-
‘ይሖዋ ኃይሉ ታላቅ ነው’ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 4
ይሖዋ ኃይሉ ታላቅ ነው’
1, 2. ኤልያስ በተለያዩ ጊዜያት ምን አስገራሚ ነገሮች አይቷል? ይሁን እንጂ በኮሬብ ተራራ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ሳለ የተመለከተው ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ክስተት ምንድን ነው?
ኤልያስ ከዚህ ቀደም ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ተመልክቷል። በአንድ ሸለቆ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ወቅት ቁራዎች በቀን ሁለት ጊዜ መግበውታል። ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ረሃብ ወቅት በማድጋው ውስጥ የነበረው ትንሽ ዱቄትና በማሰሮው ውስጥ የነበረው ጥቂት ዘይት ለዚያን ያህል ጊዜ መበርከቱ የሚያስገርም ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ወደ ይሖዋ በመጸለይ እሳት ከሰማይ እንዲወርድ ማድረግ ችሏል። (1 ነገሥት ምዕራፍ 17, 18) ይሁንና ኤልያስ ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ አስገራሚ የሆነ አንድ ሌላ ነገር ተመልክቷል።
2 በኮሬብ ተራራ በሚገኝ አንድ ዋሻ መግቢያ ላይ ተሸሽጎ ሳለ አስገራሚ ክስተቶችን ተመለከተ። በመጀመሪያ ጆሮ የሚያደነቁር ኃይለኛ ድምፅ ያለው ነፋስ ነፈሰ። ይህ ነፋስ እጅግ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ተራሮቹ ተሰነጣጠቁ እንዲሁም ዓለቶቹ ተሰባበሩ። ከዚያም ከፍተኛ የምድር መናወጥ ሆነ። በመጨረሻም እሳት ነደደ። እሳቱ አካባቢውን ሲያቃጥለው ወላፈኑ ኤልያስንም ገርፎት ሊሆን ይችላል።—1 ነገሥት 19:8-12
3. ኤልያስ ያያቸው ክስተቶች የትኛውን የአምላክ ባሕርይ የሚያንጸባርቁ ናቸው? ይህ ባሕርይ የተገለጸበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?
3 ኤልያስ ያያቸው እነዚህ ክስተቶች አንድ የጋራ ባሕርይ አላቸው፤ ሁሉም የይሖዋን ታላቅ ኃይል የሚያንጸባርቁ ናቸው። እርግጥ ነው፣ አምላክ ይህ ባሕርይ እንዳለው ለማወቅ ተአምር ማየት ያስፈልገናል ማለት አይደለም። ፍጥረት ራሱ የይሖዋ ‘ዘላለማዊ ኃይልና አምላክነት’ መግለጫ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮም 1:20) ኃይለኛ ነጎድጓድና የመብረቅ ብልጭታ፣ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ፏፏቴ እንዲሁም በከዋክብት የተሞላ የተንጣለለ ሰማይ ስትመለከት አምላክ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው አትገነዘብም? ይሁን እንጂ ዛሬ ብዙዎች ይህን የአምላክ ኃይል አያስተውሉም። የሚያስተውሉ ቢኖሩም ደግሞ ትክክለኛ ግንዛቤ ያላቸው ጥቂቶች ናቸው። ይህን መለኮታዊ ባሕርይ በትክክል መገንዘባችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል። በዚህ በክፍል አንድ ላይ፣ አቻ የማይገኝለትን የይሖዋ ኃይል በጥልቀት እንመረምራለን።
“ይሖዋ እያለፈ ነበር”
መሠረታዊ የሆነ የይሖዋ ባሕርይ
4, 5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ስም ምን ይላል? (ለ) ይሖዋ ኃይሉን ለመግለጽ በሬን እንደ ምሳሌ አድርጎ መጠቀሙ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ አቻ የማይገኝለት ኃይል አለው። ኤርምያስ 10:6 “ይሖዋ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም። አንተ ታላቅ ነህ፤ ስምህም ታላቅና ኃያል ነው” ይላል። የይሖዋ ስም፣ ታላቅና ኃያል ተብሎ እንደተገለጸ ልብ በል። ይህ ስም ደግሞ “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው አስታውስ። ይሖዋ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር ለመፍጠር እንዲሁም መሆን የሚሻውን ሁሉ ለመሆን የሚያስችለው ምንድን ነው? አንዱ ነገር ኃይሉ ነው። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ያለው ችሎታ ገደብ የለውም። ይህ ኃይል ከዋና ዋናዎቹ የአምላክ ባሕርያት መካከል የሚጠቀስ ነው።
5 ይሖዋ፣ ኃይሉ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ሊገባን ስለማይችል በቀላሉ እንድንረዳው ለማድረግ ሲል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ቀደም ሲል እንዳየነው ኃይሉን ለመግለጽ በሬን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (ሕዝቅኤል 1:4-10) በሬ ግዙፍና ኃይለኛ ፍጡር ስለሆነ የይሖዋ ኃይል በበሬ መመሰሉ ተስማሚ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በፓለስቲና ምድር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከበሬ ይበልጥ ጉልበት ያለው እንስሳ እምብዛም አያውቁም ነበር ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ አውራከስ ስለሚባለው አስፈሪ የሆነ የዱር በሬ ያውቁ ነበር፤ ይህ እንስሳ አሁን ከምድር ገጽ ጠፍቷል። (ኢዮብ 39:9-12) የሮም ገዢ የነበረው ጁሊየስ ቄሳር እነዚህ የዱር በሬዎች ከዝሆን ምንም ያህል እንደማያንሱ ገልጿል። “ጉልበታቸውም ሆነ ፍጥነታቸው አስገራሚ ነው” ሲል ጽፏል። እንዲህ ያለው እንስሳ አጠገብ ብትቆም ምን ያህል ትንሽና አቅመ ቢስ ሆነህ እንደምትታይ ገምት!
6. “ሁሉን ቻይ” ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
6 በተመሳሳይም ሰው፣ ታላቅ ኃይል ካለው ከይሖዋ አንጻር ሲታይ ኢምንትና አቅመ ቢስ ነው። ኃያላን መንግሥታት እንኳ በይሖዋ ፊት በሚዛን ላይ እንዳለ አቧራ ናቸው። (ኢሳይያስ 40:15) ገደብ የለሽ ኃይል ያለው ይሖዋ ብቻ በመሆኑ ከእሱ በስተቀር “ሁሉን ቻይ” ተብሎ ሊጠራ የሚችል የለም።a (ራእይ 15:3) ይሖዋ ‘ገደብ የሌለው ብርቱ ጉልበትና የሚያስደምም ኃይል’ አለው። (ኢሳይያስ 40:26) ምንጊዜም የማይነጥፍ የኃይል ምንጭ ነው። “ብርታት የአምላክ” ስለሆነ ከሌላ ምንጭ ኃይል ማግኘት አያስፈልገውም። (መዝሙር 62:11) ይሁንና ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጠው በምን አማካኝነት ነው?
ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጠው በምን አማካኝነት ነው?
7. የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ምንድን ነው? በበኩረ ጽሑፉ ላይ የገቡት ቃላትስ ምን ያመለክታሉ?
7 ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ያለ ገደብ ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ የዋለ የአምላክ ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1:2 ላይ ይህን መንፈስ ‘የአምላክ ኃይል’ ሲል ይጠራዋል። በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙት “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በሌሎች ጥቅሶች ላይ “ነፋስ” እና “እስትንፋስ” ተብለው ተተርጉመዋል። የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች የዕብራይስጡና የግሪክኛው ቃላት፣ በሥራ ላይ የዋለን የማይታይ ኃይል እንደሚያመለክቱ ይገልጻሉ። ነፋስን ማየት እንደማንችል ሁሉ የአምላክን መንፈስም ማየት አንችልም፤ ሆኖም የሚያከናውናቸውን ነገሮች ማየት እንችላለን።
8. የአምላክ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ ምን ተብሎ ተገልጿል? ይህ ንጽጽርስ ተስማሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
8 የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የማያከናውነው ነገር የለም። ይሖዋ ዓላማውን ሁሉ ዳር ለማድረስ ሊጠቀምበት ይችላል። ስለሆነም የአምላክ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክ “ጣት፣” “ብርቱ እጅ” ወይም ‘የተዘረጋ ክንድ’ ተብሎ መጠራቱ ተስማሚ ነው። (ሉቃስ 11:20፤ ዘዳግም 5:15፤ መዝሙር 8:3) አንድ ሰው የተለያየ ጉልበት ወይም ችሎታ የሚጠይቁ በርካታ ሥራዎችን በእጁ ማከናወን እንደሚችል ሁሉ አምላክም መንፈሱን በመጠቀም የተለያዩ ነገሮችን ማከናወን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ረቂቅ የሆነችውን አተም ለመፍጠር ወይም ቀይ ባሕርን ለመክፈል አሊያም ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በልሳን እንዲናገሩ ለማድረግ ተጠቅሞበታል።
9. ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጥበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?
9 በተጨማሪም ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ይህን ሥልጣኑን በሚጠቀምበት መንገድ ኃይሉን ይገልጣል። የምትሰጣቸውን ማንኛውንም ትእዛዝ ለመፈጸም ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተገዢዎች ቢኖሩህ ምን ይሰማሃል? ይሖዋ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ሥልጣን አለው። ትእዛዙን የሚፈጽሙ ብዙ ሰብዓዊ አገልጋዮች ያሉት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ሠራዊት ተብለው ተጠርተዋል። (መዝሙር 68:11፤ 110:3) ይሁን እንጂ ሰው ከመላእክት አንጻር ሲታይ ደካማ ፍጡር ነው። ለምሳሌ የአሦር ሠራዊት በአምላክ ሕዝብ ላይ ጥቃት በሰነዘረበት ጊዜ አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት 185,000 ወታደሮችን ገድሏል! (2 ነገሥት 19:35) የይሖዋ መላእክት “ብርቱዎችና ኃያላን” ናቸው።—መዝሙር 103:19, 20
10. (ሀ) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ የሠራዊት ጌታ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? (ለ) ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ ይበልጥ ኃያል የሆነው ማን ነው?
10 ይሖዋ የፈጠራቸው መላእክት ምን ያህል ናቸው? ነቢዩ ዳንኤል ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ መላእክት በሰማይ በይሖዋ ዙፋን ፊት ቆመው በራእይ ተመልክቷል፤ ሆኖም በሰማይ ያሉት መላእክት እነዚህ ብቻ እንደሆኑ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። (ዳንኤል 7:10) ስለዚህ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት ሊኖሩ ይችላሉ። ስለሆነም ይሖዋ የሠራዊት ጌታ ተብሎ ተጠርቷል። ይህ የማዕረግ ስም አምላክ በሚገባ የተደራጁትን ብዛት ያላቸው ኃያላን መላእክት በበላይነት እንደሚቆጣጠርና እንደሚያዝ ያመለክታል። “የፍጥረት ሁሉ በኩር” የሆነውን የሚወደውን ልጁን በእነዚህ መላእክት ላይ አዛዥ አድርጎ ሾሞታል። (ቆላስይስ 1:15) ኢየሱስ የሱራፌል፣ የኪሩቤልና የመላእክት ሁሉ አለቃ በመሆኑ ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ ይበልጥ ኃያል ነው።
11, 12. (ሀ) የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ኃይል ምን ምሥክርነት ሰጥቷል?
11 ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጥበት ሌላም መንገድ አለ። ዕብራውያን 4:12 “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የአምላክ ቃል ወይም በመንፈስ መሪነት የተነገረው መልእክት አስደናቂ ኃይል እንዳለው አስተውለሃል? ሊያጠነክረን፣ እምነታችንን ሊገነባና በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እጅግ ብልሹ በሆነ አኗኗር ከተጠመዱ ሰዎች እንዲርቁ ካሳሰበ በኋላ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) አዎን፣ “የአምላክ ቃል” ኃይል ያለው በመሆኑ እነዚህ ሰዎች አኗኗራቸውን እንዲለውጡ ረድቷቸዋል።
12 የይሖዋ ኃይል እጅግ ታላቅ በመሆኑ ማንኛውንም ነገር ከማከናወን ሊያግደው የሚችል አይኖርም። ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል” ብሏል። (ማቴዎስ 19:26) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀምበት ለምን ዓላማ ነው?
ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀመው በዓላማ ነው
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ግዑዝ የኃይል ምንጭ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ኃይሉን ምን ለማድረግ ይጠቀምበታል?
13 የይሖዋ መንፈስ ከማንኛውም ኃይል እጅግ የላቀ ነው። ይሖዋ ግዑዝ የሆነ የኃይል ምንጭ አይደለም። ኃይሉን በፈለገው መንገድ መቆጣጠርና መጠቀም የሚችል አምላክ ነው። ይሁንና ኃይሉን እንዲጠቀምበት የሚያነሳሳው ምንድን ነው?
14 ወደፊት አንድ በአንድ እንደምንመለከተው አምላክ ኃይሉን ለመፍጠር፣ ለማጥፋት፣ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ፣ አንድን ነገር ለማደስና በአጠቃላይ ፍጹም የሆነውን ዓላማውን ሁሉ ለማስፈጸም ይጠቀምበታል። (ኢሳይያስ 46:10) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያቱንና መሥፈርቶቹን ይገልጣል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈቃዱን ለመፈጸም ይኸውም በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ስሙን ለማስቀደስ እና የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ለማሳየት ይጠቀምበታል። ይህን ዓላማ ሊያከሽፍ የሚችል ምንም ነገር የለም።
15. ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ ኃይሉን ምን ለማድረግ ይጠቀምበታል? ይህስ ኤልያስ ባጋጠመው ሁኔታ የታየው እንዴት ነው?
15 በተጨማሪም ይሖዋ ኃይሉን እኛን በግለሰብ ደረጃ ለመርዳት ይጠቀምበታል። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 16:9 “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ” ይላል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የኤልያስ ታሪክ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው። ይሖዋ መለኮታዊ ኃይሉን አስፈሪ በሆነ መንገድ የገለጸለት ለምንድን ነው? ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል ኤልያስን ለማስገደል ምላ ነበር። ነቢዩ ነፍሱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ብሎ ሸሸ። ከመፍራቱና ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና ብቻውን እንደቀረ ሆኖ ተሰማው። ይሖዋ እጅግ የተጨነቀውን ኤልያስን ለማጽናናት መለኮታዊ ኃይሉን ሕያው በሆነ መንገድ ገለጸለት። ነፋሱ፣ የምድር መናወጡና እሳቱ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ኃያል የሆነው አምላክ እንደሚረዳው ለኤልያስ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው። ኤልያስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከጎኑ እያለ ኤልዛቤልን የሚፈራበት ምን ምክንያት አለው?—1 ነገሥት 19:1-12b
16. ስለ ይሖዋ ታላቅ ኃይል ማሰላሰላችን ሊያጽናናን የሚችለው ለምንድን ነው?
16 ምንም እንኳ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ተአምር የማይሠራ ቢሆንም በኤልያስ ዘመን የነበረው አምላክ አሁንም አልተለወጠም። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ዛሬም ቢሆን ኃይሉን በመጠቀም የሚወዱትን ሰዎች ለመርዳት ዝግጁ ነው። ሊደረስበት በማይችል መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የሚኖር ቢሆንም ከእኛ የራቀ አይደለም። ኃይሉን ርቀት አይገድበውም። “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው።” (መዝሙር 145:18) በአንድ ወቅት ነቢዩ ዳንኤል የይሖዋን እርዳታ እየጠየቀ ሳለ ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ አንድ መልአክ ተገልጦለታል! (ዳንኤል 9:20-23) ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች ከመርዳትና ከማበረታታት ሊያግደው የሚችል ነገር የለም።—መዝሙር 118:6
አምላክ ያለው ኃይል ሰዎች እንዳይቀርቡት የሚያደርግ ነው?
17. የይሖዋ ኃይል ፍርሃት የሚያሳድርብን ከምን አንጻር ነው? ይሁን እንጂ ምን ዓይነት ፍርሃት ሊያሳድርብን አይገባም?
17 አምላክ ያለው ኃይል እንድንፈራው ሊያደርገን ይገባል? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ይገባልም፣ አይገባምም የሚል መሆን አለበት። ልንፈራው ይገባል የምንለው ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ በአጭሩ እንደተመለከትነው ይህ የይሖዋ ባሕርይ ከአድናቆትና ከጥልቅ አክብሮት የመነጨ አምላካዊ ፍርሃት ስለሚያሳድርብን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው ፍርሃት “የጥበብ መጀመሪያ” እንደሆነ ይገልጻል። (መዝሙር 111:10) ልንፈራው አይገባም የምንለው ደግሞ አምላክ ያለው ኃይል በፍርሃት እንድንርድ ወይም ከእሱ እንድንርቅ የሚያደርግ ስላልሆነ ነው።
18. (ሀ) ብዙዎች በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን የማያምኑት ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሥልጣኑን አላግባብ እንደማይጠቀምበት እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
18 በ1887 እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ ሎርድ አክተን “ሥልጣን ያባልጋል፤ ገደብ የሌለው ሥልጣን ደግሞ የባሰ ያባልጋል” ሲሉ ጽፈው ነበር። ይህ አባባል በብዙዎች ዘንድ የማይታበል ሐቅ እንደሆነ ስለሚታመን በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይሰማል። ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሥልጣናቸውን አላግባብ ይጠቀሙበታል። (መክብብ 4:1፤ 8:9) በዚህም ምክንያት ብዙዎች በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ስለማያምኗቸው ይርቋቸዋል። ይሖዋ ገደብ የለሽ ሥልጣን አለው። ታዲያ ይህን ሥልጣኑን አላግባብ ይጠቀምበታል? በፍጹም! ቀደም ሲል እንዳየነው ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት አይፈጽምም። በዚህ በተበላሸ ዓለም ውስጥ በሥልጣን ላይ ካሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። በሥልጣኑ አላግባብ ተጠቅሞ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጠቀምም።
19, 20. (ሀ) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀመው ከየትኞቹ ሌሎች ባሕርያት ጋር በሚጣጣም መንገድ ነው? ይህስ የሚያጽናናን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ራሱን የሚገዛ አምላክ መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው? ይህ ባሕርይው የሚማርክህስ ለምንድን ነው?
19 ይሖዋ ኃይል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባሕርያትም እንዳሉት አስታውስ። ወደፊት ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን እንመረምራለን። ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህን ባሕርያቱን በተናጠል እንደሚጠቀም አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ እንደምንመለከተው ይሖዋ ምንጊዜም ኃይሉን የሚጠቀመው ከፍትሑ፣ ከጥበቡና ከፍቅሩ ጋር በሚጣጣም መንገድ ነው። በተጨማሪም አምላክ አብዛኞቹ የዓለም መሪዎች የሚጎድላቸው አንድ ባሕርይ አለው፤ ይህም ራስን መግዛት ነው።
20 ሲያዩት በሚያስፈራ አንድ ግዙፍ ሰው ፊት ስትቀርብ ምን እንደሚሰማህ አስብ። ይሁን እንጂ ስትቀርበውና ስታውቀው ደግ ሰው እንደሆነ ትገነዘባለህ። ሰዎችን በተለይ ደግሞ አቅም የሌላቸውን መርዳትና መንከባከብ ያስደስተዋል። ኃይሉን ሌሎችን ለመጉዳት አይጠቀምበትም። ሰዎች ስሙን አላግባብ ሲያጠፉ እንኳ ባሕርይው አይለወጥም። በቁጣ ከመገንፈል ይልቅ የተፈጠረውን ችግር በረጋ መንፈስ አልፎ ተርፎም በደግነት ለመፍታት ጥረት ያደርጋል። ‘እኔ ብሆን ኖሮ የዚህን ሰው ያህል አካላዊ ጥንካሬ እያለኝ እንዲህ ያለ ባሕርይ አሳይ ነበር?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ አይቀርም። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያለውን ሰው በሚገባ ስታውቀው ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ አትገፋፋም? ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ምክንያት አለን። የዚህ ምዕራፍ ርዕስ የተመሠረተበት ጥቅስ ምን እንደሚል ተመልከት፦ “ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ ነው፤ ኃይሉም ታላቅ ነው።” (ናሆም 1:3) ይሖዋ ክፉ በሆኑ ሰዎችም ላይ እንኳ ሳይቀር ኃይሉን ለመጠቀም አይቸኩልም። ነገሮችን በእርጋታ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ደግ ነው። ሊያስቆጡት የሚችሉ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢያጋጥሙትም “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑን አስመሥክሯል።—መዝሙር 78:37-41
21. ይሖዋ ሰዎች ፈቃዱን እንዲያደርጉ የማያስገድደው ለምንድን ነው? ይህ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?
21 ይሖዋ ራሱን እንደሚገዛ ያሳየበትን ሌላ ሁኔታም ተመልከት። ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ቢኖርህ ኖሮ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አንድን ነገር አንተ በፈለግኸው መንገድ ብቻ እንዲያከናውኑ ለማስገደድ ልትፈተን ትችል እንደነበር ይሰማሃል? ይሖዋ ታላቅ ኃይል ያለው አምላክ ቢሆንም ሰዎች እንዲያገለግሉት አያስገድድም። የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው እሱን በማገልገል ብቻ ቢሆንም ይሖዋ እንድናገለግለው አያስገድደንም። ከዚህ ይልቅ ለእያንዳንዱ ሰው የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል። መጥፎ ምርጫ ምን መዘዝ እንደሚያስከትልና ጥሩ ምርጫ ደግሞ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ አስቀድሞ ያሳውቃል። ምርጫውን ግን ለእኛ ይተወዋል። (ዘዳግም 30:19, 20) ይሖዋ ተገድደን ወይም ታላቅ ኃይሉ በሚያሳድርብን ፍርሃት ተሸብረን ሳይሆን በፍቅር ተነሳስተን በፈቃደኝነት እንድናገለግለው ይፈልጋል።—2 ቆሮንቶስ 9:7
22, 23. (ሀ) ይሖዋ ለሌሎች ሥልጣንና ኃይል መስጠት እንደሚያስደስተው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ ምን ጉዳይ እንመረምራለን?
22 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ ኃይል ያለው መሆኑ እንድንፈራና እንድንንቀጠቀጥ ሊያደርገን የማይገባው ለምን እንደሆነ የሚጠቁም ተጨማሪ ምክንያት እንመልከት። ሰዎች ሥልጣንን ለሌሎች ማጋራት ያስፈራቸዋል። ይሖዋ ግን ታማኝ ለሆኑ አምላኪዎቹ ሥልጣን መስጠት ያስደስተዋል። ለምሳሌ ያህል ለልጁ ከፍተኛ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:18) በተጨማሪም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታላቅነት፣ ኃያልነት፣ ውበት፣ ግርማና ሞገስ የአንተ ነው፤ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነው። . . . ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ እጅህ ሁሉንም ታላቅ ማድረግና ለሁሉም ብርታት መስጠት ይችላል።”—1 ዜና መዋዕል 29:11, 12
23 አዎን፣ ይሖዋ ኃይል ለመስጠት ዝግጁ ነው። እንዲያውም እሱን ማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ይሖዋ ኃይሉን በአግባቡና አሳቢነት በተሞላበት መንገድ የሚጠቀም አምላክ ነው። ታዲያ ይህ እንድትወድደውና ወደ እሱ እንድትቀርብ አይገፋፋህም? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይሖዋ የተለያዩ ነገሮችን ለመፍጠር ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት እንመለከታለን።
a “ሁሉን ቻይ” የሚል ፍቺ የተሰጠው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “በሁሉ ላይ የሚገዛ፣ የሥልጣን ሁሉ ባለቤት” ማለት ነው።
b መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘በነፋሱ፣ በምድር መናወጡም ሆነ በእሳቱ ውስጥ እንዳልነበረ’ ይገልጻል። በአፈ ታሪክ የሚነገሩ አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎች አምላክ በተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ እንዳለ አድርገው ያስባሉ። የይሖዋ አገልጋዮች ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም። እጅግ ታላቅ አምላክ በመሆኑ እሱ በፈጠራቸው ነገሮች ውስጥ ሊኖር አይችልም።—1 ነገሥት 8:27
-
-
‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’—ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይልወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 5
‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’—ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይል
1, 2. ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ኃይል ለማስረዳት ፀሐይ እንደ ምሳሌ ልትጠቀስ የምትችለው ለምንድን ነው?
በርዶህ እሳት ሞቀህ ታውቃለህ? እሳቱ አጠገብ ሆነህ እጆችህን ዘርግተህ እየሞቅክ ነው እንበል። በጣም ከተጠጋህ ወላፈኑ ሊያቃጥልህ ይችላል። በጣም ከራቅህ ደግሞ ይበርድሃል።
2 ቀን ቀን ሰውነታችንን የሚያሞቅ አንድ “እሳት” አለ። ይህ “እሳት” የሚገኘው ከእኛ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ነው!a በእሳት የተመሰለችው ፀሐይ ያን ከሚያህል ርቀት ለእኛ ሙቀት መስጠት የቻለችው ምን ያህል ኃይል ቢኖራት እንደሆነ ገምት! ይሁንና ምድራችን ኃይለኛ እሳት የሚንቀለቀልባትን ይህችን ምድጃ የምትዞረው በትክክለኛ ርቀት ላይ ሆና ነው። ምድር ወደ ፀሐይ ቀረብ ብትል ኖሮ በላይዋ ላይ ያለው ውኃ ሁሉ ይተን ነበር። ከፀሐይ በጣም ብትርቅ ደግሞ በምድር ላይ ያለው ውኃ ሁሉ በረዶ ይሆናል። ስለዚህ ፕላኔታችን ለፀሐይ ትንሽ ብትቀርብም ሆነ ብትርቅ ሕይወት ያለው ነገር ሊኖርባት አይችልም። በተጨማሪም በምድር ላይ ላለው ሕይወት ወሳኝ የሆነው ይህ የፀሐይ ብርሃን፣ ምንም ዓይነት ብክለት የማያስከትልና ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ የሚውል ብሎም ደስ የሚያሰኝ ነው።—መክብብ 11:7
3. ፀሐይ ምን ሐቅ ታስገነዝበናለች?
3 ሰዎች ሕልውናቸው በፀሐይ ላይ የተመካ ቢሆንም እንኳ ፀሐይ ስለምትሰጠው ጥቅም የሚያስቡት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። በመሆኑም ከፀሐይ ሊማሩ የሚችሉት ቁም ነገር ያመልጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ብርሃንንና ፀሐይን ሠራህ” ይላል። (መዝሙር 74:16) አዎን፣ ፀሐይ ‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’ የሆነውን የይሖዋን ክብር ትናገራለች። (መዝሙር 19:1፤ 146:6) ይሁንና ፀሐይ፣ ይሖዋ ለመፍጠር የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ከሚጠቁሙት የሰማይ አካላት መካከል አንዷ ብቻ ናት። እንግዲያው ትኩረታችንን ወደ ምድርና በላይዋ ወደሚኖሩት ሕያዋን ነገሮች ከማዞራችን በፊት ከእነዚህ የሰማይ አካላት መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።
ይሖዋ “ብርሃንንና ፀሐይን” ሠርቷል
“ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ”
4, 5. (ሀ) ፀሐይ ምን ያህል ኃይል አላት? ምን ያህልስ ግዙፍ ናት? (ለ) ፀሐይን ከሌሎች ከዋክብት ጋር ማነጻጸር የሚቻለው እንዴት ነው?
4 እንደምታውቀው ፀሐይ ራሷ ኮከብ ናት። ከሌሎቹ ከዋክብት አንጻር ሲታይ ለምድር ቀረብ ያለች ስለሆነች ትልቅ መስላ ትታየናለች። ለመሆኑ ፀሐይ ያላት ኃይል ምን ያህል ነው? የፀሐይ እምብርት 15,000,000 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ገደማ የሚደርስ ሙቀት አለው። ከፀሐይ እምብርት፣ ጤፍ የምታክል ቅንጣት ወስደህ ምድር ላይ ማስቀመጥ ብትችል ወደዚህች ቅንጣት ከ140 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ መቅረብ አትችልም! ፀሐይ በየሴኮንዱ ከብዙ መቶ ሚሊዮን የኑክሌር ቦምብ ፍንዳታዎች ጋር የሚመጣጠን ኃይል ታመነጫለች።
5 ፀሐይ እጅግ ግዙፍ ከመሆኗ የተነሳ ምድራችንን የሚያክሉ ከ1,300,000 የሚበልጡ ፕላኔቶችን መያዝ ትችላለች። እንዲህ ሲባል የመጨረሻዋ ግዙፍ ኮከብ ናት ማለት ነው? በፍጹም፤ እንዲያውም የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ትንሿ ቢጫ ኮከብ በማለት ይጠሯታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:41) ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የተነገሩት እነዚህ ቃላት ምን ያህል እውነት እንደሆኑ ብዙም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አሁን ፀሐይ የምትገኝበት ቦታ ላይ ቢሆን ኖሮ ምድራችንን ጭምር ሊሸፍን የሚችል ግዙፍ ኮከብ አለ። አንድ ሌላ ግዙፍ ኮከብ ደግሞ ፀሐይ ያለችበት ቦታ ላይ ቢሆን ሳተርን የተባለችው ፕላኔት እስከምትገኝበት ቦታ ሊደርስ ይችላል። ሳተርን ከምድር እጅግ ርቃ የምትገኝ ከመሆኗ የተነሳ አንዲት የጠፈር መንኮራኩር ከጥይት 40 ጊዜ እጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት እየተወነጨፈች ሳተርን ላይ ለመድረስ አራት ዓመታት ፈጅቶባታል!
6. ከሰው ችሎታ አንጻር ሲታይ ከዋክብት ሊቆጠሩ እንደማይችሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው እንዴት ነው?
6 ከዋክብት ካላቸው መጠን ይበልጥ የሚያስገርመው ብዛታቸው ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ከዋክብት እንደ ‘ባሕር አሸዋ’ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ሊቆጠሩ እንደማይችሉ ይገልጻል። (ኤርምያስ 33:22) ይህ ጥቅስ በዓይናችን ልናያቸው ከምንችላቸው በላይ በጣም ብዙ ከዋክብት እንዳሉ ይጠቁማል። እንደ ኤርምያስ ያለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በምሽት ወደ ሰማይ አንጋጦ በዓይኑ የሚያያቸውን ከዋክብት ለመቁጠር ቢሞክር ከሦስት ሺህ በላይ ሊቆጥር አይችልም። ምክንያቱም አንድ ሰው በጠራ ሰማይ ላይ ያላንዳች መሣሪያ እገዛ በዓይኑ ብቻ ከዚህ የበለጡ ከዋክብት ሊያይ አይችልም። ይህ ቁጥር ከአንድ እፍኝ አሸዋ ብዛት አይበልጥም። ይሁንና የከዋክብት ብዛት ልክ እንደ ባሕር አሸዋ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ነው።b ለመሆኑ የባሕር አሸዋን ሊቆጥር የሚችል ይኖራል?
“ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል”
7. ተመራማሪዎች በፍኖተ ሐሊብ ጋላክሲ ውስጥ ስላሉት ከዋክብት ብዛትም ሆነ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ስላሉት ጋላክሲዎች ብዛት ምን ይገምታሉ?
7 ኢሳይያስ 40:26 እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል፦ “ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ። እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው? እንደ ሠራዊት በቁጥር የሚመራቸው እሱ ነው፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።” መዝሙር 147:4 “የከዋክብትን ብዛት ይቆጥራል” ይላል። ‘የከዋክብት ብዛት’ ስንት ነው? ይህ ከባድ ጥያቄ ነው። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ምድራችን በምትገኝበት ፍኖተ ሐሊብ በመባል በሚታወቀው ጋላክሲ ውስጥ ብቻ እንኳ ከ100 ቢሊዮን የሚበልጡ ከዋክብት እንዳሉ ይገምታሉ።c አንዳንዶች ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም በጣም እንደሚበልጥ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ፍኖተ ሐሊብ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ጋላክሲዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው፤ እንዲያውም አብዛኞቹ ጋላክሲዎች ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸውን ከዋክብት ያቀፉ ናቸው። ለመሆኑ ስንት ጋላክሲዎች አሉ? ተመራማሪዎች በመቶ ቢሊዮኖች አልፎ ተርፎም በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች እንዳሉ ይገምታሉ። ስለሆነም የሰው ልጅ፣ በጋላክሲዎች ውስጥ የሚገኙትን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብት ብዛት ይቅርና የጋላክሲዎችን ብዛት እንኳ በትክክል ማወቅ የቻለ አይመስልም። ይሖዋ ግን ብዛታቸውን በትክክል ያውቃል። አልፎ ተርፎም ለእያንዳንዱ ኮከብ ስም አውጥቷል!
8. (ሀ) የፍኖተ ሐሊብን ስፋት እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ? (ለ) ይሖዋ የሰማይ አካላትን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው በምን አማካኝነት ነው?
8 ስለ ጋላክሲዎች ስፋት ስናስብ ለይሖዋ ያለን አክብሮትና አድናቆት ይጨምራል። ፍኖተ ሐሊብ የተሰኘው ጋላክሲ ከጫፍ እስከ ጫፍ 100,000 የብርሃን ዓመት ገደማ ርቀት እንዳለው ይገመታል። በሴኮንድ 300,000 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ አንድ የብርሃን ጨረር በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይህ የብርሃን ጨረር ምድራችን የምትገኝበትን ጋላክሲ ለማቋረጥ 100,000 ዓመት ይፈጅበታል! አንዳንዶቹ ጋላክሲዎች ከዚህ ጋላክሲ ብዙ ጊዜ እጥፍ ይበልጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሰማያትን እንደ መጋረጃ ‘እንደዘረጋቸው’ ይገልጻል። (መዝሙር 104:2) የእነዚህን አካላት እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረውም እሱ ነው። በጠፈር ላይ ካለችው አነስተኛ የአቧራ ቅንጣት አንስቶ እስከ ትልቁ ጋላክሲ ድረስ ያለው ነገር በሙሉ የሚንቀሳቀሰው አምላክ ባወጣው የቁስ አካል ሕግ መሠረት ነው። (ኢዮብ 38:31-33) በመሆኑም ሳይንቲስቶች ዝንፍ የማይለውን የሰማይ አካላት እንቅስቃሴ በጣም ውስብስብ ከሆነ የዳንስ ጥበብ ጋር አመሳስለውታል። እነዚህን ነገሮች ስለፈጠረው አምላክ ስታስብ እንዲህ ያለ ታላቅ ኃይል ያለው መሆኑ በአድናቆት ስሜት እንድትዋጥ አያደርግህም?
“ምድርን በኃይሉ የሠራ”
9, 10. ምድራችን የምትገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ፣ ጁፒተር፣ ምድር ራሷና ጨረቃ የይሖዋን ታላቅ ኃይል የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
9 የምንኖርባት ምድርም ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ኃይል በግልጽ ታሳያለች። በዚህ ሰፊ አጽናፈ ዓለም ውስጥ አምላክ ምድርን ያስቀመጣት በትክክለኛው ቦታ ላይ ነው። አንዳንድ ሳይንቲስቶች በብዙ ጋላክሲዎች ውስጥ እንደ ምድራችን ሕይወት ላላቸው ነገሮች ተስማሚ የሆኑ ፕላኔቶች እንደሌሉ ይናገራሉ። የፍኖተ ሐሊብ አብዛኛው ክፍል ሕይወት ላለው ነገር መኖሪያነት ምቹ ሆኖ የተፈጠረ አይደለም። የጋላክሲው ማዕከላዊ ክፍል በከዋክብት የታጨቀ ነው። በዚህም የተነሳ ኃይለኛ ጨረር የሚመነጭ ከመሆኑም በላይ በእነዚህ ከዋክብት መካከል ከፍተኛ የመሳሳብ ኃይል አለ። ወደ ጋላክሲው ጠረፍ አካባቢ ደግሞ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች አይገኙም። ምድራችን የምትገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ ያለው በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል እጅግ ተስማሚ በሆነ ቦታ ላይ ነው።
10 ከመሬት በጣም ርቃ የምትገኘው ጁፒተር የተሰኘችው ፕላኔት ለምድራችን ትልቅ ከለላ ሆና ታገለግላለች። ጁፒተር ከመሬት ሺህ ጊዜ እጥፍ ስለምትበልጥ ከፍተኛ የሆነ የስበት ኃይል አላት። በመሆኑም ጠፈርን አቋርጠው የሚመጡ ተወርዋሪ አካላትን ስባ ታስቀራለች አሊያም አቅጣጫ ታስታለች። ሳይንቲስቶች እንደሚገምቱት ከሆነ ጁፒተር ባትኖር ኖሮ ወደ መሬት የሚዥጎደጎዱት ተወርዋሪ አካላት በምድራችን ላይ የሚያደርሱት ጉዳት 10,000 ጊዜ እጥፍ ይጨምር ነበር። የምንኖርባት ምድር አንዲት ለየት ያለች ሳተላይት አለቻት። ይህች ሳተላይት ማለትም ጨረቃ እንዲሁ ለምድር ውበት የምትጨምርና በሌሊት ብርሃን የምትሰጥ አካል እንደሆነች ብቻ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ምድር ምንጊዜም ወደ አንድ ወገን ዘንበል ብላ እንድትኖር በማድረግ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲፈራረቁ ትልቅ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። ይህ ደግሞ በምድር ላይ ላለው ሕይወት በጣም ወሳኝ ነው።
11. የምድር ከባቢ አየር እንደ ከለላ ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው?
11 እያንዳንዱ የምድር ንድፍ ይሖዋ የተለያዩ ነገሮችን ለመፍጠር ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ምድርን እንደ ጃንጥላ የሚከልለውን ከባቢ አየር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ፀሐይ ጠቃሚና ጎጂ የሆኑ ጨረሮችን ታመነጫለች። ጎጂዎቹ ጨረሮች በምድር ከባቢ አየር ላይ ሲያርፉ በከባቢ አየሩ ውስጥ የሚገኘው ኦክስጅን ወደ ኦዞን ይቀየራል። ይህ የኦዞን ሽፋን አብዛኞቹን ጎጂ ጨረሮች ውጦ ያስቀራል። በመሆኑም ፕላኔታችን የተፈጠረችው የራሷ የሆነ ከለላ እንዲኖራት ተደርጋ ነው።
12. በከባቢ አየር ውስጥ የሚካሄደው የውኃ ዑደት የፈጣሪን ኃይል የሚያሳየው እንዴት ነው?
12 በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ ጋዞችን አቅፎ የያዘው ከባቢ አየር ሌሎችም አስደናቂ ገጽታዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል አንዱ የውኃ ዑደት ነው። የፀሐይ ሙቀት ከውቅያኖስና ከባሕር በየዓመቱ 400,000 ኪሎ ሜትር ኩብ ውኃ ወደ ሰማይ እንዲተን ያደርጋል። የተነነው ውኃ ወደ ደመናነት የሚለወጥ ሲሆን ደመናው ደግሞ በከባቢ አየር ውስጥ በሚገኙ ነፋሳት ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳል። ውኃው ከተጣራ በኋላ በዝናብና በበረዶ መልክ ተመልሶ ወደ ምድር ይመጣል። መክብብ 1:7 ይህን ዑደት “ጅረቶች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤ ሆኖም ባሕሩ አይሞላም። ጅረቶቹ እንደገና ይፈስሱ ዘንድ ወደሚነሱበት ወደዚያው ቦታ ተመልሰው ይሄዳሉ” ሲል ገልጾታል። እንዲህ ዓይነት ዑደት እንዲኖር ሊያደርግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።
13. የምድር ዕፀዋትና አፈር የፈጣሪን ኃይል የሚያሳዩት እንዴት ነው?
13 ሕይወት በአጠቃላይ የፈጣሪን ታላቅ ኃይል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ከ30 ፎቅ የበለጠ ርዝማኔ ካለው ከግዙፉ ሴኮያ ዛፍ አንስቶ አብዛኛውን ኦክስጅን እስከሚያመነጩት ረቂቅ የባሕር ውስጥ ዕፀዋት ድረስ ያሉት ሕያዋን ነገሮች ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ታላቅ ኃይል ያንጸባርቃሉ። ሌላው ቀርቶ በአፈር ውስጥ እንኳ እንደ ትላትል፣ ፈንገስና ረቂቅ ተሕዋሲያን ያሉ ብዙ ሕያዋን ፍጥረታት ይገኛሉ። እነዚህ በአፈር ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታት ለዕፀዋት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ወይም አፈር ኃይል እንዳለው መናገሩ የተገባ ነው።—ዘፍጥረት 4:12 የግርጌ ማስታወሻ
14. በአንዲት አነስተኛ አተም ውስጥ እንኳ ምን ያህል የታመቀ ኃይል አለ?
14 በእርግጥም “ምድርን በኃይሉ የሠራው” ይሖዋ ነው። (ኤርምያስ 10:12) የአምላክ ኃይል በፈጠራቸው ጥቃቅን ነገሮች ላይ እንኳ ሳይቀር ታይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሚሊዮን አተሞች ጎን ለጎን ቢቀመጡ የአንዲት ፀጉር ያህል እንኳ ውፍረት አይኖራቸውም። በተጨማሪም አንድ አተም ተለጥጦ 14 ፎቅ ያለው ሕንፃ ርዝማኔ እንዲኖረው ቢደረግ እንኳ የአተሙ እምብርት (ኑክሊየስ) የሚኖረው መጠን በሕንፃው ሰባተኛ ፎቅ ላይ ካለች የጨው ቅንጣት አይበልጥም። ይሁን እንጂ ከባድ የኑክሌር ፍንዳታ የሚያስከትለው በዚህች እጅግ አነስተኛ የሆነች የአተም እምብርት ውስጥ ያለው ከፍተኛ ኃይል ነው!
“እስትንፋስ ያለው ሁሉ”
15. ይሖዋ የተለያዩ የዱር እንስሳትን በመጥቀስ ኢዮብን ምን አስተምሮታል?
15 ከዚህም በተጨማሪ በምድር ላይ ያሉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው እንስሳት የፈጣሪን ኃይል የሚያሳዩ ጉልህ ማስረጃዎች ናቸው። መዝሙር 148 ይሖዋን የሚያወድሱ በርካታ ነገሮችን የሚዘረዝር ሲሆን ከእነዚህም መካከል በቁጥር 10 ላይ የተጠቀሱት “የዱር እንስሳትና የቤት እንስሳት” ይገኙበታል። ይሖዋ የሰው ልጅ ፈጣሪውን ሊፈራና ሊያከብር የሚገባው ለምን እንደሆነ ለኢዮብ በገለጸበት ወቅት እንደ አንበሳ፣ የሜዳ አህያ፣ የዱር በሬ፣ ብሄሞት (ወይም ጉማሬ) እና ሌዋታን (አዞ ሳይሆን አይቀርም) ያሉ እንስሳትን ጠቅሷል። እዚህ ላይ ይሖዋ በአጽንኦት ሊገልጽ የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ሰው እነዚህን ለማላመድ አስቸጋሪ የሆኑ ኃይለኛ ፍጥረታት የሚፈራ ከሆነ እነሱን የፈጠረውን አምላክማ ምንኛ ሊፈራና ሊያከብር ይገባል!—ኢዮብ ምዕራፍ 38-41
16. ይሖዋ ከፈጠራቸው ወፎች መካከል አንዳንዶቹ ምን አስገራሚ ተሰጥኦ አላቸው?
16 መዝሙር 148:10 ‘ክንፍ ያላቸው ወፎችንም’ ይጠቅሳል። ስንት ዓይነት የአእዋፍ ዝርያዎች እንዳሉ አስብ! ይሖዋ ኢዮብን ባነጋገረበት ወቅት ስለ ሰጎን የጠቀሰለት ሲሆን “በፈረሱና በፈረሰኛው ላይ ትስቃለች” ብሎታል። በእርግጥም ሁለት ሜትር ተኩል ርዝማኔ ያላት ይህች ወፍ መብረር የማትችል ብትሆንም እንኳ በሰዓት 65 ኪሎ ሜትር መሮጥ የምትችል ሲሆን በአንድ እርምጃ ብቻ 4 ሜትር ተኩል ትወነጨፋለች! (ኢዮብ 39:13, 18) በሌላ በኩል ደግሞ አልበትሮስ የተባለችው ወፍ አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው በባሕር ላይ በማንዣበብ ሲሆን የክንፏ ርዝማኔ ከጫፍ እስከ ጫፍ 3 ሜትር ይሆናል። ክንፎቿን ምንም ሳታርገበግብ ቀጥ አድርጋ እንደዘረጋች በርከት ላሉ ሰዓታት አየር ላይ መንሳፈፍ ትችላለች። በአንጻሩ ግን ቢ ሃሚንግበርድ የተባለችው ወፍ ርዝማኔዋ አምስት ሴንቲ ሜትር ብቻ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉት አእዋፍ ሁሉ አነስተኛዋ ናት። ክንፎቿን በሴኮንድ 80 ጊዜ ያህል ልታርገበግብ ትችላለች! ይህች ልክ እንደ ዕንቁ የምታብረቀርቅ ወፍ እንደ ሄሊኮፕተር በአየር ላይ መቆም የምትችል ከመሆኑም በላይ የኋልዮሽ መብረር ትችላለች።
17. ብሉ ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ ምን ያህል ግዙፍ ነው? ይሖዋ ስለፈጠራቸው እንስሳት ስናስብ ምን ለማድረግ እንገፋፋለን?
17 መዝሙር 148:7 “የባሕር ፍጥረታት” እንኳ ሳይቀር ይሖዋን እንደሚያወድሱ ይናገራል። በፕላኔታችን ላይ ከኖሩት እንስሳት ሁሉ በግዝፈቱ ተወዳዳሪ የለውም የሚባለውን ብሉ ዌል የተሰኘውን ዓሣ ነባሪ እስቲ እንመልከት። “ጥልቅ ውኃዎች” ውስጥ የሚገኘው ይህ ፍጥረት ርዝማኔው 30 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ እንደሆነና ክብደቱ ደግሞ ከ30 ዝሆኖች ክብደት ጋር እንደሚመጣጠን ይገመታል። ምላሱ ብቻ የአንድ ዝሆን ያህል ክብደት አለው። ልቡ ደግሞ አንድ ትንሽ መኪና ያክላል። የዚህ እንስሳ ልብ በደቂቃ 9 ጊዜ ብቻ የሚመታ ሲሆን በአንጻሩ ግን ሃሚንግበርድ የተባለችው ወፍ ልብ በደቂቃ 1,200 ጊዜ ሊመታ ይችላል። ከዚህ ዓሣ ነባሪ የደም ሥሮች አንዱ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሕፃን ልጅ በውስጡ ሊድህ ይችላል። ይህን ሁሉ ስናስብ ልባችን በአድናቆት ተሞልቶ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ ያህን ያወድስ” የሚሉትን በመዝሙር መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ የሚገኙ ቃላት ለማስተጋባት አንገፋፋም?—መዝሙር 150:6
ይሖዋ ለመፍጠር ከተጠቀመበት ኃይል የምናገኘው ትምህርት
18, 19. ይሖዋ በምድር ላይ የፈጠራቸው ሕያዋን ነገሮች ብዛት ምን ያህል ነው? የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ስለ ሉዓላዊነቱ ምን ያስገነዝቡናል?
18 ይሖዋ መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ምን ያስተምረናል? ስለፈጠራቸው ነገሮች ብዛትና ዓይነት ስናስብ በግርምት ፈዘን እንቀራለን። አንድ መዝሙራዊ “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! . . . ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (መዝሙር 104:24) ይህ ሊታበል የማይችል ሐቅ ነው! የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በምድር ላይ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሕያዋን ፍጥረታት ዝርያዎች እንዳሉ ደርሰውበታል። ይሁን እንጂ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዝርያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገምቱም አሉ። አንድ የሥነ ጥበብ ሰው አእምሮው አዲስ የፈጠራ ሥራ ማመንጨት የሚሳነው ጊዜ አለ። በተቃራኒው ግን ይሖዋ አዲስ ነገር ለመፍጠር ያለው ችሎታ መቼም ቢሆን ሊነጥፍ አይችልም።
19 ይሖዋ መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ስለ ሉዓላዊነቱ የሚያስተምረን ነገር አለ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ “ፍጡራን” በመሆናቸው “ፈጣሪ” የሚለው ቃል ራሱ ይሖዋን ከሌሎች ይለየዋል። በፍጥረት ሥራ ወቅት “የተዋጣለት ሠራተኛ” የነበረው የይሖዋ አንድያ ልጅ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ፈጣሪ’ ወይም ‘ረዳት ፈጣሪ’ የተባለበት ቦታ አናገኝም። (ምሳሌ 8:30፤ ማቴዎስ 19:4) ከዚህ ይልቅ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደሆነ እናነባለን። (ቆላስይስ 1:15) ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብቱ የተረጋገጠ ነው።—ሮም 1:20፤ ራእይ 4:11
20. ይሖዋ በምድር ላይ ያከናወናቸውን የፍጥረት ሥራዎች ካጠናቀቀ በኋላ ያረፈው ከምን አንጻር ነው?
20 ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም አዳዲስ ነገሮችን መፍጠሩን አቁሟል? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በስድስተኛው የፍጥረት ቀን የፍጥረት ሥራዎቹን ካጠናቀቀ በኋላ “[በሰባተኛው] ቀን ይሠራው ከነበረው ሥራ ሁሉ ማረፍ ጀመረ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:2) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰባተኛው “ቀን” እሱ እስከነበረበት ዘመን ድረስ እንደዘለቀ በመግለጽ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝማኔ እንዳለው አመልክቷል። (ዕብራውያን 4:3-6) ይሁን እንጂ ‘አረፈ’ ሲባል ጭራሽ መሥራት አቁሟል ማለት ነው? በፍጹም፣ ይሖዋ መሥራቱን አቁሞ አያውቅም። (መዝሙር 92:4፤ ዮሐንስ 5:17) ስለዚህ “ማረፍ” የሚለው አነጋገር በምድር ላይ የሚያከናውነውን የፍጥረት ሥራ እንዳቆመ ብቻ የሚያመለክት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ዓላማውን ዳር ለማድረስ አሁንም ድረስ መሥራቱን አላቋረጠም። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ ማስጻፉ የዚህ ሥራው አንድ አካል ነው። ከዓላማው ጋር በተያያዘ የሚያከናውነው ሥራ በምዕራፍ 19 ላይ በዝርዝር የምንመለከተውን “አዲስ ፍጥረት” ማስገኘትንም ይጨምራል።—2 ቆሮንቶስ 5:17
21. ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይል ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ምን አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል?
21 ይሖዋ በስድስቱ የፍጥረት ቀናት ማብቂያ ላይ እንደተናገረው ሁሉ አሁንም የእረፍቱ ቀን ሲያልቅ በምድር ላይ ያለው ሥራው ሁሉ “እጅግ መልካም” እንደሆነ መናገር ይችላል። (ዘፍጥረት 1:31) ከዚያ በኋላ፣ መፍጠር የሚያስችለውን ገደብ የለሽ ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በዚያን ጊዜም ቢሆን መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ በአድናቆት እንድንዋጥ እንደሚያደርገን ምንም ጥርጥር የለውም። በፍጥረት ሥራዎቹ አማካኝነት ለዘላለም ስለ ይሖዋ መማራችንን እንቀጥላለን። (መክብብ 3:11) ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን መጠን ለእሱ ያለን አክብሮትና አድናቆት የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ደግሞ ከምንጊዜውም በበለጠ ወደ ታላቁ ፈጣሪያችን እንድንቀርብ ያደርገናል።
a ይህን ለመገመት የሚያስቸግር ርቀት ቀለል ባለ ሁኔታ ለመረዳት በሚከተለው መንገድ ማነጻጸር ይቻላል፦ በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር በሚከንፍ መኪና በቀን 24 ሰዓት ብትጓዝ ይህን ርቀት ለመሸፈን ከመቶ ዓመት በላይ ይወስድብሃል!
b አንዳንዶች፣ በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ብዙም ያልተራቀቀ እንደ ቴሌስኮፕ ያለ መሣሪያ ይጠቀሙ እንደነበረ ይገምታሉ። ‘እንዲህ ያለ መሣሪያ ባይጠቀሙ ኖሮ ከዋክብት እጅግ ብዙ እንደሆኑና ሊቆጠሩ እንደማይችሉ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ?’ የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው መሠረተ ቢስ መላ ምት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈውን ይሖዋን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
c አንድ መቶ ቢሊዮን ከዋክብትን ለመቁጠር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድብህ ገምት። በሴኮንድ አንድ ኮከብ እየቆጠርክ በቀን ለ24 ሰዓት ብትቆጥር 3,171 ዓመታት ይወስድብሃል!
-
-
‘ኃያል ተዋጊ የሆነው ይሖዋ’—ለማጥፋት የሚጠቀምበት ኃይልወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 6
‘ኃያል ተዋጊ የሆነው ይሖዋ’—ለማጥፋት የሚጠቀምበት ኃይል
1-3. (ሀ) እስራኤላውያን ምን አስፈሪ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ለሕዝቦቹ የተዋጋው እንዴት ነው?
እስራኤላውያን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ምሕረት የለሹ የግብፅ ሠራዊት አሳድዶ ሊደመስሳቸው ከኋላ በመገስገስ ላይ ነው።a ወደፊት ሸሽተው እንዳያመልጡ ቀይ ባሕር አለ። ዙሪያ ገባው ደግሞ ቀጥ ያለ ተራራ ነው። ይሁንና ሙሴ ተስፋ እንዳይቆርጡ እያበረታታቸው ነው። “ይሖዋ ራሱ ስለ እናንተ ይዋጋል” በማለት ዋስትና ሰጣቸው።—ዘፀአት 14:14
2 ሆኖም ሙሴ ወደ ይሖዋ ሳይጮኽ አልቀረም። በዚህም የተነሳ አምላክ “ለምን ወደ እኔ ትጮኻለህ? . . . በትርህን አንሳና እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር፤ ባሕሩንም ክፈለው” አለው። (ዘፀአት 14:15, 16) ከዚያ በኋላ የተፈጸመውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይሖዋ ወዲያውኑ መልአኩን በማዘዝ የደመናው ዓምድ ከእስራኤላውያን ኋላ እንዲቆም አደረገ፤ ይህ የደመና ዓምድ እንደ ግድግዳ ሆኖ ግብፃውያኑን በመጋረድ ግስጋሴያቸውን ገትቶት መሆን አለበት። (ዘፀአት 14:19, 20፤ መዝሙር 105:39) ሙሴ እጁን ሲዘረጋ ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ ባሕሩን ለሁለት ከፈለው። ውኃው ወደ በረዶነት የተለወጠ ያህል ረግቶ እንደ ግድግዳ በመቆሙ መላው የእስራኤል ሕዝብ ወለል ብሎ በተከፈተው ደረቅ መሬት ተሻገረ!—ዘፀአት 14:21፤ 15:8
3 ፈርዖን ይህን ተአምር ሲመለከት ወታደሮቹ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ማዘዝ ነበረበት። ይሁን እንጂ ትዕቢተኛው ፈርዖን ወታደሮቹ ጥቃት ለመሰንዘር ወደፊት እንዲገሰግሱ ትእዛዝ ሰጠ። (ዘፀአት 14:23) ግብፃውያኑ እስራኤላውያንን በማሳደድ ወደተከፈለው ባሕር ተንደርድረው ገቡ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የሠረገሎቻቸው መንኮራኩሮች በመወላለቃቸው ትርምስምሳቸው ወጣ። እስራኤላውያን ሙሉ በሙሉ ከተሻገሩ በኋላ ይሖዋ ሙሴን “ውኃው በግብፃውያን፣ በጦር ሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ተመልሶ እንዲመጣባቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር” ሲል አዘዘው። እንደ ግድግዳ ቆሞ የነበረው ውኃ ተደርምሶ ፈርዖንንና ሠራዊቱን አሰጠማቸው!—ዘፀአት 14:24-28፤ መዝሙር 136:15
4. (ሀ) ይሖዋ በቀይ ባሕር ባከናወነው ነገር ምን ዓይነት አምላክ መሆኑን አሳይቷል? (ለ) ይህ አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ምን እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል?
4 አምላክ በቀይ ባሕር አጠገብ እስራኤላውያንን ለማዳን የወሰደው እርምጃ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከፈጸማቸው አስደናቂ ክንውኖች መካከል አንዱ ነው። በዚህም ይሖዋ “ኃያል ተዋጊ” መሆኑን አሳይቷል። (ዘፀአት 15:3) ይሁን እንጂ ይሖዋ ተዋጊ አምላክ መሆኑን ማወቅህ ስለ እሱ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ጦርነት በሰው ልጆች ላይ ብዙ መከራና ሥቃይ እንዳስከተለ አይካድም። አምላክ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሆኑ ወደ እሱ ከመቅረብ ይልቅ እንድትሸሸው ያደርግሃል?
ይሖዋ በቀይ ባሕር “ኃያል ተዋጊ” መሆኑን አሳይቷል
መለኮታዊ ጦርነት ከሰብዓዊ ግጭቶች ጋር ሲነጻጸር
5, 6. (ሀ) ይሖዋ “የሠራዊት ጌታ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መለኮታዊ ጦርነት ሰዎች ከሚያደርጉት ጦርነት የሚለየው እንዴት ነው?
5 አምላክ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሁለት መቶ ስልሳ ጊዜ ገደማ፣ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ ሁለት ጊዜ “የሠራዊት ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ሳሙኤል 1:11) ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን እጅግ ብዙ የሆነውን የመላእክት ሠራዊት ያዛል። (ኢያሱ 5:13-15፤ 1 ነገሥት 22:19) ይህ ሠራዊት ያለው የማጥፋት ኃይል እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ አይችልም። (ኢሳይያስ 37:36) ሰዎች ስለሚያደርሱት ጥፋት ማሰብ የሚያስደስት ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ የአምላክ ጦርነት በሰው ልጆች መካከል ከሚካሄዱት ግጭቶች ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ወታደራዊም ሆኑ ፖለቲካዊ መሪዎች ማንኛውንም ጦርነት ለማካሄድ የሚነሱት የተቀደሰ ዓላማ ይዘው እንደሆነ ለማሳመን ቢሞክሩም የየትኛውም ሰብዓዊ ጦርነት መንስኤ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ነው።
6 በአንጻሩ ግን ይሖዋ እንዲሁ በጭፍን ተነሳስቶ አይዋጋም። ዘዳግም 32:4 “እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው” ሲል ይገልጻል። የአምላክ ቃል ከቁጥጥር ውጭ የሆነን ቁጣ፣ ጭካኔንና ዓመፅን ያወግዛል። (ዘፍጥረት 49:7፤ መዝሙር 11:5) በመሆኑም ይሖዋ ያለበቂ ምክንያት እርምጃ አይወስድም። ያለውን ታላቅ ኃይል፣ ለማጥፋት የሚጠቀምበት በአግባቡ ከመሆኑም በላይ እንደ መጨረሻ አማራጭ አድርጎ ነው። “‘እኔ በክፉ ሰው ሞት ደስ እሰኛለሁ?’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘እኔ ደስ የምሰኘው ከመንገዱ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለም?’” ሲል በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት የተናገረው ቃል ይህን የሚያረጋግጥ ነው።—ሕዝቅኤል 18:23
7, 8. (ሀ) ኢዮብ ስለደረሰበት መከራ ምን የተሳሳተ ግምት አድሮበት ነበር? (ለ) ኤሊሁ፣ ኢዮብ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል የረዳው እንዴት ነው? (ሐ) በኢዮብ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ምን ልንማር እንችላለን?
7 ታዲያ ይሖዋ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት የጻድቁን ሰው የኢዮብን ታሪክ መለስ ብለን ለመመልከት እንሞክር። በአንድ ወቅት ሰይጣን፣ ኢዮብ (እንዲያውም ማንኛውም ሰው) መከራ ቢደርስበት በታማኝነት ከአምላክ ጎን አይቆምም ሲል ተከራክሮ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ይህ አከራካሪ ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ ሲል ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ፈቀደ። በዚህም የተነሳ ኢዮብ ጤንነቱን፣ ሀብቱንና ልጆቹን አጣ። (ኢዮብ 1:1 እስከ 2:8) ኢዮብ የተነሳውን ክርክር ስለማያውቅ አምላክ አላግባብ እየቀጣው እንዳለ ሆኖ ተሰምቶት ነበር። በዚህም ምክንያት ‘ለምን “ዒላማ” እና “ጠላት” አደረግኸኝ?’ ሲል አምላክን ጠይቋል።—ኢዮብ 7:20፤ 13:24
8 ኤሊሁ የተባለ አንድ ወጣት ኢዮብን “ትክክል እንደሆንክ በጣም እርግጠኛ ከመሆንህ የተነሳ ‘እኔ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ ነኝ’ ትላለህ?” ብሎ በመውቀስ አስተሳሰቡ የተሳሳተ እንደሆነ ነግሮታል። (ኢዮብ 35:2) ‘ከአምላክ የተሻለ አውቃለሁ’ ወይም ደግሞ ‘አምላክ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው። ኤሊሁ “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” ሲል ተናግሯል። በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከመረዳት ችሎታችን በላይ ነው፤ ኃይሉ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ፍትሑንና ታላቅ ጽድቁን አይጥስም።” (ኢዮብ 34:10፤ 36:22, 23፤ 37:23) አምላክ ያለበቂ ምክንያት እንደማይዋጋ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው ይህን በአእምሯችን በመያዝ የሰላም አምላክ የሆነው ይሖዋ ተዋጊ እንዲሆን የሚያነሳሱትን አንዳንድ ምክንያቶች እንመርምር።—1 ቆሮንቶስ 14:33
የሰላም አምላክ ተዋጊ እንዲሆን የሚያስገድዱት ሁኔታዎች
9. ቅዱስ የሆነው አምላክ የሚዋጋው ለምንድን ነው?
9 ሙሴ “ኃያል ተዋጊ” የሆነውን አምላክ ካወደሰ በኋላ “ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” ብሏል። (ዘፀአት 15:11) በተመሳሳይም ነቢዩ ዕንባቆም “ዓይኖችህ ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፤ ክፋትንም ዝም ብለህ ማየት አትችልም” ሲል ጽፏል። (ዕንባቆም 1:13) ይሖዋ የፍቅር ብቻ ሳይሆን የጽድቅ፣ የፍትሕና የቅድስና አምላክ ነው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ባሕርያቱ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት እንዲጠቀምበት ያስገድዱታል። (ኢሳይያስ 59:15-19፤ ሉቃስ 18:7) ስለዚህ አምላክ በሚዋጋበት ጊዜ ቅድስናውን አያጎድፍም። ከዚህ ይልቅ የሚዋጋው ቅዱስ ስለሆነ ነው።—ዘፀአት 39:30
10. በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተተነበየው ጠላትነት ሊያከትም የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው? ይህስ ጻድቅ ለሆኑ የሰው ልጆች ምን ጥቅም ያስገኛል?
10 የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ካመፁ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ ተመልከት። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይሖዋ የዓመፅ ድርጊታቸውን ቸል ብሎ ቢያልፍ ኖሮ በሉዓላዊ ገዢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳ ይችል ነበር። ጻድቅ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በእነሱ ላይ የሞት ፍርድ ለመበየን ተገድዷል። (ሮም 6:23) በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ አምላክ በራሱ አገልጋዮችና ‘በእባቡ’ ማለትም በሰይጣን ተከታዮች መካከል ጠላትነት እንደሚኖር ገልጿል። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:15) ይህ ጠላትነት ሊያከትም የሚችለው ሰይጣን ሲጨፈለቅ ብቻ ነው። (ሮም 16:20) ይህ የፍርድ እርምጃ የሰይጣንን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ምድር ወደ ገነትነት እንድትለወጥ ሁኔታዎችን የሚያመቻች በመሆኑ ጻድቅ ለሆኑ የሰው ልጆች ታላላቅ በረከቶች ያስገኛል። (ማቴዎስ 19:28) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ከሰይጣን ጎን የወገኑ ሁሉ በአምላክ ሕዝብ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ደህንነት ላይ ስጋት መፍጠራቸው አይቀርም። አልፎ አልፎ ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅ እጁን ጣልቃ ማስገባት ሊያስፈልገው ይችላል።
አምላክ ክፋትን ለማስወገድ እርምጃ ይወስዳል
11. አምላክ የጥፋት ውኃ ለማምጣት የተገደደው ለምንድን ነው?
11 ይሖዋ በኖኅ ዘመን እንዲህ ያለ እርምጃ ወስዶ ነበር። ዘፍጥረት 6:11, 12 “ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር፤ ሰው ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር” ይላል። አምላክ በጎ ሥነ ምግባር ከምድር ላይ ጨርሶ እስኪጠፋ ድረስ ዝም ብሎ ይመለከት ይሆን? በፍጹም። ይሖዋ የዓመፅ መንፈስ የተጠናወታቸውንና ብልሹ ሥነ ምግባር የነበራቸውን ሰዎች በሙሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ለማምጣት ተገድዷል።
12. (ሀ) ይሖዋ የአብርሃምን “ዘር” በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) አሞራውያን መጥፋታቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
12 አምላክ በከነአናውያን ላይ የበየነው ፍርድም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ በአብርሃም ዘር አማካኝነት የምድር አሕዛብ ሁሉ ለራሳቸው በረከት እንደሚያገኙ ቃል ገብቶ ነበር። ይህን ዓላማ ዳር ለማድረስ፣ አሞራውያን የተባሉ ሕዝቦች የሚኖሩበትን የከነአን ምድር ለአብርሃም ተወላጆች ለማውረስ ወሰነ። አምላክ እነዚህን ሕዝቦች ከምድራቸው በኃይል ማስወጣቱ ፍትሐዊ ይሆናል? ይሖዋ “የአሞራውያን በደል ጽዋው [እስኪሞላ]” ድረስ ከምድራቸው እንደማይባረሩ አስቀድሞ የተናገረ ሲሆን ይህም 400 ዓመታት ገደማ እንደሚወስድ አመልክቷል።b (ዘፍጥረት 12:1-3፤ 13:14, 15፤ 15:13, 16፤ 22:18) በእነዚህ ዓመታት የአሞራውያን የሥነ ምግባር አቋም ይበልጥ እያዘቀጠ ሄደ። የከነአን ምድር በጣዖት አምልኮ፣ በደም መፋሰስና ልቅ በሆነ የፆታ ብልግና ተበከለች። (ዘፀአት 23:24፤ 34:12, 13፤ ዘኁልቁ 33:52) የምድሪቱ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ሳይቀር በእሳት በማቃጠል ለአማልክቶቻቸው መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል። ቅዱስ አምላክ የሆነው ይሖዋ አምላኪዎቹ እንዲህ ያለ ክፋት በሚፈጽሙ ሕዝቦች መካከል እንዲኖሩ ሊፈቅድ ይችላል? በፍጹም! “ምድሪቱ ረክሳለች፤ እኔም ለሠራችው ስህተት ቅጣት አመጣባታለሁ፤ ምድሪቱም ነዋሪዎቿን ትተፋቸዋለች” ሲል ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 18:21-25) ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህን ሰዎች በጅምላ ጠራርጎ አላጠፋም። እንደ ረዓብ እና እንደ ገባኦናውያን ያሉትን ጥሩ አመለካከት ያላቸው ከነአናውያን አላጠፋቸውም።—ኢያሱ 6:25፤ 9:3-27
ለስሙ ሲል ይዋጋል
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ስሙን መቀደስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) ከእስራኤላውያን ጋር በተያያዘ ይሖዋ በስሙ ላይ የደረሰውን ነቀፋ ያስወገደው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ ስሙም ቅዱስ ነው። (ዘሌዋውያን 22:32) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9) በኤደን የተነሳው ዓመፅ በአምላክና በአገዛዙ ላይ ጥያቄ ያስነሳ በመሆኑ የአምላክ ስም እንዲጎድፍ አድርጓል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ስም የማጥፋት ወንጀልና ዓመፅ ቸል ብሎ ሊያልፍ አይችልም። ስሙን ከነቀፋ ለማንጻት ሲል እርምጃ ለመውሰድ ተገድዷል።—ኢሳይያስ 48:11
14 እስቲ ወደ እስራኤላውያን ታሪክ እንመለስ። እስራኤላውያን ከግብፅ የባርነት ቀንበር እስካልተላቀቁ ድረስ አምላክ የምድር አሕዛብ በዘሩ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት እንደሚያገኙ ለአብርሃም የገባውን ቃል ሊፈጽም እንደማይችል የሚሰማቸው ይኖሩ ይሆናል። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡን በብሔር ደረጃ ነፃ በማውጣትና በማደራጀት በስሙ ላይ የደረሰውን ነቀፋ አስወግዷል። ነቢዩ ዳንኤል ወደ አምላክ ሲጸልይ “ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በኃያል እጅ ያወጣህና እስከዚህ ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግክ አምላካችን ይሖዋ ሆይ” ያለው ለዚህ ነው።—ዳንኤል 9:15
15. ይሖዋ አይሁዳውያንን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ያወጣቸው ለምንድን ነው?
15 የሚያስገርመው ነገር ዳንኤል ይህን ጸሎት ያቀረበው አይሁዳውያን ይሖዋ ለስሙ ሲል ዳግመኛ እርምጃ እንዲወስድ ይጠብቁ በነበረበት ወቅት ነው። ዓመፀኛ የነበሩት አይሁዶች በዚህ ጊዜ በባቢሎን በግዞት ይገኙ ነበር። ዋና ከተማቸው ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ሆናለች። ዳንኤል አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለሳቸው የይሖዋን ስም እንደሚያስከብር በመገንዘብ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅር በል። ይሖዋ ሆይ፣ ትኩረት ስጥ፤ እርምጃም ውሰድ! አምላኬ ሆይ፣ ለራስህ ስትል አትዘግይ፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና።”—ዳንኤል 9:18, 19
ለሕዝቡ ሲል ይዋጋል
16. ይሖዋ ለስሙ ሲል የሚዋጋ መሆኑ ርኅራኄ የጎደለውና ራስ ወዳድ ነው ሊያሰኘው የማይችለው ለምን እንደሆነ አብራራ።
16 ይሖዋ ለስሙ ሲል ይዋጋል ሲባል ርኅራኄ የጎደለውና ራስ ወዳድ ነው ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ይልቁንም ከቅድስናውና ለፍትሕ ካለው ፍቅር ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ሕዝቡን ይጠብቃል። ዘፍጥረት ምዕራፍ 14ን ተመልከት። እዚህ ምዕራፍ ላይ አራት ወራሪ ነገሥታት የአብርሃምን የወንድም ልጅ ሎጥንና ቤተሰቡን ማርከው እንደወሰዱ የሚገልጽ ታሪክ እናገኛለን። አብርሃም በአምላክ እርዳታ በእነዚህ ኃያል ነገሥታት ላይ አስደናቂ ድል ተቀዳጀ! ይህ ድል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልሰፈሩ አንዳንድ ወታደራዊ ክንውኖችንም እንደያዘ በሚገመተው “የይሖዋ የጦርነት መጽሐፍ” ላይ ከተመዘገቡት ታሪኮች የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። (ዘኁልቁ 21:14) ከዚያም በኋላ ቢሆን ሌሎች በርካታ ድሎች ተገኝተዋል።
17. እስራኤላውያን ወደ ከነአን ምድር ከገቡ በኋላ ይሖዋ እንደተዋጋላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ።
17 እስራኤላውያን ወደ ከነአን ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ “አምላካችሁ ይሖዋ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የገዛ ዓይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ይዋጋላችኋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 1:30፤ 20:1) በሙሴ እግር ከተተካው ከኢያሱ አንስቶ በመሳፍንትም ሆነ ታማኝ በነበሩት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ በመዋጋት በጠላቶቻቸው ላይ በርካታ አስደናቂ ድሎች እንዲቀዳጁ አድርጓል።—ኢያሱ 10:1-14፤ መሳፍንት 4:12-17፤ 2 ሳሙኤል 5:17-21
18. (ሀ) ይሖዋ አለመለወጡ አመስጋኞች እንድንሆን የሚገፋፋን ለምንድን ነው? (ለ) በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ጠላትነት የሚያከትምበት ጊዜ ሲደርስ ምን ይከናወናል?
18 ይሖዋ አልተለወጠም፤ ይህችን ምድር ሰላም የሰፈነባት ገነት ለማድረግ ያለው ዓላማም ቢሆን አልተለወጠም። (ዘፍጥረት 1:27, 28) አምላክ አሁንም ቢሆን ክፋትን ይጠላል። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡን ከልብ ስለሚወድ ለእነሱ ሲል በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። (መዝሙር 11:7) እንዲያውም በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ጠላትነት በቅርቡ በአምላክ ሕዝብ ላይ ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ከባድ ጥቃት እንዲሰነዘር ምክንያት ይሆናል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ስሙን ለመቀደስና ሕዝቡን ለመጠበቅ ሲል ዳግመኛ “ኃያል ተዋጊ” ሆኖ ይነሳል!—ዘካርያስ 14:3፤ ራእይ 16:14, 16
19. (ሀ) አምላክ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሆኑ ወደ እሱ እንድንቀርብ ሊያደርገን የሚችለው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) አምላክ ለእኛ ሲል የሚዋጋ መሆኑ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
19 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክፉ አውሬ በአንድ ቤተሰብ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ሲል አባትየው በሕይወቱ ቆርጦ ከአውሬው ጋር በመፋለም ገደለው እንበል። ሚስቱና ልጆቹ ‘እንዴት አውሬውን ይገድለዋል?’ ብለው በማሰብ ለእሱ ጥላቻ የሚያድርባቸው ይመስልሃል? በፍጹም፤ እንዲያውም ለሕይወቱ ሳይሳሳ እነሱን ለማዳን ቆራጥ እርምጃ በመውሰዱ ይበልጥ እንደሚወዱት መገመት አያዳግትም። በተመሳሳይም አምላክ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሆኑ እሱን እንድንሸሸው ሊያደርገን አይገባም። ከዚህ ይልቅ እኛን ለመጠበቅ ሲል የሚዋጋ መሆኑ ይበልጥ እንድንወደው ይገፋፋናል። በተጨማሪም ገደብ የለሽ ለሆነው ኃይሉ ያለን አድናቆት ሊጨምር ይገባል። ይህም “በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት” እንድናቀርብ ያደርገናል።—ዕብራውያን 12:28
“ኃያል ተዋጊ” ወደሆነው አምላክ ቅረብ
20. አምላክ ያከናወናቸውን ጦርነቶች በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዝርዝር መረጃ ባናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?
20 እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ይሖዋን ለውጊያ ያነሳሱት ምክንያቶች ምን እንደሆኑ በዝርዝር አይገልጽም። ይሁን እንጂ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ ይሖዋ ኃይሉን ፍትሕ በጎደለው ወይም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ አይጠቀምበትም። ብዙውን ጊዜ የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አውድ ወይም ሥረ መሠረት ጠለቅ ብለን መመርመራችን ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል። (ምሳሌ 18:13) ዝርዝር መረጃ በማናገኝበት ጊዜ እንኳ ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቃችንና ግሩም በሆኑት ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰላችን በውስጣችን ሊፈጠር የሚችለውን ጥርጣሬ ለማስወገድ ይረዳናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በአምላካችን በይሖዋ ላይ ለመታመን የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት እናገኛለን።—ኢዮብ 34:12
21. ይሖዋ “ኃያል ተዋጊ” የሚሆንባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ምን ዓይነት አምላክ ነው?
21 ምንም እንኳ ይሖዋ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ “ኃያል ተዋጊ” ሆኖ የሚነሳ ቢሆንም ጦርነት ወዳድ ነው ማለት ግን አይደለም። ሕዝቅኤል ስለ ሰማያዊው ሠረገላ ባየው ራእይ ላይ ይሖዋ ከጠላቶቹ ጋር ለመዋጋት እንደተዘጋጀ ሆኖ ተገልጿል። ሆኖም ሕዝቅኤል አምላክን በራእይ የተመለከተው የሰላም ተምሳሌት በሆነው በቀስተ ደመና ተከብቦ ነው። (ዘፍጥረት 9:13፤ ሕዝቅኤል 1:28፤ ራእይ 4:3) ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ሰላማዊ አምላክ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክ ፍቅር ነው” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ባሕርያቱን በሙሉ የሚጠቀመው ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው። ይሖዋ ታላቅ ኃይል ያለው ቢሆንም አፍቃሪ ነው። እንዲህ ወዳለው አምላክ መቅረብ መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
a አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እስራኤላውያንን ያሳደዷቸው “600 ሠረገሎች፣ 50,000 ፈረሰኞችና 200,000 ገደማ የሚሆኑ በደንብ የታጠቁ እግረኛ ወታደሮች” እንደነበሩ ዘግቧል።—ጁዊሽ አንቲክዊቲስ፣ II, 324 [xv, 3]
b እዚህ ላይ “አሞራውያን” የሚለው ቃል በከነአን ምድር ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችን በሙሉ እንደሚያመለክት ግልጽ ነው።—ዘዳግም 1:6-8, 19-21, 27፤ ኢያሱ 24:15, 18
-
-
‘መጠጊያችን የሆነው አምላክ’—ለመጠበቅ የሚጠቀምበት ኃይልወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 7
‘መጠጊያችን የሆነው አምላክ’—ለመጠበቅ የሚጠቀምበት ኃይል
1, 2. እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ወደ ሲና ምድር ሲገቡ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተደቅነውባቸው ነበር? ይሖዋስ ያጽናናቸው እንዴት ነው?
እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ወደ ሲና ምድር በገቡበት ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተደቅነውባቸው ነበር። ከፊታቸው በጣም አስፈሪ የሆነ ጉዞ ይጠብቃቸዋል። የሚጓዙት “መርዛማ እባቦችና ጊንጦች በሞሉበት . . . ጭልጥ ያለና የሚያስፈራ ምድረ በዳ” ነው። (ዘዳግም 8:15) በተጨማሪም ከጠላት ብሔራት ሊሰነዘር የሚችለው ጥቃት ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወዳሉበት ቦታ ያመጣቸው ይሖዋ ነው። ታዲያ አምላካቸው ከዚህ ሁሉ ችግር ይታደጋቸው ይሆን?
2 ይሖዋ “እናንተን በንስር ክንፎች ተሸክሜ ወደ እኔ ለማምጣት ስል በግብፃውያን ላይ ያደረግኩትን ሁሉ እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል” በማለት አጽናናቸው። (ዘፀአት 19:4) ይሖዋ ሕዝቦቹን በምሳሌያዊ ሁኔታ በንስር ክንፍ ተሸክሞ በማውጣት ከግብፃውያን እንዳዳናቸው መለስ ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ‘የንስር ክንፍ’ መለኮታዊ ጥበቃን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ነው እንድንል የሚያደርጉን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።
3. ‘የንስር ክንፍ’ መለኮታዊ ጥበቃን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
3 ንስር ረጅምና ጠንካራ የሆኑ ክንፎቹን የሚጠቀመው ከፍ ብሎ በሰማይ ላይ ለመንሳፈፍ ብቻ አይደለም። ቀትር ላይ ሙቀቱ ኃይለኛ በሚሆንበት ጊዜ እናቲቱ ንስር ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ከሁለት ሜትር በላይ ርዝማኔ ያላቸውን ክንፎቿን በመዘርጋት ጫጩቶቿን ከፀሐይ ሐሩር ትጋርዳቸዋለች። በብርድ ጊዜ ደግሞ በክንፎቿ በማቀፍ ታሞቃቸዋለች። ንስር ጫጩቶቿን እንደምትንከባከብ ሁሉ ይሖዋም ገና ያልጠነከረውን የእስራኤል ብሔር ጠብቆታል እንዲሁም ተንከባክቦታል። በምድረ በዳ በሚጓዙበት ጊዜም ለእሱ ታማኝ ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ ኃያል በሆኑት ምሳሌያዊ ክንፎቹ ጥላ ሥር መሸሸግ ይችላሉ። (ዘዳግም 32:9-11፤ መዝሙር 36:7) ዛሬስ እኛ የአምላክን ጥበቃ እናገኛለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?
ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል
4, 5. አምላክ ሕዝቡን ለመጠበቅ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ አገልጋዮቹን መጠበቅ እንደማይሳነው የተረጋገጠ ነው። “ሁሉን ቻይ አምላክ” የሚለው ስያሜ ይሖዋ ምንም ነገር ሊበግረው የማይችል ኃይል እንዳለው ያመለክታል። (ዘፍጥረት 17:1) ምንም ነገር ሊያቆመው እንደማይችል የባሕር ማዕበል ሁሉ የይሖዋንም ኃይል ሊገታ የሚችል ነገር አይኖርም። ይሖዋ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ የሚችል ከመሆኑ አንጻር ‘ኃይሉን ተጠቅሞ ሕዝቡን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነው?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።
5 በአጭር አነጋገር መልሱ አዎን ነው! ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚጠብቅ ዋስትና ሰጥቶናል። መዝሙር 46:1 “አምላክ መጠጊያችንና ብርታታችን፣ በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን ነው” ይላል። አምላክ ‘ሊዋሽ ስለማይችል’ ሕዝቡን ለመጠበቅ የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበት እንችላለን። (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ጥበቃና እንክብካቤ ለመግለጽ የተጠቀመባቸውን ግሩም ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት።
6, 7. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ እረኛ በጎቹን የሚጠብቀው እንዴት ነበር? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በጎቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ያለውን ልባዊ ፍላጎት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የሚገልጸው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ እረኛችን ሲሆን “እኛ ሕዝቡና የማሰማሪያው በጎች ነን።” (መዝሙር 23:1፤ 100:3) እንደ በግ ምስኪን እንስሳ የለም ማለት ይቻላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ እረኛ በጎቹን ከአንበሳ፣ ከተኩላና ከድብ እንዲሁም ከሌባ ለመጠበቅ ደፋር መሆን ነበረበት። (1 ሳሙኤል 17:34, 35፤ ዮሐንስ 10:12, 13) ከዚህም ሌላ እረኛው በጎቹን በርኅራኄ መንከባከብ ይጠበቅበት ነበር። አንዲት በግ ምጥ ይዟት ከመንጋው በምትለይበት ጊዜ እረኛው አጠገቧ ሆኖ የሚጠብቃት ከመሆኑም በላይ ከወለደች በኋላ ግልገሏን አቅፎ ወደ መንጋው ይወስዳታል።
“በእቅፉም ይሸከማቸዋል”
7 ይሖዋም ልክ እንደ አንድ እረኛ እንደሚጠብቀን ቃል ገብቶልናል። (ሕዝቅኤል 34:11-16) በዚህ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ የተብራራውን ኢሳይያስ 40:11ን መለስ ብለህ አስታውስ። ይህ ጥቅስ ይሖዋን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፦ “መንጋውን እንደ እረኛ ይንከባከባል። ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በእቅፉም ይሸከማቸዋል።” ግልገሏ እረኛው ‘እንዲያቅፋት’ የምታደርገው እንዴት ነው? ወደ እረኛው ተጠግታ እግሩን ትታከከዋለች። ሆኖም ጎንበስ ብሎ በማንሳት እቅፍ የሚያደርጋት እረኛው ነው። ታላቁ እረኛ እኛን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!
8. (ሀ) አምላክ ጥበቃ የሚያደርገው ለእነማን ነው? ይህስ በምሳሌ 18:10 ላይ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ስም መሸሸጊያ እንዲሆንልን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
8 ሆኖም አምላክ የሚጠብቀው ወደ እሱ የሚቀርቡትን ብቻ ነው። ምሳሌ 18:10 “የይሖዋ ስም ጽኑ ግንብ ነው። ጻድቅ ወደዚያ በመሮጥ ጥበቃ ያገኛል” በማለት ይገልጻል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በምድረ በዳ ለመሸሸጊያነት የሚያገለግሉ ግንቦች ይገነቡ ነበር። ሆኖም አስጊ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ወደዚህ ግንብ መሮጥ የግለሰቡ ፋንታ ነው። የአምላክም ስም መሸሸጊያ ሊሆነን የሚችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። የአምላክን ስም መጥራት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፤ ስሙ በራሱ አንድ ዓይነት ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው አድርጎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዚህ ስም ባለቤት የሆነውን አምላክ ማወቅና በእሱ መታመን እንዲሁም ያወጣቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ መተርጎም ይኖርብናል። ይሖዋ በእሱ ከታመንን ጥበቃ እንደሚያደርግልንና ከለላ እንደሚሆነን ቃል የገባልን መሆኑ ምን ያህል እንደሚያስብልን የሚያሳይ ነው።
“አምላካችን . . . ሊያስጥለን ይችላል”
9. ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ የገባውን ቃል በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ አገልጋዮቼን እጠብቃለሁ ብሎ ቃል በመግባት ብቻ አልተወሰነም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላክ ሕዝቡን መጠበቅ እንደሚችል ተአምራዊ በሆነ መንገድ አሳይቷል። በጥንት እስራኤል ዘመን የይሖዋ ኃያል ‘እጅ’ የሕዝቡን ጠላቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት በቁጥጥር ሥር አድርጓል። (ዘፀአት 7:4) ይሁን እንጂ ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ ለመጠበቅ ኃይሉን የተጠቀመባቸው ጊዜያትም አሉ።
10, 11. ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉ?
10 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን ወጣቶች ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል አንሰግድም ባሉ ጊዜ ንጉሡ በጣም ተበሳጭቶ በሚንቀለቀል የእቶን እሳት ውስጥ እንደሚጥላቸው ዛተባቸው። የዘመኑ ኃያል ንጉሥ የነበረው ናቡከደነጾር “ከእጄ ሊያስጥላችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?” ሲል ተሳለቀ። (ዳንኤል 3:15) ሦስቱ ወጣቶች አምላካቸው እነሱን ለማዳን የሚያስችል ኃይል እንዳለው እርግጠኞች የነበሩ ቢሆንም በዚያ ወቅት ያድነናል ብለው ሙሉ በሙሉ አልጠበቁም ነበር። “ወደ እሳቱ የምንጣል ከሆነ የምናገለግለው አምላካችን ከሚንበለበለው የእቶን እሳት ሊያስጥለን ይችላል” ብለው መለሱለት። (ዳንኤል 3:17) በእርግጥም እሳቱ ሰባት እጥፍ እንዲነድድ ቢደረግም እንኳ ምንም ለማይሳነው አምላካቸው ይህ ከባድ ነገር አልነበረም። ይሖዋ ወጣቶቹን ከእሳቱ ውስጥ በማዳኑ ንጉሡ “እንደ እሱ ማዳን የሚችል ሌላ አምላክ የለም” ብሎ ለማመን ተገድዷል።—ዳንኤል 3:29
11 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የአንድያ ልጁን ሕይወት ወደ አይሁዳዊቷ ድንግል ማርያም ማህፀን ባዛወረ ጊዜ ኃይሉን በመጠቀም ጥበቃ ማድረግ እንደሚችል እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል። አንድ መልአክ ማርያምን “ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ” ብሏት ነበር። በተጨማሪም “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል” ሲል ገልጾላታል። (ሉቃስ 1:31, 35) የአምላክ ልጅ ከምንጊዜውም ይበልጥ ሕይወቱ ለአደጋ ተጋልጦ ነበር ማለት ይቻላል። የሰብዓዊ እናቱ ኃጢአትና አለፍጽምና ወደ ፅንሱ ይተላለፍ ይሆን? ሰይጣን ይህን ልጅ ገና ሳይወለድ ጉዳት ሊያደርስበት ወይም ሊገድለው ይችል ይሆን? በፍጹም! ይሖዋ ልጁ ከተፀነሰበት ጊዜ አንስቶ ኃጢአት እንዳይተላለፍበት እንዲሁም በሰው፣ በአጋንንትም ሆነ በሌላ በማንኛውም ኃይል ጉዳት እንዳይደርስበት ለማርያም ልዩ ጥበቃ አድርጎላት ነበር ማለት ይቻላል። ኢየሱስ ከተወለደም በኋላ ቢሆን ይሖዋ ጥበቃ አድርጎለታል። (ማቴዎስ 2:1-15) አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ውድ ልጁ ምንም ጉዳት አላገኘውም።
12. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ለአንዳንድ ግለሰቦች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ ያደረገው ለምንድን ነው?
12 ይሖዋ ለአንዳንድ ግለሰቦች እንዲህ ባለ ተአምራዊ ሁኔታ ጥበቃ ያደረገው ለምንድን ነው? ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለመላው የሰው ዘር ያወጣው ዓላማ እንዲፈጸም ሕፃን ለነበረው ለኢየሱስ ጥበቃ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ . . . ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” የተጻፈው የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ለአገልጋዮቹ እንዴት ጥበቃ እንዳደረገ የሚገልጹ በርካታ ታሪኮችን ይዟል። (ሮም 15:4) አዎን፣ እነዚህ ታሪኮች ሁሉን ማድረግ በማይሳነው አምላካችን ላይ ያለንን እምነት ያጠነክሩልናል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ አምላክ ምን ዓይነት ጥበቃ ያደርግልናል ብለን መጠበቅ እንችላለን?
አምላክ ጥበቃ ያደርግልናል ሲባል ምን ማለት ነው?
13. ይሖዋ እኛን ከማንኛውም ዓይነት ችግር ለመታደግ ተአምር የመፈጸም ግዴታ አለበት? አብራራ።
13 ይሖዋ መለኮታዊ ጥበቃ ለማድረግ ቃል የገባ ቢሆንም እኛን ከማንኛውም ዓይነት ችግር ለመታደግ ተአምር የመፈጸም ግዴታ አለበት ማለት አይደለም። አምላክ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ከችግር ነፃ ሆነን እንደምንኖር ዋስትና አልሰጠንም። ብዙ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ድህነትን፣ ጦርነትን፣ በሽታንና ሞትን ጨምሮ የተለያዩ መከራዎች ይደርሱባቸዋል። ኢየሱስ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ በእምነታቸው ምክንያት ሊገደሉ እንደሚችሉ በግልጽ ተናግሯል። እስከ መጨረሻው መጽናት አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ የተናገረውም ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 24:9, 13) ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም አገልጋዮቹን ከማንኛውም ዓይነት ችግር የሚጠብቃቸው ቢሆን ኖሮ ሰይጣን ይሖዋን ለመክሰስና ሰዎች ለአምላክ ባላቸው ታማኝነት ላይ ጥያቄ ለማንሳት ሰበብ ያገኝ ነበር።—ኢዮብ 1:9, 10
14. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በሙሉ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ጥበቃ ያደርጋል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?
14 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳ ቢሆን ይሖዋ አገልጋዮቹን በሙሉ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከሞት ይታደግ ነበር ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ያዕቆብ በ44 ዓ.ም. ገደማ በሄሮድስ ተገድሏል። ይሁንና ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ጴጥሮስን “ከሄሮድስ እጅ” አድኖታል። (የሐዋርያት ሥራ 12:1-11) የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስ ደግሞ ከጴጥሮስም ሆነ ከያዕቆብ ይበልጥ ረጅም ዕድሜ ኖሯል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ ለአገልጋዮቹ በሙሉ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ጥበቃ ያደርጋል ብለን መጠበቅ አንችልም። ከዚህም በተጨማሪ “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሁላችንንም ያጋጥሙናል። (መክብብ 9:11) ታዲያ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?
ይሖዋ አካላዊ ጥበቃ ያደርግልናል
15, 16. (ሀ) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜም ሆነ ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ለአገልጋዮቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
15 በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ የሚያደርግልንን አካላዊ ጥበቃ እንመልከት። የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን አምላክ በቡድን ደረጃ እንዲህ ዓይነቱን ጥበቃ ያደርግልናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። አለዚያ ለሰይጣን ጥቃት በእጅጉ የተጋለጥን እንሆናለን። “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን እውነተኛውን አምልኮ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ቢችል በጣም ደስ እንደሚለው መገመት አያዳግትም። (ዮሐንስ 12:31፤ ራእይ 12:17) አንዳንድ ኃያላን መንግሥታት የስብከት ሥራችንን ከማገዳቸውም በላይ እኛን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች በአቋማቸው በመጽናት ያለማሰለስ መስበካቸውን ቀጥለዋል! ኃያላን ብሔራት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውንና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ መስለው የሚታዩትን የእነዚህን ክርስቲያኖች ሥራ ማስቆም ያልቻሉት ለምንድን ነው? ይሖዋ ኃያል በሆኑት ክንፎቹ ጥላ ስለጋረዳቸው ነው!—መዝሙር 17:7, 8
16 በቅርቡ በሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ ወቅት አምላክ ስለሚያደርግልን አካላዊ ጥበቃስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ መፍራት አያስፈልገንም። ምክንያቱም “ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና ዓመፀኞችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ ያውቃል።” (ራእይ 7:14፤ 2 ጴጥሮስ 2:9) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ስለ ሁለት ነገሮች እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ከምድር ገጽ እንዲጠፉ አይፈቅድም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እስከመጨረሻው በአቋማቸው የሚጸኑ አገልጋዮቹን ቢሞቱ እንኳ በትንሣኤ በማስነሳት ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ይህ ደግሞ በዚህ ሥርዓት ለሚሞቱ የአምላክ አገልጋዮች ትልቅ ዋስትና ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29
17. ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?
17 በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቢሆን ይሖዋ የሰዎችን የልብ ዝንባሌና ሕይወት የመለወጥ ኃይል ባለው ሕያው ‘ቃሉ’ አማካኝነት ይጠብቀናል። (ዕብራውያን 4:12) በቃሉ ውስጥ የሰፈሩትን መመሪያዎች በሥራ ላይ በማዋል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአካላችን ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ ጉዳቶች ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። ኢሳይያስ 48:17 “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ” ይላል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር መከተላችን ጤናችንን እንደሚያሻሽልልንና ዕድሜ እንደሚጨምርልን ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከፆታ ብልግና እንድንርቅና ሰውነትን ከሚያረክስ ማንኛውም ነገር ራሳችንን እንድናነጻ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች በሚከተሏቸው መጥፎ ልማዶች ሳቢያ ከሚደርስባቸው ጉዳት ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። (የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) የአምላክ ቃል እንዲህ ያለ ጥበቃ ስለሚያደርግልን ከልብ አመስጋኞች ነን!
ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል
18. ይሖዋ ምን ዓይነት መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል?
18 ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋምና ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና አጠንክረን ለመያዝ የሚያስችለንን ትጥቅ በመስጠት መንፈሳዊ ጉዳት እንዳያገኘን ይጠብቀናል። ይሖዋ እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያደርግልን ለአሁኑ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን ለዘላለማዊ ደህንነታችን ሲል ነው። አምላክ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ሲል ያደረጋቸውን አንዳንድ ዝግጅቶች እንመልከት።
19. የይሖዋ መንፈስ የሚያጋጥመንን ችግር ሁሉ መቋቋም እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?
19 ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” የሆነ አምላክ ነው። (መዝሙር 65:2) በሕይወታችን ውስጥ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የልባችንን አውጥተን ለይሖዋ በመንገር ትልቅ እፎይታ ልናገኝ እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ያለብንን ችግር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባያስወግድልንም እንኳ ለእሱ ያቀረብነውን ልባዊ ጸሎት በመስማት ችግሩን ለመቋቋም ወይም ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5, 6) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሚለምኑት ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:13) ይህ መንፈስ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና ወይም ችግር እንድንቋቋም የሚረዳን ከመሆኑም በላይ በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት ችግር እስኪያስወግድልን ድረስ ጸንተን እንድንኖር የሚያስችለንን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጠናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7
20. ይሖዋ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በመጠቀም ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?
20 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ጥበቃ የሚያደርግልን በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ወደሆነው “የወንድማማች ማኅበር” ስቦናል። (1 ጴጥሮስ 2:17፤ ዮሐንስ 6:44) በዚህ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያለው ፍቅር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሰዎች ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ይህ መንፈስ እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ጥሩነት ያሉ ማራኪና ውድ ባሕርያትን እንድናፈራ ያስችለናል። (ገላትያ 5:22, 23) በመሆኑም ተጨንቀን ባለንበት ጊዜ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ወደ እኛ ቀርቦ ጠቃሚ ምክር ቢሰጠን ወይም ቢያበረታታን ይሖዋ ይህን ሰው በመጠቀም ላደረገልን እርዳታ ልናመሰግነው ይገባናል።
21. (ሀ) ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ምን ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል? (ለ) ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ባደረጋቸው ዝግጅቶች አንተ በግልህ የተጠቀምከው እንዴት ነው?
21 ከዚህም ሌላ ይሖዋ እኛን ለመጠበቅ ሲል በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ይሰጠናል። በቃሉ አማካኝነት ብርታት እንድናገኝ ሲል ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያቀርብ ሾሞታል። ይህ ታማኝ ባሪያ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ጨምሮ በርካታ ጽሑፎችን በማተምና የተለያዩ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት እንዲሁም jw.org በተባለው ድረ ገጻችን አማካኝነት የሚያስፈልገንን ‘ምግብ በተገቢው ጊዜ’ ያቀርብልናል። (ማቴዎስ 24:45) በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የቀረበ ንግግር ወይም ሐሳብ አለዚያም ደግሞ ጸሎት አበረታቶህና አጽናንቶህ ያውቃል? ወይም ደግሞ በመጽሔቶቻችን ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ልብህን በጣም ነክቶት ያውቃል? ይህ ሁሉ ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ያደረገው ዝግጅት መሆኑን መዘንጋት የለብህም።
22. ይሖዋ ምንጊዜም ኃይሉን የሚጠቀመው ምን ለማድረግ ነው? እንዲህ የሚያደርገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?
22 ይሖዋ በእርግጥም “መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።” (መዝሙር 18:30) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ምንም ዓይነት መከራ እንዳይደርስብን ይጋርደናል ብለን መጠበቅ እንደሌለብን እናውቃለን። ይሁን እንጂ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል ምንጊዜም ኃይሉን እንደሚጠቀምበት የታወቀ ነው። ይህን የሚያደርገውም ለሕዝቡ ዘላቂ ጥቅም ሲል ነው። ወደ እሱ ከቀረብንና ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት እስከ መጨረሻው ጠብቀን ከዘለቅን ዘላለማዊ የሆነ ፍጹም ሕይወት ይሰጠናል። በመሆኑም በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚደርስብን ማንኛውም መከራ “ጊዜያዊና ቀላል” እንደሆነ እንገነዘባለን።—2 ቆሮንቶስ 4:17
-
-
‘ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርገው’ ይሖዋ—ለማደስ የሚጠቀምበት ኃይልወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 8
‘ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርገው’ ይሖዋ—ለማደስ የሚጠቀምበት ኃይል
1, 2. በዛሬው ጊዜ ሰዎች ምን ነገሮችን ሊያጡ ይችላሉ? ይህስ ምን ስሜት ያሳድርባቸዋል?
አንድ ሕፃን በጣም የሚወደው መጫወቻ ሲጠፋበት ወይም ሲሰበርበት ሆድ በሚያባባ ሁኔታ ምርር ብሎ ያለቅሳል። ይሁን እንጂ ወላጁ የጠፋውን መጫወቻ ሲያገኝለት ወይም የተሰበረውን ሲጠግንለት የሕፃኑ ፊት ምን ያህል እንደሚፈካ መገመት ትችላለህ። ይህ ለወላጁ ቀላል ሥራ ሊሆን ይችላል። ሕፃኑ ግን ዳግመኛ እንደማያገኘው ሆኖ ተሰምቶት የነበረውን መጫወቻ መልሶ በማግኘቱ በጣም ሊገረምና ፍንድቅድቅ ሊል ይችላል!
2 ከሁሉ የላቀው አባት ይሖዋ በምድር ላይ ያሉት ልጆቹ ዳግመኛ እንደማያገኙት ሆኖ የተሰማቸውን ነገር መልሰው እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው። እርግጥ ነው እንዲህ ስንል ስለ ተራ መጫወቻዎች መናገራችን አይደለም። በዚህ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ግምት የምንሰጣቸውን የተለያዩ ነገሮች እናጣለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በዛሬው ጊዜ ሰዎች እንደ ቤት፣ ንብረት፣ ሥራና ጤና የመሳሰሉትን በጣም የሚሳሱላቸውን ነገሮች ሊያጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በተፈጥሮ ሀብት ላይ እየደረሰ ስላለው ውድመትና በዚህ ሳቢያ እየጠፉ ስላሉት ብዙ ዝርያዎች ስናስብ በጣም ልንጨነቅ እንችላለን። ሆኖም የምንወደውን ሰው በሞት የማጣትን ያህል ቅስማችንን የሚሰብር ነገር የለም። በዚህ ጊዜ የሚሰማን የከንቱነት ስሜት በጣም ከባድ ነው።—2 ሳሙኤል 18:33
3. በሐዋርያት ሥራ 3:21 ላይ ምን የሚያጽናና ተስፋ ተገልጿል? ይሖዋ ይህን ተስፋ የሚፈጽመውስ በምን አማካኝነት ነው?
3 በመሆኑም ይሖዋ አንድን ነገር ለማደስ ወይም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ቀጥለን እንደምንመለከተው አምላክ በምድር ላሉት ልጆቹ በርካታ ነገሮችን መልሶ ይሰጣቸዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” ለማምጣት ዓላማ እንዳለው ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 3:21) ይህን የሚያከናውነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መሲሐዊ መንግሥት አማካኝነት ነው። ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ይህ መንግሥት በ1914 በሰማይ መግዛት ጀምሯል።a (ማቴዎስ 24:3-14) ይሁንና የሚታደሰው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋ ከሚያከናውናቸው ታላላቅ የተሃድሶ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት። ከእነዚህ የተሃድሶ ሥራዎች መካከል አንዱ በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ወደፊት በስፋት ይከናወናሉ።
ንጹሑን አምልኮ መልሶ ማቋቋም
4, 5. በ607 ዓ.ዓ. የአምላክ ሕዝቦች ምን ደርሶባቸው ነበር? ይሖዋስ ምን ተስፋ ሰጣቸው?
4 ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ መልሶ አቋቁሟል። ይህ ያስፈለገበትን ምክንያት ለመረዳት ወደ ኋላ መለስ ብለን የይሁዳን መንግሥት ታሪክ በአጭሩ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ አንድን ነገር ለማደስ የሚያስችለውን ኃይሉን በምን መንገድ ሲጠቀምበት እንደቆየ ለማስተዋል ይረዳናል።—ሮም 15:4
5 በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ታማኝ አይሁዳውያን ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል ገምት። በጣም የሚወዷት ከተማቸው ከመጥፋቷም በላይ ግንቦቿ ፈራርሰዋል። ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ በምድር ላይ ብቸኛው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ማዕከል የነበረው ሰለሞን የገነባው ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ እንዳልነበር መሆኑ ነው። (መዝሙር 79:1) በሕይወት የተረፉት አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በግዞት በመወሰዳቸው የትውልድ አገራቸው የአራዊት መፈንጫ ሆነች። (ኤርምያስ 9:11) በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ሁሉ ነገር ያበቃለት ይመስል ነበር። (መዝሙር 137:1) ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት እንደሚደርስ ከረጅም ጊዜ በፊት የተናገረው ይሖዋ የተሃድሶ ዘመን እንደሚመጣም ተስፋ ሰጥቶ ነበር።
6-8. (ሀ) ዕብራውያን ነቢያት በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ምን ነገር ተጠቅሶ እናገኛለን? ይህስ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ተሃድሶ የተነገሩት በርካታ ትንቢቶች በዘመናችን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የተፈጸሙት እንዴት ነው?
6 እንዲያውም ዕብራውያን ነቢያት በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ የተሃድሶ ትንቢት ተጠቅሶ እናገኛለን።b ይሖዋ ምድራቸው ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ እንደምትመለስ፣ በነዋሪዎች እንደምትሞላ፣ ለም እንደምትሆንና ከዱር አራዊትም ሆነ ከጠላት ጥቃት እንደምትጠበቅ በእነዚህ ነቢያት አማካኝነት ቃል ገብቶላቸው ነበር። ምድራቸው እንደ ኤደን ገነት እንደምትሆን ገልጾላቸዋል! (ኢሳይያስ 65:25፤ ሕዝቅኤል 34:25፤ 36:35) ከሁሉም በላይ ደግሞ ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ ይቋቋማል፣ ቤተ መቅደሱም ዳግመኛ ይገነባል። (ሚክያስ 4:1-5) እነዚህ ትንቢቶች በግዞት ለነበሩት አይሁዳውያን ተስፋ በመስጠት በባቢሎን የኖሩባቸውን 70 ዓመታት በጽናት እንዲያሳልፉ ረድተዋቸዋል።
7 በመጨረሻም በትንቢት የተነገረው ተሃድሶ የሚከናወንበት ጊዜ ደረሰ። አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሰው ገነቡ። (ዕዝራ 1:1, 2) ከንጹሕ አምልኮ ፈቀቅ ሳይሉ በኖሩባቸው ዘመናት ሁሉ ይሖዋ የባረካቸው ከመሆኑም በላይ ምድራቸውን ለምና ፍሬያማ አድርጎላቸዋል። በተጨማሪም ከጠላቶቻቸውም ሆነ ለበርካታ ዓመታት በምድራቸው ላይ ሲፈነጩ ከነበሩት አራዊት ጠብቋቸዋል። ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ሁሉን ነገር ስላደሰላቸው እጅግ ተደስተው መሆን አለበት! ይሁን እንጂ እነዚህ የተሃድሶ ትንቢቶች በዚያን ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በተወሰነ ደረጃ ብቻ ነበር። የላቀ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት፣ አስቀድሞ የተነገረለት የንጉሥ ዳዊት ዘር በሚነግሥበት “በዘመኑ መጨረሻ” ማለትም በእኛ ዘመን ነው።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ 9:6, 7
8 ኢየሱስ በ1914 በሰማይ በሚገኘው መንግሥት ላይ ከነገሠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምድር ያሉት ታማኝ የአምላክ ሕዝቦች ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በ537 ዓ.ዓ. ድል አድራጊው የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ቀሪዎቹን አይሁዳውያን ከባቢሎን ነፃ እንዳወጣ ሁሉ ኢየሱስም ቀሪዎቹን መንፈሳዊ አይሁዳውያን ማለትም ተከታዮቹን በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች ከምታመለክተው “ታላቂቱ ባቢሎን” ተጽዕኖ አላቅቋቸዋል። (ራእይ 18:1-5፤ ሮም 2:29) በ1919 ይሖዋ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ንጹሑን አምልኮ መልሶ አቋቁሞላቸዋል። (ሚልክያስ 3:1-5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች በጸዳው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማለትም አምላክ ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት አማካኝነት አምልኳቸውን በማከናወን ላይ ናቸው። በዛሬው ጊዜ ይህ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
መንፈሳዊ ተሃድሶ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9. ከሐዋርያት ዘመን በኋላ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በእውነተኛው አምልኮ ላይ ምን ፈጽመዋል? ይሁን እንጂ ይሖዋ በዘመናችን ምን እርምጃ ወስዷል?
9 እስቲ የንጹሕ አምልኮን ታሪክ መለስ ብለን እንመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ብዙ መንፈሳዊ በረከት አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያት እውነተኛው አምልኮ እንደሚበረዝና እንደሚጠፋ ተንብየው ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ሕዝበ ክርስትና ብቅ አለች። ቀሳውስቷ የአረማውያንን ትምህርቶችና ልማዶች ማስተማር ጀመሩ። አምላክ ሥላሴ እንደሆነ አድርገው በመግለጽ እንዲሁም ሰዎች ለቀሳውስት እንዲናዘዙና ወደ ይሖዋ ከመጸለይ ይልቅ ወደ ማርያም ወይም ወደ ሌሎች “ቅዱሳን” እንዲጸልዩ በማስተማር ከአምላክ እንዲርቁ አድርገዋል። ንጹሕ አምልኮ በዚህ መንገድ ለብዙ መቶ ዘመናት ተበክሎ ከቆየ በኋላ ይሖዋ ምን እርምጃ ወሰደ? በሐሰት ሃይማኖት በተጥለቀለቀውና አምላክ በሚያወግዛቸው መጥፎ ልማዶች በተበከለው በዚህ ዓለም ውስጥ እጁን ጣልቃ በማስገባት ንጹሑን አምልኮ መልሶ አቋቁሟል! ይህ ተሃድሶ በዘመናችን ከተፈጸሙት ታላላቅ ክንውኖች አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
10, 11. (ሀ) መንፈሳዊው ገነት ምን ሁለት ዋና ዋና ገጽታዎች አሉት? ይህስ ለአንተ ምን ጥቅም ያስገኛል? (ለ) ይሖዋ ወደ መንፈሳዊው ገነት የሰበሰበው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? ምን መብትስ ያገኛሉ?
10 በመሆኑም በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይገኛሉ፤ ይህ ገነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተዋበ ነው። ይህ መንፈሳዊ ገነት ምን ነገሮችን ያቀፈ ነው? ሁለት ዋና ዋና ገጽታዎች አሉት። አንደኛው ገጽታ የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ነው። ይሖዋ ከሐሰትና ከተሳሳቱ ትምህርቶች የጸዳ የአምልኮ ሥርዓት በማቋቋም ባርኮናል። በተጨማሪም መንፈሳዊ ምግብ አትረፍርፎ ሰጥቶናል። ይህም በሰማይ ስላለው አባታችን እንድናውቅ፣ እሱን ለማስደሰት እንድንጥርና ወደ እሱ እንድንቀርብ ያስችለናል። (ዮሐንስ 4:24) ሁለተኛው የመንፈሳዊ ገነት ገጽታ ደግሞ በውስጡ ካሉት ሰዎች ጋር የተያያዘ ነው። ኢሳይያስ በትንቢት እንደተናገረው ይሖዋ “በዘመኑ መጨረሻ” ሕዝቦቹን የሰላምን ጎዳና አስተምሯቸዋል። በመካከላችን ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል። ምንም እንኳ ፍጹም ባንሆንም “አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ይረዳናል። ግሩም ባሕርያት እንድናፈራ የሚያስችለንን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጥረታችንን ይባርክልናል። (ኤፌሶን 4:22-24፤ ገላትያ 5:22, 23) ከአምላክ መንፈስ ጋር የሚስማማ ነገር የምታደርግ ከሆነ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መኖር ትችላለህ።
11 ይሖዋ ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት የሰበሰበው የሚወዳቸውን ሰዎች ማለትም እሱን የሚወዱ፣ ሰላምን የሚወዱና “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ” ሰዎችን ነው። (ማቴዎስ 5:3) የሰው ዘርም ሆነ መላዋ ምድር ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ የሚመለሱበትን ይበልጥ አስደናቂ የሆነ የተሃድሶ ዘመን ለማየት የሚታደሉት እንዲህ ያሉ ሰዎች ናቸው።
“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”
12, 13. (ሀ) ስለ ተሃድሶ የተነገሩት ትንቢቶች ሌላም ፍጻሜ አላቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በኤደን ገነት በገለጸው መሠረት ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ይህስ ምን ተስፋ ይሰጠናል?
12 ስለ ተሃድሶ የተነገሩት አብዛኞቹ ትንቢቶች የሚያመለክቱት መንፈሳዊ ተሃድሶን ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ የታመሙ፣ አንካሶች፣ ዓይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንደሚፈወሱ አልፎ ተርፎም ሞት ራሱ ለዘላለም እንደሚዋጥ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 25:8፤ 35:1-7) እነዚህ ትንቢቶች በጥንት እስራኤል ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን አላገኙም። በእኛም ዘመን ቢሆን ፍጻሜያቸውን ያገኙት በመንፈሳዊ ሁኔታ ነው፤ ወደፊት ግን ቃል በቃል በስፋት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ ብለን እንድናምን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። እንዲህ ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
13 ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ በኤደን ገነት ውስጥ አስታውቆ ነበር። ዓላማው ምድር ደስተኛና ጤናማ በሆኑ እንዲሁም አንድነት ባላቸው የሰው ልጆች እንድትሞላ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ምድርንም ሆነ በላይዋ ያሉትን ፍጥረታት የመንከባከብና መላዋን ፕላኔት ወደ ገነትነት የመለወጥ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ዓላማ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል አንዳች ነገር እንደሌለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ የሾመው መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ መላዋን ምድር ወደ ገነትነት ይለውጣታል።—ሉቃስ 23:43
14, 15. (ሀ) ይሖዋ “ሁሉንም ነገር አዲስ” የሚያደርገው እንዴት ነው? (ለ) በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን ይመስላል? አንተን ይበልጥ የሚያጓጓህ ምንድን ነው?
14 መላዋ ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ይሖዋ ያንን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። (ራእይ 21:5) ይህ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል አስብ። ይሖዋ ኃይሉን ተጠቅሞ ይህን ክፉ አሮጌ ሥርዓት ሲያጠፋ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” ይተካሉ። በሌላ አነጋገር አንድ አዲስ መንግሥት፣ ይሖዋን የሚወዱና ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎችን ያቀፈውን አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ ከሰማይ ሆኖ ያስተዳድራል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ማድረግ እንዳይችሉ ይታገዳሉ። (ራእይ 20:3) ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጆች ሰይጣንና አጋንንቱ ከሚያሳድሩት መጥፎና ጎጂ ተጽዕኖ ነፃ ይሆናሉ። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ እፎይታ ነው!
15 አምላክ መጀመሪያ ካወጣው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ይህችን ውብ ምድር መንከባከብ እንጀምራለን። ምድር በተፈጥሮዋ ራሷን በራሷ የማደስ ኃይል አላት። ለብክለት መንስኤ የሆኑት ነገሮች ከጠፉ የተበከሉ ሐይቆችና ወንዞች በውስጣቸው ያለውን መርዝ በማስወገድ ራሳቸውን ማጥራት ይችላሉ፤ ጦርነቶች ቢቆሙ በጦር መሣሪያ የተጎዱ መልክዓ ምድሮች የቀድሞ ውበታቸውን መልሰው መላበስ ይችላሉ። በዚህ የተፈጥሮ ሥርዓት በመጠቀም ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥና ስፍር ቁጥር በሌላቸው ዕፀዋትና እንስሳት እንድትሞላ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻል እንዴት የሚያስደስት ነው! የሰው ልጅ እንስሳትንና ዕፀዋትን ያለርኅራኄ መጨፍጨፉን አቁሞ በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ ጋር በሰላም መኖር ይጀምራል። ሕፃናትም እንኳ ቢሆኑ የዱር አራዊትን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት አይኖርም።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:1-9
16. ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ በገነት ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የሚታደሱት እንዴት ነው?
16 እኛም በግለሰብ ደረጃ በተለያየ መንገድ እንታደሳለን። ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተአምራዊ ፈውስ ሲካሄድ ይመለከታሉ። ኢየሱስ በምድር ሳለ እንዳደረገው በዚያን ጊዜም አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም የዓይነ ስውራንን ዓይን ያበራል፣ መስማት የተሳናቸውን ጆሮ ይከፍታል እንዲሁም ሽባዎችን ይፈውሳል። (ማቴዎስ 15:30) አረጋውያን ጉልበታቸውና ጤንነታቸው ታድሶ ወደ ወጣትነታቸው ይመለሳሉ። (ኢዮብ 33:25) በእርጅና ምክንያት የሚመጣ የቆዳ መጨማደድ አይኖርም፤ የተኮማተሩ ጡንቻዎችና ጅማቶችም ይፍታታሉ። ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአትና አለፍጽምና ያስከተሉባቸው ችግሮች ቀስ በቀስ ከላያቸው ሲወገዱ ይመለከታሉ። ይሖዋ አምላክ አስደናቂ የሆነውን ኃይሉን በመጠቀም እንዲህ ያለ ፈውስ ሲያደርግልን ምንኛ እናመሰግነው ይሆን! በዚህ አስደናቂ የተሃድሶ ዘመን የሚፈጸመውን ይበልጥ አስደሳች የሆነ አንድ ክንውን እስቲ እንመልከት።
ሙታንን ወደ ሕይወት መመለስ
17, 18. (ሀ) ኢየሱስ ሰዱቃውያንን የወቀሳቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኤልያስ ይሖዋ ምን እንዲያደርግለት ጠየቀ? ለምንስ?
17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ ሰዱቃውያን በመባል የሚታወቁ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በትንሣኤ አያምኑም ነበር። ኢየሱስ “እናንተ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ስለማታውቁ ተሳስታችኋል” ሲል ወቅሷቸዋል። (ማቴዎስ 22:29) አዎን፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም የሞቱ ሰዎችን ወደ ሕይወት መመለስ እንደሚችል ይናገራሉ። እንዴት?
18 በኤልያስ ዘመን የተፈጸመን አንድ ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። አንዲት መበለት የምትወደው አንድያ ልጇ እጇ ላይ ሞቶባታል። በመበለቲቱ ቤት በእንግድነት ተቀምጦ የነበረው ነቢዩ ኤልያስ በጣም ደንግጦ መሆን አለበት። ቀደም ሲል ኤልያስ ይህን ልጅ ከረሃብ ታድጎት የነበረ ከመሆኑም በላይ ለልጁ ልዩ ፍቅር አድሮበት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እናቱ ልቧ በሐዘን ተሰብሯል። በሞት ላጣችው ባሏ ያላት ምትክ ይህ አንድ ልጇ ብቻ ነበር። አድጎ ይጦረኛል ብላ ተስፋ የምታደርገው እሱን ነው። በጣም ከመረበሿና ግራ ከመጋባቷ የተነሳ በፈጸመችው ኃጢአት ሳቢያ አምላክ እየቀጣት እንዳለ አድርጋ አስባ ነበር። ኤልያስ የእናቲቱን ሁኔታ ሲመለከት አንጀቱ ተንሰፈሰፈ። የልጁን አስከሬን ከእናቲቱ እቅፍ ተቀብሎ በእንግድነት ወዳረፈበት ክፍል ከወሰደው በኋላ ወደ ሕይወት እንዲመልሰው ይሖዋን ተማጸነው።—1 ነገሥት 17:8-21
19, 20. (ሀ) አብርሃም፣ ይሖዋ አንድን ነገር ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው እንደሚያምን ያሳየው እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲኖረው ያደረገውስ ምንድን ነው? (ለ) ኤልያስ ላሳየው እምነት ይሖዋ ወሮታ የከፈለው እንዴት ነው?
19 ከኤልያስ ዘመን በፊትም በትንሣኤ የሚያምኑ የአምላክ አገልጋዮች ነበሩ። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የኖረው አብርሃም ይሖዋ አንድን ነገር ለማደስ ወይም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ያምን ነበር። እንዲህ ዓይነት እምነት ሊኖረው የቻለው ያለምክንያት አይደለም። አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸው በነበረበት ወቅት ዘር የመተካት ችሎታቸውን መልሶ በመስጠት ሣራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ልጅ እንድትወልድ አድርጓል። (ዘፍጥረት 17:17፤ 21:2, 3) ልጁ አድጎ ለአቅመ አዳም ሲደርስ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግለት ይሖዋ ጠየቀው። አብርሃም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ይሖዋ መልሶ ሕያው ሊያደርግለት እንደሚችል እምነት ነበረው። (ዕብራውያን 11:17-19) ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ተራራው ከመውጣቱ በፊት ከይስሐቅ ጋር ተመልሰው እንደሚመጡ ለአገልጋዮቹ በእርግጠኝነት የነገራቸው እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ሊሆን ይችላል።—ዘፍጥረት 22:5
“ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል”!
20 በጊዜው ይሖዋ ይስሐቅን መሥዋዕት ከመሆን እንዲተርፍ ስላደረገው በትንሣኤ ማስነሳት አላስፈለገውም። የመበለቲቱ ልጅ ግን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሞቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ልጁን ከሞት በማስነሳት ኤልያስ ላሳየው እምነት ወሮታ ከፍሎታል። ኤልያስም “ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል” በማለት ልጁን ለእናቱ ሰጣት።—1 ነገሥት 17:22-24
21, 22. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ከሞት ስለተነሱ ሰዎች የሚገልጹት ዘገባዎች ምን ይጠቁማሉ? (ለ) በገነት ውስጥ የሚፈጸመው ትንሣኤ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል? ይህን የሚያከናውነውስ ማን ነው?
21 ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ሞቶ የነበረን ሰው መልሶ ሕያው እንዳደረገ የሚገልጸው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይህ ነው። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለኤልሳዕ፣ ለኢየሱስ፣ ለጳውሎስና ለጴጥሮስም ይህን ኃይል በመስጠት የሞቱ ሰዎችን እንዲያስነሱ አድርጓል። እርግጥ ነው፣ በዚያን ጊዜ ተነስተው የነበሩ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ሞተዋል። ሆኖም እንዲህ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወደፊት የሚፈጸመውን ተስፋ ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናቸው።
22 ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ሲል የገባውን ቃል በገነት ውስጥ በተግባር ይፈጽማል። (ዮሐንስ 11:25) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኙ ያደርጋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ሰዎች በሞት ተለይተዋቸው ከነበሩ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ጋር ዳግም ሲገናኙና ተቃቅፈው በደስታ ሲላቀሱ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ይሖዋ እንዲህ ያለ ኃይል ያለው አምላክ በመሆኑ ሰዎች ሁሉ ያወድሱታል።
23. ይሖዋ ኃይሉን ከሁሉ በላቀ መንገድ ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ ለወደፊቱ ተስፋችን ዋስትና የሚሆነው እንዴት ነው?
23 ይሖዋ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም አስተማማኝ ዋስትና ሰጥቷል። ልጁን ኢየሱስን ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር አድርጎ ከሞት በማስነሳትና ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ማዕረግ በመስጠት ኃይሉን ከሁሉ በላቀ መንገድ አሳይቷል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አይተውታል። (1 ቆሮንቶስ 15:5, 6) በትንሣኤ ለሚጠራጠሩ ሰዎች እንኳ ይህ በቂ ማስረጃ ነው። ይሖዋ ዳግም ሕያው ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው።
24. ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? የትኛውን ተስፋስ ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል?
24 ይሖዋ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም አለው። ታማኙ ኢዮብ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት እንደሚናፍቅ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ተናግሯል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ኃይሉን እንዲህ ባለ ፍቅራዊ መንገድ የሚጠቀምበት መሆኑ ወደ እሱ እንድትቀርብ አይገፋፋህም? ይሁን እንጂ ትንሣኤ ይሖዋ ከሚያከናውነው ታላቅ የተሃድሶ ሥራ ውስጥ አንዱ ብቻ መሆኑን አስታውስ። እንግዲያው ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ ቅረብ፤ እንዲሁም አምላክ “ሁሉንም ነገር አዲስ [ለማድረግ]” የገባው ቃል ሲፈጸም የማየት ተስፋህን ከፍ አድርገህ ተመልከት።—ራእይ 21:5
a “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” የጀመረው መሲሐዊው መንግሥት ተቋቁሞ የታማኙ ንጉሥ የዳዊት ወራሽ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት ጊዜ ነው። ይሖዋ ለዳዊት፣ ዘሩ ለዘላለም እንደሚገዛ ቃል ገብቶለት ነበር። (መዝሙር 89:35-37) ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በባቢሎን ከጠፋች በኋላ በአምላክ ዙፋን ላይ የነገሠ የዳዊት ዘር አልነበረም። ሆኖም የዳዊት ዘር ሆኖ በምድር ላይ የተወለደው ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲሾም አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት የዙፋን ወራሽ ሆኗል።
b ለምሳሌ ያህል ሙሴ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብድዩ፣ ሚክያስና ሶፎንያስ እንዲህ ዓይነት መልእክት የያዘ ትንቢት ተናግረዋል።
-
-
‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 9
‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’
1-3. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ባሕር ላይ ምን አስፈሪ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? ኢየሱስስ ምን አደረገ? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’ ማለቱ ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት ተውጠዋል። በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሳለ ድንገት ማዕበል ተነሳ። በዚህ ሐይቅ ላይ ማዕበል ሲያጋጥማቸው ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በዓሣ አጥማጅነት ሥራ ረጅም ዓመታት ያሳለፉ ናቸው።a (ማቴዎስ 4:18, 19) ሆኖም በዚህ ጊዜ ያጋጠማቸው “እጅግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ” በመሆኑ ባሕሩን ክፉኛ አናወጠው። ባለ በሌለ ኃይላቸው ለመቅዘፍ ቢሞክሩም ማዕበሉን ሊቋቋሙት አልቻሉም። ማዕበሉ “ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዋ በውኃ ልትሞላ ተቃረበች።” ይህ ሁሉ ሲሆን ኢየሱስ ሕዝቡን ሲያስተምር ውሎ ስለደከመው በጀልባዋ የኋለኛ ክፍል ውስጥ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እንዳይሰምጡ ስለፈሩ ኢየሱስን ቀስቅሰው “ጌታ ሆይ፣ ማለቃችን እኮ ነው፤ አድነን!” ብለው ተማጸኑት።—ማርቆስ 4:35-38፤ ማቴዎስ 8:23-25
2 ኢየሱስ በሁኔታው ምንም አልተረበሸም። ከዚህ ይልቅ ነፋሱንና ባሕሩን “ጸጥ በል! ረጭ በል!” ሲል ገሠጸ። ወዲያውኑም ነፋሱና ማዕበሉ ቆመ፤ “ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ፈርተው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው?” ተባባሉ። በእርግጥም ነፋስንና ባሕርን እንደ ትንሽ ልጅ ሊገሥጽ የቻለው ምን ዓይነት ሰው ቢሆን ነው?—ማርቆስ 4:39-41፤ ማቴዎስ 8:26, 27
3 አዎን፣ ኢየሱስ ተራ ሰው አልነበረም። የይሖዋ ኃይል በኢየሱስ አማካኝነት አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ተገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’ ማለቱ የተገባ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:24) የአምላክ ኃይል በኢየሱስ አማካኝነት የተገለጸባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ኢየሱስ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ በእኛ ሕይወት ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
የአምላክ አንድያ ልጅ ያለው ኃይል
4, 5. (ሀ) ይሖዋ ለአንድያ ልጁ ምን ኃይልና ሥልጣን ሰጥቶታል? (ለ) ኢየሱስ አባቱ የሰጠውን የፍጥረት ሥራ ማከናወን እንዲችል ምን ተሰጥቶታል?
4 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበረውን ኃይል እስቲ እንመልከት። ይሖዋ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ የተጠራውን አንድያ ልጁን ሲፈጥር ‘ዘላለማዊ ኃይሉን’ ተጠቅሟል። (ሮም 1:20፤ ቆላስይስ 1:15) ከዚያም ይሖዋ ልጁ በፍጥረት ሥራዎቹ እንዲካፈል በማድረግ ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን ሰጥቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ልጅ አስመልክቶ ሲናገር “ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በእሱ በኩል ነው፤ ያለእሱ ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር የለም” ይላል።—ዮሐንስ 1:3
5 ይህ ሥራ ምን ያህል ስፋት እንዳለው ሙሉ በሙሉ መረዳት አዳጋች ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኃያላን መላእክትን፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎችን ያቀፈውን ግዙፍ ጽንፈ ዓለምና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ዝርያዎች የያዘችውን ምድር መፍጠር ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንደሚጠይቅ እስቲ አስብ። የአምላክ አንድያ ልጅ እነዚህን ሥራዎች ማከናወን እንዲችል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው ኃይል ማለትም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተሰጥቶት ነበር። ይህ ልጅ ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር ዋና ሠራተኛ አድርጎ ስለተጠቀመበት ከፍተኛ ደስታ አግኝቷል።—ምሳሌ 8:22-31
6. ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ምን ኃይልና ሥልጣን ተሰጥቶታል?
6 የአምላክ አንድያ ልጅ ከዚህ የላቀ ኃይልና ሥልጣን ሊሰጠው ይችላል? ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 28:18) አዎን፣ ኢየሱስ በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ላይ የመግዛት ችሎታና መብት ተሰጥቶታል። “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” እንደመሆኑ መጠን የአባቱን ሥልጣን የሚቀናቀንን ማንኛውንም የሚታይም ሆነ የማይታይ “መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን” የማጥፋት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። (ራእይ 19:16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:24-26) ይሖዋ ከራሱ በስተቀር “ያላስገዛለት ምንም ነገር የለም።”—ዕብራውያን 2:8፤ 1 ቆሮንቶስ 15:27
7. ኢየሱስ ይሖዋ የሰጠውን ኃይል አላግባብ እንደማይጠቀምበት እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ኃይሉን አላግባብ ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርብን ይገባል? በፍጹም! አባቱን እጅግ ስለሚወደው እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር አያደርግም። (ዮሐንስ 8:29፤ 14:31) ኢየሱስ አባቱ ሁሉን ማድረግ የሚያስችለውን ኃይሉን አላግባብ እንደማይጠቀምበት ጠንቅቆ ያውቃል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን [ለማሳየት]” ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንደሚጠቀም ኢየሱስ ተመልክቷል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) እንደ አባቱ ለሰው ልጆች ከፍተኛ ፍቅር ስላለው ምንጊዜም ቢሆን ኃይሉን በጎ ለሆነ ዓላማ እንደሚጠቀምበት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 13:1) በዚህ ረገድ ያስመዘገበው ታሪክ እንከን የማይወጣለት ነው። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምን ያህል ኃይል እንደነበረውና ይህን ኃይሉን እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት።
“በቃል ኃያል”
8. ኢየሱስ ከተቀባ በኋላ ምን እንዲያደርግ ኃይል ተሰጠው? ይህን ኃይልስ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
8 ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ በልጅነቱ ናዝሬት ውስጥ በነበረበት ወቅት ምንም ተአምር አልፈጸመም። ይሁን እንጂ በ29 ዓ.ም. በ30 ዓመቱ ገደማ ሲጠመቅ ይህ ሁኔታ ተለወጠ። (ሉቃስ 3:21-23) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ቀባው፤ ደግሞም ኃይል ሰጠው፤ ኢየሱስም . . . መልካም ነገር እያደረገና በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የወደቁትን እየፈወሰ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ” በማለት ይነግረናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:38) “መልካም ነገር እያደረገ” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ ኃይሉን በአግባቡ እንደተጠቀመበት የሚያመለክት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ከተቀባ በኋላ “በሥራም ሆነ በቃል ኃያል ነቢይ” ሆነ።—ሉቃስ 24:19
9-11. (ሀ) ኢየሱስ በአብዛኛው ያስተምር የነበረው በየትኞቹ ቦታዎች ነው? ትምህርቱንስ በምን መንገድ ማቅረብ ነበረበት? (ለ) ሕዝቡ በትምህርቱ የተገረሙት ለምን ነበር?
9 ኢየሱስ በቃል ኃያል የሆነው እንዴት ነው? በአብዛኛው ያስተምር የነበረው ደጅ ላይ ማለትም በሐይቅ ዳርቻዎችና በተራራ አጠገብ እንዲሁም በጎዳናዎችና በገበያ ቦታዎች ነበር። (ማርቆስ 6:53-56፤ ሉቃስ 5:1-3፤ 13:26) ትምህርቱ የአድማጮቹን ትኩረት የማይስብ ቢሆን ኖሮ ጥለውት ይሄዱ እንደነበር የታወቀ ነው። መጻሕፍት ይታተሙ ባልነበረበት በዚያ ዘመን አድማጮች ትምህርቱን በጥሞና አዳምጠው በአእምሯቸውና በልባቸው መቅረጽ ያስፈልጋቸው ነበር። በመሆኑም የኢየሱስ ትምህርት አድማጮችን የሚመስጥ፣ ግልጽና በቀላሉ ሊታወስ የሚችል መሆን ነበረበት። ይህን ማድረግ ለኢየሱስ አስቸጋሪ አልነበረም። የተራራ ስብከቱን እንደ ምሳሌ እንመልከት።
10 በ31 ዓ.ም. አንድ ቀን ጠዋት በገሊላ ባሕር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ኮረብታ ላይ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። አንዳንዶቹ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ከ100 እስከ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው የመጡ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ በስተ ሰሜን ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና የባሕር ዳርቻዎች የመጡ ናቸው። ኢየሱስ ቀርበው ሊዳስሱት ይሞክሩ የነበሩትን የታመሙ ሰዎች በሙሉ ፈወሳቸው። ሁሉንም ከፈወሰ በኋላ ማስተማር ጀመረ። (ሉቃስ 6:17-19) አስተምሮ ሲጨርስ ሰዎቹ በትምህርቱ እጅግ ተገረሙ። ለምን?
11 በተራራው ስብከት ላይ ተገኝቶ የነበረ አንድ ሰው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤ የሚያስተምራቸው . . . እንደ ባለሥልጣን ነበርና።” (ማቴዎስ 7:28, 29) አድማጮቹ ኢየሱስ እንደ ባለሥልጣን ይናገር እንደነበር ማስተዋል ችለዋል። አምላክን ወክሎ ይናገር የነበረ ሲሆን ትምህርቱም በአምላክ ቃል የተደገፈ ነበር። (ዮሐንስ 7:16) ትምህርቶቹ ግልጽ፣ ምክሮቹ አሳማኝ እንዲሁም የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች ሊታበሉ የማይችሉ ናቸው። ትምህርቱ ወሳኝ በሆኑ ቁም ነገሮች ላይ ያተኮረ ከመሆኑም በላይ የአድማጮቹን ልብ የሚነካ ነበር። ደስታ ማግኘት፣ መጸለይ፣ የአምላክን መንግሥት መፈለግና ሕይወታቸውን አስተማማኝ በሆነ መሠረት ላይ መገንባት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 5:3 እስከ 7:27) ያስተማረው ትምህርት እውነትንና ጽድቅን የተጠሙ ሰዎችን ልብ ለተግባር አነሳስቷል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ‘ለመካድና’ ሁሉን ትተው እሱን ለመከተል ፈቃደኞች ሆነዋል። (ማቴዎስ 16:24፤ ሉቃስ 5:10, 11) ኢየሱስ በቃል ኃያል ነው መባሉ ምንኛ ተገቢ ነው!
“በሥራ . . . ኃያል”
12, 13. ኢየሱስ ‘በሥራ ኃያል’ የነበረው በምን መንገድ ነው? የፈጸማቸው ተአምራት ብዙ ዓይነት ናቸው እንድንል የሚያደርገንስ ምንድን ነው?
12 ኢየሱስ ‘በሥራም ኃያል’ ነበር። (ሉቃስ 24:19) ኢየሱስ ‘በይሖዋ ኃይል’ የፈጸማቸው ከ30 የሚበልጡ ተአምራት በወንጌሎች ውስጥ በቀጥታ ተጠቅሰው እናገኛለን።b (ሉቃስ 5:17) ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት 5,000 ወንዶችን በሌላ ወቅት ደግሞ 4,000 ወንዶችን በተአምር መግቧል። ሴቶችና ልጆች ሲጨመሩ በእነዚህ ጊዜያት ኢየሱስ የመገባቸው ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር በብዙ ሺዎች የሚቆጠር እንደሚሆን ይገመታል።—ማቴዎስ 14:13-21፤ 15:32-38
13 ኢየሱስ ብዙ ዓይነት ተአምራት ፈጽሟል። አጋንንትን በማስወጣት በእነሱ ላይ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 9:37-43) ውኃን ወደ ወይን በመለወጥ ግዑዝ በሆኑ ነገሮችም ላይ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። (ዮሐንስ 2:1-11) በአንድ ወቅት “ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ” ወደ እነሱ ሲመጣ በማየታቸው ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ተገርመዋል። (ዮሐንስ 6:18, 19) በበሽታም ላይ ሥልጣን የነበረው ሲሆን አካላዊ ጉድለቶችን፣ ሥር የሰደዱ ሕመሞችንና ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ በሽታዎችን ፈውሷል። (ማርቆስ 3:1-5፤ ዮሐንስ 4:46-54) እነዚህን ፈውሶች ያከናወነው በተለያዩ መንገዶች ነው። አንዳንዶቹ የተፈወሱት ዳስሷቸው ሲሆን ገና በሩቅ ሳለ የተፈወሱም አሉ። (ማቴዎስ 8:2, 3, 5-13) ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ የተፈወሱት ወዲያውኑ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን ቀስ በቀስ ነው።—ማርቆስ 8:22-25፤ ሉቃስ 8:43, 44
‘ኢየሱስ በባሕሩ ላይ ሲራመድ ተመለከቱ’
14. ኢየሱስ በሞት ላይ እንኳ ሥልጣን እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
14 የሚያስገርመው ኢየሱስ በሞት ላይ እንኳ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን እንዳስነሳ የሚገልጹ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። አንዲትን የ12 ዓመት ልጅ፣ የአንዲትን መበለት አንድያ ልጅና እህቶቹ በጣም ይወዱት የነበረን አንድ ሰው ከሞት አስነስቷል። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:49-56፤ ዮሐንስ 11:38-44) የገጠሙት ሁኔታዎች በሙሉ ከአቅሙ በላይ አልነበሩም። የ12 ዓመቷን ልጅ ያስነሳት ወዲያው እንደሞተች ነበር። የመበለቲቱን ልጅ ያስነሳው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ ቀብር እየወሰዱት ሳለ ነበር፤ ስለዚህ ያስነሳው በዚያው በሞተበት ዕለት መሆን አለበት። አልዓዛርን ደግሞ ያስነሳው ሞቶ ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ነበር።
ኃይልን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ፣ በማስተዋልና በአሳቢነት መጠቀም
15, 16. ኢየሱስ ኃይሉን የተጠቀመው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ እንደሆነ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
15 ፍጽምና የሌለው አንድ ሰብዓዊ ገዢ የኢየሱስን ያህል ኃይል ቢኖረው ምን ያህል አላግባብ ሊጠቀምበት እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፍጹም ነው። (1 ጴጥሮስ 2:22) ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ኃይላቸውን አላግባብ በመጠቀም ሌሎችን ለመጉዳት የሚነሳሱት እንደ ራስ ወዳድነት፣ የሥልጣን ጥመኝነትና ስግብግብነት የመሳሰሉ ባሕርያት ስላሏቸው ሲሆን ኢየሱስ ግን ከእነዚህ ባሕርያት የጸዳ ነው።
16 ኢየሱስ ኃይሉን በራስ ወዳድነት የግል ጥቅሙን ለማሟላት አልተጠቀመበትም። ተርቦ በነበረበት ወቅት ድንጋዮችን ወደ ዳቦ እንዲቀይር የቀረበለትን ጥያቄ አልተቀበለም። (ማቴዎስ 4:1-4) ብዙ ቁሳዊ ነገር ያልነበረው መሆኑ ኃይሉን ለግል ጥቅሙ እንዳላዋለ የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 8:20) የተለያዩ ተአምራትን የፈጸመው በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ እንዳልሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ አለ። እነዚህን ተአምራት ለመፈጸም በተወሰነ ደረጃ መሥዋዕትነት መክፈል ጠይቆበታል። የታመሙትን በሚፈውስበት ጊዜ ኃይል ከእሱ ይወጣ ነበር። አንድ ሰው ብቻ በፈወሰበት ጊዜ እንኳ ከእሱ ኃይል እንደወጣ ታውቆት ነበር። (ማርቆስ 5:25-34) ያም ሆኖ ግን ብዙ ሰዎች እሱን በመዳሰስ እንዲፈወሱ አድርጓል። (ሉቃስ 6:19) ኢየሱስ ራስ ወዳድ እንዳልሆነ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማስረጃ ነው!
17. ኢየሱስ ኃይሉን ማስተዋል በተሞላበት መንገድ እንደተጠቀመበት ያሳየው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ ኃይሉን የተጠቀመበት ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ነው። ተአምራት የፈጸመው እንዲሁ ለታይታ ወይም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ብሎ አልነበረም። (ማቴዎስ 4:5-7) የሄሮድስን የተሳሳተ የማወቅ ጉጉት ለማርካት ሲል ብቻ ተአምር ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። (ሉቃስ 23:8, 9) ያለው ኃይል በሰው ሁሉ ዘንድ እንዲታወቅለት ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ብዙውን ጊዜ የፈወሳቸው ሰዎች ለሌሎች እንዳይናገሩ ያዝዛቸው ነበር። (ማርቆስ 5:43፤ 7:36) ዝናውን በመስማት ብቻ ለእሱ ልዩ ስሜት እንዲያድርባቸው ማድረግ አልፈለገም።—ማቴዎስ 12:15-19
18-20. (ሀ) ኢየሱስ ኃይሉን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ አንድን መስማት የተሳነው ሰው ስለፈወሰበት መንገድ ስታስብ ምን ይሰማሃል?
18 ኃያል የሆነው ኢየሱስ ሥልጣናቸውን ለሰዎች ችግርና ሥቃይ ደንታ ቢስ በሆነ መንገድ ከሚጠቀሙ ሰብዓዊ ገዢዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። ኢየሱስ ለሰዎች ያስባል። የተለያየ መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸውን ሰዎች ሲያይ አንጀቱ ስለሚንሰፈሰፍ ችግራቸውን ያስወግድላቸው ነበር። (ማቴዎስ 14:14) ለስሜታቸውና ለፍላጎታቸው ስለሚጨነቅ ኃይሉን በአሳቢነት ይጠቀምበት ነበር። በማርቆስ 7:31-37 ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው ልብ የሚነካ ታሪክ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው።
19 በዚህ ወቅት ኢየሱስ ሕዝቡ ወደ እሱ ይዘዋቸው የመጡትን በርካታ ሕሙማን ፈውሷል። (ማቴዎስ 15:29, 30) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለአንድ ሰው ልዩ አሳቢነት በማሳየት ለብቻው ነጥሎ ወሰደው። ሰውየው መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት ነበር። ኢየሱስ ይህ ሰው እንደተደናገጠ ወይም እንደተሸማቀቀ አስተውሎ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በአሳቢነት ከሕዝቡ ነጥሎ ገለል ወዳለ ቦታ ወሰደው። ከዚያም ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ሰውየው እንዲገነዘብ ለማድረግ ሲል አንዳንድ ምልክቶች ተጠቀመ። “ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አስገባ፤ እንትፍ ካለ በኋላም የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ።”c (ማርቆስ 7:33) በመቀጠል ኢየሱስ ወደ ሰማይ አሻቅቦ ተመለከተና በረጅሙ ተነፈሰ። ይህን ያደረገው ሰውየው የሚፈወሰው በአምላክ ኃይል መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው። በመጨረሻም ኢየሱስ “ተከፈት” አለ። (ማርቆስ 7:34) በዚህ ጊዜ ሰውየው መስማትና አጥርቶ መናገር ቻለ።
20 ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም የታመሙ ሰዎችን በሚፈውስበት ጊዜ እንኳ ለሰዎቹ ስሜት ያስብ የነበረ መሆኑ እንዴት ልብ የሚነካ ነው! ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ሩኅሩኅና አሳቢ ንጉሥ በመሲሐዊ መንግሥቱ ላይ ገዢ አድርጎ መሾሙ የሚያስደስት አይደለም?
ትንቢታዊ ትርጉም ያዘለ
21, 22. (ሀ) ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ምን ያመላክታሉ? (ለ) ኢየሱስ በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ሥልጣን ያለው በመሆኑ በንጉሣዊ ግዛቱ ወቅት ምን ያደርጋል ብለን መጠበቅ እንችላለን?
21 ኢየሱስ ምድር ሳለ የፈጸማቸው ተአምራት ወደፊት በንጉሣዊ ግዛቱ ውስጥ የሚፈሱትን ታላላቅ በረከቶች ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናቸው። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተአምራትን ያከናውናል። ወደፊት ከሚጠብቁን አስደሳች ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
22 ኢየሱስ የተዛባውን የምድርን ሥነ ምህዳር መልሶ ያስተካክላል። ከዚህ ቀደም ማዕበልን ጸጥ በማድረግ በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ሥልጣን እንዳለው ማሳየቱን አስታውስ። በክርስቶስ ንጉሣዊ የግዛት ዘመን ሰዎች አውሎ ነፋስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ሊያደርሱብን ይችላሉ የሚል ስጋት አያድርባቸውም። ይሖዋ ምድርንና በላይዋ የሚኖሩትን ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ በፈጠረበት ጊዜ ኢየሱስ ዋና ሠራተኛ ሆኖ በመሥራቱ የምድር አፈጣጠር ለእሱ እንግዳ አይደለም። የምድርን የተፈጥሮ ሀብት እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻል ያውቃል። በእሱ የግዛት ዘመን መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች።—ሉቃስ 23:43
23. ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ኢየሱስ የሰው ልጆች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች የሚያሟላው እንዴት ነው?
23 የሰው ልጆች ስለሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮችስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ በጥቂት ዳቦና ዓሣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መመገብ መቻሉ በእሱ የግዛት ዘመን ረሃብን እንደሚያስወግድ ያረጋግጥልናል። ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ስለሚያገኝ ረሃብ የሚባል ነገር ፈጽሞ አይኖርም። (መዝሙር 72:16) በሕመምና በበሽታ ላይ ሥልጣን ያለው መሆኑ ሕመምተኞችን፣ ማየትና መስማት የተሳናቸውን፣ አንካሶችንና ሽባዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈውስ እንድንተማመን ያደርገናል። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) ኢየሱስ ሙታንንም አስነስቶ ነበር፤ ይህም ኃያል ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ምድርን በሚገዛበት ወቅት አባቱ ከሞት እንዲነሱ የሚፈልጋቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚያስነሳ ያረጋግጥልናል።—ዮሐንስ 5:28, 29
24. ኢየሱስ ስላለው ኃይል ስናሰላስል ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል? ለምንስ?
24 ኢየሱስ ስላለው ኃይል ስናሰላስል ይህ የአምላክ ልጅ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን እናስታውስ። (ዮሐንስ 14:9) በመሆኑም ኢየሱስ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ይሖዋ ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት እንድንገነዘብ ያስችለናል። ለምሳሌ የሥጋ ደዌ ያለበትን አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ ያሳየውን ርኅራኄ አስብ። ሰውየው ሊያነጻው ይፈልግ እንደሆነ ኢየሱስን ሲጠይቀው እጅግ ስላሳዘነው ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ” አለው። (ማርቆስ 1:40-42) ይሖዋ እንዲህ በመሳሰሉ ታሪኮች አማካኝነት ‘ኃይሌን የምጠቀምበት በዚህ መንገድ ነው!’ እያለን እንዳለ አድርገን እናስብ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ኃይሉን እንዲህ ባለ ፍቅራዊ መንገድ የሚጠቀምበት መሆኑ እሱን እንድታወድስና እንድታመሰግን አይገፋፋህም?
a በገሊላ ባሕር ላይ ድንገተኛ ማዕበል ብዙ ጊዜ ይነሳል። ይህ ባሕር በጣም ዝቅተኛ ቦታ ላይ (ከባሕር ወለል በታች 200 ሜትር ገደማ ዝቅ ብሎ) ስለሚገኝ ባሕሩ ላይ ያለው አየር በአካባቢው ካለው አየር ይበልጥ ሞቃታማ ነው፤ በዚህም የተነሳ በከባቢ አየር ውስጥ ነውጥ ይፈጠራል። በስተ ሰሜን በኩል ከሚገኘው የሄርሞን ተራራ ተነስተው ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ የሚነፍሱ ኃይለኛ ነፋሳት አሉ። ጸጥ ብሎ የነበረው የአየር ጠባይ ድንገት ተለውጦ ኃይለኛ ማዕበል ሊነሳ ይችላል።
b ከዚህም በተጨማሪ በወንጌሎች ውስጥ በርከት ያሉ ተአምራት አንድ ላይ ጠቅለል ተደርገው የተገለጹባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ በአንድ ወቅት የአንዲት ‘ከተማ ሰው ሁሉ’ ኢየሱስን ለማየት ወጥቶ የነበረ ሲሆን በዚያ የነበሩትን “በርካታ” ሕሙማን ፈውሷል።—ማርቆስ 1:32-34
c እንትፍ ማለት በአይሁዶችም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ የተለመደ የፈውስ ምልክት ነበር። ምራቅን ለፈውስ ይጠቀሙበት እንደነበር የሚገልጽ ዘገባ በረቢዎች ጽሑፍ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። ኢየሱስ እንትፍ ያለው ሰውየው ሊፈወስ መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ምራቁን ለመፈወስ እንደሚያገለግል መድኃኒት አድርጎ አልተጠቀመበትም።
-
-
በኃይል አጠቃቀም ረገድ “አምላክን የምትመስሉ ሁኑ”ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
ምዕራፍ 10
በኃይል አጠቃቀም ረገድ “አምላክን የምትመስሉ ሁኑ”
1. ፍጽምና የጎደለው የሰው ልጅ ብዙውን ጊዜ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል።” ይህ የተለመደ አባባል ሥልጣንና ኃይል ሰዎችን ሊያባልግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ ሥልጣናቸውን አላግባብ ሲጠቀሙበት ይታያል። በእርግጥም በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9) የሰው ልጅ ሥልጣኑንና ኃይሉን አላግባብ መጠቀሙ ያስከተለው ሰቆቃ በቃላት ሊገለጽ አይችልም።
2, 3. (ሀ) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ያለን ኃይል ምን ነገሮችን የሚጨምር ሊሆን ይችላል? ይህን ኃይላችንንስ እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?
2 ይሖዋ አምላክ ገደብ የለሽ ኃይል ያለው ቢሆንም እንኳ ይህን ኃይሉን አላግባብ ተጠቅሞበት የማያውቅ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም? ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንዳየነው ለመፍጠር፣ ለማጥፋት፣ ለመጠበቅም ሆነ ለማደስ የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት ፍቅር ከሚንጸባረቅባቸው ዓላማዎቹ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት ስናሰላስል ወደ እሱ ለመቅረብ እንገፋፋለን። ይህ ደግሞ ኃይላችንን በአግባቡ በመጠቀም ‘አምላክን ለመምሰል’ እንድንጣጣር ሊያነሳሳን ይችላል። (ኤፌሶን 5:1) ይሁንና እዚህ ግቡ የማንባል እኛ የሰው ልጆች ምን ኃይል አለን?
3 የሰው ልጅ “በአምላክ መልክ” እና አምሳል እንደተፈጠረ አስታውስ። (ዘፍጥረት 1:26, 27) በመሆኑም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኃይል አለን። ያለን ኃይል የተለያዩ ነገሮች ለማከናወን የሚያስችል አቅምን፣ በሌሎች ላይ የሚኖረንን ሥልጣን፣ በሰዎች ላይ በተለይ ደግሞ በሚወዱን ሰዎች ላይ የምናሳድረውን ተጽዕኖ፣ አካላዊ ጥንካሬን (ጉልበትን) ወይም ቁሳዊ ሀብትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው” ብሏል። (መዝሙር 36:9) ስለዚህ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኃይላችን ምንጭ አምላክ ነው። ስለሆነም ይህን ኃይላችንን እሱን በሚያስደስት መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ቁልፉ ፍቅር ነው
4, 5. (ሀ) ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም የሚረዳው ቁልፍ ምንድን ነው? አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ይህን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? (ለ) ፍቅር ያለንን ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀም የሚረዳን እንዴት ነው?
4 ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም ቁልፉ ፍቅር ነው። አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ይህን የሚያንጸባርቅ አይደለም? በምዕራፍ 1 ላይ የአምላክን አራት ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ኃይሉን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን አስመልክቶ የተሰጠውን ማብራሪያ አስታውስ። ከእነዚህ አራት ባሕርያት መካከል ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው የትኛው ነው? ፍቅር ነው። አንደኛ ዮሐንስ 4:8 “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ሁለንተናው ፍቅር ስለሆነ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው። በማንኛውም ጊዜ ኃይሉን የሚጠቀመው በፍቅር ተነሳስቶ ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው የሚወዱትን ሁሉ ለመጥቀም ሲል ነው።
5 እኛም ያለንን ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀምበት የሚረዳን ፍቅር ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ደግ ነው። . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) በመሆኑም ፍቅር ካለን በእኛ ሥልጣን ሥር ያሉትን ሰዎች አናንገላታም ወይም አንጨቁንም። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች አክብሮት የምናሳይ ከመሆኑም በላይ ለእነሱ ፍላጎትና ስሜት ቅድሚያ እንሰጣለን።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4
6, 7. (ሀ) አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ባሕርይ ሥልጣንንና ኃይልን አላግባብ ከመጠቀም እንድንቆጠብ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አምላክን ላለማሳዘን መፍራትና አምላክን መውደድ ምን ዝምድና እንዳላቸው በምሳሌ አስረዳ።
6 ፍቅር ያለንን ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀምበት ሊረዳን ከሚችል ሌላም ባሕርይ ጋር ዝምድና አለው። ይህ ባሕርይ ለአምላክ ያለን ፍርሃት ነው። አምላክን መፍራታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ምሳሌ 16:6 “[ሰው] ይሖዋን በመፍራት ከክፋት ይርቃል” ይላል። ልንርቃቸው ከሚገቡ ክፉ ነገሮች አንዱ ኃይልን አላግባብ መጠቀም ነው። አምላክን መፍራታችን በእኛ ሥልጣን ሥር ያሉ ሰዎችን እንዳንበድል ያግደናል። እንዴት? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በእነዚህ ሰዎች ላይ የምንፈጽመው ነገር በአምላክ ፊት እንደሚያስጠይቀን እንገነዘባለን። (ነህምያ 5:1-7, 15) ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ሌላም የሚጨምረው ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍርሃትን” ለመግለጽ የተጠቀሱት ቃላት ብዙውን ጊዜ ከጥልቅ አድናቆትና አክብሮት የመነጨ ፍርሃትን ያመለክታሉ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ፍርሃትን ለእሱ ካለን ፍቅር ጋር አዛምዶ ይገልጸዋል። (ዘዳግም 10:12, 13) ይህ ከአድናቆት የመነጨ አክብሮት አምላክን ላለማሳዘን ስንል የምናሳየውን ትክክለኛ ፍርሃት ይጨምራል። እንዲህ ዓይነት ፍርሃት የምናሳየው ይቀጣናል ብለን በመስጋት ሳይሆን አምላክን ከልብ ስለምንወደው ነው።
7 ይህን ለማስረዳት በአንድ ትንሽ ልጅና በአባቱ መካከል የሚኖረውን ጥሩ ግንኙነት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ልጁ አባቱ እንደሚወደው በሚገባ ያውቃል። ይሁን እንጂ አባቱ ከእሱ ምን እንደሚጠብቅና ቢያጠፋ ሊቀጣው እንደሚችልም ያውቃል። እንዲህ ሲባል ግን አባቱን በመፍራት እየተሸማቀቀ ይኖራል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አባቱን ከልብ እንደሚወደው የታወቀ ነው። ልጁ አባቱን የሚያስደስት ነገር ለማድረግ ይጥራል። አምላክን የሚፈራ ሰው የሚያደርገውም እንዲሁ ነው። ሰማያዊ አባታችን የሆነውን ይሖዋን ስለምንወደው ‘ልቡን የሚያሳዝን’ ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን። (ዘፍጥረት 6:6) ከዚህ ይልቅ ልቡን ለማስደሰት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። (ምሳሌ 27:11) ያለንን ሥልጣንና ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም የምንጥረውም ለዚህ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።
በቤተሰብ ውስጥ
8. (ሀ) ባል በቤተሰብ ውስጥ ምን ሥልጣን አለው? ሥልጣኑንስ እንዴት ሊጠቀምበት ይገባል? (ለ) አንድ ባል ሚስቱን እንደሚያከብራት ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
8 በመጀመሪያ እስቲ በቤተሰብ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንመልከት። ኤፌሶን 5:23 “[ባል] የሚስቱ ራስ ነው” ሲል ይገልጻል። አንድ ባል አምላክ የሰጠውን ይህን ሥልጣን ሊጠቀምበት የሚገባው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችን “[ከሚስቶቻችሁ] ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ። . . . ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው” በማለት ይመክራቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7) እዚህ ጥቅስ ላይ “አክብሮት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዋጋ፣ ግምት፣ . . . ማዕረግ” ማለት ነው። የዚህ ቃል ርቢ “ስጦታ” እና “ክቡር” ተብሎም ተተርጉሟል። (የሐዋርያት ሥራ 28:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:7) ሚስቱን የሚያከብር ባል አይደበድባትም ወይም በማዋረድና በማንቋሸሽ የከንቱነት ስሜት እንዲሰማት አያደርግም። ከዚህ ይልቅ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳላት በመገንዘብ በአክብሮት ይይዛታል። ለእሱ ምን ያህል ውድ ወይም ክቡር እንደሆነች በግልም ይሁን በሰው ፊት በቃልና በድርጊት ይገልጽላታል። (ምሳሌ 31:28) እንዲህ ያለው ባል የሚስቱን ፍቅርና አክብሮት ብቻ ሳይሆን የአምላክንም ሞገስ ያገኛል።
ባሎችና ሚስቶች አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት በማሳየት ኃይላቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይችላሉ
9. (ሀ) ሚስት በቤተሰብ ውስጥ ምን ቦታ አላት? (ለ) አንዲት ሚስት ያላትን ችሎታ ባሏን ለመደገፍ እንድትጠቀምበት ሊረዳት የሚችለው ምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት አለው?
9 ሚስቶችም በቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የራስነት ሥልጣንን ሳይጥሱ በባሎቻቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ስላሳደሩ ወይም ባሎቻቸው የተሳሳተ ውሳኔ እንዳያደርጉ ስለረዱ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ይናገራል። (ዘፍጥረት 21:9-12፤ 27:46 እስከ 28:2) አንዲት ሚስት ከባሏ ይበልጥ ፈጣን የሆነ አእምሮ ወይም እሱ የሌሉት አንዳንድ ችሎታዎች ይኖሯት ይሆናል። ሆኖም ባሏን ‘በጥልቅ ማክበር’ ያለባት ከመሆኑም በላይ ‘ለጌታ እንደምትገዛ ሁሉ ለባሏ መገዛት’ ይኖርባታል። (ኤፌሶን 5:22, 33) አምላክን ለማስደሰት ያላት ፍላጎት ባሏን ከመናቅ ወይም በባሏ ላይ ለመሠልጠን ከመሞከር ይልቅ ያላትን ችሎታ እሱን ለመደገፍ እንድትጠቀምበት ሊያነሳሳት ይችላል። እንዲህ ያለች “ጥበበኛ ሴት” ከባሏ ጋር በመተባበር ቤተሰቧን ለመገንባት ትጥራለች። እንዲህ በማድረግ ከአምላክ ጋር ያላትን ሰላም ጠብቃ ትኖራለች።—ምሳሌ 14:1
10. (ሀ) አምላክ ለወላጆች ምን ሥልጣን ሰጥቷል? (ለ) “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? እንዴትስ መሰጠት ይኖርበታል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
10 አምላክ ለወላጆችም የሰጠው ሥልጣን አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኤፌሶን 6:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተግሣጽ” የሚለው ቃል “ኮትኩቶ ማሳደግን፣ ማሠልጠንንና ማስተማርን” ሊያመለክት ይችላል። ልጆች በጥሩ ሁኔታ ተኮትኩተው እንዲያድጉ ከተፈለገ በግልጽ የተቀመጡ መመሪያዎችና ደንቦች ሊሰጧቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ተግሣጽ ወይም ማሠልጠኛ ከፍቅር ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። (ምሳሌ 13:24) ስለሆነም “የተግሣጽ በትር” የልጆችን ስሜትም ሆነ አካል የሚጎዳ መሆን የለበትም።a (ምሳሌ 22:15፤ 29:15) ድርቅ ያለ ሕግ ማውጣት ወይም ፍቅርና ርኅራኄ የሌለው ተግሣጽ መስጠት የወላጅነት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ከመሆኑም በላይ የልጁን ስሜት ሊጎዳ ይችላል። (ቆላስይስ 3:21) በሌላ በኩል ግን ልጆች በተገቢው መንገድ ሚዛናዊ የሆነ ተግሣጽ የሚሰጣቸው ከሆነ ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸው እንዲሁም ጥሩ ልጆች ሆነው እንዲያድጉ የሚፈልጉ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል።
11. ልጆች ኃይላቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?
11 ልጆችስ ያላቸውን ኃይል በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ 20:29 “የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው” ይላል። በእርግጥም ወጣቶች ያላቸውን ጉልበትና ኃይል በተሻለ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን’ ሲያገለግሉ ብቻ ነው። (መክብብ 12:1) ወጣቶች የሚያደርጉት ነገር በወላጆቻቸው ስሜት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዳለ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 23:24, 25) ልጆች ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ወላጆቻቸውን ሲታዘዙና በትክክለኛው የሕይወት ጎዳና ላይ ሲጓዙ የወላጆቻቸውን ልብ ደስ ያሰኛሉ። (ኤፌሶን 6:1) እንዲህ ማድረጋቸው “ጌታን ያስደስተዋል።”—ቆላስይስ 3:20
በጉባኤ ውስጥ
12, 13. (ሀ) ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) ሽማግሌዎች መንጋውን በርኅራኄ መያዝ ያለባቸው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
12 ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩ የበላይ ተመልካቾችን ሾሟል። (ዕብራውያን 13:17) ለዚህ ኃላፊነት የበቁ ወንዶች አምላክ የሰጣቸውን ሥልጣን ለመንጋው አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግና መንጋውን በመንፈሳዊ ለመንከባከብ ሊጠቀሙበት ይገባል። ሽማግሌዎች ሥልጣናቸውን የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመጫን ሊጠቀሙበት ይገባል? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ በጉባኤው ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ማየት የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስ ለበላይ ተመልካቾች “በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ [ጠብቁ]” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) ይህ ማሳሰቢያ ሽማግሌዎች እያንዳንዱን የመንጋው አባል በርኅራኄ እንዲይዙ ሊገፋፋቸው ይገባል።
13 ይህን ሁኔታ በሚከተለው መንገድ በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል። የቅርብ ጓደኛህ አንድ ውድ ዕቃ እንድትይዝለት በአደራ ሰጠህ እንበል። ይህን ዕቃ በውድ ዋጋ እንደገዛው ታውቃለህ። በመሆኑም ዕቃውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደምትይዘው የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አምላክ ለሽማግሌዎች ውድ ዋጋ ያለው ንብረት ማለትም በበጎች የተመሰሉ አባላትን ያቀፈ ጉባኤ በአደራ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 21:16, 17) ይሖዋ በጎቹን በጣም ስለሚወዳቸው በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ደም ገዝቷቸዋል። ይሖዋ ለበጎቹ ከሁሉ የላቀውን ውድ ዋጋ ከፍሏል። ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች ይህን ስለሚገነዘቡ የይሖዋን በጎች በእንክብካቤ ይይዛሉ።
‘የአንደበት ኃይል’
14. አንደበት ምን ኃይል አለው?
14 መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበት የሞትና የሕይወት ኃይል አላት” ይላል። (ምሳሌ 18:21) በእርግጥም አንደበት ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። አሳቢነት በጎደለው ወይም ክብርን ዝቅ በሚያደርግ አነጋገር ስሜቱ ያልቆሰለ ማን አለ? ይሁን እንጂ አንደበት የመፈወስም ኃይል አለው። ምሳሌ 12:18 “የጥበበኞች ምላስ . . . ፈውስ ነው” ይላል። አዎን፣ የሚያበረታታና መንፈስን የሚያድስ ቃል የልብን ቁስል እንደሚጠግንና እንደሚፈውስ ዘይት ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
15, 16. አንደበታችንን ሌሎችን ለማበረታታት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
15 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:14 “የተጨነቁትን አጽናኗቸው” የሚል ምክር ይሰጣል። አዎን፣ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንዲህ ያሉትን ሰዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በይሖዋ ፊት ውድ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥሩ ጎናቸውን ለይተህ በመጥቀስ ከልብ አመስግናቸው። ይሖዋ ‘ልባቸው ለተሰበረና መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ ሰዎች እንደሚያስብና እንደሚጨነቅ እንዲሁም እንደሚወዳቸው የሚያሳዩ ጥቅሶችን አንብብላቸው። (መዝሙር 34:18) አንደበታችንን ሌሎችን ለማጽናናት የምንጠቀምበት ከሆነ ‘ተስፋ የቆረጡትን የሚያጽናናውን’ ሩኅሩኅ አምላካችንን እንደምንመስል እናሳያለን።—2 ቆሮንቶስ 7:6 ሕያው ቃል
16 በተጨማሪም አንደበታችን ያለውን ኃይል ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ቀርበን ለማበረታታት ልንጠቀምበት እንችላለን። የቅርብ ዘመድ ወይም ወዳጅ የሞተባቸው ወንድሞች ወይም እህቶች አሉ? እንደምናስብላቸውና የሐዘናቸው ተካፋይ እንደሆንን የሚያሳዩ ቃላትን ብንናገር ሊጽናኑ ይችላሉ። ፈላጊ እንደሌላቸው የሚሰማቸው በዕድሜ የገፉ ወንድም ወይም እህት አሉ? የታሰበባቸው ቃላት በመናገር እንደሚወደዱና እንደሚፈለጉ እንዲሰማቸው መርዳት እንችላለን። በከባድ ሕመም የሚሠቃይ ሰው ካለ ደግሞ ስልክ ደውለህ፣ ካርድ ልከህ ወይም በአካል ተገኝተህ ብታበረታታው እጅግ ሊጽናና ይችላል። አንደበታችን ያለውን ኃይል ሌሎችን ‘ለማነጽ’ ስንጠቀምበት ፈጣሪያችን እጅግ ይደሰታል።—ኤፌሶን 4:29
17. አንደበታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?
17 አንደበታችን ያለውን ኃይል ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ስንናገር ነው። ምሳሌ 3:27 “ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል” ይላል። ሕይወት አድን የሆነውን ምሥራች ለሰዎች የመንገር ግዴታ አለብን። ይሖዋ በደግነት የሰጠንን አስቸኳይ መልእክት ለራሳችን ብቻ ይዘን መቀመጥ ተገቢ አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 9:16, 22) ሆኖም ይሖዋ በዚህ ሥራ እንድንካፈል የሚፈልገው እስከ ምን ድረስ ነው?
ምሥራቹን ለሌሎች መስበክ ኃይላችንን በአግባቡ መጠቀም የምንችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው
‘በሙሉ ኃይላችን’ ይሖዋን ማገልገል
18. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው?
18 ለይሖዋ ያለን ፍቅር በክርስቲያናዊው አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ ይገፋፋናል። በዚህ ረገድ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ልናደርግ የሚገባውን ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት።” (ቆላስይስ 3:23) ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠውን ትእዛዝ አስመልክቶ ሲናገር “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:30) አዎን፣ ይሖዋ እያንዳንዳችን በሙሉ ነፍሳችን እንድንወደውና እንድናገለግለው ይፈልጋል።
19, 20. (ሀ) ነፍስ የሚለው ቃል ልብን፣ አእምሮንና ኃይልን የሚያጠቃልል ከሆነ በማርቆስ 12:30 ላይ እነዚህ ነገሮች ተለይተው የተጠቀሱት ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ምን ማለት ነው?
19 በሙሉ ነፍስ አምላክን ማገልገል ሲባል ምን ማለት ነው? ነፍስ የሚለው ቃል አካላዊና አእምሯዊ ችሎታን ጨምሮ የአንድን ሰው ሁለንተና ያመለክታል። ነፍስ ልብን፣ አእምሮንና ኃይልን የሚያጠቃልል ከሆነ በማርቆስ 12:30 ላይ እነዚህ ነገሮች ተለይተው የተጠቀሱት ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው ራሱን (ነፍሱን) ለባርነት ሊሸጥ ይችል ነበር። ሆኖም ባሪያው ጌታውን በሙሉ ልብ ላያገለግለው ይችላል፤ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ችሎታውን ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞ ጌታውን ለማገልገል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። (ቆላስይስ 3:22) በመሆኑም ኢየሱስ ልብን፣ አእምሮንና ኃይልን ለይቶ መጥቀስ የፈለገው ምንም ነገር ሳንቆጥብ አምላክን ማገልገል እንዳለብን ጎላ አድርጎ ለመግለጽ መሆን አለበት። አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ሲባል ያለንን ኃይልና ጉልበት ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ራሳችንን ለእሱ አገልግሎት ማዋል ማለት ነው።
20 በሙሉ ነፍስ ማገልገል አለብን ሲባል ሁላችንም ለአገልግሎት የምናውለው ጊዜና ጉልበት እኩል መሆን አለበት ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ምክንያቱም የእያንዳንዳችን ሁኔታና ችሎታ ይለያያል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ ጤንነትና ጉልበት ያለው አንድ ወጣት በዕድሜ መግፋት ሳቢያ አቅሙ ውስን ከሆነ ሰው ይበልጥ በስብከቱ ሥራ ብዙ መሥራት ይችል ይሆናል። ትዳር ያልያዘና የቤተሰብ ኃላፊነት የሌለበት አንድ ሰው የቤተሰብ ኃላፊነት ካለበት ሰው ይበልጥ ማገልገል ይችል ይሆናል። በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችል አቅምና ሁኔታ ካለን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! እርግጥ ነው፣ በዚህ ረገድ ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር የምንተችና የምንነቅፍ መሆን የለብንም። (ሮም 14:10-12) ከዚህ ይልቅ ኃይላችንን ሌሎችን ለማበረታታት ልንጠቀምበት ይገባል።
21. ኃይላችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
21 ይሖዋ ያለውን ኃይል በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ፍጹም ምሳሌያችን ነው። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ብንሆንም እሱን ለመምሰል የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። በእኛ ሥልጣን ሥር ያሉትን ሁሉ በአክብሮት በመያዝ ኃይላችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሰጠንን ሕይወት አድን የሆነ የስብከት ሥራ በሙሉ ነፍሳችን ማከናወን ይኖርብናል። (ሮም 10:13, 14) አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ በሙሉ ነፍስህ እሱን ለማገልገል የምታደርገው ጥረት ይሖዋን እንደሚያስደስተው አስታውስ። አቅምህንና ሁኔታህን የሚረዳልህን እንዲህ ያለውን አፍቃሪ አምላክ ለማገልገል አትነሳሳም? ኃይልህን መጠቀም የምትችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይህ ነው።
-