የጥናት ርዕስ 49
ይሖዋ ጸሎቴን ይመልስልኛል?
“እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።”—ኤር. 29:12
መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ
ማስተዋወቂያa
1-2. ይሖዋ ጸሎታችንን እንዳልመለሰልን የሚሰማን ለምን ሊሆን ይችላል?
“በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።” (መዝ. 37:4) ይሖዋ የገባልን ቃል ምንኛ የሚያስደስት ነው! ሆኖም ይሖዋ የምንጠይቀውን ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ይሰጠናል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል? ይህ ጥያቄ መነሳት ያስፈለገው ለምንድን ነው? የሚከተሉትን ምሳሌዎች ለማሰብ ሞክር። አንዲት ያላገባች እህት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል ትጸልያለች። ሆኖም ወደ ትምህርት ቤቱ ሳትጋበዝ ዓመታት አለፉ። አንድ ወጣት ወንድም በጉባኤ ውስጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲል ካለበት ከባድ ሕመም እንዲያድነው ይሖዋን ይጠይቀዋል። ይሁንና ጤንነቱ አልተሻሻለም። ክርስቲያን ወላጆች ልጃቸው እውነት ውስጥ እንዲቆይ ይጸልያሉ። ያም ቢሆን ልጃቸው ይሖዋን ማገልገሉን ለማቆም ወሰነ።
2 አንተም ይሖዋ አንድ ነገር እንዲያደርግልህ ጠይቀኸው እስካሁን አልመለሰልህ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ይሖዋ የአንዳንዶችን ጸሎት ቢመልስም የአንተን ግን እንደማይመልስልህ ሊሰማህ ይችላል። ወይም ደግሞ ያጠፋኸው ነገር እንዳለ ይሰማህ ይሆናል። ጃኔትb የተባለች እህት እንደዚህ ተሰምቷት ነበር። እሷና ባለቤቷ በቤቴል ለማገልገል ሲጸልዩ ቆይተዋል። እንዲህ ብላለች፦ “በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቴል እንደምንገባ እርግጠኛ ነበርኩ።” ሆኖም ዓመታት ቢያልፉም እንኳ ጃኔትና ባለቤቷ ቤቴል እንዲያገለግሉ አልተጋበዙም። ጃኔት እንዲህ ብላለች፦ “አዘንኩ፤ ግራ ተጋባሁ። ‘ይሖዋን አሳዝኜው ይሆን?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። ቤቴል መግባት እንድንችል በግልጽ ጠይቄው ነበር። ታዲያ ጸሎቴን ያልመለሰልኝ ለምንድን ነው?”
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
3 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ጸሎታችንን መስማቱን እንኳ እንጠራጠር ይሆናል። በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችም እንደዚህ ተሰምቷቸዋል። (ኢዮብ 30:20፤ መዝ. 22:2፤ ዕን. 1:2) ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (መዝ. 65:2) ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ (1) ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን መጠበቅ እንችላለን? (2) ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? (3) በምንጠይቃቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ የሚኖርብን ለምን ሊሆን ይችላል?
ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን መጠበቅ እንችላለን?
4. በኤርምያስ 29:12 መሠረት ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል?
4 ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ቃል ገብቶልናል። (ኤርምያስ 29:12ን አንብብ።) አምላካችን ታማኝ አገልጋዮቹን ስለሚወዳቸው ጸሎታቸውን ፈጽሞ ችላ አይልም። (መዝ. 10:17፤ 37:28) ይህ ማለት ግን የጠየቅነውን ነገር ሁሉ ይሰጠናል ማለት አይደለም። የጠየቅናቸውን አንዳንዶቹን ነገሮች ለማግኘት እስከ አዲሱ ዓለም ድረስ መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል።
5. ይሖዋ ጸሎታችንን ሲሰማ ምን ነገር ከግምት ያስገባል? አብራራ።
5 ይሖዋ ጸሎታችንን ሲሰማ ዓላማውን ከግምት ያስገባል። (ኢሳ. 55:8, 9) የይሖዋ ዓላማ፣ ምድር በደስታ ለእሱ በሚገዙ ወንዶችና ሴቶች እንድትሞላ ማድረግን ያካትታል። ሆኖም ሰይጣን፣ ሰዎች ራሳቸውን ቢያስተዳድሩ የተሻለ እንደሆነ ተከራክሯል። (ዘፍ. 3:1-5) ይሖዋ የዲያብሎስ ክስ ሐሰት መሆኑ እንዲረጋገጥ ሲል የሰው ልጆች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። የሰው ልጆች አገዛዝ በዛሬው ጊዜ የምናያቸውን አብዛኞቹን ችግሮች አስከትሏል። (መክ. 8:9) ይሖዋ እነዚህን ችግሮች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ እንደማያስወግዳቸው እንገነዘባለን። ምክንያቱም እንደዚያ ካደረገ አንዳንዶች፣ ሰዎች ራሳቸውን የማስተዳደር ብቃት እንዳላቸውና ችግሮቻችንን መቅረፍ እንደሚችሉ ሊሰማቸው ይችላል።
6. የይሖዋ መንገዶች ምንጊዜም ፍቅርና ፍትሕ የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ መተማመን ያለብን ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ ለተመሳሳይ ጥያቄዎች የተለያየ መልስ ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና በታመመ ጊዜ ይሖዋ እንዲያድነው ለምኖ ነበር። ይሖዋም ፈወሰው። (2 ነገ. 20:1-6) በሌላ በኩል ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሥጋውን የሚወጋውን እሾህ’ እንዲያስወግድለት ይሖዋን ጠይቆ ነበር፤ ይህ እሾህ የጤና እክል ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ይሖዋ ችግሩን አላስወገደለትም። (2 ቆሮ. 12:7-9) የሐዋርያው ያዕቆብንና የሐዋርያው ጴጥሮስን ምሳሌም እንመልከት። ንጉሥ ሄሮድስ ሁለቱንም ሊገድላቸው ፈልጎ ነበር። ጉባኤው ለጴጥሮስ ይጸልይ ነበር፤ ለያዕቆብም ጸልዮ መሆን አለበት። ሆኖም ያዕቆብ ተገደለ፤ ጴጥሮስ ግን በተአምር ተረፈ። (ሥራ 12:1-11) ‘ይሖዋ ጴጥሮስን አድኖ ያዕቆብ ግን እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን አይነግረንም።c በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር ቢኖር ይሖዋ ‘ፈጽሞ ፍትሕን እንደማያጓድል’ ነው። (ዘዳ. 32:4) በተጨማሪም ይሖዋ ጴጥሮስንም ሆነ ያዕቆብን እንደሚወዳቸው እናውቃለን። (ራእይ 21:14) አንዳንድ ጊዜ ያልጠበቅነው ነገር ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስበት መንገድ ምንጊዜም ፍቅርና ፍትሕ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ስለምንተማመን በሚሰጠን መልስ ላይ ጥያቄ አናነሳም።—ኢዮብ 33:13
7. ምን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባል? ለምንስ?
7 ያለንበትን ሁኔታ ከሌሎች ጋር ላለማወዳደር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ይሖዋ አንድ ነገር እንዲያደርግልን ጠይቀነው መልስ አላገኘን ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግን አንድ ክርስቲያን ተመሳሳይ ጸሎት አቅርቦ ይሖዋ የእሱን ጸሎት እንደመለሰለት ሰማን። አና የተባለች እህት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟታል። ባለቤቷ ማቲው ከካንሰር እንዲድን ጸልያ ነበር። በዚያው ወቅት ሁለት አረጋውያን እህቶችም ከካንሰር ጋር እየታገሉ ነበር። አና ለማቲውም ሆነ ለእነዚህ እህቶች አጥብቃ ጸለየችላቸው። እህቶች ከበሽታው አገገሙ፤ ማቲው ግን ሞተ። መጀመሪያ ላይ አና፣ እነዚህ እህቶች ማገገም የቻሉት ይሖዋ ስለረዳቸው እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ከሆነ ደግሞ፣ ባለቤቷ እንዲድን ያቀረበችውን ጸሎት ያልመለሰላት ለምን እንደሆነ ግራ ተጋባች። እርግጥ ነው፣ ሁለቱ እህቶች የዳኑት እንዴት እንደሆነ አናውቅም። በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር ይሖዋ መከራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድ እንዲሁም የሞቱ ወዳጆቹን ለማስነሳት እንደሚጓጓ ነው።—ኢዮብ 14:15
8. (ሀ) በኢሳይያስ 43:2 መሠረት ይሖዋ የሚደግፈን እንዴት ነው? (ለ) ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ጸሎት የሚረዳን እንዴት ነው? (ጸሎት የሚያጋጥመንን ችግር ለመቋቋም ይረዳናል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።)
8 ይሖዋ ምንጊዜም ይደግፈናል። አፍቃሪ አባታችን ይሖዋ ስንሠቃይ ማየት አይፈልግም። (ኢሳ. 63:9) ያም ቢሆን እንደ ወንዝና ነበልባል ያሉ ፈተናዎች እንዳይደርሱብን አይከላከልልንም። (ኢሳይያስ 43:2ን አንብብ።) ነገር ግን በመካከላቸው ‘ለማለፍ’ እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። እንዲሁም የሚደርስብን መከራ ዘላቂ ጉዳት እንዲያስከትልብን አይፈቅድም። ይሖዋ ኃያል ቅዱስ መንፈሱን በመስጠትም እንድንጸና ይረዳናል። (ሉቃስ 11:13፤ ፊልጵ. 4:13) በዚህም የተነሳ፣ ለመጽናትና ለእሱ ምንጊዜም ታማኝ ለመሆን የሚያስፈልገንን ማንኛውንም እርዳታ እንደሚሰጠን መተማመን እንችላለን።d
ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው?
9. በያዕቆብ 1:6, 7 መሠረት ይሖዋ እንደሚረዳን መተማመን ያለብን ለምንድን ነው?
9 ይሖዋ እንድንተማመንበት ይጠብቅብናል። (ዕብ. 11:6) አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥመን መከራ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። እንዲያውም ይሖዋ የሚረዳን መሆኑን መጠራጠር ልንጀምር እንችላለን። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ ኃይል “ቅጥር መውጣት” እንደምንችል ያረጋግጥልናል። (መዝ. 18:29) በመሆኑም በጥርጣሬ ከመዋጥ ይልቅ ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚመልስልን በመተማመን በሙሉ እምነት ልንጸልይ ይገባል።—ያዕቆብ 1:6, 7ን አንብብ።
10. ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
10 ይሖዋ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ እንድንወስድ ይጠብቅብናል። ለምሳሌ አንድ ወንድም በክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲል ከሥራው እረፍት ለማግኘት እንዲረዳው ይሖዋን ሊጠይቅ ይችላል። ይሖዋ ይህን ጸሎት የሚመልሰው እንዴት ሊሆን ይችላል? ወንድም አሠሪውን እንዲያነጋግር ድፍረት ሊሰጠው ይችላል። ሆኖም ወንድም አሠሪውን በማነጋገር ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። በተደጋጋሚ መጠየቅ ሊያስፈልገው ይችላል። ከሌላ ሠራተኛ ጋር ፈረቃ ለመቀያየር ሊሞክርም ይችላል። አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ፣ ያለደሞዝ እረፍት ለመውሰድ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል።
11. ስለሚያሳስበን ነገር በተደጋጋሚ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
11 ይሖዋ ስለሚያሳስበን ነገር በተደጋጋሚ እንድንጸልይ ይጠብቅብናል። (1 ተሰ. 5:17) ኢየሱስ የምናቀርበው አንዳንድ ጸሎት ወዲያውኑ መልስ እንደማያገኝ ጠቁሟል። (ሉቃስ 11:9) በመሆኑም ተስፋ አትቁረጥ! ከልብህ በተደጋጋሚ ጸልይ። (ሉቃስ 18:1-7) ስለ አንድ ጉዳይ መጸለያችንን ስንቀጥል ይሖዋ ያንን ነገር በጣም እንደምንፈልገው ማየት ይችላል። በተጨማሪም ይሖዋ እኛን የመርዳት ችሎታ እንዳለው እንደምናምን እናሳያለን።
በምንጠይቃቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ የሚኖርብን ለምን ሊሆን ይችላል?
12. (ሀ) ከጸሎታችን ጋር በተያያዘ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን አንዱ ጥያቄ ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) ጸሎታችን ይሖዋን እንደምናከብረው የሚያሳይ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (“ጸሎቴ ለይሖዋ አክብሮት እንዳለኝ ያሳያል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
12 በጸሎት የጠየቅነውን ነገር ካላገኘን ራሳችንን ሦስት ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን። አንደኛ፣ ‘ጥያቄዬ ተገቢ ነው?’ ብዙውን ጊዜ፣ የሚበጀንን ነገር እንደምናውቅ ይሰማናል። ሆኖም የጠየቅናቸው ነገሮች ላይጠቅሙን ይችላሉ። የምንጸልየው ስለ አንድ ችግር ከሆነ ለዚያ ችግር እኛ ከጠየቅነው የተሻለ መፍትሔ ሊኖር ይችላል። የምንጠይቃቸው አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ላይስማሙ ይችላሉ። (1 ዮሐ. 5:14) ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን ወላጆች እንደ ምሳሌ እንመልከት። ልጃቸው እውነት ውስጥ እንዲቆይ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀውት ነበር። ጥያቄያቸው ተገቢ ይመስላል። ይሁንና ይሖዋ ማናችንንም እንድናገለግለው አያስገድደንም። ልጆቻችንን ጨምሮ ሁላችንም እሱን ለማገልገል እንድንመርጥ ይፈልጋል። (ዘዳ. 10:12, 13፤ 30:19, 20) በመሆኑም እነዚህ ወላጆች የልጃቸውን ልብ ለመንካት እንዲረዳቸው ይሖዋን ቢጠይቁ የተሻለ ነው፤ ይህም ልጃቸው ይሖዋን እንዲወደውና የእሱ ወዳጅ እንዲሆን ሊያነሳሳው ይችላል።—ምሳሌ 22:6፤ ኤፌ. 6:4
13. በዕብራውያን 4:16 መሠረት ይሖዋ የሚረዳን መቼ ነው? አብራራ።
13 ሁለተኛ፣ ‘ይሖዋ ጥያቄዬን የሚመልስበት ጊዜ አሁን ነው?’ ጸሎታችን ወዲያውኑ መመለስ እንዳለበት ይሰማን ይሆናል። ሆኖም መልስ ለመስጠት ከሁሉ የተሻለውን ጊዜ የሚያውቀው ይሖዋ ነው። (ዕብራውያን 4:16ን አንብብ።) የጠየቅነውን ነገር ወዲያውኑ ካላገኘን ይሖዋ ‘አይሆንም’ እንዳለን ሊሰማን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋ መልስ ‘ትንሽ ጠብቅ’ ሊሆን ይችላል። ከበሽታው ለመዳን የጸለየውን ወጣት ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ በተአምር ቢፈውሰው፣ ሰይጣን ይህ ወንድም ይሖዋን ማገልገሉን የቀጠለው ስለተፈወሰ እንደሆነ ይናገር ይሆናል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) በዚያ ላይ ደግሞ ይሖዋ ሁሉንም በሽታ የሚያስወግድበትን ጊዜ ቀጥሯል። (ኢሳ. 33:24፤ ራእይ 21:3, 4) እስከዚያ ግን ተአምራዊ ፈውስ እንደምናገኝ ልንጠብቅ አንችልም። በመሆኑም ይህ ወንድም በሽታውን በጽናት መቋቋምና አምላክን በታማኝነት ማገልገሉን መቀጠል እንዲችል ጥንካሬና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ሊጠይቅ ይችላል።—መዝ. 29:11
14. ከጃኔት ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
14 በቤቴል ለማገልገል ጸልያ የነበረችውን የጃኔትን ተሞክሮ በድጋሚ እንመልከት። ይሖዋ ጸሎቷን የመለሰላት እንዴት እንደሆነ የተገነዘበችው ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ያንን ጊዜ እኔን ለማስተማርና ለመሞረድ ተጠቅሞበታል። በእሱ ላይ ያለኝ እምነት ማደግ ነበረበት። የግል ጥናት ልማዴም መሻሻል ነበረበት። በተጨማሪም ባለሁበት ሁኔታ ላይ የማይመካ ውስጣዊ ደስታ ማግኘት ነበረብኝ።” ከጊዜ በኋላ ጃኔትና ባለቤቷ በወረዳ ሥራ እንዲካፈሉ ተጋበዙ። ጃኔት ያሳለፈችውን ሕይወት መለስ ብላ ስታስብ እንዲህ ብላለች፦ “እኔ በጠበቅኩት መንገድ ባይሆንም ይሖዋ ጸሎቴን መልሶልኛል። ጸሎቴን በአስደናቂ መንገድ እንደመለሰልኝ ያስተዋልኩት ከጊዜ በኋላ ነው። ሆኖም የእሱን ፍቅርና ደግነት በማጣጣሜ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
ይሖዋ ለጸሎትህ መልስ እንዳልሰጠህ ከተሰማህ ጥያቄህን ለመቀየር ሞክር (አንቀጽ 15ን ተመልከት)f
15. ጥያቄያችንን ሰፋ ማድረግ የሚኖርብን ለምን ሊሆን ይችላል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
15 ሦስተኛ፣ ‘ጥያቄዬን ብቀይር ይሻል ይሆን?’ የምንፈልገውን ነገር ለይተን በመጥቀስ መጸለያችን ጥሩ ቢሆንም ጥያቄያችንን ሰፋ ማድረጋችን ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ለማስተዋል ሊረዳን ይችላል። በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል ስትጸልይ የነበረችውን ያላገባች እህት መለስ ብለን እናስብ። በትምህርት ቤቱ መካፈል የፈለገችው እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ማገልገል ስለፈለገች ነው። በመሆኑም በትምህርት ቤቱ ለመካፈል መጸለይዋን ብትቀጥልም ይሖዋ አገልግሎቷን ለማስፋት የሚረዱ ሌሎች አጋጣሚዎችን እንድታስተውል እንዲረዳት መጠየቅ ትችላለች። (ሥራ 16:9, 10) ከዚያም በአቅራቢያዋ ያለ ጉባኤ ተጨማሪ አቅኚዎች ያስፈልጉት እንደሆነ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን በመጠየቅ ከጸሎቷ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ትችላለች። ወይም ደግሞ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ የሚያስፈልጉት የት እንደሆነ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ጽፋ መጠየቅ ትችላለች።e
16. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
16 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ ጸሎታችንን ፍቅርና ፍትሕ በሚንጸባረቅበት መንገድ እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 4:3፤ ኢሳ. 30:18) አንዳንድ ጊዜ የጠበቅነውን መልስ አናገኝ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ጸሎታችንን ፈጽሞ ችላ አይልም። በጣም ይወደናል። ፈጽሞ አይተወንም። (መዝ. 9:10) በመሆኑም ልብህን በፊቱ በማፍሰስ ‘ሁልጊዜ በእሱ ታመን።’—መዝ. 62:8
መዝሙር 43 የምስጋና ጸሎት
a ይህ ርዕስ፣ ይሖዋ ጸሎታችንን ምንጊዜም ፍቅርና ፍትሕ በሚንጸባረቅበት መንገድ እንደሚመልስልን መተማመን የምንችለው ለምን እንደሆነ ያብራራል።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
d ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጸሎት የሚያጋጥመንን ችግር ለመቋቋም ይረዳናል የሚለውን ቪዲዮ ከjw.org ላይ ተመልከት።
e በሌላ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ ለማገልገል ራስህን ማቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ መመሪያ ለማግኘት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕ. 10 ከአን. 6-9 ተመልከት።
f የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት እህቶች ለመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ከማመልከታቸው በፊት ጸለዩ። በኋላ ላይ አንደኛዋ ተጋበዘች፤ ሌላኛዋ ግን አልተጋበዘችም። በትምህርት ቤቱ እንድትካፈል ያልተጋበዘችው እህት ከልክ በላይ ከማዘን ይልቅ ወደ ይሖዋ በመጸለይ አገልግሎቷን ለማስፋት የሚያስችሉ ሌሎች አጋጣሚዎችን እንድታስተውል እንዲረዳት ጠየቀችው። ከዚያም ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ በመጻፍ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ለማገልገል ራሷን አቀረበች።