የሚያስችል የአውሮፕላን ክንፍ ንድፍ ያወጣ መሐንዲስ ለልፋቱ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ሁለገብ የሆነ ፋሻ ወይም ይበልጥ ምቹ የሆነ ልብስ አሊያም ነዳጅ ቆጣቢ መኪና ለመሥራት የሚያስችል ንድፍ ያወጣ ሰው ለሥራው ይመሰገናል። እንዲያውም ለንድፍ አውጪው እውቅና ሳይሰጥ ወይም የእርሱን ፈቃድ ሳያገኝ ግኝቱን የቀዳ አንድ አምራች ኩባንያ እንደ ወንጀለኛ ይቆጠራል።

      የተፈጥሮ ንድፎችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቀድተው የምሕንድስና ችግሮቻቸውን የፈቱ ከፍተኛ ሥልጠና ያገኙ ተመራማሪዎች ዋነኛው ንድፍ ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌለው የዝግመተ ለውጥ ውጤት ነው ማለታቸው ምክንያታዊ ይመስልሃል? ቅጂውን ለመሥራት ከፍተኛ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ ካስፈለገ የመጀመሪያውን ለመሥራት የበለጠ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ አያስፈልግም? የበለጠ ምስጋና መሰጠት ያለበት ለማን ነው? ለዋናው ሠዓሊ ወይስ የአሳሳል ስልቱን ተምሮ ሥዕሉን አስመስሎ ለሠራ ተማሪ?

      ምክንያታዊ መደምደሚያ

      ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው በርካታ ሰዎች በተፈጥሮ ውስጥ የሚታየውን አስደናቂ ንድፍ ከተመለከቱ በኋላ እንደሚከተለው ሲል የጻፈውን መዝሙራዊ ቃላት አስተጋብተዋል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች።” (መዝሙር 104:24) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሷል። “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 1:19, 20

      ይሁን እንጂ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያላቸውና በአምላክ የሚያምኑ በርካታ ቅን ሰዎች አምላክ በዓለም ውስጥ የሚገኙትን በጣም አስደናቂ ነገሮች የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል?

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ቬልክሮ፣ በርዶክ የሚባለውን ተክል እሾሃማ ፍሬ በመቅዳት የተሠራ እንደመንጠቆ የሚሰካኩ ጥቃቅን ጭረቶች ያሉት ማያያዣ ነው።

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ተፈጥሮ እነዚህን ድንቅ ሐሳቦች ልታፈልቅ የቻለችው እንዴት ነው?

      [በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      የተፈጥሮ የፈጠራ ባለቤት ማነው?

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

      ቅጂውን ለመሥራት ከፍተኛ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ ካስፈለገ የመጀመሪያውን ለመሥራት የበለጠ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ አያስፈልግም?

      ይህ እንደልቡ የሚታጠፍ አውሮፕላን በሲጋል ክንፍ አምሳል የተሠራ ነው

      የጌኮ እግር አይቆሽሽም፣ አሻራ አይተውም፣ ቴፍሎን በተቀባባቸው ነገሮች ላይ ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም ነገር ላይ በቀላሉ ሊጣበቅ ወይም ሊነሳ ይችላል። ተመራማሪዎች ይህን ለመቅዳት በሙከራ ላይ ናቸው

      ቦክስፊሽ የተባለው የዓሣ ዝርያ ያለው አስደናቂ ንድፍ የአየርን ግፊት በቀላሉ ጥሶ ማለፍ የሚችል መኪና ንድፍ ለማውጣት አስችሏል

      [ምንጭ]

      አውሮፕላን:- Kristen Bartlett/ University of Florida; የጌኮ እግር:- Breck P. Kent; ቦክስፊሽ ዓሣ እና መኪና:- Mercedes-Benz USA

      [በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

      በተፈጥሯቸው ጠቢባን የሆኑ ተጓዦች

      ብዙ ፍጥረታት ቦታ ሳይጠፋቸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ የመጓዝ በተፈጥሮ ያገኙት ‘ጥበብ’ አላቸው። (ምሳሌ 30:24, 25) እስቲ ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።

      ◼ የጉንዳን ትራፊክ ቁጥጥር ምግባቸውን ለመቃረም የሚሰማሩ ጉንዳኖች መንገድ ሳይጠፋቸው ወደ ጉድጓዳቸው የሚመለሱት እንዴት ነው? የእንግሊዝ ተመራማሪዎች እነዚህ ፍጥረታት ጠረናቸውን እንደ ዱካ ትተው ከማለፋቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ጉንዳኖች በቀላሉ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን መንገድ ለመሥራት በጂኦሜትሪ እንደሚጠቀሙ ደርሰውበታል። ለምሳሌ ፋሮ የሚባሉት የጉንዳን ዝርያዎች “ከጉድጓዳቸው ሲወጡ ከ50 እስከ 60 ዲግሪ የሚታጠፉ የተለያዩ መንገዶችን ተከትለው ይሄዳሉ” በማለት ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። ታዲያ ይህ ምን የሚያስደንቅ ነገር አለው? አንዲት ጉንዳን ወደ ጉድጓዷ በምትመለስበት ጊዜ መገንጠያ ላይ ስትደርስ በመጠኑ የሚታጠፈውን መንገድ ተከትላ በመሄድ ወደ ጉድጓዷ ትደርሳለች። ይኸው ጽሑፍ “እንደባላ የሚገነጠል መንገድ መኖሩ” ጉንዳኖቹ በሁለት አቅጣጫ ያለ ችግር እንዲጓዙ የሚረዳቸው ከመሆኑም በላይ መንገድ ስተው የሚያባክኑትን ጊዜ በእጅጉ ይቀንስላቸዋል” ይላል።

      ◼ የአእዋፍ ኮምፓስ በርካታ ወፎች በተለያየ የአየር ሁኔታ ውስጥ ረዥም ርቀት ተጉዘው ምንም ዝንፍ ሳይሉ ትክክለኛው ቦታ ላይ ይደርሳሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ተመራማሪዎች አእዋፍ የምድርን ስበት የመለየት ችሎታ እንዳላቸው ደርሰውበታል። ይሁን እንጂ ሳይንስ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “የምድር የስበት መሥመር ከቦታ ቦታ ስለሚለያይ ሁልጊዜ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ላያመለክት ይችላል።” ታዲያ ከቦታ ቦታ የሚፈልሱ አእዋፍ አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የሚያስችላቸው ምንድን ነው? አእዋፍ በእያንዳንዱ ምሽት ውስጣዊ ኮምፓሳቸውን በምትጠልቀው ጀምበር አቅጣጫ ያስተካክላሉ። ፀሐይ የምትጠልቅበት አቅጣጫ እንደየወራቱና አካባቢው ከምድር ወገብ ባለው ርቀት መጠን ስለሚለያይ ተመራማሪዎች ወፎቹ “የዓመቱን ወራትና ጊዜ የሚነግራቸውን ተፈጥሯዊ ሰዓት” ተጠቅመው ለውጡን ያስተካክላሉ ብለው እንደሚያስቡ ሳይንስ ዘግቧል።

      ጉንዳን የጂኦሜትሪ እውቀት እንዲኖራት ያስቻላት ማን ነው? አእዋፍ ኮምፓስ፣ ተፈጥሯዊ ሰዓትና እነዚህ መሣሪያዎች የሚያስተላልፉትን መረጃ ለመተርጎም የሚያስችል አንጎል እንዲኖራቸው ያደረገው ማነው? ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌለው ዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ የረቀቀ ችሎታ ያለው ፈጣሪ?

      [ምንጭ]

      © E.J.H. Robinson 2004

  • አምላክ ሕይወትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ነው?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • አምላክ ሕይወትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ነው?

      “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።” —ራእይ 4:11

      ቻርልስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳቡን ለዓለም ካስተዋወቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት ከዚህ ንድፈ ሐሳብ ጋር ማስታረቅ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ጀመሩ።

      በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን እንደሆኑ ከሚናገሩት ታዋቂ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል አብዛኞቹ አምላክ ሕይወትን ለማስገኘት በሆነ መንገድ ዝግመተ ለውጥን ተጠቅሟል የሚለውን ሐሳብ የሚቀበሉ ይመስላል። አንዳንዶች አምላክ ጽንፈ ዓለሙን ሲፈጥር ሕይወት ከሌላቸው ኬሚካሎች ሕይወት እንዲጀምር በማድረግ የኋላ ኋላ በዚሁ ሂደት አማካኝነት የሰው ልጅ እንዲገኝ አድርጓል ብለው ያስተምራሉ። ቴየስቲክ ኢቮሉሽን የሚባለውን ይህን ትምህርት የሚቀበሉ ቡድኖች አምላክ አንድ ጊዜ ሂደቱን ካስጀመረ በኋላ እጁን ጣልቃ አላስገባም ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ አብዛኞቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እንዲገኙ ያደረገ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ሂደቱን ለማፋጠን ጣልቃ ይገባ እንደነበረ ይሰማቸዋል።

      ሁለቱን ትምህርቶች ማስታረቅ ይቻላል?

      የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በእርግጥ ሊስማማ ይችላል? የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ከሆነ ስለ መጀመሪያው ሰው ስለ አዳም አፈጣጠር የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ  የሞራል ትምህርት ከመስጠት የበለጠ ፋይዳ የሌለው ቃል በቃል ሊወሰድ የማይችል ታሪክ ይሆናል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ 2:18-24) ኢየሱስ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ያለ አመለካከት ነበረው? እንዲህ ብሎ ነበር:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:4-6

      ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ላይ የተገለጸውን የፍጥረት ታሪክ ነው። ኢየሱስ የመጀመሪያው ጋብቻ የፈጠራ ታሪክ እንደሆነ አድርጎ ቢያምን ኖሮ ጋብቻ ቅዱስ መሆኑን ለማስረዳት ማስረጃ አድርጎ ይጠቅሰው ነበር? በፍጹም። ኢየሱስ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ታሪክ የጠቀሰው እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ያውቅ ስለነበረ ነው።—ዮሐንስ 17:17

      የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም በተመሳሳይ ስለ ፍጥረት በሚናገረው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ ያምኑ ነበር። ለምሳሌ ሉቃስ በጻፈው ወንጌል ላይ የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ወደኋላ እየተቆጠረ እስከ አዳም ድረስ ተዘርዝሯል። (ሉቃስ 3:23-38) አዳም ሐሳብ የወለደው ሰው ከሆነ ይህ የትውልድ ሐረግ ከተጨባጭ ሐቅ ወደ ፈጠራ የተሸጋገረው የት ላይ ነው? የዚህ የዘር ሐረግ መነሻ ፈጠራ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ከዳዊት የትውልድ ሐረግ የተገኘ መሲሕ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሆኖ ሊጠቀስ ይችል ነበር? (ማቴዎስ 1:1) የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ “ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ [መረመርሁ]” ብሏል። እርሱም በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ታሪክ ያምን እንደነበረ ግልጽ ነው።—ሉቃስ 1:3

      ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሱስ ላይ የነበረው እምነት በዘፍጥረት ዘገባ ላይ የተመሠረተ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ።” (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22) ኃጢአትም ሆነ የኃጢአት ውጤት የሆነው ሞት ወደ ዓለም ለመግባታቸው ምክንያት የሆነው አዳም የሰው ዘር የመጀመሪያ አባት ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ በውርስ የሚተላለፈውን ኃጢአት ለማስወገድ የሚሞትበት ምን ምክንያት ይኖራል?—ሮሜ 5:12፤ 6:23

      ሰዎች ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ታሪክ ላይ ያላቸውን እምነት ለማዳከም መሞከር የክርስትናን እምነት መሠረት ከመናድ ተለይቶ አይታይም። የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና የክርስቶስ ትምህርት ፈጽሞ ሊጣጣሙ አይችሉም። እነዚህን እምነቶች ለማስታረቅ የሚደረገው ማንኛውም ጥረት ‘በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ የሚነዳና በትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚንገዋለል’ ደካማ እምነት ከማስገኘት ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም።—ኤፌሶን 4:14

      በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ እምነት

      መጽሐፍ ቅዱስ ለበርካታ መቶ ዓመታት የትችትና የጥቃት ዒላማ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትክክል መሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተረጋግጧል። መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ፣ ከጤናና ከሳይንስ ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸው ጉዳዮች በሙሉ እምነት የሚጣልባቸው መሆኑ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። ስለ ሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት የሚሰጠው ምክር አስተማማኝና ዘመን የማይሽረው ነው። ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችና ንድፈ ሐሳቦች አንድ ሰሞን ብቅ ብሎ ወዲያው እንደሚጠወልግ ሣር ናቸው፤ የአምላክ ቃል ግን “ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 40:8

      የዝግመተ ለውጥ ትምህርት በሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳብነት ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያብብና ሲስፋፋ የቆየ ሰብዓዊ ፍልስፍና ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተፈጥሮ የተራቀቀ ንድፍ አውጪ እንዳለው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እየበዙ በመምጣታቸው ለእነዚህ ማስረጃዎች ምላሽ ለመስጠት ሲባል የዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ራሱ አዝጋሚ ለውጥ እያደረገ ነው። ይህን ጉዳይ በይበልጥ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። በዚሁ እትም ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ርዕሶች በማንበብ ይህን ማድረግ ትችላለህ። በተጨማሪም በዚህና በ32ኛው ገጽ ላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት ማንበብ ትችላለህ።

      በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር ካደረግክ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቀድሞዎቹ ዘመናት በሚናገራቸው ነገሮች ላይ ያለህ እምነት መጠናከሩ አይቀርም። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚሰጠው ተስፋ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። (ዕብራውያን 11:1) በተጨማሪም ‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’ የሆነውን ይሖዋን ለማወደስ ትገፋፋ ይሆናል።—መዝሙር 146:6

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በዚህ ብሮሹር ውስጥ ተገልጸዋል

      Is There a Creator Who Cares About You? አንዳንድ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን በመመርመር አሳቢ የሆነው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት አድርግ

      ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? “አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ በዚህ መጽሐፍ በምዕራፍ 3 ላይ ተብራርቷል

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ኢየሱስ ስለ ፍጥረት በሚናገረው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ ያምን ነበር። ታዲያ እርሱ ተሳስቶ ነበር?

      [በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ዝግመተ ለውጥ ምንድን ነው?

      ዝግመተ ለውጥ ተብሎ የሚተረጎመው “ኢቮሉሽን” የሚለው እንግሊዝኛ ቃል “በአንድ አቅጣጫ የሚጓዝ የለውጥ ሂደት” የሚል ፍቺ አለው። ይሁን እንጂ ቃሉ በተለያዩ መንገዶችም ይሠራበታል። ለምሳሌ ያህል ሕይወት የሌላቸው ነገሮች የሚያደርጉትን ከፍተኛ ለውጥ ያመለክታል፤ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው እድገት ለዚህ እንደ አብነት ይጠቀሳል። በተጨማሪም ቃሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ማለትም ዕፅዋትና እንስሳት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ የሚያደርጉትን ዓይነት ለውጥ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ቃሉ አብዛኛውን ጊዜ ሕይወት የተገኘው ሕይወት ከሌላቸው ኬሚካሎች እንደሆነ የሚገልጸውን ንድፈ ሐሳብ ለማመልከትም ይሠራበታል፤ በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት እነዚህ ኬሚካሎች የመባዛት ችሎታ ያላቸው ሴሎች አስገኙና ሴሎቹ ይበልጥ ውስብስብ ወደሆኑ ፍጥረታት እየተሻሻሉ ሄዱ። በመጨረሻም ከሁሉ የበለጠ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው ተገኘ። በዚህ መጽሔት ውስጥ “ዝግመተ ለውጥ” የሚለው ሐረግ የተሠራበት በዚህ በሦስተኛ ትርጉሙ ነው።

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      የሕዋ ፎቶ:- J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA

  • ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

      በአሁኑ ጊዜ በፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሊሃይ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቤሄ በ1996 ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ—ዘ ባዮኬሚካል ቻሌንጅ ቱ ኢቮሉሽን (የዳርዊን እንቆቅልሽ—ባዮኬሚካላዊ ግኝቶች በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ላይ ያስከተሉት ፈተና) የተባለ መጽሐፍ አሳትመው ነበር። የነሐሴ 1998 ንቁ! መጽሔት እትም “ምድር ላይ የተገኘነው ተፈጥረን ነው ወይስ በአጋጣሚ?” በሚል ዋና ርዕስ ሥር ተከታታይ ጽሑፎችን ይዞ ወጥቶ የነበረ ሲሆን እዚያ ላይ የማይክል ቤሄ መጽሐፍ ተጠቅሷል። ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ የተባለው መጽሐፍ ከወጣ ወዲህ ባሳለፍናቸው አሥር ዓመታት ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብን የሚደግፉ ሳይንቲስቶች ቤሄ ያነሱትን የመከራከሪያ ነጥብ ለማስተባበል ተረባርበዋል። ተቺዎች ቤሄ ሃይማኖታዊ እምነታቸው (የሮማ ካቶሊክ አማኝ ናቸው) ሳይንሳዊ የማመዛዘን ችሎታቸውን አጨልሞባቸዋል ሲሉ ከስሰዋቸዋል። ሌሎች ደግሞ የሚያቀርቡት የመከራከሪያ ነጥብ ሳይንሳዊ አይደለም ብለዋል። ንቁ! እኚህ ሰው የሰነዘሩት ሐሳብ ይህን ያህል አወዛጋቢ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት ራሳቸውን አነጋግሯቸዋል።

      ንቁ!:- ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ የተንጸባረቀባቸው ናቸው ብለው እንዲያምኑ ያደረጎት ምንድን ነው?

      ፕሮፌሰር ቤሄ:- የተለያዩ ክፍሎች ያሉትና ውስብስብ ሥራ የሚያከናውን መሣሪያ በምንመለከትበት ጊዜ ሠሪ ወይም ንድፍ አውጪ እንዳለው እንረዳለን። ለአብነት ያህል፣ በየቀኑ ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ሣር ማጨጃ ማሽንና መኪና ያሉትን ወይም የእነዚህን ያህል ውስብስብነት የሌላቸውን መሣሪያዎች እንመልከት። ብዙውን ጊዜ እንደ ምሳሌ የምጠቅሰው የአይጥ ወጥመድን ነው። የተለያዩ ክፍሎች አንድ ላይ ተቀናጅተው አይጥ የመያዝ ተግባራቸውን ሲፈጽሙ ስለምታይ ይህን ነገር የሠራ አንድ ሰው መኖር አለበት ብለህ ታስባለህ።

      በአሁኑ ጊዜ ሳይንስ ሴልን የመሳሰሉትን የሕይወት መሠረታዊ ክፍሎች ለይቶ ለማወቅ በሚያስችለው የእድገት ደረጃ ላይ ደርሷል። በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ እነዚህ መሠረታዊ ክፍሎች እንደ አንድ ውስብስብ ማሽን የተራቀቀ አሠራር እንዳላቸው ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በሴሎች ውስጥ አስፈላጊ ነገሮችን ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ የሚያጓጉዙ “የጭነት ተሽከርካሪዎች” አሉ። እንዲሁም እነዚህ “ተሽከርካሪዎች” የሚታጠፉበትን ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያመለክቱ ሞለኪውል የሚባሉ ጥቃቅን “ጠቋሚ ምልክቶች” አሉ። አንዳንድ ሴሎች በፈሳሽ ውስጥ እንዲጓዙ የሚያስችላቸው ውጪያዊ “መቅዘፊያ ሞተር” አላቸው። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ሰዎች እንዲህ ያሉ የተወሳሰቡ መሣሪያዎችን ሲመለከቱ እነዚህን ነገሮች የሠራ አንድ ንድፍ አውጪ መኖር አለበት ብለው መደምደማቸው አይቀርም። የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ምንም ይበል ምን፣ ውስብስብ ለመሆናቸው ሌላ ምክንያት ልንሰጥ አንችልም። እንዲህ ያለ ውስብስብ ነገር ሲያጋጥመን ሠሪ አለው ብለን መደምደማችን የተለመደ በመሆኑ ይህ ውስብስብ የሞለኪውሎች ቅንብርም የረቀቀ ችሎታ ያለው አንድ ንድፍ አውጪ አለው ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው።

      ንቁ!:- አብዛኞቹ ባልደረቦችዎ በእርስዎ አመለካከት የማይስማሙት ለምን ይመስልዎታል?

      ፕሮፌሰር ቤሄ:- ብዙ ሳይንቲስቶች በእኔ አመለካከት የማይስማሙት፣ ሕይወት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለው ሐሳብ ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ ጋር እንደሚጋጭ ስለሚሰማቸውና ከተፈጥሮ ኃይሎች በላይ ወደሆነ አካል ሊያመለክት ይችላል ብለው ስለሚያስቡ ነው። ብዙዎችን እንዲህ ያለው መደምደሚያ ያስፈራቸዋል። ይሁን እንጂ ሳይንስ ማስረጃዎቹ ወደሚጠቁሙት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበት የታወቀ ነው። በእኔ አመለካከት ተቀባይነት የሌለው ፍልስፍና ይሆናል በሚል ስሜት ጠንካራ ማስረጃ ያለውን መደምደሚያ ከመቀበል ወደኋላ ማለት ፈሪነት ነው።

      ንቁ!:- ተፈጥሮ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለው አስተሳሰብ ድንቁርናን ያስፋፋል ለሚሉ ተቺዎች ምን መልስ ይሰጣሉ?

      ፕሮፌሰር ቤሄ:- በተፈጥሮ ውስጥ የረቀቀ ንድፍ ተንጸባርቋል የሚለው መደምደሚያ ከድንቁርና የመነጨ አይደለም። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ካለማወቅ የመነጨ ሳይሆን በማወቃችን የደረስንበት መደምደሚያ ነው። ዳርዊን ከ150 ዓመት በፊት ዚ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ የተባለውን መጽሐፉን ባወጣ ጊዜ ሕይወት ይህን ያህል የተወሳሰበ መስሎ አይታይም ነበር። ሳይንቲስቶች ሴል በጣም ተራ ነገር በመሆኑ ባሕር ውስጥ ካለ ጭቃ በድንገት ሊገኝ እንደሚችል ይሰማቸው ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን ሳይንስ፣ ሴል በጣም ውስብስብ እንዲያውም በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን ከተሠሩ መሣሪያዎች ሁሉ ይበልጥ የረቀቀ መሆኑን ደርሶበታል። ሴል ውስብስብ መሆኑ በዓላማ እንደተነደፈ ይጠቁማል።

      ንቁ!:- ዝግመተ ለውጥ በተፈጥሯዊ ምርጦሽ (NATURAL SELECTION) አማካኝነት እንዲህ ያለውን ውስብስብ የሞለኪውሎች ቅንብር ሊያስገኝ እንደሚችል ሳይንስ ማስረጃ ማቅረብ ችሏል?

      ፕሮፌሰር ቤሄ:- ሳይንሳዊ ጽሑፎችን ብትመረምር ሥራዬ ብሎ እንዲህ ያለ ሙከራ ያደረገ ሰው እንደሌለ ትገነዘባለህ። ይህንን ስል እንደ ሴል ያሉ ውስብስብ ነገሮች በዳርዊን ንድፈ ሐሳብ መሠረት እንዴት ሊገኙ እንደሚችሉ የሚያሳይ መጠነኛ ሙከራም ሆነ ዘርዘር ያለ ሳይንሳዊ ጥናት አልተደረገም ማለቴ ነው። የእኔ መጽሐፍ ከወጣ በኋላ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ እንደ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ እና የአሜሪካ ሳይንሳዊ እድገት ማኅበር ያሉት በርካታ ሳይንሳዊ ድርጅቶች፣ አባሎቻቸው የሕይወት ውስብስብነት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለውን ሐሳብ ለማስተባበል የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አስቸኳይ ጥሪ ቢያስተላልፉም እንኳ የተገኘ ውጤት የለም።

      ንቁ!:- ምንም ጥቅም የሌላቸው የሚመስሉ የዕፅዋት ወይም የእንስሳት አካል ክፍሎች መኖራቸው የንድፍ ጉድለት መኖሩን ይጠቁማል ለሚሉ ሰዎች ምን መልስ ይሰጣሉ?

      ፕሮፌሰር ቤሄ:- የአንድ ፍጡር የአካል ክፍል ምን ተግባር እንደሚያከናውን ስላላወቅን ብቻ ምንም ጥቅም የለውም ማለት አንችልም። ለምሳሌ ያህል፣ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ተደርገው የሚታዩ አንዳንድ ትናንሽ ብልቶች የሰውና የሌሎች ፍጥረታት አካላት የአሠራር ጉድለት ያለባቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ ተብሎ ይታሰብ ነበር። ለአብነት ያህል፣ በአንድ ወቅት ትርፍ አንጀትና እንጥል ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ተደርጎ ይታሰብ ስለነበረ ተቆርጠው ይወጡ ነበር። አሁን ግን እነዚህ ብልቶች በሽታን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ስለተደረሰበት ጥቅም እንደሌላቸው ተደርገው መታየታቸው ቀርቷል።

      ሊዘነጋ የማይገባው ሌላው ነገር በባዮሎጂ በአጋጣሚ የሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸው ነው። መኪናዬ ስርጉድ ያለ ነገር ስላለው ወይም ጎማው ስለሚተነፍስ ብቻ መኪናው ወይም ጎማው ታስቦበት አልተሠራም ለማለት አይቻልም። በተመሳሳይም በባዮሎጂ በአጋጣሚ የሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸው ሕይወትን የመሰለው ውስብስብ ነገር በአጋጣሚ ተገኘ ለማለት አያስደፍርም። እንዲህ ያለው ክርክር ፈጽሞ ምክንያታዊ አይደለም።

      [በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “በእኔ አመለካከት ተቀባይነት የሌለው ፍልስፍና ይሆናል በሚል ስሜት ጠንካራ ማስረጃ ያለውን መደምደሚያ ከመቀበል ወደኋላ ማለት ፈሪነት ነው”

  • የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?

      እውቅ የዝግመተ ለውጥ ሳይንቲስት የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዶውከንዝ “ዝግመተ ለውጥ የፀሐይን ትኩሳት ያህል የተረጋገጠ ሐቅ ነው” ብለዋል። ፀሐይ የምታቃጥል መሆኗን በሙከራም ሆነ ቀጥታ በመመልከት ማረጋገጥ እንደሚቻል የታወቀ ነው። ይሁንና በሙከራ አማካኝነትም ሆነ ቀጥታ በመመልከት የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ተጨባጭ ሐቅ መሆኑን በማያዳግም ሁኔታ ማረጋገጥ ይቻላል?

      ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አንድ ነገር ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። በርካታ ሳይንቲስቶች የእንስሳትም ሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች በጊዜ ሂደት መጠነኛ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ደርሰውበታል። ቻርልስ ዳርዊን ይህን ሂደት “በተከታታይ ለውጥ ያደረገ ዝርያ” በማለት ጠርቶታል። ዕፅዋትንና እንስሳትን የሚያዳቅሉ ሰዎች እንዲህ ያለውን ለውጥ ማየታቸው የተለመደ ከመሆኑም በላይ በሙከራ ሲያረጋግጡትና ዘዴውን ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።a በመሆኑም እንዲህ ያለው ለውጥ ተጨባጭነት ያለው ሐቅ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ሳይንቲስቶች እንዲህ ያለውን ትንንሽ ለውጥ “ማይክሮኢቮሉሽን” በማለት ይጠሩታል። ስያሜውም ራሱ እንደሚያመለክተው በርካታ ሳይንቲስቶች እነዚህ ትንንሽ ለውጦች ማክሮኢቮሉሽን ወደሚባል ማንም በዓይኑ ወዳላየው በጣም ትልቅ ለውጥ እንደሚሸጋገሩ ማስረጃ ይሆናሉ ብለው ያምናሉ።

      ይሁንና ዳርዊን ሊታዩ በሚችሉ በእነዚህ ለውጦች ብቻ አልተወሰነም። ዚ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ በተባለው ዝነኛ መጽሐፉ ላይ “እንደ እኔ አመለካከት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ የተለያዩ ፍጡራን ሳይሆኑ በቁጥር ጥቂት የሆኑ ሕያዋን ነገሮች ዝርያዎች ናቸው” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ውስብስብ እንዳልሆኑ ተደርገው የሚታሰቡት ‘እነዚህ ጥቂት ሕያዋን ነገሮች’ በጣም ረዥም በሆነ የጊዜ ሂደት “በጣም ጥቃቅን በሆኑ ለውጦች” አማካኝነት ቀስ በቀስ እየተለወጡ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች እንዳስገኙ ተናግሯል። የዝግመተ ለውጥ አስተማሪዎች እነዚህ ጥቃቅን ለውጦች ሲጠራቀሙ ትልልቅ ለውጦችን በማስገኘታቸው ዓሣዎች በየብስና በባሕር ወደሚኖሩ እንስሳት፣ ዝንጀሮዎች ደግሞ ወደ ሰው እንደተለወጡ ይናገራሉ። እንዲህ ያለው ትልቅ ለውጥ ማክሮኢቮሉሽን ተብሎ ይጠራል። ብዙዎች ይህ ሁለተኛ አባባል ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት ‘በአንድ ዝርያ (species) ውስጥ ጥቃቅን ለውጦች የሚከሰቱ ከሆነ ዝግመተ ለውጥ በረዥም የጊዜ ሂደት ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን ሊያስገኝ የማይችልበት ምን ምክንያት ይኖራል?’ በማለት ይጠይቃሉ።b

      የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት በሦስት ዋና ዋና ግምታዊ ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው:-

      1. የሚውቴሽን ሂደት አዳዲስ ዝርያዎችን ለመፍጠር የሚያስፈልገውን ጥሬ ዕቃ ያስገኛል።c

      2. አዳዲስ ዝርያዎች የሚገኙት በተፈጥሯዊ ምርጦሽ (natural selection) ምክንያት ነው።

      3. ወደ አለትነት በተለወጡ ቅሪተ አካላት ውስጥ ዕፅዋትና እንስሳት ያደረጉትን ማክሮኢቮሉሽናዊ ለውጥ የሚያሳይ መረጃ ይገኛል።

      ማክሮኢቮሉሽን ተጨባጭ ሐቅ ነው ለማለት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አለ?

      የሚውቴሽን ሂደት አዳዲስ ዝርያዎችን ሊያስገኝ ይችላል?

      የአንድ ተክል ወይም እንስሳ ዝርዝር ባሕርይ በአብዛኛው የሚወሰነው በእያንዳንዱ ሴል ኒውክሊየስ ውስጥ የሚገኘው ጂን በሚሰጠው መመሪያ ነው።d በእነዚህ የጂን ባሕርያት ላይ በየጊዜው የሚደርሰው ሚውቴሽን ወይም ድንገተኛ ለውጥ በእንስሳቱ ወይም በዕፅዋቱ የወደፊት ዝርያዎች ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። የሚውቴሽን ጄኔቲክስ ጥናት መሥራችና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ኸርማን ሙለር በ1946 “ከስንት አንዴ የሚከሰቱት እነዚህ ጥቃቅን ለውጦች ተጠራቅመው እንስሳትንና ዕፅዋትን በሰው ሠራሽ ዘዴዎች ለማሻሻል ከማስቻላቸውም በላይ በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት ተፈጥሯዊው ዝግመተ ለውጥ እንዲካሄድ መንገድ ጠርገዋል” በማለት ተናግረዋል።

      በእርግጥም የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት ሚውቴሽን አዳዲስ ዝርያዎችን (species) ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆኑ የዕፅዋትና የእንስሳት ቤተሰቦችን (families) ሊያስገኝ ይችላል በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ታዲያ ይህን የድፍረት አነጋገር በሙከራ ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ይኖራል? ለ100 ዓመት ያህል በጄኔቲክስ የምርምር መስክ የተደረገ ጥናት ያስገኘውን ውጤት እንመልከት።

      በ1930ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ሳይንቲስቶች ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በሚውቴሽን አማካኝነት አዳዲስ የዕፅዋት ዝርያዎችን ማስገኘት ከቻለ ሰዎች በምርጫቸው የሚያካሂዱት ሚውቴሽን ወይም ለውጥ ይበልጥ ውጤታማ መሆን አለበት የሚል ስሜት አድሮባቸው ነው። ጀርመን ውስጥ የማክስ ፕላንክ ዕፅዋትን የማዳቀል ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ቮልፍ ኢከሃርት ሎኒግ ከንቁ! መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አብዛኞቹ ባዮሎጂስቶች፣ በተለይ ደግሞ የጄኔቲክስ ተመራማሪዎችና አዳቃዮች በደስታ ፈንጥዘው” ነበር ብለዋል። እንዲህ ያስፈነጠዛቸው ምን ነበር? ለ28 ዓመታት በዕፅዋት ሚውቴሽን የጄኔቲክስ መስክ የተሰማሩት ሎኒግ “እነዚህ ተመራማሪዎች ከዚያ በፊት ይሠራበት የነበረውን ዕፅዋትንና እንስሳትን የማዳቀል ዘዴ ሙሉ በሙሉ መለወጥ የሚችሉበት ጊዜ ላይ የደረሱ መስሏቸው ነበር። ሚውቴሽኖችን በማካሄድና ጠቃሚ የሆኑትን በመምረጥ አዳዲስና የተሻሉ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን ማግኘት የሚችሉ መስሏቸው ነበር” ብለዋል።e

      በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስያና በአውሮፓ የሚገኙ ሳይንቲስቶች የዝግመተ ለውጥን ሂደት እንደሚያፋጥኑ የታመነባቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰባቸው የምርምር ፕሮግራም ማካሄድ ጀመሩ። ከአርባ ለሚበልጡ ዓመታት ጥልቅ ምርምር ከተደረገ በኋላ ምን ውጤት ተገኘ? ፒተር ፎን ዜንግቡሽ የተባሉት ተመራማሪ “ምርምሩን ለማካሄድ በጣም ብዙ ገንዘብ ቢፈስም በጨረር አማካኝነት የጂኖችን ባሕርይ ለውጦ የተሻሉ ዝርያዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት በአብዛኛው ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል” ብለዋል። ሎኒግም እንዲሁ “በ1980ዎቹ ዓመታት፣ የዓለም ሳይንቲስቶች የነበራቸው ተስፋና ደስታ መጨረሻው ውድቀት ሆኗል። በምዕራባውያን አገሮች በሚውቴሽን አማካኝነት ማዳቀል ራሱን የቻለ የምርምር ዘርፍ መሆኑ ቀረ። በሚውቴሽን የተገኙ ዝርያዎች በሙሉ ለማለት ይቻላል ‘የማይፈለጉ ባሕርያት’ በማሳየት ወዲያው ሞተዋል ወይም ከተፈጥሮ ዝርያዎች የበለጡ ደካሞች ሆነው ተገኝተዋል” በማለት ተናግረዋል።f

      ያም ሆኖ ግን ስለ ሚውቴሽን በጥቅሉ ለማጥናት በፈጀው 100 ዓመትና በሚውቴሽን አማካኝነት ለማዳቀል የሚያስችል ምርምር ለማድረግ በወሰደው 70 ዓመት ጊዜ ውስጥ የተሰበሰበው መረጃ ሳይንቲስቶች ሚውቴሽን አዳዲስ ዝርያዎችን ለማስገኘት ስላለው ችሎታ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ሎኒግ መረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “ሚውቴሽን ነባሩን [የተክል ወይም የእንስሳ] ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ዝርያ ሊለውጥ አይችልም። ይህ መደምደሚያ በ20ኛው መቶ ዘመን ከተደረጉ የሚውቴሽን ምርምሮች ከተገኙት ተሞክሮዎችና ውጤቶች እንዲሁም ከሒሳብ ሕግ ጋር ይስማማል። በመሆኑም ይህ ሕግ (ሎው ኦቭ ሪከረንት ቬሪዬሽን) በግልጽ የታወቀ የጂን ባሕርይ ያላቸው ዝርያዎች በድንገተኛ ሚውቴሽን ምክንያት ሊፈርስ ወይም ሊጣስ የማይችል ድንበር እንዳላቸው ይጠቁማል።”

      ከላይ የሠፈሩት ሐቆች ምን አንድምታ እንደሚኖራቸው እንመልከት። ከፍተኛ ሥልጠና የተሰጣቸው ሳይንቲስቶች በሰው ሠራሽ ዘዴዎች ተጠቅመውና የተሻሉ የሚውቴሽን ውጤቶችን መርጠው አዳዲስ ዝርያዎችን ማስገኘት ካልቻሉ ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌለው ሂደት የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ሚውቴሽን አንድን ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ መለወጥ እንደማይችል በምርምር ከተረጋገጠ ማክሮኢቮሉሽን ተካሄደ ተብሎ የሚታሰበው እንዴት ነው?

      ተፈጥሯዊ ምርጦሽ አዳዲስ ዝርያዎችን ያስገኛል?

      ዳርዊን ናቹራል ሴሌክሽን ወይም ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በማለት የጠራው ሂደት ከአካባቢያቸው ጋር በሚገባ የተላመዱትን ዝርያዎች ሲጠቅም ያልተላመዱት ግን ቀስ በቀስ ሞተው እንዲያልቁ ያደርጋል ብሎ ያምን ነበር። በዘመናችን ያሉ የዝግመተ ለውጥ ምሁራን፣ ዝርያዎች በሚሰራጩበትና በተወሰኑ አካባቢዎች ተለይተው መኖር በሚጀምሩበት ጊዜ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ለአዲሱ አካባቢ ይበልጥ ምቹ የሆነ የጂን ለውጥ ያደረጉ ዝርያዎችን ብቻ ይመርጣል ብለው ያስተምራሉ። ከዚህም በላይ እነዚህ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆኑ ዝርያዎች ቀስ በቀስ እንደሚቀየሩ ያምናሉ።

      ቀደም ሲል እንደተገለጸው የሚውቴሽን ሂደት ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆኑ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን ሊያስገኝ እንደማይችል በምርምር የተገኙ መረጃዎች አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎቹ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ጠቃሚ ሚውቴሽኖችን እየመረጠ አዳዲስ ዝርያዎችን ያስገኛል ለሚለው ሐሳባቸው ምን ማስረጃ ማቅረብ ይችላሉ? የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ በ1999 ያወጣው አንድ ብሮሹር “አዳዲስ ዝርያዎች እንደሚገኙ አሳማኝ ማስረጃ የሚሆነን በአሁኑ ጊዜ የዳርዊን ፊንቾች በሚባሉትና ዳርዊን በጋላፓጎስ ደሴቶች ላይ ጥናት ባካሄደባቸው 13 የድንቢጥ ዝርያዎች ላይ የታየው ሁኔታ ነው” በማለት ተናግሯል።

      በ1970ዎቹ ዓመታት በፒተርና በሮዝሜሪ ግራንት የሚመራ የምርምር ቡድን ፊንች በሚባሉት በእነዚህ የአእዋፍ ዝርያዎች ላይ ባደረገው ጥናት ከአንድ ዓመት የድርቅ ዘመን በኋላ ትናንሽ መንቆር ወይም አፍ ካላቸው ፊንቾች ይልቅ ትላልቅ መንቆር ያላቸው ፊንቾች ድርቁን መቋቋም እንደቻሉ ተገነዘበ። የዚህ ወፍ አሥራ ሦስቱ ዝርያዎች ተለይተው ከሚታወቁባቸው መንገዶች አንዱ የመንቆራቸው መጠንና ቅርጽ በመሆኑ ይህ ግኝት ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ተብሎ ታስቦ ነበር። ብሮሹሩ በመቀጠል “ፒተርና ሮዝሜሪ በደሴቶቹ ላይ በየአሥር ዓመቱ ድርቅ ቢከሰት አዲስ የፊንች ዝርያ ሊገኝ የሚችለው በ200 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ የሚገልጽ ግምታዊ ሐሳብ ሰንዝረዋል” በማለት አስፍሯል።

      ይሁን እንጂ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚው ያዘጋጀው ብሮሹር ከዚህ ጋር የሚጋጩ አንዳንድ ሐቆችን ሳይጠቅስ አልፏል። ከድርቁ በኋላ ባሉት ዓመታት፣ ትናንሽ መንቆር ያላቸው ፊንቾች ትላልቅ መንቆር ካላቸው ይልቅ በዝተው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት ፒተር ግራንት እና የድኅረ ምረቃ ተማሪ የሆነው ላይል ጊብስ ኔቸር በተባለው የሳይንስ መጽሔት ላይ በ1987 “ምርጫው ወደኋላ ሲመለስ” እንደተመለከቱ ጽፈዋል። ግራንት በ1991 “ተፈጥሯዊ ምርጦሽ የተደረገባቸው አእዋፍ ብዛት” የአየሩ ሁኔታ በተለወጠ ቁጥር “ሲለዋወጥ ኖሯል” ሲሉ ጽፈዋል። በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ የተለያዩ የፊንች “ዝርያዎች” እርስ በርስ ተዋልደው ችግር የመቋቋም አቅም ያላቸው ዝርያዎች እንዳስገኙ አስተውለዋል። ፒተርና ሮዝሜሪ ግራንት እነዚህ ዝርያዎች እርስ በርስ መዳቀላቸውን ቢቀጥሉ በ200 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት “ዝርያዎች” አንድ ይሆናሉ ሲሉ ደምድመዋል።

      የዝግመተ ለውጥ ባዮሎጂስት የሆኑት ጆርጅ ክሪስቶፈር ዊልያምስ በ1966 “መጀመሪያውኑም ቢሆን የተፈጥሯዊ ምርጦሽ ንድፈ ሐሳብ ለዝግመተ ለውጥ ማስረጃ ተደርጎ መቅረቡ አሳዛኝ ነገር ይመስለኛል። የበለጠ ማስረጃ የሚሆነው ሕያዋን ፍጥረታት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ ሲሉ ለሚያደርጉት ለውጥ ነው” በማለት ጽፈዋል። በ1999፣ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አስተማሪ የሆኑት ጀፍሪ ሽዋርዝ፣ ዊልያም የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል ከሆነ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ዝርያዎች በአካባቢያቸው የሚከሰተውን ለውጥ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል እንጂ “ምንም ዓይነት አዲስ ነገር አይፈጥርም” ሲሉ ጽፈዋል።

      በእርግጥም የዳርዊን ፊንቾች ወደ “አዲስ ነገር” አልተለወጡም። አሁንም ቢሆን ያው ፊንቾች ናቸው። እርስ በርስ መዋለዳቸው ደግሞ አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አማኞች የዝርያዎችን (species) አመጣጥ ለማብራራት በሚሞክሩበት ዘዴ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጓል። በተጨማሪም ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የሳይንስ ተቋማት እንኳ ሳይቀሩ መረጃዎችን አዛብተው ከማቅረብ ወደኋላ እንደማይሉ ይጠቁማሉ።

      ቅሪተ አካላት የማክሮኢቮሉሽን ማስረጃዎችን ይዘዋል?

      ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ ያዘጋጀው ከላይ የተጠቀሰው ብሮሹር አንባቢያን፣ ሳይንቲስቶች ያገኟቸው ቅሪተ አካላት የማክሮኢቮሉሽንን ሂደት በሚገባ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘዋል የሚል ግንዛቤ እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ሐሳብ ይዟል። እንዲህ ይላል:- “በዓሦች እና በየብስና በባሕር ሊኖሩ በሚችሉ ፍጥረታት፣ በየብስም ሆነ በባሕር ሊኖሩ በሚችሉት እንስሳትና በተሳቢ እንስሳት፣ በተሳቢ እንስሳት እና በአጥቢ እንስሳት እንዲሁም በዝንጀሮ መሰል እንስሳት የተለያዩ ትውልዶች መካከል ያሉ በርካታ የመሸጋገሪያ እንስሳት ዝርያዎች በመገኘታቸው ከአንዱ ዝርያ ወደ ሌላው ሽግግር የተደረገበትን ጊዜ በትክክል ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል።”

      እንዲህ ያለው የድፍረት አነጋገር በእጅጉ የሚያስገርም ነው። ለምን? ናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት በ2004 ቅሪተ አካላት ይዘውታል የሚባለው መረጃ “ከ1,000 የፊልም ጥብጣቦች ውስጥ 999ኙ በማቀናበሪያ ክፍል ውስጥ ከጠፉበት የዝግመተ ለውጥ ፊልም” ጋር እንደሚመሳሰል ገልጿል። ታዲያ ቀሪው አንድ “ጥብጣብ” የማክሮኢቮሉሽንን ሂደት በትክክል መዝግቦ ይዟል ለማለት ይቻላል? የቅሪተ አካላት መረጃ ምን ያሳያል? ዝግመተ ለውጥን በጥብቅ የሚደግፉት ናይልስ ኤልድሪጅ ለብዙ ዘመናት “በአብዛኞቹ ዝርያዎች ላይ ምንም ዓይነት አዝጋሚ ለውጥ አልታየም ለማለት ይቻላል” በማለት መረጃው የሚያመለክተውን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።

      እስከዛሬ ድረስ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሳይንቲስቶች 200 ሚሊዮን የሚያህሉ ትላልቅ ቅሪተ አካላትንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን ቅሪተ አካላትን ቆፍረው በማውጣት መዝግበው ይዘዋል። ብዙ ተመራማሪዎች ይህ እጅግ ትልቅና ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ መዝገብ ዋነኞቹ የእንስሳት ዝርያዎች በሙሉ ድንገት በአንድ ጊዜ እንደተገኙና ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይታይባቸው እንደኖሩ፣ ብዙ ዝርያዎች ደግሞ በተገኙበት ቅጽበት በድንገት መጥፋታቸውን እንደሚያረጋግጥ ይስማማሉ። ጆናታን ዌልስ የተባሉት ባዮሎጂስት የቅሪተ አካላትን ማስረጃ ከመረመሩ በኋላ “በኪንግደም፣ በፋይለምና በክላስ ደረጃ ከአንድ የጋራ ቅድመ አያት የመጣ የለውጥ ሂደት መኖሩን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ የለም። ቅሪተ አካላትንና ሞለኪውላዊ መረጃዎችን መሠረት አድርገን ስንመለከተው ጥሩ ድጋፍ ያለው ንድፈ ሐሳብ ነው ለማለት እንኳን አይቻልም” ብለዋል።

      የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው ወይስ ፈጠራ?

      ብዙ እውቅ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ማክሮኢቮሉሽን የተረጋገጠ ሐቅ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱት ለምንድን ነው? ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ሪቻርድ ለዎንተን የሪቻርድ ዶውከንዝን አንዳንድ ማብራሪያዎች ከተቹ በኋላ ብዙ ሳይንቲስቶች ምክንያታዊ ያልሆኑ ሳይንሳዊ ድምዳሜዎችን የሚቀበሉት “በቁስ አካላዊነት (materialism) ለማመን ቃል ስለገባን ነው” ሲሉ ጽፈዋል።g ለዎንተን “መለኮታዊ እግር በራችን እንዲደርስ መፍቀድ አንችልም” ሲሉ መጻፋቸው ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ መኖሩን ማሰብ እንኳን እንደማይፈልጉ ያሳያል።

      በዚህ ረገድ፣ ሮድኔይ ስታርክ የተባሉት ሶሽዮሎጂስት በሳይንቲፊክ አሜሪካን ላይ “ሳይንሳዊ ሰው ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ከሃይማኖት ሰንሰለት ነጻ መውጣት አለብህ የሚለው አመለካከት ለሁለት መቶ ዓመታት ሲለፈፍ ቆይቷል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም ምርምር በሚያካሂዱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ “ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች ሃይማኖት አልባ በሆኑ ሰዎች ሲናቁ በመቆየታቸው አፋቸውን ዘግተው ለመኖር መርጠዋል” ብለዋል። ስታርክ እንዳሉት “[በሳይንሱ ማኅበረሰብ] ቁንጮዎች ዘንድ ሃይማኖት የሌላቸውን ሰዎች የመሸለም ዘይቤ አለ።”

      የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት እውነት ነው ብለህ የምትቀበል ከሆነ አምላክ የለሽ የሆኑ ሳይንቲስቶች ሳይንሳዊ ግኝቶችን በሚተረጉሙበት ጊዜ የግል እምነታቸው ተጽዕኖ አያደርግባቸውም ብለህ ማመን ይኖርብሃል። በቢሊዮን በሚቆጠሩ የሚውቴሽን ሂደቶች ላይ አንድ መቶ ዓመት ለሚያክል ጊዜ በተካሄደው ጥናት ሚውቴሽን አንድን ነባር ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ ሊለውጥ አለመቻሉ በሚገባ ቢረጋገጥም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ በሚውቴሽንና በተፈጥሯዊ ምርጦሽ የተገኙ ናቸው ብለህ ማመን ይኖርብሃል። የቅሪተ አካላት መረጃዎች ዋነኞቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ድንገት በአንድ ጊዜ የተገኙ እንጂ ሕልቆ መሳፍርት በሌላቸው ዘመናት ውስጥ ከአንዱ ዝርያ ወደ ሌላው የተለወጡ አለመሆናቸውን አበክረው ቢያመለክቱም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ከአንድ የጋራ ቅድመ አያት እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው ብለህ ማመን አለብህ። ታዲያ እንዲህ ያለው እምነት በተጨባጭ ሐቅ ላይ የተመሠረተ ይመስልሃል? ወይስ ተረት ነው?

      [የግርጌ ማስታወሻዎች]

      a ውሻ የሚያዳቅሉ ሰዎች የሚፈልጉትን እየመረጡ በማዳቀል ከጊዜ በኋላ አጠር ያሉ እግሮች ወይም ረዘም ያለ ፀጉር ያላቸው ውሾች እንዲወለዱ ማድረግ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የሚያስገኙት ለውጥ አንዳንድ ጂኖችን ከጥቅም ውጭ በማድረጋቸው ምክንያት የመጣ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዳክስሁንድ የሚባለው የውሻ ዝርያ በጣም ድንክዬ የሆነው ለስላሳ አጥንቶቹ (cartilage) ተገቢውን እድገት ማድረግ ስላልቻሉ ነው።

      b በዚህ ርዕስ ውስጥ “ዝርያ” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢጠቀስም ቃሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደማይገኝ ልብ ሊባል ይገባዋል። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ከዚህ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ‘ወገን’ የሚለው ቃል ነው። ብዙውን ጊዜ ሳይንቲስቶች በዝግመተ ለውጥ አዳዲስ ዝርያዎች ተገኝተዋል የሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወገን’ በሚለው ውስጥ ያለውን ልዩነት በማየት ነው።

      c “ሕይወት ያላቸው ነገሮች በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡት እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      d የአንድን ሕያው አካል ቅርጽና ተግባር በመወሰን ረገድ የአንድ ሴል ሳይቶፕላዝም፣ የውጭ ሽፋንና ሌሎች ነገሮች የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል።

      e በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሰው የሎኒግ አስተያየት የራሳቸው እንጂ የማክስ ፕላንክን የምርምር ተቋም የሚወክል አይደለም።

      f በሚውቴሽን ላይ የተደረጉት ሙከራዎች በተደጋጋሚ እንዳረጋገጡት በሚውቴሽን አማካኝነት አዳዲስ ባሕርያት ያላቸውን ዝርያዎች የማግኘቱ አጋጣሚ በጣም እየቀነሰ ሲሄድ ተመሳሳይ የባሕርይ ለውጥ ያደረጉ ዝርያዎችን የማግኘቱ አጋጣሚ ግን እየጨመረ መጥቷል። ሎኒግ ከዚህ ክስተት በመነሳት “ሎው ኦቭ ሪከረንት ቬሪዬሽን” (ተደጋግሞ የሚከሰት ልዩነት ደንብ) የሚባል ሕግ አውጥተዋል። በተጨማሪም ከዕፅዋት ሚውቴሽን ውጤቶች ውስጥ ለቀጣይ ምርምር ብቁ ሆነው የተገኙት ከ1 በመቶ ያነሱ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል የንግድ ጠቀሜታ እንዳላቸው የታመነባቸው ከ1 በመቶ ያነሱ ናቸው። እንስሳትን በሚውቴሽን በማዳቀል የተገኘውም ውጤት ከዚህ እጅግ የከፋ በመሆኑ ዘዴው ሥራ ላይ እንዳይውል ተደርጓል።

      g ቁስ አካላዊነት የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ ‘ብቸኛው ወይም መሠረታዊው ነባራዊ ሁኔታ የሚታየው ቁስ አካል ነው፤ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ጨምሮ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ወደ ሕልውና የመጡት ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ኃይል ፈጽሞ ጣልቃ ሳይገባባቸው ነው’ የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ያመለክታል።

      [በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “ሚውቴሽን አንድን ነባር [የተክል ወይም የእንስሳ] ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ ሊለውጥ አይችልም”

      [በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      በዳርዊን ፊንቾች ላይ የተደረገው ምርምር ግፋ ቢል ዝርያዎች ከአየሩ ጠባይ ጋር ለመላመድ ራሳቸውን እንደሚለዋውጡ ቢያሳይ ነው

      [በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ቅሪተ አካላት በያዙት መረጃ መሠረት ዋነኞቹ የእንስሳት ዝርያዎች ድንገት በአንድ ጊዜ የተገኙ ሲሆን ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይታይባቸው ኖረዋል

      [በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

      (መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )

      ሕይወት ያላቸው ነገሮች በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡት እንዴት ነው?

      ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከዝርያ (species) ተነስቶ እስከ ኪንግደም በሚደርስ እያደር እየሰፋ በሚሄድ ክፍል ይመደባሉ።h ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ በታች የተዘረዘረውን የሰውንና የትንኝን አመዳደብ ተመልከት።

      ሰው ትንኝ

      ስፒሽስ ሳፒየንስ ሜላኖጋስተር

      ጂነስ ሆሞ ድሮሶፊላ

      ፋሚሊ ሆሚኒድስ ድሮሶፊሊድስ

      ኦርደር ፕራይሜትስ ዲፕተራ

      ክላስ ማማልስ ኢንሴክትስ

      ፋይለም ኮርዴትስ አርትሮፖድስ

      ኪንግደም አኒማልስ አኒማልስ

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      h ማሳሰቢያ:- ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ዕፅዋትና እንስሳት “እንደየወገናቸው” ዘራቸውን እንደሚተኩ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:12, 21, 24, 25) ይሁን እንጂ “ወገን” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይንሳዊ ስያሜ ባለመሆኑ “ስፒሽስ” ከሚለው ቃል ጋር አንድ እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።

      [ምንጭ]

      ሰንጠረዡ ጆናታን ዌልስ ባዘጋጁት የዝግመተ ለውጥ ዋና ዋና ንድፈ ሐሳቦች—ሳይንሳዊ ናቸው ወይስ ተረት? ስለ ዝግመተ ለውጥ የምንሰጠው አብዛኛው ትምህርት ስህተት የሆነበት ምክንያት በተባለው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ የተመሠረተ ነው

      [በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

      የሚውቴሽን ውጤት የሆነች ትንኝ (ከላይ) የአካል ጉድለት ይኑራት እንጂ ያው ትንኝ ነች

      [ምንጭ]

      © Dr. Jeremy Burgess/Photo Researchers, Inc.

      [በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

      በዕፅዋት ላይ የተደረጉ የሚውቴሽን ሙከራዎች በተደጋጋሚ እንዳመለከቱት አዳዲስ ባሕርያት ያላቸውን ዝርያዎች የማግኘቱ አጋጣሚ በጣም እያነሰ ሲሄድ ተመሳሳይ ባሕርይ ያላቸው ዝርያዎች ቁጥር ግን ጨምሯል

      (የሚውቴሽን ውጤት የሆነው ይህ ተክል ትላልቅ አበቦች አሉት)

      [በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      From a Photograph by Mrs. J. M. Cameron/ U.S. National Archives photo

      [በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      የፊንች ራሶች:- © Dr. Jeremy Burgess/ Photo Researchers, Inc.

      [በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

      ዳይነሶር:- © Pat Canova/Index Stock Imagery; ቅሪተ አካላት:- GOH CHAI HIN/AFP/Getty Images

  • በፈጣሪ የምናምንበት ምክንያት
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • በፈጣሪ የምናምንበት ምክንያት

      በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ ሊቃውንት ፍጥረት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ እንደተንጸባረቀበት ያምናሉ። በምድር ላይ የሚኖሩ ሕያዋን ፍጥረታት እንዲያው በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው ብሎ ማመን ምክንያታዊ መስሎ አይታያቸውም። በዚህም ምክንያት በርካታ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች በፈጣሪ ያምናሉ።

      ከእነዚህ አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የግዑዙ ጽንፈ ዓለም ንድፍ አውጪና ፈጣሪ እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት አግኝተዋል። እነዚህ ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ለምንድን ነው? ንቁ! መጽሔት አንዳንዶቹን አነጋግሯቸዋል። የሰጡትን አስተያየት ለማወቅ መፈለግህ አይቀርም።a

      ‘ሕይወት ለመረዳት የሚከብድ ውስብስብነት አለው’

      ◼ ቮልፍ-ኤከሃርት ሎኒግ

      አጭር የሕይወት ታሪክ:- ላለፉት 28 ዓመታት በዕፅዋት ጄኔቲክ ሚውቴሽን መስክ ሳይንሳዊ ጥናት ሳካሂድ ቆይቻለሁ። ከእነዚህ ውስጥ 21ዱን ዓመታት የሠራሁት ኮሎኝ፣ ጀርመን በሚገኘው የማክስ ፕላንክ ዕፅዋትን የማዳቀል ምርምር ተቋም ውስጥ ነው። በተጨማሪም ለሠላሳ ዓመታት ያህል በክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ አገልግያለሁ።

      በጄኔቲክስ የጥናት መስክ ያካሄድኩት በሙከራ ላይ የተመሠረተ ምርምርም ሆነ እንደ ፊዚዮሎጂና ሞርፎሎጂ ባሉት የባዮሎጂ ትምህርት ዘርፎች ያደረግሁት ጥናት ሕይወት ለመረዳት የሚከብድ ውስብስብነት ያለው መሆኑን እንዳስተውል ረድቶኛል። በእነዚህ ዘርፎች ላይ ያደረግሁት ጥናት ሌላው ቀርቶ ሕይወት የተገነባባቸው በጣም ረቂቅ ነገሮች እንኳ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ሠሪ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያለኝን እምነት አጠንክሮልኛል።

      የሳይንሱ ማኅበረሰብ ሕይወት የተገነባባቸው ነገሮች በጣም ውስብስብ መሆናቸውን በሚገባ ያውቃል። ይሁን እንጂ እነዚህ አስደናቂ ሐቆች የሚቀርቡት የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ እንደሚደግፉ ተደርገው ነው። በእኔ አስተያየት ግን የመጽሐፍ ቅዱስን የፍጥረት ዘገባ ለማጣጣል ከሚቀርቡት የመከራከሪያ ነጥቦች መካከል በጣም ጠንካራ የሚባለው እንኳን በሳይንሳዊ መመዘኛ ሲለካ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አይገኝም። እነዚህን የመከራከሪያ ነጥቦች ለበርካታ ዓመታት መርምሬያለሁ። ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ባሕርይ በጥንቃቄ ካጠናሁና ጽንፈ ዓለሙ የሚገዛባቸው ሕግጋት ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚያመቻቹ ከመረመርኩ በኋላ በፈጣሪ ለማመን ተገድጃለሁ።

      ‘የምመለከታቸው ነገሮች በሙሉ ያለ ምክንያት የተገኙ አይደሉም’

      ◼ ባይረን ሊዮን ሜዶስ

      አጭር የሕይወት ታሪክ:- የምኖረው በዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን የምሠራው በብሔራዊ የበረራና ሕዋ አስተዳደር [NASA] በሌዘር ፊዚክስ የጥናት ዘርፍ ውስጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ የዓለምን የአየር ሁኔታና ሌሎች ፕላኔታዊ ክስተቶችን ለመቆጣጠርና ለማጥናት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥናት እካፈላለሁ። እንዲሁም በቨርጂንያ አካባቢ በሚገኘው በኪልማርኖክ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ።

      በምርምር ሥራዬ ብዙውን ጊዜ የፊዚክስ ሕግጋትን አጠናለሁ። አንዳንድ ነገሮች እንዴትና ለምን እንደሚከሰቱ ለመረዳት እፈልጋለሁ። በተሰማራሁበት የጥናት መስክ የምመለከታቸው ነገሮች በሙሉ ያለ ምክንያት የተገኙ እንዳልሆኑ የሚያረጋግጥልኝ ግልጽ መረጃ አገኛለሁ። በሳይንሳዊ መሥፈርት ሲመዘን በተፈጥሮ ያሉትን ነገሮች በሙሉ አምላክ እንደፈጠራቸው ማመኑ ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማኛል። የተፈጥሮ ሕግጋት ፈጽሞ ዝንፍ የማይሉ መሆናቸው ግሩም የማደራጀት ችሎታ ያለው ፈጣሪ ያወጣቸው መሆኑን እንዳምን ያስገድደኛል።

      እንዲህ ያለው መደምደሚያ ግልጽ ሆኖ ሳለ በጣም ብዙ ሳይንቲስቶች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት ለምንድን ነው? የዝግመተ ለውጥ አማኞች መረጃዎቹን የሚመዝኑት አስቀድመው ከደረሱበት መደምደሚያ አንጻር ስለሆነ ይሆን? ሳይንቲስቶች እንዲህ ማድረጋቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ በግልጽ የሚታይ ነገር ምንም ያህል አሳማኝ ቢሆን ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ያስችላል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል፣ በሌዘር ፊዚክስ ላይ ጥናት የሚያደርግ ሰው ብርሃን ብዙውን ጊዜ የሞገድነት ባሕርይ ስለሚታይበት ልክ እንደ ድምፅ ሞገድ ነው ብሎ ሊከራከር ይችላል። ይሁን እንጂ ብርሃን ፎቶንስ የሚባሉ ቅንጣቶች እንዳሉት የሚያሳይ ባሕርያትም ስላሉት ይህ መደምደሚያው የተሟላ አይሆንለትም። በተመሳሳይም ዝግመተ ለውጥ እውነት እንደሆነ አድርገው የሚከራከሩ ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የሚደርሱት ቁንጽል ሐቅ ይዘው ነው። በአእምሯቸው የያዙት ግምታዊ ሐሳብ መረጃዎቹን በሚመዝኑበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ይፈቅዳሉ።

      የዝግመተ ለውጥ “ሊቃውንት” ራሳቸው ዝግመተ ለውጥ በተከናወነበት መንገድ ላይ እርስ በርሳቸው እየተወዛገቡ ባሉበት በዚህ ጊዜ ንድፈ ሐሳቡን ተጨባጭ ሐቅ እንደሆነ አድርጎ የሚቀበል ሰው መኖሩ በጣም ያስገርመኛል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሊቃውንት 2 ሲደመር 2 አራት እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ግን 3 ወይም 6 ነው ብለው ቢከራከሩ ሒሳብ የተረጋገጠ ሐቅ ነው ብለህ ትቀበል ነበር? የሳይንስ ሚና በማስረጃ፣ በሙከራ እንዲሁም በሠርቶ ማሳያ ሊረጋገጥ የሚችለውን ብቻ መቀበል ከሆነ ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከአንድ የጋራ ቅድመ አያት ተገኝቷል የሚለው ንድፈ ሐሳብ ሳይንሳዊ ሐቅ አይደለም።

      “እንዲሁ በራሱ ሊገኝ የሚችል ምንም ነገር የለም”

      ◼ ኬኔት ሎይድ ታናካ

      አጭር የሕይወት ታሪክ:- ጂኦሎጂስት ስሆን በአሁኑ ጊዜ ፍላግስታፍ፣ አሪዞና የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የምድር ጥናት ተቋም ባልደረባ ነኝ። ለሠላሳ ዓመታት ለማለት ይቻላል፣ ሌሎች ፕላኔቶችን ጨምሮ በተለያዩ የምድር ጥናት መስኮች ላይ በሚደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ተካፍያለሁ። በርካታ የጥናት ጽሑፎቼና የማርስ ጂኦሎጂያዊ ካርታዎቼ እውቅ በሆኑ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ በማበረታታት በየወሩ 70 ሰዓት ያህል አሳልፋለሁ።

      በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እንዳምን የሚያደርግ ትምህርት የተሰጠኝ ቢሆንም ጽንፈ ዓለምን ለማስገኘት የሚያስፈልገው ብርቱ ኃይል እጅግ ኃያል ከሆነ ፈጣሪ ካልሆነ በስተቀር በራሱ ሊገኝ ይችላል ብዬ እንዳምን አላደረገኝም። እንዲሁ በራሱ ሊገኝ የሚችል ምንም ነገር የለም። በተጨማሪም የፈጣሪን መኖር የሚያሳምን ጠንካራ ማረጋገጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አግኝቻለሁ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተሰማራሁበት የሳይንስ ዘርፍ ጋር የሚስማሙ ምድር ክብ መሆኗንና “በባዶው ላይ” እንደተንጠለጠለች የሚገልጹ ሳይንሳዊ ሐቆችን አግኝቻለሁ። (ኢዮብ 26:7፤ ኢሳይያስ 40:22) እነዚህ ሐቆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉት ሰዎች በምርምር ከማረጋገጣቸው ከረዥም ዘመናት በፊት ነው።

      እስቲ የገዛ ራሳችንን አፈጣጠር እንመልከት። የስሜት ሕዋሳት፣ ማንነትን የማወቅ ችሎታ፣ ረቂቅ ነገሮችን የማስተዋል ችሎታ፣ ሐሳባችንን የመግለጽ ችሎታና የተለያዩ ስሜቶች አሉን። በተለይ ደግሞ የመውደድና የመወደድ እንዲሁም ሌሎች ስላሳዩን ፍቅር አድናቆታችንን የመግለጽ ችሎታ አለን። አስደናቂ የሆኑት እነዚህ የሰው ልጅ ችሎታዎች ከየት እንደተገኙ ከዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ማብራሪያ ማግኘት አንችልም።

      ‘የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ይደግፋሉ ተብለው የሚጠቀሱት የመረጃ ምንጮች ምን ያህል ተአማኒነት አላቸው?’ እያልን ራሳችንን እንጠይቅ። ከምድር ጥናት የተገኙት መረጃዎች ያልተሟሉና የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ ግራ የሚያጋቡ ናቸው። የዝግመተ ለውጥ አማኞች ተከናውኗል የሚሉትን ይህን ሒደት ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ተጠቅመው በቤተ ሙከራ ሊያረጋግጡልን አልቻሉም። ሳይንቲስቶች በአብዛኛው መረጃዎችን በሚያሰባስቡበት ጊዜ ጥሩ የምርምር ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ቢሆንም እነዚህን መረጃዎች በሚተነትኑበትና በሚተረጉሙበት ጊዜ ግን ራስ ወዳድነት ያሸንፋቸዋል። መረጃዎቹ አጠራጣሪ ወይም ተቃራኒ በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ የራሳቸውን አስተሳሰብ ማራመድ እንደሚቀናቸው የታወቀ ነው። ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡት ለተሰማሩበት የሥራ መስክና ለግል ዝናቸው ነው።

      ሳይንቲስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ትክክለኛ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ እንድችል በግልጽ ከታወቁና ከተረጋገጡ ሐቆች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማውን እውነት ለማግኘት እጥራለሁ። እኔ በበኩሌ ከሁሉም ይበልጥ ምክንያታዊ ሆኖ ያገኘሁት በፈጣሪ ማመን ነው።

      “በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ንድፍ”

      ◼ ፓውላ ኪንቸሎ

      አጭር የሕይወት ታሪክ:- በሴልና በሞለኪውል ባዮሎጂ እንዲሁም በማይክሮባዮሎጂ የምርምር ዘርፎች የበርካታ ዓመታት ልምድ አለኝ። በአሁኑ ጊዜ የምሠራው አትላንታ፣ ጆርጅያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኤመሪ ዩኒቨርሲቲ ነው። በተጨማሪም ለሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር ነጻ አገልግሎት እሰጣለሁ።

      በባዮሎጂ የጥናት ዘርፍ በሴልና በሴል ክፍሎች ላይ ብቻ አራት ዓመት የፈጀ ትምህርት ወስጃለሁ። ስለ ዲ ኤን ኤ፣ አር ኤን ኤ፣ ፕሮቲኖችና፣ ኬሚካላዊ ሂደቶች ባወቅሁ መጠን ሴሎች ስላላቸው ውስብስብነት፣ የተቀናጀ አሠራርና ትክክለኝነት ያለኝ አድናቆት ይጨምራል። የሰው ልጅ ስለ ሴሎች የደረሰበት የእውቀት ደረጃ በእጅጉ ቢያስደንቀኝም ገና ብዙ ያላወቃቸው ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። በአምላክ መኖር እንዳምን ያስገደደኝ በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ንድፍ ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ የፈጣሪን ማንነት አሳውቆኛል፤ ይህ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ይባላል። እርሱ ጥበበኛ ንድፍ አውጪ ብቻ ሳይሆን ለእኔ የሚያስብ ደግና አፍቃሪ አባት እንደሆነም ጭምር አሳምኖኛል። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ከመግለጹም በላይ የወደፊቱ ጊዜ አስደሳች እንደሚሆን ተስፋ ይሰጣል።

      በትምህርት ቤት ስለ ዝግመተ ለውጥ በመማር ላይ የሚገኙ ወጣቶች በምን ማመን እንደሚኖርባቸው ለመወሰን ይቸገሩ ይሆናል። እንዲህ ያለው ጊዜ ግራ የሚያጋባ ሊሆንባቸው ይችላል። በአምላክ የሚያምኑ ከሆነ ስለዚህ ንድፈ ሐሳብ ሲማሩ እምነታቸው ፈተና ላይ ይወድቃል። ይሁን እንጂ ይህን ፈተና በዙሪያችን ባለው ተፈጥሮ ውስጥ የሚንጸባረቁትን አስደናቂ ነገሮች በመመርመርና ስለ ፈጣሪና ስለ ባሕርያቱ ያላቸውን እውቀት በማሳደግ ሊወጡት ይችላሉ። እኔ በግሌ እንዲህ ስላደረግሁ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ዘገባ ትክክል እንደሆነ እንዲሁም ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር እንደማይጋጭ ለማመን ችያለሁ።

      ‘የተፈጥሮ ሕጎች ያልተወሳሰቡና ግልጽ ናቸው’

      ◼ ኤንሪኬ ኤርናንዴስ-ላሙስ

      አጭር የሕይወት ታሪክ:- በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነኝ። በተጨማሪም በሜክሲኮ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ንድፈ ሐሳቦች ተመራማሪ ነኝ። በአሁኑ ጊዜ ከዋክብት እንዲያድጉ የሚያደርገውን ግራቮተርማል ካታስትሮፍ የሚባለውን ክስተት እንቆቅልሽ የሚፈታ የቴርሞዳይናሚክስ ማብራሪያ ለማግኘት በሚደረገው ጥናት ላይ እካፈላለሁ። በተጨማሪም ዲ ኤን ኤ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ጥናት አካሂጃለሁ።

      በአጭሩ ሕይወት በጣም ውስብስብ በመሆኑ እንዲያው በአጋጣሚ ሊገኝ አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣ በዲ ኤን ኤ ሞለኪውል ውስጥ የሚገኘውን በጣም ሰፊ የመረጃ ክምችት እንመልከት። አንዲት ክሮሞዞም በራስዋ ልትገኝ የምትችልበት አጋጣሚ ቢበዛ ከ9 ትሪሊዮን አንድ በመሆኑ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም ማለት ይቀላል። ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌላቸው ኃይሎች አንድን ክሮሞዞም ብቻ ሳይሆን በሕያዋን ፍጥረታት ውስጥ የሚገኙትን በጣም ውስብስብ አሠራሮች በሙሉ አስገኙ ብሎ ማመን ሞኝነት እንደሆነ ይሰማኛል።

      በተጨማሪም በአጉሊ መነጽር ብቻ ሊታይ ከሚችለው አነስተኛ የቁስ አካል ቅንጣት አንስቶ በሕዋ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት በጣም ግዙፍ የደመና አካላት ውስጥ የሚታየውን እጅግ የተወሳሰበ ባሕርይ ሳጠና እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚመሩባቸው ሕጎች ያልተወሳሰቡና ግልጽ መሆናቸው ያስደንቀኛል። ለእኔ እነዚህ ሕግጋት የአንድ ታላቅ የሒሳብ ሊቅ ብቻ ሳይሆን ታላቅ የሥነ ጥበብ ሊቅ የሥራ ውጤቶች መሆናቸውን ያረጋግጡልኛል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ስነግራቸው ይደነቃሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዴት በአምላክ ታምናለህ ብለው ይጠይቁኛል። አብዛኞቹ ሃይማኖቶች አማኞቻቸው ስለሚማሯቸው ነገሮች ማስረጃ እንዲሰጣቸው እንዲጠይቁ ወይም ስለ እምነታቸው ምርምር እንዲያደርጉ ስለማያበረታቱ እንዲህ ቢሰማቸው አያስደንቅም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ እንድንጠቀም ያበረታታል። (ምሳሌ 3:21) ተፈጥሮ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ የተንጸባረቀበት መሆኑን የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው ማስረጃ ጋር ተዳምረው አምላክ እንዳለ ብቻ ሳይሆን ይህ አምላክ ጸሎቶቻችንን በትኩረት የሚያዳምጥ መሆኑን እንዳምን አድርገውኛል።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሊቃውንት የሰጡት አስተያየት የራሳቸውን እንጂ የሚሠሩበትን ተቋም አመለካከት የሚያንጸባርቅ አይደለም።

      [በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      በስተ ጀርባ የሚታየው የማርስ ምስል:- Courtesy USGS Astrogeology Research Program, http://astrogeology.usgs.gov

  • በዕፅዋት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ንድፎች
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • በዕፅዋት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ንድፎች

      ብዙ ዕፅዋት የሚያድጉት ክብ ቅርጽ ይዘው እንደሆነ አስተውለህ ታውቃለህ? ለምሳሌ አንድ አናናስ በአንድ አቅጣጫ የሚሄዱ 8 የቅርፊት ዙሮች፣ በተቃራኒው አቅጣጫ የሚሄዱ ደግሞ 5 ወይም 13 ዙሮች ሊኖሩት ይችላል። (ሥዕል 1ን ተመልከት።) በሱፍ አበባ ላይ ያሉትን ፍሬዎች ብትመለከት 55 እና 89 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ዙሮች አንዳቸው ሌላውን አቋርጠው ትመለከት ይሆናል። እንዲያውም በአበባ ጎመን ላይ ሳይቀር ዙሮች ልትመለከት ትችላለህ። ዕፅዋት ዙሮች እንዳላቸው ካወቅህበት ጊዜ አንስቶ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ መደብሮች የምትሄደው ለየት ያለ አመለካከት በመያዝ ይሆናል። ዕፅዋት በዚህ ሁኔታ የሚያድጉት ለምንድን ነው? የዙሮቹ ቁጥር የተለየ ትርጉም ይኖረው ይሆን?

      ዕፅዋት የሚያድጉት እንዴት ነው?

      አብዛኞቹ ዕፅዋት እንደ ግንድ፣ ቅጠልና አበባ የመሰሉትን አዳዲስ ክፍሎች የሚያወጡት አደግ (ሜሪስቴም) ከሚባል ማዕከላዊ ቦታ ነው። ፕሪሞርዲየም የሚባለው የተክሉ እያንዳንዱ አዲስ ክፍል ከማዕከላዊው ቦታ ወጥቶ በአዲስ አቅጣጫ በማደግ ከእርሱ በፊት ከተሠራው የተክሉ ክፍል ጋር ሲቀናጅ ማዕዘን ይሠራል።a (ሥዕል 2ን ተመልከት።) አብዛኞቹ ዕፅዋት አዳዲስ ክፍሎች የሚያወጡት ክብ ቅርጽ በሚያስገኝ ለየት ያለ ማዕዘን ነው። ይህ ማዕዘን ምንድን ነው?

      እስቲ ለሚከተለው ሁኔታ መፍትሄ ለማግኘት ሞክር:- ምንም ቦታ ሳታባክን አዳዲስ የተክል ክፍሎችን የመብቀያው ቦታ ላይ አጠጋግተህ ለመደርደር እየሞከርክ እንደሆነ አስብ። እያንዳንዱ አዲስ ፕሪሞርዲየም ከእርሱ በፊት ካደገው ጋር ሲነጻጸር የሙሉ ክብ ሁለት አምስተኛ በሚያክል ማዕዘን ላይ እንዲያድግ አደረግህ እንበል። ይህ ሁኔታ ችግር የሚያስከትል ሲሆን ይህም እያንዳንዱ አምስተኛ ፕሪሞርዲየም ከተመሳሳይ ቦታና በተመሳሳይ አቅጣጫ የሚያድግ መሆኑ ነው። በመደዳ የሚቀመጡ ፕሪሞርዲየሞች ስለሚኖሩ በመስመሮቹ መሃል ያለው ቦታ ይባክናል። (ሥዕል 3ን ተመልከት።) ማንኛውም የክቡ ሙሉ ክፍልፋይ ወይም ፍራክሽን መስመሮች እንዲፈጠሩ ስለሚያደርግ የሚባክን ቦታ መኖሩ አይቀርም። ቦታ ሳይባክን ጥቅጥቅ ብለው የሚያድጉበት ሁኔታ የሚፈጠረው “ወርቃማ ማዕዘን” በሚባለው 137.5 ዲግሪ ገደማ ላይ ብቻ ነው። (ሥዕል 5ን ተመልከት።) ይህን ማዕዘን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

      ወርቃማው ማዕዘን በጣም ተስማሚ የሆነው የአንድ ዙር ሙሉ ክፍልፋይ ሊሆን ስለማይችል ነው። የአንድ ሙሉ ዙር 5/8 ወደ እርሱ የተጠጋ ነው፣ 8/13ኛው ደግሞ ይበልጥ የተጠጋ ሲሆን 13/21ኛው ደግሞ ከዚያ ይበልጥ በጣም የሚቀርበው ቢሆንም የአንድ ዙር ወርቃማውን መጠን በትክክል ሊገልጽ የሚችል ክፍልፋይ ግን የለም። ስለዚህ በአደግ ላይ አንድ አዲስ ቅጠል ከእርሱ በፊት ካደገው ቅጠል በ137.5 ዲግሪ ማዕዘን ላይ ካደገ ሁለት ቅጠሎች ፈጽሞ በአንድ አቅጣጫ ሊያድጉ አይችሉም። (ሥዕል 4ን ተመልከት።) በዚህም ምክንያት ፕሪሞርዲያው እንደ ጨረር የሚወጣ ከመሆን ይልቅ ጥምዝ ቅርጽ ይኖረዋል።

      በኮምፒውተር እገዛ የተሠራ ከአንድ ማዕከላዊ ቦታ የሚነሳ የፕሪሞርዲያ እድገት የሚያሳዩ ሥዕሎች ተለይተው የሚታዩ ዙሮች የሚኖሯቸው በአዳዲስ እድገቶች መካከል የሚኖረው ማዕዘን ትክክል ሲሆን ብቻ ነው። ከወርቃማው ማዕዘን በአንድ አሥረኛ ዲግሪ እንኳን ዝንፈት ቢፈጠር ተመሳሳይ ውጤት ሊገኝ አይችልም።—ሥዕል 5ን ተመልከት።

      በአንድ አበባ ላይ የሚኖሩ መልካ አበቦች ስንት ናቸው?

      በወርቃማ ማዕዘን ላይ የተመሠረተ እድገት በሚኖርበት ጊዜ የመልካ አበቦች ቁጥር የፊቦናቺ ሥርዓት የሚባለውን ሕግ ይከተላል። ይህ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው በ13ኛው መቶ ዘመን ይኖር በነበረው ሊዮናርዶ ፊቦናቺ በተባለ የሂሣብ ሊቅ ነው። በዚህ ሥርዓት መሠረት ከ1 በኋላ ያለው እያንዳንዱ ቁጥር ከፊቱ ያሉት ሁለት ቁጥሮች ድምር ሲሆን ይህም እንደሚከተለው ነው—1, 1, 2, 3, 5, 8, 13, 21, 34, 55 ወዘተ።

      ክብ ቅርጽ ይዘው የሚያድጉ የብዙ ዕፅዋት አበቦች አብዛኛውን ጊዜ የፊቦናቺን ሥርዓት የተከተለ የመልካ አበቦች ቁጥር አሏቸው። የዕፅዋቱን ባሕርይ የሚከታተሉ አንዳንዶች እንዳሉት በአብዛኛው የቀጋ አበቦች 5 መልካ አበቦች፣ ብለድሩትስ የተባለው አበባ 8፣ ፋየርዊድስ 13፣ ኤስተርስ 21፣ በየቦታው የሚገኘው ዴይዚ 34 እንዲሁም ማይክልማስ ዴይዚ 55 ወይም 89 መልካ አበቦች አሏቸው። (ሥዕል 6ን ተመልከት።) ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በአብዛኛው የፊቦናቺን ሥርዓት የሚከተል ገጽታ አላቸው። ለምሳሌ ሙዝ ከመሃል ተቆርጦ ሲታይ አምስት ጎኖች አሉት።

      ‘ሁሉንም ነገር ውብ አድርጎ ሠራው’

      የሥነ ጥበብ ሰዎች እንደ ወርቃማው ማዕዘን ለዓይናችን እጅግ አምሮ የሚታይ ሥርዓት እንደሌለ ከተገነዘቡ ብዙ ጊዜ ሆኗል። ዕፅዋት ይህን ምሥጢራዊ ማዕዘን ተከትለው እንዲያድጉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች ይህ አንድ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ መኖሩን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ እንደሆነ ያምናሉ።

      ብዙዎች የሕያዋን ነገሮችን አፈጣጠርና እኛም በእነዚህ ፍጥረታት ለመደሰት በመቻላችን ላይ ሲያሰላስሉ በሕይወት እንድንደሰት የሚፈልግ ፈጣሪ መኖሩን ይገነዘባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን ሲናገር “ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” ይላል።—መክብብ 3:11

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a የሚገርመው ነገር፣ በሱፍ አበባ ላይ የሚያድጉ ወደ ሱፍ ፍሬነት የሚለወጡ ትንንሽ አበቦች ክብ ቅርጽ መሥራት የሚጀምሩት ከመካከል ሳይሆን ከዳር መሆኑ ይህን አበባ ከሌሎቹ ዕፅዋት የተለየ ያደርገዋል።

      [በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

      ሥዕል 1

      (ጽሑፉን ተመልከት)

      ሥዕል 2

      (ጽሑፉን ተመልከት)

      ሥዕል 3

      (ጽሑፉን ተመልከት)

      ሥዕል 4

      (ጽሑፉን ተመልከት)

      ሥዕል 5

      (ጽሑፉን ተመልከት)

      ሥዕል 6

      (ጽሑፉን ተመልከት)

      [በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      አደግ (ሜሪስቴም) ጎልቶ ሲታይ

      [በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      R. Rutishauser, University of Zurich, Switzerland

      [በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      ነጭ አበባ:- Thomas G. Barnes @ USDA-NRCS PLANTS Database

  • የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል?

      ሕይወት ዓላማ ያለው ይመስልሃል? የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ከሆነ ሳይንቲፊክ አሜሪካን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣው “በዚህ ዘመን ስለ ዝግመተ ለውጥ ያለን ግንዛቤ . . . ይህ ነው የሚባል የሕይወት ዓላማ እንደሌለ ይጠቁማል” የሚለው ሐሳብ ትክክል ነው ማለት ነው።

      እነዚህ ቃላት ምን አንድምታ እንደሚኖራቸው እንመልከት። ይህ ነው የሚባል የሕይወት ዓላማ ከሌለ በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ በጎ ሥራዎችን ለመሥራት ከመጣጣር ምናልባትም በዘር የሚተላለፉ ባሕርያትን ለቀጣዩ ትውልድ ከማስተላለፍ የዘለለ ዓላማ የለህም ማለት ነው። አንድ ጊዜ ከሞትክ በኋላ ለዘላለም ጠፍተህ ትቀራለህ። የማሰብ፣ ምክንያቶችን የማገናዘብና በሕይወት ትርጉም ላይ የማሰላሰል ችሎታ ያለው አንጎልህ ተፈጥሮ በአጋጣሚ ያስገኘው ነገር ይሆናል።

      ይህ ብቻ ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ወይ አምላክ የለም፣ ቢኖርም በሰው ልጆች ጉዳይ እጁን ጣልቃ አያስገባም ይላሉ። እንደ ሁለቱም ሐሳቦች ከሆነ የወደፊት ዕጣችን በፖለቲከኞች፣ በምሑራንና በሃይማኖት መሪዎች እጅ የወደቀ ይሆናል። የእነዚህ ቡድኖች ያለፈ ታሪክ ሲታይ ሰብዓዊውን ማኅበረሰብ እንደ ነቀዝ እየበላው ያለው ምስቅልቅል፣ ግጭትና ሙስና መቀጠሉ አይቀርም። በእርግጥም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ቢሆን ኖሮ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” የሚለውን አደገኛ መርህ የምንከተልበት በቂ ምክንያት ይኖረን ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:32

      ሆኖም ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ከላይ በተገለጹት አባባሎች አይስማሙም። ከዚህም ሌላ ለእነዚህ አባባሎች ምንጭ የሆነውን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አይቀበሉም። በአንጻሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነ ያምናሉ። (ዮሐንስ 17:17) ስለሆነም “የሕይወት ምንጭ ከአንተ [ከአምላክ] ዘንድ ነው” በማለት እንዴት እንደተፈጠርን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ያምናሉ። (መዝሙር 36:9) እነዚህ ቃላት ከፍተኛ አንድምታ አላቸው።

      ሕይወት በእርግጥ ትርጉም አለው። ፈጣሪያችን ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው ለመኖር ለሚመርጡ ሁሉ ፍቅራዊ ዓላማ አለው። (መክብብ 12:13) ይህ ዓላማ ከምስቅልቅል፣ ከግጭትና ከሙስና ሌላው ቀርቶ ከሞት እንኳ ሙሉ በሙሉ በጸዳ ዓለም የመኖር ተስፋን ይጨምራል። (ኢሳይያስ 2:4፤ 25:6-8) በመላው ዓለም የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መማርና የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከምንም በላይ ሕይወት ትርጉም እንዲኖረው እንደሚያደርግ መመሥከር ይችላሉ።—ዮሐንስ 17:3

      የምታምንበት ነገር የአሁኑን ደስታህን ብቻ ሳይሆን የወደፊት ሕይወትህን ጭምር ስለሚነካ በእርግጥም የሚያመጣው ለውጥ አለ። ምርጫው ለአንተ የተተወ ነው። የምታምነው ተፈጥሮ የረቀቀ ችሎታ ባለው አንድ ንድፍ አውጪ እንደተሠራ የሚያረጋግጡትን እየጨመሩ የመጡ ማስረጃዎች ማስተባበል ባልቻለው ንድፈ ሐሳብ ነው? ወይስ ምድርና በምድር ላይ የሚኖሩት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ‘ሁሉን የፈጠረው’ የይሖዋ አምላክ አስደናቂ የእጅ ሥራ መሆናቸውን በሚናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ?—ራእይ 4:11

  • ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

      ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?

      ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ስለ ፍጥረት የሚገልጸው ዘገባ ሐሰት መሆኑን ሳይንስ እንዳረጋገጠ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ግጭት የተፈጠረው በሳይንስና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ሳይሆን በሳይንስና ወግ አጥባቂ ክርስቲያኖች ተብለው በሚጠሩት ሃይማኖታዊ ወገኖች እምነት መካከል ነው። ከእነዚህ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ፣ ግዑዙ ፍጥረት በሙሉ ከ10,000 ዓመታት በፊት እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል ብለው በሐሰት ይናገራሉ።

      መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን አባባል አይደግፍም። ይህ ቢሆን ኖሮ ባለፈው መቶ ዓመት ሳይንስ የደረሰባቸው ብዙ ግኝቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ላይ የጥርጣሬ ደመና ያጠሉ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ላይ የተደረገ ጥንቃቄ የታከለበት ጥናት ይህ ሐሳብ ከተረጋገጡ ሳይንሳዊ ሐቆች ጋር እንደማይጋጭ ያሳያል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ከወግ አጥባቂ “ክርስቲያኖች” እና ከብዙዎቹ ክሪኤሽኒስቶች (የፍጥረት አማኞች) ጋር አይስማሙም። ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ትንታኔ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ምን እንደሆነ ያሳያል።

      “በመጀመሪያ” የተባለው የትኛው ጊዜ ነው?

      የዘፍጥረት ዘገባ የሚጀምረው “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው ቀላል፣ ሆኖም ብዙ መልእክት የያዘ አገላለጽ ነው። (ዘፍጥረት 1:1) በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው ድርጊት ከቁጥር 3 ጀምሮ በተተረኩት የፍጥረት ቀናት ውስጥ እንደማይካተት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይስማማሉ። ይህም ትልቅ ትርጉም አለው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት መረዳት እንደሚቻለው የፍጥረት ቀናት ከመጀመራቸው በውል ተለይተው ከማይታወቁ ዘመናት አስቀድሞ፣ አጠቃላዩ ጽንፈ ዓለም ተፈጥሯል፤ ይህ ፕላኔቷ ምድራችንንም ይጨምራል።

      ጂኦሎጂስቶች የምድር ዕድሜ 4 ቢሊዮን ዓመት እንደሚሆን የሚገምቱ ሲሆን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ደግሞ የጽንፈ ዓለም ዕድሜ 15 ቢሊዮን ዓመት እንደሚሆን የሚገልጽ ስሌት ሠርተዋል። ታዲያ እነዚህ ግኝቶችም ሆኑ በዚህ ረገድ ወደፊት የሚደረጉ ማሻሻያዎች ከዘፍጥረት 1:1 ጋር ይጋጫሉ? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሰማያትንና የምድርን’ ትክክለኛ ዕድሜ ለይቶ አይናገርም። በዚህም ምክንያት ሳይንስ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስሕተት መሆኑን አያሳይም።

      የፍጥረት ቀኖች ርዝማኔያቸው ምን ያህል ነበር?

      ስለ ፍጥረት ቀናት ርዝማኔስ ምን ሊባል ይችላል? የእያንዳንዳቸው ርዝማኔ ቃል በቃል 24 ሰዓት ነው? አንዳንዶች የዘፍጥረት ጸሐፊ የሆነው ሙሴ ከጊዜ በኋላ ስለ ሳምንታዊው ሰንበት ሲናገር፣ ከስድስቱ የፍጥረት ቀናት በኋላ ያለው ሰባተኛው ቀን ለሰንበት እንደ ምሳሌ መሆኑን ስለጠቀሰ እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ርዝማኔው ቃል በቃል 24 ሰዓት ነው ይላሉ። (ዘፀአት 20:11) ታዲያ የዘፍጥረት ዘገባ ይህን አባባል ይደግፋል?

      በፍጹም። “ቀን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል 24 ሰዓትን ብቻ ሳይሆን የተለያየ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ የአምላክን የፍጥረት ሥራ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ ስድስቱንም ቀናት እንደ አንድ ቀን አድርጎ ጠቅሷል። (ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን “እግዚአብሔርም ብርሃኑን ‘ቀን’፣ ጨለማውን ‘ሌሊት’ ብሎ ጠራው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:5) እዚህ ላይ “ቀን” ተብሎ የተገለጸው ከ24 ሰዓት ውስጥ ከፊሉ ጊዜ ብቻ ነው። እንግዲያው፣ የእያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ርዝማኔ 24 ሰዓት ነው ብሎ በጭፍን ለመናገር የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም።

      ታዲያ የፍጥረት ቀኖቹ ርዝማኔ ምን ያህል ነበር? በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1 እና 2 ላይ የተሠራባቸው ቃላት እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን ረዥም ዘመናትን እንደሚያመለክት ይጠቁማሉ።

      ፍጥረታት መታየት የጀመሩት ቀስ በቀስ ነው

      ሙሴ የዘፍጥረትን ዘገባ የጻፈው በዕብራይስጥ ሲሆን ታሪኩን ያቀረበው ሁኔታውን በምድር ላይ ሆኖ ከሚያይ ሰው አንጻር ነው። እነዚህ ሁለት ነጥቦች ጽንፈ ዓለም የፍጥረት ጊዜ ወይም “ቀናት” ከመጀመራቸው በፊት እንደነበረ ካገኘነው እውቀት ጋር ተዳምረው፣ በፍጥረት ዘገባ ዙሪያ የተነሱት አብዛኞቹ ውዝግቦች መፍትሔ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። እንዴት?

      የዘፍጥረትን ዘገባ በጥንቃቄ ስንመረምረው በአንዱ “ቀን” የተጀመሩት ክንውኖች በቀጣዩ ቀን ወይም በቀጣዮቹ ቀናትም ይቀጥላሉ። ለምሳሌ ከመጀመሪያው “ቀን” በፊት፣ ቀደም ሲል ከተፈጠረችው ፀሐይ የሚመጣው ብርሃን ወደ ምድር እንዳይደርስ ያገደው ነገር ነበረ፤ ምናልባትም ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከልሎት ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 38:9) በመጀመሪያው “ቀን” ብርሃን ወደ ምድር እንዳይደርስ የከለለው ነገር መወገድ ጀመረና ደብዘዝ ያለ ብርሃን ወደ ምድር ከባቢ አየር ዘልቆ መግባት ቻለ።a

      በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሁለተኛው “ቀን” ብርሃን በደንብ እንዳያልፍ የሚከልለው ነገር ይበልጥ በመጥራቱ በላይ ካለው ጥቅጥቅ ደመናና በታች ካለው ውቅያኖስ መካከል ጠፈር ሊኖር ቻለ። በአራተኛው “ቀን” ፀሐይና ጨረቃ “በሰማይ” ላይ መታየት እስኪችሉ ድረስ ከባቢ አየሩ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነ ሄደ። (ዘፍጥረት 1:14-16) በሌላ አነጋገር በምድር ላይ ሆኖ ሁኔታውን ከሚከታተል ሰው አንጻር ፀሐይና ጨረቃ በግልጽ መታየት ጀመሩ። እነዚህ ክስተቶች የተከናወኑት ደረጃ በደረጃ ነው።

      በተጨማሪም የዘፍጥረት ዘገባ፣ ከባቢ አየሩ ብርሃን እንዳያገኝ የከለለው ነገር እየተገፈፈ በሄደ መጠን ነፍሳትንና ስስ ክንፍ ያላቸውን (membrane-winged) ፍጥረታት ጨምሮ የሚበሩ እንስሳት በአምስተኛው “ቀን” መታየት እንደጀመሩ ይገልጻል። ይሁን እንጂ በስድስተኛውም “ቀን” አምላክ “የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር” ይሠራ እንደነበር ያመለክታል።—ዘፍጥረት 2:19

      በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ በእያንዳንዱ “ቀን” ወይም የፍጥረት ወቅት የተፈጸሙት ዐበይት ክንውኖች በአንድ አፍታ ሳይሆን ቀስ በቀስ እንደተፈጠሩና ምናልባትም በአንዱ “ቀን” የተጀመረው የፍጥረት ሥራ ወደ ቀጣዮቹ የፍጥረት “ቀናትም” እየተሸጋገረ ቀጥሎ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል።

      እንደየወገናቸው

      ዕፅዋትና እንስሳት ቀስ በቀስ ወደ ሕልውና መምጣታቸው አምላክ የተለያየ ዓይነት ዝርያ ያላቸውን ፍጥረታት ለመፍጠር በዝግመተ ለውጥ እንደተጠቀመ ያመለክታልን? በፍጹም። ታሪኩ በግልጽ የሚያሳየው አምላክ ዋና ዋናዎቹን የዕፅዋትና የእንስሳት ‘ወገኖች’ በሙሉ መፍጠሩን ነው። (ዘፍጥረት 1:11, 12, 20-25) እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ‘ወገኖች’ የአካባቢያቸውን ሁኔታ መለዋወጥ እንዲላመዱት የሚያስችላቸው ፕሮግራም በውስጣቸው ተቀርጾ ነበር? የአንድን ‘ወገን’ ድንበር የሚደነግገው ምንድን ነው? ይህንን በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው’ እንደተፈጠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:21) ይህ አነጋገር በአንድ ‘ወገን’ ውስጥ የሚፈጠረው የዓይነት መብዛት ገደብ እንዳለው ያመለክታል። ዋና ዋናዎቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ባለፉት ረዥም ዘመናት ውስጥ የታየባቸው ለውጥ በጣም ጥቂት መሆኑን የቅሪተ አካል ማስረጃዎችና ዘመናዊ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

      አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች ከሚናገሩት በተቃራኒ ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ጨምሮ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያውም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርብ ዘመን እንደተፈጠረ የዘፍጥረት መጽሐፍ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ዘፍጥረት ስለ ጽንፈ ዓለም አፈጣጠርና በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ወደ ሕልውና ስለመምጣታቸው ያሰፈረው ዘገባ በቅርብ ጊዜ ከተደረሰባቸው ብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር ይስማማል።

      በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት የራሳቸው ፍልስፍና ስላላቸው ሁሉንም ነገር የፈጠረው አምላክ ስለመሆኑ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አይቀበሉትም። ይሁን እንጂ ሙሴ ጥንታዊ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ማለትም በዘፍጥረት ላይ ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለውና ሕይወትም ወደ ሕልውና የመጣው ደረጃ በደረጃና በረዥም ዘመን ውስጥ መሆኑን መጻፉ ትኩረት የሚስብ ነው። ሙሴ ከ3,500 ዓመታት በፊት እንዲህ ያለውን ከሳይንስ አንጻር ትክክል የሆነ እውቀት ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ አንድ አሳማኝ ማብራሪያ አለ። ይኸውም እንዲህ ያለውን ጥልቅ እውቀት ለሙሴ የሰጠው ሰማያትንና ምድርን ለመፍጠር ኃይልና ጥበብ ያለው አካል ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት’ እንደሆነ ለሚያቀርበው ሐሳብ ክብደት ይሰጠዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a እዚህ ላይ በመጀመሪያው “ቀን” የሆነውን ነገር ለመግለጽ ያገለገለው የዕብራይስጥ ቃል አጠቃላይ ብርሃንን የሚያመለክት ኦር የተባለ ቃል ሲሆን በአራተኛው “ቀን” ለተገኘው ብርሃን ያገለገለው ግን የብርሃኑን ምንጭ ለይቶ የሚጠቅስ ማኦር የሚል ቃል ነው።

      ይህን አስተውለኸዋል?

      ◼ አምላክ ጽንፈ ዓለምን ከፈጠረ ምን ያህል ጊዜ ሆኖታል?—ዘፍጥረት 1:1

      ◼ ምድር የተፈጠረችው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው 6 ቀናት ውስጥ ነው?—ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም

      ◼ ሙሴ ስለ ምድር አፈጣጠር የጻፈው ነገር ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?—2 ጢሞቴዎስ 3:16

      [በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      የዘፍጥረት መጽሐፍ፣ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያውም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በቅርብ ዘመን እንደተፈጠረ አያስተምርም

      [በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።”—ዘፍጥረት 1:1

      [በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      ጽንፈ ዓለም:- IAC/RGO/David Malin Images

      [በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

      NASA photo

  • በፍጥረት እንደማምን በደንብ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2006 | መስከረም
    • የወጣቶች ጥያቄ . . .

      በፍጥረት እንደማምን በደንብ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

      “በክፍል ውስጥ በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ስማረው የኖርኩትን ነገር ሁሉ አጠያያቂ አደረገብኝ። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እውነት እንደሆነ ተደርጎ መቅረቡ ያሸማቅቀኝ ነበር።”—የ18 ዓመቱ ራየን

      “የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዝግመተ ለውጥ አጥብቃ የምታምን አስተማሪ ነበረችኝ። እንዲያውም በመኪናዋ ላይ የዳርዊንን ምልክት ትለጥፋለች! ይህም በፈጣሪ እንደማምን በግልጽ ለመናገር እንድፈራ አድርጎኝ ነበር።”—የ19 ዓመቱ ታይለር

      “የኅብረተሰብ ትምህርት መምህሬ በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ የምንማረው ስለ ዝግመተ ለውጥ መሆኑን ስትናገር በጣም ፈርቼ ነበር። በዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ ረገድ አቋሜን በክፍል ውስጥ ማስረዳት እንደሚጠበቅብኝ አውቅ ነበር።”—የ14 ዓመቷ ራኬል

      አንተም እንደ ራየን፣ ታይለርና ራኬል በክፍል ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ርዕስ ሲነሳ ትጨነቅ ይሆናል። አንተ የምታምነው ‘ሁሉን የፈጠረው’ አምላክ መሆኑን ነው። (ራእይ 4:11) በዙሪያህ የምትመለከተው ነገር ሁሉ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ የተንጸባረቀበት ነው። ይሁን እንጂ የመማሪያ መጻሕፍቱና አስተማሪህም ጭምር ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው ይላሉ። ታዲያ አንተ ማን ሆነህ ነው እነዚህን ሁሉ “ሊቃውንት” የምትሟገተው? ደግሞስ ስለ አምላክ መናገር ብትጀምር የክፍል ጓደኞችህ ምን ይላሉ?

      እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች የሚያስጨንቁህ ከሆነ አይዞህ! በፍጥረት የምታምነው አንተ ብቻ አይደለህም። እንዲያውም በርካታ የሳይንስ ሊቃውንትም ሳይቀር የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ አይቀበሉትም። ብዙ መምህራንም ቢሆኑ በዝግመተ ለውጥ አያምኑም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ አገር የመማሪያ መጻሕፍቱ ከሚያቀርቡት ሐሳብ በተቃራኒ ከ5 ተማሪዎች መካከል 4ቱ በፈጣሪ ያምናሉ።

      ያም ቢሆን ‘በፍጥረት እንደማምን ማስረዳት ቢኖርብኝ ምን እላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ሁኔታው ቢያስፈራህም እንኳ በልበ ሙሉነት አቋምህን መግለጽ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ ዝግጅት ይጠይቃል።

      በመጀመሪያ እምነትህን ፈትሽ!

      ወላጆችህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆኑ በፍጥረት የምታምነው እነርሱ ስላስተማሩህ ይሆናል። አሁን ግን እያደግህ ስትሄድ ለእምነትህ ጽኑ መሠረት ኖሮህ ‘በአእምሮህ’ ተጠቅመህ አምላክን ማምለክ ትፈልጋለህ። (ሮሜ 12:1) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች “ሁሉን ነገር ፈትኑ” በማለት አበረታቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) አንተስ ስለ ፍጥረት ባለህ እምነት ረገድ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

      በመጀመሪያ ጳውሎስ ስለ አምላክ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ተመልከት:- “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል።” (ሮሜ 1:20) እነዚህን ቃላት በአእምሮህ ይዘህ የሰውን አካል፣ መሬትን፣ ሰፊ የሆነውን ጽንፈ ዓለምና የውቅያኖስን ጥልቆች መርምር። አስደናቂ ከሆነው የነፍሳት፣ የዕፅዋትና የእንስሳት ዓለም ውስጥ አንተን የሚማርክህን መስክ መርጠህ አሰላስል። ከዚያም ‘በአእምሮህ’ ተጠቅመህ ራስህን ‘ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳምነኝ ምንድን ነው?’ ብለህ ጠይቅ።

      ይህን ጥያቄ ለመመለስ የ14 ዓመቱ ሳም የሰውን አካል በምሳሌነት ይጠቅሳል። “እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄ የተሠራ ከመሆኑም በላይ ውስብስብ ነው” ብሏል። አክሎም “ሁሉም የአካል ክፍሎች ግሩም በሆነ ሁኔታ ተቀናጅተው ይሠራሉ። የሰው አካል የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ሊሆን አይችልም!” ይላል። ሆሊ የተባለችው የ16 ዓመት ልጃገረድም ሳም በተናገረው ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ትላለች:- “የስኳር በሽታ እንዳለብኝ ከተነገረኝ ጊዜ ጀምሮ የሰው አካል እንዴት እንደሚሠራ ብዙ ተምሬያለሁ። በጣም አስገራሚ ነው። ለምሳሌ ጣፊያ፣ በጨጓራና በአንጀት አካባቢ የምትገኝ አንዲት ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ደምና ሌሎች የአካላችን ክፍሎች በትክክል መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ታበረክታለች።”

      ሌሎች ወጣቶች ደግሞ በፈጣሪ የማመንን ጉዳይ የሚመለከቱት ከሌላ አቅጣጫ ነው። የ19 ዓመቱ ጄረድ እንዲህ ብሏል:- “ለእኔ ትልቁ ማስረጃ መንፈሳዊ ነገሮችን የምንፈልግ መሆናችን እንዲሁም ውበትን ማድነቃችንና የመማር ፍላጎት ያለን መሆኑ ነው። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ሊያሳምነን እንደሚፈልገው እነዚህ ባሕርያት ለመኖር የሚያስፈልጉን አይደሉም። ሊያሳምነኝ የሚችለው ብቸኛው ማብራሪያ እነዚህ ባሕርያት ሊኖሩን የቻሉት በመኖር እንድንደሰት በሚፈልግ አካል ስለተፈጠርን መሆኑ ነው።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ታይለርም ከዚሁ ድምዳሜ ላይ ደርሷል። እሱም “ዕፅዋት ሕይወት እንዲቀጥል የሚጫወቱትን ሚና እንዲሁም አስደናቂ የሆነውን የአፈጣጠራቸውን ውስብስብነት ሳስብ ፈጣሪ እንዳለ እርግጠኛ እሆናለሁ” ብሏል።

      ሁሉም ነገር የተገኘው አምላክ ፈጥሮት መሆኑን አስቀድመህ በጥንቃቄ ካሰብክበትና ይህንንም ከልብ ካመንክበት ይህን እምነትህን መግለጽ ቀላል ይሆንልሃል። ስለዚህ አንተም እንደ ሳም፣ ሆሊ፣ ጄረድና ታይለር የአምላክን ድንቅ የእጅ ሥራዎች ጊዜ ወስደህ አሰላስልባቸው። ከዚያም እነዚህ ፍጥረታት “የሚነግሩህን” ነገር ልብ ብለህ “አድምጥ።” እንዲህ ካደረግህ፣ አምላክ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ባሕርያቱንም ጭምር ‘ከፍጥረቱ በግልጽ ማየት’ እንደሚቻል በተናገረው በሐዋርያው ጳውሎስ አባባል አንተም እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም።a

      ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እወቅ

      ስለ ፍጥረት በሚገባ ለማስረዳት አምላክ የሠራቸውን ነገሮች በጥልቀት ከመመልከትም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ሐሳብ በማይሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ መከራከር አያስፈልግህም። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት:-

      ◼ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፌ መሬትና ሥርዓተ ፀሐይ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደኖሩ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሬትና ስለ ሥርዓተ ፀሐይ ዕድሜ አይናገርም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ዘገባ፣ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ የመጀመሪያው የፍጥረት “ቀን” ከመጀመሩ አስቀድሞ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደነበረ ሳይንስ ከሚገልጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ዘፍጥረት 1:1, 2

      ◼ አስተማሪዬ፣ ምድር በስድስት ቀናት ውስጥ ልትፈጠር እንደማትችል ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ስድስቱ የፍጥረት “ቀናት” እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ እንደነበራቸው አይገልጽም። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ መጽሔት ላይ ከገጽ 18-20 ተመልከት።

      ◼ እንስሳትና ሰዎች በጊዜ ሂደት እንዴት እንደተለወጡ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች በክፍል ውስጥ ቀርበው ውይይት አድርገንባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች “እንደየወገናቸው” እንደፈጠረ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:20, 21) ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌለው ነገር እንደመጣ ወይም አምላክ በአንድ ሴል አማካኝነት የዝግመተ ለውጥን ሂደት እንዳስጀመረ የሚገልጸውን ሐሳብ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፍም። ቢሆንም ከእያንዳንዱ ‘ወገን’ በርከት ያሉ ዓይነቶች ሊገኙ ይችላሉ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ‘ወገን’ ውስጥ ለውጥ እንደሚከሰት የሚገልጸውን ሐሳብ አይቃወምም።

      ስለ እምነትህ እርግጠኛ ሁን!

      በፍጥረት የምታምን በመሆንህ የምትሸማቀቅበት ወይም የምታፍርበት ምንም ምክንያት የለም። ማስረጃዎቹን ሁሉ ከመረመርን፣ ድንቅ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንደሠራን ማመን ፍጹም ምክንያታዊ አልፎ ተርፎም ከሳይንስ ጋር የሚስማማ ሆኖ እናገኘዋለን። ያላንዳች አሳማኝ ማስረጃ ከፍተኛ እምነት እንድናሳድርና ተአምር ሠሪ ሳይኖር በተፈጸመ ተአምር እንድናምን የሚጠይቅብን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እንጂ በፈጣሪ ማመን አይደለም። እንዲያውም በዚህ ንቁ! መጽሔት ላይ የቀረቡትን ሌሎች ርዕሰ ትምህርቶችም ከመረመርክ በኋላ ማስረጃው የሚደግፈው ሁሉም ነገር የተገኘው አምላክ ስለፈጠረው ነው የሚለውን እምነት መሆኑን እርግጠኛ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም። ደግሞም በማሰብ ኃይልህ ተጠቅመህ ጉዳዩን በጥንቃቄ ካጤንከው በክፍል ውስጥ ለዚህ እምነትህ ጥብቅና ለመቆም ድፍረት ይኖርሃል።

      ቀደም ሲል የጠቀስናት ራኬል የተገነዘበችው ይህንን ነው። “እምነቴን ሸሽጌ ዝም ማለት እንደሌለብኝ ለመገንዘብ ጥቂት ቀናት ወስዶብኛል” ትላለች። አክላም እንዲህ ብላለች:- “ለአስተማሪዬ፣ ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ ላይ በተለይ እንድትመለከታቸው የምፈልጋቸውን ክፍሎች አስምሬ ሰጠኋት። ከዚያ በኋላ መጽሐፉ የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ከተለየ አቅጣጫ እንድትመለከተው እንደረዳትና ለወደፊቱ ስለ ዝግመተ ለውጥ ስታስተምር ከዚህ መጽሐፍ ያገኘችውን እውቀት ግምት ውስጥ እንደምታስገባ ነገረችኝ!”

      www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ብዙ ወጣቶች ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? እና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? በተሰኙት የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ውስጥ የሠፈሩትን መረጃዎች በመመርመር ተጠቅመዋል። ሁለቱም መጻሕፍት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

      ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

      ◼ ስለ ፍጥረት ያለህን እምነት በትምህርት ቤት ሳትሸማቀቅ ለመናገር የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

      ◼ ሁሉንም ነገሮች ለፈጠረው አምላክ ያለህን አድናቆት እንዴት ልታሳይ ትችላለህ?—የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27

      [በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      “ማስረጃ ሞልቷል”

      “ወላጆቹ በፈጣሪ እንዲያምን ላስተማሩትና በትምህርት ቤት ግን የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ እየተማረ ላለ ወጣት ምን ትይዋለሽ?” ይህ ጥያቄ ማይክሮባዮሎጂስት ለሆነች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቀርቦላት ነበር። መልሷ ምን ነበር? “በአምላክ መኖር የምታምነው ወላጆችህ ስላስተማሩህ ብቻ ሳይሆን አንተው ራስህ ማስረጃውን መርምረህ ወደዚህ መደምደሚያ ስለደረስህ መሆኑን ለራስህ ለማረጋገጥ እንደሚያስችልህ አጋጣሚ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል። አንዳንድ ጊዜ መምህራን የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ‘እንዲያረጋግጡ’ ሲጠየቁ ይህን ማድረግ እንደማይችሉና ይህን ጽንሰ ሐሳብ የተቀበሉት ስለተማሩት ብቻ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንተም በፈጣሪ ላይ ባለህ እምነት ረገድ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊገጥምህ ይችላል። በእርግጥ አምላክ መኖሩን ለራስህ ማረጋገጥህ ጠቃሚ የሚሆነው ለዚህ ነው። ፈጣሪ መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሞልቷል። ይህን በተመለከተ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች አይደለም” ብላለች።

      [በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

      አንተን የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

      ፈጣሪ መኖሩን አንተ እንድታምን ያደረጉህን ሦስት ነገሮች ከዚህ በታች ዘርዝር:-

      1. ......

      2. ......

      3. ......

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ