የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ዮሴፍ ከሌሎች እስረኞች ጋር ምድር ቤት ውስጥ ታስሮ።

      ምዕራፍ 11

      “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው”

      1, 2. (ሀ) ዮሴፍ በተለያዩ ጊዜያት ምን ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል? (ለ) ይሖዋ ኢፍትሐዊ የሆነውን ድርጊት ለማስተካከል ምን እርምጃ ወስዷል?

      አንድ መልከ መልካም ወጣት፣ አስገድደህ ለመድፈር ሞክረሃል በሚል በሐሰት ተወንጅሎ ባልሠራው ጥፋት ወህኒ ተጥሏል። ሆኖም በደል ሲፈጸምበት ይህ የመጀመሪያው አልነበረም። ዮሴፍ የተባለው ይህ ወጣት ከተወሰኑ ዓመታት በፊትም ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ወንድሞቹ ስለጠሉት ሊገድሉት አስበው ነበር። በኋላ ግን ሐሳባቸውን በመለወጥ ባሪያ እንዲሆን ለባዕድ አገር ሰዎች ሸጡት። በባርነት በሚያገለግልበት ቤት የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ ልታባብለው ብትሞክርም ያቀረበችለትን ግብዣ ሳይቀበል ቀረ። በዚህ የተናደደችው ይህች ሴት በሐሰት ወንጅላ አሳሰረችው። የሚያሳዝነው ደግሞ ዮሴፍ አስታዋሽ ያለው አይመስልም ነበር።

      2 ይሁን እንጂ ‘ጽድቅንና ፍትሕን የሚወደው’ አምላክ ዮሴፍ የደረሰበትን ነገር ሁሉ ይመለከት ነበር። (መዝሙር 33:5) ይሖዋ፣ ዮሴፍ ከወህኒ የሚወጣበትን ሁኔታ በማመቻቸት ኢፍትሐዊ የሆነውን ድርጊት ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ እስር ቤት የነበረውን ዮሴፍን ከማስፈታቱም በተጨማሪ ከፍተኛ ሥልጣንና ክብር እንዲያገኝ አድርጓል። (ዘፍጥረት 40:15፤ 41:41-43፤ መዝሙር 105:17, 18) በመጨረሻም ዮሴፍ ከተወነጀለበት ክስ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ያገኘውንም ከፍተኛ ሥልጣን የአምላክን ዓላማ ለማስፈጸም ተጠቅሞበታል።—ዘፍጥረት 45:5-8

      ዮሴፍ በእስር ቤት አላግባብ ተንገላቷል

      3. ሁላችንም ፍትሕን የምንሻ መሆናችን ሊያስገርም የማይገባው ለምንድን ነው?

      3 እንዲህ ያለው ታሪክ ልብ የሚነካ አይደለም? ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸም ያላየ ወይም በራሱ ላይ ያልደረሰበት ማን አለ? አዎን፣ ሁላችንም ሌሎች ፍትሐዊና ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ እንዲይዙን እንፈልጋለን። ይሖዋ የእሱን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ አድርጎ ስለፈጠረን ይህ ፍላጎት ያለን መሆኑ ሊያስገርም አይገባም፤ ከይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት አንዱ ደግሞ ፍትሕ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይሖዋን በሚገባ ለማወቅ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት መረዳት ያስፈልገናል። ይህን ካደረግን አስደናቂ የሆኑትን መንገዶቹን ይበልጥ ልናደንቅና ከምንጊዜውም በበለጠ ወደ እሱ ለመቅረብ ልንገፋፋ እንችላለን።

      ፍትሕ ምንድን ነው?

      4. ብዙውን ጊዜ ሰዎች ፍትሕን የሚረዱት እንዴት ነው?

      4 ብዙውን ጊዜ ሰዎች ፍትሕን የሚረዱት ሕግን በአግባቡ ከማስፈጸም አንጻር ነው። ራይት ኤንድ ሪዝን—ኤቲክስ ኢን ቲዮሪ ኤንድ ፕራክቲስ የተባለው መጽሐፍ “ፍትሕ ከሕግ፣ ከግዴታ፣ ከመብትና ከኃላፊነት ጋር የተያያዘ ሲሆን አድልዎ የሌለበት ወይም ተገቢ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ይጠይቃል” ይላል። የይሖዋ ፍትሕ ግን እንዲሁ ድርቅ ባለ መንገድ ሕግን ለማስፈጸም ብቻ የቆመ አይደለም።

      5, 6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍትሕን” ለማመልከት የገቡት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? (ለ) አምላክ ፍትሐዊ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

      5 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ፍትሕን ለማመልከት የገቡትን ቃላት ጠለቅ ብሎ በመመርመር የይሖዋ ፍትሕ ያለውን ስፋትና ጥልቀት በሚገባ መረዳት ይቻላል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ፍትሕን ለማመልከት የተሠራባቸው ሦስት መሠረታዊ ቃላት አሉ። በብዙ ቦታዎች ላይ “ፍትሕ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ትክክል የሆነው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ዘፍጥረት 18:25) ሌሎቹ ሁለት ቃላት ደግሞ በብዙ ቦታዎች ላይ “ጽድቅ” ተብለው ተተርጉመዋል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ጽድቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ትክክለኛ ወይም ፍትሐዊ መሆን” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ስለዚህ ጽድቅና ፍትሕ የሚሉት ቃላት ተቀራራቢ ትርጉም አላቸው።—አሞጽ 5:24

      6 በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ፍትሐዊ ነው ሲል፣ ምንጊዜም አድልዎ የሌለበት ትክክለኛ ነገር ያደርጋል ማለቱ ነው። (ሮም 2:11) አምላክ ያዳላል ወይም አግባብ ያልሆነ ነገር ይፈጽማል ማለት ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ነው። ታማኙ ኤሊሁ “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 34:10) በእርግጥም ይሖዋ ፍትሕ ሊያጓድል አይችልም። ለምን? ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን እንመልከት።

      7, 8. (ሀ) ይሖዋ ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር ማድረግ የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያከናውን የሚገፋፋው ምንድን ነው?

      7 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ቅዱስ ነው። ምዕራፍ 3 ላይ እንዳየነው ይሖዋ በንጽሕናውና በጽድቅ አቋሙ ወደር አይገኝለትም። ስለሆነም ጠማማ ወይም ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር ሊያደርግ አይችልም። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ሰማያዊ አባታችን ቅዱስ በመሆኑ በልጆቹ ላይ ፈጽሞ በደል እንደማይፈጽም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ኢየሱስ በአባቱ ላይ እንዲህ ዓይነት እምነት ነበረው። በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ሌሊት “ቅዱስ አባት ሆይ፣ . . . ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው” ሲል ስለ ደቀ መዛሙርቱ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:11) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ቅዱስ አባት” የሚለው መጠሪያ የተሰጠው ለይሖዋ ብቻ ነው። በቅድስና ከይሖዋ ጋር ሊተካከል የሚችል ሰብዓዊ አባት ስለማይኖር ይህ መጠሪያ ለእሱ ብቻ መሰጠቱ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ፣ ንጹሕ በሆነውና ምንም ዓይነት ኃጢአት በሌለበት አባቱ ጥበቃ ሥር እስከሆኑ ድረስ ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለ ሙሉ እምነት ነበረው።—ማቴዎስ 23:9

      8 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የተላበሰ አምላክ ነው። ይህ ፍቅር ማንኛውንም ነገር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያከናውን ይገፋፋዋል። ዘረኝነትን፣ ወገናዊነትንና አድሏዊነትን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ብዙውን ጊዜ ከፍቅር ሳይሆን ከስግብግብነትና ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ሲናገር “ይሖዋ ጻድቅ ነውና፤ የጽድቅ ሥራዎችን ይወዳል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 11:7) ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ ይሖዋ ፍትሕን እወዳለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 61:8) አምላካችን ይሖዋ ትክክል ወይም ፍትሕ የሆነ ነገር ማድረግ እንደሚያስደስተው ማወቅ አያጽናናም?—ኤርምያስ 9:24

      ምሕረትና ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ

      9-11. (ሀ) የይሖዋ ፍትሕና ምሕረት ምን ዝምድና አላቸው? (ለ) ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ፍትሕና ምሕረት ያሳየው እንዴት ነው?

      9 አቻ እንደማይገኝላቸው እንደ ሌሎቹ የይሖዋ ባሕርያት ሁሉ ፍትሑም ፍጹምና እንከን የማይገኝበት ነው። ሙሴ ይሖዋን እንዲህ ሲል አወድሷል፦ “እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው።” (ዘዳግም 32:3, 4) ይሖዋ ፍትሑን የሚገልጽበት መንገድ ሁሉ እንከን የማይወጣለት ነው፤ በጣም ልዝብ ወይም ከልክ በላይ ጥብቅ አይደለም።

      10 የይሖዋ ፍትሕና ምሕረት ተዛማጅ ነገሮች ናቸው። መዝሙር 116:5 “ይሖዋ ሩኅሩኅና ጻድቅ [“ፍትሐዊ፣” ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል] ነው፤ አምላካችን መሐሪ ነው” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ፍትሐዊና መሐሪ አምላክ ነው። ሁለቱ ባሕርያት እርስ በርስ አይቃረኑም። ይሖዋ ፍትሑ ከልክ በላይ ጥብቅ የሆነ ይመስል ምሕረት የሚያሳየው ፍርዱን ለማለዘብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ባሕርያት እርስ በርስ የሚደጋገፉ በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ ይሖዋ አንድ ላይ ሲጠቀምባቸው ይታያል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

      11 የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአትን የወረሱ በመሆናቸው በኃጢአት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት ማለትም ሞት ይገባቸዋል። (ሮም 5:12) ሆኖም ኃጢአተኞች መሞታቸው ለይሖዋ የሚሰጠው ምንም ደስታ የለም። ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆነ፣ ሩኅሩኅና መሐሪ’ አምላክ ነው። (ነህምያ 9:17) ይሁንና ቅዱስ አምላክ በመሆኑ ኃጢአትን በቸልታ ሊያልፍ አይችልም። ታዲያ ኃጢአትን ለወረሱ የሰው ልጆች ምሕረት ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሰው ዘርን ለማዳን ቤዛ እንዳዘጋጀ የሚገልጸው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ውድ እውነት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። በምዕራፍ 14 ላይ ስለዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት በዝርዝር እንመለከታለን። ይህ ዝግጅት አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍትሕም ምሕረትም የተንጸባረቀበት ነው። ይሖዋ በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ፍጹም የሆነውን ፍትሑን ሳያዛባ ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ምሕረት ሊያሳይ ይችላል።—ሮም 3:21-26

      የይሖዋ ፍትሕ ማራኪ ነው

      12, 13. (ሀ) የይሖዋ ፍትሕ ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚጋብዘን ለምንድን ነው? (ለ) ዳዊት የይሖዋን ፍትሕ በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? ይህስ ሊያጽናናን የሚችለው እንዴት ነው?

      12 የይሖዋ ፍትሕ፣ ርኅራኄ የጎደለውና ከእሱ እንድንርቅ የሚያደርግ ሳይሆን እንድንወደውና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚገፋፋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ፍትሕ ወይም ጽድቅ ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ይገልጻል። ይሖዋ ፍትሑን የሚገልጥባቸውን አንዳንድ ማራኪ ገጽታዎች እንመልከት።

      13 ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ ለአገልጋዮቹ ታማኝ እንዲሆን ይገፋፋዋል። መዝሙራዊው ዳዊት ይህን በራሱ ሕይወት ማየት ችሏል። ዳዊት ከራሱ የሕይወት ተሞክሮም ሆነ አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ካደረገው ምርምር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም። ምንጊዜም ጥበቃ ያገኛሉ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 37:28) ይህ እንዴት የሚያጽናና ዋስትና ነው! አምላካችን ለእሱ ታማኝ የሆኑትን መቼም ቢሆን አይተዋቸውም። በመሆኑም ይሖዋ እንደማይከዳንና ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግልን ልንተማመን እንችላለን። ፍትሑ ለዚህ ዋስትና ነው!—ምሳሌ 2:7, 8

      14. ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ለድሆች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      14 የአምላክ ፍትሕ የተቸገሩ ሰዎችን ስሜትና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ለድሆች እንደሚያስብ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ ወላጅ የሌላቸው ልጆችና መበለቶች ተገቢውን እንክብካቤ ሊያገኙ የሚችሉበትን ዝግጅት ያካተተ ነው። (ዘዳግም 24:17-21) ይሖዋ እንዲህ ያሉ ቤተሰቦች፣ ኑሮ ምን ያህል ሊከብድባቸው እንደሚችል ስለሚያውቅ እሱ ራሱ እንደ አባት ጠባቂ እንዲሁም “አባት ለሌለው ልጅና ለመበለት [የሚፈርድ]” ዳኛ ሆኖላቸዋል።a (ዘዳግም 10:18፤ መዝሙር 68:5) እስራኤላውያን ረዳት የሌላቸውን ሴቶችና ልጆች የሚበድሉ ከሆነ ይሖዋ የእነዚህን ሰዎች ጩኸት እንደሚሰማና እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። “ቁጣዬም ይነድዳል” ሲል ተናግሯል። (ዘፀአት 22:22-24) ቁጣ ከይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት አንዱ ባይሆንም እንኳ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ኢፍትሐዊ ድርጊት በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉና ረዳት በሌላቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግፍ የጽድቅ ቁጣ እንዲቆጣ ያነሳሳዋል።—መዝሙር 103:6

      15, 16. ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳየው ግሩም ማስረጃ ምንድን ነው?

      15 በተጨማሪም ይሖዋ “ለማንም የማያዳላና ጉቦ የማይቀበል አምላክ” መሆኑን ገልጿል። (ዘዳግም 10:17) ይሖዋ በሥልጣን ላይ እንዳሉ ብዙ ሰዎች በቁሳዊ ሀብት ወይም ከውጭ በሚታይ ነገር አይደለልም። ምንም ዓይነት የወገናዊነትና የአድሏዊነት ስሜት አይታይበትም። ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳይ አንድ ግሩም ማስረጃ እንመልከት። የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች በመሆን የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ የተዘረጋው በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ጥቂት ሰዎች ብቻ አይደለም። “ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ይህ አስደናቂ ተስፋ የተዘረጋው በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ የትኛውም ዓይነት የቆዳ ቀለም ላላቸው ወይም በየትኛውም አገር ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ነው። ከዚህ የላቀ እውነተኛ ፍትሕ ሊኖር ይችላል?

      16 ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ በጥንቃቄ ልንመረምረው የሚገባ ሌላ ገጽታም አለው። ይህም የጽድቅ ሥርዓቱን በሚጥሱ ሰዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ የሚመለከት ነው።

      ሳይቀጣ አያልፍም

      17. በዚህ ዓለም ውስጥ የሚታዩት አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች የይሖዋን ፍትሕ አጠያያቂ ሊያደርጉ የማይችሉት ለምን እንደሆነ አብራራ።

      17 አንዳንዶች ‘ይሖዋ ዓመፅን በቸልታ የማያልፍ ከሆነ በዛሬው ጊዜ ግፍና ምግባረ ብልሹነት ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው?’ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች መስፋፋት የይሖዋን ፍትሕ አጠያያቂ ሊያደርግ አይችልም። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ የሚታዩት አብዛኞቹ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ሰዎች ከአዳም በወረሱት ኃጢአት ምክንያት የመጡ ናቸው። ራሳቸው በመረጡት የኃጢአት ጎዳና የሚመላለሱ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች መስፋፋታቸው አያስገርምም፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ አይቀጥልም።—ዘዳግም 32:5

      18, 19. ይሖዋ የጽድቅ ሕግጋቱን ሆን ብለው የሚጥሱ ሰዎችን ለዘላለም እንደማይታገሥ የሚያሳየው ምንድን ነው?

      18 ይሖዋ በቅን ልቦና ተነሳስተው ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ታላቅ ምሕረት የሚያሳይ ቢሆንም ቅዱስ በሆነው ስሙ ላይ ነቀፋ የሚያስከትል ሁኔታን ለዘላለም አይታገሥም። (መዝሙር 74:10, 22, 23) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ አይዘበትበትም፤ ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ያደርጋል። ይሖዋ “መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ . . . ጥፋተኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ” አምላክ ነው። (ዘፀአት 34:6, 7) በመሆኑም ይሖዋ ሆን ብለው የጽድቅ ሕግጋቱን የሚጥሱ ሰዎችን የቀጣባቸው ጊዜያት አሉ።

      19 ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ከጥንት እስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበረ እንመልከት። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ እንኳ በተደጋጋሚ ጊዜያት በአምላክ ላይ ዓምፀዋል። ምንም እንኳ መጥፎ ድርጊታቸው ‘ስሜቱን ቢጎዳውም’ ወዲያው እርግፍ አድርጎ አልተዋቸውም። (መዝሙር 78:38-41) ከዚህ ይልቅ በተደጋጋሚ ጊዜያት ምሕረት በማሳየት ከመጥፎ መንገዳቸው መመለስ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። “በክፉው ሰው ሞት ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ በሕይወት እንዲኖር እፈልጋለሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለምን ትሞታላችሁ?” ሲል ተማጽኗቸዋል። (ሕዝቅኤል 33:11) ይሖዋ ሕይወትን እንደ ውድ ነገር ስለሚመለከት በተደጋጋሚ ጊዜያት ነቢያቱን በመላክ እስራኤላውያን ከመጥፎ መንገዳቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ሞክሯል። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ልበ ደንዳና የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋን ለመስማትና ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ብለዋል። በመጨረሻም ይሖዋ ለቅዱስ ስሙ ይኸውም ይህ ስም የሚወክለውን ማንነቱን ለማሳየት ሲል ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው።—ነህምያ 9:26-30

      20. (ሀ) ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ስለ እሱ ምን ያስተምረናል? (ለ) አንበሳ ከአምላክና ከዙፋኑ ጋር ተያይዞ መገለጹ የተገባ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

      20 ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የነበረው ግንኙነት ስለ እሱ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ። ሁሉን ማየት የሚችሉት ዓይኖቹ የሚፈጸመውን ዓመፅ ሁሉ እንደሚመለከቱና ይህም እሱን እንደሚያሳዝነው ያስገነዝበናል። (ምሳሌ 15:3) በተጨማሪም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል ሁኔታ ካለ ምሕረት ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ማወቃችን የሚያጽናና ነው። ከዚህም ሌላ ይሖዋ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ አይቸኩልም። ይሖዋ ለረጅም ጊዜ ስለሚታገሥ ብዙ ሰዎች አምላክ በክፉዎች ላይ እርምጃ አይወስድም ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ይደርሳሉ። ሆኖም አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት መለኮታዊ ትዕግሥት ገደብ እንዳለው ስለሚያሳይ እንዲህ ያለው የሰዎች አመለካከት ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። ይሖዋ ለጽድቅ የቆመ አምላክ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ፍትሕን ለማስከበር ቆራጥ አቋም መውሰድ ሲሳናቸው ይታያል፤ ይሖዋ ግን ትክክል ለሆነው ነገር ለመቆም ድፍረቱ አለው። አንበሳ ድፍረት የሚጠይቀውን የፍትሕ ባሕርይ የሚወክል እንደመሆኑ መጠን ከአምላክና ከዙፋኑ ጋር ተያይዞ መገለጹ የተገባ ነው።b (ሕዝቅኤል 1:10፤ ራእይ 4:7) በመሆኑም ይሖዋ ግፍን ከምድር ገጽ ጠራርጎ ለማስወገድ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው የይሖዋን ፍትሕ በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል፦ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ እርምጃ ይወስዳል፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ደግሞ ምሕረት ያደርጋል።—2 ጴጥሮስ 3:9

      የፍትሕ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅረብ

      21. ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ ስለሚወስድበት መንገድ ስናሰላስል ስለ እሱ ምን አመለካከት ሊያድርብን ይገባል? ለምንስ?

      21 ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ ስለሚወስድበት መንገድ ስናሰላስል ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ብቻ የቆመ ርኅራኄ የሌለው ጨካኝ ፈራጅ እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይገባንም። ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ ለልጆቹ መልካም ነገር እንደሚያስብ አፍቃሪ ሆኖም ጥብቅ አቋም ያለው አባት አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ይሖዋ ፍትሐዊ ወይም ጻድቅ አባት እንደመሆኑ መጠን ትክክል ለሆነው ነገር ጥብቅ አቋም ያለው ቢሆንም የእሱን እርዳታና ምሕረት ለሚሹት ምድራዊ ልጆቹ ርኅራኄ ያሳያል።—መዝሙር 103:10, 13

      22. ይሖዋ ፍትሑን መሠረት በማድረግ ምን ተስፋ ዘርግቶልናል? ይህን ያደረገልንስ ለምንድን ነው?

      22 የአምላክ ፍትሕ፣ ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት ብቻ የቆመ እንዳልሆነ ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ ፍትሑን መሠረት በማድረግ አስደሳች ተስፋ ማለትም ‘ጽድቅ በሚሰፍንበት’ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆነ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላካችን ይህን ያደረገው ፍትሑ በተቻለ መጠን ሰዎችን ለማዳን እንጂ ለማጥፋት የቆመ ስላልሆነ ነው። በእርግጥም ስለ ይሖዋ ፍትሕ ያለን ግንዛቤ እየጨመረ በሄደ መጠን ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ እንገፋፋለን። ይሖዋ ይህን ድንቅ ባሕርይ ያንጸባረቀባቸውን መንገዶች በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ በጥልቀት እንመረምራለን።

      a ‘አባት የሌለው ልጅ’ የሚለው መግለጫ ለሴቶች ልጆችም እንደሚሠራ የታወቀ ነው። ስለ ሰለጰአድ ሴቶች ልጆች የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ፣ አባት ለሌላቸው ሴቶች ልጆችም በጥልቅ እንደሚያስብ ያሳያል። ሰለጰአድ የሞተው ወንድ ልጅ ሳይወልድ ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ፣ የሰለጰአድ ሴቶች ልጆች የአባታቸውን ርስት እንዲወርሱ ውሳኔ አስተላለፈ። በተጨማሪም ይህ ውሳኔ አባት የሌላቸውን ሴቶች ልጆች ሁሉ መብት የሚያስከብር ሕግ ሆኖ እንዲጸና አደረገ።—ዘኁልቁ 27:1-8

      b ይሖዋ ከሃዲ በሆነችው እስራኤል ላይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድ ሲገልጽ ራሱን በአንበሳ መስሏል።—ኤርምያስ 25:38፤ ሆሴዕ 5:14

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ኤርምያስ 18:1-11 ይሖዋ ሰዎችን ለመቅጣት እንደማይቸኩል ለኤርምያስ ያስተማረው እንዴት ነው?

      • ዕንባቆም 1:1-4, 13፤ 2:2-4 ይሖዋ ግፍን ለዘላለም እንደማይታገሥ ለዕንባቆም ያረጋገጠለት እንዴት ነው?

      • ዘካርያስ 7:8-14 ይሖዋ በሌሎች ላይ ግፍ ስለሚፈጽሙ ሰዎች ምን ይሰማዋል?

      • ሮም 2:3-11 ይሖዋ በግለሰቦችም ሆነ በብሔራት ላይ የሚፈርደው ምንን መሠረት በማድረግ ነው?

  • “አምላክ ፍትሕ ያዛባል?”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ ሲዘንብ ሎጥና ሁለት ሴቶች ልጆቹ በሰላም ዞአር ገቡ።

      ምዕራፍ 12

      “አምላክ ፍትሕ ያዛባል?”

      1. ግፍ ሲፈጸም ስናይ ምን ሊሰማን ይችላል?

      አንዲት አረጋዊት መበለት ያጠራቀሟትን ገንዘብ ሰው አጭበርብሮ ወሰደባቸው። አንድ አራስ ልጅ አውላላ ሜዳ ላይ ተጥሎ ተገኘ። አንድ ሰው ባልሠራው ወንጀል ተከሶ ለእስር ተዳረገ። እንዲህ ስለመሳሰሉት ድርጊቶች ስትሰማ ምን ይሰማሃል? እነዚህ ነገሮች አእምሮህን እንደሚረብሹት የታወቀ ነው፤ ደግሞም አያስገርምም። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ትክክል ወይም ስህተት ብሎ ለሚያስበው ነገር ጠንከር ያለ ስሜት አለው። በመሆኑም ግፍ ሲፈጸም ስናይ ያናድደናል። ግፍ የተፈጸመበት ሰው እንዲካስና በዳዩ ትክክለኛውን ቅጣት እንዲያገኝ እንፈልጋለን። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ‘ለመሆኑ አምላክ ይህን ግፍ ያያል? የሚያይ ከሆነስ ለምን እርምጃ አይወስድም?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

      2. ዕንባቆም ሲፈጸም ስላየው ግፍ ምን ተሰምቶት ነበር? ይሖዋስ ያልገሠጸው ለምንድን ነው?

      2 ከጥንት ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በተለያዩ ጊዜያት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አንስተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ዕንባቆም “ለምን በደል ሲፈጸም እንዳይ ታደርገኛለህ? ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ የሚፈጸመው ለምንድን ነው? ጠብና ግጭትስ ለምን በዛ?” ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዕንባቆም 1:3) ዕንባቆም በቅንነት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በማቅረቡ ይሖዋ አልገሠጸውም፤ ምክንያቱም ሰዎች የፍትሕ ባሕርይ እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው እሱ ራሱ ነው። አዎን፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የእሱን ፍጹም ፍትሕ እንድናንጸባርቅ አድርጎ ፈጥሮናል።

      ይሖዋ ግፍን ይጠላል

      3. ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

      3 ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ እንደሆነ ተመለከተ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:5) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። ብዙውን ጊዜ ስለ ፍትሕ መጓደል ያለን ግንዛቤ በሰማናቸው ወይም ባየናቸው አንዳንድ ክስተቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በጣም ውስን ነው። በአንጻሩ ግን ይሖዋ በመላው ምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይመለከታል! ከዚህም በላይ የሰዎችን የልብ ዝንባሌ ማለትም ከሚፈጽሟቸው ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በስተ ጀርባ ያለውን መጥፎ አስተሳሰብ ሁሉ ያያል።—ኤርምያስ 17:10

      4, 5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ግፍ ለሚፈጸምባቸው ሰዎች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በራሱ በይሖዋ ላይስ በደል የተፈጸመው እንዴት ነው?

      4 ይሁን እንጂ ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከማየት ባሻገር በዚህ ሳቢያ ለሚሠቃዩት ሰዎች ያስባል። ሕዝቦቹ “በሚጨቁኗቸውና በሚያንገላቷቸው [ጠላት ብሔራት] የተነሳ ሲቃትቱ” ይሖዋ ያዝን ነበር። (መሳፍንት 2:18) አንዳንድ ሰዎች የፍትሕ መጓደል የዕለት ተዕለት ክስተት ሲሆንባቸው ሁኔታውን እየተላመዱት ስለሚሄዱ በደል እየተፈጸመባቸው ላሉ ሰዎች ያላቸው አዘኔታ እንደሚቀንስ አስተውለህ ይሆናል። ይሖዋ ግን እንዲህ አይደለም! በመላው ምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ለ6,000 ዓመታት ሲመለከት የቆየ ቢሆንም እንዲህ ላለው ድርጊት ያለው ጥላቻ አልቀነሰም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “ውሸታም ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች” እና “ባወራ ቁጥር ውሸት የሚናገር ሐሰተኛ ምሥክር” በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ መሆናቸውን ይገልጽልናል።—ምሳሌ 6:16-19

      5 በተጨማሪም ይሖዋ የእስራኤልን ጨቋኝ ገዢዎች አጥብቆ እንዳወገዘ ልብ በል። “ትክክል የሆነውን ነገር [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ማወቅ አይገባችሁም?” ሲል በነቢዩ አማካኝነት ጠይቋቸዋል። ሥልጣናቸውን ምን ያህል አላግባብ እየተጠቀሙበት እንዳሉ ኃይለኛ መልእክት ባላቸው ቃላት ከገለጸላቸው በኋላ እነዚህ ብልሹ መሪዎች ምን እንደሚጠብቃቸው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም። ክፉ ድርጊት በመፈጸማቸው፣ በዚያን ጊዜ ፊቱን ይሰውርባቸዋል።” (ሚክያስ 3:1-4) ይህ ሁኔታ ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ምን ያህል እንደሚጠላ የሚያሳይ ነው! እንዲህ ያለው በደል በራሱም ላይ ደርሷል! ሰይጣን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይሖዋን ሲነቅፈው ኖሯል። (ምሳሌ 27:11) ከዚህም በተጨማሪ ‘ምንም ኃጢአት ያልሠራው’ ልጁ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በተገደለበት ጊዜ የተፈጸመው ከሁሉ የከፋ ግፍ ይሖዋን በእጅጉ አሳዝኖታል። (1 ጴጥሮስ 2:22፤ ኢሳይያስ 53:9) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ግፍ በሚፈጸምባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ይህ ሁኔታ በጣም ያሳስበዋል።

      6. ግፍ ሲፈጸም ስናይ ምን ሊሰማን ይችላል? ለምንስ?

      6 ይሁንና ግፍ ሲፈጸም ስናይ ወይም በራሳችን ላይ በደል ሲደርስብን መበሳጨታችን ወይም ማዘናችን ያለ ነገር ነው። የተፈጠርነው በአምላክ አምሳል ሲሆን ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ደግሞ ከይሖዋ ባሕርይ ጋር ጨርሶ አይሄድም። (ዘፍጥረት 1:27) ታዲያ ይሖዋ ፍትሕ ሲጓደል እያየ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው?

      ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥያቄ

      7. በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የተሰነዘረውና በአገዛዙ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ የተነሳው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

      7 አምላክ የፍትሕ መጓደል እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት፣ ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው አንድ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው ፈጣሪ ምድርንም ሆነ በእሷ ላይ የሚኖሩትን ሁሉ የመግዛት መብት አለው። (መዝሙር 24:1፤ ራእይ 4:11) ይሁን እንጂ በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የተሰነዘረ ከመሆኑም ሌላ በአገዛዙ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው ሰው አዳም መኖሪያው በሆነችው ገነት ውስጥ ከነበረ አንድ ዛፍ እንዳይበላ አምላክ አዝዞት ነበር። ይህን ትእዛዝ ጥሶ ፍሬውን ቢበላስ? አምላክ “በእርግጥ ትሞታለህ” ሲል አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አምላክ ለአዳምም ሆነ ለሚስቱ ለሔዋን የሰጠው ትእዛዝ ከባድ አልነበረም። ሆኖም ሰይጣን፣ አምላክ ፍሬውን እንዳይበሉ የከለከላቸው አላግባብ እንደሆነ ሔዋንን አሳመናት። ከፍሬው ብትበላስ? ሰይጣን እንዲህ በማለት ዓይን ያወጣ ውሸት ነገራት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።”—ዘፍጥረት 3:1-5

      8. (ሀ) ሰይጣን ለሔዋን የነገራት ነገር ምን መልእክት ያዘለ ነው? (ለ) ሰይጣን ከአምላክ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያነሳው ምን ላይ ነው?

      8 ሰይጣን እንዲህ ብሎ ሲናገር ይሖዋ ሔዋንን የደበቃት ትልቅ ቁም ነገር እንዳለ ብቻ ሳይሆን እንደዋሻትም መናገሩ ነበር። ይሖዋ በሚለው ስም የሚጠራውን አምላክ መልካምነት እንድትጠራጠር አደረጋት። ሰይጣን በዚህ መንገድ በአምላክ ስም ላይ ከባድ ነቀፋ ሰነዘረ። ከዚህም ሌላ በይሖዋ ሉዓላዊነት ማለትም በሚገዛበት መንገድ ላይ ጥያቄ አስነሳ። ሰይጣን ጥያቄ ያነሳው ‘አምላክ ሉዓላዊ ነው ወይስ አይደለም?’ በሚለው ሐቅ ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያነሳው ጥያቄ ‘አምላክ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑ ተገቢ ነው? አገዛዙስ ትክክለኛ ነው?’ የሚል ነው። በሌላ አነጋገር ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነቱን በአግባቡ ወይም ለተገዢዎቹ በሚበጅ መንገድ አልተጠቀመበትም ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።

      9. (ሀ) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመፃቸው ምን አስከተለባቸው? ሰይጣን የተናገረው ውሸት ምን ወሳኝ ጥያቄዎች አስነስቷል? (ለ) ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

      9 አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ በመብላት በአምላክ ላይ ዓመፁ። በዚህም ምክንያት አምላክ አስቀድሞ በደነገገው መሠረት ሞት ተበየነባቸው። ሰይጣን የተናገረው ውሸት መልስ የሚያሻቸው ወሳኝ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ይሖዋ የሰውን ልጅ የመግዛት መብት አለው ወይስ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው? ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነቱን የሚጠቀመው ለሌሎች በሚበጅ መንገድ ነው? ይሖዋ ሁሉን ማድረግ የሚያስችለውን ኃይሉን ተጠቅሞ እነዚህን ዓመፀኞች ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ሆኖም ጥያቄ የተነሳው በአምላክ ኃይል ላይ ሳይሆን በስሙ ማለትም በአገዛዙ ላይ ነው። ስለዚህ አዳምን፣ ሔዋንንና ሰይጣንን ወዲያውኑ ማጥፋት የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ አይሆንም። እንዲያውም እንዲህ ያለው እርምጃ የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት ይበልጥ አጠያያቂ ሊያደርግ ይችል ነበር። የሰው ልጆች ያለአምላክ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት የግድ ጊዜ መስጠት ያስፈልግ ነበር።

      10. ታሪክ የሰውን ልጅ አገዛዝ በተመለከተ ምን ሐቅ አረጋግጧል?

      10 ታዲያ ያለፈው የሰው ልጅ ታሪክ ምን ሐቅ አረጋግጧል? ባለፉት ሺህ ዓመታት ሰዎች አምባገነናዊም ሆኑ ዲሞክራሲያዊ አገዛዞችን እንዲሁም የሶሻሊዝምና የኮሚኒዝም ሥርዓትን ጨምሮ ብዙ ዓይነት መስተዳድሮችን ሞክረዋል። “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ለመግዛት ያደረገው ሙከራ ያስከተለውን ውጤት ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ። (መክብብ 8:9) ነቢዩ ኤርምያስ “ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” ሲል መናገሩ ትክክል ነው።—ኤርምያስ 10:23

      11. ይሖዋ የሰው ዘር መከራ እንዲደርስበት የፈቀደው ለምንድን ነው?

      11 ይሖዋ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ብዙ ሥቃይና መከራ እንደሚያስከትል መጀመሪያውኑም ያውቅ ነበር። ታዲያ ይህ እንደሚሆን እያወቀ የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀዱ ኢፍትሐዊ አይሆንም? በፍጹም! ለምሳሌ ያህል፣ ልጅህ በጣም በመታመሙ ሕይወቱ እንዲተርፍ የግድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልገዋል እንበል። ቀዶ ሕክምናው ልጅህን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደሚያሠቃየው ስለምታውቅ ሁኔታው በጣም እንደሚያስጨንቅህ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሕክምናው ልጅህን ከበሽታው እንደሚገላግለውና በቀሪው ሕይወቱ ጤናማ ሆኖ እንዲኖር እንደሚረዳውም ታውቃለህ። በተመሳሳይም አምላክ ሰብዓዊ አገዛዝ ሥቃይና መከራ እንደሚያስከትል ያውቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:16-19) ሆኖም ዘላቂና አስተማማኝ እፎይታ እንዲገኝ ከተፈለገ የሰው ልጆች በሙሉ ዓመፅ የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት እንዲመለከቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያውቅ ነበር። በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ ለዘለቄታው ወይም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ ሊያገኝ የሚችለው በዚህ መንገድ ነው።

      የሰውን ልጅ ታማኝነት በተመለከተ የተነሳ ጥያቄ

      12. በኢዮብ ሁኔታ እንደታየው ሰይጣን የሰው ልጆችን ምን ብሎ ከስሷል?

      12 ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳ አንድ ሌላ ጥያቄም አለ። ሰይጣን የአምላክ አገዛዝ ትክክለኛና ጻድቅ ስለመሆኑ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት የይሖዋን ስም ከማጥፋቱም በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች ለፈጣሪያቸው ያላቸው ታማኝነት አጠያያቂ እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ የእነሱንም ስም አጥፍቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን ጻድቁን ሰው ኢዮብን አስመልክቶ ለይሖዋ ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ በል፦ “እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፤ ከብቱም በምድሪቱ ላይ በዝቷል። ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”—ኢዮብ 1:10, 11

      13. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያቀረበው ክስ ምን መልእክት ያዘለ ነው? ይህ ክስ ሁሉንም የሰው ዘር የሚመለከት ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

      13 እንደ ሰይጣን አባባል ከሆነ ኢዮብ ለአምላክ ያደረ ሰው ሊሆን የቻለው ይሖዋ ጥበቃ ስላደረገለትና ስለተንከባከበው ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ የሆነው በፍቅር ተነሳስቶ ሳይሆን በጥቅም ተደልሎ ነው። በመሆኑም ሰይጣን፣ ‘አምላክ በረከቱን ቢነፍገው ኢዮብ ፈጣሪውን ይሰድባል’ ሲል ተከራክሯል። ሰይጣን፣ ኢዮብ “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” እንደነበረና በዚህ ረገድ ጎልቶ የሚታይ ግሩም ምሳሌ እንደሆነ ያውቅ ነበር።a ስለሆነም ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ማድረግ ቻለ ማለት የተቀረውን የሰው ዘር በተመለከተም ምን ትርጉም ሊያስተላልፍ እንደሚችል አስብ። በመሆኑም ሰይጣን ያነሳው ጥያቄ የሁሉንም የአምላክ አገልጋዮች ታማኝነት የሚመለከት ነው። እንዲያውም “[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል” በማለት ጥያቄው ኢዮብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰው ልጆችንም የሚመለከት እንደሆነ ጠቁሟል።—ኢዮብ 1:8፤ 2:4

      14. ሰይጣን በሰዎች ላይ የሰነዘረውን ክስ በተመለከተ ታሪክ ምን ይመሠክራል?

      14 እንደ ኢዮብ ያሉ ብዙ ሰዎች መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንደተገኙ ታሪክ ይመሠክራል። ይህ ደግሞ የሰይጣንን አባባል ውድቅ ያደርገዋል። እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙ ሲሆን ይህ አቋማቸው ሰይጣን ‘የሰው ልጆች መከራ ከደረሰባቸው አምላክን ከማገልገል ወደኋላ ይላሉ’ ሲል ላነሳው ክርክር አጥጋቢ መልስ አስገኝቷል። (ዕብራውያን 11:4-38) አዎን፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን ለመተው ፈቃደኞች አልሆኑም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው እንኳ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጣቸው በመተማመን ይበልጥ ወደ እሱ ተጠግተዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7-10

      15. አምላክ ቀደም ሲል የወሰዳቸውንና ወደፊት የሚወስዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች አስመልክቶ ምን ጥያቄ ሊነሳ ይችላል?

      15 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍትሕ የተገለጠው ሉዓላዊነቱንና ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸውን በተመለከተ ከተነሱት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። ይሖዋ በግለሰቦችም ሆነ በብሔራት ላይ የበየነውን ፍርድ የሚገልጹ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። በተጨማሪም ወደፊት የሚወስዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች የሚገልጹ ትንቢቶች አሉ። ይሖዋ ቀደም ሲል የወሰዳቸውም ሆኑ ወደፊት የሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ትክክለኛ ናቸው ብለን ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

      የአምላክ ፍትሕ የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?

      በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ ሲዘንብ ሎጥና ሁለት ሴቶች ልጆቹ በሰላም ዞአር ገቡ። የጨው ዓምድ የሆነችው የሎጥ ሚስት ከበስተ ጀርባ ትታያለች።

      ይሖዋ በምንም ዓይነት ‘ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አያጠፋም’

      16, 17. ሰዎች ከእውነተኛ ፍትሕ ጋር በተያያዘ ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

      16 ይሖዋ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው” መባሉ የተገባ ነው። (ዘዳግም 32:4) ማንኛችንም ብንሆን ስለ ራሳችን እንዲህ ብለን መናገር አንችልም። ምክንያቱም ስለ ማንኛውም ነገር ያለን ግንዛቤ ውስን በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር መለየት ሊሳነን ይችላል። አብርሃምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሰዶም በክፋት ድርጊቶች ተሞልታ የነበረ ቢሆንም እንኳ አብርሃም፣ ከተማዋን እንዳያጠፋት ይሖዋን ተማጽኖት ነበር። “በእርግጥ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህ?” ሲል ይሖዋን ጠይቋል። (ዘፍጥረት 18:23-33) ይሖዋ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር አያጠፋም። በሰዶም ላይ ‘እሳትና ድኝ ያዘነበው’ ጻድቁ ሎጥና ልጆቹ ሸሽተው ወደ ዞአር ከተማ ከገቡ በኋላ ነበር። (ዘፍጥረት 19:22-24) በአንጻሩ ደግሞ ዮናስ አምላክ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት በማድረጉ ‘እጅግ ተቆጥቶ’ ነበር። ዮናስ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚጠፉ ተናግሮ ስለነበር ከልብ ንስሐ ቢገቡም እንኳ መጥፋት አለባቸው የሚል አቋም ይዞ ነበር።—ዮናስ 3:10 እስከ 4:1

      17 ይሖዋ፣ ፍትሑ ክፉዎችን ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን ጻድቃንንም ለማዳን የቆመ እንደሆነ ለአብርሃም አረጋግጦለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ዮናስ፣ ይሖዋ መሐሪ አምላክ መሆኑን መገንዘብ አስፈልጎት ነበር። ክፉ ሰዎች አካሄዳቸውን ካስተካከሉ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነው። (መዝሙር 86:5) ይሖዋ ለሥልጣናቸው እንደሚሰጉ ሰብዓዊ ገዢዎች፣ ኃይሉን በማሳየት ሌሎችን ለማስፈራራት ሲል ብቻ የቅጣት እርምጃ አይወስድም፤ ወይም እንደ ደካማ ሊያስቆጥረኝ ይችላል በሚል ስሜት ርኅራኄ ከማሳየት ወደኋላ አይልም። ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው።—ኢሳይያስ 55:7፤ ሕዝቅኤል 18:23

      18. ይሖዋ በስሜት ብቻ ተገፋፍቶ እንደማይፈርድ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥቀስ።

      18 ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲሁ በስሜት የሚመራ አምላክ አይደለም። ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ ተዘፍቀው በነበረበት ጊዜ ይሖዋ “እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፤ ለፈጸምሻቸውም አስጸያፊ ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ አደርግሻለሁ። ዓይኔ አያዝንልሽም፤ ደግሞም አልራራልሽም፤ የተከተልሽው መንገድ የሚያስከትለውን ውጤት አመጣብሻለሁ” ሲል ጥብቅ አቋሙን ገልጿል። (ሕዝቅኤል 7:3, 4) በመሆኑም ሰዎች ከመጥፎ ድርጊታቸው አልታረም ሲሉ ይሖዋ ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል። ሆኖም ይሖዋ ፍርድ የሚሰጠው በቂ በሆነ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ነው። ለምሳሌ ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ ታላቅ ጩኸት በሰማ ጊዜ “ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 18:20, 21) ይሖዋ ተጨባጭ ማስረጃ ሳያገኙ ለመፍረድ እንደሚቸኩሉ ሰዎች ባለመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በእርግጥም ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ” ነው።—ዘዳግም 32:4

      በይሖዋ ፍትሕ ላይ እምነት ይኑርህ

      19. ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ የሚወስድበትን መንገድ በተመለከተ አእምሯችን ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን?

      19 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ቀደም ባሉት ዘመናት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ይሰጣል ብለን ልንጠብቅ አንችልም። በተጨማሪም ይሖዋ ወደፊት በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ በሰዎች ላይ ስለሚወስደው የፍርድ እርምጃ ዝርዝር መረጃ አናገኝም። እንዲህ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወይም ትንቢቶች ግልጽ በማይሆኑልን ጊዜ “የሚያድነኝን አምላክ በትዕግሥት እጠብቃለሁ” ሲል እንደጻፈው እንደ ነቢዩ ሚክያስ ዓይነት ታማኝነት ልናሳይ እንችላለን።—ሚክያስ 7:7

      20, 21. ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛ እርምጃ እንደሚወስድ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

      20 ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛውን እርምጃ እንደሚወስድ ልንተማመን እንችላለን። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚፈጸሙ አንዳንድ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ችላ የተባሉ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል። (ሮም 12:19) ይሖዋን በትዕግሥት የምንጠባበቅ ከሆነ “አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም!” ሲል እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ጠንካራ እምነት እንዳለን እናሳያለን።—ሮም 9:14

      21 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙ ሰዎች በሚደርስባቸው “ግፍ” እና ጭቆና እየተሠቃዩ ነው። (መክብብ 4:1) ይሁን እንጂ ይሖዋ አልተለወጠም። አሁንም ቢሆን ግፍን የሚጠላ ሲሆን በዚህ ምክንያት እየተሠቃዩ ላሉ ሰዎች ከልብ ያዝናል። ይሖዋንና ሉዓላዊነቱን በታማኝነት ከደገፍን በመንግሥቱ አማካኝነት ግፍንና ጭቆናን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7

      a ይሖዋ ኢዮብን አስመልክቶ ሲናገር “በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም” ብሏል። (ኢዮብ 1:8) ስለሆነም ኢዮብ የኖረው ዮሴፍ ከሞተ በኋላ ሆኖም ሙሴ የእስራኤል መሪ ሆኖ ከመሾሙ በፊት እንደሆነ መገመት ይቻላል። ስለዚህ በወቅቱ ንጹሕ አቋምን በመጠበቅ ረገድ እንደ ኢዮብ ያለ ሰው አልነበረም ሊባል ይችላል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዘዳግም 10:17-19 ይሖዋ እንደማያዳላ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      • ኢዮብ 34:1-12 የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥምህ ኤሊሁ የተናገራቸው ቃላት በአምላክ ፍትሕ ላይ ያለህን እምነት ሊያጠናክሩልህ የሚችሉት እንዴት ነው?

      • መዝሙር 1:1-6 ይሖዋ የጻድቃንንም ሆነ የክፉዎችን ድርጊት በሚገባ እንደሚመዝን ማወቃችን የሚያጽናናን ለምንድን ነው?

      • ሚልክያስ 2:13-16 ይሖዋ ባሎቻቸው ባልረባ ነገር በፈቷቸው ሚስቶች ላይ ስለተፈጸመው ግፍ ምን ተሰምቶት ነበር?

  • “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ሙሴ አሥርቱን ትእዛዛት የያዙ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ይዞ።

      ምዕራፍ 13

      “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው”

      1, 2. ብዙ ሰዎች ለሕግ ያላቸው አክብሮት እየቀነሰ የመጣው ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ እኛ ስለ አምላክ ሕግ ምን ሊሰማን ይችላል?

      “ሕግ ምን ቢከቱበት የማይሞላ ጉድጓድ ነው። . . . ያገኘውን ሁሉ ይውጣል።” ይህ በ1712 ከታተመ አንድ መጽሐፍ የተወሰደ አባባል ነው። የመጽሐፉ ደራሲ የፍርድ ቤት ሙግቶች ለረጅም ጊዜ እንዲጓተቱ የሚያደርገውንና ፍትሕ የሚሹ ሰዎችን ለኪሳራ የሚዳርገውን የሕግ አሠራር አውግዟል። በበርካታ አገሮች ያለው የሕግ አሠራርና የፍትሕ ሥርዓት በጣም የተወሳሰበ፣ የተዛባ፣ አድሏዊነት የሚንጸባረቅበትና ተለዋዋጭ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ለሕግ ያላቸው አክብሮት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።

      2 በአንጻሩ ደግሞ ከ2,700 ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፉትን “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!” የሚሉትን ቃላት ልብ በል። (መዝሙር 119:97) መዝሙራዊው እንዲህ ሊሰማው የቻለው ለምንድን ነው? እሱ የጠቀሰው ሕግ አንድ ሰብዓዊ መንግሥት ሳይሆን ይሖዋ አምላክ ያወጣው በመሆኑ ነው። ስለ ይሖዋ ሕግ እያወቅህ በሄድክ መጠን አንተም እንደ መዝሙራዊው ለማለት ልትገፋፋ ትችላለህ። የይሖዋን ሕግ መመርመርህ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው ሕግ አውጪ ምን አመለካከት እንዳለው እንድትገነዘብ ይረዳሃል።

      ከሁሉ የላቀው ሕግ አውጪ

      3, 4. ይሖዋ ሕግ አውጪ መሆኑን ያሳየው በምን መንገዶች ነው?

      3 መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 4:12) በእርግጥም ትክክለኛው ሕግ አውጪ ይሖዋ ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ የሰማይ አካላት እንኳ የሚንቀሳቀሱት እሱ ባወጣላቸው “ሕጎች” መሠረት ነው። (ኢዮብ 38:33) እልፍ አእላፋት የሆኑት የይሖዋ ቅዱሳን መላእክትም በተለያየ ሥልጣንና ደረጃ ተከፋፍለው ይሖዋ በሚሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት የሚያገለግሉ በመሆናቸው በመለኮታዊ ሕግ የሚመሩ ናቸው።—መዝሙር 104:4፤ ዕብራውያን 1:7, 14

      4 ይሖዋ ለሰው ልጆችም ሕግ ሰጥቷል። እያንዳንዳችን የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ሕሊና ተሰጥቶናል። ሕሊና ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር ለይተን ማወቅ እንድንችል የሚረዳ በውስጣችን የተቀመጠ ራሱን የቻለ ሕግ ነው ሊባል ይችላል። (ሮም 2:14) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ፍጹም የሆነ ሕሊና ተሰጥቷቸው ስለነበር ብዙ ሕግ አላስፈለጋቸውም። (ዘፍጥረት 2:15-17) ይሁን እንጂ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንዲችሉ ተጨማሪ ሕግ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ አምላክ እንደ ኖኅ፣ አብርሃምና ያዕቆብ ላሉት የጥንት አባቶች ሕግ የሰጣቸው ሲሆን እነሱም የተሰጣቸውን ሕግ ለቤተሰቦቻቸው አስተላልፈዋል። (ዘፍጥረት 6:22፤ 9:3-6፤ 18:19፤ 26:4, 5) በኋላም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ሕዝብ ሕግ በመስጠት ቀደም ካሉት ጊዜያት ለየት ባለ መንገድ ሕግ አውጪ መሆኑን አሳይቷል። ይህ ሕግ ስለ ይሖዋ የፍትሕ ባሕርይ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል።

      የሙሴ ሕግ ጠቅለል ያለ ገጽታ

      5. የሙሴ ሕግ አስቸጋሪና ውስብስብ የሆኑ ደንቦችን የያዘ ነው? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      5 ብዙዎች የሙሴ ሕግ አስቸጋሪና ውስብስብ የሆኑ ደንቦች የያዘ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ በአጠቃላይ ከ600 የሚበልጡ ሕግጋት ተካትተው ይገኛሉ። ይህ በጣም ብዙ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል ሕግ መጻሕፍት በድምሩ ከ150,000 በላይ ገጾች ነበሯቸው። በየሁለት ዓመቱ ደግሞ ከ600 የሚበልጡ ሕጎች ይጨመራሉ! ስለዚህ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ሰብዓዊ ሕጎች አንጻር ሲታይ የሙሴ ሕግ በጣም አነስተኛ ነው። ሆኖም አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ዛሬ ያሉት ሕጎች የማይዳስሷቸውን የሕይወት ዘርፎች ሁሉ የሚዳስስ ነው። እስቲ የሙሴን ሕግ ጠቅለል ያለ ገጽታ እንመልከት።

      6, 7. (ሀ) የሙሴን ሕግ ከሌሎች ሕጎች ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? በዚህ ሕግ ውስጥ ከሰፈሩት ሕግጋት ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የትኛው ነው? (ለ) እስራኤላውያን የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደተቀበሉ የሚያሳዩት እንዴት ነበር?

      6 ሕጉ የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚያጎላ ነበር። በመሆኑም የሙሴ ሕግ ከሌላ ከማንኛውም ሕግ የላቀ ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሰፈሩት ሕግጋት ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው “እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው። አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” የሚለው ሕግ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ለእሱ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹት እንዴት ነው? ለሉዓላዊነቱ በመገዛትና እሱን በማገልገል ነው።—ዘዳግም 6:4, 5፤ 11:13

      7 እያንዳንዱ እስራኤላዊ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሰዎች በመገዛት የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደተቀበለ ያሳይ ነበር። ወላጆች፣ የነገድ አለቆች፣ ፈራጆች፣ ካህናትና ንጉሡ መለኮታዊ ሥልጣንን የሚወክሉ ናቸው። ይሖዋ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚያምፁ ግለሰቦችን በእሱ ላይ እንዳመፁ አድርጎ ይመለከታቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሕዝቡን የሚጨቁኑ ወይም የሚያንገላቱ ከሆነ የይሖዋ ቁጣ ይወርድባቸዋል። (ዘፀአት 20:12፤ 22:28፤ ዘዳግም 1:16, 17፤ 17:8-20፤ 19:16, 17) በመሆኑም ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎችም ሆኑ በእነሱ ሥር ያሉት ተገዢዎች የአምላክን ሉዓላዊነት የመደገፍ ኃላፊነት ነበረባቸው።

      8. ሕጉ ለይሖዋ ቅድስና የቆመ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

      8 ሕጉ ለይሖዋ ቅድስና የቆመ ነበር። “ቅዱስ” እና “ቅድስና” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት በሙሴ ሕግ ውስጥ ከ280 ጊዜ በላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። ሕጉ አንድን እስራኤላዊ ሊያረክሱ የሚችሉ ወደ 70 የሚጠጉ የተለያዩ ነገሮችን በመዘርዘር የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕና ርኩስ የሆነውን ነገር እንዲለዩ ረድቷቸዋል። ሕጉ አካላዊ ንጽሕናን፣ አመጋገብን አልፎ ተርፎም ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድን የሚመለከቱ ደንቦችን የያዘ ነበር። እንዲህ ያሉት ደንቦች ለጤንነት እጅግ ጠቃሚ ናቸው።a ይሁን እንጂ እነዚህ ደንቦች የተሰጡበት ዋና ዓላማ ሕዝቡ፣ በአካባቢው ያሉት ወራዳ ሥነ ምግባር ያላቸው ብሔራት ከሚፈጽሟቸው መጥፎ ድርጊቶች በመራቅ የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኝ ማድረግ ነበር። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

      9, 10. የሕጉ ቃል ኪዳን የፆታ ግንኙነትንና ልጅ መውለድን በተመለከተ ምን ደንቦችን ይዟል? እነዚህ ደንቦችስ ምን ጥቅሞች አስገኝተዋል?

      9 በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱት ደንቦች በተጋቡ ሰዎች መካከልም እንኳ የሚደረግ የፆታ ግንኙነት ለተወሰነ ጊዜ እንደሚያረክስ ይገልጻሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ አንዲት ሴት ልጅ በምትወልድበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ ትረክሳለች። (ዘሌዋውያን 12:2-4፤ 15:16-18) እንዲህ ያሉት ደንቦች እነዚህን ንጹሕ የሆኑ የአምላክ ስጦታዎች የሚያንቋሽሹ አይደሉም። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:18-25) ከዚህ ይልቅ እነዚህ ደንቦች ሕዝቡን ከብክለት በመጠበቅ የይሖዋ ቅድስና ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው የሚያደርጉ ናቸው። የእስራኤላውያን አጎራባች ብሔራት፣ የፆታ ግንኙነትና የመራባት ሥርዓት የአምልኳቸው ክፍል የነበረ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የከነአናውያን የአምልኮ ሥርዓት የወንድና የሴት ዝሙት አዳሪነትንም የሚያካትት ነበር። በዚህም ሳቢያ እጅግ ወራዳ የሆኑ ድርጊቶችና ልማዶች ተስፋፍተው ነበር። በአንጻሩ ግን የሙሴ ሕግ የይሖዋ አምልኮ ከማንኛውም የፆታ ርኩሰት ሙሉ በሙሉ የጠራ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።b ይሁንና ሌሎች ጥቅሞችም ነበሩት።

      10 እነዚህ ሕጎች አንድ የሚያስተምሩት እውነታም አለ።c ለመሆኑ የአዳም ኃጢአት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የሚተላለፈው እንዴት ነው? በፆታ ግንኙነትና በመዋለድ አይደለም? (ሮም 5:12) አዎን፣ ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ኃጢአት ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የሚኖር ነገር እንደሆነ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። እንዲያውም ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ነን። (መዝሙር 51:5) በመሆኑም ቅዱስ ወደሆነው አምላካችን ለመቅረብ ምሕረት ማግኘትና ከኃጢአታችን መቤዠት ያስፈልገናል።

      11, 12. (ሀ) ሕጉ ምን ዓይነት ፍርድ እንዲሰጥ ያዝዝ ነበር? (ለ) ሕጉ ፍትሕ እንዳይዛባ ይከላከል የነበረው እንዴት ነው?

      11 ሕጉ ፍጹም የሆነውን የይሖዋን ፍትሕ የሚያንጸባርቅ ነበር። የሙሴ ሕግ ከፍትሕ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተመጣጣኝና ሚዛናዊ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ያደርግ ነበር። በመሆኑም ሕጉ “ሕይወት ስለ ሕይወት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ እንዲሁም እግር ስለ እግር ይሁን” ሲል ይገልጻል። (ዘዳግም 19:21) ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ የሚበየነው ቅጣት ከወንጀሉ ጋር የሚመጣጠን መሆን ነበረበት። ይህ መለኮታዊ ፍትሕ በሕጉ ላይ ጎልቶ የተንጸባረቀ ከመሆኑም በላይ በምዕራፍ 14 ላይ እንደምንመለከተው የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት በተመለከተ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት እንድንችል ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6

      12 ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ ፍትሕ እንዳይዛባ ይከላከላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክስ ተቀባይነት እንዲኖረው ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች ያስፈልጉ ነበር። በሐሰት መመሥከር ከፍተኛ ቅጣት ያስከትል ነበር። (ዘዳግም 19:15, 18, 19) በተጨማሪም ሙስናና ጉቦ በእጅጉ የተወገዙ ድርጊቶች ነበሩ። (ዘፀአት 23:8፤ ዘዳግም 27:25) የአምላክ ሕዝቦች በንግድ ጉዳዮችም እንኳ ሳይቀር የይሖዋን የፍትሕ መሥፈርት መጠበቅ ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 19:35, 36፤ ዘዳግም 23:19, 20) ይህ የላቀና ፍትሐዊ የሆነ ሕግ እስራኤላውያንን በእጅጉ ጠቅሟቸዋል!

      ምሕረት የተንጸባረቀባቸውና ከአድልዎ ነፃ የሆኑ ሕጎች

      13, 14. ሕጉ ለሌባም ሆነ ንብረቱ ለተሰረቀበት ሰው ፍትሐዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

      13 የሙሴ ሕግ ድርቅ ያሉ ምሕረት የለሽ ደንቦችን የያዘ ነው? በፍጹም! ንጉሥ ዳዊት በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 19:7) ሕጉ ምሕረት የተንጸባረቀበትና ምንም ዓይነት አድልዎ የማያደርግ እንደሆነ በሚገባ ያውቅ ነበር። ሕጉ ምሕረትና ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

      14 በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አገሮች ያለው ሕግ ልል ከመሆኑም ሌላ የወንጀል ተጠቂ ከሆኑት ሰዎች ይልቅ ወንጀለኞቹን የሚጠቅም ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሌቦች ሊታሰሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የወንጀሉ ተጠቂዎች የተዘረፈባቸው ንብረት ላይመለስላቸው ይችላል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለመንግሥት የሚከፍሉት ግብር እነዚህን ወንጀለኞች ለመቀለብ ይውላል። በጥንት እስራኤል እንደ አሁኑ እስር ቤቶች አልነበሩም። ከዚህም በተጨማሪ የሚበየነው ቅጣት ጥብቅ ገደብ ነበረው። (ዘዳግም 25:1-3) አንድ ሌባ የሰረቀውን ነገር መልሶ መተካት ይጠበቅበት የነበረ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ክፍያ ይበየንበት ነበር። የክፍያው መጠን እንደ ሁኔታው ይለያያል። ፈራጆቹ የኃጢአተኛውን የንስሐ ዝንባሌ ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን በመመዘን መፍረድ ይጠበቅባቸው ነበር። በዘሌዋውያን 6:1-7 ላይ የተገለጸው ካሳ በዘፀአት 22:7 ላይ ከተጠቀሰው ካሳ ያነሰ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።

      15. በሙሴ ሕግ መሠረት ሳያውቅ ሕይወት ያጠፋ ሰው ምሕረት የሚያገኘውና ፍትሐዊ ውሳኔ የሚበየንበት እንዴት ነው?

      15 ሕጉ ባለማወቅ ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች ምሕረት የሚያገኙበትንም ሁኔታ አመቻችቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሳያውቅ ሕይወት በሚያጠፋበት ጊዜ በቅርብ ወዳለ መማጸኛ ከተማ በመሸሽ ተገቢውን እርምጃ ከወሰደ ሕይወት ስለ ሕይወት መክፈል አይጠበቅበትም። ብቃት ያላቸው ፈራጆች ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ ግለሰቡ ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማው ውስጥ ይቆያል። ከዚያ በኋላ ወደፈለገው ቦታ ሄዶ መኖር ይችላል። በዚህ መንገድ አምላክ ባደረገው የምሕረት ዝግጅት መጠቀም ይችላል። ይህ ሕግ እግረ መንገዱንም የሰው ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ የሚጠቁም ነው።—ዘኁልቁ 15:30, 31፤ 35:12-25

      16. ሕጉ አንዳንድ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስከብረው እንዴት ነው?

      16 ሕጉ ሰብዓዊ መብቶችንም የሚያስከብር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ለተበደሩ ሰዎች እንዴት ከለላ እንደሚሆን ተመልከት። ሕጉ ተበዳሪው ቤት ውስጥ ገብቶ መያዣ መውሰድን ይከለክላል። ከዚህ ይልቅ አበዳሪው ውጭ ቆሞ ተበዳሪው ለመያዣነት የሚሰጠውን ዕቃ እስኪያመጣለት መጠበቅ ይኖርበታል። ይህም የግለሰቡ ቤት እንዳይደፈር ይረዳል። አበዳሪው የተበዳሪውን ልብስ በመያዣነት ወስዶ ከነበረ ተበዳሪው ሌሊት ለብሶት የሚተኛው ልብስ ሊሆን ስለሚችል አመሻሹ ላይ ሊመልስለት ይገባ ነበር።—ዘዳግም 24:10-14

      17, 18. እስራኤላውያን ከጦርነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከሌሎች ብሔራት የተለዩ የነበሩት እንዴት ነው? ለምንስ?

      17 በሕጉ ውስጥ ጦርነትን የሚመለከቱ ደንቦችም እንኳ ሳይቀሩ ተካትተዋል። የአምላክ ሕዝቦች ከሌሎች ብሔራት ጋር ይዋጉ ነበር። ይህን ያደርጉ የነበረው ግን ‘በይሖዋ ጦርነት’ የአምላክ ወኪሎች ሆነው ለማገልገል እንጂ የበላይ ወይም ኃያል መሆናቸውን ለማስመሥከር ብለው አልነበረም። (ዘኁልቁ 21:14) ብዙውን ጊዜ እስራኤላውያን በቅድሚያ ጠላቶቻቸው በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ይጠይቁ ነበር። አንዲት ከተማ ይህን ግብዣ ለመቀበል አሻፈረኝ በምትልበት ጊዜ እስራኤላውያን አምላክ የሰጣቸውን መመሪያ በመከተል ከተማዋን ይከብቡ ነበር። በታሪክ ዘመናት እንደታዩት እንደ ብዙዎቹ ወታደሮች የእስራኤል ሠራዊት አባላት ሴቶችን አስገድደው አይደፍሩም ወይም ያገኙትን ሰው ሁሉ በጅምላ አይጨፈጭፉም። ሌላው ቀርቶ ሕጉ ጠላቶቻቸው የተከሏቸውን የፍራፍሬ ዛፎች በመጨፍጨፍ በአካባቢው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ይከለክል ነበር።d የሌሎች ብሔራት ሠራዊት ግን እንዲህ እንዳያደርጉ የሚከለክል ሕግ አልነበራቸውም።—ዘዳግም 20:10-15, 19, 20፤ 21:10-13

      18 በአንዳንድ አገሮች ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ለውትድርና እንደሚሠለጥኑ ስትሰማ አይዘገንንህም? በጥንት እስራኤል ከ20 ዓመት በታች የሆነ ማንም ሰው ለውትድርና አይመለመልም ነበር። (ዘኁልቁ 1:2, 3) ሌላው ቀርቶ ትልቅ ሰውም እንኳ ቢሆን በጣም የሚፈራ ከሆነ ከወታደራዊ ግዳጅ ነፃ ይሆን ነበር። አዲስ ሙሽራ የሆነ ሰው ደግሞ ሕይወትን ሊያሳጣ በሚችለው የውትድርና አገልግሎት ከመሰማራቱ በፊት ወራሽ የሚሆን ልጅ ወልዶ መሳም እንዲችል ለአንድ ዓመት ከግዳጅ ነፃ ይሆን ነበር። በዚህ መንገድ አዲሱ ሙሽራ ‘በቤቱ ተቀምጦ ሚስቱን ሊያስደስታት’ እንደሚችል ሕጉ ይገልጻል።—ዘዳግም 20:5, 6, 8፤ 24:5

      19. ሕጉ ለሴቶች፣ ለልጆች፣ ለቤተሰቦች፣ ለመበለቶችና ወላጅ ለሌላቸው ልጆች ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት ነበር?

      19 በተጨማሪም ሕጉ ሴቶች፣ ልጆችና ቤተሰቦች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚረዱ ደንቦችን ያካተተ ነበር። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ዘወትር ጊዜ እንዲያሳልፉና መንፈሳዊ ነገሮችን እንዲያስተምሯቸው ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸምን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽሞ የሚከለክል ሲሆን እንዲህ የሚያደርግ ሰው በሞት ይቀጣ ነበር። (ዘሌዋውያን ምዕራፍ 18) ከዚህም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ የቤተሰብን አንድነትና ሰላማዊ ሕይወት የሚያናጋውንና ክብር የሚያሳጣውን ምንዝርን ያወግዛል። ሕጉ ለመበለቶችና ወላጅ ለሌላቸው ልጆች ጥበቃ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በደል እንዳይፈጸምባቸው አጥብቆ ያስጠነቅቃል።—ዘፀአት 20:14፤ 22:22-24

      20, 21. (ሀ) የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን ከአንድ በላይ እንዳያገቡ ያልከለከለው ለምንድን ነው? (ለ) ፍቺን በተመለከተ በሕጉ ላይ የሰፈረው ደንብ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ካስተማረው ሥርዓት የሚለየው ለምንድን ነው?

      20 ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንዶች ‘ሕጉ ከአንድ በላይ ማግባት የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። (ዘዳግም 21:15-17) እንዲህ ያሉትን ሕጎች በዚያ ዘመን ከነበረው ሁኔታ አንጻር መመርመር ይኖርብናል። የሙሴን ሕግ በአሁኑ ጊዜ ካለው ሁኔታና ልማድ አንጻር የሚመለከቱ ሰዎች ሕጉን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። (ምሳሌ 18:13) ይሖዋ በኤደን ያቋቋመው ሥርዓት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለዘላለም በጋብቻ ተሳስረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18, 20-24) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤላውያን በሰጠበት ወቅት ከአንድ በላይ ማግባት ለበርካታ መቶ ዘመናት የቆየ ልማድ ሆኖ ነበር። ይሖዋ “ግትር” የሆኑት ሕዝቦቹ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ የሚያዘውን ሕግ ጨምሮ በጣም መሠረታዊ የሆኑትን ትእዛዛት እንኳ ሳይቀር በተደጋጋሚ ጊዜያት እንደሚጥሱ በሚገባ ያውቃል። (ዘፀአት 32:9) በመሆኑም ይሖዋ በዚያ ወቅት የጋብቻ ልማዳቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲለውጡ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አልታየውም። ያም ሆነ ይህ ከአንድ በላይ ማግባት ይሖዋ ያቋቋመው ሥርዓት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይሁንና ይሖዋ ይህን ልማድ አላግባብ እንዳይጠቀሙበት ለማድረግ በሙሴ ሕግ አማካኝነት አንዳንድ ገደቦችን አበጅቷል።

      21 በተጨማሪም የሙሴ ሕግ አንድ ሰው ሚስቱን ሊፈታ የሚችልባቸውን የተለያዩ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ይጠቅሳል። (ዘዳግም 24:1-4) አምላክ ለአይሁድ ሕዝብ ይህን የፈቀደው “[የልባቸውን] ደንዳናነት አይቶ” እንደሆነ ኢየሱስ ገልጿል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የፈቀደው ለጊዜው ብቻ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹ ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ያወጣውን የጋብቻ ሥርዓት እንዲከተሉ አስተምሯል።—ማቴዎስ 19:8

      ሕጉ ፍቅር እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ነበር

      22. የሙሴ ሕግ ፍቅር ማሳየትን የሚያበረታታው በምን መንገዶች ነው? ለእነማንስ?

      22 በዛሬው ጊዜ ሰዎች ፍቅር እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ሕግ ይኖራል ብለህ ታስባለህ? የሙሴ ሕግ ለፍቅር የላቀ ቦታ የሚሰጥ ነበር። እንዲያውም በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ብቻ እንኳ “ፍቅር” የሚለው ቃል በተለያየ መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ከሰፈሩት ታላላቅ ትእዛዛት ሁለተኛውን ደረጃ የያዘ ነው። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ማቴዎስ 22:37-40) የአምላክ ሕዝቦች የራሳቸው ወገን ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ለሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎችም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማሳየት ነበረባቸው፤ በአንድ ወቅት እነሱም የባዕድ አገር ሰው እንደነበሩ እንዲያስታውሱ ተነግሯቸዋል። ድሆችንና የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች በቁሳዊ ነገር በመርዳት እንዲሁም በእነዚህ ሰዎች ላይ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከመፈጸም በመታቀብ ለእነሱ ያላቸውን ፍቅር ማሳየት ነበረባቸው። ሌላው ቀርቶ ለእንስሳት እንኳ ደግነትና አሳቢነት ማሳየት ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘፀአት 23:6፤ ዘሌዋውያን 19:14, 33, 34፤ ዘዳግም 22:4, 10፤ 24:17, 18

      23. የመዝሙር 119 ጸሐፊ ምን ለማድረግ ተገፋፍቷል? እኛስ ምን ለማድረግ መነሳሳት ይኖርብናል?

      23 እንዲህ ያለ አስደናቂ ሕግ የተሰጠው ሌላ ሕዝብ አለ? መዝሙራዊው “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!” ሲል መጻፉ ምንም አያስደንቅም! ይሁን እንጂ መዝሙራዊው እንዲሁ በማድነቅ ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ይህን ሕግ ከልብ ለመታዘዝና በሕይወቱ ተግባራዊ ለማድረግ ጥሯል። “ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል። (መዝሙር 119:11, 97) አዎን፣ የይሖዋን ሕግ ዘወትር ያጠና ነበር። ይህም ለሕጉ ያለው ፍቅር ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ እንዲሄድ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ሕግ ላወጣው ለይሖዋ አምላክ ያለው ፍቅርም የዚያኑ ያህል ጨምሯል። አንተም መለኮታዊውን ሕግ በመመርመር የፍትሕ አምላክና ከሁሉ የላቀ ሕግ አውጪ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ምኞታችን ነው።

      a ለምሳሌ ያህል እዳሪ እንዲቀበር፣ የታመመ ሰው እስኪድን ድረስ ከሌሎች ሰዎች ተገልሎ እንዲቀመጥና አስከሬን የነካ ሰው እንዲታጠብ የሚያዙት ሕጎች በዘመኑ ከነበረው አስተሳሰብ እጅግ የመጠቁ ነበሩ።—ዘሌዋውያን 13:4-8፤ ዘኁልቁ 19:11-13, 17-19፤ ዘዳግም 23:13, 14

      b የከነአናውያን ቤተ መቅደሶች የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም የሚያገለግሉ ክፍሎች የነበሯቸው ሲሆን በሙሴ ሕግ ግን የረከሱ ሰዎች ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት እንኳ አይፈቀድላቸውም ነበር። የፆታ ግንኙነት በራሱ ለተወሰነ ጊዜ የሚያረክስ ስለሆነ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት ክፍል ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው።

      c ሕጉ የተሰጠበት ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ሕዝብ ለማስተማር ነበር። እንዲያውም ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ “ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው ቶራህ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ትምህርት” ማለት እንደሆነ ይገልጻል።

      d ሕጉ “ሰው ይመስል የሜዳን ዛፍ ከበህ ማጥፋት አለብህ?” ሲል በግልጽ ይጠይቃል። (ዘዳግም 20:19) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው አይሁዳዊው ምሁር ፊሎ ይህን ሕግ በመጥቀስ አምላክ “ሰዎች በጠላቶቻቸው ሳቢያ ያደረባቸውን ቁጣ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ነገሮች ላይ መወጣታቸው አግባብ አይደለም” የሚል አመለካከት እንዳለው ገልጿል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 24:19 እንዲህ ያሉ ሕጎችን ስለሚያወጣው አምላክ ምን ይሰማሃል?

      • መዝሙር 19:7-14 ዳዊት ስለ “ይሖዋ ሕግ” ምን ተሰምቶታል? እኛስ የአምላክን ሕጎች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

      • ሚክያስ 6:6-8 ይህ ጥቅስ የይሖዋን ሕጎች እንደ ሸክም አድርጎ መመልከት ተገቢ እንዳልሆነ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?

      • ማቴዎስ 23:23-39 ፈሪሳውያን የሕጉ መንፈስ እንዳልገባቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ይህስ ለእኛ ትልቅ ትምህርት የሚሆነን እንዴት ነው?

  • ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ኢየሱስ ሚዛን አጠገብ ቆሞ።

      ምዕራፍ 14

      ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ

      1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ያሉበትን ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው? ብቸኛው መፍትሔስ ምንድን ነው?

      “ፍጥረት ሁሉ . . . አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ [ይገኛል]።” (ሮም 8:22) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጆች የሚገኙበትን አሳዛኝ ሁኔታ በዚህ መንገድ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ሥቃይ፣ ኃጢአትና ሞት ምንም ዓይነት መፍትሔ የሌላቸው ነገሮች ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደ ሰዎች አቅሙ ውስን አይደለም። (ዘኁልቁ 23:19) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ ከሥቃይና ከመከራ ለመገላገል የሚያስችለንን ቤዛ አዘጋጅቶልናል።

      2 ቤዛው ይሖዋ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው። ከኃጢአትና ከሞት ባርነት መላቀቅ የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ኤፌሶን 1:7) በሰማይም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው በቤዛው ዝግጅት ላይ ነው። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጴጥሮስ 1:4) ለመሆኑ ቤዛው ምንድን ነው? ወደር የለሽ ስለሆነው የይሖዋ ፍትሕስ ምን ያስተምረናል?

      ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

      3. (ሀ) ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ በአዳም ዘሮች ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ እንዲሁ መሰረዝ የማይችለው ለምንድን ነው?

      3 ቤዛ ያስፈለገው አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነው። አዳም በአምላክ ላይ በማመፁ ለዘሮቹ በሽታን፣ ሐዘንን፣ ሥቃይንና ሞትን አውርሷል። (ዘፍጥረት 2:17፤ ሮም 8:20) አምላክ ለእኛ በማዘን የሞት ፍርዱን እንዲሁ መሰረዝ አይችልም። እንዲህ ቢያደርግ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” የሚለውን ራሱ ያወጣውን ሕግ ችላ እንዳለ ያስቆጥርበታል። (ሮም 6:23) በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ መንገድ ፍትሐዊ ሕጎቹን የሚሽር ቢሆን ኖሮ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሥርዓት አልበኝነትና ሕገ ወጥነት ይነግሥ ነበር!

      4, 5. (ሀ) ሰይጣን የአምላክን ስም ያጠፋው እንዴት ነው? ይሖዋ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት የተሰማውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች በተመለከተ ምን ክስ አቅርቧል?

      4 ምዕራፍ 12 ላይ እንደተመለከትነው በኤደን የተፈጸመው ዓመፅ ትላልቅ ጥያቄዎችንም አስነስቷል። ሰይጣን የአምላክን መልካም ስም አጉድፏል። ይሖዋ ውሸታም እንደሆነና ፍጥረታቱን ነፃነት የሚነፍግ ጨካኝና አምባገነን ገዢ እንደሆነ አድርጎ ከሶታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) በተጨማሪም ሰይጣን፣ ይሖዋ ምድርን ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ለመሙላት ያለው ዓላማ የተሰናከለ እንዲመስል በማድረግ ያሰበውን ማሳካት የማይችል አምላክ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። (ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ባይፈቅድ ኖሮ የማሰብ ችሎታ ያላቸው አብዛኞቹ ፍጥረታቱ በእሱ አገዛዝ ላይ ያላቸውን አመኔታ ሊያጡ ይችሉ ነበር።

      5 ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ እንደሆነና ችግር ቢደርስባቸው ሁሉም አምላክን እንደሚክዱ በመግለጽ ስማቸውን አጥፍቷል። (ኢዮብ 1:9-11) አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው እነዚህ የላቀ ግምት የሚሰጣቸው አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ሲል ነው። ይሖዋ፣ ሰይጣን ያቀረባቸው የሐሰት ክሶች መልስ እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት ተሰምቶታል። ይሁን እንጂ አምላክ እነዚሁ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙና የሰው ልጆች እንዲድኑ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

      ቤዛ ምንድን ነው?

      6. አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ያደረገው ዝግጅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምን የተለያዩ መንገዶች ተገልጿል?

      6 ይሖዋ ያቀረበው መፍትሔ ታላቅ ምሕረትና ፍጹም የሆነ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነው። ሰዎች መቼም ቢሆን እንዲህ ያለ ግሩም መፍትሔ ሊያመጡ አይችሉም። ይሁንና ይሖዋ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ የተጠቀመበት ዝግጅት በሚያስደንቅ ሁኔታ በጣም ቀላል ነው። ይህ ዝግጅት መዋጀት፣ ማስታረቅና ማስተሰረይ ተብሎ በተለያየ መንገድ ተገልጿል። (ዳንኤል 9:24፤ ገላትያ 3:13፤ ቆላስይስ 1:19, 20) ይሁን እንጂ ይህን ዝግጅት በተሻለ መንገድ የሚገልጸው ኢየሱስ ራሱ የተጠቀመበት ቃል ነው። “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ [በግሪክኛ ሊትሮን] አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 20:28

      7, 8. (ሀ) “ቤዛ” የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ቤዛ የሚለው ቃል ተመጣጣኝ የሆነን ነገር የሚያመለክተው በምን መንገድ ነው?

      7 ቤዛ ምንድን ነው? ቤዛን ለመግለጽ የገባው የግሪክኛ ግስ “መፍታት፣ መልቀቅ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል የጦር እስረኞችን ለማስለቀቅ የሚከፈልን ገንዘብ ለማመልከት ይሠራበት ነበር። እንግዲያው ቤዛ፣ አንድን ነገር መልሶ ለማግኘት የሚከፈል ዋጋ እንደሆነ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ቤዛ” (ኮፌር) የሚለው ቃል “መሸፈን” የሚል ትርጉም ካለው ግስ የመጣ ነው። ይህም መቤዠት የሚለው ቃል ኃጢአትን መሸፈን የሚል ትርጉም እንዳለውም እንድንገነዘብ ይረዳናል።

      8 ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይህ ቃል (ኮፌር) “ምንጊዜም ተመጣጣኝ የሆነን ነገር እንደሚያመለክት” ይገልጻል። በመሆኑም ኃጢአትን ለመቤዠት ወይም ለመሸፈን የሚከፈለው ዋጋ በኃጢአቱ ሳቢያ የጠፋውን ነገር ሙሉ በሙሉ የሚያካክስ ወይም የሚሸፍን መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ “ሕይወት ስለ ሕይወት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ እንዲሁም እግር ስለ እግር ይሁን” ሲል ይገልጻል።—ዘዳግም 19:21

      9. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የእንስሳት መሥዋዕቶች ያቀርቡ የነበረው ለምንድን ነው? ይሖዋስ ለእነዚህ መሥዋዕቶች ምን አመለካከት ነበረው?

      9 ከአቤል አንስቶ በምድር ላይ የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ይህን ማድረጋቸው ኃጢአት እንዳለባቸውና መቤዠት እንደሚያስፈልጋቸው እንደተገነዘቡ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ አምላክ ‘በዘሩ’ አማካኝነት ነፃ ለማውጣት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያመለክት ነው። (ዘፍጥረት 3:15፤ 4:1-4፤ ዘሌዋውያን 17:11፤ ዕብራውያን 11:4) ይሖዋ እንዲህ ያሉትን መሥዋዕቶች የተቀበለ ሲሆን እነዚህን ሰዎች አገልጋዮቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች ያቀርቧቸው የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ውስጣዊ ስሜታቸውን ለመግለጽ ያህል ብቻ የሚያገለግሉ ነበሩ። እንስሳት ከሰዎች ያነሱ በመሆናቸው የሰውን ኃጢአት ሊሸፍኑ አይችሉም። (መዝሙር 8:4-8) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም” ይላል። (ዕብራውያን 10:1-4) እንዲህ ያሉት መሥዋዕቶች ለእውነተኛው ቤዛዊ መሥዋዕት እንደ ምሳሌ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ።

      “ተመጣጣኝ ቤዛ”

      10. (ሀ) ቤዛው ከማን ጋር የሚመጣጠን መሆን አለበት? ለምንስ? (ለ) አንድ ሰው ብቻ መሥዋዕት መሆኑ በቂ የሚሆነው ለምንድን ነው?

      10 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ” ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) በመሆኑም የቤዛው ክፍያ፣ ፍጹም ሰው ከነበረው ከአዳም ጋር የሚመጣጠን ሕይወት ነው። (ሮም 5:14) ታዲያ ይህን የፍትሕ መሥፈርት ሊያሟላ የሚችለው ማን ነው? አዳም ባጠፋው ፍጹም ሕይወት ምትክ “ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊሆን የሚችለው በአዳም ላይ ከተበየነው የሞት ፍርድ ነፃ የሆነ ፍጹም ሰው ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) ለእያንዳንዱ የአዳም ዘር ተመጣጣኝ የሆነ ቤዛ ለመክፈል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መሥዋዕት መሆን አያስፈልጋቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ” ሲል ገልጿል። (ሮም 5:12) “ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ” አምላክ “በአንድ ሰው በኩል” የሰውን ዘር ለመቤዠት ዝግጅት አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 15:21) እንዴት?

      “ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ”

      11. (ሀ) ቤዛውን የሚከፍለው ሰው ‘ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን የሚቀምሰው’ እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን ከቤዛው ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይችሉት ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

      11 ይሖዋ አንድ ፍጹም ሰው በፈቃደኝነት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ዝግጅት አደረገ። ሮም 6:23 እንደሚገልጸው “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው።” ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ሰው “ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን [ይቀምሳል]።” በሌላ አነጋገር ለአዳም ኃጢአት ደሞዝ ይከፍላል። (ዕብራውያን 2:9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:24) ይህ ከሕግ አንጻር ትልቅ ትርጉም አለው። ቤዛው ታዛዥ በሆኑ የአዳም ዘሮች ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ በመሻር የኃጢአትን መዘዝ ከሥሩ ነቅሎ ያስወግዳል።a—ሮም 5:16

      12. አንድ ዕዳ መከፈሉ ለብዙ ሰዎች ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በምሳሌ አስረዳ።

      12 ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በምትኖርበት ከተማ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ነዋሪዎች በአንድ ትልቅ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው እንበል። አንተም ሆንክ ጎረቤቶችህ ይህ ፋብሪካ በሚከፍላችሁ ደሞዝ ጥሩ ኑሮ ትኖራላችሁ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ፋብሪካ ተዘጋ። ለምን? የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ በሙስና በመዘፈቁና ድርጅቱን ለኪሳራ በመዳረጉ ነው። አንተም ሆንክ አብረውህ የሚሠሩት ሰዎች በድንገት ከሥራ በመውጣታችሁ የተለያዩ ወጪዎቻችሁን የምትሸፍኑበት ገንዘብ በማጣት ችግር ላይ ወደቃችሁ። አንድ ሰው በፈጸመው ሙስና ሳቢያ የትዳር ጓደኛችሁ፣ ልጆቻችሁና ለፋብሪካው በዱቤ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ተቋማት ሳይቀሩ ለችግር ተዳርገዋል። ይህ ሁኔታ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን! አንድ ባለጸጋ ሰው የፋብሪካውን ጥቅም በመገንዘብና ችግር ላይ ለወደቁት ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በማዘን ፋብሪካውን ከደረሰበት ኪሳራ ለመታደግ እርምጃ ይወስዳል። የፋብሪካውን ዕዳ በሙሉ በመክፈል እንደገና ተከፍቶ ሥራ እንዲጀምር ያደርጋል። ይህ ዕዳ መከፈሉ በዚያ ተቀጥረው ይሠሩ ለነበሩ በርካታ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለፋብሪካው አበዳሪዎች ትልቅ እፎይታ ያስገኛል። በተመሳሳይም አዳም ያመጣው ዕዳ መከፈሉ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ትልቅ በረከት ያስገኛል።

      ቤዛውን ሊያቀርብ የሚችለው ማን ነው?

      13, 14. (ሀ) ይሖዋ ለሰው ዘር ቤዛ ያቀረበው እንዴት ነው? (ለ) ቤዛው የተከፈለው ለማን ነው? ቤዛው በዚህ መንገድ መከፈሉስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      13 ‘የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደውን በግ’ ሊያቀርብ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 1:29) ይሁን እንጂ አምላክ የሰውን ዘር ለማዳን እንዲሁ አንድ መልአክ አልላከም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ላቀረበው ክስ የማያዳግም ምላሽ መስጠት የሚችለውን መልአክ መርጦ ልኳል። አዎን፣ ይሖዋ ‘ልዩ ደስታ እንዲሰማው የሚያደርገውን’ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ተወዳዳሪ የሌለው መሥዋዕት ከፍሏል። (ምሳሌ 8:30) የአምላክ ልጅ በሰማይ የነበረውን ሕይወት በፈቃደኝነት በመተው ‘ራሱን ባዶ አደረገ።’ (ፊልጵስዩስ 2:7) ይሖዋ የበኩር ልጁን ሕይወት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ማርያም ወደምትባል አይሁዳዊት ድንግል ማህፀን አዛወረው። (ሉቃስ 1:27, 35) ይህ የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ከሆነ በኋላ ኢየሱስ ተብሎ ቢጠራም ከአዳም ጋር ፍጹም ተመጣጣኝ ስለሆነ ከሕግ አንጻር ሁለተኛው አዳም ተብሎ ሊጠራ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በመሆኑም ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ዘር ቤዛ ሊሆን ይችላል።

      14 ይህ ቤዛ የተከፈለው ለማን ነው? መዝሙር 49:7 ይህ ቤዛ የተከፈለው “ለአምላክ” እንደሆነ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ቤዛውን ያዘጋጀው ራሱ ይሖዋ አይደለም? አዎን፣ እሱ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን ቤዛው ገንዘብን ከአንድ ኪስ አውጥቶ ወደ ሌላ ኪስ የመክተት ያህል ትርጉም የለሽ ነገር እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። ቤዛው የተከፈለው ፍትሕ የሚጠይቀውን መሥፈርት ለማሟላት እንጂ እንዲሁ አንድን ነገር በሌላ ለመተካት ብቻ ተብሎ አይደለም። ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም እንኳ ቤዛውን በመክፈል ፍጹም ለሆነው ፍትሑ ያለውን የጸና አቋም አሳይቷል።—ዘፍጥረት 22:7, 8, 11-13፤ ዕብራውያን 11:17፤ ያዕቆብ 1:17

      15. ኢየሱስ መከራ መቀበሉና መሞቱ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

      15 በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛውን ለመክፈል ሲል ራሱን በፈቃደኝነት ለመከራ አሳልፎ ሰጠ። በሐሰት ክሶች ተወንጅሎ ተያዘ፣ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈረደበት፣ በመጨረሻም በእንጨት ላይ በሚስማር ተቸነከረ፤ ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱበት ፈቅዷል። ኢየሱስ ይህን ያህል መከራ መቀበሉ አስፈላጊ ነበር? አዎን፣ ምክንያቱም የአምላክ አገልጋዮችን የታማኝነት አቋም በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ነበረበት። አምላክ፣ ኢየሱስ ሕፃን እያለ ሄሮድስ እሱን ለመግደል ያደረገውን ሙከራ አክሽፏል። (ማቴዎስ 2:13-18) ካደገ በኋላ ግን ኢየሱስ፣ ሰይጣን ለሚሰነዝርበት ጥቃት ምላሽ የሰጠው የተነሱትን አከራካሪ ጉዳዮች በሚገባ ተገንዝቦ ነው።b ይህ ነው የማይባል ግፍ ቢደርስበትም እንኳ “ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣ ከኃጢአተኞች የተለየ” ሆኖ እስከ መጨረሻው ድረስ በመጽናት ይሖዋ መከራ እየደረሰባቸውም ቢሆን በታማኝነት ጸንተው የሚቆሙ አገልጋዮች እንዳሉት በማያሻማ ሁኔታ አስመሥክሯል። (ዕብራውያን 7:26) ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት “ተፈጸመ!” ብሎ በድል አድራጊነት ስሜት መናገሩ ምንም አያስገርምም።—ዮሐንስ 19:30

      የመቤዠት ተልእኮውን ከፍጻሜ ማድረስ

      16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎችን እንዲቤዥ የተሰጠውን ተልእኮ ማከናወኑን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ” መቅረቡ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

      16 ይሁንና ኢየሱስ ሰዎችን እንዲቤዥ የተሰጠውን ተልእኮ ገና አላጠናቀቀም ነበር። በሞተ በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ከሞት አስነሳው። (የሐዋርያት ሥራ 3:15፤ 10:40) ይሖዋ ይህን በማድረግ ልጁ ላከናወነው የታማኝነት አገልግሎት ወሮታ ከመክፈሉም በላይ የአምላክ ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሰጠውን የመቤዠት ተልእኮ ከፍጻሜ ማድረስ የሚችልበትን አጋጣሚም ከፍቶለታል። (ሮም 1:4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-8) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ክርስቶስ . . . ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ . . . ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን አስገኘልን። ክርስቶስ የገባው በሰው እጅ ወደተሠራውና የእውነተኛው ቅዱስ ስፍራ አምሳያ ወደሆነው ስፍራ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ አሁን ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ ወደ ሰማይ ገብቷል።”—ዕብራውያን 9:11, 12, 24

      17 ክርስቶስ ቃል በቃል ደሙን ወደ ሰማይ ይዞ ሊሄድ አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:50) ከዚህ ይልቅ ወደ ሰማይ ይዞ የሄደው ደሙ የሚወክለውን ነገር ማለትም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ዋጋ ነው። ከዚያም የሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ በአምላክ ፊት አቀረበ። ይሖዋ ይህን መሥዋዕት ተቀብሎታል? አዎን፣ ተቀብሎታል። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ለዚህ ማስረጃ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚያን ጊዜ የተከናወነው ነገር እጅግ የሚያስደስት ቢሆንም ቤዛው የሚያስገኘው አስደናቂ ጥቅም በዚህ ብቻ የሚወሰን አልነበረም።

      ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

      18, 19. (ሀ) በክርስቶስ ደም አማካኝነት ከአምላክ ጋር የመታረቅ አጋጣሚ የተከፈተላቸው ሁለት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? (ለ) “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አሁንም ሆነ ወደፊት በቤዛው አማካኝነት የሚያገኟቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

      18 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ፣ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ በክርስቶስ በኩል ከራሱ ጋር ለማስታረቅ እንደወደደ ገልጿል። በተጨማሪም ጳውሎስ ይህ እርቅ ሁለት የተለያዩ ቡድኖችን ማለትም “በሰማያት ያሉትን ነገሮች” እና ‘በምድር ያሉትን ነገሮች’ እንደሚያጠቃልል አብራርቷል። (ቆላስይስ 1:19, 20፤ ኤፌሶን 1:10) የመጀመሪያው ቡድን በሰማይ ካህናት ሆኖ የማገልገልና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው በምድር ላይ የመግዛት ተስፋ ያላቸውን 144,000 ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:4፤ 14:1-3) እነዚህ ነገሥታትና ካህናት በሺው ዓመት የግዛት ዘመን፣ ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ቀስ በቀስ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች እንዲዳረሱ ያደርጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ራእይ 20:6፤ 21:3, 4

      19 ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች ናቸው። ራእይ 7:9-17 እነዚህ ሰዎች በቅርቡ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት የሚተርፉ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንደሆኑ ይገልጻል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከቤዛው ለመጠቀም የሺው ዓመት ግዛት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ መጠበቅ አለባቸው ማለት አይደለም። ገና ከአሁኑ “[ልብሳቸውን] በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።” በቤዛው ስለሚያምኑ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ከዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት መንፈሳዊ ጥቅሞችን በማግኘት ላይ ናቸው። የአምላክ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን ተቆጥረዋል። (ያዕቆብ 2:23) ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስለከፈለ “ያለምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን [መቅረብ]” ይችላሉ። (ዕብራውያን 4:14-16) ስህተት በሚሠሩበት ጊዜም አምላክ በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ይላቸዋል። (ኤፌሶን 1:7) ምንም እንኳ ፍጹም ባይሆኑም ንጹሕ ሕሊና ይኖራቸዋል። (ዕብራውያን 9:9፤ 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) በመሆኑም በዛሬው ጊዜም እንኳ ሰዎች ከአምላክ ጋር እርቅ በመፍጠር ላይ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 5:19, 20) በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ደግሞ ቀስ በቀስ “ከመበስበስ ባርነት ነፃ [ወጥተው] የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ።—ሮም 8:21

      20. በቤዛው ዝግጅት ላይ ማሰላሰልህ ምን እንድታደርግ ይገፋፋሃል?

      20 የቤዛውን ዝግጅት ስላደረገልን “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል [የሚታደገን] አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” (ሮም 7:25) የቤዛው ዝግጅት እንዲሁ ሲታይ ቀላል ሊመስል ቢችልም ከምናስበው በላይ አስገራሚ ነው። (ሮም 11:33) በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልተን በዚህ የቤዛ ዝግጅት ላይ ካሰላሰልን ልባችን በጥልቅ ሊነካና የፍትሕ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ልንገፋፋ እንችላለን። በተጨማሪም “ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል” ብለን እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን ለማወደስ እንገፋፋለን።—መዝሙር 33:5

      a አዳምና ሔዋን ከቤዛው ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም። የሙሴ ሕግ ሆን ብሎ ነፍስ የሚያጠፋን ሰው በተመለከተ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስቀምጧል፦ “ሞት ለሚገባው ነፍሰ ገዳይ ሕይወት ቤዛ አትቀበሉ።” (ዘኁልቁ 35:31) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ያመፁት ሆን ብለው ስለሆነ ሞት ይገባቸዋል። በዚህም ምክንያት ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጥተዋል።

      b ኢየሱስ ለአዳም ኃጢአት ተመጣጣኝ ቤዛ ሊሆን የሚችለው ሕፃን ሆኖ ሳይሆን ሙሉ ሰው ከሆነ በኋላ ሲሞት ነው። አዳም ኃጢአት የሠራው፣ ድርጊቱ የሚያስከትልበትን መዘዝ እያወቀ ሆን ብሎ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ኢየሱስም “የኋለኛው አዳም” ለመሆንና የአዳምን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን በራሱ ምርጫና ውሳኔ ከይሖዋ ጎን መቆሙን ማስመሥከር የሚችልበት ዕድሜ ላይ መሆን ነበረበት። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በመሆኑም መሥዋዕታዊ ሞቱን ጨምሮ ኢየሱስ በታማኝነት ያሳለፈው ሕይወት ሰዎችን “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊት” ሆኖ አገልግሏል።—ሮም 5:18, 19 የግርጌ ማስታወሻ

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዘኁልቁ 3:39-51 ቤዛው ፍጹም ተመጣጣኝ መሆን ያስፈለገው ለምንድን ነው?

      • መዝሙር 49:7, 8 አምላክ ቤዛውን ስለከፈለልን አመስጋኞች ልንሆን የሚገባን ለምንድን ነው?

      • ኢሳይያስ 43:25 ይህ ጥቅስ ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ ሰዎችን ለማዳን እንዳልሆነ እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?

      • 1 ቆሮንቶስ 6:20 ቤዛው በሥነ ምግባራችንና በአኗኗራችን ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይገባል?

  • ኢየሱስ ‘ፍትሕን በምድር ላይ ያሰፍናል’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ኢየሱስ የገንዘብ መንዛሪዎቹን ጠረጴዛ አየገለበጠ ከቤተ መቅደስ እንዲወጡ ሲያዛቸው።

      ምዕራፍ 15

      ኢየሱስ ‘ፍትሕን በምድር ላይ ያሰፍናል’

      1, 2. ኢየሱስ የተቆጣው መቼ ነው? ለምንስ?

      ኢየሱስ በጣም ተቆጥቷል፤ ደግሞም ሊቆጣ ይገባዋል። ይሁንና ኢየሱስ ገር ሰው ስለሆነ እንዲህ መቆጣቱ ሊያስገርምህ ይችላል። (ማቴዎስ 21:5) በእርግጥ ቁጣው የጽድቅ ቁጣ ስለነበር ስሜቱ ከቁጥጥር ውጪ አልሆነም።a ይሁን እንጂ ይህ ሰላማዊ ሰው እንዲህ የተቆጣው ለምንድን ነው? ፈጽሞ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጸም በማየቱ ነው።

      2 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ለነበረው ቤተ መቅደስ ልዩ አክብሮት ነበረው። በምድር ላይ ሰማያዊ አባቱ የሚመለክበት ብቸኛው ቅዱስ ስፍራ ይህ ነበር። በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ አይሁዳውያን ረጅም መንገድ ተጉዘው ለአምልኮ ወደዚህ ስፍራ ይመጡ ነበር። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አሕዛብ እንኳ ሳይቀሩ ለእነሱ ወደተመደበው ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ይመጡ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አገልግሎቱን እንደጀመረ አካባቢ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ አንድ እጅግ አሳዛኝ ነገር ተመለከተ። ስፍራው የገበያ እንጂ የአምልኮ ቦታ አይመስልም ነበር! በነጋዴዎችና በገንዘብ መንዛሪዎች ተጨናንቋል። ታዲያ አግባብ ያልሆነው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች የአምላክን ቤተ መቅደስ ይጠቀሙበት የነበረው ሕዝቡን ለመበዝበዝ አልፎ ተርፎም ለመዝረፍ ነበር። እንዴት?—ዮሐንስ 2:14

      3, 4. በይሖዋ ቤት ውስጥ ምን ብዝበዛ ይካሄድ ነበር? ኢየሱስስ ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ምን እርምጃ ወሰደ?

      3 የሃይማኖት መሪዎቹ ለቤተ መቅደሱ ግብር የሚከፍል ማንኛውም ሰው አንድ የተወሰነ ዓይነት ሳንቲም ብቻ እንዲጠቀም የሚያዝ ሕግ አውጥተው ነበር። ግብር ከፋዮቹ እንዲህ ዓይነቱን ሳንቲም ለማግኘት ገንዘባቸውን ለመመንዘር ይገደዱ ነበር። ስለዚህ ገንዘብ መንዛሪዎች በቤተ መቅደሱ ውስጥ ጠረጴዛ ዘርግተው እያተረፉ ገንዘብ ይመነዝሩ ነበር። እንስሳትን መሸጥም ሌላው ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ ነበር። መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጡ ሰዎች በከተማው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ነጋዴ እንስሳ መግዛት ይችሉ የነበረ ቢሆንም ያመጡት እንስሳ በቤተ መቅደሱ ኃላፊዎች ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። ከዚያው ከቤተ መቅደሱ የሚገዙት እንስሳ ግን ተቀባይነት እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነበር። ነጋዴዎቹ እነዚህ ሰዎች አማራጭ እንደሌላቸው ስለሚያውቁ አንዳንድ ጊዜ ውድ ዋጋ ያስከፍሏቸው ነበር።b ይህ ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት ንግድ ብቻ ሳይሆን ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ነበር!

      4 ኢየሱስ በአባቱ ቤት እንዲህ ያለ ፍትሐዊ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጸም በዝምታ ሊመለከት አይችልም! የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ከብቶቹንና በጎቹን ከቤተ መቅደሱ አስወጣቸው። ከዚያም ወደ ገንዘብ ለዋጮቹ በመሄድ ጠረጴዛቸውን ገለበጠ። ጠረጴዛው ላይ ተቆልሎ የነበረው ሳንቲም ወለሉ ላይ ሲበተን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ርግብ ሻጮቹን “እነዚህን ከዚህ አስወጡ!” ሲል በቁጣ ተናገራቸው። (ዮሐንስ 2:15, 16) ለምን እንዲህ ታደርጋለህ ብሎ ሊቃወመው የደፈረ አልነበረም።

      “እነዚህን ከዚህ አስወጡ!”

      “ቁርጥ አባቱን”

      5-7. (ሀ) ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ያሳለፈው ሕይወት ፍትሕን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል? የእሱን ሕይወት በመመርመርስ ምን ልንማር እንችላለን? (ለ) ኢየሱስ፣ ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ያስከተለውን የፍትሕ መጓደል ለማስተካከል ምን አድርጓል? ወደፊትስ ምን ያደርጋል?

      5 እርግጥ ነው፣ ነጋዴዎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ተመልሰው በመምጣት ንግዳቸውን ቀጥለው ነበር። ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ይህንኑ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ አገኛቸው፤ በመሆኑም ቤቱን “የዘራፊዎች ዋሻ” ያደረጉትን ሰዎች በመቃወም በአንድ ወቅት ይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት በመጥቀስ አወገዛቸው። (ኤርምያስ 7:11፤ ማቴዎስ 21:13) አዎን፣ ኢየሱስ ሕዝቡን ሲበዘብዙና የአምላክን ቤተ መቅደስ ሲያረክሱ በመመልከቱ አባቱ የተሰማው ዓይነት ስሜት ተሰምቶታል። ይህ ደግሞ ምንም አያስገርምም! ኢየሱስ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት ከአባቱ ብዙ ተምሯል። በዚህም የተነሳ የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ ተላብሷል። ታዲያ “ቁርጥ አባቱን” ማለት ይህ አይደል? ስለዚህ ስለ ይሖዋ የፍትሕ ባሕርይ በሚገባ ለማወቅ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ከመመርመር የተሻለ ዘዴ የለም።—ዮሐንስ 14:9, 10

      6 ሰይጣን ይሖዋ አምላክን ውሸታም ብሎ አላግባብ ሲወነጅልና በይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥር ክስ ሲሰነዝር የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሁኔታውን በቅርብ ይከታተል ነበር። ይህ የይሖዋን ስም በእጅጉ የሚያጎድፍ መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነበር! በተጨማሪም ኢየሱስ ለጥቅም ካልሆነ በስተቀር ማንም ፍጡር በፍቅር ተገፋፍቶ ይሖዋን አያገለግልም ሲል ሰይጣን ያነሳውን ክርክር ሰምቷል። ኢየሱስ በእነዚህ የሐሰት ክሶች እጅግ እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። ይህ ውንጀላ መሠረተ ቢስ መሆኑን በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ሲያውቅ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት! (2 ቆሮንቶስ 1:20) ይህን የሚያከናውነው እንዴት ነው?

      7 ምዕራፍ 14 ላይ እንደተመለከትነው የይሖዋ ፍጥረታት ለአምላካቸው ታማኞች አይሆኑም ሲል ሰይጣን ላነሳው ክርክር ኢየሱስ የማያዳግም ምላሽ ሰጥቷል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ በአምላክ ቅዱስ ስም ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችል መሠረት ጥሏል፤ ይህም የአምላክ አገዛዝ ትክክለኛ አይደለም የሚለውን ውሸት ማጋለጥንም ይጨምራል። ኢየሱስ የይሖዋ ዋና ወኪል በመሆኑ በመላው ጽንፈ ዓለም መለኮታዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:31) በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወትም መለኮታዊ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነበር። ይሖዋ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “መንፈሴን በእሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነም ለብሔራት ያሳውቃል” ብሏል። (ማቴዎስ 12:18) ኢየሱስ ይህ ቃል ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?

      ኢየሱስ “ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ” ግልጽ አደረገ

      8-10. (ሀ) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ያወጧቸው ወጎች ሕዝቡ ለሴቶችና አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች ንቀት እንዲያድርበት ይገፋፉ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) የአይሁዳውያን የቃል ሕግ ይሖዋ ያወጣውን የሰንበት ሕግ ያወሳሰበው እንዴት ነው?

      8 ኢየሱስ የይሖዋን ሕግ ይወድና ያከብር ነበር። ይሁን እንጂ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሕጉን ከማጣመማቸውም በላይ አላግባብ ይጠቀሙበት ነበር። ኢየሱስ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! . . . በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ” ሲል ተናግሯቸዋል። (ማቴዎስ 23:23) እነዚህ የአምላክ ሕግ አስተማሪዎች መለኮታዊ “ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ” ግልጽ ከማድረግ ይልቅ እንዲድበሰበስና እንዲሰወር አድርገዋል። እንዴት? እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

      9 ይሖዋ ሕዝቦቹ በአካባቢያቸው ከሚኖሩት አረማዊ ብሔራት ጋር እንዳይወዳጁ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (1 ነገሥት 11:1, 2) ይሁን እንጂ አንዳንድ አክራሪ የሃይማኖት መሪዎች ሕዝቡ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን ሁሉ በንቀት እንዲመለከቱ ይገፋፉ ነበር። ሌላው ቀርቶ የአይሁዳውያን የሕግ መጽሐፍ በሆነው በሚሽና ላይ “አሕዛብ ከእንስሳት ጋር የፆታ ግንኙነት የማድረግ ልማድ እንዳላቸው ስለሚታመን አንድ አይሁዳዊ ከብቱን በእነሱ ማረፊያ ማሳደር የለበትም” የሚል ደንብ ሰፍሮ ይገኛል። እንዲህ ያለው ጭፍን ጥላቻ ኢፍትሐዊ ወይም አግባብነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ከሙሴ ሕግ መንፈስ ጋር የሚቃረን ነበር። (ዘሌዋውያን 19:34) ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ ሕጎችንም አውጥተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሚስት ከባሏ ጎን ሳይሆን ከኋላ ኋላ እየተከተለች እንድትሄድ የሚያዝ የቃል ሕግ ነበራቸው። አንድ ወንድ ሚስቱን ጨምሮ ከማንኛዋም ሴት ጋር በአደባባይ ቆሞ ማውራት አይችልም ነበር። ልክ እንደ ባሪያዎች ሴቶችም ፍርድ ቤት ቆመው መመሥከር አይፈቀድላቸውም ነበር። ሌላው ቀርቶ ወንዶች፣ ሴት ሆነው ባለመፈጠራቸው አምላክን የሚያመሰግኑበት የተለመደ ጸሎት ነበራቸው።

      10 የአምላክ ሕግ የሃይማኖት መሪዎቹ ባወጧቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጎችና ደንቦች ተውጦ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የሰንበት ሕግ አይሁዳውያን በሰንበት ዕለት ሥራ ከመሥራት ታቅበው የአምልኮ ሥርዓት እንዲያከናውኑና እንዲያርፉ ያዛል። ፈሪሳውያን ግን ይህን ሕግ ውስብስብና አስቸጋሪ አድርገውት ነበር። “ሥራ” ሲባል ምን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት የሚገልጽ የራሳቸውን ዝርዝር ደንብ አውጥተዋል። እንደ ማጨድና ማደን ያሉ 39 የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን “ሥራ” ብለው ፈርጀው ነበር። ይህ ደግሞ ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል። አንድ ሰው በሰንበት ቁንጫ ቢገድል እንዳደነ ይቆጠራል? በመንገድ ሲያልፍ እሸት ቀጥፎ ቢበላ እንዳጨደ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል? የታመመን ሰው ቢፈውስ ሥራ ሠርቷል ሊባል ይችላል? እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች የሚመለከቱ የማያፈናፍኑ ዝርዝር ደንቦች ወጥተው ነበር።

      11, 12. ኢየሱስ በአምላክ ቃል ውስጥ የማይገኙትን የፈሪሳውያን ወጎች እንደሚቃወም ያሳየው እንዴት ነው?

      11 እንዲህ ያለ ወግና ሥርዓት ተንሰራፍቶ እያለ ኢየሱስ መለኮታዊ ፍትሕ ምን እንደሆነ በትክክል እንዲገነዘቡ ሰዎችን የረዳው እንዴት ነው? ትምህርቱም ሆነ አኗኗሩ የእነዚህን ሃይማኖታዊ መሪዎች አቋም የሚያወግዝ ነበር። ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት። “ለሌሎች በምታስተላልፉት ወግ የአምላክን ቃል ትሽራላችሁ” በማለት ያወጧቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወጎች አውግዟል።—ማርቆስ 7:13

      12 ኢየሱስ ፈሪሳውያን የሰንበትን ሕግ በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ እንደሆነና የሕጉን ዓላማ እንደሳቱ በግልጽ አስተምሯል። መሲሑ “የሰንበት ጌታ” እንደሆነ በመግለጽ በሰንበት ሰዎችን የመፈወስ ሥልጣን እንዳለው ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:8) ይህንንም ጎላ አድርጎ ለማሳየት በሰንበት ቀን በይፋ ፈውሷል። (ሉቃስ 6:7-10) እንዲህ ያሉት ፈውሶች በሺው ዓመት ግዛት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከናውናቸውን ተአምራት ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናሙናዎች ናቸው። ይህ የሺህ ዓመት ግዛት ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች በሙሉ ለብዙ መቶ ዘመናት ተጭኗቸው ከኖረው ከኃጢአትና ከሞት ቀንበር የሚገላገሉበት ታላቅ ሰንበት ይሆናል።

      13. ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ምን ሕግ ሥራ ላይ ውሏል? ይህስ ከሙሴ ሕግ የሚለየው እንዴት ነው?

      13 በተጨማሪም ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሥራ ላይ በዋለው አዲስ ሕግ ማለትም ‘በክርስቶስ ሕግ’ አማካኝነት ፍትሕ ምን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ አድርጓል። (ገላትያ 6:2) ይህ ሕግ ቀደም ሲል እንደነበረው የሙሴ ሕግ በአብዛኛው የያዘው በዝርዝር የሰፈሩ ትእዛዛትን ሳይሆን መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነው። ይሁንና አንዳንድ ቀጥተኛ የሆኑ ትእዛዛትንም ይዟል። ከእነዚህ ትእዛዛት አንዱን ኢየሱስ “አዲስ ትእዛዝ” ሲል ጠርቶታል። ተከታዮቹን እሱ እንደወደዳቸው እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) አዎን፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ‘በክርስቶስ ሕግ’ የሚመሩ ሰዎች ሁሉ መለያ ምልክት ነው።

      ሕያው የሆነ የፍትሕ ምሳሌ

      14, 15. ኢየሱስ የተሰጠው ሥልጣን ገደብ ያለው መሆኑን እንደተገነዘበ ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ በእሱ ላይ ምን እምነት እንዲያድርብን ያደርገናል?

      14 ኢየሱስ ፍቅርን በቃል በማስተማር ብቻ አልተወሰነም። ‘በክርስቶስ ሕግ’ ይመራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህን ሕግ በመላ አኗኗሩ አንጸባርቋል። ኢየሱስ ፍትሕን ያንጸባረቀባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

      15 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ ኢፍትሐዊ ድርጊት እንዳይፈጽም ይጠነቀቅ ነበር። ብዙውን ጊዜ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ኢፍትሐዊ የሆኑ ድርጊቶች የሚፈጽሙት ሲታበዩና አለቦታቸው ሲገቡ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። ኢየሱስ ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አልነበረም። በአንድ ወቅት አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “መምህር፣ ወንድሜ ውርሳችንን እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው። ሆኖም ኢየሱስ “አንተ ሰው፣ በእናንተ መካከል ፈራጅና ዳኛ እንድሆን ማን ሾመኝ?” ሲል መለሰለት። (ሉቃስ 12:13, 14) ኢየሱስ እንዲህ ያለ መልስ መስጠቱ አያስገርምም? የኢየሱስ እውቀትና የማመዛዘን ችሎታ አልፎ ተርፎም አምላክ የሰጠው ሥልጣን በምድር ላይ ካለ ከማንም ሰው የላቀ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች የመፍረድ ሥልጣን ስላልተሰጠው በጉዳዩ እጁን ጣልቃ ማስገባት አልፈለገም። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ በኖረባቸው ብዙ ሺህ ዓመታትም እንኳ ሳይቀር እንዲህ ያለውን የትሕትና ባሕርይ አሳይቷል። (ይሁዳ 9) ራሱን ዝቅ በማድረግ ትክክለኛውን ፍርድ ለይሖዋ መተዉ የሚደነቁ ግሩም ባሕርያት እንዳሉት የሚያሳይ ነው።

      16, 17. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲሰብክ ፍትሕን ያንጸባረቀው እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስ የፍትሕ ባሕርይ ምሕረት የተንጸባረቀበት እንዴት ነው?

      16 በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሰበከበት መንገድ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነበር። ምንም ዓይነት አድልዎ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመስበክ ጥረት አድርጓል። በአንጻሩ ግን ፈሪሳውያን ድሃና ተራ የሆኑትን ሰዎች ይንቁ የነበረ ሲሆን አምሃአሬትስ ወይም “የምድሪቱ ሰዎች” በሚለው የንቀት መጠሪያ ይጠሯቸው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ያለውን መድልዎ እንደማይደግፍ በግልጽ አሳይቷል። ምሥራቹን ለሰዎች ሲሰብክ አልፎ ተርፎም ከሰዎች ጋር ሲበላ፣ ሲመግባቸው፣ ሲፈውሳቸውም ሆነ ከሞት ሲያስነሳቸው “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” እውነትን እንዲያውቁ የሚፈልገው አባቱ ያለውን የፍትሕ ባሕርይ አንጸባርቋል።c—1 ጢሞቴዎስ 2:4

      17 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የኢየሱስ የፍትሕ ባሕርይ ምሕረት የተንጸባረቀበት ነበር። ኃጢአተኞችን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (ማቴዎስ 9:11-13) ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን ከመርዳት ወደኋላ አይልም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አሕዛብ የሆኑ ሁሉ በጥርጣሬ ዓይን ሊታዩ ይገባል የሚለውን የዘመኑን የሃይማኖት መሪዎች አመለካከት አልደገፈም። ምንም እንኳ ኢየሱስ በዋነኝነት የተላከው ለአይሁዳውያን ቢሆንም በምሕረት ተገፋፍቶ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎችን የረዳበትና ያስተማረበት ጊዜ አለ። በአንድ ወቅት “በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ታላቅ እምነት ያለው አንድም ሰው አላገኘሁም” ብሎ በመናገር የአንድን ሮማዊ የጦር መኮንን አገልጋይ ፈውሷል።—ማቴዎስ 8:5-13

      18, 19. (ሀ) ኢየሱስ ለሴቶች አክብሮት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የተወው ምሳሌ በድፍረትና በፍትሕ መካከል ያለውን ዝምድና እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?

      18 በተጨማሪም ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ብዙዎቹ አይሁዳውያን ለሴቶች የነበራቸውን አመለካከት አልደገፈም። ከዚህ ይልቅ በድፍረት ፍትሐዊ የሆነውን ነገር አድርጓል። እንደ አሕዛብ ሁሉ ሳምራውያን ሴቶችም እንደ ርኩስ ይታዩ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት ከመስበክ ወደኋላ አላለም። እንዲያውም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ የተናገረው ለዚች ሴት ነው። (ዮሐንስ 4:6, 25, 26) ፈሪሳውያን፣ ሴቶች የአምላክን ሕግ መማር የለባቸውም የሚል አቋም የነበራቸው ቢሆንም ኢየሱስ ጊዜና ጉልበቱን ሳይቆጥብ ሴቶችን አስተምሯል። (ሉቃስ 10:38-42) በአይሁዶች ወግ መሠረት ሴቶች ለምሥክርነት አይበቁም የሚል አስተሳሰብ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠው ለሴቶች ነው። አልፎ ተርፎም ይህን አስደናቂ ዜና ሄደው ለወንዶቹ ደቀ መዛሙርት እንዲያበስሩ ልኳቸዋል!—ማቴዎስ 28:1-10

      19 አዎን፣ ኢየሱስ ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ ለብሔራት አሳውቋል። ይህን ለማድረግም ሕይወቱን ለአደጋ እስከማጋለጥ ደርሷል። ይህ የኢየሱስ ምሳሌ ለእውነተኛ ፍትሕ መቆም ድፍረት እንደሚጠይቅ ያስገነዝበናል። “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” መባሉ የተገባ ነው። (ራእይ 5:5) አንበሳ ድፍረት የሚጠይቀውን የፍትሕ ባሕርይ እንደሚወክል አስታውስ። ይሁንና በቅርቡ ኢየሱስ የላቀ የፍትሕ እርምጃ ይወስዳል። “ፍትሕን በምድር ላይ [ያሰፍናል]።”—ኢሳይያስ 42:4

      መሲሐዊው ንጉሥ ‘ፍትሕን በምድር ላይ ያሰፍናል’

      20, 21. በዘመናችን መሲሐዊው ንጉሥ በመላው ምድርና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደረገው እንዴት ነው?

      20 ኢየሱስ በ1914 መሲሐዊ ንጉሥ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በምድር ላይ ፍትሕ እንዲስፋፋ ሲያደርግ ቆይቷል። እንዴት? በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ ነው። በምድር ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ተከታዮች ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚናገረውን እውነት ለሰዎች ሁሉ በማስተማር ላይ ናቸው። ልክ እንደ ኢየሱስ ያላንዳች አድልዎ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመስበክ ወጣት አረጋዊ፣ ሀብታም ድሃ፣ ወንድ ሴት ሳይሉ ሁሉም ሰው የፍትሕ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ መማር የሚችልበትን አጋጣሚ እንዲያገኝ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

      21 በተጨማሪም ኢየሱስ፣ እሱ ራስ በሆነለት ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍትሕን በማስፈን ላይ ነው። አስቀድሞ በተነገረው መሠረት “ሰዎችን” ማለትም ጉባኤውን የሚመሩ ታማኝ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን “ስጦታ አድርጎ” ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:8-12) እነዚህ ወንዶች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ ውድ የሆነውን የአምላክ መንጋ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይጠብቃሉ። ሽማግሌዎች የመንጋው አባላት ያሉበት የኑሮ ደረጃ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ሁሉም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዙ እንደሚፈልግ ይገነዘባሉ።

      22. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ስለተንሰራፋው የፍትሕ መጓደል ምን ይሰማዋል? ልጁንስ ምን እንዲያደርግ ሾሞታል?

      22 ይሁን እንጂ ኢየሱስ በቅርቡ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በመላው ምድር ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ ብልሹ ዓለም በግፍ ተሞልቷል። ብዙ ሕፃናት በረሃብ እየረገፉ ሳለ የጦር መሣሪያ ለማምረትና ተድላን የሚያሳድዱ ራስ ወዳድ ሰዎችን ፍላጎት ለማርካት ይህ ነው የማይባል ጊዜና ገንዘብ የሚጠፋ መሆኑ ይቅር የማይባል ግፍ ነው። በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት መትረፍ ሲችሉ ለሞት መዳረጋቸው በዓለም ላይ የፍትሕ መጓደል ምን ያህል እንደተንሰራፋ ከሚያሳዩት በርካታ ማስረጃዎች አንዱ ሲሆን እንዲህ ያሉት ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የይሖዋን የጽድቅ ቁጣ ይቀሰቅሳሉ። በምድር ላይ ያለውን የፍትሕ መጓደል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ የጽድቅ ጦርነት እንዲያካሂድ ልጁን ሾሞታል።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-15

      23. ክርስቶስ ከአርማጌዶን በኋላ ፍትሕ ለዘላለም እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?

      23 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍትሕ ክፉዎችን በማጥፋት ብቻ አይወሰንም። ይሖዋ ልጁን “የሰላም መስፍን” አድርጎም ሾሞታል። ከአርማጌዶን ጦርነት በኋላ የኢየሱስ መንግሥት በምድር ዙሪያ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ “በፍትሕ” ይገዛል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ከዚያም ኢየሱስ በዓለም ላይ ብዙ ሥቃይና መከራ ያስከተለውን የፍትሕ መጓደል ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። ፍጹም ከሆነው የይሖዋ ፍትሕ ጎን ለዘላለም በታማኝነት ይቆማል። እንግዲያው ዛሬ የይሖዋን ፍትሕ ለመኮረጅ ጥረት ማድረጋችን ወሳኝ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

      a ኢየሱስ የጽድቅ ቁጣ በመቆጣት እንደ ይሖዋ መሆኑን አሳይቷል፤ ይሖዋ በክፋት ሁሉ ላይ ‘ቁጣውን ለመግለጽ ዝግጁ’ ነው። (ናሆም 1:2) ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ዓመፀኛ የሆኑት ሕዝቦቹ ቤቱን “የዘራፊዎች ዋሻ” እንዳደረጉት ከገለጸ በኋላ “ንዴቴና ቁጣዬ በዚህ ቦታ . . . ላይ ይፈስሳል” ሲል ተናግሯል።—ኤርምያስ 7:11, 20

      b ሚሽና እንደሚገልጸው ከሆነ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡት ርግቦች ዋጋ እየተወደደ መምጣቱ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር። ወዲያውኑ የርግቦቹ ዋጋ 99 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል! በዚህ አትራፊ ንግድ ይበልጥ ይጠቀሙ የነበሩት እነማን ናቸው? አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በቤተ መቅደሱ የሚካሄደውን ንግድ በአብዛኛው የተቆጣጠሩት የሊቀ ካህናቱ የሐና ቤተሰቦች እንደነበሩና ይህም ለቤተሰቡ ከፍተኛ ሀብት እንዳስገኘ ይናገራሉ።—ዮሐንስ 18:13

      c ፈሪሳውያን ሕግን ያልተማረው ተራው ሕዝብ “የተረገመ ነው” የሚል አመለካከት ነበራቸው። (ዮሐንስ 7:49) ማንም ሰው እንዲህ ያሉትን ሰዎች ማስተማር ወይም ከእነዚህ ሰዎች ጋር መነገድ፣ መብላት ወይም መጸለይ የለበትም ይሉ ነበር። አንድ ሰው ሴት ልጁን እንዲህ ላለ ሰው ቢድር ለአውሬ እንደሰጣት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ፈሪሳውያን እነዚህ ተራ ሰዎች ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ እንኳ የላቸውም የሚል እምነት ነበራቸው።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • መዝሙር 45:1-7 መሲሐዊው ንጉሥ ፍጹም የሆነ ፍትሕ እንደሚያሰፍን እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      • ማቴዎስ 12:19-21 በትንቢቱ መሠረት መሲሑ የተቸገሩትንና የተደቆሱትን የሚይዘው በምን መንገድ ነው?

      • ማቴዎስ 18:21-35 ኢየሱስ እውነተኛ ፍትሕ ምሕረት እንደሚንጸባረቅበት ያስተማረው እንዴት ነው?

      • ማርቆስ 5:25-34 ኢየሱስ መለኮታዊ ፍትሕ የሰዎችን ሁኔታ ግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ያሳየው እንዴት ነው?

  • ‘ፍትሕን በማድረግ’ ከአምላክ ጋር መሄድ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች አንዲት እህትንና ሁለት ልጆቿን ቤቷ ሄደው ሲያበረታቱ። እህት ስትናገር በጥሞና እያዳመጧት ነው።

      ምዕራፍ 16

      ‘ፍትሕን በማድረግ’ ከአምላክ ጋር መሄድ

      1-3. (ሀ) ይሖዋ ባለውለታችን ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ሕይወታችንን የታደገው አፍቃሪ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው?

      እየሰመጠች ባለች መርከብ ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በሕይወት የመትረፍ ተስፋህ ተሟጥጦ ባለበት ሰዓት አንድ የነፍስ አድን ሠራተኛ ደርሶ አዳነህ እንበል። ከመርከቧ አውጥቶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየወሰደህ ሳለ “አይዞህ፣ ተርፈሃል” ሲልህ ምን ያህል እንደምትደሰት ልትገምት ትችላለህ። ይህ ሰው ትልቅ ውለታ እንደዋለልህ አይሰማህም? እሱ ባይደርስልህ ኖሮ በሕይወት አትተርፍም ነበር።

      2 ይህ ምሳሌ ይሖዋ ያደረገልንን ነገር በመጠኑም ቢሆን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሖዋ ትልቅ ባለውለታችን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ቤዛ በመክፈል ከኃጢአትና ከሞት መዳፍ እንድንላቀቅ ያደረገን እሱ ነው። በዚህ ውድ መሥዋዕት እስካመንን ድረስ ኃጢአታችን ይቅር እንደሚባልልንና የወደፊት ሕይወታችን ዋስትና እንደሚኖረው ስለምናውቅ ምንም ዓይነት ስጋት አያድርብንም። (1 ዮሐንስ 1:7፤ 4:9) ምዕራፍ 14 ላይ እንዳየነው ይሖዋ ፍቅሩንና ፍትሑን ከሁሉ በላቀ መንገድ የገለጸው በዚህ የቤዛ ዝግጅት ነው። ታዲያ እኛ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

      3 ሕይወታችንን የታደገው አፍቃሪ አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ መመርመራችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በነቢዩ ሚክያስ በኩል እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን ነግሮሃል። ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ታማኝነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!” (ሚክያስ 6:8) ይሖዋ ‘ፍትሕን እንድናደርግ’ እንደሚፈልግ ልብ በል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

      ‘እውነተኛውን ጽድቅ’ መከታተል

      4. ይሖዋ በጽድቅ መሥፈርቶቹ እንድንመራ እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?

      4 ይሖዋ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች እንድንከተል ይፈልጋል። ፍትሐዊና ጻድቅ በሆኑት በእነዚህ መሥፈርቶች የምንመራ ከሆነ ፍትሕንና ጽድቅን እየተከታተልን ነው ማለት ነው። ኢሳይያስ 1:17 “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን ፈልጉ” ይላል። የአምላክ ቃል “ጽድቅን ፈልጉ” ሲል ያሳስበናል። (ሶፎንያስ 2:3) በተጨማሪም “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅ . . . ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (ኤፌሶን 4:24 ) ዓመፅ፣ ርኩሰትና የፆታ ብልግና ቅድስናን የሚጻረሩ ስለሆኑ እውነተኛ ጽድቅ ወይም እውነተኛ ፍትሕ እንዲህ ካሉት ነገሮች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አይኖረውም።—መዝሙር 11:5፤ ኤፌሶን 5:3-5

      5, 6. (ሀ) ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተል ሸክም የማይሆንብን ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅን መከታተል ቀጣይ ሂደት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      5 ይሖዋ ያወጣቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች መከተል ሸክም ነው? በፍጹም። ከልባችን ይሖዋን የምንወድ ከሆነ መሥፈርቶቹን መከተል ሸክም አይሆንብንም። ግሩም ባሕርያት ያሉትን አምላካችንን ስለምንወደው እሱን በሚያስደስት መንገድ ለመመላለስ እንጥራለን። (1 ዮሐንስ 5:3) ይሖዋ “የጽድቅ ሥራዎችን ይወዳል።” (መዝሙር 11:7) ስለዚህ መለኮታዊውን ፍትሕ ወይም ጽድቅ መከተል የምንፈልግ ከሆነ ይሖዋ የሚወደውን መውደድ፣ የሚጠላውን ደግሞ መጥላት ይኖርብናል።—መዝሙር 97:10

      6 ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ጽድቅን መከታተል ሊከብዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። በኃጢአት ልማዶች የተተበተበውን አሮጌውን ስብዕና ገፈን መጣልና አዲሱን ስብዕና መልበስ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ ስብዕና በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ‘እየታደሰ እንደሚሄድ’ ይገልጻል። (ቆላስይስ 3:9, 10) እዚህ ላይ የገባው “እየታደሰ የሚሄደው” የሚለው አገላለጽ አዲሱን ስብዕና የመልበሱ ሂደት ቀጣይነት እንዳለውና ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደሚጠይቅ ያመለክታል። ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የቱንም ያህል ብንጥር በወረስነው ኃጢአት ምክንያት በሐሳብ፣ በቃል ወይም በድርጊት የምንሰናከልባቸው ጊዜያት አሉ።—ሮም 7:14-20፤ ያዕቆብ 3:2

      7. ጽድቅን ለመከታተል በምናደርገው ጥረት የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

      7 ጽድቅን ለመከታተል በምናደርገው ጥረት የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? እርግጥ ነው፣ ኃጢአትን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። በሌላ በኩል ግን በምንሠራቸው ስህተቶች የተነሳ ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንን ተሰምቶን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ሩኅሩኅ የሆነው አምላካችን ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ሞገሱን መልሰው ማግኘት የሚችሉበትን ዝግጅት አድርጓል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት እንዳትሠሩ ነው” ካለ በኋላ የተናገረው ሐሳብ ያጽናናናል። “[በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት] ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሏል። (1 ዮሐንስ 2:1) አዎን፣ ኃጢአት የወረስን ብንሆንም እንኳ ይሖዋ በፊቱ ሞገስ አግኝተን እንድናገለግለው ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። ይህ እሱን ለማስደሰት የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ አይገፋፋንም?

      ምሥራቹና መለኮታዊ ፍትሕ

      8, 9. የምሥራቹ መታወጅ የይሖዋን ፍትሕ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      8 የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በመስበኩ ሥራ በትጋት በመካፈል ፍትሕን ማድረግ አልፎ ተርፎም መለኮታዊውን ፍትሕ መኮረጅ እንችላለን። በይሖዋ ፍትሕና በምሥራቹ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

      9 ይሖዋ በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ይህን ክፉ ሥርዓት አያጠፋም። ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸመውን ሁኔታ አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር “አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት” ብሏል። (ማርቆስ 13:10፤ ማቴዎስ 24:3) “አስቀድሞ” የሚለው አነጋገር ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ ከተሰበከ በኋላ የሚከናወኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ያመለክታል። በትንቢት የተነገረው ታላቁ መከራ ከእነዚህ ክንውኖች አንዱ ሲሆን ይህም በክፉዎች ላይ ጥፋት የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ጽድቅ ለሚሰፍንበት አዲስ ዓለም መንገድ የሚጠርግ ይሆናል። (ማቴዎስ 24:14, 21, 22) ይሖዋ በክፉዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ ፍትሐዊ አይደለም ብሎ ሊከራከር የሚችል አይኖርም። አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንዲነገር በማድረግ እነዚህ ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው ከጥፋት መትረፍ እንዲችሉ በቂ ዕድል ሰጥቷቸዋል።—ዮናስ 3:1-10

      10, 11. ምሥራቹን መስበካችን መለኮታዊ ፍትሕን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

      10 ምሥራቹን መስበካችን መለኮታዊ ፍትሕን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሌሎች እንዲድኑ ለመርዳት የተቻለንን ጥረት ማድረጋችን ትክክለኛው እርምጃ ነው። እየሰመጠች ካለች መርከብ ላይ በሕይወት ስለመትረፍ የሚናገረውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። ሕይወት አድን ጀልባ ላይ ከወጣህ በኋላ ገና ከውኃ ውስጥ ያልወጡትን ሌሎች ሰዎች ለመርዳት ጥረት እንደምታደርግ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም በዚህ ክፉ ዓለም “ባሕር” ውስጥ ላለመስመጥ እየተፍጨረጨሩ ያሉትን ሰዎች የመርዳት ግዴታ አለብን። እርግጥ ነው፣ ብዙዎች የምንነግራቸውን መልእክት አይቀበሉም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እስከታገሠ ድረስ ‘ለንስሐ እንዲበቁ’ እና መዳን እንዲችሉ አጋጣሚ የመስጠት ኃላፊነት አለብን።—2 ጴጥሮስ 3:9

      11 ምንም ሳናዳላ ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን መስበካችን ፍትሕ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ነው። “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት [እንዳለው]” አስታውስ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ መኮረጅ ከፈለግን በሰዎች ላይ ለመፍረድ መቸኮል የለብንም። ከዚህ ይልቅ ዘራቸው፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ወይም የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ምሥራቹን መስበክ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን ሰምተው እርምጃ እንዲወስዱ አጋጣሚ እንከፍትላቸዋለን።—ሮም 10:11-13

      ሌሎችን የምንይዝበት መንገድ

      12, 13. (ሀ) በሌሎች ላይ ለመፍረድ መቸኮል የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ “መፍረዳችሁን ተዉ” እና “አትኮንኑ” ሲል የሰጠው ምክር ምን ትርጉም አለው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

      12 በተጨማሪም ይሖዋ እኛን በሚይዝበት መንገድ ሌሎችን በመያዝ ፍትሕን ማንጸባረቅ እንችላለን። ይሁንና ብዙውን ጊዜ ሰዎችን በጥርጣሬ ዓይን በማየትና ስህተቶቻቸውን በመለቃቀም በእነሱ ላይ መፍረድ ይቀናናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እያንዳንዱን ዝንባሌያችንን በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከትና ስህተቶቻችንን የማያልፍ ቢሆን ምን ይሰማን ነበር? ደግነቱ ይሖዋ እንዲህ አያደርግም። መዝሙራዊው “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 130:3) ፍትሐዊና መሐሪ የሆነው አምላካችን አንድ በአንድ ስህተታችንን የማይከታተል በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን አይገባንም? (መዝሙር 103:8-10) ታዲያ እኛስ ሌሎችን እንዴት ልንይዝ ይገባል?

      13 የአምላክ ፍትሕ ምሕረት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ከተገነዘብን በረባ ባልረባው ሰውን ለመተቸት ወይም በማይመለከቱን ጉዳዮች ገብተን በሌሎች ላይ ለመፍረድ አንቸኩልም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 7:1 የግርጌ ማስታወሻ) ሉቃስ እንደዘገበው ደግሞ ኢየሱስ “ሌሎችን አትኮንኑ፤ እናንተም ፈጽሞ አትኮነኑም” ሲል አክሎ ተናግሯል።a (ሉቃስ 6:37) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መናገሩ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሌሎች ላይ መፍረድ እንደሚቀናቸው መገንዘቡን ያሳያል። የኢየሱስ አድማጮች በሌሎች ላይ የመፍረድ ልማድ ከነበራቸው ይህን ልማዳቸውን እርግፍ አድርገው መተው ይጠበቅባቸው ነበር።

      አንዲት እህት የአካል ጉዳተኛ ለሆነ አረጋዊ ሰው እና ለአንዲት ትንሽ ልጅ ስትመሠክር።

      ምሥራቹን ሳናዳላ ለሁሉም ሰዎች በመስበክ መለኮታዊውን ፍትሕ እናንጸባርቃለን

      14. በሌሎች ላይ ‘መፍረዳችንን መተው’ ያለብን ለምንድን ነው?

      14 በሌሎች ላይ ‘መፍረዳችንን መተው’ ያለብን ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ እኛ እንዲህ የማድረግ ሥልጣን የለንም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ [ይሖዋ] ብቻ ነው” ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። በመሆኑም “በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ አቅርቧል። (ያዕቆብ 4:12፤ ሮም 14:1-4) በተጨማሪም በወረስነው ኃጢአት ሳቢያ የተዛባ ፍርድ ወደ መስጠት ልናደላ እንችላለን። መሠረተ ቢስ ጥላቻ፣ ቅናት፣ ራስን ከፍ አድርጎ መመልከትና እነዚህን የመሳሰሉ ዝንባሌዎች ለሌሎች ሰዎች ያለንን አመለካከት ሊያዛቡብን ይችላሉ። ሌሎች ጉድለቶችም እንዳሉብን ማሰባችን የሰዎችን ስህተት ከመለቃቀም እንድንታቀብ ሊያደርገን ይገባል። የሰዎችን ልብ ማንበብም ሆነ ያሉበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። እንግዲያው የእምነት አጋሮቻችን የሚያደርጉትን ነገር በመጥፎ የምንተረጉም ወይም አምላክን ለማገልገል የሚያደርጉትን ጥረት የምንተች እኛ ማን ነን? የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ጉድለት ሳይሆን መልካም ጎናቸውን በመመልከት ይሖዋን ለመኮረጅ ጥረት ማድረጋችን ምንኛ የተሻለ ነው!

      15. በአምላክ ሕዝቦች መካከል ምን ነገሮች ቦታ የላቸውም? ለምንስ?

      15 የቤተሰባችንን አባላት ስለምንይዝበት መንገድስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ፣ ቤት ሰላም የሰፈነበት ሊሆን ሲገባው አንዳንዴ ከሁሉ የከፋ ትችትና ነቀፋ የሚሰነዘርበት ቦታ መሆኑ ያሳዝናል። በቤተሰባቸው አባላት ላይ የስድብ ወይም የዱላ ናዳ የሚያወርዱ ባሎች፣ ሚስቶች ወይም ወላጆች ማየት የተለመደ ነው። ሆኖም ስድብ፣ አሽሙር እንዲሁም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ቦታ የላቸውም። (ኤፌሶን 4:29, 31፤ 5:33፤ 6:4) ኢየሱስ “መፍረዳችሁን ተዉ” እና “አትኮንኑ” ሲል የሰጠው ምክር በቤተሰብ ውስጥም እንደሚሠራ መዘንጋት አይኖርብንም። ፍትሕን ማንጸባረቅ ይሖዋ እኛን በሚይዘን መንገድ ሌሎችን መያዝንም እንደሚጨምር አስታውስ። ይሖዋ ጨካኝና ምሕረት የለሽ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለሚወዱት ሰዎች “ከአንጀት የሚራራ” አምላክ ነው። (ያዕቆብ 5:11 የግርጌ ማስታወሻ) ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌያችን ነው!

      “ፍትሕ ለማስፈን” የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች

      16, 17. (ሀ) ይሖዋ ሽማግሌዎች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል? (ለ) ኃጢአት የሠራ ሰው ከልቡ ንስሐ ካልገባ ምን መደረግ ይኖርበታል? ለምንስ?

      16 ሁላችንም ፍትሕን የማንጸባረቅ ኃላፊነት ያለብን ቢሆንም በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ከሁሉ የላቀ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ኢሳይያስ ‘መኳንንትን’ ወይም ሽማግሌዎችን በተመለከተ የተናገረውን ትንቢት ተመልከት፦ “እነሆ፣ ንጉሥ ለጽድቅ ይነግሣል፤ መኳንንትም ፍትሕ ለማስፈን ይገዛሉ።” (ኢሳይያስ 32:1) አዎን፣ ይሖዋ ሽማግሌዎች በፍትሕ እንዲያገለግሉ ይፈልጋል። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

      17 እነዚህ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ፍትሕ ወይም ጽድቅ እንዲሰፍን የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅ እንዳለባቸው በሚገባ ያውቃሉ። ሽማግሌዎች አንዳንድ ከባድ ኃጢአቶችን በመመርመር ፍርድ የሚሰጡባቸው ጊዜያት አሉ። በዚህ ጊዜ፣ መለኮታዊ ፍትሕ በተቻለ መጠን ምሕረት እንዲያሳዩ እንደሚጠይቅባቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም ኃጢአት የሠራው ሰው ንስሐ እንዲገባ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ግለሰቡ እርዳታ ተደርጎለትም ከልቡ ንስሐ ሳይገባ ቢቀርስ? የይሖዋ ቃል “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት” በማለት ፍጹም ፍትሐዊ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድበት ያዛል። በመሆኑም ሽማግሌዎች፣ ግለሰቡ ከጉባኤው እንዲወገድ ይወስናሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 2 ዮሐንስ 9-11) ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ሲወስዱ የሚያዝኑ ቢሆንም የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና ለመጠበቅ ይህን ማድረጉ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። በዚህ ጊዜም እንኳ ቢሆን ግለሰቡ አንድ ቀን ወደ ልቡ ተመልሶ ከጉባኤው ጋር እንደሚቀላቀል ተስፋ ያደርጋሉ።—ሉቃስ 15:17, 18

      18. ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ምን ማስታወስ አለባቸው?

      18 ፍትሕ ለማስፈን የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር መስጠትም ይጠበቅባቸዋል። እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች የሌሎችን ስህተት አይለቃቅሙም። በተጨማሪም በትንሹም በትልቁም እርማት ለመስጠት አይሞክሩም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን “ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና [ሊከተል]” ይችላል። ሽማግሌዎች፣ መለኮታዊ ፍትሕ ጨካኝ ወይም ርኅራኄ የጎደለው እንዳልሆነ ማስታወሳቸው ግለሰቡን “በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት [እንዲያደርጉ]” ይገፋፋቸዋል። (ገላትያ 6:1) በመሆኑም ሽማግሌዎች ስህተት የሠራውን ሰው ከመዝለፍ ወይም ሻካራ ቃል ከመናገር ይቆጠባሉ። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚሰጥ ምክር ግለሰቡን ሊያበረታታው ይችላል። ሽማግሌዎች ስህተት የሠራው ሰው እያደረገ ያለው ነገር የሚያስከትለውን ውጤት በግልጽ በማስቀመጥ ተግሣጽ በሚሰጡበት ጊዜ እንኳ ግለሰቡ የይሖዋ መንጋ አባል እንደሆነ አይዘነጉም።b (ሉቃስ 15:7) አብዛኛውን ጊዜ፣ ከፍቅር የመነጨና በደግነት የሚሰጥ ምክር ወይም ተግሣጽ ስህተት የሠራውን ሰው እንዲታረም ሊረዳው ይችላል።

      19. ሽማግሌዎች ምን ውሳኔዎችን ያደርጋሉ? እነዚህ ውሳኔዎችስ በምን ላይ የተመረኮዙ መሆን አለባቸው?

      19 ሽማግሌዎች የእምነት አጋሮቻቸውን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን የሚያደርጉባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞች በሽማግሌነት ወይም በጉባኤ አገልጋይነት ለማገልገል ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን ተሰብስበው የሚወያዩበት ጊዜ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ምንም ዓይነት አድልዎ ማድረግ እንደሌለባቸው ያውቃሉ። በራሳቸው የግል ስሜት ሳይሆን አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች ላይ ተመርኩዘው “መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥላቻና ከአድልዎ በራቀ መንገድ” ትክክለኛ ውሳኔ ያደርጋሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:21

      20, 21. (ሀ) ሽማግሌዎች ምን ጥረት ያደርጋሉ? ለምንስ? (ለ) ሽማግሌዎች “የተጨነቁትን” ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

      20 ሽማግሌዎች መለኮታዊ ፍትሕን የሚያንጸባርቁባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ኢሳይያስ ሽማግሌዎች “ፍትሕ ለማስፈን” እንደሚያገለግሉ ከተነበየ በኋላ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እያንዳንዱም ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣ ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣ በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 32:1, 2) ስለሆነም ሽማግሌዎች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው የእረፍትና የመጽናኛ ምንጭ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።

      21 በዛሬው ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጡ በርካታ ችግሮች ስላሉ ብዙዎች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ሽማግሌዎች፣ “የተጨነቁትን” ለማጽናናት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? (1 ተሰሎንቄ 5:14) ችግራቸውን እንደ ራሳችሁ ችግር አድርጋችሁ በመመልከት በርኅራኄ አዳምጧቸው። (ያዕቆብ 1:19) በልባቸው ያለውን ጭንቀት የሚያካፍሉት የሚያምኑት ሰው ይፈልጉ ይሆናል። (ምሳሌ 12:25) ይሖዋም ሆነ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንደሚወዷቸውና ከፍ አድርገው እንደሚመለከቷቸው እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (1 ጴጥሮስ 1:22፤ 5:6, 7) ከዚህም በተጨማሪ አብራችኋቸው ጸልዩ፤ በግላችሁም ልትጸልዩላቸው ትችላላችሁ። አንድ ሽማግሌ አብሯቸው መጸለዩ በእጅጉ ሊያጽናናቸው ይችላል። (ያዕቆብ 5:14, 15) የተጨነቁትን ለመርዳት ከልብ የምታደርጉትን ጥረት የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ እንደሚመለከተው አትዘንጉ።

      ሽማግሌዎች ያዘኑትንና የተከዙትን በማበረታታት የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ ያንጸባርቃሉ

      22. የይሖዋን ፍትሕ ልንኮርጅ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህስ ምን ውጤት አለው?

      22 በእርግጥም የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ በመኮረጅ ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን! የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በመከተል፣ ሕይወት አድን የሆነውን ምሥራች ለሌሎች በመንገርና የሰዎችን ስህተት ከመለቃቀም ይልቅ መልካም ጎናቸውን በማየት መለኮታዊውን ፍትሕ እናንጸባርቃለን። ሽማግሌዎች ደግሞ የጉባኤውን መንፈሳዊ ንጽሕና በመጠበቅ፣ ገንቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመስጠት፣ ከአድልዎ ነፃ የሆነ ውሳኔ በመወሰን እንዲሁም ያዘኑትንና የተከዙትን በማጽናናት መለኮታዊውን ፍትሕ ያንጸባርቃሉ። ይሖዋ ሕዝቡ ‘ፍትሕን በማድረግ’ ከእሱ ጋር ለመሄድ የሚያደርጉትን ጥረት ከሰማይ ሆኖ ሲመለከት ምንኛ ይደሰታል!

      a በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኘው አገላለጽ በሂደት ላይ ያለንና መቆም ያለበትን ድርጊት የሚያመለክት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ አድማጮቹ እያደረጉ ያሉትን ነገር እንዲተዉ ይኸውም በሌሎች ላይ መፍረዳቸውን ወይም ሌሎችን መኮነናቸውን እንዲያቆሙ መምከሩ ነበር።

      b መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:2 ላይ ሽማግሌዎች አልፎ አልፎ ‘መውቀስ፣ መገሠጽ እንዲሁም አጥብቀው መምከር’ እንዳለባቸው ይናገራል። ‘አጥብቆ መምከር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ፓራካሌኦ) “ማበረታታት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው ፓራክሊቶስ የሚለው የግሪክኛ ቃል፣ ሕግ ነክ ለሆኑ ጉዳዮች ለአንድ ግለሰብ ጥብቅና የሚቆምን ሰው ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ጠንከር ያለ ወቀሳ በሚሰጡበት ጊዜም እንኳ ግባቸው ግለሰቡን በመንፈሳዊ መርዳት ነው።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዘዳግም 1:16, 17 ይሖዋ በእስራኤል የነበሩት ዳኞች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር? ሽማግሌዎችስ ከዚህ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

      • ኤርምያስ 22:13-17 ይሖዋ የትኞቹን የግፍ ድርጊቶች በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? የእሱን የፍትሕ ባሕርይ ለመኮረጅ ወሳኝ የሆነውስ ነገር ምንድን ነው?

      • ማቴዎስ 7:2-5 የእምነት ባልንጀሮቻችንን ስህተት መለቃቀም የሌለብን ለምንድን ነው?

      • ያዕቆብ 2:1-9 ይሖዋ ስለ ማዳላት ምን አመለካከት አለው? እኛስ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይህን ምክር ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ