የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w24 ጥር ገጽ 26-31
  • ይሖዋ እጅግ ይወድሃል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ እጅግ ይወድሃል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ በጣም ይወደናል
  • ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸው እንዴት ነው?
  • ስለ ይሖዋ ፍቅር ስታስብ ምን ይሰማሃል?
  • እጅግ አፍቃሪ ወደሆነው አምላካችን ቅረብ
  • ይሖዋ እንደሚወድህ አምነህ ተቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • እርስ በርስ መቀራረባችን ይበጀናል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ቤዛው ምን ያስተምረናል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
w24 ጥር ገጽ 26-31

የጥናት ርዕስ 4

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ

ይሖዋ እጅግ ይወድሃል

“ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ [ነው።]”—ያዕ. 5:11

ዓላማ

የይሖዋ ፍቅር ወደ እሱ እንድንቀርብ እንዲሁም እሱ እንደሚጠብቀን፣ እንደሚንከባከበንና ኃይላችንን እንደሚያድስልን እርግጠኞች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1. ስለ ይሖዋ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው?

ይሖዋ ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክረህ ታውቃለህ? ወደ እሱ ስትጸልይ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ይሖዋ በዓይን ባይታይም መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ መንገዶች ይገልጸዋል። ይሖዋ “ፀሐይና ጋሻ” እንዲሁም “የሚባላ እሳት” ተብሎ ተጠርቷል። (መዝ. 84:11፤ ዕብ. 12:29) ሕዝቅኤል ስለ ይሖዋ ባየው ራእይ ላይ የሰንፔር ድንጋይ፣ እንደ ብረት የሚያብረቀርቅ ነገር እንዲሁም ደማቅ ቀስተ ደመና ተመልክቷል። (ሕዝ. 1:26-28) እነዚህ አገላለጾች ስለ ይሖዋ ስናስብ እንድንደመም አልፎ ተርፎም እንድንፈራ ሊያደርጉን ይችላሉ።

2. አንዳንዶች ወደ ይሖዋ እንዳይቀርቡ የሚያግዳቸው ምን ሊሆን ይችላል?

2 ይሖዋን ልናየው ስለማንችል እሱ እንደሚወደን ማመን ሊከብደን ይችላል። አንዳንዶች በሕይወታቸው ካጋጠሟቸው ነገሮች በመነሳት ይሖዋ ፈጽሞ ሊወዳቸው እንደማይችል ይሰማቸዋል። ምናልባት አፍቃሪ አባት አላሳደጋቸው ይሆናል። ይሖዋ እንዲህ ያሉት ስሜቶች የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ ይረዳል። እኛን ለመርዳት ሲል ማራኪ የሆኑትን ባሕርያቱን በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል።

3. ስለ ይሖዋ ፍቅር በጥልቀት መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?

3 ይሖዋን ከሁሉ በተሻለ መንገድ የሚገልጸው ቃል ፍቅር የሚለው ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ፍቅር ነው። ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። የአምላክ ፍቅር በጣም ታላቅና ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ እሱን ለማይወዱት ሰዎች ጭምር ፍቅር ያሳያል። (ማቴ. 5:44, 45) በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ይሖዋና ስለ ፍቅሩ በጥልቀት እንመረምራለን። ስለ አምላካችን ይበልጥ በተማርን መጠን ይበልጥ እየወደድነው እንሄዳለን።

ይሖዋ በጣም ይወደናል

4. ስለ ይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ስታስብ ምን ይሰማሃል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ” ነው። (ያዕ. 5:11) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ራሱን ከአፍቃሪ እናት ጋር አመሳስሏል። (ኢሳ. 66:12, 13) ሕፃን ልጇን በፍቅር የምትንከባከብን እናት እስቲ ለማሰብ ሞክር። ልጇን ጭኗ ላይ አድርጋ እያዘለለች ታጫውተዋለች፤ ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት የድምፅ ቃናም ታነጋግረዋለች። ሲያለቅስ ወይም ሲያመው የሚያስፈልገውን ነገር ትሰጠዋለች። እኛም ስንጨነቅ ይሖዋ እንደሚወደን ልንተማመን ይገባል። መዝሙራዊው “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ” በማለት ጽፏል።—መዝ. 94:19

አንዲት እናት ሕፃን ልጇን ደረቷ ላይ አስጠግታ አቅፋው በርኅራኄ ዓይን ስታየው።

“እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ” (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)


5. የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

5 ይሖዋ ታማኝ ነው። (መዝ. 103:8) ስህተት በምንሠራበት ጊዜም ተስፋ አይቆርጥብንም። እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ይሖዋን አሳዝነውታል፤ ሆኖም ንስሐ በሚገቡበት ጊዜ ፍቅሩን አረጋግጦላቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤ የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ።” (ኢሳ. 43:4, 5) የአምላክ ፍቅር አሁንም አልተቀየረም። ሁልጊዜም እንደሚወደን መተማመን እንችላለን። ከባድ ስህተት ሠርተን ቢሆንም እንኳ ይሖዋ አይተወንም። ንስሐ ገብተን ወደ ይሖዋ ስንመለስ ፍቅሩ ያው እንደሆነ እንገነዘባለን። “ይቅርታው ብዙ” እንደሆነ አረጋግጦልናል። (ኢሳ. 55:7) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ይቅርታ ‘ከእሱ ዘንድ የመታደስ ዘመን እንደሚያመጣልን’ ይገልጻል።—ሥራ 3:19

6. ዘካርያስ 2:8 ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

6 ዘካርያስ 2:8⁠ን አንብብ። ይሖዋ ስለሚወደን ስሜታችንን ይረዳልናል፤ እንዲሁም ጥበቃ ሊያደርግልን ይጓጓል። ስንጎዳ ያዝናል። በመሆኑም “እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቀኝ” ብለን በልበ ሙሉነት መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 17:8) ዓይናችን የምንሳሳለትና ውድ የሆነ የአካላችን ክፍል ነው። ስለዚህ ይሖዋ ከዓይኑ ብሌን ጋር ሲያመሳስለን ‘እናንተን የነካ ውድ ንብረቴን እንደነካ ይቆጠራል’ ያለን ያህል ነው።

7. ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ እያንዳንዳችንን እንደሚወደን እንድንተማመን ይፈልጋል። ሆኖም ቀደም ሲል ባጋጠሙን ነገሮች የተነሳ እሱ እንደማይወደን ሊሰማን እንደሚችል ያውቃል። ወይም ደግሞ አሁን እያጋጠሙን ባሉት ሁኔታዎች የተነሳ ይሖዋ የሚወደን መሆኑን ልንጠራጠር እንችላለን። ታዲያ ይሖዋ እንደሚወደን ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለኢየሱስ፣ ለቅቡዓኑና ለሁላችንም ያለውን ፍቅር ያሳየባቸውን መንገዶች መመርመራችን ይጠቅመናል።

ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸው እንዴት ነው?

8. ኢየሱስ አባቱ እንደሚወደው እርግጠኛ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋና የሚወደው ልጁ ኢየሱስ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት አብረው ሲኖሩ እጅግ በጣም የጠበቀ ዝምድና መሥርተዋል። ማቴዎስ 17:5 ላይ ይሖዋ ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋ በኢየሱስ ‘በጣም እንደሚደሰትበት’ በመግለጽ ሊወሰን ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስን ምን ያህል እንደሚወደው እንድናውቅ ስለፈለገ “የምወደው ልጄ” በማለት ጠርቶታል። ይሖዋ በኢየሱስ ይኮራ ነበር፤ የሰጠውን ተልእኮ የተወጣበት መንገድም አስደስቶታል። (ኤፌ. 1:7) ኢየሱስም ቢሆን አባቱ እንደሚወደው ተጠራጥሮ አያውቅም። የይሖዋ ፍቅር ለኢየሱስ እውን ነበር። አባቱ እንደሚወደው በተደጋጋሚ በእርግጠኝነት ተናግሯል።—ዮሐ. 3:35፤ 10:17፤ 17:24

9. ይሖዋ ለቅቡዓኑ ያለውን ፍቅር የሚያሳየው የትኛው ቃል ነው? አብራራ። (ሮም 5:5)

9 ይሖዋ ለቅቡዓኑ ያለውን ፍቅርም ገልጿል። (ሮም 5:5⁠ን አንብብ።) ጥቅሱ ላይ ያለውን “ፈሷል” የሚለውን ቃል ልብ በል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ ቃሉ “እንደ ጅረት ወርዶብናል” ሊባል እንደሚችል ገልጿል። ይሖዋ ለቅቡዓኑ ያለው ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! ቅቡዓኑ ‘በአምላክ የተወደዱ’ እንደሆኑ ያውቃሉ። (ይሁዳ 1) ሐዋርያው ዮሐንስ “የአምላክ ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!” በማለት ስሜታቸውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። (1 ዮሐ. 3:1) ይሁንና ይሖዋ ፍቅር የሚያሳየው ለቅቡዓኑ ብቻ ነው? በፍጹም! ይሖዋ ሁላችንንም እንደሚወደን አሳይቷል።

10. ይሖዋ ለአንተ ያለውን ፍቅር ከሁሉ በላቀ መንገድ ያሳየው እንዴት ነው?

10 የይሖዋ ፍቅር የታየበት ከሁሉ የላቀው መንገድ የትኛው ነው? ቤዛው ነው። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ እንዲህ ያለ ፍቅር ታይቶ አያውቅም! (ዮሐ. 3:16፤ ሮም 5:8) ይሖዋ ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልና የእሱ ወዳጆች እንድንሆን ሲል ውድ ልጁን ለሁሉም የሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (1 ዮሐ. 4:10) ይሖዋና ኢየሱስ በከፈሉት ዋጋ ላይ ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን ለእያንዳንዳችን ያላቸው ፍቅር ይበልጥ ይገባናል። (ገላ. 2:20) ቤዛው የተከፈለው የይሖዋን ፍትሕ ለማስፈጸም ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የፍቅር ስጦታ ነው። ይሖዋ በእሱ ዘንድ በጣም ውድ የሆነውን ኢየሱስን መሥዋዕት በማድረግ እንደሚወደን አረጋግጦልናል። ይሖዋ ልጁ ለእኛ ሲል ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈቅዷል።

11. ከኤርምያስ 31:3 ምን እንማራለን?

11 እስካሁን እንደተመለከትነው ይሖዋ ፍቅሩን ከመደበቅ ይልቅ እንደሚወደን በግልጽ ነግሮናል። (ኤርምያስ 31:3⁠ን አንብብ።) ይሖዋ ስለሚወደን ወደ ራሱ ስቦናል። (ከዘዳግም 7:7, 8 ጋር አወዳድር።) የትኛውም አካል ወይም ማንኛውም ነገር ከዚህ ፍቅር ሊለየን አይችልም። (ሮም 8:38, 39) ስለዚህ ፍቅር ስታስብ ምን ይሰማሃል? መዝሙር 23⁠ን በማንበብ ዳዊት ስለ ይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ምን እንደተሰማው ተመልከት። ከዚያም የይሖዋ ፍቅር ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው እንመለከታለን።

ስለ ይሖዋ ፍቅር ስታስብ ምን ይሰማሃል?

12. መዝሙር 23 ስለ ምን ይናገራል?

12 መዝሙር 23:1-6⁠ን አንብብ። በመዝሙር 23 ላይ ዳዊት በይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት ገልጿል። ዳዊት በእሱና በእረኛው በይሖዋ መካከል ስላለው የጠበቀ ዝምድና ተናግሯል። ዳዊት የይሖዋን አመራር በመከተሉ የደህንነት ስሜት ተሰምቶታል፤ እንዲሁም በእሱ ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ዳዊት የይሖዋ ፍቅር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደሚከተለው ያውቅ ነበር። ይህን ያህል እንዲተማመን ያደረገው ምንድን ነው?

13. ዳዊት ይሖዋ እንደሚንከባከበው እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው?

13 “የሚጎድልብኝ ነገር የለም።” ዳዊት የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ ይሖዋ ስላሟላለት በደንብ እንደተንከባከበው ተሰምቶታል። ዳዊት የይሖዋን ወዳጅነትና ሞገስ አግኝቷል። በመሆኑም ወደፊት ምንም ቢመጣ የይሖዋ እንክብካቤ እንደማይቋረጥበት እርግጠኛ ነበር። ዳዊት በይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ማንኛውንም ጭንቀት አሸንፎ ጥልቅ ደስታና እርካታ ማግኘት ችሏል።—መዝ. 16:11

14. ይሖዋ በፍቅር የሚንከባከበን እንዴት ሊሆን ይችላል?

14 በተለይ በሕይወታችን ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ በፍቅር ይንከባከበናል። ቤቴል ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ያገለገለችው ክሌርa ቤተሰቧ በተደጋጋሚ መከራ ሲደርስበት አቅመ ቢስ እንደሆነች ተሰምቷት ነበር። አባቷ አንጎላቸው ውስጥ ደም ፈሰሰ፤ አንደኛዋ እህቷ ከጉባኤ ተወገደች፤ እንዲሁም ቤተሰቦቿ ንግዳቸውንና ቤታቸውን አጡ። ታዲያ ይሖዋ በፍቅር የተንከባከባቸው እንዴት ነው? ክሌር እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ለቤተሰቦቼ በየዕለቱ የሚያስፈልጋቸውን አሟልቶላቸዋል። ይሖዋ በተደጋጋሚ ከሚያስፈልገን በላይ አትረፍርፎ ሰጥቶናል። የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ ያየሁባቸውን ጊዜያት ሁሌም አስታውሳቸዋለሁ፤ ከፍ አድርጌም እመለከታቸዋለሁ። እነዚህ ትዝታዎች ያጋጠሙኝን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣት ረድተውኛል።”

15. ዳዊት ኃይሉ የታደሰው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 “ኃይሌን ያድሳል።” ዳዊት ባጋጠሙት ችግሮችና መከራዎች የተነሳ በጭንቀት የተዋጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። (መዝ. 18:4-6) ሆኖም የይሖዋ ፍቅርና እንክብካቤ ኃይሉን አድሶለታል። ይሖዋ የዛለውን ወዳጁን ‘ወደለመለመ መስክ’ እና “ውኃ ወዳለበት የእረፍት ቦታ” መርቶታል። በዚህም የተነሳ ዳዊት ኃይሉ ታድሶ ይሖዋን ማገልገሉን መቀጠል ችሏል።—መዝ. 18:28-32

ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች ከአንድ ምንጭ ውኃ ሲጠጡ፤ ዳዊት ይሖዋን እያወደሰ ነው።

ዳዊት በጣም በተጨነቀበት ጊዜም እንኳ የይሖዋ ታላቅ ፍቅርና እንክብካቤ ኃይሉን አድሶለታል (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)


16. የይሖዋ ፍቅር ኃይልህን ያደሰልህ እንዴት ነው?

16 ዛሬም በተመሳሳይ በሕይወታችን ውስጥ ችግርና መከራ ቢያጋጥመንም “ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም።” (ሰቆ. 3:22፤ ቆላ. 1:11) ሬቸልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ባለቤቷ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እሷንም ሆነ ይሖዋን በተወ ጊዜ በሐዘን ተውጣ ነበር። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገላት? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንደምወደድ እንዲሰማኝ አድርጓል። ይሖዋ የሰጠኝ ወዳጆች አብረውኝ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ ምግብ ያመጡልኛል፤ የሚያበረታቱ ሐሳቦችና ጥቅሶች ይልኩልኛል፤ ጥሩ ፊት ያሳዩኛል፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚንከባከበኝ ያስታውሱኛል። ይሖዋ ትልቅና አፍቃሪ የሆነ ቤተሰብ ስለሰጠኝ ምንጊዜም አመሰግነዋለሁ።”

17. ዳዊት “ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ አልፈራም” ያለው ለምንድን ነው?

17 “አንተ ከእኔ ጋር ስለሆንክ፣ ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ አልፈራም።” ዳዊት ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀበት ብዙ ጊዜ ነበር፤ ደግሞም ኃያል የሆኑ በርካታ ጠላቶች ነበሩት። ሆኖም የይሖዋ ፍቅር ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲኖር ረድቶታል። ዳዊት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሖዋ አብሮት እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። ይህ ደግሞ ብርታት ሰጥቶታል። “[ይሖዋ] ከምፈራው ነገር ሁሉ ታደገኝ” ብሎ መዘመር የቻለው ለዚህ ነው። (መዝ. 34:4) ዳዊት ፍርሃት የተሰማው ጊዜ ቢኖርም ይሖዋ እንደሚወደው ማወቁ ፍርሃቱን ለማሸነፍ ረድቶታል።

18. ይሖዋ እንደሚወድህ መተማመንህ ፍርሃት ሲሰማህ የሚያጠነክርህ እንዴት ነው?

18 ይሖዋ እንደሚወደን እርግጠኛ መሆናችን አስፈሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን የሚያጠነክረን እንዴት ነው? ሱዚ የተባለች አቅኚ፣ ልጇ የራሱን ሕይወት ባጠፋበት ወቅት እሷና ባለቤቷ ምን እንደተሰማቸው ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ድንገተኛ መከራ ሲያጋጥማችሁ አቅመ ቢስ እንደሆናችሁ ሊሰማችሁና በስጋት ልትዋጡ ትችላላችሁ። ሆኖም የይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንድንረጋጋ አድርጎናል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሬቸል እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ምሽት ሐዘኑ በጣም ከብዶኝ በጭንቀትና በፍርሃት በተዋጥኩበት ወቅት ድምፄን ከፍ አድርጌ ይሖዋን ተማጸንኩት። እናት ልጇን እንደምታባብል ይሖዋ ወዲያውኑ ልቤን አረጋጋልኝ፤ ከዚያም እንቅልፍ ወሰደኝ። ያን ዕለት ፈጽሞ አልረሳውም።” ታሶስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ በውትድርና ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለአራት ዓመታት ታስሮ ነበር። ታሶስ የይሖዋን ፍቅርና እንክብካቤ ያጣጣመው እንዴት ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ነገር አሟልቶልኛል፤ እንዲያውም ከዚያ አብልጦ ሰጥቶኛል። ይህም በእሱ ይበልጥ እንድተማመን ረድቶኛል። በተጨማሪም እስር ቤቱ የሚያስጨንቅ ቦታ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ደስታ ሰጥቶኛል። ይህም ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ተቀራርቤ በሠራሁ መጠን ከእሱ ጥሩነት ይበልጥ እንደምጠቀም እንድተማመን ረዳኝ። ስለዚህ እዚያው እስር ቤት እያለሁ በዘወትር አቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ።”

እጅግ አፍቃሪ ወደሆነው አምላካችን ቅረብ

19. (ሀ) ይሖዋ እንደሚወደን ማወቃችን በጸሎታችን ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? (ለ) በግለሰብ ደረጃ ልብህን የሚነካው ስለ ይሖዋ ፍቅር የሚናገረው የትኛው አገላለጽ ነው? (“የይሖዋን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩ አገላለጾች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

19 እስካሁን የተመለከትናቸው ተሞክሮዎች በሙሉ ‘የፍቅር አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነ ያረጋግጡልናል። (2 ቆሮ. 13:11) በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጠናል። ‘ታማኝ ፍቅሩ እንደከበበን’ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 32:10) ይሖዋ ፍቅሩን ያሳየን እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን እሱ ይበልጥ እውን ይሆንልናል፤ እንዲሁም ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን። በነፃነት ልናነጋግረውና ፍቅሩ ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ልንነግረው እንችላለን። ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልንና ሊረዳን እንደሚጓጓ በመተማመን የሚያሳስበንን ነገር ሁሉ ልናካፍለው እንችላለን።—መዝ. 145:18, 19

የይሖዋን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩ አገላለጾች

መዝሙር 32:10፦ “በይሖዋ የሚታመን ሰው . . . ታማኝ ፍቅሩ ይከበዋል።”

ኤርምያስ 31:3፦ “በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ። ከዚህም የተነሳ በታማኝ ፍቅር ወደ እኔ ሳብኩሽ።”

ዮሐንስ 16:27፦ “አብ ራሱ ይወዳችኋል።”

ያዕቆብ 5:11፦ “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ [ነው።]”

20. የይሖዋ ፍቅር ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

20 ብርድ በሆነ ቀን የተቀጣጠለ እሳት እንደሚስበን ሁሉ የይሖዋ ፍቅርም ወደ እሱ እንድንቀርብ ያነሳሳናል። የይሖዋ ፍቅር ታላቅና ማራኪ ነው። እንግዲያው የይሖዋን ፍቅር አጣጥም። ሁላችንም ‘ይሖዋን እወደዋለሁ’ በማለት ለፍቅሩ ምላሽ እንስጥ!—መዝ. 116:1

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • የይሖዋን ፍቅር እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ?

  • ይሖዋ በጣም እንደሚወድህ መተማመን የምትችለው ለምንድን ነው?

  • የይሖዋ ፍቅር ምን እንዲሰማህ ያደርጋል?

መዝሙር 108 የአምላክ ታማኝ ፍቅር

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ