የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w23 ግንቦት ገጽ 8-13
  • ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ በጠበቅነው መንገድ መልስ ላይሰጠን ይችላል
  • ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ጸሎታችንን የሚመልስባቸው መንገዶች
  • የይሖዋን መልስ ማስተዋልና መቀበል እምነት ይጠይቃል
  • መልስ የሚያገኙት የእነማን ጸሎቶች ናቸው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • መግቢያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2021
  • ይሖዋ ጸሎቴን ይመልስልኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
w23 ግንቦት ገጽ 8-13

የጥናት ርዕስ 21

ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው?

“የምንጠይቀውንም ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ የምንጠይቀውን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን።”—1 ዮሐ. 5:15

መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ

ማስተዋወቂያa

1-2. ከጸሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ጥርጣሬ ሊያድርብን ይችላል?

ይሖዋ ጸሎትህን የሚመልስ መሆኑን ተጠራጥረህ ታውቃለህ? ከሆነ፣ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በርካታ ወንድሞችና እህቶች በተለይ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ይሖዋ ጸሎታቸውን የሚሰማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ይገባቸዋል። እኛም በመከራ ውስጥ ስንሆን ይሖዋ ጸሎታችንን እየመለሰልን ያለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ሊከብደን ይችላል።

2 ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደሚመልስ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። (1 ዮሐ. 5:15) በተጨማሪም የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ጸሎታችንን ያልመለሰልን የሚመስለው ለምን ሊሆን ይችላል? ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ነው?

ይሖዋ በጠበቅነው መንገድ መልስ ላይሰጠን ይችላል

3. ይሖዋ ወደ እሱ እንድንጸልይ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚወደንና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ዋስትና ይሰጠናል። (ሐጌ 2:7፤ 1 ዮሐ. 4:10) በጸሎት የእሱን እርዳታ እንድንጠይቅ የጋበዘን ለዚህ ነው። (1 ጴጥ. 5:6, 7) ምንጊዜም ከእሱ ጋር ተቀራርበን እንድንኖር እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም ሊረዳን ይፈልጋል።

ዳዊት በገና ይዞ፤ ከተወረወረበት ጦር ለመሸሽ ሲሞክር።

ይሖዋ ዳዊትን ከጠላቶቹ በመታደግ ጸሎቱን መልሶለታል (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደሚመልስ እንዴት እናውቃለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደመለሰላቸው የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ ወደ አእምሮህ የሚመጣ ምሳሌ አለ? እስቲ ንጉሥ ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዳዊት በመላ ሕይወቱ አደገኛ የሆኑ በርካታ ጠላቶችን ተጋፍጧል። በመሆኑም በተደጋጋሚ የይሖዋን እርዳታ ይጠይቅ ነበር። ለምሳሌ በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ልመና አቅርቧል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ፤ እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውን ልመና አዳምጥ። እንደ ታማኝነትህና እንደ ጽድቅህ መጠን መልስልኝ።” (መዝ. 143:1) ይሖዋ ዳዊትን በመታደግ ጸሎቱን መልሶለታል። (1 ሳሙ. 19:10, 18-20፤ 2 ሳሙ. 5:17-25) ዳዊት “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው” ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ችሏል። እኛም እንዲህ ያለ እምነት ሊኖረን ይችላል።—መዝ. 145:18

ሐዋርያው ጳውሎስ ለይሖዋ ምልጃ ሲያቀርብ።

ይሖዋ ለጳውሎስ ለመጽናት የሚያስችል ኃይል በመስጠት ጸሎቱን መልሶለታል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. በጥንት ዘመን የነበሩ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ለጸሎታቸው የሚጠብቁትን መልስ አግኝተዋል? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ይሖዋ በጠበቅነው መንገድ ጸሎታችንን ላይመልስልን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞታል። ‘ሥጋውን የሚወጋውን እሾህ’ አምላክ እንዲያስወግድለት ጸልዮ ነበር። ጳውሎስ ይህን ከባድ ችግር አስመልክቶ ሦስት ጊዜ ጸልዮአል። ታዲያ ይሖዋ ጸሎቱን መልሶለታል? አዎ፣ ግን የመለሰለት ጳውሎስ በጠበቀው መንገድ አይደለም። ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ እሱን በታማኝነት ማገልገሉን ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ኃይል ሰጥቶታል።—2 ቆሮ. 12:7-10

6. አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ጸሎታችንን እንዳልመለሰልን ሊሰማን የሚችለው ለምንድን ነው?

6 እኛም አንዳንድ ጊዜ የጸሎታችን መልስ ከጠበቅነው የተለየ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ እኛን መርዳት የሚችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲያውም “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” ይችላል። (ኤፌ. 3:20) በመሆኑም ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን ባልጠበቅነው ጊዜ ወይም ባልጠበቅነው መንገድ ሊሆን ይችላል።

7. በጸሎት የምንጠይቀውን ነገር መቀየር የሚያስፈልገን ለምን ሊሆን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

7 የይሖዋ ፈቃድ ይበልጥ ግልጽ ሲሆንልን በጸሎት የምንጠይቀውን ነገር መቀየር ሊያስፈልገን ይችላል። የወንድም ማርቲን ፖይትጺንገርን ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ፖይትጺንገር ትዳር ከመሠረተ ብዙም ሳይቆይ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታሰረ። መጀመሪያ አካባቢ ይጸልይ የነበረው ከማጎሪያ ካምፑ ወጥቶ ሚስቱን መንከባከብና በስብከቱ ሥራ መካፈሉን መቀጠል እንዲችል ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከማጎሪያ ካምፑ የሚወጣበትን መንገድ እንዳመቻቸለት የሚያሳይ ምንም ምልክት ለሁለት ሳምንት ያህል አላገኘም። ስለዚህ “ይሖዋ፣ እባክህ ምን እንዳደርግ እንደምትፈልግ አሳየኝ” ብሎ መጸለይ ጀመረ። ከዚያም በካምፑ ውስጥ ያሉት ሌሎቹ ወንድሞች ስላሉበት ሁኔታ ማሰብ ጀመረ። ብዙዎቹ የሚስቶቻቸውና የልጆቻቸው ጉዳይ በጣም ያሳስባቸው ነበር። ከዚያም ወንድም ፖይትጺንገር እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ “ይሖዋ፣ ስለሰጠኸኝ አዲስ ምድብ አመሰግንሃለሁ። ወንድሞቼን እንዳበረታታና እንዳጠናክር እርዳኝ።” በካምፑ ውስጥ ለቀጣዮቹ ዘጠኝ ዓመታት ይህን ሲያደርግ ቆይቷል!

8. በምንጸልይበት ጊዜ የትኛውን እውነታ ከግምት ማስገባት ይኖርብናል?

8 ይሖዋ ዓላማ እንዳለውና ዓላማውን የሚፈጽመው በወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይህ ዓላማው በዛሬው ጊዜ ብዙ መከራ እያስከተሉ ያሉትን ችግሮች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋትን ያካትታል፤ ከእነዚህ ችግሮች መካከል የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ሕመምና ሞት ይገኙበታል። ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ዓላማውን ይፈጽማል። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 21:3, 4) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ሰይጣን ዓለምን እንዲገዛ ፈቅዶለታል።b (ዮሐ. 12:31፤ ራእይ 12:9) ይሖዋ የሰው ልጆች በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ቢፈታላቸው የሰይጣን አገዛዝ የተሳካለት ሊመስል ይችላል። ስለዚህ ይሖዋ የገባቸውን አንዳንድ ቃሎች እስኪፈጽም ድረስ መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህ ሲባል ግን ምንም ዓይነት እርዳታ አያደርግልንም ማለት አይደለም። ይሖዋ እኛን የሚረዳባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ጸሎታችንን የሚመልስባቸው መንገዶች

9. ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

9 ጥበብ ይሰጠናል። ይሖዋ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ጥበብ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። በተለይ ቀሪውን ሕይወታችንን የሚነኩ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ አምላካዊ ጥበብ ያስፈልገናል፤ ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል ‘ትዳር ልመሥርት ወይስ ሳላገባ ልኑር?’ የሚለው አንዱ ነው። (ያዕ. 1:5) ማሪያ የተባለች ያላገባች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ።c በዘወትር አቅኚነት በደስታ እያገለገለች ሳለ ከአንድ ወንድም ጋር ተዋወቀች። እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኝነታችን እየተጠናከረ ሲመጣ ይበልጥ ተዋደድን። ውሳኔ ማድረግ እንዳለብኝ ገብቶኝ ነበር። ስለ ጉዳዩ አጥብቄ ጸለይኩ። የይሖዋ አመራር ያስፈልገኝ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ለእኔ ውሳኔ እንደማያደርግልኝ አውቃለሁ።” ማሪያ ጥበብ ለማግኘት ያቀረበችውን ጸሎት ይሖዋ እንደመለሰላት ተሰምቷታል። እንዴት? በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ስታደርግ ጥያቄዎቿን የሚመልሱ ጥሩ ጥሩ ሐሳቦች አገኘች። በተጨማሪም ታማኝ የሆነች እናቷ የሰጠቻትን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ተቀበለች። ይህ ምክር፣ ማሪያ ስሜቷን መለስ ብላ እንድትገመግም ረድቷታል። በመጨረሻም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ ቻለች።

በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ያለ ወንድም መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ።

ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችል ኃይል የሚሰጠን እንዴት ነው? (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. በፊልጵስዩስ 4:13 መሠረት ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚረዳቸው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። ይሖዋ ለሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገለት ሁሉ እኛም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም እንድንችል ኃይል ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 4:13⁠ን አንብብ።) ቤንጃሚን የተባለ ወንድም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዲቋቋም ይሖዋ የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ቤንጃሚን ወጣት ሳለ እሱና ቤተሰቡ ለበርካታ ዓመታት አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ኖረዋል። ቤንጃሚን እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እሱን የሚያስደስተውን ነገር ማድረግ እንድችል ኃይል እንዲሰጠኝ ሁልጊዜ እጸልይ ነበር። ይሖዋ የአእምሮ ሰላም፣ መስበኬን ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት እንዲሁም በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድሆን የሚረዱ ጽሑፎች በመስጠት ጸሎቴን መልሶልኛል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የእምነት ባልንጀሮቼን ተሞክሮዎች ማንበቤና ይሖዋ እንዲጸኑ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ማስተዋሌ ታማኝ ሆኜ ለመኖር ያለኝን ቁርጠኝነት አጠናክሮልኛል።”

በእምነት ባልንጀሮችህ አማካኝነት የይሖዋን እርዳታ ተመልክተህ ታውቃለህ? (አንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)d

11-12. ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተሰባችንን ተጠቅሞ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት ሊሆን ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 መንፈሳዊ ቤተሰባችንን ይጠቀማል። ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ አጥብቆ ጸልዮ ነበር። አምላክን እንደተሳደበ ተደርጎ መቆጠሩ ከሚያስከትልበት ነቀፋ እንዲታደገው ይሖዋን ለመነው። ይሖዋ፣ ኢየሱስ የጠየቀውን ነገር ከማድረግ ይልቅ አንድ መልአክ በመላክ አበረታታው። (ሉቃስ 22:42, 43) ይሖዋ እኛንም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት እንዲደውሉልን ወይም እንዲጠይቁን በማነሳሳት ሊረዳን ይችላል። ሁላችንም ለእምነት ባልንጀሮቻችን “መልካም ቃል” ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፈለግ እንችላለን።—ምሳሌ 12:25

12 ሚርያም የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ባለቤቷ ከሞተ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሚርያም በትካዜና በተስፋ መቁረጥ ተውጣ ቤት ውስጥ ብቻዋን ቁጭ ብላ ነበር። ማልቀሷን ማቆም አልቻለችም። የምታነጋግረው ሰው ማግኘት ፈልጋ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ማንም ሰው ጋር ለመደወል የሚያስችል ጉልበት አልነበረኝም። ስለዚህ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ገና እያለቀስኩና እየጸለይኩ ሳለሁ ስልኬ ጠራ። የደወለው ጥሩ ወዳጄ የሆነ የጉባኤ ሽማግሌ ነበር።” ሚርያም ከዚያ ወንድምና ከባለቤቱ ማጽናኛ አገኘች። ይህ ወንድም እንዲደውልላት ያነሳሳው ይሖዋ እንደሆነ እርግጠኛ ነች።

አንድ ሐኪም ለአንድ ባልና ሚስት መረጃ የያዘ ጽሑፍ ሲያሳያቸው።

ይሖዋ ሌሎች እንዲረዱን የሚያነሳሳቸው እንዴት ሊሆን ይችላል? (ከአንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት)

13. ይሖዋ እሱን የማያመልኩ ሰዎችን ተጠቅሞ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

13 እሱን የማያመልኩ ሰዎችን ሊጠቀም ይችላል። (ምሳሌ 21:1) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ፣ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች አገልጋዮቹን እንዲረዷቸው በማነሳሳት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል። ለምሳሌ ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ከተማዋን በመጠገኑ ሥራ ለመካፈል ያቀረበውን ጥያቄ ንጉሥ አርጤክስስ እንዲመልስለት አነሳስቶታል። (ነህ. 2:3-6) በዛሬው ጊዜም እርዳታ ሲያስፈልገን ይሖዋ እሱን የማያመልኩ ሰዎችን ጭምር በማነሳሳት ሊረዳን ይችላል።

14. ከሱ ሂንግ ተሞክሮ ልብህን የነካው ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ሱ ሂንግ የተባለች እህት ይሖዋ በአንድ ሐኪም አማካኝነት እንደረዳት ተሰምቷታል። ልጇ የተለያዩ የአእምሮ ሕመሞች አሉበት። በአንድ ወቅት ከባድ አደጋ ስለደረሰበት እሷና ባለቤቷ ልጃቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ሥራ አቆሙ። በዚህም የተነሳ የገንዘብ ችግር አጋጠማቸው። ሱ ሂንግ አቅሟ ሙሉ በሙሉ እንደተሟጠጠ ተሰምቷት እንደነበር ገልጻለች። ልቧን በይሖዋ ፊት በማፍሰስ እንዲረዳት ጠየቀችው። በዚህ ጊዜ የልጇ ሐኪም እነሱን ለመርዳት ወሰነ። በመሆኑም የመንግሥትን ድጎማ እንዲሁም ዋጋው ረከስ ያለ ቤት ማግኘት ቻሉ። ከጊዜ በኋላ ሱ ሂንግ እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን እጅ ማየት ችለናል። በእርግጥም እሱ ‘ጸሎት ሰሚ’ ነው።”—መዝ. 65:2

የይሖዋን መልስ ማስተዋልና መቀበል እምነት ይጠይቃል

15. አንዲት እህት ጸሎቷ መልስ እያገኘ እንደሆነ እንድታስተውል የረዳት ምንድን ነው?

15 የምናቀርበው ጸሎት ብዙውን ጊዜ የሚመለሰው ተአምራዊ በሚመስል መንገድ አይደለም። ሆኖም ለሰማዩ አባታችን ታማኝ ለመሆን የሚረዳንን መልስ እናገኛለን። ስለዚህ ይሖዋ ለጸሎትህ የሚሰጥህን መልስ ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ዮኮ የተባለች እህት ይሖዋ ጸሎቷን እንደማይመልስላት ተሰምቷት ነበር። በኋላ ግን ይሖዋን የጠየቀቻቸውን ነገሮች በዝርዝር መጻፍ ጀመረች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የማስታወሻ ደብተሯን መለስ ብላ ስትመለከት ይሖዋ አብዛኞቹን ጸሎቶቿን እንደመለሰላት ተገነዘበች፤ እንዲያውም ከተመለሱላት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን መጠየቋን እንኳ ረስታ ነበር። እኛም አልፎ አልፎ ቆም ብለን ይሖዋ ጸሎታችንን እየመለሰልን ያለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ይኖርብናል።—መዝ. 66:19, 20

16. ከጸሎት ጋር በተያያዘ እምነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 11:6)

16 እምነት የምናሳየው ወደ ይሖዋ በመጸለይ ብቻ ሳይሆን ለጸሎታችን የሚሰጠንን ማንኛውንም መልስ በመቀበልም ጭምር ነው። (ዕብራውያን 11:6⁠ን አንብብ።) ማይክና ባለቤቱ ክሪሲ ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማይክና ክሪሲ በቤቴል የማገልገል ግብ ነበራቸው። ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “ከተጋባን በኋላ ለበርካታ ዓመታት ለቤቴል አገልግሎት አመልክተን ነበር፤ ይህን ግባችንን በተመለከተም ብዙ ጊዜ ጸልየናል። ግን በቤቴል እንድናገለግል አልተጋበዝንም።” ማይክና ክሪሲ፣ ይሖዋ እሱን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዲያገለግሉት ሊጠቀምባቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንደሚያውቅ እርግጠኞች ነበሩ። ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ በዘወትር አቅኚነት በማገልገል እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች በመካፈል አቅማቸው የፈቀደውን ማድረጋቸውን ቀጠሉ። በአሁኑ ወቅት በወረዳ ሥራ እየተካፈሉ ነው። ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ጸሎታችንን በጠበቅነው መንገድ ያልመለሰልን ጊዜ አለ። ሆኖም ጸሎታችንን መልሶልናል፤ ደግሞም የሰጠን መልስ ከጠበቅነው እጅግ የተሻለ ነው።”

17-18. በመዝሙር 86:6, 7 መሠረት ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 መዝሙር 86:6, 7⁠ን አንብብ። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይሖዋ ጸሎቱን እንደሰማውና እንደመለሰለት እርግጠኛ ነበር። አንተም ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማና እንደሚመልስልህ መተማመን ትችላለህ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተመለከትናቸው ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ጥበብና ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። መንፈሳዊ ቤተሰባችንን አልፎ ተርፎም በአሁኑ ወቅት እሱን የማያመልኩ ሰዎችን በመጠቀም በሆነ መንገድ ሊረዳን ይችላል።

18 ይሖዋ ጸሎታችንን በጠበቅነው መንገድ ላይመልስልን ቢችልም ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ነን። የሚያስፈልገንን ነገር ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ይሰጠናል። እንግዲያው ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እንደሚንከባከብህ፣ በመጪው አዲስ ዓለም ደግሞ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ እርግጠኛ በመሆን በእምነት መጸለይህን ቀጥል።—መዝ. 145:16

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ይሖዋ ጸሎታችንን በጠበቅነው መንገድ የማይመልስልን ለምን ሊሆን ይችላል?

  • ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ።

  • የጸሎታችንን መልስ ለማስተዋል በምንሞክርበት ወቅት እምነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 46 ይሖዋ እናመሰግንሃለን

a ይሖዋ ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ እስከጸለይን ድረስ ጸሎታችንን እንደሚመልስልን ቃል ገብቶልናል። ፈተና ሲያጋጥመን ለእሱ ያለንን ታማኝነት ለመጠበቅ እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስልን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

b ሰይጣን ዓለምን እንዲገዛ ይሖዋ የፈቀደለት ለምን እንደሆነ ለማወቅ በሰኔ 2017 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ትኩረታችሁን አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ አድርጉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እናትና ልጇ ስደተኞች ሆነው ወደ አንድ አገር መጡ። የእምነት ባልንጀሮቻቸው ሞቅ አድርገው በመቀበል የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ሰጧቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ