“የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” የ1999 የአውራጃ ስብሰባ
1 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው በነበረበት ወቅት ሙሴ ለአምላክ መመሪያ አድናቆት እንዲኖራቸው ተማጽኗቸዋል። እንዲህ አላቸው:- “ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና።” (ዘዳ. 32:45-47) በይሖዋ ዘንድ ሕይወታችን እጅግ ክቡር ከመሆኑ የተነሳ እርሱ በዋጋ በማይተመነው ቃሉ አማካኝነት እኛን መምራቱን በመቀጠሉ አመስጋኞች አይደለንምን? በመሆኑም ለሦስት ቀን የሚደረገውን “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባና ይሖዋ ያዘጋጀልንን በረከት ለማግኘት በጉጉት እንጠባበቃለን።
2 ይሖዋ ስብሰባው ላይ እንድትገኙ እንደሚፈልግ ስለምታምኑ በሁሉም የስብሰባው ቀናት ለመገኘት ከወዲሁ ዝግጅት አድርጋችሁ ሊሆን ይችላል። ካልሆነ ግን አስቀድማችሁ አስፈላጊውን የእረፍት ቀንና ለትራንስፖርት ወጪ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት መጣር ይኖርባችኋል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ስብሰባው ላይ ለመገኘት በግል የሚያደርጉትን ጥረት እንዲሁም የሚከፍሏቸውን መሥዋዕቶች እንደሚመለከትና እንዲህ ዓይነቶቹን ድርጊቶች በአድናቆት እንደሚያስታውስ እርግጠኛ ሁኑ። (ዕብ. 6:10) በእያንዳንዱ የስብሰባ ቀን ከመክፈቻው መዝሙር አንስቶ እስከ መደምደሚያው ጸሎት ድረስ በመገኘት ይሖዋ ለእኛ የሚናገረውን ቃል እንደምናደንቅ እናሳያለን። (ዘዳ. 4:10) በተጨማሪም ስብሰባውን በማዘጋጀት የተሳተፉ በርካታ ወንድሞች ላሳዩት ትጋት የተሞላበት ሥራ ያለንን አድናቆት እናሳያለን።
3 በእያንዳንዱ የስብሰባ ቦታ በሺዎች የሚቆጠሩ የአምላክ ሕዝቦች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ዝግጅት ማድረግ አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣትንና በጥሩ ሁኔታ መደራጀትን ይጠይቃል። የአውራጃ ስብሰባ ዝግጅቶች ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንደተደረጉ ማወቃችን ‘ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሆን’ ዘንድ ትብብር እንድናሳይ ሊገፋፋን ይገባል። (1 ቆሮ. 14:40) ከመንፈሳዊ ምግብና ከክርስቲያናዊ ጓደኝነት እንድትጠቀሙ ለስብሰባው የተሟላ ዝግጅት አድርጋችሁ መምጣት ትችሉ ዘንድ ቀጥሎ ያለው መረጃና ማሳሰቢያ ቀርቧል።
ከስብሰባው በፊት
4 መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠኗቸውና ፍላጎት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ስብሰባው ላይ ለመገኘት በግል በሚያደርጉት ዝግጅት ረገድ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል? በዚያ የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ ያነሳሳቸው ይሆናል። (1 ቆሮ. 14:25) ሽማግሌዎች በተለይ በዕድሜ የገፉ የጉባኤውን አባላት ጨምሮ ማረፊያ ወይም ትራንስፖርት ለማግኘት እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ማወቅና የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲሟላላቸው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መርዳት አለባቸው።—ገላ. 6:10
5 ማረፊያ ለማግኘት የምታደርጉትን ዝግጅት አጠናቅቃችኋል? የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ያጸደቃቸው የተለየ ሁኔታ ላላቸው ማረፊያ መጠየቂያ ቅጾች ካሉ እነዚህ ቅጾች ወዲያውኑ በጉባኤው ጸሐፊ አማካኝነት ጉዳዩ ለሚመለከተው የአውራጃ ስብሰባ ክፍል መላክ አለባቸው። የተለየ ሁኔታ ላላቸው በሚለው ዝግጅት ሥር ማረፊያ ቦታ ተመድቦላችሁ ከነበረና አሁን ግን መሰረዝ ካስፈለጋችሁ እባካችሁ ቦታዎቹን ለሌሎች መመደብ እንዲቻል ወዲያውኑ በዚያ የሚገኘውን የመስተንግዶ ክፍል አሳውቁ።
6 ስብሰባው ላይ ያለው የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ የተቋቋመው ድንገተኛ ሁኔታዎችን ብቻ ለማስተናገድ ስለሆነ አስፈላጊነቱን ካመናችሁበት የራሳችሁን መድኃኒት ይዛችሁ እንድትመጡ እናሳስባችኋለን። አንተ ወይም አንድ የቤተሰብህ አባል እንደ ልብ በሽታ፣ ስኳር ወይም የሚጥል በሽታ የመሳሰሉ አሳሳቢ የጤና ችግሮች ካሉባችሁ ለስብሰባ ስትመጡ፣ ቤት ወይም እረፍት ላይ ስትሆኑ እንደምታደርጉት ሁሉ ለእነዚህ በሽታዎች የሚያስፈልገውን መድኃኒት ማምጣት አትርሱ። ሁኔታውን የሚረዳ አንድ የቤተሰብ አባል ወይም የቅርብ ጓደኛ አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት የተሻለ ልምድ ስለሚኖረው ከታማሚው አለመለየቱ ጥበብ ይሆናል።
7 ወደ ስብሰባው ስትሄዱም ሆነ ከስብሰባው ስትመለሱ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች መፈጠራቸው አይቀርም። በዚህ ጊዜ ለሌሎች እውነትን ለማካፈል ዝግጁ ትሆናላችሁ? ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ ሁላችንም ነዳጅ ማደያ ላይ ለሚሠሩም ሆነ በጉዟችን ለምናገኛቸው ሌሎች ሰዎች ትራክት በማበርከት መሳተፍ እንችላለን። ፍላጎት ላላቸው ሰዎች መጽሔቶች፣ ብሮሹሮች ወይም ሌላ ጽሑፍ ማበርከት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። መደበኛ በሆኑ የስብከት ዘዴዎች ለማናገኛቸው ሰዎች መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ ሁኑ።
8 ወደ አውራጃ ስብሰባ የሚደረግ ጉዞን በተመለከተ ጥንቃቄ የማድረግን ጉዳይ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ለተሽከርካሪዎች የሚፈቀደውን የጭነት ልክ በሚመለከት የወጣውን የትራፊክ ሕግ ማክበር ብቻ ሳይሆን ለሕይወትም ከፍተኛ አክብሮት አላቸው። የሚያሳዝነው ግን ከተገቢው በላይ ከመጫን ወይም የተበላሹ መኪናዎችን ከመንዳት ጋር የተያያዙ አሳዛኝ አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን ይህም እስከ ሕይወት መጥፋትና ዘላቂ የሆኑ ከባድ የአካል ጉዳቶችን እስከማስከተል ደርሷል። ስለዚህ ጉባኤዎች አውቶቡስ ሲከራዩ አሊያም ታክሲ ሲኮናተሩ ወይም የግል መኪና የሚጠቀሙ ቤተሰቦች ከተገቢው በላይ አለመጫናቸው ወይም የተበላሹ መኪናዎችን አለማሽከርከራቸው ጠቃሚ ነው።—ማቴ. 22:21፤ ሮሜ 12:1
በስብሰባው ወቅት
9 በእያንዳንዱ ቀን የመሰብሰቢያው ቦታ በሮች የሚከፈቱት ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ይሆናል። መቀመጫ መያዝ የምትችሉት ለቤተሰባችሁ አባል ወይም አብሯችሁ በመኪና ለሚጓዝ ሰው ብቻ ነው። ምቹ የሆኑ መቀመጫዎች ለአረጋውያን ወንድሞችና እህቶች የተመደቡ ሲሆን የአካል ጉዳተኞች ለሆኑና በተሽከርካሪ ወንበር ለሚጠቀሙ ወንድሞች የሚሆን ቦታም ይኖራል። በእያንዳንዱ ቀን የተቀመጣችሁበትን አካባቢ ለቅቃችሁ ስትሄዱ እባካችሁ አንድም የረሳችሁት ዕቃ አለመኖሩን አረጋግጡ። እባካችሁ፣ ንጽሕናን በተመለከተም ጠንቃቃ ሁኑ፤ እንዲሁም በተቀመጣችሁበት አካባቢ ያለውን ማንኛውንም ወረቀት፣ ቆርኪ ወይም ቆሻሻ አንሱ።
10 አውራጃ ስብሰባው ላይ ለመጠመቅ ተዘጋጅተሃል? ለቅዳሜ ጠዋት ፕሮግራም ለዕጩ ተጠማቂዎች የተዘጋጀ መቀመጫ ስለሚኖር አስተናጋጆቹ ይህን ቦታ ያሳዩሃል። እባክህ፣ በተቻለህ መጠን ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የተመደበው ቦታ ላይ ተቀመጥ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመዝሙር መጽሐፍ፣ ፎጣ እና ተገቢ የጥምቀት ልብስ ማምጣት አትርሳ። ውኃ ሲነካቸው ሰውነትን የሚያሳዩ የፖሊስተር ልብሶችን አትጠቀሙ። ሽማግሌዎች ከዕጩ ተጠማቂዎች ጋር ሆነው አገልግሎታችን የተባለው መጽሐፍ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ሲከልሱ እያንዳንዱ ዕጩ ተጠማቂ እነዚህ ነጥቦች ገብተውት እንደሆነ ማረጋገጥ አለባቸው። ጥምቀት አንድ ሰው ለይሖዋ አምላክ ያደረገውን የግል ውሳኔ የሚገልጽበት ስለሆነ ተጠማቂዎች ፎቶ ለመነሳት ብለው በጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ችግር መፍጠር የለባቸውም።
11 ስብሰባው ላይ ካሜራ፣ ምስልና ድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች መጠቀም ትችሉ ይሆናል። ሆኖም የሚይዙት ቦታም ሆነ አጠቃቀማቸው መተላለፊያዎችን መዝጋት፣ የሌሎችን ዕይታ መጋረድ ወይም ሌሎች ፕሮግራሙን እንዳይከታተሉ ሐሳባቸውን መስረቅ የለበትም። እነዚህ መሣሪያዎች ለስብሰባው ከሚያገለግለው የኤሌትሪክም ሆነ የድምፅ መስመር ጋር ሳይገናኙ በራሳቸው የሚሠሩ መሆን አለባቸው።
12 ጊዜ ለመቆጠብና ነገሮችን ለማቅለል ሲባል ማኅበሩ በእያንዳንዱ ቀን የራሳችንን ምሳ እንድናመጣ ሐሳብ አቅርቦልናል። አብዛኞቹ ወንድሞች ይህን መመሪያ የተከተሉ ሲሆን በምሳ እረፍት ጊዜ ያመጡትን ምግብ ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው ለመመገብ አስችሏቸዋል። ብዙዎች በምሳ እረፍት ዘና ለማለት መቻላቸው እንዲሁም ከወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ተጨማሪ ጊዜ ማግኘታቸው አስደሳች እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ምግብና የሚጠጡ ነገሮችን አስቀድሞ ማዘጋጀትንና መቀመጫው ሥር ሊቀመጥ በሚችል በአንድ ትንሽ መያዣ ወይም ማቀዝቀዣ ውስጥ ማድረግን ይጠይቃል። ስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ ይህን መመሪያ እንዲከተሉ እንጠይቃለን። ከእናንተ ጋር ወደ ስብሰባው የሚመጡ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም የራሳቸውን ምግብ ይዘው መምጣት አለባቸው። ጠርሙሶችንም ሆነ የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት አይፈቀድም።
13 በእያንዳንዱ ቀን ስብሰባው ካበቃ በኋላ በፈቃደኝነት ቦታውን ለማጽዳት መተባበር ትችላለህ? ወይም ከሌሎቹ የአውራጃ ስብሰባ ክፍሎች በአንዱ መሥራት ትችላለህ? ባለፈው ዓመት በቂ ፈቃደኛ ሠራተኞች አልነበሩንም። ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ እርዳታ መስጠት የምትችል ከሆነ እባክህ ስብሰባው ላይ ለሚገኘው የፈቃደኛ ሠራተኛ አገልግሎት ክፍል አሳውቅ። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከወላጆቻቸው ወይም ሌላ ኃላፊነት ከሚሰማው ጎልማሳ ሰው ጋር ሆነው እንዲሠሩ ይፈቀድላቸዋል። እርግጥ ሁላችንም ማንኛውንም ቆሻሻ በማንሳትና ተገቢው ቦታ ላይ በመጣል መሰብሰቢያውን ለማጽዳት መተባበር እንችላለን። በተለይ ለዚህ ጉዳይ ሁሉም ንቁ እንዲሆኑ እናበረታታለን።
14 አውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ ልንከተለው የሚገባ ሥርዓታማ አለባበስና የፀጉር አያያዝ ምን ዓይነት እንደሆነ የሚገልጽ ጥሩ መመሪያ አግኝተናል። ለምሳሌ ያህል:- ይህን ጉዳይ በተመለከተ የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪዎች ላይ መመሪያ ወጥቷል፣ ጽሑፎቻችን ላይ ሥዕሎችና ፎቶግራፎች ቀርበዋል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ የሚናገረው ነገር ሰፍሯል። (ሮሜ 12:2፤ 1 ጢሞ. 2:9, 10) ሰዎች ማንነታችንንና የተሰበሰብንበትን ዓላማ ያውቃሉ። በመሆኑም አለባበሳችንና የፀጉር አያያዛችን በራሱ ጉልህ ምሥክርነት ይሰጣል። በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች ጥሩ ምሳሌ ናቸው። አልፎ አልፎ ግን የአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ አንዳንዶች በአለባበሳቸውና በፀጉር አበጣጠራቸው የዓለምን መንፈስ እንደሚያንጸባርቁ ተስተውሏል። ሰውነትን የሚያሳይ ማንኛውም ዓይነት ልብስ ግለሰቡ መንፈሳዊ ሰው እንደሆነ የሚናገረውን ነገር አጠያያቂ ያደርግበታል። ልከኛ፣ ንጹህና ሥርዓታማ ሆኖ መቅረብ ይበልጥ ማራኪ ነው። የሥራ ወይም የመዝናኛ ልብስ ለብሶ መምጣት ተገቢ አይደለም። ስለዚህ የቤተሰብ ራሶች የቤተሰባቸው አባላት ምን ዓይነት ልብስ ለመልበስ እንደመረጡ ማወቅ አለባቸው። ትንንሽ ልጆችም ሳይቀር ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ከስብሰባው ቦታ ወጥተን በምንሄድበት ጊዜም ይሠራል። የቀኑ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊትና ካበቃም በኋላ ደረት ላይ የሚለጠፈውን ባጅ ማድረጋችን ከይሖዋና ከንጹሕ ሕዝቦቹ ጎን መሆናችንን በይበልጥ ያሳውቃል።—ከማርቆስ 8:38 ጋር አወዳድር።
15 በተጨማሪ አካላዊ ንጽሕና በአግባቡ እጅ መታጠብን ያጠቃልላል፤ በተለይ ደግሞ መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ ይህ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ዓላማ የሚውል ሳሙና እና ውኃ ለማቅረብ ጥረት የሚደረግ ሲሆን ወላጆች እጃቸውን በሳሙና በመታጠብ ረገድ ለልጆቻቸው ምሳሌ በመሆን እንዲያሰለጥኗቸው እናበረታታቸዋለን። ያለ ሳሙና መታጠብ ያን ያህል ጠቃሚ ባለመሆኑ ይህ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተለይ በእጃችን ምግብ ልንነካ ስለምንችል እንዲህ ማድረጋችን በሽታ ለመከላከል ይረዳናል።
16 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ‘ስንፍና በሕፃን ልብ እንደታሰረ’ እና ‘ያልተቀጣ ብላቴና እናቱን እንደሚያሳፍር’ በመንፈስ አነሳሽነት ጽፏል። (ምሳሌ 22:15፤ 29:15) ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ወቅት፣ ቁጥጥር ያልተደረገላቸው ወጣት ምሥክሮች ከፕሮግራሙ ለመጠቀም የሚጥሩትን ወንድሞችና እህቶች ፀጥታ ነስተዋል። ባለፈው ዓመት በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ አንዳንድ ወጣቶች ሌላው ቀርቶ ፕሮግራሙ በግልጽ በማይሰማባቸው ራቅ ብለው በሚገኙ መቀመጫ ቦታዎች ላይ ታይተዋል። እነዚህ ወጣቶች እነርሱን ጭምር ግምት ውስጥ በማስገባት ከተዘጋጀው መንፈሳዊ ፕሮግራም እየተጠቀሙ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ለሚያሳዩት ጠባይ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ስለሆኑ አንድ እናት ወይም አባት ልጆቹ ሥርዓት መያዛቸውንና የይሖዋን መመሪያ እየተከታተሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት አጠገባቸው ካስቀመጧቸው ብቻ ነው።
17 ስብሰባው ለማንኛውም ሰው ክፍት ስለሆነ ልጆቻችንንና ንብረቶቻችንን በጥንቃቄ መያዛችን ጥበብ ነው። ልጆቻችን ከይሖዋ የተገኙ ውድ ስጦታዎች ናቸው። ሆኖም ዓለም ሰይጣን ያለውን አድብቶ የማጥቃት ባሕርይ እንደሚያንጸባርቅ እናውቃለን። ስለዚህ እባካችሁ በማንኛውም ጊዜ ልጆቻችሁ የት እንደሆኑ ተከታተሉ። በተጨማሪም ካሜራ፣ ቦርሳና ሌሎች ውድ ዕቃዎችን ምንጊዜም በእጃችሁ መያዝ አለባችሁ እንጂ የምትቀመጡበት ቦታ ላይ መተው የለባችሁም። መኪናችሁ መቆለፉን አረጋግጡ፤ እንዲሁም ንብረታችሁን በመኪናችሁ ዕቃ ማስቀመጫ ውስጥ ክተቱ አሊያም በእጃችሁ ያዙት። እንዲህ ማድረጋችሁ አንድ ሰው መኪናችሁን ለመስበር የሚፈተንበትን ሁኔታ ይቀንሳል። ዱርዬዎች፣ ለማኞችና ሌሎች ለፕሮግራሙ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች መኖራቸውን ከተመለከታችሁ እባካችሁ ለአስተናጋጆች አሳውቁ።
18 ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ወንድሞችና እህቶች ማስታወሻ ሲይዙ ማየት ያበረታታል። አጫጭር ማስታወሻዎች መያዝ አእምሯችሁን ለማሰባሰብና ዋና ዋና ነጥቦችን ለማስታወስ ይረዳችኋል። ከጊዜ በኋላ፣ የያዛችሁትን ማስታወሻ ከቤተሰባችሁ ወይም ከጓደኞቻችሁ ጋር መከለሳችሁ ጎላ ያሉት የስብሰባው ነጥቦች እንዳይረሷችሁ ለማስታወስ አጋጣሚ ይሰጣችኋል።
19 የይሖዋ ሕዝቦች ለቲኦክራሲያዊ ጉዳዮች አስተዋጽኦ በማድረግ ረገድ ምንጊዜም ለጋስ እንደሆኑ አሳይተዋል። (ዘጸ. 36:5-7፤ 2 ዜና 31:10፤ ሮሜ 15:26, 27) በፈቃደኝነት ለዓለም አቀፉ ሥራ የምታደርጉት አስተዋጽኦ የአውራጃ ስብሰባዎቹ ለሚደረጉበት ትላልቅ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ኪራይ የሚወጣውን ወጪ ለመሸፈን ያገለግላል። በቼክ አስተዋጽኦ የምታደርጉ ከሆነ እባካችሁ ክፍያው “ለይሖዋ ምሥክሮች” እንዲሰጥ አድርጉ።
20 አሞጽ 3:7 ላይ እንደሰፈረው ይሖዋ ‘ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም እንደማያደርግ’ ተናግሯል። ይሖዋ ‘ምሥጢር ገላጭ’ እንደመሆኑ መጠን በትክክልና ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ያገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡ አድርጓል። (ዳን. 2:28, 47) ገና ፍጻሜያቸውን ያላገኙ ታላላቅ ተስፋዎችም አሉ። “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” የተባለው የ1999 የአውራጃ ስብሰባ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያላችሁን እምነት ያጠናክርላችኋል። ይሖዋ ለእናንተ የሚናገረውን ቃል በጥሞና አዳምጡ። የምታዩትንና የምትሰሙትን ነገር በአገልግሎት፣ በጉባኤና በግል ሕይወታችሁ ውስጥ በሥራ አውሉት። በእያንዳንዱ ቀን በዚህ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ድግስ ላይ ለመገኘት የምታደርጉትን ዝግጅት በሙሉ ይሖዋ አብዝቶ እንዲባርክላችሁ እንጸልያለን!
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል3]
አርብ፣ ቅዳሜና እሁድ ሙሉ ቀን ስብሰባው ላይ ለመገኘት ዕቅድ አውጡ!
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል4]
(ወደ ገጽ 6 ዞሯል)
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል6]
የአውራጃ ስብሰባ . . . (ከገጽ 4 የዞረ)