3 “እነሆ፣ በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ
የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮኞች ስመልስ፣+
2 ብሔራትን ሁሉ ሰብስቤ
ወደ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ።
ለሕዝቤና ርስቴ ለሆነው ለእስራኤል ስል
በዚያ ከእነሱ ጋር እፋረዳለሁ፤+
በብሔራት መካከል በትነዋቸዋልና፤
ደግሞም ምድሬን ተከፋፍለዋታል።+
3 በሕዝቤ ላይ ዕጣ ይጣጣላሉና፤+
ዝሙት አዳሪ ለማግኘት ሲሉ ወንድ ልጅን አሳልፈው ይሰጣሉ፤
የወይን ጠጅ ለመጠጣት ሲሉም ሴት ልጅን ይሸጣሉ።
4 ጢሮስ፣ ሲዶና እና የፍልስጤም ግዛቶች ሁሉ፣
ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ?
ላደረግኩባችሁ ነገር ብድራት ልትመልሱልኝ ነው?
ብድራት የምትመልሱልኝ ከሆነ
ብድራታችሁን ወዲያውኑ፣ በፍጥነት በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ።+
5 ምክንያቱም እናንተ ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤+
እጅግ ምርጥ የሆነውን ውድ ንብረቴንም ወደ ቤተ መቅደሶቻችሁ አስገብታችኋል፤
6 ደግሞም ከምድራቸው ርቀው እንዲሄዱ ለማድረግ ስትሉ
የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ለግሪኮች ሸጣችሁ፤+
7 እነሆ፣ እነሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች እንዲመለሱ አነሳሳቸዋለሁ፤+
ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ።
8 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሕዝብ እሸጣለሁ፤+
እነሱም በሩቅ ላለ ብሔር ይኸውም ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤
ይሖዋ ራሱ ይህን ተናግሯልና።
9 በብሔራት መካከል ይህን አውጁ፦+
‘ለጦርነት ተዘጋጁ! ኃያላን ሰዎችን አነሳሱ!
ወታደሮቹ ሁሉ ቀርበው ጥቃት ይሰንዝሩ!+
10 ማረሻችሁን ሰይፍ፣ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ።
ደካማው ሰው “እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።
11 እናንተ ዙሪያውን ያላችሁ ብሔራት ሁሉ፣ ኑና ተረዳዱ፤ አንድ ላይም ተሰብሰቡ!’”+
ይሖዋ ሆይ፣ ኃያላንህን ወደዚያ ቦታ አውርድ።
12 “ብሔራት ይነሱና ወደ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ ይምጡ፤
ዙሪያውን ባሉት ብሔራት ሁሉ ላይ ለመፍረድ በዚያ እቀመጣለሁና።+
13 መከሩ ስለደረሰ ማጭድ ስደዱ።
የወይን መጭመቂያው ስለሞላ ኑ፣ ወርዳችሁ እርገጡ።+
ማጠራቀሚያዎቹ ሞልተው አፍስሰዋል፤ ክፋታቸው እጅግ በዝቷልና።
14 ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ የፍርድ ውሳኔ በሚሰጥበት ሸለቆ ተሰብስቧል፤
የፍርድ ውሳኔ በሚሰጥበት ሸለቆ የይሖዋ ቀን ቀርቧልና።+
15 ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤
ከዋክብትም ብርሃናቸውን አይሰጡም።
16 ይሖዋም ከጽዮን እንደ አንበሳ ያገሳል፤
ከኢየሩሳሌም ድምፁን በኃይል ያሰማል።
ሰማይና ምድር ይናወጣሉ፤
ይሖዋ ግን ለሕዝቡ መጠጊያ፣+
ለእስራኤል ሕዝብ ምሽግ ይሆናል።
17 እናንተም እኔ በተቀደሰው ተራራዬ+ በጽዮን የምኖር አምላካችሁ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።
ኢየሩሳሌም ቅዱስ ስፍራ ትሆናለች፤+
እንግዶችም ከእንግዲህ በእሷ አያልፉም።+
18 በዚያ ቀን ተራሮቹ ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤+
ኮረብቶቹ ወተት ያፈሳሉ፤
የይሁዳ ጅረቶችም ሁሉ በውኃ ይሞላሉ።
ከይሖዋም ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤+
የሺቲምንም ሸለቆ ያጠጣል።
19 ግብፅ ግን ባድማ ትሆናለች፤+
ኤዶምም በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ+
በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ስለፈጸመች+
ጠፍ ምድረ በዳ ትሆናለች።+
20 ይሁንና ይሁዳ ምንጊዜም፣
ኢየሩሳሌምም ከትውልድ እስከ ትውልድ የሰው መኖሪያ ትሆናለች።+
21 ንጹሕ አድርጌ ያልቆጠርኩትን ደማቸውን ንጹሕ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤+
ይሖዋም በጽዮን ይኖራል።”+