5 ልጄ ሆይ፣ ጥበቤን ልብ በል።
ማስተዋልን በተመለከተ የምሰጠውን ትምህርት በጥሞና አዳምጥ፤+
2 ይህም የማመዛዘን ችሎታህን እንድትጠብቅ፣
በከንፈሮችህም እውቀትን በጥንቃቄ እንድትይዝ ነው።+
3 የጋጠወጥ ሴት ከንፈር እንደ ማር እንጀራ ያንጠባጥባልና፤+
አፏም ከዘይት ይለሰልሳል።+
4 በመጨረሻ ግን እንደ ጭቁኝ ትመርራለች፤+
ደግሞም በሁለት በኩል እንደተሳለ ሰይፍ ትሆናለች።+
5 እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ።
እርምጃዎቿ በቀጥታ ወደ መቃብር ይመራሉ።
6 ስለ ሕይወት መንገድ ግድ የላትም።
በጎዳናዎቿ ላይ ትባዝናለች፤ ወዴት እንደሚወስዱም አታውቅም።
7 እንግዲህ ልጆቼ ሆይ፣ አዳምጡኝ፤
ከምናገረውም ቃል አትራቁ።
8 ከእሷ ራቅ፤
ወደ ቤቷም ደጃፍ አትቅረብ፤+
9 ይህም ክብርህን ለሌሎች አሳልፈህ እንዳትሰጥ ነው፤+
ቀሪ የሕይወት ዘመንህም በመከራ የተሞላ እንዳይሆን ነው፤+
10 ደግሞም እንግዳ የሆኑ ሰዎች ጥሪትህን እንዳያሟጥጡ፣+
የለፋህበትንም ነገር የባዕድ አገር ሰው እንዳይወርሰው ነው።
11 አለዚያ በሕይወትህ ማብቂያ
ሥጋህና መላ ሰውነትህ እየመነመነ ሲሄድ ትቃትታለህ፤+
12 ደግሞም እንዲህ ትላለህ፦ “ምነው ተግሣጽን ጠላሁ!
ልቤስ ምነው ወቀሳን ናቀ!
13 የአስተማሪዎቼን ቃል አላዳመጥኩም፤
መምህሮቼንም በጥሞና አልሰማሁም።
14 በመላው ጉባኤ መካከል
ሙሉ በሙሉ ልጠፋ ምንም አልቀረኝም ነበር።”+
15 ከራስህ ጉድጓድ እንዲሁም
ከገዛ ምንጭህ የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ።+
16 ምንጮችህ ወደ ውጭ፣
ጅረቶችህም በአደባባይ ሊፈሱ ይገባል?+
17 ለአንተ ብቻ ይሁኑ፤
ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ።+
18 ምንጭህ የተባረከ ይሁን፤
ከወጣትነት ሚስትህም ጋር ደስ ይበልህ፤+
19 እሷ እንደምትወደድ ሚዳቋና እንደምታምር የተራራ ፍየል ናት።+
ጡቶቿ ምንጊዜም ያርኩህ።
ፍቅሯ ምንጊዜም ይማርክህ።+
20 ልጄ ሆይ፣ ጋጠወጥ ሴት ለምን ትማርክሃለች?
ባለጌ ሴትንስ ለምን ታቅፋለህ?+
21 የሰው መንገድ በይሖዋ ዓይኖች ፊት ነውና፤
እሱ መንገዱን ሁሉ ይመረምራል።+
22 ክፉ ሰው የገዛ ጥፋቱ ወጥመድ ይሆንበታል፤
ኃጢአቱም እንደ ገመድ ተብትቦ ይይዘዋል።+
23 ተግሣጽ ከማጣቱ የተነሳ ይሞታል፤
በጣም ሞኝ ከመሆኑም የተነሳ መንገድ ይስታል።