52 ጽዮን ሆይ፣+ ተነሺ! ተነሺ! ብርታትን ልበሺ!+
ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ የሚያምሩ ልብሶችሽን ልበሺ!+
ከእንግዲህ ወዲህ ያልተገረዘና ርኩስ የሆነ ወደ አንቺ አይገባምና።+
2 ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አቧራሽን አራግፊ፤ ተነስተሽ ቦታሽን ያዢ።
ምርኮኛ የሆንሽው የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ አንገትሽ ላይ ያለውን ማሰሪያ ፍቺ።+
3 ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦
“ያለዋጋ ተሸጣችሁ ነበር፤+
ያለገንዘብም ትቤዣላችሁ።”+
4 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦
“በመጀመሪያ ሕዝቤ ባዕድ ሆኖ ለመኖር ወደ ግብፅ ወረደ፤+
ከዚያም አሦር ያላንዳች ምክንያት በጭቆና ገዛው።”
5 “ታዲያ እዚህ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ይላል ይሖዋ።
“ሕዝቤ የተወሰደው ያለዋጋ ነውና።
የሚገዟቸው በድል አድራጊነት ጉራ ይነዛሉ”+ ይላል ይሖዋ፤
“ስሜንም ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ ያቃልላሉ።+
6 በዚህ ምክንያት ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤+
በዚህም የተነሳ የተናገርኩት እኔ እንደሆንኩ በዚያ ቀን ያውቃሉ።
እነሆ፣ እኔ ነኝ!”
7 ምሥራች ይዞ የሚመጣ፣+
ሰላምን የሚያውጅ፣+
የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚያበስር፣
መዳንን የሚያውጅ፣
ጽዮንንም “አምላክሽ ነግሦአል!”+ የሚል በተራሮች ላይ እግሮቹ እንዴት ያማሩ ናቸው!
8 ስሚ! ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ።
በአንድነት ሆነው እልል ይላሉ፤
ይሖዋ ጽዮንን መልሶ ሲሰበስብ በግልጽ ያያሉና።
9 እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣ ደስ ይበላችሁ፤ በአንድነትም እልል በሉ፤+
ይሖዋ ሕዝቡን አጽናንቷልና፤+ ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቷል።+
10 ይሖዋ በብሔራት ሁሉ ፊት ቅዱስ ክንዱን ገልጧል፤+
የምድር ዳርቻዎችም ሁሉ የአምላካችንን የማዳን ሥራዎች ያያሉ።+
11 እናንተ የይሖዋን ዕቃ የምትሸከሙ፣+
ገለል በሉ፣ ገለል በሉ፤ ከዚያ ውጡ፤+ ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትንኩ!+
ከመካከሏ ውጡ፤+ ንጽሕናችሁን ጠብቁ።
12 ተደናግጣችሁ አትወጡም፤
ሸሽታችሁም አትሄዱም፤
ይሖዋ በፊታችሁ ይሄዳልና፤+
የእስራኤል አምላክም ደጀን ይሆናችኋል።+
13 እነሆ፣ አገልጋዬ+ ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው በጥልቅ ማስተዋል ነው።
ላቅ ያለ ቦታ ይሰጠዋል፤
ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግም ይከበራል።+
14 ብዙዎች በመገረም ትኩር ብለው እንዳዩት ሁሉ፣
(መልኩ ከማንኛውም ሰው የባሰ፣
ግርማ የተላበሰ ቁመናውም ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ ተጎሳቁሎ ነበር)
15 እሱም ብዙ ብሔራትን+ ያስደንቃል።
ነገሥታት በእሱ ፊት አፋቸውን ይዘጋሉ፤+
ምክንያቱም ያልተነገራቸውን ያያሉ፤
ወዳልሰሙትም ነገር ትኩረታቸውን ያዞራሉ።+