የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w19 መጋቢት ገጽ 26-28
  • ጥሩነት—እንዴት ልታዳብረው ትችላለህ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥሩነት—እንዴት ልታዳብረው ትችላለህ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥሩነት ምንድን ነው?
  • ‘ይሖዋ ጥሩ ነው’
  • “መልካም ማድረግን ተማሩ”
  • ጥሩነት የሚያስገኘው ውጤት
  • “ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • የይሖዋ ጥሩነት ብዛት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ይሖዋ—ከሁሉ የላቀው የጥሩነት ምሳሌ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ምንጊዜም ጥሩነት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
w19 መጋቢት ገጽ 26-28

ጥሩነት—እንዴት ልታዳብረው ትችላለህ?

  • ፍቅር

  • ደስታ

  • ሰላም

  • ትዕግሥት

  • ደግነት

  • ጥሩነት

  • እምነት

  • ገርነት

  • ራስን መግዛት

ሁላችንም በሌሎች ዘንድ እንደ ጥሩ ሰው ተደርገን መታየት እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ጥሩነትን ማሳየት ተፈታታኝ ነው። በርካታ ሰዎች “ጥሩ ነገር የማይወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞ. 3:3) ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ የራሳቸውን መሥፈርት ስለሚከተሉ ‘ጥሩውን መጥፎ፣ መጥፎውን ጥሩ’ ይላሉ። (ኢሳ. 5:20) እንዲሁም ሁላችንም ከራሳችን አስተዳደግና አለፍጽምና ጋር እንታገላለን። አንa የተባለች አንዲት እህት ለአሥርተ ዓመታት ይሖዋን ብታገለግልም “ጥሩ ሰው መሆን እችላለሁ ብዬ ማሰብ ይከብደኛል” በማለት ተናግራለች። እኛም ልክ እንደ እሷ ይሰማን ይሆናል።

ደስ የሚለው፣ ሁላችንም ጥሩነትን ማዳበር እንችላለን! ጥሩነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ውጤት ሲሆን ይህ መንፈስ ደግሞ ጥሩነትን ማዳበር ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርግ ከማንኛውም ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ተጽዕኖ የበለጠ ኃይል አለው። ከዚህ በመቀጠል ጥሩነት ምን እንደሆነና ይህን ባሕርይ ይበልጥ በተሟላ መንገድ ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ጥሩነት ምንድን ነው?

በአጭር አነጋገር፣ ጥሩነት መልካም መሆንን ያመለክታል። በተጨማሪም የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃንና በጎነትን እንዲሁም ከክፋት ወይም ከብልሽት ነፃ መሆንን ያካትታል። ጥሩነት በተግባር ማለትም ለሌሎች ጠቃሚ ነገር በማድረግ የሚገለጽ ግሩም ባሕርይ ነው።

አንዳንዶች በራሳቸው ተነሳስተው ለቤተሰባቸውና ለወዳጆቻቸው መልካም ነገር እንደሚያደርጉ አስተውለህ ይሆናል፤ ሆኖም አንድ ሰው እንዲህ ስላደረገ ብቻ ጥሩ ሰው ነው ሊባል ይችላል? እርግጥ ማናችንም ብንሆን ፍጹም በሆነ መንገድ ይህን ባሕርይ ልናንጸባርቅ አንችልም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ይላል። (መክ. 7:20) ሐዋርያው ጳውሎስም “መልካምb የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል። (ሮም 7:18) እንግዲያው ይህን ባሕርይ ለማዳበር፣ የጥሩነት ምንጭ ከሆነው አካል ትምህርት መቅሰማችን ምንኛ ምክንያታዊ ነው!

‘ይሖዋ ጥሩ ነው’

ጥሩ ለሆነው ነገር መሥፈርት የሚሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “አንተ ጥሩ ነህ፤ ሥራህም ጥሩ ነው። ሥርዓትህን አስተምረኝ” ይላል። (መዝ. 119:68) በዚህ ጥቅስ ላይ የይሖዋ ጥሩነት የተንጸባረቀባቸውን ሁለት ገጽታዎች እንመለከታለን።

ይሖዋ ጥሩ ነው። ጥሩነት የይሖዋ ማንነት ክፍል ነው። ይሖዋ “ጥሩነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ” ብሎ ለሙሴ በተናገረበት ወቅት የሆነውን ነገር ተመልከት። ጥሩነቱን ጨምሮ የይሖዋ ክብር በሙሴ ፊት ባለፈ ጊዜ ሙሴ የሚከተሉትን ቃላት ሰምቷል፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፣ ጥፋተኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ።” (ዘፀ. 33:19፤ 34:6, 7) ይህ ጥቅስ የይሖዋ ጥሩነት፣ በእያንዳንዱ ባሕርይው ላይ ተንጸባርቆ እንደሚታይ ያስገነዝበናል። ኢየሱስ ጥሩነትን በማሳየት ረገድ ከሰው ልጆች መካከል ወደር የማይገኝለት ቢሆንም እንኳ “ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” ብሎ ተናግሯል።—ሉቃስ 18:19

አንድ አባትና ልጅ የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ሲመለከቱ

የይሖዋ ጥሩነት በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ በግልጽ ይታያል

የይሖዋ ሥራዎች ጥሩ ናቸው። ይሖዋ የሠራቸው ነገሮች ሁሉ ጥሩነቱን ያንጸባርቃሉ። “ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው፤ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ይታያል።” (መዝ. 145:9) የይሖዋ ጥሩነት አድልዎ የሌለበት ነው፤ ለሰው ልጆች በሙሉ ሕይወትንና በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሰጥቷል። (ሥራ 14:17) ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ማለቱም ጥሩነቱን ያሳያል። መዝሙራዊው “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 86:5) በተጨማሪም “ንጹሕ አቋም ይዘው የሚመላለሱትን ይሖዋ አንዳች መልካም ነገር [እንደማይነፍጋቸው]” እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝ. 84:11

“መልካም ማድረግን ተማሩ”

በአምላክ መልክ ስለተፈጠርን ጥሩ የመሆንና መልካም የማድረግ ችሎታ አለን። (ዘፍ. 1:27) ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ አገልጋዮች “መልካም ማድረግን ተማሩ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኢሳ. 1:17) ይሁን እንጂ ይህን ግሩም ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።

አንደኛ፣ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ እንችላለን፤ የአምላክ መንፈስ ክርስቲያኖች እውነተኛ ጥሩነትን እንዲያዳብሩ ይረዳል። (ገላ. 5:22) አዎ፣ ይህ መንፈስ ጥሩ የሆነውን እንድንወድና ክፉ የሆነውን እንድንጠላ ያነሳሳናል። (ሮም 12:9) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ ‘ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር እንድናደርግና እንድንናገር ሊያጸናን’ ይችላል።—2 ተሰ. 2:16, 17

ሁለተኛ፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ማንበብ ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ “የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ” ያስተምረናል፤ እንዲሁም “ለማንኛውም መልካም ሥራ” ያስታጥቀናል። (ምሳሌ 2:9፤ 2 ጢሞ. 3:17) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና ባነበብነው ላይ ማሰላሰላችን ልባችንን ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ በሚገልጹ ጥሩ ነገሮች ለመሙላት ያስችለናል። በዚህ መንገድ፣ ወደፊት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን መልካም ነገሮች ልባችን ውስጥ እናከማቻለን።—ሉቃስ 6:45፤ ኤፌ. 5:9

ሦስተኛ፣ ‘ጥሩ የሆነውን ለመከተል’ የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። (3 ዮሐ. 11) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥሩነት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን እናገኛለን። እርግጥ ነው፣ ከሁሉ የላቀውን ምሳሌ የተዉልን ይሖዋና ኢየሱስ ናቸው። ይሁን እንጂ በጥሩነታቸው ምሳሌ ሆነው የተጠቀሱ ሰዎችም አሉ። ምናልባትም ጣቢታና በርናባስ ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። (ሥራ 9:36፤ 11:22-24) ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ በወሰዷቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ታሪካቸውን መመርመርህ ይጠቅምሃል። በቤተሰብህ ወይም በጉባኤህ ውስጥ ቅድሚያውን ወስደህ ሌሎችን መርዳት የምትችልባቸውን አቅጣጫዎች አስብ። ደግሞም ጣቢታና በርናባስ ጥሩ ሰው በመሆን ረገድ መልካም ስም ማትረፋቸው እንዴት እንደጠቀማቸው አትርሳ። አንተም ጥሩ ሰው ከሆንክ ልክ እንደ እነሱ ጥቅም ልታገኝ ትችላለህ።

በተጨማሪም ጥሩነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በዘመናችን ያሉ ሰዎችን ማሰብ እንችላለን። ከእነዚህ መካከል ‘ጥሩ የሆነውን ነገር የሚወዱ’ ታታሪ የጉባኤ ሽማግሌዎች ይገኙበታል። በቃልም ሆነ በተግባር “ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ” ታማኝ እህቶችንም ቢሆን አንዘነጋም። (ቲቶ 1:8፤ 2:3) ሮዝሊን የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኛዬ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ለመርዳትና ለማበረታታት ልዩ ጥረት ታደርጋለች። ስላሉበት ሁኔታ የምታስብ ሲሆን ብዙ ጊዜ ትናንሽ ስጦታዎችን ትሰጣቸዋለች፤ በተጨማሪም በሌሎች ተግባራዊ መንገዶች ትረዳቸዋለች። ጓደኛዬ በጣም ጥሩ ሰው እንደሆነች ይሰማኛል።”

ይሖዋ “መልካም የሆነውን [እንድንፈልግ]” ያበረታታናል። (አሞጽ 5:14) እንዲህ ማድረጋችን የእሱን መሥፈርቶች እንድንወድ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎታችን እንዲጠናከር ጭምር ይረዳናል።

ጥሩ ሰው ለመሆንና ጥሩ ነገር ለማድረግ እንጥራለን

ጥሩነት ለማሳየት፣ ሌሎችን የሚያስደምሙ ለየት ያሉ ወይም ትላልቅ ነገሮችን ማድረግ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ አንድ ሠዓሊ አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ በትልቁ ቀለም በመቀባት ውብ ሥዕል መሣል የሚችል ይመስልሃል? ሠዓሊው የሚፈልገውን ዓይነት ሥዕል ለመሣል በትንሽ በትንሹ ደጋግሞ ቀለም መቀባት ይኖርበታል። በተመሳሳይም ሰዎችን ለመርዳት ስንል አዘውትረን ትናንሽ ነገሮችን ማድረጋችን ጥሩ እንደሆንን ሊያሳይ ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ነገር ለመሥራት “ዝግጁ” እንድንሆን ያሳስበናል። (2 ጢሞ. 2:21፤ ቲቶ 3:1) ሌሎች ያሉበትን ሁኔታ በንቃት የምንከታተል ከሆነ “ባልንጀራችንን የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ [ልናስደስተው]” የምንችልባቸውን መንገዶች እናስተውል ይሆናል። (ሮም 15:2) ይህም ያለንን ነገር ማካፈልን ሊጨምር ይችላል። (ምሳሌ 3:27) ሰዎችን ቤታችን ጋብዘን ቀለል ያለ ምግብ አብረን መመገብ ወይም እርስ በርስ መተናነጽ እንችላለን። የታመመ ሰው ካለ ፖስት ካርድ ልንልክለት፣ ሄደን ልንጠይቀው ወይም ስልክ ልንደውልለት እንችላለን። አዎ፣ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል” መናገር የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።—ኤፌ. 4:29

እኛም እንደ ይሖዋ ለሁሉም ሰው መልካም ማድረግ እንፈልጋለን። በመሆኑም ሰዎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ እንይዛለን። ይህን ማድረግ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ የመንግሥቱን ምሥራች ለሁሉም ሰው መስበክ ነው። ኢየሱስ ባዘዘን መሠረት፣ ለሚጠሉን ሰዎች ጭምር መልካም ማድረግ ይኖርብናል። (ሉቃስ 6:27) ለሌሎች ደግነት ማሳየትና ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረግ መቼም ቢሆን ስህተት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም “እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም።” (ገላ. 5:22, 23) ተቃውሞ ወይም ችግር በሚደርስብን ጊዜ እንኳ መልካም ምግባር ማሳየታችን ሰዎችን ወደ እውነት ለመሳብና አምላክን ለማስከበር ያስችለናል።—1 ጴጥ. 3:16, 17

ጥሩነት የሚያስገኘው ውጤት

“ጥሩ ሰው . . . የሥራውን ውጤት ያገኛል።” (ምሳሌ 14:14) ጥሩነት ከሚያስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ለሌሎች መልካም ስናደርግ አብዛኛውን ጊዜ እነሱም በምላሹ መልካም ያደርጉልናል። (ምሳሌ 14:22) አንዳንዶች መልካም ባያደርጉልን እንኳ በጽናት ጥሩነት ማሳየታችን ልባቸው እንዲለሰልስና አመለካከታቸው እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል።—ሮም 12:20 ግርጌ

ብዙዎች ጥሩ የሆነውን ማድረጋቸውና ከክፋት መራቃቸው ምን ያህል እንደጠቀማቸው ይመሠክራሉ። የናንሲን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ናንሲ “ከልጅነቴ አንስቶ ለምንም ነገር ግድ የሌለኝ፣ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ሕይወት የምመራና ለሰዎች አክብሮት የጎደለኝ ሰው ነበርኩ” በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ ጥሩ የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መማርና በሥራ ላይ ማዋል ስጀምር ግን ይበልጥ ደስተኛ እየሆንኩ መጣሁ። አሁን ለራሴ አክብሮት ማዳበር ችያለሁ።”

ጥሩነትን እንድናዳብር የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀው ምክንያት እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን የሚያስደስተው መሆኑ ነው። የምናደርገውን ነገር ብዙዎች ባያዩት እንኳ ይሖዋ ያየዋል። እሱ እያንዳንዱን መልካም ድርጊትም ሆነ ሐሳብ ያውቃል። (ኤፌ. 6:7, 8) ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? “ጥሩ ሰው የይሖዋን ሞገስ ያገኛል።” (ምሳሌ 12:2) እንግዲያው ጥሩነትን ማዳበራችንን እንቀጥል። ይሖዋ “መልካም ሥራ የሚሠራ ሁሉ . . . ክብር፣ ሞገስና ሰላም ያገኛል” በማለት ቃል ገብቷል።—ሮም 2:10

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b “መልካም” እና “ጥሩ” የሚሉት ቃላት ተመሳሳይ ነገር ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ