የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • በአንድ ላይ እየበረሩ ላይ ዝዮች።

      ምዕራፍ 17

      ‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’

      1, 2. ሰባተኛውን ቀን በተመለከተ የይሖዋ ዓላማ ምን ነበር? በዚህ ቀን መጀመሪያ ላይ የአምላክን ጥበብ የሚፈትን ምን ሁኔታ ተከሰተ?

      በስድስተኛው የፍጥረት ቀን ከተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ የላቀውን ቦታ የያዘው የሰው ልጅ ታላቅ አዘቅት ውስጥ ወደቀ። ይሖዋ የሰውን ልጅ ጨምሮ “የሠራውን እያንዳንዱን ነገር” ከተመለከተ በኋላ “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) ይሁን እንጂ በሰባተኛው ቀን መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር በማበር በአምላክ ላይ ዓመፁ። በዚህም ሳቢያ ለኃጢአት፣ ለአለፍጽምና እና ለሞት ተዳረጉ።

      2 ይሖዋ ሰባተኛውን ቀን በተመለከተ የነበረው ዓላማ ሁሉ የከሸፈ ይመስል ነበር። ይህ ቀን ቀደም ሲል እንደነበሩት ስድስት ቀናት ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝማኔ አለው። ይሖዋ ይህን ቀን ቀድሶት የነበረ ሲሆን በዚህ ቀን ማብቂያ ላይ መላዋ ምድር ገነት እንድትሆንና ፍጹም በሆኑ የሰው ልጆች እንድትሞላ ዓላማ ነበረው። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:3) ሆኖም የሰው ልጅ በአምላክ ላይ ማመፁ ብዙ መዘዝ አስከትሏል። ታዲያ ይህ ዓላማ ዳር ሊደርስ የሚችለው እንዴት ነው? አምላክ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? ይህ ሁኔታ የይሖዋን ጥበብ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈትን ነበር ማለት ይቻላል።

      3, 4. (ሀ) ይሖዋ በኤደን የተፈጸመውን ዓመፅ በተመለከተ የወሰደው እርምጃ ድንቅ የሆነውን ጥበቡን የሚያሳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ጥበብ ስንመረምር የትኛውን ሐቅ በትሕትና አምነን ልንቀበል ይገባል?

      3 ይሖዋ ወዲያው እርምጃ ወሰደ። በኤደን ባመፁት ላይ የፍርድ ብያኔ ያስተላለፈ ከመሆኑም በላይ በእነሱ ዓመፅ ሳቢያ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማስወገድ ዓላማ እንዳለው የሚጠቁም ተስፋ ፈንጥቋል። (ዘፍጥረት 3:15) አርቆ ማስተዋል የተንጸባረቀበት ይህ የይሖዋ ዓላማ በኤደን ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለብዙ ሺህ ዓመታት የዘለቀና የወደፊቱንም ጊዜ የሚያካትት ነው። ይህ ዓላማ የተወሳሰበ ባይሆንም እንኳ ከፍተኛ ጥልቀትና ትርጉም ያለው በመሆኑ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ይህን ዓላማ በመመርመርና በማጥናት በእጅጉ ሊጠቀም ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። ክፋት፣ ኃጢአትና ሞት ይወገዳሉ። ታማኝ የሰው ልጆች ፍጹም ይሆናሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰባተኛው ቀን ከማብቃቱ በፊት ነው። በመሆኑም ዓመፁ ያስከተለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ምድርንና የሰው ልጆችን በተመለከተ ያለው ዓላማ አስቀድሞ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ፍጻሜውን ያገኛል!

      4 ይህ ጥበብ ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት እንዲያድርብን አያደርግም? ሐዋርያው ጳውሎስ በአድናቆት ስሜት ተገፋፍቶ ‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’ ሲል ጽፏል። (ሮም 11:33) የዚህን መለኮታዊ ባሕርይ የተለያዩ ገጽታዎች በምንመረምርበት ጊዜ፣ ማለቂያ ስለሌለው የይሖዋ ጥበብ ልናውቅ የምንችለው ጥቂቱን ብቻ እንደሆነ በትሕትና አምነን መቀበል አለብን። (ኢዮብ 26:14) በመጀመሪያ እስቲ የዚህን ድንቅ ባሕርይ ትርጉም እንመርምር።

      መለኮታዊ ጥበብ ምንድን ነው?

      5, 6. በእውቀትና በጥበብ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? የይሖዋ እውቀትስ ምን ያህል ሰፊ ነው?

      5 ጥበብ ከእውቀት የተለየ ነው። ኮምፒውተሮች ብዙ እውቀትና መረጃ መያዝ ይችላሉ፤ ሆኖም እነዚህን መሣሪያዎች ጥበበኛ ብሎ መጥራት ይከብዳል። ይሁንና እውቀትና ጥበብ የተያያዙ ነገሮች ናቸው። (ምሳሌ 10:14) ለምሳሌ ያህል፣ አንድን በሽታ በተመለከተ ጥበብ ያለበት ምክር ማግኘት ብትፈልግ ስለ ሕክምና ምንም እውቀት የሌለውን ሰው ታማክራለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! ስለዚህ አንድ ሰው እውነተኛ ጥበብ ሊኖረው የሚችለው ትክክለኛ እውቀት ሲኖረው ነው።

      6 ይሖዋ ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል እውቀት አለው። “የዘላለም ንጉሥ” እንደመሆኑ መጠን መጀመሪያ የሌለውና ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት የኖረው እሱ ብቻ ነው። (ራእይ 15:3) በመሆኑም ይሖዋ ሁሉን ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከአምላክ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው” በማለት ይገልጻል። (ዕብራውያን 4:13፤ ምሳሌ 15:3) ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የሠራቸውን ነገሮች ጠንቅቆ ያውቃል። የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ያደረጉትን ሁሉ ተመልክቷል። የሁሉንም ሰው ልብ የሚመረምር ሲሆን ከእሱ የተሰወረ ምንም ነገር የለም። (1 ዜና መዋዕል 28:9) የፈለግነውን የመምረጥ ነፃነት የሰጠን በመሆኑ ጥበብ ያለበት ምርጫ ስናደርግ ሲያይ ይደሰታል። “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ጊዜ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጸሎቶችን ማስተናገድ ይችላል! (መዝሙር 65:2) በተጨማሪም ይሖዋ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ እንዳለው ግልጽ ነው።

      7, 8. ይሖዋ ማስተዋል፣ ጥልቅ ግንዛቤና ጥበብ አለው የምንለው ለምንድን ነው?

      7 ይሖዋ እውቀት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ እውነታዎች እርስ በርስ እንዴት እንደሚዛመዱና አንድ ላይ ሲቀናጁ ምን መልክ እንደሚኖራቸው የመረዳት ችሎታ አለው። ጥሩውንና መጥፎውን፣ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን የማመዛዘንና ለይቶ የማወቅ ችሎታ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ውጫዊ ገጽታን ከመመልከት አልፎ ልብን ይመረምራል። (1 ሳሙኤል 16:7) በመሆኑም ይሖዋ እውቀት ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ግንዛቤና የማስተዋል ችሎታ አለው። ይሁን እንጂ ጥበብ ከዚህ ሁሉ የላቀ ነው።

      8 ጥበብ፣ እውቀትን፣ ግንዛቤንና ማስተዋልን በሥራ ላይ የማዋል ችሎታ ነው። እንዲያውም “ጥበብ” ተብለው የተተረጎሙት በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙት አንዳንድ ቃላት በቀጥታ ሲተረጎሙ “የተፈለገውን ውጤት የሚያስገኝ ዘዴ” ወይም “ተግባራዊ ጥበብ” የሚል ፍቺ አላቸው። ስለዚህ የይሖዋ ጥበብ እንዲሁ ፅንሰ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊና የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ነው። ይሖዋ ጥልቅ የሆነውን እውቀቱንና ማስተዋሉን በመጠቀም ምንጊዜም ትክክለኛውን ውሳኔ የሚያደርግ ሲሆን ውሳኔውም ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዲፈጸም ያደርጋል። እውነተኛ ጥበብ ማለት ይህ ነው! ይሖዋ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” የሚለው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እውነተኛ መሆኑን የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። (ማቴዎስ 11:19) ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያከናወናቸው ሥራዎች ጥበቡን የሚያሳዩ ጥሩ ማስረጃዎች ናቸው።

      የመለኮታዊ ጥበብ ማስረጃዎች

      9, 10. (ሀ) ይሖዋ ምን ዓይነት ጥበብ አለው? ይህን ጥበቡን ያሳየውስ እንዴት ነው? (ለ) የሴል አሠራር የይሖዋን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      9 ውብ የሆኑ ቁሳቁሶችን የሚሠራ አንድ ባለሙያ ያለውን የፈጠራ ችሎታ አድንቀህ ታውቃለህ? ይህ አስደናቂ የሆነ ጥበብ ነው። (ዘፀአት 31:1-3) የዚህ ዓይነቱ አስደናቂ ጥበብ ምንጭና ባለቤት ይሖዋ ነው። ንጉሥ ዳዊት “በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ስለተፈጠርኩ አወድስሃለሁ። ሥራዎችህ አስደናቂ ናቸው፤ ይህን በሚገባ አውቃለሁ” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (መዝሙር 139:14) በእርግጥም ስለ ሰው አካል ይበልጥ ስናውቅ በይሖዋ ጥበብ እጅግ እንደመማለን።

      10 ለምሳሌ ያህል፣ ሕይወትህ ሀ ብሎ የጀመረው የአባትህ የወንድ ዘር በእናትህ ማህፀን ውስጥ ከነበረ እንቁላል ጋር ተገናኝቶ አንድ ነጠላ ሴል በተፈጠረበት ቅጽበት ነው። ወዲያው ይህ ሴል መባዛት ይጀምራል። አንድ ሙሉ ሰው 100 ትሪሊዮን ገደማ ሴሎች አሉት። እነዚህ ሴሎች ረቂቅ ናቸው። አማካይ የሆነ መጠን ያላቸው 10,000 ሴሎች አንድ ላይ ቢሆኑ ከአንዲት ስፒል አናት አይበልጡም። ሆኖም እያንዳንዱ ሴል ከምንገምተው በላይ ውስብስብ ነው። ከማንኛውም ሰው ሠራሽ ማሽን ወይም ፋብሪካ ይበልጥ የረቀቀ ነው። ሳይንቲስቶች እንደሚሉት አንድ ሴል በግንብ ከታጠረ ከተማ ጋር ይመሳሰላል፤ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው በሮች፣ የመጓጓዣ አገልግሎት፣ የመገናኛ አውታሮች፣ የኃይል ማመንጫ ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ የቆሻሻ ማስወገጃ ዘዴ፣ ተረፈ ምርትን ወደ ጠቃሚ ምርት የሚቀይሩ ተቋማት፣ የመከላከያ ኃይልና ማዕከላዊ መስተዳድር አሉት። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሴል በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከራሱ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ሌላ ሴል ሊያስገኝ ይችላል።

      11, 12. (ሀ) በፅንስ ውስጥ ያሉ ሴሎች የተለያየ የሥራ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያደርገው ምንድን ነው? ይህስ በመዝሙር 139:16 ላይ ከሚገኘው አባባል ጋር የሚስማማው እንዴት ነው? (ለ) የሰው አንጎል “ግሩምና ድንቅ” ሆነን እንደተፈጠርን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      11 እርግጥ ሁሉም ሴሎች አንድ ዓይነት ናቸው ማለት አይደለም። የአንድ ፅንስ ሴሎች እየተባዙ ሲሄዱ የተለያየ የሥራ ድርሻ ይኖራቸዋል። አንዳንዶቹ የነርቭ ሌሎቹ ደግሞ የአጥንት፣ የጡንቻ፣ የደም ወይም የዓይን ሴሎች ይሆናሉ። ይህን የሥራ ክፍፍል የሚያደርጉት ዲ ኤን ኤ በተባለው ጀነቲካዊ ንድፍ ውስጥ በተቀመጠላቸው ፕሮግራም በመመራት ነው። ዳዊት “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ” ሲል በመንፈስ ተነሳስቶ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—መዝሙር 139:16

      12 አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች በጣም ውስብስብ ናቸው። አንጎልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንዳንድ ሳይንቲስቶች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እስካሁን በምርምር ከተደረሰባቸው ነገሮች ሁሉ የአንጎልን ያህል ውስብስብ የሆነ ነገር የለም ይላሉ። አንጎል 100 ቢሊዮን ገደማ የነርቭ ሴሎች አሉት፤ ይህም እኛ በምንገኝበት ጋላክሲ ውስጥ ከሚገኙት ከዋክብት ብዛት ጋር የሚመጣጠን ነው። እያንዳንዱ የነርቭ ሴል ከሌሎች ሴሎች ጋር የሚገናኝባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አውታሮች አሉ። ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሰው አንጎል በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አብያተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን መረጃ በሙሉ ምናልባትም ከዚያ በጣም የበለጠ መረጃ መያዝ ይችላል። ሳይንቲስቶች ይህን “ድንቅ” የአካል ክፍል ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲያጠኑ የኖሩ ቢሆንም የአንጎልን አሠራር ሙሉ በሙሉ መረዳት አዳጋች እንደሚሆን ተናግረዋል።

      13, 14. (ሀ) ጉንዳኖችና ሌሎች ፍጥረታት “በደመ ነፍስ ጥበበኞች” እንደሆኑ የሚያሳየው ምንድን ነው? ይህስ ስለ ፈጣሪያቸው ምን ያስተምረናል? (ለ) እንደ ሸረሪት ድር ያሉ ነገሮች “በጥበብ” ተሠርተዋል የምንለው ለምንድን ነው?

      13 ሆኖም የይሖዋ የፈጠራ ጥበብ የታየው በሰው ልጆች ላይ ብቻ አይደለም። መዝሙር 104:24 “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! ሁሉንም በጥበብ ሠራህ። ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች” ይላል። የይሖዋ ጥበብ በዙሪያችን ባሉ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል ጉንዳኖች “በደመ ነፍስ ጥበበኞች” ናቸው። (ምሳሌ 30:24) ጉንዳኖች በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ የተደራጁ ናቸው። በቡድን ተደራጅተው የሚኖሩ አንዳንድ የጉንዳን ዝርያዎች፣ መጠለያ ሠርተው ጥቃቅን ነፍሳትን በማርባት ከእነሱ የሚያገኙትን ንጥረ ነገር ይመገባሉ። ሌሎች ጉንዳኖች ደግሞ ፈንገስ በማልማት የግብርና ሥራ ያከናውናሉ። ሌሎች በርካታ ፍጥረታትም በደመ ነፍስ ባላቸው ጥበብ በመጠቀም አስደናቂ ነገሮችን ያከናውናሉ። አንዲት ዝንብ በአየር ላይ የምታሳየውን ትርዒት በጣም ዘመናዊ የሚባሉት አውሮፕላኖች እንኳ ሊያሳዩ አይችሉም። አንዳንድ ወፎች በከዋክብት፣ በምድር መግነጢሳዊ መስክ ወይም በውስጣቸው ባለ ተፈጥሯዊ ካርታ በመመራት ወቅቶችን ጠብቀው ከቦታ ወደ ቦታ ይፈልሳሉ። የሥነ ሕይወት ባለሙያዎች በእነዚህ ፍጥረታት ውስጥ የተነደፈውን የረቀቀ ፕሮግራም ለብዙ ዓመታት ሲያጠኑ ኖረዋል። በእርግጥም ይህን ፕሮግራም የነደፈው ፈጣሪ እጅግ ጥበበኛ ነው!

      14 ሳይንቲስቶች ከይሖዋ የፈጠራ ጥበብ ብዙ ትምህርት ቀስመዋል። ሌላው ቀርቶ ባዮሚሜቲክስ የሚባል የምሕንድስና ዘርፍ ያለ ሲሆን በዚህ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች የተፈጥሮ ንድፎችን አስመስለው ለመሥራት ይሞክራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሸረሪት ድር ስትመለከት ውበቱ ያስገርምህ ይሆናል። አንድን መሐንዲስ ግን ይበልጥ የሚያስገርመው በሸረሪት ድር ላይ የተንጸባረቀው ንድፍ ሊሆን ይችላል። በቀላሉ የሚበጠሱ የሚመስሉ አንዳንድ የሸረሪት ድሮች ተመጣጣኝ መጠን ካለው ሽቦ እንዲሁም ጥይት የማይበሳው ልብስ ለመሥራት ከሚያገለግል ክር የበለጠ ጥንካሬ አላቸው። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? የሸረሪት ድር ተገምዶ የዓሣ ማጥመጃ መረብ የሚያህል መጠን እንዲኖረው ቢደረግ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ እየበረረ ያለን የመጓጓዣ አውሮፕላን ሊያቆም ይችላል! በእርግጥም ይሖዋ ሁሉን “በጥበብ” ሠርቷል።

      ምስሎች፦ በፍጥረት ላይ የተንጸባረቀው የይሖዋ ጥበብ፦ 1. የሸረሪት ድር። 2. ትናንሽ ቅጠሎች የተሸከሙ ጉንዳኖች መስመራቸውን ጠብቀው ሲጓዙ። 3. በአንድ ላይ እየበረሩ ላይ ዝዮች።

      የምድር ፍጥረታት “በደመ ነፍስ ጥበበኞች” እንዲሆኑ ያደረገው ማን ነው?

      በሰማይ ባሉ ፍጥረታት ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ

      15, 16. (ሀ) የሰማይ አካላት ስለ ይሖዋ ጥበብ ምን ያስገነዝቡናል? (ለ) ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መላእክት በበላይነት ማስተዳደር መቻሉ ስለ ጥበቡ ምን ይጠቁመናል?

      15 በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ የፍጥረት ሥራዎች የይሖዋን ጥበብ ያንጸባርቃሉ። በምዕራፍ 5 ላይ በተወሰነ ደረጃ የተመለከትናቸው የሰማይ አካላት እንዲሁ በዘፈቀደ የተቀመጡ አይደሉም። ከዋክብት በጋላክሲዎች የተደራጁ ናቸው። እነዚህ ጋላክሲዎች በአንድነት በመከማቸት ክላስተር የተባሉ የከዋክብት ረጨቶች ስብስብ ፈጥረዋል። እነዚህ ክላስተሮች ደግሞ አንድ ላይ በመሆን ሱፐርክላስተር የሚባሉ ይበልጥ ግዙፍ የሆኑ የከዋክብት ክምችቶችን ፈጥረዋል። ይህም ይሖዋ ያወጣቸው ‘ሰማያት የሚመሩባቸው ሕጎች’ ከፍተኛ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው እንደሆኑ ያሳያሉ። (ኢዮብ 38:33) ይሖዋ የሰማይ አካላትን “ሠራዊት” ሲል መጥራቱ ምንም አያስደንቅም! (ኢሳይያስ 40:26) ይሁን እንጂ የይሖዋ ጥበብ በላቀ ደረጃ የተንጸባረቀበት ሌላም ሠራዊት አለ።

      16 በምዕራፍ 4 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈ ትልቅ ሠራዊት ዋና አዛዥ ስለሆነ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚል የማዕረግ ስም አለው። ይህም ይሖዋ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የይሖዋ ጥበብ የታየው እንዴት ነው? ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ምንጊዜም ሥራ ላይ እንደሆኑ አስታውስ። (ዮሐንስ 5:17) የልዑሉ አምላክ አገልጋዮች የሆኑት መላእክትም ምንጊዜም በሥራ የተጠመዱ እንደሆኑ መገመት ይቻላል። በተጨማሪም እነዚህ መላእክት ከሰው ልጆች የላቀ የማሰብ ችሎታና ኃይል እንዳላቸው አስታውስ። (ዕብራውያን 1:7፤ 2:7) ሆኖም ይሖዋ እነዚህ ሁሉ መላእክት በደስታ ‘ቃሉን በመፈጸምና’ ‘ፈቃዱን በማድረግ’ በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሥራ ተጠምደው እንዲኖሩ አድርጓል። (መዝሙር 103:20, 21) አምላክ እነዚህን ሁሉ መላእክት ማስተዳደር መቻሉ ምን ያህል ታላቅ ጥበብ እንዳለው የሚያሳይ ነው!

      ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” ነው

      17, 18. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” ነው የሚለው ለምንድን ነው? ጥበቡ እንድንደመም ሊያደርገን የሚገባውስ ለምንድን ነው?

      17 ከዚህ ሁሉ ማስረጃ አንጻር ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ጥበብ ከሁሉ የላቀ እንደሆነ መናገሩ ሊያስገርመን ይገባል? ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” እንደሆነ ይገልጻል። (ሮም 16:27) ፍጹም የተሟላ ጥበብ ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። የእውነተኛ ጥበብ ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። (ምሳሌ 2:6) ምንም እንኳ ኢየሱስ ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ጥበብ ያለው ቢሆንም በራሱ ጥበብ ከመመካት ይልቅ የአባቱን መመሪያ ለመከተል የመረጠው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 12:48-50

      18 ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ጥበብ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ሲገልጽ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) ጳውሎስ “እንዴት” የሚለውን ቃል በመጠቀም ለይሖዋ ጥበብ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጿል። “ጥልቅ” የሚለውን ቃል መጠቀሙም በአእምሯችን የሚፈጥረው ምስል አለ። ስለ ይሖዋ ጥበብ ስናሰላስል መጨረሻው የማይታይን ገደል ቁልቁል የመመልከት ያህል ጥልቅና ሰፊ ሊሆንብን ይችላል። በዝርዝር ልንገልጸው ቀርቶ ልንገምተው እንኳ አንችልም። (መዝሙር 92:5) ይህ ራሳችንን በትሕትና ዝቅ እንድናደርግ አይገፋፋንም?

      19, 20. (ሀ) ንስር ለመለኮታዊ ጥበብ ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን አሻግሮ የመመልከት ችሎታ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

      19 በተጨማሪም ወደፊት የሚሆነውን ማወቅ የሚችለው ይሖዋ ብቻ በመሆኑ እሱ “ብቻ ጥበበኛ” መባሉ ተገቢ ነው። ይሖዋ መለኮታዊ ጥበብን ለማመልከት፣ ከርቀት የማየት ችሎታ ያለውን ንስርን እንደ ምሳሌ እንደተጠቀመበት አስታውስ። ጎልደን ኢግል የተባለው የንስር ዝርያ 5 ኪሎ ግራም ገደማ ብቻ የሚመዝን ቢሆንም ዓይኑ ከሰው ዓይን ይበልጣል። ንስር ከፍተኛ የማየት ችሎታ ያለው በመሆኑ ከብዙ መቶ ሜትሮች ምናልባትም ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ሆኖ ትናንሽ እንስሳትን ማየት ይችላል! በአንድ ወቅት ይሖዋ ራሱ ስለ ንስር ሲናገር “ዓይኖቹም እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ ይመለከታሉ” ብሏል። (ኢዮብ 39:29) በተመሳሳይም ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ ‘ከሩቅ መመልከት’ ይችላል!

      20 ይህ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ይዟል፤ ይኸውም ያልተፈጸሙ የወደፊት ክስተቶችን እንደ ታሪክ አስቀድሞ አስቀምጧቸዋል። የተለያዩ ውጊያዎችን ማን ድል እንደሚያደርግ፣ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን አነሳስና አወዳደቅ አልፎ ተርፎም የአንዳንድ የጦር አዛዦችን የውጊያ ስልት ሳይቀር የሚገልጹ ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የተነገሩት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ ነው።—ኢሳይያስ 44:25 እስከ 45:4፤ ዳንኤል 8:2-8, 20-22

      21, 22. (ሀ) ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ የምታደርጋቸውን ምርጫዎች ሁሉ አስቀድሞ ያውቃል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የይሖዋ ጥበብ ፍቅር ወይም ርኅራኄ የጎደለው አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

      21 እንዲህ ሲባል ግን አምላክ በሕይወትህ ውስጥ የምታደርጋቸውን ምርጫዎች አስቀድሞ ያውቃል ማለት ነው? የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጥያቄ ‘አዎን’ የሚል መልስ ይሰጣሉ። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ‘አምላክ የወደፊቱን የማወቅ ችሎታውን መቆጣጠር አይችልም’ የሚል አንድምታ ያለው በመሆኑ ሰዎች ለይሖዋ ጥበብ ዝቅ ያለ ግምት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ለመዝፈን የሚያስችል ጥሩ ድምፅ ቢኖርህ ይህ ችሎታህ ከቁጥጥርህ ውጭ ሆኖ ሁልጊዜ ትዘፍናለህ ማለት ነው? ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነው! በተመሳሳይም ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ቢኖረውም ሁልጊዜ ይጠቀምበታል ማለት አይደለም። እንዲህ ቢያደርግ ራሱ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት መጋፋት ይሆንበታል፤ ይሖዋ ይህንን ውድ ስጦታ በፍጹም አይወስድብንም።—ዘዳግም 30:19, 20

      22 ከሁሉ የከፋው ደግሞ የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው አስተሳሰብ፣ የይሖዋ ጥበብ ፍቅር፣ ርኅራኄ ወይም አዘኔታ የጎደለው ነው የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑ ነው። ይህ ግን ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ጥበበኛ ልብ አለው” ይላል። (ኢዮብ 9:4) ይህ ሲባል ግን ይሖዋ ቃል በቃል ልብ አለው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ይህን ቃል እንደ ፍቅር ያሉ ውስጣዊ ስሜቶችንና ዝንባሌዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። ስለዚህ የይሖዋ ጥበብ እንደ ሌሎቹ ባሕርያቱ ሁሉ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው።—1 ዮሐንስ 4:8

      23. የይሖዋ ጥበብ እጅግ የላቀ መሆኑ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?

      23 የይሖዋ ጥበብ ሙሉ እምነት የሚጣልበት ነው። ከእኛ ጥበብ እጅግ የላቀ በመሆኑ የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ፍቅራዊ ምክር ይሰጠናል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) ፍጹም ጥበብ ወዳለው አምላካችን ይበልጥ መቅረብ እንድንችል እስቲ የይሖዋን ጥበብ ጠለቅ ብለን እንመርምር።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ኢዮብ 28:11-28 መለኮታዊ ጥበብ ምን ያህል ውድ ነው? በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችንስ ምን ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል?

      • መዝሙር 104:1-25 የይሖዋ ጥበብ በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ የተንጸባረቀው እንዴት ነው? ይህስ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?

      • ምሳሌ 3:19-26 ስለ ይሖዋ ጥበብ የምናሰላስልና ተግባራዊ የምናደርገው ከሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

      • ዳንኤል 2:19-28 ይሖዋ ሚስጥር ገላጭ የተባለው ለምንድን ነው? ይሖዋ ትንቢት በመናገር ረገድ ያለው ጥበብ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

  • ‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ጥቅልል ላይ ሲጽፍ።

      ምዕራፍ 18

      ‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ

      1, 2. ይሖዋ የጻፈልን “ደብዳቤ” ምንድን ነው? ይህን ያደረገውስ ለምንድን ነው?

      ሩቅ ካለ አንድ ወዳጅህ ወይም ዘመድህ ደብዳቤ ደርሶህ ያውቃል? ከምንወደው ሰው የተላከ ደብዳቤ ማግኘት በሕይወታችን ውስጥ በጣም ከሚያስደስቱን ነገሮች አንዱ ነው። ስለ ጤንነቱ፣ ስላጋጠሙት ሁኔታዎችና ስላቀዳቸው ነገሮች ስንሰማ እንደሰታለን። የምንወደው ሰው ምንም እንኳ በአካል ከእኛ የራቀ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ የደብዳቤ ልውውጥ እንደሚያቀራርበን የታወቀ ነው።

      2 ታዲያ ከምንወደው አምላክ የተላከ መልእክት ከመቀበል ይበልጥ ሊያስደስተን የሚችል ነገር ይኖራል? ይሖዋ “ደብዳቤ” ጽፎልናል ማለት ይቻላል፤ ይህ ደብዳቤ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ስለ ማንነቱ፣ ስላከናወናቸው ነገሮች፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ሌሎች ነገሮችም ገልጾልናል። ይሖዋ ቃሉን የሰጠን ወደ እሱ እንድንቀርብ ስለሚፈልግ ነው። ፍጹም ጥበበኛ የሆነው አምላክ ከሁሉ የተሻለውን መንገድ በመጠቀም ሐሳቡን ገልጾልናል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት መንገድም ሆነ የያዘው መልእክት የአምላክን ወደር የለሽ ጥበብ የሚያሳይ ነው።

      ቃሉን በጽሑፍ ማስፈር ለምን አስፈለገ?

      3. ይሖዋ ሕጉን ለሙሴ ያስተላለፈው በምን መንገድ ነው?

      3 አንዳንዶች ‘ይሖዋ ለሰዎች ሐሳቡን ለመግለጽ ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ሌላ መንገድ መጠቀም፣ ለምሳሌ በቀጥታ ከሰማይ ሆኖ መናገር አይችልም ነበር?’ የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ በመላእክት አማካኝነት ከሰማይ ሆኖ የተናገረባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ለእስራኤላውያን ሕጉን የሰጠው በዚህ መንገድ ነበር። (ገላትያ 3:19) ከሰማይ የተሰማው ድምፅ በጣም ያስፈራ ስለነበር እስራኤላውያን ይሖዋ በቀጥታ ከሚያነጋግራቸው ይልቅ በሙሴ አማካኝነት ቢያነጋግራቸው እንደሚመርጡ ገልጸዋል። (ዘፀአት 20:18-20) በመሆኑም ይሖዋ ከ600 በላይ ደንቦችን የያዘውን ሕግ ለሙሴ በቃል ነግሮታል።

      4. የአምላክ ሕግ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ በቃል ቢተላለፍ ኖሮ ምን ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አስረዳ።

      4 ይሁንና ሕጉ በጽሑፍ ባይሰፍር ኖሮ ምን ሁኔታ ይፈጠር ነበር? ሙሴ እያንዳንዱን ዝርዝር ደንብ በማስታወስ ምንም ሳያጓድል ለሕዝቡ ማስተላለፍ ይችል ነበር? ሕዝቡስ ሙሴ የነገራቸውን እያንዳንዱን ነገር አስታውሰው ከእነሱ በኋላ ለሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ማስተላለፍ ይችሉ ነበር? ይህ የአምላክን ሕግ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ አይደለም። በረድፍ የተቀመጡ በርካታ ሰዎች አንድን ታሪክ አንዳቸው ለሌላው እየተናገሩ ታሪኩን እንዲያስተላልፉ ብታደርግ በመጨረሻ ላይ ምን ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ገምት። በረድፉ መጨረሻ ላይ ያለው ሰው ምን እንደሰማ ብትጠይቀው የታሪኩ ይዘት በእጅጉ ተለውጦ ታገኘዋለህ። የአምላክ ሕግ ግን በዚህ መንገድ እንዲተላለፍ ስላልተደረገ እንዲህ ዓይነት ችግር አላጋጠመውም።

      5, 6. ይሖዋ ሙሴን ምን እንዲያደርግ አዝዞታል? የይሖዋ ቃል በጽሑፍ በመስፈሩ በእጅጉ ተጠቅመናል የምንለው ለምንድን ነው?

      5 ይሖዋ ቃሉ በጽሑፍ እንዲሰፍር ማድረጉ ጥበብ ነበር። ሙሴን “ከአንተም ሆነ ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የምገባው በእነዚህ ቃላት መሠረት ስለሆነ እነዚህን ቃላት ጻፍ” ሲል አዝዞታል። (ዘፀአት 34:27) በመሆኑም በ1513 ዓ.ዓ. የአምላክን ቃል በጽሑፍ ማስፈር ተጀመረ። በቀጣዮቹ 1,610 ዓመታት ይሖዋ ወደ 40 ለሚጠጉ ሰዎች “በተለያዩ ጊዜያትና በብዙ መንገዶች” ቃሉን በመናገር በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ አድርጓል። (ዕብራውያን 1:1) በእነዚህ ጊዜያት ታማኝና ትጉህ የሆኑ ገልባጮች ቅዱሳን መጻሕፍት እንዳሉ ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ በጥንቃቄ ይገለብጡ ነበር።—ዕዝራ 7:6፤ መዝሙር 45:1

      6 ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ሐሳቡን ለእኛ በመግለጡ በእጅጉ ተጠቅመናል። ከምትወደው ሰው በጣም የሚያጽናና ደብዳቤ ደርሶህ ያውቃል? ሌላ ጊዜም ደግመህ ደጋግመህ ልታነበው ስለምትፈልግ ደብዳቤውን ታስቀምጠዋለህ። የይሖዋ “ደብዳቤም” እንዲሁ ነው። ይሖዋ ቃሉን በጽሑፍ ስላሰፈረልን አዘውትረን ማንበብና በያዘው መልእክት ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (መዝሙር 1:2) መጽናኛ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ “ከቅዱሳን መጻሕፍት . . . መጽናኛ” ልናገኝ እንችላለን።—ሮም 15:4

      በሰዎች ማስጻፍ ለምን አስፈለገ?

      7. ይሖዋ ቃሉን ለማስጻፍ ሰዎችን በመጠቀም ጥበቡን ያሳየው እንዴት ነው?

      7 ይሖዋ ቃሉን ለማስጻፍ ሰዎችን በመጠቀም ጥበቡን አሳይቷል። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ መላእክትን ቢጠቀም ኖሮ አሁን ያለው ዓይነት ጣዕም ይኖረው ነበር? እርግጥ ነው፣ መላእክት ይሖዋን እነሱ ካላቸው የላቀ ግንዛቤ አንጻር ሊገልጹት፣ ለእሱ ያላቸውን ታማኝነትና ፍቅር በሚጽፉት መልእክት ሊያንጸባርቁ እንዲሁም ታማኝ ስለሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ጥሩ የሆነ ዘገባ ሊያቀርቡ ይችሉ ነበር። ሆኖም ከእኛ እጅግ የላቀ እውቀት፣ ተሞክሮና ኃይል ያላቸው ፍጹም መንፈሳዊ ፍጥረታት ያሰፈሩትን ሐሳብ መረዳት እንችል ነበር?—ዕብራውያን 2:6, 7

      8. ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ እንዲጠቀሙ ነፃነት የሰጣቸው በምን መንገድ ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

      8 ይሖዋ ሰዎችን በመጠቀም ቃሉን ለእኛ ተስማሚ በሆነ መንገድ አስጽፎልናል፤ ይህ ዘገባ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ ቢሆንም ሰብዓዊ ስሜት የተንጸባረቀበት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ በመጠቀም “ደስ የሚያሰኙ ቃላትን” መርጠው “የእውነትን ቃል በትክክል” እንዲጽፉ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። (መክብብ 12:10, 11) መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ የአጻጻፍ ስልት ሊኖረው የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጸሐፊውን አስተዳደግና ሙያ እንዲሁም ባሕርይ ያንጸባርቃል።a ሆኖም እነዚህ ሰዎች “ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው” ተናግረዋል። (2 ጴጥሮስ 1:21) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ “የአምላክ ቃል” ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13

      “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው”

      9, 10. መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ልባችንን የሚነካና ስሜታችንን የሚማርክ እንዲሆን ያስቻለው ለምንድን ነው?

      9 መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ልባችንን የሚነካና ስሜታችንን የሚማርክ እንዲሆን አድርጎታል። ጸሐፊዎቹ የእኛው ዓይነት ስሜት ያላቸው ነበሩ። ፍጽምና የሌላቸው እንደመሆናቸው መጠን እንደ እኛው የተለያዩ ፈተናዎችንና ተጽዕኖዎችን መቋቋም አስፈልጓቸዋል። እንዲያውም የአምላክ መንፈስ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ስለ ራሳቸው ስሜትና ከገጠሟቸው ችግሮች ጋር ስላደረጉት ትግል እንዲጽፉ አነሳስቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) በመሆኑም መላእክት ቢሆኑ ኖሮ ሊገልጹት የማይችሉትን ሰብዓዊ ስሜት ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ጽፈዋል።

      10 የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዳዊት ከባድ ኃጢአቶችን ከፈጸመ በኋላ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን የሚገልጽ አንድ መዝሙር በማቀናበር አምላክ ይቅር እንዲለው ተማጽኗል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦- “[ከኃጢአቴ] አንጻኝ። መተላለፌን በሚገባ አውቃለሁና፤ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነው። እነሆ፣ በደለኛ ሆኜ ተወለድኩ፤ እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ። ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ። አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም።” (መዝሙር 51:2, 3, 5, 11, 17) ይህን ስታነብ ጸሐፊው ምን ያህል ልቡ በሐዘን እንደተደቆሰ አልተሰማህም? ፍጽምና ከጎደለው ሰው ሌላ እንዲህ ያለውን ጥልቅ ስሜት ማን ሊገልጸው ይችላል?

      ስለ ሰዎች የሚናገረው ለምንድን ነው?

      11. መጽሐፍ ቅዱስ “ለእኛ ትምህርት” የሚሆኑ ምን እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን ይዟል?

      11 መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ማራኪ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረገ ሌላም ነገር አለ። በአብዛኛው የሚናገረው ስለ ሰዎች ይኸውም አምላክን ስላገለገሉ ወይም በእሱ ላይ ስላመፁ ሰዎች ነው። ስላጋጠሟቸው ነገሮች፣ ስለደረሱባቸው መከራዎችና ስላገኙት ደስታ የሚገልጹ ዘገባዎችን እናነባለን። በሕይወታቸው ውስጥ ያደረጉት ምርጫ ምን ውጤት እንዳስከተለባቸው የሚገልጹ ዘገባዎችንም እናገኛለን። እንዲህ ያሉት ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት “ለእኛ ትምህርት” እንዲሆኑ ነው። (ሮም 15:4) ይሖዋ እነዚህን እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች እንደ ምሳሌ በመጠቀም ልብ በሚነካ መንገድ ያስተምረናል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

      12. ታማኝ ስላልሆኑ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ጥቅም አላቸው?

      12 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ስላልሆኑ አልፎ ተርፎም ክፉ ስለሆኑ ሰዎችና ስለደረሰባቸው ነገር ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች ስለፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚገልጹት ዘገባዎች ልንርቃቸው የሚገቡ መጥፎ ባሕርያትን በቀላሉ ለይተን እንድናውቅ ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከክህደት እንድንርቅ መመሪያ ሊሰፍርልን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ድርጊት ምን ያህል መጥፎ መሆኑን ለማስረዳት ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን እንደ ምሳሌ ከመጥቀስ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል? (ማቴዎስ 26:14-16, 46-50፤ 27:3-10) እንዲህ ያሉ ዘገባዎች መጥፎ ባሕርያትን ለይተን እንድናውቅና እንድንጠላ በማድረግ ረገድ ይበልጥ ኃይል አላቸው።

      13. መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ባሕርያትን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

      13 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ስለሆኑ በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ለአምላክ ያደሩ እንደነበሩ የሚገልጹ ዘገባዎችን እናገኛለን። እኛም ወደ አምላክ ለመቅረብ ምን ዓይነት ባሕርያትን ማዳበር እንዳለብን ከእነዚህ ሰዎች ሕያው ምሳሌ ልንማር እንችላለን። እነዚህ ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንደ ምሳሌ ልንወስድ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ምን ማለት እንደሆነና አምላክን ለማስደሰት ይህን ባሕርይ ማሳየታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጽልናል። (ዕብራውያን 11:1, 6) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እምነትን በተግባር ያሳዩ ሰዎችን ሕያው ምሳሌም ይዟል። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ በነበረበት ወቅት ያሳየውን እምነት አስብ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 22፤ ዕብራውያን 11:17-19) እንዲህ ያሉት ዘገባዎች “እምነት” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ እንድንገነዘብ ያስችሉናል። ይሖዋ ጥሩ ባሕርያትን እንድናዳብር ከማሳሰብ በተጨማሪ እንዲህ ያሉ ሕያው ምሳሌዎችን በቃሉ ውስጥ ማካተቱ ምንኛ ጥበብ ነው!

      14, 15. መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ስለመጣች አንዲት ሴት ምን ይገልጻል? ይህስ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

      14 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች ይሖዋ ምን ዓይነት ባሕርያት ያሉት አምላክ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስላያት ሴት የሚገልጸውን ታሪክ ተመልከት። ኢየሱስ መዋጮ በሚደረግበት ሣጥን አቅራቢያ ተቀምጦ መዋጮ የሚያደርጉትን ሰዎች ይመለከት ነበር። ብዙ ባለጠጎች “ከትርፋቸው” መዋጮ ያደርጉ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ አንዲት ድሃ መበለት ያደረገችው መዋጮ ትኩረቱን ሳበው። ይህች ሴት “በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” መዋጮ አደረገች።b ያለቻት ገንዘብ ይህችው ነበረች። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት የነበረው ኢየሱስ “በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች” ሲል ተናግሯል። ከኢየሱስ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ሌሎች ሁሉ ያደረጉት መዋጮ አንድ ላይ ቢደመር እንኳ ይህች ሴት ካደረገችው መዋጮ ጋር አይተካከልም።—ማርቆስ 12:41-44፤ ሉቃስ 21:1-4፤ ዮሐንስ 8:28

      15 በዚያን ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ከመጡት ሰዎች ሁሉ ይህች መበለት ተለይታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሷ የሚያስገርም አይደለም? ይህ ምሳሌ ይሖዋ የምናደርገውን ነገር የሚያደንቅ አምላክ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። የምናቀርበው ስጦታ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ሊሆን ቢችልም እንኳ በሙሉ ነፍሳችን እስካደረግነው ድረስ ይሖዋ በደስታ ይቀበለዋል። ይሖዋ ይህን አስደሳች ሐቅ ለማስገንዘብ ሊጠቀምበት የሚችል ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም!

      መጽሐፍ ቅዱስ የማይገልጻቸው ነገሮች

      16, 17. ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን በቃሉ ውስጥ አለማካተቱም እንኳ ጥበቡን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      16 ለምትወደው ሰው ደብዳቤ በምትጽፍበት ጊዜ፣ ልትገልጽለት የምትችለው ብዙ ነገር ቢኖርም ሁሉንም በዝርዝር መጻፍ እንደማትችል የታወቀ ነው። ስለዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች መርጠህ መጻፍ ይኖርብሃል። በተመሳሳይም ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የተወሰኑ ግለሰቦችንና ክንውኖችን ብቻ መርጦ አስፍሮልናል። ይሁንና እነዚህ ዘገባዎችም ቢሆኑ ሁልጊዜ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ይገልጻሉ ማለት አይደለም። (ዮሐንስ 21:25) ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስለሚወስደው የፍርድ እርምጃ የሚሰጠው መግለጫ በአእምሯችን ውስጥ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ አይሰጠን ይሆናል። ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን በቃሉ ውስጥ አለማካተቱ በራሱ ጥበቡን የሚያሳይ ነው። እንዴት?

      17 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት መንገድ በልባችን ውስጥ ያለውን ለመመርመር የሚያስችል ነው። ዕብራውያን 4:12 እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ቃል [ወይም መልእክት] ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን . . . እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ወደ ልባችን ዘልቆ በመግባት ትክክለኛው አስተሳሰባችንና ዝንባሌያችን ምን እንደሆነ እንዲታወቅ ያደርጋል። መተቸት የሚቀናው ልብ ይዘው ቃሉን የሚያነቡ ሰዎች ዝርዝር መረጃዎችን ያልያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ ቅር ያሰኟቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ይሖዋ አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ፍትሐዊ አምላክ ስለ መሆኑም እንኳ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ።

      18, 19. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ወዲያው መልስ ልናገኝላቸው ያልቻልናቸው ጥያቄዎች በአእምሯችን ውስጥ እንዲፈጠሩ ቢያደርግ መረበሽ የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክን ቃል ለመረዳት አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህስ የይሖዋን ታላቅ ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      18 በአንጻሩ ግን ቃሉን በቅን ልቦና ተነሳስተን የምናነብ ከሆነ ስለ ይሖዋ የሚኖረን ግንዛቤ በአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በመሆኑም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ወዲያው መልስ ልናገኝላቸው ያልቻልናቸውን ጥያቄዎች ቢያስነሳብን አንረበሽም። ሁኔታውን ከአንድ ትልቅ ተገጣጣሚ ሥዕል ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱን ሥዕል ስንገጣጥም አንዳንዴ የምንፈልገውን ቁራጭ ላናገኝ እንችላለን፤ አንዳንዶቹ ቁርጥራጮች ደግሞ የቱ ጋ እንደሚገቡ ግራ ሊገባን ይችላል። ሆኖም የሥዕሉን የተወሰነ ክፍል ገጣጥመን ከጨረስን አጠቃላይ መልኩ ምን ሊመስል እንደሚችል እንረዳለን። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብን መጠን ስለ ይሖዋ ያለን እውቀት ደረጃ በደረጃ እያደገና እየሰፋ ይሄዳል፤ ስለ ማንነቱ አጠቃላይ ምስል ይኖረናል። እስካሁን ያጠናነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይሖዋ አፍቃሪና ፍትሐዊ አምላክ እንደሆነ በአጥጋቢ ሁኔታ እንድንገነዘብ ያደረገን በመሆኑ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መረዳት ቢያዳግተን ወይም ከአምላክ ባሕርይ ጋር እንዴት እንደሚጣጣም ባይገባን ብዙም አንጨነቅም።

      19 እንግዲያው የአምላክን ቃል ለመረዳት አዎንታዊ አመለካከት ይዘን በቅን ልቦና ልናነበውና ልናጠናው ይገባል። ይህ የይሖዋን ታላቅ ጥበብ የሚያሳይ አይደለም? አንዳንድ ምሁራን የሚጽፏቸውን መጻሕፍት አንብበው የሚረዱት ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ብቻ ሊረዱት የሚችሉትን መጽሐፍ መጻፍ የሚችለው ጥበበኛ የሆነው አምላክ ነው!—ማቴዎስ 11:25

      “ጥበብ” የያዘ መጽሐፍ

      20. የተሻለውን የሕይወት ጎዳና ሊነግረን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ሊረዳ የሚችል ምን ነገር ይዟል?

      20 ይሖዋ የተሻለው የሕይወት ጎዳና የቱ እንደሆነ በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል። ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ምን እንደሚያስፈልገን ከእኛ በላይ ያውቃል። የመወደድ፣ ደስታ የማግኘትና ዘላቂ ወዳጅነት የመመሥረት ፍላጎትን ጨምሮ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አሁንም አልተለወጡም። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችን ዓላማ ያለው እንዲሆን የሚረዳ “ጥበብ” የሞላበት መጽሐፍ ነው። (ምሳሌ 2:6) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት አራት ክፍሎች እያንዳንዳቸው ጥበብ ያዘለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንዴት ሥራ ላይ ልናውል እንደምንችል የሚገልጽ ምዕራፍ ይዘዋል፤ ለአብነት ያህል አንድ ምሳሌ እንመልከት።

      21-23. ቁጣንና ቂምን በውስጣችን አምቀን እንዳንይዝ የሚረዳን የትኛው ጥበብ ያዘለ ምክር ነው?

      21 ቂም የሚይዙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን እንደሚጎዱ አስተውለሃል? ቂም ከባድ ሸክም ነው። ቂም ከያዝን እሱን ብቻ የምናብሰለስል ከመሆኑም በላይ ሰላም ይነሳናል፤ እንዲሁም ደስታ ያሳጣናል። ቁጣን አምቆ መያዝ በልብ በሽታም ሆነ በሌሎች ከባድ በሽታዎች የመጠቃት አጋጣሚን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል አንዳንድ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚህ ሳይንሳዊ ጥናቶች ከመካሄዳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል። (መዝሙር 37:8) ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

      22 የአምላክ ቃል የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል፦ “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤ በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል።” (ምሳሌ 19:11) ማስተዋል አንድን ነገር እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ብሎ የማየትና የመመርመር ችሎታ ነው። አንድ ሰው አንድን ነገር የተናገረበትን ወይም ያደረገበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል። ውስጣዊ ዝንባሌውን፣ ስሜቱንና ያለበትን ሁኔታ በትክክል ለመረዳት መጣራችን ስለ እሱ መጥፎ አመለካከት እንዳንይዝ ሊረዳን ይችላል።

      23 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ቆላስይስ 3:13) “እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ” የሚለው አባባል ሊያበሳጨን የሚችለውን ባሕርይ በመቻል ሌሎችን መታገሥ እንዳለብን የሚጠቁም ነው። እንዲህ ያለው ትዕግሥት በትንሽ በትልቁ ቅር እንዳንሰኝ ሊረዳን ይችላል። “ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለው አነጋገር ደግሞ ቅር የተሰኘንበትን ነገር እርግፍ አድርጎ መተውን ያመለክታል። ጥበበኛ የሆነው አምላካችን ይቅር ለማለት የሚያስችል ምክንያት እስካለ ድረስ ሌሎችን ይቅር ማለት እንደሚኖርብን ያውቃል። ይህን የምናደርገው ለእነሱ ጥቅም ብለን ብቻ ሳይሆን ለእኛም የአእምሮ ሰላም ስለሚሰጠን ነው። (ሉቃስ 17:3, 4) የአምላክ ቃል በእርግጥም ጥበብ ያዘለ ነው!

      24. መለኮታዊውን ጥበብ የሕይወታችን መመሪያ የምናደርገው ከሆነ ምን ጥቅም እናገኛለን?

      24 ይሖዋ ያለው ከፍተኛ ፍቅር ሐሳቡን ለሰው ልጆች እንዲገልጽ ገፋፍቶታል። ይህንንም ለማድረግ ከሁሉ የተሻለውን መንገድ ተጠቅሟል፤ ይኸውም ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ መልእክቱን እንዲጽፉ አድርጓል። በመሆኑም የይሖዋ ጥበብ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ላይ ይገኛል። ይህ ጥበብ “እጅግ አስተማማኝ” ነው። (መዝሙር 93:5) ይህን ጥበብ የሕይወታችን መመሪያ አድርገን የምንጠቀምበትና ለሌሎች የምናስተምር ከሆነ ፍጹም ጥበበኛ ወደሆነው አምላካችን ይበልጥ እንቀርባለን። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በመተንበይና ዓላማውን በመፈጸም ረገድ ያለውን የላቀ ጥበብ እንመለከታለን።

      a ለምሳሌ ያህል፣ እረኛ የነበረው ዳዊት በእረኝነት ባሳለፈው ሕይወት የተመለከታቸውን ነገሮች እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። (መዝሙር 23) ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረው ማቴዎስ ገንዘብንና የተለያዩ አኃዞችን በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 17:27፤ 26:15፤ 27:3) ሐኪም የነበረው ሉቃስ ደግሞ የሕክምና እውቀት እንዳለው የሚያሳዩ አገላለጾችን ተጠቅሟል።—ሉቃስ 4:38፤ 14:2፤ 16:20

      b መበለቷ የከተተችው ሁለት ሌፕተን ነበር፤ ሌፕተን በወቅቱ አይሁዳውያን ከሚጠቀሙባቸው ሳንቲሞች ሁሉ በጣም አነስተኛ ዋጋ ነበረው። ሁለት ሌፕተን የአንድ ሰው የቀን ደሞዝ 1/64 ነበሩ። እነዚህ ሁለት ሳንቲሞች በዘመኑ የነበሩት ድሆች ይመገቧት የነበረችውን በጣም ርካሽ የሆነች ወፍ ማለትም አንዲት ድንቢጥ እንኳ መግዛት አይችሉም ነበር።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ምሳሌ 2:1-6 በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ጥበብ ለማግኘት ምን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል?

      • ምሳሌ 2:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ሥራ ላይ ብናውል ምን ጥቅሞች እናገኛለን?

      • ሮም 7:15-25 ይህ ጥቅስ ይሖዋ ቃሉን ለማስጻፍ ሰዎችን መጠቀሙ ጥበብ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      • 1 ቆሮንቶስ 10:6-12 መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላውያንን እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ ከሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ትምህርት እናገኛለን?

  • “በቅዱስ ሚስጥር የተገለጠው . . . የአምላክ ጥበብ”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • አብርሃም በከዋክብት የተሸፈነውን ሰማይ ቀና ብሎ ሲመለከት።

      ምዕራፍ 19

      “በቅዱስ ሚስጥር የተገለጠው . . . የአምላክ ጥበብ”

      1, 2. ትኩረታችንን ሊስብ የሚገባው የትኛው “ቅዱስ ሚስጥር” ነው? ለምንስ?

      ሚስጥር የሆነ ነገር ስለሚያጓጓና ትኩረት ስለሚስብ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሚስጥር መያዝ ይከብዳቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “አንድን ጉዳይ መሰወር ለአምላክ ክብሩ ነው” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 25:2) አዎን፣ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢና ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እሱ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ አንዳንድ ነገሮችን ከሰዎች ሚስጥር አድርጎ የመሰወር መብት አለው።

      2 ሆኖም ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የገለጸው አንድ አስገራሚና ትኩረት የሚስብ ሚስጥር አለ። ይህም “[የአምላክ ፈቃድ] ቅዱስ ሚስጥር” በመባል ይታወቃል። (ኤፌሶን 1:9) ይህ ቅዱስ ሚስጥር ምን እንደሆነ መረዳትህ የማወቅ ጉጉትህን ከማርካት የበለጠ ጥቅም አለው። ለመዳን የሚያስችል አጋጣሚ የሚከፍትልህ ከመሆኑም በላይ ይህ ነው የማይባለውን የይሖዋ ጥበብ በተወሰነ ደረጃ እንድታስተውል ይረዳሃል።

      ደረጃ በደረጃ ተገለጠ

      3, 4. በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ተስፋ የሚፈነጥቀው እንዴት ነው? “ሚስጥር” የሆነው ነገርስ ምንድን ነው?

      3 አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲሠሩ ይሖዋ ምድር ገነት እንድትሆንና ፍጹም በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ለማድረግ የነበረው ዓላማ የከሸፈ መስሎ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ችግሩ እልባት የሚያገኝበትን አቅጣጫ ያስቀመጠው ወዲያውኑ ነው። “በአንተና [በእባቡና] በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ” በማለት ተናግሯል።—ዘፍጥረት 3:15

      4 ይህ መግለጫ ግራ የሚያጋባና እንቆቅልሽ ነበር። ሴቲቱ ማን ነች? እባቡ ማን ነው? የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው “ዘር” ማን ነው? አዳምና ሔዋን የራሳቸውን ግምት ከመስጠት በቀር በትክክል የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ሆኖም አምላክ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ ታማኝ ለሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ተስፋ የሚፈነጥቁ ነበሩ። ጽድቅ ድል ማድረጉና የይሖዋ ዓላማ ዳር መድረሱ የማይቀር ነው። ግን እንዴት? ይህ ሚስጥር ነበር! መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሚስጥር ‘በቅዱስ ሚስጥር የተገለጠ የአምላክ ጥበብ፣ የተሰወረ ጥበብ’ በማለት ይገልጸዋል።—1 ቆሮንቶስ 2:7

      5. ይሖዋ ሚስጥሩን ደረጃ በደረጃ የገለጠው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

      5 ይሖዋ “ሚስጥርን የሚገልጥ” አምላክ ስለሆነ ከዚህ ሚስጥር ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችን መግለጹ አይቀርም። (ዳንኤል 2:28) ሆኖም ይህን የሚያደርገው ደረጃ በደረጃ ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን “እንዴት ነው የተወለድኩት?” ብሎ ቢጠይቀው አባትየው በምን መንገድ እንደሚመልስለት ማሰብ እንችላለን። አስተዋይ የሆነ አባት የሚሰጠው መልስ ከልጁ የመረዳት ችሎታ ጋር የሚመጣጠን ነው። ልጁ እያደገ ሲሄድ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠዋል። በተመሳሳይም ይሖዋ ፈቃዱንና ዓላማውን ለሕዝቦቹ መቼ መግለጽ እንዳለበት ያውቃል።—ምሳሌ 4:18፤ ዳንኤል 12:4

      6. (ሀ) ቃል ኪዳን ወይም ውል ለምን ዓላማ ያገለግላል? (ለ) ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ቃል ኪዳን መግባቱ አስገራሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

      6 ይሖዋ ይህን ሚስጥር የገለጠው እንዴት ነው? የተለያዩ ቃል ኪዳኖችን በመግባት ወይም ውሎችን በመዋዋል ነው። ቤት ለመግዛት ወይም ገንዘብ ለማበደር አሊያም ለመበደር ውል የተዋዋልክባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ውል ለስምምነቱ መፈጸም ሕጋዊ ዋስትና ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከሰዎች ጋር እንዲህ ዓይነት ቃል ኪዳን መግባት ወይም ውል መዋዋል ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይሖዋ አንድን ነገር እንደሚፈጽም መናገሩ ብቻ በቂ ዋስትና ሊሆን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ያም ሆኖ አምላክ በተለያየ ጊዜ፣ የገባው ቃል ሕጋዊ በሆነ ውል የተደገፈ እንዲሆን አድርጓል። እነዚህ ሕጋዊ የሆኑ ውሎች፣ ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።—ዕብራውያን 6:16-18

      ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን

      7, 8. (ሀ) ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ምን ቃል ኪዳን ገባ? ይህስ ቅዱሱ ሚስጥር በተወሰነ ደረጃ እንዲገለጥ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ዘሩ የሚመጣበት የዘር ሐረግ ደረጃ በደረጃ ግልጽ እየሆነ እንዲመጣ ያደረገው እንዴት ነው?

      7 የሰው ልጅ ከገነት ከተባረረ ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ ይሖዋ ታማኝ ለሆነው አገልጋዩ ለአብርሃም “[ዘርህን] በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት . . . በእርግጥ አበዛዋለሁ፤ . . . ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ” ሲል ነግሮታል። (ዘፍጥረት 22:17, 18) እዚህ ላይ ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ ሕጋዊ በሆነ ቃል ኪዳንና በመሐላ አጽንቶታል። (ዘፍጥረት 17:1, 2፤ ዕብራውያን 6:13-15) የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ የሰው ልጆችን ለመባረክ በውል ራሱን ሕጋዊ ግዴታ ውስጥ ማስገባቱ እጅግ የሚያስገርም ነው!

      “ዘርህንም በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት . . . አበዛዋለሁ”

      8 ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን፣ ተስፋ የተደረገበት ዘር ሰው ሆኖ እንደሚመጣ ጠቁሟል፤ ምክንያቱም ይህ ዘር የሚመጣው በአብርሃም በኩል ነው። ይሁን እንጂ ዘሩ ማን ነው? ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ዘሩ ከአብርሃም ልጆች መካከል በይስሐቅ በኩል እንደሚመጣ አስታወቀ። ከይስሐቅ ሁለት ልጆች መካከል ደግሞ ያዕቆብ ተመረጠ። (ዘፍጥረት 21:12፤ 28:13, 14) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ያዕቆብ ከአሥራ ሁለት ወንዶች ልጆቹ መካከል አንዱን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢታዊ ቃል ተናገረ፦ “ሴሎ [ወይም “ባለቤት የሆነው፣” የግርጌ ማስታወሻ] እስኪመጣ ድረስ በትረ መንግሥት ከይሁዳ፣ የአዛዥም በትር ከእግሮቹ መካከል አይወጣም፤ ለእሱም ሕዝቦች ይታዘዙለታል።” (ዘፍጥረት 49:10) ይህ ትንቢት ዘሩ በይሁዳ በኩል እንደሚመጣና ንጉሥ እንደሚሆን የሚጠቁም ነበር።

      ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን

      9, 10. (ሀ) ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ምን ቃል ኪዳን ገብቷል? ይህ ቃል ኪዳንስ ለሕዝቡ ምን ጥበቃ አድርጓል? (ለ) ሕጉ የሰው ልጆች ቤዛ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳየው እንዴት ነው?

      9 በ1513 ዓ.ዓ. ይሖዋ ቅዱሱ ሚስጥር ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን የሚረዳ አንድ ዝግጅት አደረገ። ከአብርሃም ዘሮች ማለትም ከእስራኤል ብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገባ። እርግጥ ነው፣ ይህ የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን በአሁኑ ወቅት ተፈጻሚነቱ አብቅቷል፤ ያም ቢሆን ተስፋ የተደረገበት ዘር እንዲመጣ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። እንዴት? ሦስት መንገዶችን እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ ሕጉ ጥበቃ የሚያደርግ ግድግዳ ሆኖ አገልግሏል። (ኤፌሶን 2:14) በሕጉ ውስጥ የሰፈሩት የጽድቅ ደንቦች፣ እንደ አጥር በመሆን እስራኤላውያን አምላክን ከማያገለግሉት አሕዛብ የተለዩ እንዲሆኑ አድርገዋል። በመሆኑም ይህ ሕግ ተስፋ የተሰጠበት ዘር የሚመጣበት የዘር ሐረግ እንዳይበረዝ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። መሲሑ ከይሁዳ ነገድ የሚወለድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ የእስራኤል ብሔር ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል።

      10 በሁለተኛ ደረጃ ሕጉ የሰው ዘር ቤዛ እንደሚያስፈልገው በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል። ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ፍጹም የሆነውን ይህን ሕግ በተሟላ ሁኔታ ሊጠብቁ እንደማይችሉ በተግባር ታይቷል። በመሆኑም ሕጉ “ቃል የተገባለት ዘር እስኪመጣ ድረስ ሕግ ተላላፊነትን ይፋ ለማድረግ” መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። (ገላትያ 3:19) በሕጉ መሠረት የእንስሳት መሥዋዕት በማቅረብ ጊዜያዊ የሆነ የኃጢአት ስርየት ማግኘት ይቻል ነበር። ይሁንና ጳውሎስ እንደገለጸው “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ [ስለማይችል]” እነዚህ መሥዋዕቶች ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥላ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ። (ዕብራውያን 10:1-4) በመሆኑም ይህ ቃል ኪዳን ታማኝ አይሁዳውያንን “ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ [ሞግዚት]” ሆኗል።—ገላትያ 3:24

      11. የሕጉ ቃል ኪዳን ለእስራኤል ሕዝብ ምን ልዩ አጋጣሚ ከፍቶ ነበር? ሆኖም ሕዝቡ በብሔር ደረጃ ይህ አጋጣሚ ያመለጠው ለምንድን ነው?

      11 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ቃል ኪዳኑ የእስራኤል ሕዝብ ታላቅ መብት ሊያገኝ የሚችልበትን አጋጣሚ ከፍቷል። ይሖዋ ቃል ኪዳኑን እስከጠበቁ ድረስ “የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር” እንደሚሆኑ ነግሯቸዋል። (ዘፀአት 19:5, 6) በኋላም የሰማያዊው የካህናት መንግሥት የመጀመሪያዎቹ አባላት እንዲሆኑ የተመረጡት ሰዎች በሥጋ እስራኤላውያን ናቸው። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ የእስራኤል ሕዝብ በሕጉ ቃል ኪዳን ላይ በማመፁና መሲሐዊውን ዘር አልቀበልም በማለቱ ይህን መብት አጥቷል። ታዲያ የካህናት መንግሥቱን አባላት ቁጥር የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ይህ የተባረከ ሕዝብ ተስፋ ከተደረገበት ዘር ጋር ዝምድና የሚኖረውስ እንዴት ነው? እነዚህ የቅዱሱ ሚስጥር ገጽታዎች አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ግልጽ ይሆናሉ።

      ከዳዊት ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን

      12. ይሖዋ ከዳዊት ጋር ምን ቃል ኪዳን ገብቷል? ይህስ የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር በተወሰነ ደረጃ ግልጽ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው?

      12 ይሖዋ በ11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ሌላ ቃል ኪዳን በገባበት ወቅት ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል። ታማኝ ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት “ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። . . . የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ” በማለት ቃል ገብቶለታል። (2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ መዝሙር 89:3) በዚህም ተስፋ የተደረገበት ዘር በዳዊት የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ ግልጽ ሆነ። ይሁን እንጂ አንድ ተራ ሰው ለዘላለም ሊገዛ ይችላል? (መዝሙር 89:20, 29, 34-36) ደግሞስ አንድ ሰብዓዊ ንጉሥ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ሊታደግ ይችላል?

      13, 14. (ሀ) በመዝሙር 110 ላይ በተገለጸው መሠረት ይሖዋ ለተቀባው ንጉሥ ምን ቃል ገብቷል? (ለ) የይሖዋ ነቢያት ዘሩን በተመለከተ ምን ተጨማሪ መግለጫዎች ሰጥተዋል?

      13 ዳዊት በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሖዋ ጌታዬን ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው። ይሖዋ ‘እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ!’ ሲል ምሏል፤ ደግሞም ሐሳቡን አይለውጥም።” (መዝሙር 110:1, 4) ዳዊት የተናገራቸው ቃላት በቀጥታ የሚያመለክቱት ተስፋ የተደረገበትን ዘር ወይም መሲሕ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:35, 36) ይህ ንጉሥ የሚገዛው በኢየሩሳሌም ሆኖ ሳይሆን በሰማይ በይሖዋ ‘ቀኝ’ ተቀምጦ ነው። ይህም በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር ላይ እንደሚገዛ የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 2:6-8) እዚህ ላይ አምላክ ግልጽ ያደረገው አንድ ሌላም ነገር አለ። ይሖዋ፣ መሲሑ ‘እንደ መልከጼዴቅ ካህን’ እንደሚሆን በመግለጽ ምሏል። በአብርሃም ዘመን ካህንም፣ ንጉሥም ሆኖ እንዳገለገለው እንደ መልከጼዴቅ ሁሉ አስቀድሞ የተነገረለት ዘርም ንጉሥ እና ካህን ሆኖ እንዲያገለግል በቀጥታ በአምላክ ይሾማል።—ዘፍጥረት 14:17-20

      14 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ ቅዱስ ሚስጥሩን በነቢያቱ አማካኝነት ደረጃ በደረጃ አሳውቋል። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ ዘሩ መሥዋዕት ሆኖ እንደሚሞት ገልጿል። (ኢሳይያስ 53:3-12) ሚክያስ መሲሑ የሚወለድበትን ቦታ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሚክያስ 5:2) ዳንኤል ደግሞ ዘሩ የሚገለጥበትንና የሚሞትበትን ጊዜ ሳይቀር ተንብዮአል።—ዳንኤል 9:24-27

      ቅዱሱ ሚስጥር ተገለጠ!

      15, 16. (ሀ) የይሖዋ ልጅ ‘ከሴት ሊወለድ’ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሰብዓዊ ወላጆቹ የወረሰው ነገር ምንድን ነው? በትንቢት የተነገረለት ዘር ሆኖ የተገለጠውስ መቼ ነው?

      15 ዘሩ በምድር ላይ እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ እነዚህ ትንቢቶች እንዴት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ምንም የሚታወቅ ነገር አልነበረም። ገላትያ 4:4 “ዘመኑ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ከሴት የተወለደውን . . . ልጁን ላከ” በማለት ይገልጻል። በ2 ዓ.ዓ. አንድ መልአክ ማርያም ለምትባል አንዲት አይሁዳዊት ድንግል እንዲህ አላት፦ “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል፤ ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና የአምላክ ልጅ ይባላል።”—ሉቃስ 1:31, 32, 35

      16 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማህፀን በማዛወር ከሴት እንዲወለድ አደረገ። ማርያም ፍጽምና የጎደላት ሴት ነበረች። ሆኖም ኢየሱስ “የአምላክ ልጅ” በመሆኑ ከማርያም ኃጢአትን አልወረሰም። በሌላ በኩል ደግሞ የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆች የዳዊት ዘሮች ስለነበሩ የዳዊት ዙፋን ሕጋዊ ወራሽ የመሆን መብት እንዲያገኝ አስችለውታል። (የሐዋርያት ሥራ 13:22, 23) በ29 ዓ.ም. ኢየሱስ ሲጠመቅ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ የቀባው ሲሆን “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:16, 17) በዚህ መንገድ ዘሩ ተገለጠ። (ገላትያ 3:16) ይህ ወቅት ቅዱሱ ሚስጥር ይበልጥ ግልጽ የሚሆንበት ጊዜ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 1:10

      17. በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ የመጣው እንዴት ነው?

      17 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰው እባብ ሰይጣን እንደሆነና የእባቡ ዘር ደግሞ የሰይጣን ተከታዮች እንደሆኑ ገልጿል። (ማቴዎስ 23:33፤ ዮሐንስ 8:44) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰይጣንም ሆነ ዘሮቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጨፈለቁት እንዴት እንደሆነ ተገለጸ። (ራእይ 20:1-3, 10, 15) ሴቲቱ ደግሞ “ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም” ወይም የአምላክ ሚስት እንደሆነች በሌላ አባባል መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል እንደምታመለክት ግልጽ ሆነ።a—ገላትያ 4:26፤ ራእይ 12:1-6

      አዲሱ ቃል ኪዳን

      18. ‘የአዲሱ ቃል ኪዳን’ ዓላማ ምንድን ነው?

      18 ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ከሁሉ አስገራሚው እውነታ ግልጽ የሆነው ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ‘አዲሱ ቃል ኪዳን’ በነገራቸው ጊዜ ነው። (ሉቃስ 22:20) ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ከእሱ በፊት እንደነበረው የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን “የካህናት መንግሥት” የሚያስገኝ ነው። (ዘፀአት 19:6፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ሆኖም በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት የሚቋቋመው ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ብሔር ነው፤ ይህ ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ ሲሆን ታማኝ የሆኑትን ቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮች ብቻ ያቀፈ ነው። (ገላትያ 6:16) በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት እነዚህ ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር በመሆን ለሰው ልጆች በረከት ያስገኛሉ!

      19. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን ለሰው ዘር በረከት የሚያመጣ “የካህናት መንግሥት” ሊያስገኝ የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች “አዲስ ፍጥረት” የተባሉት ለምንድን ነው? በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚያገለግሉትስ ስንት ናቸው?

      19 ሆኖም አዲሱ ቃል ኪዳን ለሰው ዘር በረከት የሚያመጣ “የካህናት መንግሥት” ሊያስገኝ የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አዲሱ ቃል ኪዳን የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በኃጢአታቸው የሚኮንን ሳይሆን ኢየሱስ በከፈለው መሥዋዕት አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። (ኤርምያስ 31:31-34) ይህም በይሖዋ ፊት ጻድቃን ተደርገው እንዲቆጠሩ ያደርጋል፤ በመሆኑም በሰማይ ያለው ቤተሰቡ አባል አድርጎ የሚቀበላቸው ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ ይቀባቸዋል። (ሮም 8:15-17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21) በመሆኑም ‘በሰማይ ተጠብቆ ለሚቆያቸው ሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ይወለዳሉ።’ (1 ጴጥሮስ 1:3, 4) የሰው ልጆች የተፈጠሩት በምድር ላይ እንዲኖሩ ከመሆኑ አንጻር ይህ ተስፋ የተሰጣቸው በመንፈስ የተወለዱ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “አዲስ ፍጥረት” ተብለው ተጠርተዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ሆነው ከኃጢአት የተቤዠውን የሰው ዘር የሚገዙት ሰዎች ቁጥር 144,000 እንደሚሆን ይገልጻል።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4

      20. (ሀ) በ36 ዓ.ም. ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ምን ነገር ተገለጠ? (ለ) ለአብርሃም ቃል የተገባውን በረከት የሚያገኙት እነማን ናቸው?

      20 እነዚህ ቅቡዓን ከኢየሱስ ጋር “የአብርሃም ዘር” ክፍል ሆነዋል።b (ገላትያ 3:29) የዚህ ዘር የመጀመሪያዎቹ አባላት ሥጋዊ አይሁዳውያን ናቸው። ይሁን እንጂ በ36 ዓ.ም. የቅዱሱ ሚስጥር አንድ ሌላ ገጽታ ተገለጠ፤ አሕዛብ ወይም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችም የሰማያዊው ተስፋ ተካፋይ እንደሚሆኑ ታወቀ። (ሮም 9:6-8፤ 11:25, 26፤ ኤፌሶን 3:5, 6) ለአብርሃም ቃል የተገባውን በረከት የሚያገኙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው? የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የተከፈለው ለመላው ዓለም ስለሆነ የዚህ በረከት ተካፋዮች የሚሆኑት ቅቡዓን ብቻ አይደሉም። (1 ዮሐንስ 2:2) ይሖዋ ቁጥራቸው ያልተወሰነ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በሰይጣን ሥርዓት ላይ ከሚደርሰው ጥፋት እንደሚተርፉ በኋላ ላይ ገለጸ። (ራእይ 7:9, 14) ሌሎች ብዙ ሰዎችም ከሞት ተነስተው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ!—ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:11-15፤ 21:3, 4

      የአምላክ ጥበብና ቅዱሱ ሚስጥር

      21, 22. ቅዱሱ ሚስጥር የይሖዋን ጥበብ የሚገልጠው በምን መንገዶች ነው?

      21 ቅዱሱ ሚስጥር “በርካታ ገጽታዎች ያሉት የአምላክ ጥበብ” አስደናቂ መገለጫ ነው። (ኤፌሶን 3:8-10) ይህን ሚስጥር በማዘጋጀትም ሆነ ደረጃ በደረጃ በመግለጥ ይሖዋ ታላቅ ጥበቡን አሳይቷል! ጥበበኛ የሆነው አምላክ የሰዎችን የመረዳት ችሎታ ግምት ውስጥ አስገብቷል፤ ሚስጥሩ የተገለጠው ደረጃ በደረጃ መሆኑ የሰዎች ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዲገለጥም አድርጓል።—መዝሙር 103:14

      22 ይሖዋ ኢየሱስን ንጉሥ አድርጎ መምረጡም ወደር የለሽ ጥበቡን የሚያሳይ ነው። የይሖዋ ልጅ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካለ ከማንኛውም ፍጥረት ይበልጥ እምነት የሚጣልበት ነው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ በኖረበት ዘመን ብዙ ዓይነት መከራዎች ደርሰውበታል። የሰው ልጆች ያሉባቸውን ችግሮች በሚገባ ይረዳል። (ዕብራውያን 5:7-9) ከኢየሱስ ጋር አብረው ስለሚገዙትስ ምን ማለት ይቻላል? ባለፉት መቶ ዘመናት ከተለያዩ ዘሮች፣ ቋንቋዎችና የኑሮ ደረጃዎች የተመረጡ ወንዶችና ሴቶች በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል። በዚህ ቡድን ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ያልደረሰባቸውና ያልተወጡት መከራ የለም ማለት ይቻላል። (ኤፌሶን 4:22-24) በእነዚህ ሩኅሩኅ ነገሥታትና ካህናት አገዛዝ ሥር መኖር ምንኛ አስደሳች ነው!

      23. ከይሖዋ ቅዱስ ሚስጥር ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖች ምን መብት አላቸው?

      23 ሐዋርያው ጳውሎስ “ካለፉት ሥርዓቶችና ካለፉት ትውልዶች አንስቶ ተሰውሮ የቆየው ቅዱስ ሚስጥር . . . [አሁን] ለቅዱሳኑ ተገልጧል” ሲል ጽፏል። (ቆላስይስ 1:26) አዎን፣ በመንፈስ የተቀቡት የይሖዋ ቅዱሳን አገልጋዮች ቅዱሱን ሚስጥር በተመለከተ ብዙ ግንዛቤ ያገኙ ሲሆን ይህንንም እውቀት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች አካፍለዋል። ይሖዋ “የፈቃዱን ቅዱስ ሚስጥር ለእኛ [በማሳወቁ]” ሁላችንም ታላቅ መብት አግኝተናል። (ኤፌሶን 1:9) ሌሎችም ወደር የለሽ የሆነውን የይሖዋ አምላክ ጥበብ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ይህን አስደናቂ ሚስጥር እናካፍላቸው!

      a በተጨማሪም “ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር” በኢየሱስ በኩል ተገልጧል። (1 ጢሞቴዎስ 3:16) ያላንዳች እንከን በታማኝነት ከአምላክ ጎን የሚቆም ሊኖር ይችላል? የሚለው ጥያቄ ለረጅም ጊዜ መልስ ሳያገኝ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል። ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ አስገኝቷል። የሰይጣንን ፈተናዎች ሁሉ በመቋቋም በታማኝነት ጸንቷል።—ማቴዎስ 4:1-11፤ 27:26-50

      b በተጨማሪም ኢየሱስ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ‘የመንግሥት ቃል ኪዳን’ ገብቷል። (ሉቃስ 22:29, 30) ኢየሱስ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል ሆነው በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲገዙ ከዚህ “ትንሽ መንጋ” ጋር ውል የተዋዋለ ያህል ነው።—ሉቃስ 12:32

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዮሐንስ 16:7-12 ኢየሱስ እውነትን ደረጃ በደረጃ በመግለጥ ረገድ የአባቱን ምሳሌ የኮረጀው እንዴት ነው?

      • 1 ቆሮንቶስ 2:6-16 ብዙዎች የይሖዋን ቅዱስ ሚስጥሮች መረዳት የማይችሉት ለምንድን ነው? እኛስ እነዚህን ሚስጥሮች መረዳት የምንችለው እንዴት ነው?

      • ኤፌሶን 3:10 በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ከአምላክ ቅዱስ ሚስጥር ጋር በተያያዘ ምን መብት አግኝተዋል?

      • ዕብራውያን 11:8-10 በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ስለ ቅዱሱ ሚስጥር ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ባይኖራቸውም እንኳ ይህ ቅዱስ ሚስጥር እምነት እንዲኖራቸው የረዳቸው እንዴት ነው?

  • “ጥበበኛ ልብ አለው”—ግን ትሑት ነው
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • አንድ አባት በርከክ ብሎ ልጁን በፍቅር ዓይን እየተመለከተው።

      ምዕራፍ 20

      “ጥበበኛ ልብ አለው”—ግን ትሑት ነው

      1-3. ይሖዋ ትሑት ነው ብለን በእርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

      አንድ አባት ለትንሽ ልጁ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ማስተማር ፈለገ እንበል። ልጁ ትምህርቱን ከልቡ ሊቀበል የሚችለው አባትየው በምን መንገድ ቢያነጋግረው ነው? ልጁን ቁልቁል እያየ ቢያፈጥበትና ቢጮኽበት ነው ወይስ በርከክ ብሎ በፍቅርና በለሰለሰ አንደበት ቢያነጋግረው? ጥበበኛና ትሑት የሆነ አባት ልጁን በደግነት ማነጋገር እንደሚመርጥ የታወቀ ነው።

      2 ይሖዋ ምን ዓይነት አባት ነው? ትዕቢተኛና ኃይለኛ ነው ወይስ ትሑትና ገር? ይሖዋ ሁሉን የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ ወደር የለሽ ጥበብ ያለው አምላክ ነው። ይሁን እንጂ እውቀትና ጥበብ በራሱ ሰዎች ትሑት እንዲሆኑ እንደማያደርግ አስተውለህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እውቀት ያስታብያል” ሲል ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 3:19፤ 8:1) ሆኖም “ጥበበኛ ልብ” ያለው ይሖዋ ትሑት ነው። (ኢዮብ 9:4) ይሖዋ ትሑት ነው የሚለው አባባል ቦታውን ወይም ታላቅነቱን ዝቅ የሚያደርግ ሳይሆን ፈጽሞ የትዕቢት ባሕርይ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

      3 ይሖዋ ቅዱስ ነው። ትዕቢት የሚያረክስ በመሆኑ ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ሊኖረው አይችልም። (ማርቆስ 7:20-22) በተጨማሪም ነቢዩ ኤርምያስ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “አንተ በእርግጥ ታስታውሳለህ፤ እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለህ” ብሏል።a (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:20) የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ፍጽምና የጎደለውን ኤርምያስን ለመርዳት ሲል ወደ እሱ ‘ለማጎንበስ’ ወይም ዝቅ ለማለት ፈቃደኛ መሆኑ የሚያስገርም ነው! (መዝሙር 113:7) አዎን፣ ይሖዋ ትሑት ነው። ሆኖም አምላክ ትሑት ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ትሕትና ከጥበብ ጋር ምን ዝምድና አለው? ይህስ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      ይሖዋ ትሑት መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      4, 5. (ሀ) ትሕትና ምንድን ነው? በየትኞቹ ባሕርያትስ ይንጸባረቃል? የድክመት ወይም የፍርሃት ምልክት ተደርጎ ሊታይ የማይገባውስ ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከዳዊት ጋር በነበረው ግንኙነት ትሕትናን ያሳየው እንዴት ነው? የይሖዋ ትሕትና ለእኛ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

      4 ትሕትና ማለት ራስን ከፍ አድርጎ አለመመልከት እንዲሁም ከእብሪትና ከኩራት መራቅ ማለት ነው። ይህ ባሕርይ የውስጣዊ ማንነት መገለጫ ሲሆን እንደ ገርነት፣ ትዕግሥትና ምክንያታዊነት ባሉት ባሕርያት ይንጸባረቃል። (ገላትያ 5:22, 23) ይሁን እንጂ እነዚህ አምላካዊ ባሕርያት፣ የድክመት ወይም የፍርሃት ምልክት ተደርገው መታየት የለባቸውም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት ስላሉት የጽድቅ ቁጣ አይቆጣም ወይም አስፈላጊ ሲሆን የማጥፋት ኃይሉን አይጠቀምም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትሕትናውና ገርነቱ፣ ራሱን ፍጹም በሆነ ሁኔታ መቆጣጠር እንደሚችልና ታላቅ ኃይሉን ምንጊዜም በትክክለኛው መንገድ እንደሚጠቀምበት የሚያሳይ ነው። (ኢሳይያስ 42:14) ይሖዋ ትሑት መሆኑ ጥበበኛ እንደሆነም የሚያሳይ ነው፤ እንዴት? ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ የሚሰጥ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “ትሕትና . . . ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ባሕርይ ሲሆን የጥበብ ሁሉ መሠረት ነው” ሲል ገልጿል። እንግዲያው እውነተኛ ጥበብና ትሕትና የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። የይሖዋ ትሕትና የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      ጥበበኛ የሆነ አባት ልጆቹን የሚይዘው በትሕትናና በገርነት ነው

      5 ንጉሥ ዳዊት “የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤ ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል፤ ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል” በማለት ለይሖዋ ዘምሯል። (መዝሙር 18:35) ይሖዋ ይህን ፍጽምና የጎደለው ሰው በየዕለቱ ለመንከባከብና ለመጠበቅ ሲል ራሱን ዝቅ ያደረገ ያህል ነበር። ዳዊት መዳን ማግኘት ብሎም ታላቅ ንጉሥ መሆን የሚችለው ይሖዋ በዚህ መንገድ ራሱን ዝቅ ለማድረግ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቧል። በእርግጥም ይሖዋ በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ እንደ አንድ አፍቃሪና ገር አባት ባይዘን ኖሮ የመዳን ተስፋ ይኖረን ነበር?

      6, 7. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ አምላክ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ የማናገኘው ለምንድን ነው? (ለ) በገርነትና በጥበብ መካከል ምን ዝምድና አለ? በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነንስ ማን ነው?

      6 በትሕትናና ልክን በማወቅ መካከል ልዩነት እንዳለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ልክን ማወቅ፣ ታማኝ ሰዎች ሊያዳብሩት የሚገባ ግሩም ባሕርይ ነው። እንደ ትሕትና ሁሉ ይህ ባሕርይም ከጥበብ ጋር ዝምድና አለው። ምሳሌ 11:2 “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” በማለት ይገልጻል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ አምላክ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸበት ቦታ አናገኝም። ለምን? ልክን ማወቅ የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አቅምንና ገደብን አምኖ መቀበልን ለማመልከት ነው። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የራሱን የጽድቅ መሥፈርቶች ለመጠበቅ ሲል በራሱ ላይ ገደብ ያበጃል እንጂ ምንም ዓይነት ገደብ የለበትም። (ማርቆስ 10:27፤ ቲቶ 1:2) ከዚህም በተጨማሪ ልዑል አምላክ እንደመሆኑ መጠን የማንም ተገዢ አይደለም። ስለዚህ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ አምላክ ነው ሊባል አይችልም።

      7 ይሁን እንጂ ይሖዋ ትሑትና ገር ነው። አገልጋዮቹም ገርነት ለእውነተኛ ጥበብ ወሳኝ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከጥበብ የመነጨ ገርነት’ ስለማሳየት ይናገራል።b (ያዕቆብ 3:13) ይሖዋ በዚህ ረገድ የተወውን ግሩም ምሳሌ እስቲ እንመልከት።

      ይሖዋ ለሌሎች ኃላፊነት ይሰጣል እንዲሁም ያዳምጣቸዋል

      8-10. (ሀ) ይሖዋ ኃላፊነት ለመስጠትና ሌሎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ ከመላእክቱ ጋር ባለው ግንኙነት ትሕትናን ያሳየው እንዴት ነው?

      8 ይሖዋ ኃላፊነት ለመስጠትና የሌሎችን ሐሳብ ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ ትሕትናውን የሚያሳይ ግሩም ማስረጃ ነው። እርዳታ ወይም ምክር የሚያስፈልገው አምላክ ባለመሆኑ ሌሎችን ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ በጣም የሚያስገርም ነው። (ኢሳይያስ 40:13, 14፤ ሮም 11:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በዚህ መንገድ ትሑት መሆኑን ያሳየባቸውን በርካታ አጋጣሚዎች ይጠቅሳል።

      9 ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም በአንድ ወቅት ያጋጠመውን አስገራሚ ሁኔታ ተመልከት። ሦስት እንግዶች ወደ ቤቱ መጥተው የነበረ ሲሆን አብርሃም ከእነዚህ መካከል አንዱን “ይሖዋ” ሲል ጠርቶታል። በእርግጥ እንግዶቹ መላእክት ነበሩ፤ ከመካከላቸው አንዱ ግን ይሖዋን ወክሎ በይሖዋ ስም የመጣ ነበር። በመሆኑም መልአኩ አብርሃምን ሲያነጋግረው ይሖዋ እያነጋገረው ያለ ያህል ነበር። በዚህ መልአክ አማካኝነት ይሖዋ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት” ታላቅ እንደሆነ ለአብርሃም ገለጸለት። አክሎም “ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ። ነገሩ እንደዚያ ካልሆነም ማወቅ እችላለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 18:3, 20, 21) እንዲህ ሲባል ግን ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ራሱ ‘ወርዶ’ በሰዶምና በገሞራ የነበረውን ሁኔታ ይመለከታል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን እንዲያጣሩ መላእክትን ልኳል። (ዘፍጥረት 19:1) ለምን? ሁሉን ማየት የሚችለው ይሖዋ በእነዚህ ከተሞች ያለውን ሁኔታ ራሱ “ማወቅ” አይችልም ነበር? እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ ትሑት ስለሆነ እነዚህ መላእክት ሁኔታውን እንዲያጣሩና በሰዶም የነበረውን የሎጥ ቤተሰብ እንዲያነጋግሩ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል።

      10 በተጨማሪም ይሖዋ ሌሎች የሚሰጡትን ሐሳብ ይሰማል። በአንድ ወቅት፣ ክፉ የሆነውን ንጉሥ አክዓብን ለማጥፋት ባሰበ ጊዜ መላእክቱ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ ጠይቋቸው ነበር። ይሖዋ የሌሎች ምክር እንደማያስፈልገው የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ አንድ መልአክ ያቀረበውን ሐሳብ በመቀበል ያንኑ ሐሳብ እንዲያስፈጽም ተልእኮ ሰጠው። (1 ነገሥት 22:19-22) ይህ ሁኔታ ይሖዋ ምን ያህል ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ አይደለም?

      11, 12. አብርሃም ይሖዋ ትሑት መሆኑን የተገነዘበው እንዴት ነው?

      11 ይሖዋ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች እንኳ የሚያሳስባቸውን ነገር ሲገልጹ ለመስማት ፈቃደኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት እንዳሰበ በነገረው ጊዜ ታማኙ አብርሃም ግራ ተጋብቶ ነበር። አብርሃም “ይህ በአንተ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?” በማለት ተናገረ። ‘በከተሞቹ ውስጥ 50 ጻድቃን ቢገኙ ስፍራውን አትምርም?’ ሲል ይሖዋን ጠየቀው። ይሖዋም ይህ ቢሆን ከተሞቹን እንደማያጠፋቸው አረጋገጠለት። ሆኖም አብርሃም ቁጥሩን ወደ 45፣ ወደ 40 እና ከዚያም በታች ዝቅ በማድረግ መጠየቁን ቀጠለ። ይሖዋ በተደጋጋሚ ማረጋገጫ ቢሰጠውም አብርሃም ቁጥሩ አሥር እስኪደርስ ድረስ መጠየቁን አላቆመም። አብርሃም ይሖዋ ምን ያህል መሐሪ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አልተረዳ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ፣ ወዳጁና አገልጋዩ የሆነው አብርሃም ያሳሰበውን ጉዳይ ሲናገር በትዕግሥትና በትሕትና አዳምጦታል።—ዘፍጥረት 18:23-33

      12 ከፍተኛ እውቀት ካላቸው ምሁራን መካከል ተራ ሰዎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ በትዕግሥት ለመስማት ፈቃደኞች የሚሆኑት ስንቶቹ ናቸው?c አምላካችን ግን እንዲህ በማድረግ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። አብርሃም ከአምላክ ጋር ባደረገው በዚህ ውይይት ይሖዋ “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑንም ተገንዝቧል። (ዘፀአት 34:6) አብርሃም ልዑሉ አምላክ በሚወስደው እርምጃ ላይ ጥያቄ የማንሳት መብት እንደሌለው ተገንዝቦ ሳይሆን አይቀርም፣ “ይሖዋ እባክህ፣ አትቆጣ” ሲል ሁለት ጊዜ ተማጽኗል። (ዘፍጥረት 18:30, 32) በእርግጥ አብርሃም ባነሳው ጥያቄ ይሖዋ አልተቆጣም። ‘ከጥበብ የመነጨ ገርነት’ አንጸባርቋል።

      ይሖዋ ምክንያታዊ ነው

      13. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ምክንያታዊ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? ይህ ቃል ይሖዋን በሚገባ ይገልጸዋል የምንለውስ ለምንድን ነው?

      13 ይሖዋ ትሑት መሆኑን የሚያሳየው ሌላው ግሩም ባሕርይ ምክንያታዊነቱ ነው። የሚያሳዝነው ግን ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ይህ ባሕርይ ይጎድላቸዋል። ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ የሚያቀርቡትን ሐሳብ ለመስማት ብቻ ሳይሆን ከጽድቅ ሥርዓቶቹ ጋር የሚጋጭ እስካልሆነ ድረስ ሐሳባቸውን ለመቀበልም ፈቃደኛ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ምክንያታዊ” የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እሺ ብሎ መቀበል” ማለት ነው። ይህ ባሕርይም ቢሆን የመለኮታዊ ጥበብ መለያ ነው። ያዕቆብ 3:17 “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ምክንያታዊ” እንደሆነ ይገልጻል። ወደር የለሽ ጥበብ ያለው ይሖዋ ምክንያታዊ የሆነው በምን መንገድ ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው የማስተናገድ ልዩ ችሎታ አለው። ስሙ ራሱ እንደሚጠቁመው ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። (ዘፀአት 3:14) ይህ ሁኔታ ይሖዋ የተለያዩ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው የሚያስተናግድ ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም?

      14, 15. ሕዝቅኤል የይሖዋን ሰማያዊ ሠረገላ በተመለከተ ያየው ራእይ ስለ ይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ምን ያስተምረናል? ይህ ድርጅት ከሰብዓዊ ድርጅቶች የሚለየውስ እንዴት ነው?

      14 ይሖዋ የተለያዩ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው የሚያስተናግድ አምላክ መሆኑን እንድንገነዘብ የሚረዳ አንድ ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አለ። ነቢዩ ሕዝቅኤል መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል የሚያሳይ አንድ ራእይ ተመልክቶ ነበር። በራእዩ ላይ እጅግ ግዙፍ የሆነ አስገራሚ ሠረገላ ማለትም ይሖዋ ምንጊዜም የሚቆጣጠረውን “ተሽከርካሪ” ተመለከተ። ይህ ሠረገላ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። የሠረገላው ትላልቅ መንኮራኩሮች በአራቱም ጎን መሄድ የሚችሉና ዙሪያቸውን በዓይን የተሞሉ ናቸው፤ ስለዚህ በየትኛውም አቅጣጫ ማየት የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ መቆም ወይም መዞር ሳያስፈልጋቸው በቅጽበት አቅጣጫቸውን መቀየር ይችላሉ። በተጨማሪም ይህ ግዙፍ ሠረገላ ሰዎች እንደሚሠሯቸው ከባድ መኪኖች አይንቀራፈፍም። በመብረቅ ፍጥነት እየተጓዘም እንኳ ዘጠና ዲግሪ መታጠፍ ይችላል! (ሕዝቅኤል 1:1, 14-28) አዎን፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተለያዩ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው እንደሚያስተናግድ ሁሉ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ድርጅቱም በየጊዜው የሚፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎች እንደ አስፈላጊነቱ ማስተናገድ ይችላል።

      15 የሰው ልጆች ይህን ልዩ የይሖዋ ችሎታ ሙሉ በሙሉ ሊኮርጁ አይችሉም። እንዲያውም በአብዛኛው ሲታይ የሰው ልጆችም ሆኑ ድርጅቶቻቸው ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታ የላቸውም፤ እንዲሁም ምክንያታዊነትና እሺ ባይነት ይጎድላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ወይም አንድ ዕቃ ጫኝ ባቡር ግዝፈታቸውና ጉልበታቸው በጣም ሊያስገርመን ይችላል። ሆኖም ድንገተኛ ለውጥ የሚጠይቅ ክስተት ቢፈጠር ሁኔታውን ለመወጣት ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይችላሉ? ባቡሩ በሐዲዱ ላይ አንድ ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥመው አቅጣጫውን ሊቀይር እንደማይችል የታወቀ ነው። ወዲያውኑ ባቡሩን ማቆምም የማይቻል ነገር ነው። አንድ ግዙፍ ዕቃ ጫኝ ባቡር ፍሬኑ ከተያዘ በኋላ እንኳ ሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ ሊሄድ ይችላል! በተመሳሳይም አንድ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ሞተሩ ከጠፋ በኋላ ስምንት ኪሎ ሜትር ሊጓዝ ይችላል። መርከቡ የኋላ ማርሽ ከገባለትም በኋላ እንኳ ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ፊት ሊሄድ ይችላል! በአብዛኛው ግትርነት የሚንጸባረቅባቸው ሰብዓዊ ድርጅቶች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ብዙውን ጊዜ የሰው ልጆች ኩራት ስላለባቸው አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ ነገሮችን እንደ ሁኔታው ለማስተናገድ ፈቃደኞች አይሆኑም። እንዲህ ያለው ግትር አቋም የተለያዩ ድርጅቶችን ኪሳራ ላይ ከመጣሉም በላይ መንግሥታትን ለውድቀት ዳርጓል። (ምሳሌ 16:18) ይሖዋም ሆነ ድርጅቱ ከዚህ ፈጽሞ የተለዩ መሆናቸው እንዴት የሚያስደስት ነው!

      ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      16. ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት ለሎጥ ያደረገለት ነገር ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      16 በሰዶምና በገሞራ ላይ ስለደረሰው ጥፋት እስቲ እንደገና እንመልከት። የይሖዋ መልአክ “ወደ ተራራማው አካባቢ ሽሽ!” የሚል ግልጽ መመሪያ ለሎጥና ለቤተሰቡ ሰጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ሎጥ ይህ መመሪያ ስለከበደው “እባክህ ይሖዋ፣ ወደዚያስ አልሂድ!” ሲል ለመነ። ሎጥ ወደ ተራራው ቢሸሽ ሊሞት እንደሚችል ስለተሰማው እሱና ቤተሰቡ በአቅራቢያቸው ወደምትገኝ ዞአር ወደምትባል ከተማ መሸሽ እንዲፈቀድላቸው ተማጸነ። ይሖዋ ይህችን ከተማ ለማጥፋት አስቦ ነበር። ሎጥም ቢሆን ‘እሞታለሁ’ ብሎ የሚፈራበት አጥጋቢ ምክንያት አልነበረውም። ሎጥ ወደ ተራራው ቢሸሽ ይሖዋ በዚያ ጥበቃ እንደሚያደርግለት የተረጋገጠ ነው! ያም ሆኖ ይሖዋ የሎጥን ልመና እሺ ብሎ ተቀበለ። መልአኩ ሎጥን “እሺ ይሁን፣ ያልካትን ከተማ ባለማጥፋት አሁንም አሳቢነት አሳይሃለሁ” አለው። (ዘፍጥረት 19:17-22) ይህ ሁኔታ ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳይ አይደለም?

      17, 18. ስለ ነነዌ ሰዎች የሚገልጸው ዘገባ ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      17 በተጨማሪም ይሖዋ ከልብ ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች ምንጊዜም ምሕረት በማሳየት ሊወስድ ባሰበው እርምጃ ላይ ተገቢውን ማስተካከያ ያደርጋል። ነቢዩ ዮናስ በክፋትና በግፍ ወደተሞላችው የነነዌ ከተማ በተላከ ጊዜ ምን ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር አስታውስ። ዮናስ በነነዌ ጎዳናዎች እየተዘዋወረ ‘ታላቂቱ ከተማ በ40 ቀን ውስጥ ትጠፋለች’ በማለት ከአምላክ የተቀበለውን መልእክት አወጀ። ይሁን እንጂ ሁኔታዎቹ ድንገት ተለወጡ። የነነዌ ሰዎች ንስሐ ገቡ!—ዮናስ ምዕራፍ 3

      18 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ያደረገውን ነገር ዮናስ ከሰጠው ምላሽ ጋር ማነጻጸሩ ጠቃሚ ነው። ይሖዋ ሰዎቹ ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ፣ “ኃያል ተዋጊ” በመሆን ሊወስደው የነበረውን እርምጃ በመተው ይቅር ባይ ሆነ።d (ዘፀአት 15:3) በአንጻሩ ግን ዮናስ ምሕረት ከማሳየት ይልቅ ግትር አቋም ይዞ ነበር። እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ መሆን ሲገባው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መርከብ ወይም ባቡር አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ተቸግሮ ነበር። ጥፋት ይመጣል ብሎ አውጇል፣ ስለዚህ ጥፋት መምጣት አለበት! ይሁን እንጂ ይሖዋ በትዕግሥት ለዮናስ አንድ የማይረሳ ትምህርት ሰጠው፤ ዮናስን ምክንያታዊና መሐሪ መሆን እንደሚያስፈልገው አስገነዘበው።—ዮናስ ምዕራፍ 4

      አንድ ወጣት በዕድሜ የገፉ አንድን ወንድምን አገልግሎት ላይ በደስታ ሲረዳቸው።

      ይሖዋ ምክንያታዊ አምላክ በመሆኑ አቅማችንን ያውቃል

      19. (ሀ) ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ምሳሌ 19:17 ይሖዋ “ጥሩና ምክንያታዊ” ጌታ እንዲሁም ትሑት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      19 ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገርም ምክንያታዊ ነው። ንጉሥ ዳዊት “እሱ እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 103:14) ይሖዋ አቅማችንንና ያለብንን ጉድለት ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል። ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥሩና ምክንያታዊ” የሆኑ ሰብዓዊ ጌቶችን ‘በቀላሉ ከማይደሰቱ’ ጌቶች ጋር ያነጻጽራል። (1 ጴጥሮስ 2:18) ይሖዋ ምን ዓይነት ጌታ ነው? ምሳሌ 19:17 “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል” በማለት ይገልጻል። በመሆኑም ይሖዋ አገልጋዮቹ ለችግረኞች የሚያደርጉትን እያንዳንዱን መልካም ነገር የሚያስተውል ጥሩና ምክንያታዊ ጌታ ነው። የሚያስገርመው ደግሞ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ፣ እንዲህ ያለውን ቸርነት የሚያደርጉ ሰዎች ለእሱ እንዳበደሩት አድርጎ የሚቆጥር መሆኑ ነው! ይህም ይሖዋ ምን ያህል ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

      20. ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማና መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      20 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ካሉት አገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነትም ገርና ምክንያታዊ ነው። በእምነት የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል። መላእክትን ልኮ እንዲያነጋግሩን ባያደርግም እንኳ ለጸሎታችን መልስ እንደማይሰጥ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ ከእስር እንዲፈታ ‘መጸለያቸውን እንዲቀጥሉ’ በጠየቀበት ወቅት “ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ” ብሏቸው እንደነበር አስታውስ። (ዕብራውያን 13:18, 19) ስለዚህ ይሖዋ ባንጸልይ ኖሮ የማያደርገውን ነገር ስለጸለይን ብቻ ለማድረግ ሊነሳሳ ይችላል።—ያዕቆብ 5:16

      21. የይሖዋን ትሕትና በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ልንደርስ አይገባም? ስለ ይሖዋ ትሕትና ምን ይሰማሃል?

      21 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ገር፣ ታጋሽና ምክንያታዊ በመሆን እንዲሁም ሌሎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ በመስማት ትሕትና ያሳያል ሲባል ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር የሚጋጭ ነገር ያደርጋል ማለት አይደለም። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የይሖዋን የሥነ ምግባር ሕግጋት በማላላት የመንጎቻቸውን ጆሮ የሚኮረኩረውን ነገር ሲያስተምሩ ምክንያታዊነት እያሳዩ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:3) ይሁን እንጂ ሰዎች ከራሳቸው ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ነገር ለማድረግ ሲሉ የአምላክን ሕግጋት ለማላላት የሚያደርጉት ጥረት አምላክ ከሚያሳየው ምክንያታዊነት ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም። ይሖዋ ቅዱስ አምላክ ስለሆነ የጽድቅ መሥፈርቶቹን በምንም መንገድ አያላላም። (ዘሌዋውያን 11:44) እንግዲያው የይሖዋ ምክንያታዊነት ትሕትናውን የሚያሳይ በመሆኑ ልናደንቀው ይገባል። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ የሆነው አምላክ ትሑት መሆኑን ማወቅህ እጅግ አያስደስትህም? ይሖዋ አስፈሪ ግርማ ያለው ቢሆንም ገር፣ ታጋሽና ምክንያታዊ አምላክ ነው። እንዲህ ወዳለው አምላክ መቅረብ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

      a የጥንት ገልባጮች (ሶፌሪም) ይህን ጥቅስ ሲገለብጡ ወደ ታች ያጎነበሰው ይሖዋ ሳይሆን ኤርምያስ እንደሆነ አድርገው ጽፈዋል። በዚህ መንገድ የጻፉት አምላክ እንዲህ ያለውን ትሕትና የሚጠይቅ ድርጊት ይፈጽማል ብለው መጻፍ ተገቢ እንደሆነ ስላልተሰማቸው መሆን አለበት። በዚህም የተነሳ ይህ ግሩም ጥቅስ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ በትክክል ሳይተረጎም ቀርቷል። ይሁን እንጂ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ኤርምያስ “አስበኝ፣ አቤቱ አስበኝ፣ ወደ እኔም ጎንበስ በል” ሲል አምላክን እንደተማጸነ በመግለጽ ይህን ጥቅስ በትክክል ተርጉሞታል።

      b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “ከጥበብ የሚመነጭ ትሕትና” እና “የጥበብ መለያ የሆነው ገርነት” በማለት ተርጉመውታል።

      c መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥትን ከትዕቢት ጋር ያነጻጽራል። (መክብብ 7:8) የይሖዋ ትዕግሥት፣ ትሑት መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:9

      d መዝሙር 86:5 ላይ ይሖዋ “ጥሩ . . . ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ” ተብሏል። ይህ መዝሙር ወደ ግሪክኛ ሲተረጎም ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሚለው ሐረግ ኤፒኢኪስ ወይም “ምክንያታዊ” ተብሎ ተተርጉሟል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዘፀአት 32:9-14 ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አስመልክቶ ልመና ባቀረበበት ወቅት ይሖዋ ያደረገው ነገር ትሕትናውን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      • መሳፍንት 6:36-40 ይሖዋ፣ ጌድዮን ላቀረበው ጥያቄ የሰጠው መልስ ትዕግሥቱንና ምክንያታዊነቱን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      • መዝሙር 113:1-9 ይሖዋ ለሰዎች የሚያደርገው ነገር ትሕትናውን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      • ሉቃስ 1:46-55 ማርያም፣ ይሖዋ ትሑት ለሆኑና ዝቅ ላሉ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ተገንዝባ ነበር? በዚህ ረገድ ልንመስለው የምንችለውስ እንዴት ነው?

  • ኢየሱስ ‘ከአምላክ የመጣውን ጥበብ’ ገልጧል
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ሲያስተምር።

      ምዕራፍ 21

      ኢየሱስ ‘ከአምላክ የመጣውን ጥበብ’ ገልጧል

      1-3. ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት የአገሩ ሰዎች ላስተማረው ትምህርት ምን ምላሽ ሰጡ? ያልተገነዘቡትስ ነገር ምን ነበር?

      አድማጮቹ በትምህርቱ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ ፈዘው ያዳምጡታል። ወጣቱ ኢየሱስ በምኩራብ ውስጥ ቆሞ እያስተማረ ነው። ኢየሱስ እዚያው ከተማ ውስጥ ያደገና በአናጺነት ሲሠራ የቆየ በመሆኑ ለአድማጮቹ እንግዳ ሰው አልነበረም። እንዲያውም አንዳንዶቹ እሱ ባነጻቸው ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ወይም እሱ በሠራው ሞፈርና ቀንበር የሚገለገሉ ሊሆኑ ይችላሉ።a ይሁንና አናጺ የነበረው ይህ ሰው ፊታቸው ቆሞ ሲያስተምር ምን ተሰምቷቸው ይሆን?

      2 ሲያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ “ይህ ሰው ይህን ጥበብ . . . ከየት አገኘ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ “ይህ አናጺው የማርያም ልጅ . . . አይደለም?” ሲሉም አክለው ተናግረዋል። (ማቴዎስ 13:54-58፤ ማርቆስ 6:1-3) የሚያሳዝነው፣ ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት የአገሩ ሰዎች ‘ይህ ሰው የምናውቀው ተራ አናጺ አይደል እንዴ?’ በማለት ናቁት። በጥበቡ ቢገረሙም አልተቀበሉትም። ይህ ጥበብ ከራሱ የመነጨ እንዳልሆነ አልተገነዘቡም ነበር።

      3 እውነት ግን ኢየሱስ ይህን ጥበብ ያገኘው ከየት ነው? “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ለእኛ ከአምላክ የመጣ ጥበብ . . . ሆኖልናል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 1:30) የይሖዋ ጥበብ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት ተገልጧል። በመሆኑም ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ መናገር ችሏል። (ዮሐንስ 10:30) ኢየሱስ ‘ከአምላክ የመጣውን ጥበብ’ የገለጠባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመርምር።

      ያስተማረው ትምህርት

      4. (ሀ) የኢየሱስ መልእክት ዋነኛ ጭብጥ ምን ነበር? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ምክር ምንጊዜም ተግባራዊና አድማጮቹን የሚጠቅም የሆነው ለምንድን ነው?

      4 በመጀመሪያ ኢየሱስ ምን እንዳስተማረ እንመርምር። የመልእክቱ ዋና ጭብጥ ‘የአምላክ መንግሥት ምሥራች’ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ይህ መንግሥት የይሖዋን ስም በማስቀደስ፣ ጻድቅ ገዢ መሆኑን በማረጋገጥና ለሰው ዘር ዘላቂ በረከት በማስገኘት ረገድ ትልቅ ሚና ስለሚጫወት የመልእክቱ ዋነኛ ጭብጥ መሆኑ ተገቢ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ለዕለታዊ ሕይወት የሚጠቅሙ ምክሮችን ያዘለ ነው። በትንቢት በተነገረለት መሠረት “ድንቅ መካሪ” መሆኑን አስመሥክሯል። (ኢሳይያስ 9:6) ደግሞስ ምክሩ ድንቅ መሆኑ ምን ያስገርማል? ስለ አምላክ ቃልና ፈቃድ ጥልቅ እውቀት ያለው ከመሆኑም በላይ የሰዎችን ተፈጥሮ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ከዚህም በተጨማሪ ለሰዎች ከፍተኛ ፍቅር አለው። በመሆኑም ምክሩ ምንጊዜም ተግባራዊና አድማጮቹን የሚጠቅም ነው። ኢየሱስ ያስተማረው “የዘላለም ሕይወት ቃል” ነው። አዎን፣ ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ መዳን ያስገኛል።—ዮሐንስ 6:68

      5. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ከጠቀሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

      5 የተራራው ስብከት፣ ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ወደር የለሽ ጥበብ የተንጸባረቀበት መሆኑን የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ከማቴዎስ 5:3 እስከ 7:27 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ስብከት ከ20 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ሊቀርብ ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ የተራራ ስብከት ውስጥ የሚገኘው ምክር፣ ጊዜ የማይሽረው በመሆኑ በዚያን ጊዜ ጠቃሚ የነበረውን ያህል ዛሬም ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር (5:23-26, 38-42፤ 7:1-5, 12)፣ በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆን (5:27-32) እንዲሁም ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት (6:19-24፤ 7:24-27) እንዴት እንደሚቻል የሚገልጹ ሐሳቦችን ጨምሮ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ጠቅሷል። ሆኖም ኢየሱስ ጥበብ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ በመናገር ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ማስረጃ በማቅረብ አሳማኝ በሆነ መንገድ አብራርቶላቸዋል።

      6-8. (ሀ) ኢየሱስ ጭንቀትን ማስወገድ እንደሚገባ ለማስገንዘብ ምን አሳማኝ ምክንያቶችን ጠቅሷል? (ለ) የኢየሱስ ምክር አምላካዊ ጥበብ ያዘለ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

      6 ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ ስለ ቁሳዊ ነገሮች መጨነቅን አስመልክቶ የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር እንመልከት። ኢየሱስ “ስለ ሕይወታችሁ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ” ሲል ምክር ሰጥቷል። (ቁጥር 25) ምግብና ልብስ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ስለሆኑ እነዚህን ነገሮች ስለማግኘት ማሰብ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች “አትጨነቁ” ብሎናል።b ለምን?

      7 ኢየሱስ ይህን ጉዳይ አሳማኝ በሆነ መንገድ እንዴት እንዳስረዳ ተመልከት። ሕይወታችንንና አካላችንን የሰጠን ይሖዋ ሕይወታችንን ለማቆየት የሚያስችል ምግብና ሰውነታችንን ለመሸፈን የሚያስችል ልብስ መስጠት ይሳነዋል? (ቁጥር 25) አምላክ ወፎችን የሚመግብና አበቦችን ውበት የሚያለብስ ከሆነ ለሚያመልኩት ሰዎችማ ይበልጥ አያስብም? (ቁጥር 26, 28-30) በእርግጥም ከልክ በላይ መጨነቅ ዋጋ የለውም። ምንም ያህል ብንጨነቅ በዕድሜያችን ርዝማኔ ላይ ቅንጣት ታክል መጨመር አንችልም።c (ቁጥር 27) ታዲያ እንዲህ ያለውን ጭንቀት እንዴት ማስወገድ ይቻላል? ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ምንጊዜም ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ እንድንሰጥ መክሮናል። ይህን የሚያደርጉ ሰዎች በየዕለቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሰማያዊ አባታቸው ‘እንደሚሰጣቸው’ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (ቁጥር 33) በመጨረሻም ኢየሱስ ከዛሬ አልፈን ነገ ስለሚሆነው ነገር እያሰብን መጨነቅ እንደማይገባ በመግለጽ በጣም ጠቃሚ የሆነ ምክር ሰጥቷል። (ቁጥር 34) ደግሞስ ገና ይሁን አይሁን ለማናውቀው ነገር ከልክ በላይ የምንጨነቅበት ምን ምክንያት አለ? እንዲህ ያለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ሥራ ላይ ማዋላችን አስጨናቂ በሆኑ ነገሮች በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ውጥረት ይቀንስልናል።

      8 በእርግጥም ኢየሱስ የሰጠው ምክር ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት ጠቃሚ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ጠቃሚ ነው። ይህ ሁኔታ የኢየሱስ ምክር አምላካዊ ጥበብ ያዘለ እንደሆነ አያሳይም? ሰዎች የሚሰጡት በጣም የተሻለ ነው የሚባለው ምክር እንኳ ጊዜ ሊያልፍበትና በሌላ ሊተካ ይችላል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ትምህርቶች ፈጽሞ ጊዜ የማይሽራቸው ናቸው። ይህ ድንቅ መካሪ ያስተማረው “የአምላክን ቃል” በመሆኑ በዚህ ልንገረም አይገባም።—ዮሐንስ 3:34

      ያስተማረበት መንገድ

      9. ኢየሱስን እንዲይዙ የተላኩት ወታደሮች ስለ ኢየሱስ ትምህርት ምን አሉ? ይህስ የተጋነነ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

      9 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ የአምላክን ጥበብ እንዴት እንደሚያንጸባርቅ እንመልከት። በአንድ ወቅት ኢየሱስን እንዲይዙ ተልከው የነበሩ ወታደሮች ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፤ ለምን? “ማንም ሰው እንደዚህ ተናግሮ አያውቅም” ብለዋል። (ዮሐንስ 7:45, 46) ይህ ምንም ማጋነን አይደለም። “ከላይ” ማለትም ከሰማይ የመጣው ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የላቀ እውቀትና ተሞክሮ አለው። (ዮሐንስ 8:23) ማንም ሰው እንደ እሱ ሊያስተምር አይችልም። ይህ ጥበበኛ አስተማሪ ከተጠቀመባቸው የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል እስቲ ሁለቱን ብቻ እንመልከት።

      “ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ”

      10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበት መንገድ አስደናቂ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ምን ዓይነት ታሪኮችን ይጠቀም ነበር? ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ታሪኮች ውጤታማ እንደሆኑ የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?

      10 ምሳሌዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ ለሕዝቡ . . . በምሳሌ ተናገረ። እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር” ሲል ይገልጻል። (ማቴዎስ 13:34) በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያጋጥሙ ነገሮችን እየጠቀሰ ጥልቅ የሆኑ እውነቶችን በማስተማር ረገድ ያለው ወደር የለሽ ችሎታ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ዘር የሚዘሩ ገበሬዎችን፣ ሊጥ የሚያቦኩ ሴቶችን፣ በገበያ ቦታ የሚጫወቱ ልጆችን፣ መረባቸውን የሚጥሉ ዓሣ አጥማጆችንና የጠፋባቸውን በግ የሚፈልጉ እረኞችን ምሳሌ አድርጎ ጠቅሷል፤ እነዚህ ነገሮች ለኢየሱስ አድማጮች እንግዳ አልነበሩም። አንድን አስፈላጊ እውነት በየዕለቱ ከሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ጋር አዛምዶ መግለጽ ትምህርቱ በአድማጮች አእምሮና ልብ ውስጥ በቀላሉ እንዲቀረጽ እንዲሁም እንዳይረሱት ለማድረግ ይረዳል።—ማቴዎስ 11:16-19፤ 13:3-8, 33, 47-50፤ 18:12-14

      11 ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ጥሩ ሥነ ምግባርን ወይም መንፈሳዊ እውነትን ለማስተማር ምሳሌዎችን ወይም አጫጭር ታሪኮችን ይጠቀም ነበር። አጫጭር ታሪኮችን መረዳትም ሆነ ማስታወስ ቀላል በመሆኑ ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ታሪኮች ትምህርቱ በአድማጮቹ አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ኢየሱስ በተጠቀመባቸው በብዙዎቹ ታሪኮች ላይ አባቱን ሊረሱ በማይችሉ ሕያው ምሳሌዎች ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጠፍቶ ስለነበረው ልጅ የሚናገረውን ታሪክ ሲያነብ ነጥቡ የማይገባው ማን አለ? የእውነትን መንገድ ትቶ የነበረ ሰው ከልብ ንስሐ ሲገባና ሲመለስ ይሖዋ እንደሚያዝንለትና በርኅራኄ እንደሚቀበለው ሕያው በሆነ መንገድ የሚያስተምር ታሪክ ነው።—ሉቃስ 15:11-32

      12. (ሀ) ኢየሱስ በሚያስተምርበት ጊዜ ጥያቄዎችን ለምን ዓላማ ይጠቀም ነበር? (ለ) ኢየሱስ ሥልጣኑን በተመለከተ ጥያቄ ያነሱትን የሃይማኖት መሪዎች አፍ ያስያዘው እንዴት ነው?

      12 ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም። ኢየሱስ አድማጮቹ በራሳቸው አንድ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ፣ የልባቸውን ዝንባሌ እንዲመረምሩ ወይም አንድ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ጥያቄዎችን ይጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 12:24-30፤ 17:24-27፤ 22:41-46) የሃይማኖት መሪዎቹ ማን ሥልጣን እንደሰጠው ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ “ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን ያገኘው ከአምላክ ነው ወይስ ከሰው?” በማለት ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለሰላቸው። የሃይማኖት መሪዎቹ በጥያቄው በመደናገጥ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ?” ሆኖም “ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።” ስለዚህም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። (ማርቆስ 11:27-33፤ ማቴዎስ 21:23-27) ኢየሱስ ይህን ቀላል ጥያቄ በመጠቀም አፋቸውን ያስያዛቸው ከመሆኑም በላይ የልባቸው ተንኮል እንዲጋለጥ አድርጓል።

      13-15. ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረው ታሪክ የኢየሱስን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      13 ኢየሱስ በሚጠቅሳቸው ምሳሌዎች መካከል አንዳንድ የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን በማንሳት ሁለቱን የማስተማሪያ ዘዴዎች አጣምሮ የተጠቀመባቸው ጊዜያት አሉ። አንድ አይሁዳዊ ሕግ አዋቂ ‘የዘላለም ሕይወት እንዳገኝ ምን ላድርግ?’ ብሎ በጠየቀው ጊዜ አምላክንና ባልንጀራውን እንዲወድ የሚያዙትን በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙ ትእዛዛት አስታወሰው። ሰውየው ግን ጻድቅ መሆኑን ማሳየት ስለፈለገ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አንድ ታሪክ ነገረው። አንድ አይሁዳዊ ሰው ብቻውን እየተጓዘ ሳለ ዘራፊዎች ደብድበው በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ። ሁለት አይሁዳውያን በዚያ አለፉ፤ መጀመሪያ ያለፈው ካህን ሲሆን ቀጣዩ ደግሞ ሌዋዊ ነው። ሁለቱም ሰውየውን እንዳላዩ ሆነው አልፈውት ሄዱ። በኋላም አንድ ሳምራዊ በዚያ በኩል መጣ። ሲያየው በጣም ስላዘነለት ቁስሎቹን በመጠራረግ ካሰረለት በኋላ ወደ እንግዶች ማደሪያ በመውሰድ በዚያ እንዲያርፍና እንዲያገግም አደረገ። ኢየሱስ ታሪኩን ሲደመድም “ታዲያ ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” ሲል ሕግ አዋቂውን ጠየቀው። ሰውየውም “ምሕረት በማሳየት የረዳው ነው” በማለት መለሰለት።—ሉቃስ 10:25-37

      14 ይህ ታሪክ የኢየሱስን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው? በኢየሱስ ዘመን አይሁዳውያን እንደ “ባልንጀራ” የሚቆጥሩት የእነሱን ወግ የሚከተሉትን አይሁዳውያን ብቻ ነበር፤ ሳምራውያንንማ ጨርሶ እንደ ባልንጀራ አይመለከቷቸውም ነበር። (ዮሐንስ 4:9) ኢየሱስ፣ የተደበደበው ሰው ሳምራዊ፣ የረዳው ደግሞ አይሁዳዊ እንደሆነ አድርጎ ታሪኩን ቢያቀርብ ኖሮ አይሁዳዊው ሕግ አዋቂ ለሳምራውያን የነበረውን መጥፎ አመለካከት እንዲለውጥ ለማድረግ ይረዳው ነበር? ኢየሱስ፣ ሳምራዊው አይሁዳዊውን እንደረዳው አድርጎ ታሪኩን ያቀረበው ሆን ብሎ ነው። ኢየሱስ በታሪኩ መደምደሚያ ላይ ያቀረበውን ጥያቄም ልብ በል። ጥያቄው የሕግ አዋቂው የትኩረት አቅጣጫ እንዲቀየር የሚያደርግ ነበር። ሕግ አዋቂው ‘ባልንጀራዬ ማን ነው?’ ብሎ ሲጠይቅ ትኩረት ያደረገው የእሱ ባልንጀራ የሚሆነው ሰው እንዲያሟላ በሚጠበቅበት ነገር ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ያተኮረው መልካም በተደረገለት ማለትም በተደበደበው ሰው ላይ ሳይሆን መልካም ባደረገው ማለትም በሳምራዊው ሰው ላይ ነው። እውነተኛ ባልንጀራ የትኛውንም ዘር ሳይለይ በራሱ ተነሳስቶ ለሌሎች ፍቅር ያሳያል። ኢየሱስ ይህን ነጥብ ለማስገንዘብ ከዚህ የተሻለ ሌላ የማስተማሪያ ዘዴ ሊጠቀም አይችልም።

      15 ታዲያ ሰዎች “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ [ቢደነቁና]” ወደ እሱ ለመቅረብ ቢነሳሱ ያስደንቃል? (ማቴዎስ 7:28, 29) እንዲያውም በአንድ ወቅት “ብዙ ሰዎች” የሚበሉት እንኳ ሳይኖራቸው ከእሱ ጋር ሦስት ቀን ቆይተዋል!—ማርቆስ 8:1, 2

      አኗኗሩ

      16. ኢየሱስ በመለኮታዊ ጥበብ እንደሚመራ በተግባር ‘ያሳየው’ እንዴት ነው?

      16 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ በአኗኗሩ የይሖዋን ጥበብ እንዴት እንዳንጸባረቀ እንመርምር። ጥበብ በተግባር የሚገለጽ ከመሆኑም ሌላ የተፈለገውን ውጤት ያስገኛል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል ጥበበኛ . . . ማን ነው?” ሲል ከጠየቀ በኋላ “[ይህን] በመልካም ምግባሩ ያሳይ” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ያዕቆብ 3:13) የኢየሱስ አኗኗር በመለኮታዊ ጥበብ እንደሚመራ ‘የሚያሳይ’ ነበር። በአኗኗሩም ሆነ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት፣ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንደነበረው ያሳየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

      17. ኢየሱስ አኗኗሩ ፍጹም ሚዛናዊ እንደነበረ የሚጠቁሙት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

      17 ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የሌላቸው ሰዎች በአብዛኛው ወደ አንድ ጽንፍ የመሄድ ዝንባሌ እንደሚታይባቸው አስተውለሃል? አዎን፣ ሚዛናዊ መሆን ጥበብ ይጠይቃል። ኢየሱስ በመለኮታዊ ጥበብ ስለሚመራ ፍጹም ሚዛናዊ ነበር። በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ነገሮች ነበር። ምሥራቹን በማወጁ ሥራ ተጠምዶ ነበር። “የመጣሁት ለዚሁ ነው” ሲል ተናግሯል። (ማርቆስ 1:38) ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጥ እንዳልነበር የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ብዙም ቁሳዊ ንብረት አልነበረውም። (ማቴዎስ 8:20) ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል ባሕታዊ ነበር ማለት አይደለም። ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደሆነው እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ደስተኛ የነበረ ሲሆን ሌሎችም እንዲደሰቱ ያደርግ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ 6:15) በሙዚቃ፣ በዘፈንና በጭፈራ በሚደምቀው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተገኘ ጊዜ የሠርጉን የደስታ መንፈስ የሚያጠፋ ነገር አላደረገም። እንዲያውም የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦታል፤ እንደሚታወቀው ደግሞ የወይን ጠጅ “የሰውን ልብ ደስ [ያሰኛል]።” (መዝሙር 104:15፤ ዮሐንስ 2:1-11) ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት በሰዎች ቤት የተጋበዘ ሲሆን እነዚህንም አጋጣሚዎች ለማስተማር ተጠቅሞባቸዋል።—ሉቃስ 10:38-42፤ 14:1-6

      18. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?

      18 ኢየሱስ ሌሎችን የሚይዝበት መንገድም ጥልቅ ማስተዋል እንዳለው የሚያሳይ ነበር። የሰዎችን አፈጣጠር ማወቁ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ረድቶታል። ፍጹም እንዳልሆኑ በሚገባ ያውቅ የነበረ ቢሆንም ያሏቸውን መልካም ባሕርያትም ተገንዝቧል። ይሖዋ ወደ ራሱ የሳባቸው እነዚህ ሰዎች ለውጥ አድርገው ምን ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስተውሏል። (ዮሐንስ 6:44) አንዳንድ ድክመቶች ቢኖሩባቸውም እምነት ጥሎባቸዋል። ለደቀ መዛሙርቱ ከባድ ኃላፊነት መስጠቱ እምነት እንደጣለባቸው የሚያሳይ ነው። ምሥራቹን የመስበክ ተልእኮ የሰጣቸው ሲሆን ይህን ተልእኮ እንደሚወጡም እርግጠኛ ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የሰጣቸውን ሥራ በታማኝነት እንዳከናወኑ ይመሠክራል። (የሐዋርያት ሥራ 2:41, 42፤ 4:33፤ 5:27-32) በእርግጥም ኢየሱስ በእነሱ ላይ እምነት መጣሉ ትክክል ነበር።

      19. ኢየሱስ ‘ገርና በልቡ ትሑት’ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

      19 በምዕራፍ 20 ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ትሕትናና ገርነት ከጥበብ ጋር የሚዛመዱ ባሕርያት እንደሆኑ ይገልጻል። በዚህ ረገድ ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ኢየሱስስ? ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየው ትሕትና ልብ የሚነካ ነው። ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን ከእነሱ ይበልጥ ነበር። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱን አልናቃቸውም። የበታች እንደሆኑ ወይም ብቃት እንደሌላቸው ሆኖ እንዲሰማቸውም አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ያለባቸውን የአቅም ገደብ ግምት ውስጥ ያስገባ የነበረ ሲሆን ድክመቶቻቸውንም በትዕግሥት ያልፍ ነበር። (ማርቆስ 14:34-38፤ ዮሐንስ 16:12) ሕፃናት እንኳ ሳይፈሩ ወይም ሳይሸማቀቁ ይቀርቡት የነበረ መሆኑ አስደናቂ አይደለም? በነፃነት ሊቀርቡት የቻሉት ‘ገርና በልቡ ትሑት’ መሆኑን ስለተገነዘቡ ነው።—ማቴዎስ 11:29፤ ማርቆስ 10:13-16

      20. ኢየሱስ ልጇ በጋኔን የተያዘች ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት ካቀረበችለት ልመና ጋር በተያያዘ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

      20 ኢየሱስ የይሖዋን የትሕትና ባሕርይ ያንጸባረቀበት ሌላም ወሳኝ መንገድ አለ። ምሕረት ለማሳየት በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ምክንያታዊና እሺ ባይ መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ አንዲት ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት፣ ጋኔን የያዛትን ልጇን እንዲፈውስላት የጠየቀችውን ጊዜ አስታውስ። ኢየሱስ ልጇን እንደማይፈውስላት በሦስት የተለያዩ መንገዶች ጠቁሟት ነበር፦ በመጀመሪያ ምንም መልስ ሳይሰጣት ቀረ፤ ቀጥሎ ደግሞ የተላከው ለአይሁድ እንጂ ለአሕዛብ አለመሆኑን በቀጥታ ነገራት፤ በመጨረሻም ይህንኑ ነጥብ የሚያስገነዝብ ምሳሌ በደግነት ነገራት። ሆኖም ሴትየዋ ውትወታዋን በመቀጠል ከፍተኛ እምነት እንዳላት አሳየች። ኢየሱስ ይህን ለየት ያለ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ምን ምላሽ ሰጠ? ሐሳቡን በመለወጥ፣ አላደርግም ብሎ የነበረውን ነገር አደረገ። የሴትየዋን ልጅ ፈወሰላት። (ማቴዎስ 15:21-28) ይህ እጅግ የሚያስደንቅ ትሕትና አይደለም? ትሕትና ደግሞ የእውነተኛ ጥበብ ዋና መሠረት ነው።

      21. የኢየሱስን ባሕርይ፣ ያስተማረውን ትምህርትና ያደረጋቸውን ነገሮች ለመኮረጅ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

      21 በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ የሆነው ሰው ያስተማረው ትምህርትና ያደረገው ነገር በወንጌሎች ውስጥ ሰፍሮ የሚገኝ በመሆኑ እጅግ አመስጋኞች ነን! ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን እናስታውስ። የኢየሱስን ባሕርይ፣ ያስተማረውን ትምህርትና ያደረጋቸውን ነገሮች በመኮረጅ የአምላክን ጥበብ ማዳበር እንችላለን። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የአምላክን ጥበብ እንዴት በሕይወታችን ማሳየት እንደምንችል እንመለከታለን።

      a በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አናጺዎች ቤቶችን ይገነቡ እንዲሁም የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችንና የእርሻ መገልገያ መሣሪያዎችን ይሠሩ ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ሰማዕቱ ጀስቲን “ኢየሱስ ሞፈርና ቀንበር በመሥራት የሚታወቅ አናጺ ነበር” ሲል ጽፏል።

      b “መጨነቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ሰው ሐሳቡ መከፋፈሉን ወይም ትኩረቱ መሰረቁን ያመለክታል። በመሆኑም ቃሉ በማቴዎስ 6:25 ላይ የተሠራበት ሐሳብን የሚከፋፍልንና ደስታን የሚያሳጣን ጭንቀትና ፍርሃት ለማመልከት ነው።

      c እንዲያውም ከልክ ያለፈ ጭንቀትና ውጥረት ለልብ በሽታና ለሌሎች በርካታ በሽታዎች በማጋለጥ ዕድሜን ሊያሳጥር እንደሚችል አንዳንድ ሳይንሳዊ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ምሳሌ 8:22-31 መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሰው ተደርጋ የተገለጸችውን ጥበብን በተመለከተ የሚሰጠው መግለጫ የይሖዋን የበኩር ልጅ ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል የምንለው ለምንድን ነው?

      • ማቴዎስ 13:10-15 ኢየሱስ የተናገራቸው ምሳሌዎች የአድማጮቹ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዲገለጥ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወቱት እንዴት ነው?

      • ዮሐንስ 1:9-18 ኢየሱስ የአምላክን ጥበብ መግለጥ የቻለው ለምንድን ነው?

      • ዮሐንስ 13:2-5, 12-17 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን በተግባር የተደገፈ ትምህርት ሰጥቷቸዋል?

  • ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስታጠና።

      ምዕራፍ 22

      ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?

      1-3. (ሀ) ሰለሞን በሁለት ሴቶች መካከል የተነሳውን ጭቅጭቅ በዳኘበት ጊዜ አስደናቂ የሆነ ጥበብ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ቃል ገብቷል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

      ፍርድ ለመስጠት የሚያስቸግር ጉዳይ ነው፤ ሁለት ሴቶች በአንድ ሕፃን እየተጨቃጨቁ ነው። እነዚህ ሴቶች በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ሁለቱም በጥቂት ቀናት ልዩነት ልጅ ወለዱ። ከተወለዱት ሕፃናት መካከል አንደኛው ሞተ፤ በመሆኑም ሁለቱ ሴቶች ‘በሕይወት ያለው ሕፃን የእኔ ነው’፣ ‘የእኔ ነው’ በሚል ጭቅጭቅ ፈጠሩ።a ሁኔታው ሲፈጠር ያየ አንድም የዓይን ምሥክር አልነበረም። ጉዳዩ ችሎት ፊት ቀርቦ የታየ ሊሆን ቢችልም እንኳ እልባት ሊያገኝ ባለመቻሉ የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን እንዲዳኘው ተደረገ። ንጉሡ ሐቁ እንዲወጣ ማድረግ ይችል ይሆን?

      2 ሰለሞን የሴቶቹን ጭቅጭቅ ለተወሰነ ጊዜ ካዳመጠ በኋላ ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ። ከዚያም ሕፃኑ ለሁለት ተሰንጥቆ እንዲካፈሉት ትእዛዝ አስተላለፈ። እውነተኛዋ የሕፃኑ እናት ይህን ስትሰማ በጣም የምትወደው ልጇ ከሚቆረጥ ይልቅ ለሌላኛዋ ሴት እንዲሰጥ ንጉሡን ተማጸነች። ሌላኛዋ ሴት ግን ‘ሕፃኑ ለሁለት ተቆርጦ እንካፈል’ አለች። በዚህ ጊዜ ሰለሞን እውነቱ ተገለጠለት። አንዲት እናት የአብራኳ ክፋይ ለሆነው ልጇ ምን ያህል እንደምትራራ ስለሚያውቅ ይህን ዘዴ በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ አደረገ። ሰለሞን ‘እናቱ እሷ ናት’ በማለት ልጁ እንዲሰጣት ሲወስን እናቲቱ ምን እንደተሰማት ልትገምት ትችላለህ።—1 ነገሥት 3:16-27

      3 ይህ የሚያስደንቅ ጥበብ አይደለም? ሕዝቡ ሰለሞን ጉዳዩ እንዴት እልባት እንዲያገኝ እንዳደረገ ሲሰሙ “የአምላክን ጥበብ እንደታደለ ስለተመለከቱ” ለንጉሡ አክብሮታዊ ፍርሃት አደረባቸው። አዎን፣ ይህ የሰለሞን ጥበብ መለኮታዊ ስጦታ ነበር። ይሖዋ “ጥበበኛና አስተዋይ ልብ” ሰጥቶታል። (1 ነገሥት 3:12, 28) እኛስ የአምላክን ጥበብ ማግኘት እንችላለን? አዎን፣ ሰለሞን “ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣል” ሲል በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ጽፏል። (ምሳሌ 2:6) ይሖዋ ጥበብን ማለትም እውቀትንና ማስተዋልን በአግባቡ የመጠቀም ችሎታን ከልብ ለሚፈልጉት ሰዎች እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። ታዲያ ከሰማይ የሆነውን ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ጥበብ በአኗኗራችን ማንጸባረቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

      “ጥበብን አግኝ”—እንዴት?

      4-7. ጥበብ ለማግኘት ምን አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ?

      4 የአምላክን ጥበብ ለማግኘት የላቀ የማሰብ ችሎታ ወይም ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ሊኖረን ይገባል? በፍጹም። ዘራችን፣ ያለንበት የኑሮ ሁኔታ ወይም የትምህርት ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ጥበቡን ሊሰጠን ፈቃደኛ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:26-29) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብን አግኝ” በማለት ስለሚመክረን ጥበብ ለማግኘት ከእኛም የሚጠበቅ ነገር አለ። (ምሳሌ 4:7) ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

      5 በመጀመሪያ ደረጃ አምላክን መፍራት አለብን። ምሳሌ 9:10 “የጥበብ መጀመሪያ [“ጥበብን ለማግኘት የመጀመሪያው እርምጃ፣” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል] ይሖዋን መፍራት ነው” በማለት ይናገራል። ይሖዋን መፍራት የእውነተኛ ጥበብ መሠረት ነው። ለምን? ጥበብ እውቀትን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመጠቀም ችሎታን እንደሚያካትት አስታውስ። አምላክን መፍራት ሲባል በፍርሃት መራድ ማለት ሳይሆን በጥልቅ አክብሮት ተነሳስቶ ለእሱ መገዛት ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ለተግባር የሚያነሳሳ ነው። ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ካለን እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንኖር ይገፋፋናል። ይሖዋ ያወጣቸው መሥፈርቶች መመሪያውን ለሚከተሉ ሁሉ ምንጊዜም ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኙ በመሆናቸው እሱን መፍራታችን ከሁሉ የተሻለ የጥበብ መንገድ ነው።

      6 በሁለተኛ ደረጃ ትሑት እና ልካችንን የምናውቅ መሆን አለብን። ትሑትና ልካችንን የምናውቅ ካልሆንን የአምላክን ጥበብ ማግኘት አንችልም። (ምሳሌ 11:2) ለምን? ትሑቶች እና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ሁሉን እንደምናውቅና እኛ ያልነው ሁልጊዜ ትክክል እንደሆነ አድርገን አናስብም፤ በተጨማሪም የይሖዋን አመለካከት ማወቅ እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለን። ይሖዋ “ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤” ለትሑታን ግን ጥበብን ይሰጣል።—ያዕቆብ 4:6

      7 በሦስተኛ ደረጃ በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክን ቃል ማጥናት አስፈላጊ ነው። የይሖዋ ጥበብ በቃሉ ውስጥ ተገልጿል። ይህን ጥበብ ለማግኘት ጥልቅ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-5) በአራተኛ ደረጃ ደግሞ መጸለይ ያስፈልገናል። አምላክ ጥበብ እንዲሰጠን ከልብ ከለመንነው በልግስና ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5) መንፈሱን እንዲሰጠን የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል። መንፈሱ ደግሞ ችግራችንን ለመወጣት፣ ራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችለንን በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ውድ ሀብት ፈልገን እንድናገኝ ይረዳናል።—ሉቃስ 11:13

      የአምላክን ጥበብ ለማግኘት ጥልቅ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል

      8. አምላካዊ ጥበብ እንዳለን የሚታወቀው በምንድን ነው?

      8 በምዕራፍ 17 ላይ እንደተመለከትነው የይሖዋ ጥበብ በተግባር የሚገለጽ ነው። ስለሆነም በእርግጥ የአምላክን ጥበብ ካገኘን ይህ በአኗኗራችን ይንጸባረቃል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የመለኮታዊ ጥበብ ፍሬዎችን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።” (ያዕቆብ 3:17) እነዚህን የመለኮታዊ ጥበብ ገጽታዎች አንድ በአንድ ስንመረምር ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ በአኗኗሬ እያንጸባረቅሁ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።

      “ንጹሕ . . . ከዚያም ሰላማዊ”

      9. ንጹሕ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? ንጽሕና የጥበብ ገጽታ ከሆኑት ባሕርያት መጀመሪያ ተደርጎ መጠቀሱስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

      9 “በመጀመሪያ ንጹሕ ነው።” ንጹሕ የሚለው ቃል ውጫዊ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ንጽሕናንም ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን ከልብ ጋር ያዛምደዋል፤ ይሁን እንጂ ከሰማይ የሆነው ጥበብ በክፉ ሐሳብ፣ ምኞትና ፍላጎት ወደተበከለ ልብ ሊገባ አይችልም። (ምሳሌ 2:10፤ ማቴዎስ 15:19, 20) ሆኖም አለፍጽምናችን በፈቀደልን መጠን ልባችን ንጹሕ ከሆነ ‘ከክፉ እንርቃለን፤ መልካሙንም እናደርጋለን።’ (መዝሙር 37:27፤ ምሳሌ 3:7) ንጽሕና የጥበብ ገጽታ ከሆኑት ባሕርያት መጀመሪያ ተደርጎ መጠቀሱ ተገቢ አይደለም? ደግሞስ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ካልሆንን ከሰማይ የሆነውን ጥበብ ሌሎች ገጽታዎች እንዴት ማንጸባረቅ እንችላለን?

      10, 11. (ሀ) ሰላማዊ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የእምነት ባልንጀራህን እንዳስቀየምክ ከተሰማህ ሰላም ፈጣሪ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

      10 “ከዚያም ሰላማዊ።” ከሰማይ የሆነው ጥበብ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ሰላምን አጥብቀን እንድንሻ ይገፋፋናል። (ገላትያ 5:22) የይሖዋን ሕዝብ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውን “የሰላም ማሰሪያ” ከማደፍረስ እንቆጠባለን። (ኤፌሶን 4:3) ሰላም በሚደፈርስበት ጊዜ ደግሞ ዳግመኛ ሰላም እንዲሰፍን የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በሰላም መኖራችሁን ቀጥሉ፤ የፍቅርና የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋር ይሆናል” በማለት ይገልጻል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ስለዚህ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እስከኖርን ድረስ የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት የምናሳየው ባሕርይ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በቀጥታ ይነካል። ታዲያ ሰላም ፈጣሪዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

      11 የእምነት ባልንጀራህን እንዳስቀየምክ ከተሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:23, 24) ቀዳሚውን እርምጃ ወስደህ ወንድምህን በማነጋገር ይህን ምክር ልትሠራበት ትችላለህ። ይህን የምታደርግበት ዓላማ ምንድን ነው? ‘ከወንድምህ ጋር መታረቅ’ ነው።b ይህ እንዲሆን ደግሞ ቅር የሚያሰኘው ምንም ምክንያት እንደሌለው ከመግለጽ ይልቅ ስሜቱን እንደጎዳኸው አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። ቀደም ሲል የነበራችሁን ሰላማዊ ግንኙነት የማደስ ግብ ይዘህ ካነጋገርከውና በውይይታችሁ ወቅትም ይህንን አመለካከት ካንጸባረቅህ በመካከላችሁ የነበረው አለመግባባት ተወግዶ ይቅር ልትባባሉ ትችላላችሁ። ቀዳሚውን እርምጃ በመውሰድ ከወንድምህ ጋር እርቅ ለመፍጠር መጣርህ በአምላክ ጥበብ እንደምትመራ ያሳያል።

      “ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ”

      12, 13. (ሀ) በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምክንያታዊ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ፍቺ ምንድን ነው? (ለ) ምክንያታዊ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      12 “ምክንያታዊ።” ምክንያታዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምክንያታዊ” ተብሎ የተቀመጠውን የግሪክኛ ቃል መተርጎም አስቸጋሪ ነው። ቃሉ ‘እሺ ባይ መሆን’ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ተርጓሚዎች ይህን ቃል “ገር፣” “ታጋሽ” እና “አሳቢ” ብለው ተርጉመውታል። ይህን ከሰማይ የሆነውን ጥበብ አንድ ገጽታ በአኗኗራችን ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

      13 ፊልጵስዩስ 4:5 “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “ምክንያታዊ ናቸው የሚል ስም አትርፉ” ሲል ተርጉሞታል። (ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ፣ በጄ ቢ ፊሊፕስ) ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባው ነገር እኛ ለራሳችን ያለን አመለካከት ሳይሆን ሌሎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት መሆኑን ልብ በል። ምክንያታዊ የሆነ ሰው ሕጉ ካልተከበረ ብሎ ድርቅ አይልም ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ አይሟገትም። ከዚህ ይልቅ የሌሎችን ሐሳብ ለመስማትና ተገቢ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ያሉትን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናል። በተጨማሪም ገርና የሚመች ባሕርይ ያለው ነው እንጂ አስቸጋሪ አይደለም። ይህ ባሕርይ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚያስፈልግ ቢሆንም በይበልጥ ግን ሽማግሌ ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል። ሽማግሌዎች ገር ከሆኑ ሌሎች በቀላሉ ሊቀርቧቸው ይችላሉ። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ሁላችንም ‘አሳቢ፣ ምክንያታዊና ገር ነው የሚል ስም እያተረፍኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።

      14. “ለመታዘዝ ዝግጁ” መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      14 “ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ።” እንዲህ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ አይገኝም። አንድ ምሁር እንደገለጹት ከሆነ ይህ ቃል “አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት ከወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ነው።” “በቀላሉ እሺ ብሎ የሚቀበል” እና “ታዛዥ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ከሰማይ በሆነው ጥበብ የሚመራ ሰው ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን መመሪያ ያለምንም ማንገራገር ይታዘዛል። አንዴ አንድ ውሳኔ ላይ ከደረሰ ምንም ዓይነት ሐሳብ ቢቀርብለት የማይቀበል ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተሳሳተ እርምጃ እንደወሰደ ወይም የተሳሳተ ውሳኔ እንደወሰነ የሚያሳይ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ሲቀርብለት ወዲያውኑ አቋሙን ይለውጣል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ስም አትርፈሃል?

      “ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት”

      15. ምሕረት ምንድን ነው? በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምሕረት” እና “መልካም ፍሬዎች” አንድ ላይ መጠቀሳቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

      15 “ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት።”c ከሰማይ የሆነው ጥበብ ‘ምሕረት የሞላበት’ እንደሆነ ስለተገለጸ ምሕረት የዚህ ጥበብ ወሳኝ ገጽታ ነው። “ምሕረት” እና “መልካም ፍሬዎች” አንድ ላይ እንደተጠቀሱ ልብ በል። ይህ መሆኑም የተገባ ነው፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሕረት የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው እርምጃ በመውሰድ የሚገለጽ አሳቢነትን እንዲሁም ውጤቱ በደግነት ተግባሮች የሚታይን የርኅራኄ ስሜት ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ምሕረት የሚለው ቃል “አንድ ሰው በደረሰበት መጥፎ ሁኔታ ማዘንንና ያንን ሰው ለመርዳት መሞከርን” እንደሚያመለክት ገልጿል። ስለሆነም የአምላክ ጥበብ ከአእምሮ ብቻ ሳይሆን ከልብ ጋርም የሚያያዝ ባሕርይ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ እንደ ርኅራኄ፣ አዘኔታና አሳቢነት ባሉት ስሜቶችም የሚመራ ነው። ታዲያ ምሕረት የሞላብን መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      16, 17. (ሀ) ለአምላክ ካለን ፍቅር በተጨማሪ የስብከቱን ሥራ እንድናከናውን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) ምሕረት የሞላብን መሆናችንን ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

      16 ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች መናገር እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህን ሥራ እንድናከናውን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ሆኖም ምሕረትና ርኅራኄም እንዲህ እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ማቴዎስ 22:37-39) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ይገኛሉ። (ማቴዎስ 9:36) የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች እነዚህን ሰዎች ችላ ያሏቸው ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ እንዲታወሩ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ መመሪያም ሆነ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ የሚያመጣቸውን በረከቶች አያውቁም። እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ የተራቡ እንደሆኑ ስናስብ ለእነሱ ያለን ርኅራኄ ስለ ይሖዋ ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል።

      አንድ ባልና ሚስት እና ሁለት ልጆቻቸው፣ ምግብ እንዲሁም የጥገና መሣሪያዎች ይዘው አንዲት አረጋዊት እህትን ሲጠይቁ።

      ለሌሎች ምሕረት ወይም ርኅራኄ በማሳየት ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ ማንጸባረቅ እንችላለን

      17 ምሕረት የሞላብን መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው? ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረውን ምሳሌ አስታውስ። ይህ ሳምራዊ፣ ተደብድቦና ተዘርፎ በመንገድ ዳር የወደቀ አንድ ሰው ሲያይ ስላዘነለት ‘ምሕረት በማሳየት ረድቶታል፤’ ቁስሎቹን ያሰረለት ሲሆን ተገቢውን እንክብካቤ አድርጎለታል። (ሉቃስ 10:29-37) ይህ ምሳሌ፣ ምሕረት ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ማድረግን የሚጨምር እንደሆነ የሚያሳይ አይደለም? መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም” እንድናደርግ ያበረታታናል። (ገላትያ 6:10) ይህን ልናደርግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ተመልከት። አንድ አረጋዊ ወንድም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያመላልሳቸው ሰው ይፈልጉ ይሆናል። በጉባኤህ ውስጥ ያለች አንዲት መበለት እህት ቤቷ ውስጥ አንዳንድ የጥገና ሥራዎች የሚያከናውንላት ሰው ትፈልግ ይሆናል። (ያዕቆብ 1:27) ተስፋ የቆረጠ አንድ ሰው “መልካም ቃል” በመናገር የሚያጽናናው ይፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 12:25) በእነዚህ መንገዶች ምሕረት ማሳየታችን ከሰማይ የሆነውን ጥበብ በአኗኗራችን እያንጸባረቅን እንዳለን ያረጋግጣል።

      “አድልዎና ግብዝነት የሌለበት”

      18. ከሰማይ በሆነው ጥበብ የምንመራ ከሆነ ምን ነገርን ከልባችን ነቅለን ለማስወገድ እንጥራለን? ለምንስ?

      18 ‘አድልዎ የሌለበት።’ የአምላክ ጥበብ ያለው ሰው፣ የእሱ ዘር ወይም ብሔር ከሌሎች እንደሚበልጥ አያስብም። በዚህ ጥበብ የምንመራ ከሆነ ማንኛውንም ዓይነት የአድልዎ ስሜት ከልባችን ውስጥ ነቅለን ለማስወገድ እንጥራለን። (ያዕቆብ 2:9) የሰዎችን የትምህርት ደረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ ወይም የጉባኤ ኃላፊነት በማየት አናዳላም፤ በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችን በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚሰጣቸው ቦታ የቱንም ያህል ዝቅተኛ ቢሆን አንንቃቸውም። እነዚህን ሰዎች ይሖዋ እስከወደዳቸው ድረስ እኛም ልንወዳቸው ይገባል።

      19, 20. (ሀ) “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በጥንት ዘመን ምን ለማመልከት ይሠራበት ነበር? (ለ) “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      19 “ግብዝነት የሌለበት።” “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አንድን ገጸ ባሕርይ ወክሎ የሚጫወትን ተዋናይ” ሊያመለክት ይችላል። በጥንት ዘመን የግሪክና የሮም ተዋናዮች በሚተውኑበት ወቅት ትላልቅ ጭምብሎችን ያጠልቁ ነበር። በመሆኑም “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አስመሳይ የሆነን ሰው ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። “ግብዝነት የሌለበት” የሚለው የአምላክ ጥበብ ገጽታ ለሌሎች የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ያለንን አመለካከትም ሊነካው ይገባል።

      20 ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ለእውነት የምንታዘዝ’ ከሆነ “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” እንደሚኖረን ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 1:22) አዎን፣ ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ከአንገት በላይ መሆን የለበትም። ጭምብል በማጥለቅ ወይም በማስመሰል ሌሎችን ማታለል የለብንም። ፍቅራችን ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ የእምነት ባልንጀሮቻችን እውነተኛ ማንነታችንን ስለሚያውቁ ያምኑናል። ክርስቲያኖች ግብዞች አለመሆናቸው በሐቀኝነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በጉባኤው ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል።

      “ጥበብን . . . ጠብቅ”

      21, 22. (ሀ) ሰለሞን የነበረውን ጥበብ ጠብቆ ማቆየት ሳይችል የቀረው ለምንድን ነው? (ለ) ያለንን ጥበብ ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ በማድረጋችን የምንጠቀመውስ እንዴት ነው?

      21 የአምላክ ጥበብ ልንጠብቀው የሚገባ የይሖዋ ስጦታ ነው። ሰለሞን “ልጄ ሆይ፣ . . . ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 3:21) የሚያሳዝነው ግን ሰለሞን ራሱ ይህን ምክር አልሠራበትም። ይሖዋን በታዘዘባቸው ዘመናት ሁሉ ጠቢብ ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ያገባቸው የባዕድ አገር ሴቶች ልቡ ከይሖዋ ንጹሕ አምልኮ እንዲርቅ አደረጉት። (1 ነገሥት 11:1-8) እውቀት በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ምንም ፋይዳ እንደሌለው በሰለሞን ላይ የደረሰው ሁኔታ በግልጽ ያሳያል።

      22 ያለንን ጥበብ ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በማንበብ ብቻ ሳይሆን የተማርነውን ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት በማድረግ ጭምር ነው። (ማቴዎስ 24:45) መለኮታዊ ጥበብን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ። በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል። ከዚህም በላይ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም የሚኖረውን ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ከሁሉ በላይ ደግሞ ከሰማይ የሆነውን ጥበብ ማዳበራችን የጥበብ ሁሉ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።

      a አንደኛ ነገሥት 3:16 ሁለቱ ሴቶች ዝሙት አዳሪዎች እንደሆኑ ይገልጻል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ያብራራል፦ “እነዚህ ሴቶች ዝሙት አዳሪዎች የተባሉት መተዳደሪያቸው ስለሆነ ሳይሆን ልጅ የወለዱት በዝሙት እንደሆነ ለመግለጽ ሊሆን ይችላል፤ ሴቶቹ አይሁዳውያን ምናልባትም የሌላ አገር ዝርያ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።”—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

      b “ታረቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ “ጠላትነትን አስወግዶ ወዳጅነት መመሥረት፣ እርቅ መፍጠር፣ ቀድሞ ወደነበረው ጥሩ ግንኙነት ወይም ስምምነት መመለስ” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል። በመሆኑም ዓላማህ ከተቻለ፣ ቅር በተሰኘው ግለሰብ ልብ ውስጥ የተፈጠረውን መጥፎ ስሜት በማስወገድ ለውጥ ማምጣት ነው።—ሮም 12:18

      c ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ርኅራኄና መልካም ተግባሮች የሞሉበት” ይላል።—ኤ ትራንስሌሽን ኢን ዘ ላንግዌጅ ኦቭ ዘ ፒፕል፣ በቻርልስ ቢ ዊልያምስ

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ዘዳግም 4:4-6 ጥበበኞች መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?

      • መዝሙር 119:97-105 የአምላክን ቃል በትጋት የምናጠናና በሥራ ላይ ለማዋል የምንጥር ከሆነ ምን ጥቅም እናገኛለን?

      • ምሳሌ 4:10-13, 20-27 የይሖዋን ጥበብ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

      • ያዕቆብ 3:1-16 በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች ጥበበኞችና አስተዋዮች መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ