የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ‘እሱ አስቀድሞ ወዶናል’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት።

      ምዕራፍ 23

      ‘እሱ አስቀድሞ ወዶናል’

      1-3. የኢየሱስን ሞት ከሌላው ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

      የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ አንድ ሰው ባልሠራው ጥፋት ተወንጅሎ ከተፈረደበት በኋላ ተሠቃይቶ እንዲሞት ተደረገ። በሰው ዘር ታሪክ እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊና ጭካኔ የተሞላበት ፍርድ ሲፈረድ ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አይደለም። ሆኖም ይህን የሞት ቅጣት ከሌላው ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ።

      2 ይህ ሰው በከፍተኛ ሥቃይ እያጣጣረ በነበረባቸው የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በሰማይ ላይ የታየው ክስተት ራሱ በወቅቱ የተፈጸመው ሁኔታ ልዩ ትርጉም እንዳለው የሚጠቁም ነበር። ገና እኩለ ቀን የነበረ ቢሆንም ምድሪቱ በድንገት በጨለማ ተዋጠች። አንድ ታሪክ ጸሐፊ ‘የፀሐይ ብርሃን እንደጠፋ’ ዘግቧል። (ሉቃስ 23:44, 45) ይህ ሰው እስትንፋሱ ሊያቆም ሲል “ተፈጸመ!” በማለት የማይረሳ ቃል ተናግሯል። በእርግጥም ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት አንድ አስደናቂ ነገር ፈጽሟል። ይህ ሰው ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ፍቅር በታሪክ ዘመናት ሁሉ የትኛውም ሰው ካሳየው ፍቅር የላቀ ነው።—ዮሐንስ 15:13፤ 19:30

      3 ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚያ የመከራ ቀን (ኒሳን 14, 33 ዓ.ም.) ብዙ ሥቃይ እንደደረሰበትና እንደሞተ የሚገልጸውን ታሪክ የማያውቅ የለም ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ብዙዎች ልብ የማይሉት አንድ ትልቅ እውነታ አለ። ኢየሱስ ብዙ ሥቃይ የደረሰበት ቢሆንም እንኳ ከእሱ ይበልጥ የተሠቃየ አንድ አካል አለ። እንዲያውም በዚያ ዕለት የበለጠ መሥዋዕት የከፈለውና አቻ የማይገኝለት ፍቅር ያሳየው እሱ ነው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ፍቅር ያሳየ ማንም የለም። ይህን ፍቅሩን የገለጸው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ቀጥሎ ለምንመረምረው በጣም አስፈላጊ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ለይሖዋ ፍቅር ተስማሚ መግቢያ ነው።

      ከሁሉ የላቀው የፍቅር መግለጫ

      4. አንድ ሮማዊ ወታደር ኢየሱስ ተራ ሰው አለመሆኑን እንዲገነዘብ ያደረገው ምንድን ነው? ምን ብሎስ ተናግሯል?

      4 በኢየሱስ ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ ያስፈጸመው ሮማዊ መቶ አለቃ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ምድሪቱን በሸፈነው ጨለማም ሆነ ከሞተ በኋላ በተከሰተው ኃይለኛ የምድር ነውጥ በጣም ተደናግጦ ነበር። “ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 27:54) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተራ ሰው አልነበረም። ይህ ወታደር የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ ያስገደለው የልዑሉን አምላክ አንድያ ልጅ ነው። አምላክ ልጁን ምን ያህል ይወደው ነበር?

      5. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከአባቱ ጋር የኖረበት ጊዜ ምን ያህል ረጅም እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

      5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ሲል ይጠራዋል። (ቆላስይስ 1:15) የይሖዋ ልጅ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንኳ ይኖር እንደነበረ ልብ በል። እንግዲያው ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የኖረው ለምን ያህል ጊዜ ነው? አንዳንድ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም የ13 ቢሊዮን ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ይገምታሉ። ይህ ምን ያህል ረጅም ዘመን እንደሆነ መገመት ትችላለህ? አንድ የጠፈር አካላት ማዕከል፣ ሰዎች የዚህን ዘመን ርዝማኔ እንዲረዱ ለማገዝ 110 ሜትር ርዝመት ያለው የጊዜ ሰንጠረዥ አዘጋጅቶ ነበር። ጎብኚዎች ይህን የጊዜ ሰንጠረዥ ተከትለው ሲጓዙ እያንዳንዱ እርምጃቸው የሚወክለው ከጽንፈ ዓለም ዕድሜ 75 ሚሊዮን ዓመት የሚሆነውን ጊዜ ነው። የሰው ዘር ምድር ላይ የኖረበት አጠቃላይ ዘመን፣ በጊዜ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ ከአንዲት የፀጉር ቅንጣት በማትበልጥ መስመር ተወክሏል። እንግዲህ ይህን የሳይንቲስቶቹን ግምት ይዘን ብንነሳ እንኳ የይሖዋን ልጅ ዕድሜ ለማስቀመጥ ሙሉው የጊዜ ሰንጠረዥ አይበቃም! ኢየሱስ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምን ሲያከናውን ነበር?

      6. (ሀ) የይሖዋ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምን ሲያከናውን ነበር? (ለ) ይሖዋና ልጁ ምን ዓይነት ወዳጅነት አላቸው?

      6 የአምላክ ልጅ “የተዋጣለት ሠራተኛ” በመሆን አባቱን በደስታ ሲያገለግል ነበር። (ምሳሌ 8:30) መጽሐፍ ቅዱስ “[ያለኢየሱስ] ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር የለም” ሲል ይገልጻል። (ዮሐንስ 1:3) በመሆኑም ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው ከልጁ ጋር አብሮ በመሥራት ነው። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፈው ይሆን! በወላጅና በልጅ መካከል ያለው ፍቅር እጅግ ጠንካራ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ደግሞም “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” (ቆላስይስ 3:14) ይሖዋና ኢየሱስ ይህን ያህል ረጅም ዘመን አብረው ሲያሳልፉ በመካከላቸው ያለው ትስስር ምን ያህል የጠበቀ እንደሚሆን መገመት የሚችል ይኖራል? በእርግጥም በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ያለው የጠበቀ ወዳጅነትና ፍቅር አቻ የለውም።

      7. ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ይሖዋ ስለ ልጁ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?

      7 ይሁንና ይሖዋ፣ ልጁን ሰው ሆኖ እንዲወለድ ወደ ምድር ላከው። ይህን ለማድረግ ሲል የሚወደውን ልጁን ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ከአጠገቡ ማጣት ግድ ሆኖበታል። ከሰማይ ሆኖ የኢየሱስን አስተዳደግ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በትኩረት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው ተጠመቀ። ይሖዋ ስለ ልጁ ምን ተሰምቶት ነበር? “በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:17) ኢየሱስ አስቀድሞ ስለ እሱ የተነገሩትን ትንቢቶች በሙሉ በታማኝነት በመፈጸም ከእሱ የሚጠበቀውን ሁሉ እንዳከናወነ ሲመለከት አባቱ እጅግ እንደተደሰተ ምንም ጥርጥር የለውም!—ዮሐንስ 5:36፤ 17:4

      8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ምን ደረሰበት? በሰማይ ያለው አባቱስ ይህን ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? (ለ) ይሖዋ ልጁ ይህ ሁሉ ሥቃይ እንዲደርስበትና እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?

      8 ይሁን እንጂ ይሖዋ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. የተፈጸመውን ሁኔታ ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? በዚያ ሌሊት ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሲሰጠውና ሰዎች መጥተው ሲይዙት፣ ወዳጆቹ ትተውት ሲሄዱና አላግባብ ለፍርድ ሲቀርብ ይሖዋ ምን ተሰምቶት ይሆን? ጠላቶቹ ሲያፌዙበት፣ ሲተፉበትና በቡጢ ሲመቱት፣ ጀርባው እስኪተለተል ሲገርፉት ብሎም እጅና እግሩ በእንጨት ላይ በሚስማር ሲቸነከርና ተሰቅሎ እያለ አላፊ አግዳሚው ሲሰድበው አባቱ ምን ተሰምቶት ይሆን? የሚወደው ልጁ በጭንቅ እያጣጣረ ወደ እሱ ሲጮኽ እንዲሁም የመጨረሻዋን እስትንፋስ ተንፍሶ የሞትን ጽዋ ሲጎነጭና ለመጀመሪያ ጊዜ ከሕልውና ውጪ ሲሆን ይሖዋ ምን ተሰምቶት ይሆን?—ማቴዎስ 26:14-16, 46, 47, 56, 59, 67፤ 27:38-44, 46፤ ዮሐንስ 19:1

      9 ይህን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል። ይሖዋ ስሜት ያለው እንደመሆኑ መጠን ልጁ ሲሞት የተሰማው ሥቃይ በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ነው። በቃል ልንገልጸው የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ይሖዋ ይህን ሁኔታ እንዲፈቅድ የገፋፋውን ነገር ነው። አብ እንዲህ ያለው ሥቃይ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ በዮሐንስ 3:16 ላይ አንድ አስደናቂ ሐሳብ ገልጾልናል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትልቅ ትርጉም ያለው መልእክት ያዘለ በመሆኑ የወንጌል ፍሬ ሐሳብ ተብሎ ይጠራል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” ስለዚህ ይሖዋ ይህን እንዲፈቅድ ግድ ያለው ፍቅር ነው። ይሖዋ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት በማድረግ ያሳየን ፍቅር ከዚህ ቀደም ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ የላቀ ነው።

      “አምላክ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል”

      የመለኮታዊ ፍቅር ትርጉም

      10. ሰዎች ምን ማግኘት ይሻሉ? “ፍቅር” የሚለው ቃል ትርጉምስ ምን እየሆነ መጥቷል?

      10 “ፍቅር” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? የሰው ልጆች ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ፍቅር ነው። ሰዎች ከልደት እስከ ሕልፈት ፍቅርን ይሻሉ፣ ፍቅርን ሲያገኙ ሕይወታቸው ያብባል፣ ፍቅርን ሲያጡ ደግሞ ይኮሰምናሉ አልፎ ተርፎም ይሞታሉ። ያም ሆኖ ፍቅርን እንዲህ ነው ብሎ መግለጽ በጣም ያስቸግራል። እርግጥ ነው፣ ስለ ፍቅር ብዙ ተብሏል። ስለ ፍቅር ብዙ ተጽፏል፣ ብዙ ተዘፍኗል እንዲሁም ብዙ ተገጥሟል። ይሁንና ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ፍቅርን በትክክል የሚገልጹ ሆነው አልተገኙም። እንዲያውም ስለ ፍቅር ብዙ ከመባሉ የተነሳ ትክክለኛ ትርጉሙ ግራ እያጋባ መጥቷል።

      11, 12. (ሀ) ስለ ፍቅር ብዙ ትምህርት መቅሰም የምንችለው ከየት ነው? ለምንስ? (ለ) በጥንቱ የግሪክ ቋንቋ የተጠቀሱት የፍቅር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው የትኛው የፍቅር ዓይነት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ሐ) አጋፔ የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የተሠራበት ምን ዓይነት ፍቅርን ለማመልከት ነው?

      11 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ ይሰጣል። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ “ፍቅርን ማወቅ የሚቻለው በሚያከናውነው ተግባር ብቻ ነው” በማለት ይገልጻል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይሖዋ ለፍጥረታቱ ስላለው የጠለቀ ፍቅር ብዙ ያስተምሩናል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ፍቅሩን በተግባር ከገለጸበት የቤዛ ዝግጅት ይበልጥ ይህን ባሕርይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምን ነገር ይኖራል? በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ ይሖዋ ፍቅሩን በተግባር የገለጸባቸውን ሌሎች በርካታ ምሳሌዎች እንመለከታለን። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍቅርን” ለማመልከት የገቡትን ቃላት በመመርመር ግንዛቤያችንን ማስፋት እንችላለን። በጥንቱ የግሪክ ቋንቋ “ፍቅርን” ለማመልከት የሚያገለግሉ አራት ቃላት ነበሩ።a ከእነዚህ መካከል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው አጋፔ የሚለው ቃል ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ፍቅርን ለመግለጽ የሚያስችል ከዚህ የተሻለ ቃል የለም” ሲል ዘግቧል። ለምን?

      12 አጋፔ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የተሠራበት በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅርን ለማመልከት ነው። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ፍቅር ለአንድ ሰው ባለን ስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የሚወዱንን ከመውደድም ያለፈ ነው፤ አንድ ሰው አስቦበትና በዓላማ የሚያሳየው የፍቅር ዓይነት ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ክርስቲያናዊ ፍቅር ፈጽሞ ከራስ ወዳድነት መንፈስ ነፃ በሆነ መንገድ የሚገለጽ ፍቅር ነው። እስቲ ዮሐንስ 3:16⁠ን በድጋሚ ተመልከት። አምላክ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ የወደደው የትኛውን “ዓለም” ነው? ከኃጢአት ሊቤዥ የሚችለውን የሰው ዘር ዓለም ነው። ይህም በኃጢአት ጎዳና እየተመላለሱ ያሉ ብዙ ሰዎችን ይጨምራል። ይህ ሲባል ይሖዋ እነዚህን ሰዎች የሚወዳቸው የቅርብ ወዳጁ አድርጎ የሚቆጥረውን ታማኙን አብርሃምን ይወድበት በነበረው መንገድ ነው ማለት ነው? (ያዕቆብ 2:23) እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ቢጠይቅበትም እንኳ በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም ሰው ደግነት ያሳያል። ሁሉም ንስሐ እንዲገቡና አኗኗራቸውን እንዲለውጡ ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ደግሞም ብዙዎች ይህን አድርገዋል። እነዚህን ሰዎች ወዳጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል።

      13, 14. ክርስቲያናዊ ፍቅር በአብዛኛው ጥልቅ የመውደድ ስሜትን እንደሚያካትት የሚያሳየው ምንድን ነው?

      13 ይሁንና አንዳንዶች አጋፔ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበትን መንገድ በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው። ምንም ዓይነት ስሜት የማይንጸባረቅበት፣ እንዲሁ በደንብና በሥርዓት ብቻ የሚመራ ፍቅር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ክርስቲያናዊ ፍቅር ብዙውን ጊዜ ጥልቅ የመውደድ ስሜትን የሚያካትት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስ “አብ ወልድን ይወዳል” ሲል በጻፈ ጊዜ የተጠቀመው አጋፔ የተባለውን ቃል ነው። ታዲያ ይህ ፍቅር ጨርሶ ስሜት የማይንጸባረቅበት ነው? በፍጹም፤ ኢየሱስ በዮሐንስ 5:20 ላይ ይህንኑ ሐሳብ ለመግለጽ ፊሌኦ የተባለውን የግሪክኛ ቃል መጠቀሙ ይህ ፍቅር የጠበቀ የመውደድ ስሜት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 3:35) የይሖዋ ፍቅር ብዙውን ጊዜ ጥልቅ ስሜትን ያካተተ ነው። እንዲህ ሲባል ግን እንዲሁ በስሜት ይመራል ማለት አይደለም። ምንጊዜም ፍቅሩን የሚገልጸው ጥበብና ፍትሕ በሚንጸባረቅባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶቹ በመመራት ነው።

      14 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሁሉም የይሖዋ ባሕርያት ፍጹም፣ ምንም እንከን የማይወጣላቸውና ማራኪ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ ማራኪ የሆነው ግን ፍቅር ነው። የፍቅርን ያህል ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ነገር የለም። የሚያስደስተው ደግሞ ከይሖዋ ባሕርያት ሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ፍቅር ነው። ይህን ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው?

      “አምላክ ፍቅር ነው”

      15. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ በተመለከተ ምን ይላል? ይህን አገላለጽ ለየት የሚያደርገውስ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

      15 መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎቹ የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት በተለየ መልኩ ስለ ፍቅር የሚናገረው አንድ ነገር አለ። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘አምላክ ኃይል ነው’ ወይም ‘አምላክ ፍትሕ ነው’ ወይም ደግሞ ‘አምላክ ጥበብ ነው’ አይሉም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት አሉት፤ የእነዚህ ባሕርያት ዋነኛ ምንጭ እሱ ከመሆኑም በላይ በጥበብ፣ በፍትሕም ሆነ በኃይል ረገድ አቻ የለውም። አራተኛውን ባሕርይ በተመለከተ ግን “አምላክ ፍቅር ነው” የሚል ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው አነጋገር ተጠቅሶ እናገኛለን።b (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ምን ማለት ነው?

      16-18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” የሚለው ለምንድን ነው? (ለ) በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጅ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ ለመግለጽ ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

      16 “አምላክ ፍቅር ነው” ሲባል “አምላክ ማለት ፍቅር ማለት ነው፤ ፍቅር ማለት አምላክ ማለት ነው” እንደማለት ያህል እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋን እንደ አንድ ረቂቅ የሆነ ባሕርይ አድርገን ልንወስደው አይገባም። ከፍቅር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ስሜቶችና ባሕርያት ያሉት አምላክ ነው። ይሁንና ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ ሲናገር “አምላክ ሁለንተናው ፍቅር ነው፤ ፍቅር ማንነቱ ነው” ብሏል። ነጥቡን በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል፦ የይሖዋ ኃይል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ያስችለዋል። ፍትሑና ጥበቡ ደግሞ ድርጊቱን ይመሩለታል። ለድርጊት የሚያነሳሳው ግን ፍቅር ነው። በተጨማሪም ሌሎቹን ባሕርያቱን የሚጠቀምባቸው ፍቅሩን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው።

      17 ብዙውን ጊዜ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል። በመሆኑም በመሠረታዊ ሥርዓት ስለሚመራው የፍቅር ዓይነት ማወቅ ከፈለግን ስለ ይሖዋ መማር ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ ሰዎችም ይህን ግሩም ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን እያከናወነ በነበረበት ወቅት ልጁን “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንሥራ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 1:26) በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የማፍቀር ችሎታ ያላቸውና በዚህ ረገድ አምላካቸውን መምሰል የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያቱን ለመግለጽ የተለያዩ ፍጥረታትን ምሳሌ አድርጎ እንደተጠቀመ አስታውስ። ይሁንና ጎላ ብሎ የሚታየውን ባሕርይውን ማለትም ፍቅሩን ለመግለጽ ምሳሌ አድርጎ የተጠቀመው በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን የሰውን ልጅ ነው።—ሕዝቅኤል 1:10

      18 በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር የምናሳይ ከሆነ ከሁሉ የላቀውን የይሖዋ ባሕርይ እያንጸባረቅን ነው ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:19) ይሁን እንጂ ይሖዋ አስቀድሞ የወደደን እንዴት ነው?

      ቀድሞ የወደደን ይሖዋ ነው

      19. በይሖዋ የፍጥረት ሥራ ውስጥ ፍቅር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

      19 ፍቅር ምንጊዜም የነበረ የይሖዋ ባሕርይ ነው። ለመሆኑ ይሖዋ ለመፍጠር እንዲነሳሳ የገፋፋው ምንድን ነው? ብቸኝነት ተሰምቶት ወይም አብሮት የሚሆን ፈልጎ አይደለም። ይሖዋ ምንም የሚጎድለው ነገር ስለሌለ ከሌላ የሚፈልገው አንዳች ነገር የለም። የሕይወትን ስጦታ የሚያደንቁ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን በመፍጠር የሕይወትን ጣዕም እንዲቀምሱ ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። “ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ የሆነው” አንድያ ልጁ ነው። (ራእይ 3:14) ከዚያም ይሖዋ አንድያ ልጁን ዋና ሠራተኛ አድርጎ በመጠቀም ከመላእክት አንስቶ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና አምጥቷል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ቆላስይስ 1:16) መላእክት ነፃነት፣ የማሰብ ችሎታና ስሜት ያላቸው ኃያል መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው፤ በመሆኑም እርስ በርሳቸው በተለይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ አግኝተዋል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ይሖዋ አስቀድሞ ስለወደዳቸው እነሱም ይወዱታል።

      20, 21. አዳምና ሔዋን ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ ምን ነገሮችን ተመልክተዋል? ሆኖም ይሖዋ ላሳያቸው ፍቅር ምን ምላሽ ሰጡ?

      20 የሰው ልጆችንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ፍቅሩን በብዙ መንገዶች አሳይቷቸዋል። መኖሪያቸው በነበረችው ኤደን ገነት ውስጥ የሚያዩት ነገር ሁሉ ፈጣሪያቸው ለእነሱ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ አምላክ በስተ ምሥራቅ፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ ተከለ፤ የሠራውንም ሰው በዚያ አስቀመጠው” ይላል። (ዘፍጥረት 2:8) ውብ የሆነ የአትክልት ስፍራ ወይም መናፈሻ አይተህ ታውቃለህ? በጣም የማረከህ ነገር ምንድን ነው? በዛፎች መካከል አልፎ የሚመጣው የፀሐይ ብርሃን? በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የሚያማምሩ አበቦች? እየተንሿሿ የሚወርደው ጅረት? የአእዋፍ ዝማሬ ወይም የተለያዩ ነፍሳት የሚያሰሙት በጣም የሚመስጥ ድምፅ? ወይስ የዛፎቹ፣ የፍራፍሬዎቹና የአበቦቹ መዓዛ? በእርግጥም እንዲህ ያለ የአትክልት ስፍራ ያስደስታል፤ ያም ቢሆን በዛሬው ጊዜ፣ በኤደን የነበረውን የአትክልት ስፍራ የሚወዳደር መናፈሻ ሊኖር አይችልም። ለምን?

      21 ያንን የአትክልት ስፍራ ያዘጋጀው ይሖዋ ራሱ ነው! በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ እጅግ ውብ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዓይን የሚማርኩ ዛፎችና ግሩም ጣዕም ያላቸው ፍሬዎች የሞሉበት ነበር። ይህ ሰፊ የአትክልት ስፍራ በቂ ውኃ ያገኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ አስደናቂ የሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት እንስሳት ይርመሰመሱበት ነበር። አዳምና ሔዋን እርካታ የሚያስገኝ ሥራንና ፍጹም የሆነ ወዳጅነትን ጨምሮ በሕይወታቸው እንዲደሰቱ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውላቸው ነበር። ይሖዋ አስቀድሞ የወደዳቸው በመሆኑ እነሱም በአጸፋው ሊወድዱት ይገባ ነበር። ይሁንና ይህን ሳያደርጉ ቀሩ። የሰማይ አባታቸውን በፍቅር ተነሳስተው ሊታዘዙት ሲገባ ራስ ወዳድ በመሆን ዓመፁበት።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 2

      22. ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን በኤደን ባመፁ ጊዜ የወሰደው እርምጃ ፍቅሩ ታማኝ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      22 ይህ ይሖዋን እጅግ እንዳሳዘነው ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁን እንጂ ይህ ዓመፅ ልቡ በሰው ልጆች ላይ እንዲጨክን አድርጎታል? በፍጹም! መጽሐፍ ቅዱስ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል። (መዝሙር 136:1) በመሆኑም የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን የአዳምና የሔዋን ዘሮች ለመዋጀት የሚያስችል ፍቅራዊ ዝግጅት እንደሚያደርግ ወዲያውኑ አስታወቀ። ቀደም ሲል እንዳየነው ይህ ዝግጅት የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆበታል።—1 ዮሐንስ 4:10

      23. ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ምንድን ነው? የሚቀጥለው ምዕራፍ ለየትኛው ጥያቄ መልስ ይሰጣል?

      23 አዎን፣ ይሖዋ ከመጀመሪያ አንስቶ ቀዳሚ በመሆን ለሰው ልጆች ፍቅሩን አሳይቷል። ይሖዋ ‘አስቀድሞ እንደወደደን’ የሚያሳዩ በርካታ ሁኔታዎች አሉ። ፍቅር ባለበት ሰላምና ደስታ ስለሚኖር ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መገለጹ ምንም አያስደንቅም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ይሁን እንጂ እዚህ ላይ አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ይነሳል። በእርግጥ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ይወደናል? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

      a “መውደድ (እንደ ቅርብ ወዳጅ ወይም ወንድም አድርጎ መመልከት)” የሚል ትርጉም ያለው ፊሌኦ የተባለው ግስ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተሠርቶበታል። ስቶርጊ የተባለው ቃል የጠበቀ ቤተሰባዊ ፍቅርን ያመለክታል፤ በ2 ጢሞቴዎስ 3:3 ላይ በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደሚጠፋ የተገለጸው የፍቅር ዓይነት ይህ ነው። ኤሮስ ወይም በተቃራኒ ፆታዎች መካከል በሚኖረው መሳሳብ የሚፈጠረው ፍቅር በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የሚናገርባቸው ቦታዎች አሉ።—ምሳሌ 5:15-20

      b ከዚህ ጋር ተመሳሳይ አገላለጽ የሚጠቀሙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል “አምላክ ብርሃን ነው” እና “አምላካችን የሚባላ እሳት ነው” የሚሉ ጥቅሶች እናገኛለን። (1 ዮሐንስ 1:5፤ ዕብራውያን 12:29) ይሁን እንጂ እነዚህ አገላለጾች ይሖዋን የሚያነጻጽሩት ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በመሆኑ ዘይቤያዊ አነጋገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። ይሖዋ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ በብርሃን ሊመሰል ይችላል። “ጨለማ” ወይም ርኩሰት በእሱ ዘንድ የለም። ኃይሉን በመጠቀም ማጥፋት የሚችል በመሆኑም ከእሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • መዝሙር 63:1-11 የይሖዋን ፍቅር ምን ያህል ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል? ይህ ፍቅርስ ምን ዓይነት የመተማመን ስሜት ያሳድርብናል?

      • ሆሴዕ 11:1-4፤ 14:4-8 ይሖዋ ለእስራኤል (ወይም ለኤፍሬም) አባታዊ ፍቅር ያሳየው በምን መንገዶች ነው? ይህን ያደረገውስ ምን በደል ፈጽመውበት እያለ ነው?

      • ማቴዎስ 5:43-48 ይሖዋ ለመላው የሰው ዘር አባታዊ ፍቅር እያሳየ ያለው እንዴት ነው?

      • ዮሐንስ 17:15-26 ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ ያቀረበው ጸሎት ይሖዋ እንደሚወደን ጥሩ ማረጋገጫ የሚሆነን እንዴት ነው?

  • “ከአምላክ ፍቅር ሊለየን” የሚችል ነገር የለም
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • በሐዘን ተውጣ እያለቀሰች ያለች ሴት።

      ምዕራፍ 24

      “ከአምላክ ፍቅር ሊለየን” የሚችል ነገር የለም

      1. አንዳንድ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ምን ዓይነት አፍራሽ ስሜት ይሰማቸዋል?

      ይሖዋ አንተን እንደሚወድህ ይሰማሃል? አንዳንዶች ዮሐንስ 3:16 እንደሚገልጸው አምላክ በጥቅሉ የሰውን ዘር እንደሚወድ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ‘አምላክ እኔን በግለሰብ ደረጃ ሊወደኝ አይችልም’ ብለው ያስባሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖችም እንኳ አልፎ አልፎ እንዲህ ያለ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረበት አንድ ሰው “አምላክ ስለ እኔ ያስባል ብዬ ማመን ይከብደኛል” ሲል ተናግሯል። አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት ይሰማሃል?

      2, 3. ‘ይሖዋ አይወደኝም ወይም ከቁብ አይቆጥረኝም’ ብለን እንድናስብ የሚፈልገው ማን ነው? እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ መዋጋት የምንችለውስ እንዴት ነው?

      2 ሰይጣን ‘ይሖዋ አይወደኝም ወይም ከቁብ አይቆጥረኝም’ ብለን እንድናስብ ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የትዕቢትና የኩራት መንፈስ እንዲያድርባቸው በማድረግ እንደሚያስት የታወቀ ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ይሁን እንጂ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡና የከንቱነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግም ያስደስተዋል። (ዮሐንስ 7:47-49፤ 8:13, 44) በተለይ ደግሞ ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ይህን ዘዴ በእጅጉ እየተጠቀመበት ይገኛል። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ያደጉት ‘ፍቅር በሌለበት’ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ሌሎች ደግሞ የዕለት ተዕለት ውሏቸው ጨካኝ፣ ራስ ወዳድና ግትር ከሆኑ ሰዎች ጋር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አንዳንዶች ለብዙ ዓመታት ሲደርስባቸው የኖረው ግፍ፣ የዘር መድልዎ ወይም ጥላቻ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው አሊያም ደግሞ የሚወዳቸው እንደሌለ ሆኖ እንዲሰማቸው አድርጓቸው ሊሆን ይችላል።

      3 እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ። ብዙዎቻችን አንዳንድ ጊዜ አላግባብ ራሳችንን እንኮንናለን። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል “ነገሮችን ለማቅናት” እና “ምሽግን ለመደርመስ” ማለትም ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ለማስወገድ እንደሚረዳ አስታውስ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4) መጽሐፍ ቅዱስ “[ልባችን] በፊቱ እንዲረጋጋ እናደርጋለን፤ ይህን የምናደርገው ልባችን እኛን በሚኮንንበት ነገር ሁሉ ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል” ይላል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ልባችን እንዲረጋጋ’ ማለትም ይሖዋ እንደሚወደን እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርጉ አራት አሳማኝ ነጥቦችን ይጠቅሱልናል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመልከት።

      በይሖዋ ፊት ውድ ነህ

      4, 5. ኢየሱስ ድንቢጦችን አስመልክቶ የተናገረው ምሳሌ በይሖዋ ፊት ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      4 በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለው በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም። የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።” (ማቴዎስ 10:29-31) እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የኢየሱስ አድማጮች ምን ትርጉም እንደነበራቸው ተመልከት።

      አንዲት ድንቢጥ ጫጩቷን ስትመግብ።

      “እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ”

      5 ‘አንድ ሰው ድንቢጥ የሚገዛበት ምን ምክንያት አለ?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። በኢየሱስ ዘመን ለምግብነት ይሸጡ ከነበሩት ወፎች ሁሉ በጣም ርካሿ ድንቢጥ ነበረች። አንድ ሰው በጣም ዝቅተኛ ዋጋ ባላት አንድ ሳንቲም ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችል እንደነበረ ልብ በል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በኋላ እንደገለጸው አንድ ሰው ሁለት ሳንቲሞች ከከፈለ አራት ሳይሆን አምስት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር። አምስተኛዋ ወፍ ምንም ዋጋ እንደሌለው ነገር በምርቃት መልክ የምትሰጥ ናት። እነዚህ ፍጥረታት በሰዎች ፊት ዋጋ አይኖራቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ፈጣሪ ለእነዚህ ፍጥረታት ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ኢየሱስ “አንዷም እንኳ [በምርቃት መልክ የምትሰጠው እንኳ ሳትቀር] በአምላክ ዘንድ አትረሳም” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 12:6, 7) ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ምን ማለት እንደፈለገ መረዳት እንችላለን። ይሖዋ ለአንዲት ድንቢጥ እንኳ ይህን ያህል ዋጋ የሚሰጥ ከሆነ ሰውንማ ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት መገመት አያዳግትም! ኢየሱስ እንደገለጸው ይሖዋ ስለ እኛ እያንዳንዷን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። የራሳችን ፀጉር እንኳ ሳይቀር የተቆጠረ ነው!

      6. ኢየሱስ የራሳችን ፀጉር እንኳ የተቆጠረ እንደሆነ ሲናገር ማጋነኑ እንዳልነበር እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      6 ፀጉር ደግሞ ይቆጠራል እንዴ? አንዳንዶች እዚህ ላይ ኢየሱስ በጣም እንዳጋነነ አድርገው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ እስቲ ስለ ትንሣኤ ተስፋ አስብ። ይሖዋ እኛን መልሶ የሚፈጥረን ምን ያህል ቢያውቀን ነው! በእሱ ፊት ውድ በመሆናችን ጀነቲካዊ ንድፋችንን እንዲሁም የብዙ ዓመት ትዝታዎቻችንንና በሕይወታችን ውስጥ የተከናወኑ ነገሮችን ጨምሮ እያንዳንዷን ነገር በሚገባ ያስታውሳል።a ከዚህ አንጻር ሲታይ በአማካይ 100,000 ገደማ የሚሆነውን ፀጉራችንን መቁጠር በጣም ቀላል ነገር ነው።

      ይሖዋ እኛን ሲመረምር የሚያተኩረው በምን ላይ ነው?

      7, 8. (ሀ) ይሖዋ የሰዎችን ልብ በሚመረምርበት ጊዜ የሚደሰተው የትኞቹን ባሕርያት ሲመለከት ነው? (ለ) ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

      7 በሁለተኛ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አገልጋዮቹን በሚመረምርበት ጊዜ ትኩረት የሚያደርገው በምን ነገር ላይ እንደሆነ ይገልጻል። በአጭር አነጋገር ይሖዋ መልካም ባሕርያችንንና የምናደርገውን ጥረት ሲመለከት ይደሰታል። ንጉሥ ዳዊት ልጁን ሰለሞንን “ይሖዋ ልብን ሁሉ ይመረምራልና፤ ሐሳብንና ውስጣዊ ዝንባሌን ሁሉ ይረዳል” ብሎታል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) አምላክ ዓመፀኛ በሆነውና በጥላቻ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ በሚመረምርበት ጊዜ ሰላምን፣ እውነትንና ጽድቅን የሚወድ ልብ ሲያገኝ ምንኛ ይደሰት ይሆን! ይሖዋ እሱን የሚወድ እንዲሁም ስለ እሱ ለመማርና እንዲህ ያለውን እውቀት ለሌሎች ማካፈል የሚፈልግ ልብ ሲያገኝ ምን ያደርጋል? ይሖዋ ስለ እሱ ለሌሎች የሚናገሩ ሰዎችን በትኩረት እንደሚመለከት ተናግሯል። እንዲያውም እሱን “ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ” ሰዎች ያዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” አለው። (ሚልክያስ 3:16) እንዲህ ያሉት ባሕርያት በይሖዋ ፊት የተወደዱ ናቸው።

      8 ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው አንዳንድ መልካም ሥራዎች ምንድን ናቸው? ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጴጥሮስ 2:21) አምላክ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው አንዱ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ነው። ሮም 10:15 “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!” ይላል። እርግጥ ብዙ ጊዜ እግሮቻችን “ያማሩ” ወይም ውብ እንደሆኑ አድርገን አናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተጠቀሱት እግሮች የሚያመለክቱት የይሖዋ አገልጋዮች ምሥራቹን ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት ነው። እንዲህ ያለው ጥረት በይሖዋ ፊት ያማረና የተወደደ ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

      9, 10. (ሀ) ይሖዋ የተለያዩ ችግሮችን በጽናት ለመቋቋም የምናደርገውን ጥረት እንደሚያደንቅ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን በተመለከተ ምን ዓይነት አፍራሽ አመለካከት የለውም?

      9 ይሖዋ የምናሳየውን ጽናትም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ማቴዎስ 24:13) ሰይጣን ይሖዋን ማምለክህን እንድትተው እንደሚፈልግ አስታውስ። እያንዳንዱን ቀን ለይሖዋ ታማኝ ሆነህ የምታሳልፍ ከሆነ ይሖዋን ለሚነቅፈው ለሰይጣን መልስ በመስጠት ረገድ የበኩልህን አስተዋጽኦ ታደርጋለህ። (ምሳሌ 27:11) ይሁንና ጸንቶ መኖር ቀላል አይደለም። የጤና እክል፣ የኑሮ ውድነት፣ ጭንቀትና ሌሎች ችግሮች እያንዳንዱን ቀን ፈታኝ ሊያደርጉብን ይችላሉ። በተጨማሪም የጠበቅነው ነገር እንዳሰብነው ቶሎ አለመፈጸሙ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። (ምሳሌ 13:12) እንዲህ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ስንጸና ይሖዋ እጅግ ይደሰታል። ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን “እንባዬን በአቁማዳህ አጠራቅም” በማለት የጠየቀው ለዚህ ነው። አክሎም “ደግሞስ በመጽሐፍህ ውስጥ ሰፍሮ የለም?” ሲል በእርግጠኝነት ተናግሯል። (መዝሙር 56:8) አዎን፣ ይሖዋ ከእሱ ጎን በታማኝነት ለመቆም ስንል የምናፈስሰውን እንባና የሚደርስብንን ሥቃይ ፈጽሞ አይረሳም። እንዲህ ያለውን መከራና ሥቃይ በጽናት ለመቋቋም የምናደርገው ጥረት በይሖዋ ዘንድ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል።

      የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም የምናሳየውን ጽናት ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል

      10 ይሁንና ራሱን የሚኮንን ልብ በአምላክ ፊት ምን ያህል ውድ እንደሆንን የሚያሳየውን ይህን ማስረጃ ላይቀበል ይችላል። ‘ከእኔ ይበልጥ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ አገልጋዮች አሉ። ይሖዋ እኔን ከእነሱ ጋር ሲያነጻጽረኝ ምንኛ ያዝንብኝ ይሆን!’ እያለ ራሱን ሊኮንን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ አንዱን ከሌላው አያወዳድርም፤ በተጨማሪም ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። (ገላትያ 6:4) ልባችንን ጠልቆ የመመርመር ችሎታ ያለው ሲሆን ያለንን ማንኛውም መልካም ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከታል።

      ይሖዋ መልካም ጎናችንን አበጥሮ ያወጣዋል

      11. ይሖዋ ለአቢያህ ካደረገው ነገር ምን ልንማር እንችላለን?

      11 በሦስተኛ ደረጃ ይሖዋ ልባችንን በሚመረምርበት ጊዜ መልካም ጎናችንን አበጥሮ ያወጣዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከሃዲ የሆነው የንጉሥ ኢዮርብዓም ሥርወ መንግሥት ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ በወሰነ ጊዜ ከንጉሡ ልጆች አንዱ የሆነው አቢያህ በወግ በማዕረግ መቀበር እንዳለበት ተናግሮ ነበር። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ . . . አንድ መልካም ነገር [አግኝቶበታል]” ይላል። (1 ነገሥት 14:1, 10-13) ይሖዋ የአቢያህን ልብ በመመርመር ያለውን “መልካም ነገር” አበጥሮ አውጥቶታል። በአቢያህ ልብ ውስጥ የተገኘው መልካም ነገር ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ይሖዋ ከፍ አድርጎ ስለተመለከተው በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል። አልፎ ተርፎም የዚያ ከሃዲ ቤተሰብ አባል ለነበረው ለዚህ ልጅ ተገቢውን ምሕረት በማሳየት ክሶታል።

      12, 13. (ሀ) ይሖዋ ለንጉሥ ኢዮሳፍጥ ያደረገው ነገር ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜም እንኳ መልካም ጎናችንን እንደሚመለከት የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ሁሉ ይሖዋም ለመልካም ባሕርያችንና ሥራዎቻችን ምን አመለካከት አለው?

      12 ይሖዋ ጥሩ ንጉሥ ለነበረው ለኢዮሳፍጥ ያደረገው ነገር በዚህ ረገድ የተሻለ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ንጉሡ ማስተዋል የጎደለው ድርጊት በፈጸመ ጊዜ የይሖዋ ነቢይ “በዚህ ምክንያት ይሖዋ በአንተ ላይ ተቆጥቷል” ብሎታል። ይህ እንዴት የሚያስደነግጥ አነጋገር ነው! ይሁን እንጂ ይሖዋ በነቢዩ በኩል ያስተላለፈው መልእክት በዚህ አላበቃም። “ይሁንና . . . መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” ሲል አክሎ ተናግሯል። (2 ዜና መዋዕል 19:1-3) በመሆኑም ይሖዋ የጽድቅ ቁጣው የኢዮሳፍጥን መልካም ነገር እንዳያይ አላገደውም። ይሖዋ ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች ምንኛ የተለየ ነው! ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሲያበሳጩን መልካም ጎናቸው አይታየንም። ራሳችንም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የሚሰማን ሐዘን፣ ኀፍረትና የጥፋተኝነት ስሜት መልካም ጎናችን እንዳይታየን ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ንስሐ ከገባንና የሠራነውን ኃጢአት ላለመድገም ጥረት ካደረግን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን አስታውስ።

      13 አንድ የወርቅ ማዕድን የሚፈልግ ሰው ወርቁን ብቻ እየለየ በማስቀረት አላስፈላጊ የሆነውን ኮረት እንደሚያስወግድ ሁሉ ይሖዋም ልብህን በሚመረምርበት ጊዜ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶችን እየለየ ያስወግዳል። መልካም ባሕርያትህንና ሥራዎችህንስ ምን ያደርጋል? እነዚህን እንደ “ተፈላጊ ማዕድናት” ለይቶ ያስቀራቸዋል! አፍቃሪ የሆኑ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በሕፃንነታቸው የሣሏቸውን ሥዕሎች ወይም የሠሯቸውን የእጅ ሥራዎች እንደ ማስታወሻ አድርገው ለረጅም ዓመታት እንደሚያስቀምጡ አስተውለሃል? ምናልባትም ልጆቹ እነዚህን ነገሮች ረስተዋቸው ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ደግሞ ከሁሉ ይበልጥ አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ነው። ከእሱ ጎን በታማኝነት እስከቆምን ድረስ መልካም ሥራዎቻችንንና ባሕርያታችንን ፈጽሞ አይረሳም። እንዲያውም እንዲህ ያሉ ነገሮችን መርሳት በይሖዋ ዘንድ ፍትሕ እንደማዛባት ይቆጠራል፤ እሱ ደግሞ ፍትሕ አያዛባም። (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋ መልካም ጎናችንን አበጥሮ የሚያወጣበት ሌላም መንገድ አለ።

      14, 15. (ሀ) ፍጽምና የጎደለን መሆናችን ይሖዋ መልካም ጎናችንን እንዳያይ ሊያግደው የማይችለው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ይሖዋ መልካም ባሕርያችን ምን እንዲሆን ያደርጋል? ታማኝ አገልጋዮቹን የሚመለከታቸውስ እንዴት ነው?

      14 ይሖዋ ካለብን አለፍጽምና ባሻገር ይመለከታል፤ ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንችል ያስተውላል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሥዕሎች ወይም ሌሎች የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለመጠገን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በለንደን ብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ባለው 30 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚያወጣ የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ሥዕል ላይ ተኩሶ ጉዳት አድርሶ ነበር፤ ይሁንና ይህ ሥዕል ጉዳት ስለደረሰበት መጣል አለበት ያለ ሰው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ወደ 500 ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ ያስቆጠረውን ይህን ድንቅ የጥበብ ሥራ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ወዲያውኑ ጥረት ማድረግ ተጀመረ። ለምን? ምክንያቱም በሥነ ጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ በጣም ውድ ስለሆነ ነው። ታዲያ አንተ በእርሳስ ከተሳለ ሥዕል እጅግ አትበልጥም? በወረስከው አለፍጽምና ምክንያት እንከን ቢኖርብህም እንኳ በአምላክ ፊት የላቀ ዋጋ እንዳለህ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 72:12-14) የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ጥበበኛው አምላክ ይሖዋ፣ ለፍቅራዊ እንክብካቤው ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ወደ ፍጽምና ደረጃ ለመመለስ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አይልም።—የሐዋርያት ሥራ 3:21፤ ሮም 8:20-22

      15 አዎን፣ ይሖዋ እኛ ራሳችን እንኳ ሳናስተውለው የምንቀረውን መልካም ጎናችንን ይመለከታል። በተጨማሪም እሱን በታማኝነት ማገልገላችንን ከቀጠልን ፍጽምና ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ መልካም ባሕርያችን እየዳበረ እንዲሄድ ያደርጋል። የሰይጣን ዓለም ለእኛ ያለው አመለካከት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደከበሩ ነገሮች አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ሐጌ 2:7

      ይሖዋ ፍቅሩን በተግባር ያሳያል

      16. ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳየው ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ምንድን ነው? ይህስ ለእያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ስጦታ እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

      16 በአራተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ብዙ ነገር አድርጓል። ሰይጣን፣ ‘ይሖዋ አይወዳችሁም’ ወይም ‘በአምላክ ፊት ዋጋ የላችሁም’ እያለ ለሚያስፋፋው ውሸት የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አጥጋቢ መልስ ይሆናል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት የደረሰበት ሥቃይም ሆነ ይሖዋ የሚወደው ልጁ ሲሞት ዝም ብሎ ማየቱ ያስከተለበት ከዚያ የባሰ ሥቃይ ይሖዋና ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚወዱን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሰዎች ይህ መሥዋዕት ለእነሱ በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ስጦታ እንደሆነ አድርገው ማመን ይከብዳቸዋል። ይህ ፈጽሞ እንደማይገባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ እንደነበረ አስታውስ። ሆኖም ‘የአምላክ ልጅ ወድዶኛል፤ ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ በማለት ተናግሯል።—ገላትያ 1:13፤ 2:20

      17. ይሖዋ ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበን እንዴት ነው?

      17 ይሖዋ ከክርስቶስ መሥዋዕት ተጠቃሚዎች እንድንሆን በግለሰብ ደረጃ በመርዳት ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 6:44) አዎን፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ወደ ልጁና ወደ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ይስበናል። እንዴት? በግለሰብ ደረጃ ምሥክርነቱ እንዲደርሰን አድርጓል፤ እንዲሁም የአቅም ገደብና አለፍጽምና ቢኖርብንም እንኳ መንፈሳዊ እውነቶችን ማስተዋልና ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል በቅዱስ መንፈሱ ይረዳናል። ይሖዋ እስራኤልን በተመለከተ “በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ። ከዚህም የተነሳ በታማኝ ፍቅር ወደ እኔ ሳብኩሽ” ሲል እንደተናገረ ሁሉ ለእኛም እንዲሁ ሊናገር ይችላል።—ኤርምያስ 31:3

      18, 19. (ሀ) ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ልናይ የምንችልበት ትልቁ መንገድ ምንድን ነው? ይህን ጉዳይ የሚከታተለው ራሱ እንደሆነ የሚያሳየውስ ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ቃል ይሖዋ ችግራችንን እንደ ራሱ አድርጎ በማየት ጸሎታችንን እንደሚያዳምጥ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?

      18 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እንደሚወደን ልናይ የምንችልበት ትልቁ መንገድ የጸሎት መብት ነው ሊባል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ እያንዳንዳችንን ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ ጸሎታችንን ይሰማል። እንዲያውም “ጸሎት ሰሚ” ተብሏል። (መዝሙር 65:2) ይህን ሥልጣን ለማንም፣ ሌላው ቀርቶ ለልጁ እንኳ አልሰጠም። ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስበው፤ የጽንፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነው አምላክ ሳንሸማቀቅ የልባችንን አውጥተን እንድንነግረው እየጋበዘን ነው። ጸሎታችንን የሚሰማውስ እንዴት ነው? በግድየለሽነትና በቀዘቀዘ ስሜት ነው? በፍጹም።

      19 ይሖዋ የሌሎችን ችግር እንደ ራሱ አድርጎ የሚያይ አምላክ ነው። አንድ በዕድሜ የገፉ ታማኝ ክርስቲያን ይህን ባሕርይ ሲገልጹት “በአንተ ሥቃይ የእኔም ልብ ይታመማል” ሲሉ ተናግረዋል። ይሖዋ የእኛ ሥቃይ ይሰማዋል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝቡ በእስራኤላውያን ላይ የደረሰውን ሥቃይ ሲመለከት ምን እንደተሰማው ሲገልጽ “በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ” ይላል። (ኢሳይያስ 63:9) ይሖዋ እንዲሁ ችግራቸውን መመልከት ብቻ ሳይሆን እሱም አብሮ ተሠቃይቷል። “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” በማለት ለአገልጋዮቹ የተናገረው ቃል ሥቃያቸው ምን ያህል እንደሚሰማው በግልጽ የሚያሳይ ነው።b (ዘካርያስ 2:8) የዓይን ብሌን ሲነካ ምን ያህል እንደሚያምም መገመት አያዳግትም! አዎን፣ ይሖዋ ስሜታችንን ይረዳል። ስንሠቃይ እሱም አብሮ ይሠቃያል።

      20. በሮም 12:3 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የትኛውን ሚዛናዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ማስወገድ ያስፈልገናል?

      20 አንድ የበሰለ ክርስቲያን አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅርና ከፍ ያለ ግምት የሚያሳየውን ይህን ማስረጃ ሰበብ አድርጎ በመጠቀም ለመኩራራት ወይም ራሱን ከፍ አድርጎ ለመመልከት አይዳዳውም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ።” (ሮም 12:3) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ” ሲል ይገልጻል። (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ስለዚህ ሰማያዊ አባታችን እንዲህ የሚወደን መሆኑ የሚያስደስተን ቢሆንም የአምላክ ፍቅር ይገባናል የምንለው እንዳልሆነ በማስታወስ ሚዛናችንን መጠበቅ ይኖርብናል።—ሉቃስ 17:10

      21. ሰይጣን የሚያስፋፋቸውን የትኞቹን ውሸቶች መቀበል የለብንም? ልባችን ይሖዋ የሰጠንን የትኛውን ማረጋገጫ እንዲቀበል ማድረግ ይኖርብናል?

      21 ‘ይሖዋ አይወዳችሁም’ ወይም ‘በአምላክ ፊት ዋጋ የላችሁም’ የሚለውን ውሸት ጨምሮ ሰይጣን የሚያስፋፋው ማንኛውም ውሸት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ። በሕይወትህ ውስጥ ያሳለፍከው ነገር፣ አምላክ የቱንም ያህል ታላቅ ፍቅር ያለው ቢሆን አንተን ሊወድህ እንደማይችል ሆኖ እንዲሰማህ አድርጎሃል? ወይም ያከናወንከው መልካም ሥራ፣ ሁሉን ማየት የሚችለው የአምላክ ዓይን እንኳ ሊያስተውለው የማይችል ኢምንት ነገር እንደሆነ ይሰማሃል? አሊያም ደግሞ የሠራኸውን ኃጢአት የአምላክ ውድ ልጅ የከፈለው መሥዋዕት እንኳ ሊሸፍነው እንደማይችል አድርገህ ታስባለህ? ከሆነ በጣም ተሳስተሃል። ሰይጣን የሚያስፋፋውን እንዲህ ያለ ውሸት ፈጽሞ መቀበል የለብህም! ልባችን ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን የሚከተለውን ሐቅ አምኖ እንዲቀበል ማድረግ ይኖርብናል፦ “ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።”—ሮም 8:38, 39

      a መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት የትንሣኤ ተስፋን ከይሖዋ የማስታወስ ችሎታ ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። ታማኙ የአምላክ አገልጋይ ኢዮብ ይሖዋን ‘ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ ባስታወስከኝ!’ ብሎታል። (ኢዮብ 14:13) ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተናግሯል። ይሖዋ ከሞት ሊያስነሳቸው የሚፈልጋቸውን ሰዎች በሚገባ የሚያስታውሳቸው በመሆኑ ይህ አነጋገር ተገቢ ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29

      b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ ሲተረጉሙ የአምላክን ሕዝብ የሚነካ የአምላክን ሳይሆን የራሱን ዓይን ወይም የእስራኤልን ሕዝብ ዓይን እንደሚነካ አድርገው ገልጸውታል። ይህ ስህተት የተፈጠረው በጥቅሱ ላይ የሰፈረው ሐሳብ አክብሮት የጎደለው እንደሆነ የተሰማቸው አንዳንድ ጸሐፊዎች ጥቅሱን በራሳቸው መንገድ ለማስተካከል በመሞከራቸው ነው። የወሰዱት የተሳሳተ እርምጃ የይሖዋ ጥልቅ የርኅራኄ ስሜት እንዲሰወር አድርጓል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • መዝሙር 139:1-24 ንጉሥ ዳዊት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በእጅጉ እንደሚያስብልን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

      • ኢሳይያስ 43:3, 4, 10-13 ይሖዋ ምሥክሮቹ ሆነው ለሚያገለግሉት ሰዎች ምን ዓይነት ስሜት አለው? ይህን ስሜቱን በተግባር የገለጸውስ እንዴት ነው?

      • ሮም 5:6-8 ኃጢአተኛ መሆናችን ከይሖዋ ፍቅር ተጠቃሚ እንዳንሆን ሊያግደን እንደማይችል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

      • ይሁዳ 17-25 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር የምንችለው እንዴት ነው? ይህንን እንዳናደርግ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን የሚችለው ነገርስ ምንድን ነው?

  • ‘ከአንጀት የሚራራልን አምላካችን’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ፊቷ ላይ የርኅራኄ ስሜት የሚነበብባት ሴት።

      ምዕራፍ 25

      ‘ከአንጀት የሚራራልን አምላካችን’

      1, 2. (ሀ) አንዲት እናት ልጇ ሲያለቅስ ምን ታደርጋለች? (ለ) እናት ለልጇ ካላት ርኅራኄ የሚበልጠው የማን ርኅራኄ ነው?

      እኩለ ሌሊት ላይ ሕፃኑ ያለቅሳል። እናትየው ወዲያውኑ ከእንቅልፏ ነቃች። የልጇ ነገር ስለሚያሳስባት እንደ ድሮው እንቅልፍ ድብን አድርጎ አይወስዳትም። ሕፃኑ ምን ፈልጎ እንዳለቀሰ ለይታ ታውቃለች። ጡት ፈልጎ፣ መታቀፍ ፈልጎ ወይም ደግሞ የሽንት ጨርቅ እንዲቀየርለት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ሕፃኑ ያለቀሰበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን የሚያስፈልገውን ታደርግለታለች። ልጇ እያለቀሰ አስችሏት ዝም ብላ አትተኛም።

      2 አንዲት እናት የአብራኳ ክፋይ ለሆነው ልጇ እጅግ ጥልቅ የሆነ ርኅራኄ ስሜት እንዳላት የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላካችን ለሰው ልጆች ያለው ርኅራኄ ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። ይህን ግሩም ባሕርይ መመርመራችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል። እንግዲያው ርኅራኄ ምን እንደሆነና አምላካችን ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቀው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።

      ርኅራኄ ምንድን ነው?

      3. “ምሕረት ማሳየት” ወይም “መራራት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ ምን ያመለክታል?

      3 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርኅራኄና በምሕረት መካከል የቅርብ ዝምድና አለ። ከአንጀት የመራራት ስሜትን የሚገልጹ በርከት ያሉ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ራኻም የተባለው የዕብራይስጥ ግስ ብዙውን ጊዜ “ምሕረት ማሳየት” ወይም “መራራት” ተብሎ ይተረጎማል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህ ግስ “የምንወዳቸውን ወይም የእኛን እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ችግር ወይም ሥቃይ ስንመለከት የሚሰማንን ጥልቅ የሆነ የርኅራኄ ስሜት” ያመለክታል። ይሖዋ ስሜቱን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ የዕብራይስጥ ቃል “ማህፀን” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ዝምድና ያለው ሲሆን “የእናት ርኅራኄ” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል።a—ዘፀአት 33:19፤ ኤርምያስ 33:26

      ልጇን እቅፍ ያደረገች እናት።

      ‘እናት ከማህፀኗ የወጣውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች?’

      4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ርኅራኄ ለመግለጽ እናት ለልጇ ያላትን ስሜት እንደ ምሳሌ አድርጎ የሚጠቀመው እንዴት ነው?

      4 መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ርኅራኄ ለመግለጽ እናት ለልጇ ያላትን ስሜት እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። በኢሳይያስ 49:15 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች? ከማህፀኗ ለወጣውስ ልጅ አትራራም [በዕብራይስጡ፣ ራኻም]? እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም።” ይህ ልብ የሚነካ አገላለጽ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ያህል እንደሚራራ ጎላ አድርጎ ያሳያል። እንዴት?

      5 አንዲት እናት፣ ሕፃን ልጇን ማጥባት ወይም መንከባከብ ትረሳለች ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። አንድ ሕፃን ሌት ተቀን የእናቱን ፍቅርና እንክብካቤ ካላገኘ በራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል የታወቀ ነው። የሚያሳዝነው ግን “ተፈጥሯዊ ፍቅር” በጠፋበት “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ልጆቻቸውን ቸል የሚሉ አልፎ ተርፎም የሚጥሉ እናቶች እንዳሉ የሚገልጹ ዘገባዎችን መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3) ይሖዋ ግን “እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም” ሲል ተናግሯል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለው ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ምንጊዜም አይለወጥም። እናት ለልጇ ካላት ርኅራኄ እንኳ የላቀ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ ኢሳይያስ 49:15⁠ን አስመልክተው ሲናገሩ “ይህ አገላለጽ የአምላክን ፍቅር በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተጠቀሱት እጅግ ልብ የሚነኩ መግለጫዎች አንዱ ምናልባትም ከሁሉ የላቀው ነው” ብለዋል።

      6. ብዙ ሰዎች ርኅራኄን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው? ሆኖም ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?

      6 ርኅራኄ የደካማነት ምልክት ነው? ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሴኔካ የተባለው በኢየሱስ ዘመን የኖረ ሮማዊ ፈላስፋና የታወቀ ምሁር “አዘኔታ የሚያሳይ ደካማ አእምሮ ያለው ነው” ሲል አስተምሯል። ሴኔካ ስሜት አልባ መሆንን የሚያበረታታው የኢስጦይኮች ፍልስፍና አራማጅ ነበር። ‘አስተዋይ ሰው ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን መርዳት ቢችልም እንዲህ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ ማሳየት የለበትም፤ ምክንያቱም ይህ አእምሮውን እረፍት ይነሳዋል’ ሲል ተናግሯል። እንዲህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት አመለካከት ሰዎች ለሌሎች ከልብ የመነጨ ርኅራኄ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው። ይሖዋ ግን እንዲህ ዓይነት አምላክ አይደለም! “ከአንጀት የሚራራና መሐሪ” አምላክ ስለመሆኑ በቃሉ ውስጥ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ያዕቆብ 5:11 የግርጌ ማስታወሻ) ደግሞም ቀጥለን እንደምንመለከተው ርኅራኄ ደካማነትን ሳይሆን ጥንካሬን የሚያሳይ አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ይህን ባሕርይ የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

      ይሖዋ ለአንድ ሕዝብ ያሳየው ርኅራኄ

      7, 8. እስራኤላውያን በጥንቷ ግብፅ መከራ የደረሰባቸው እንዴት ነው? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠ?

      7 ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገው ነገር ርኅራኄውን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ማብቂያ አካባቢ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ይኖሩ ነበር፤ በዚያ ከባድ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር። ግብፃውያን “የሸክላ ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና . . . ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን መራራ [አድርገውባቸው]” ነበር። (ዘፀአት 1:11, 14) እስራኤላውያን ሥቃዩ ሲበዛባቸው እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ታዲያ ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?

      8 ይሖዋ በእጅጉ አዘነላቸው። እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “በግብፅ የሚኖረውን የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ አስገድደው በሚያሠሯቸው ሰዎች የተነሳ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ።” (ዘፀአት 3:7) ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ሲያይ ወይም ጩኸታቸውን ሲሰማ አንጀቱ አልቻለም። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 24 ላይ እንዳየነው ይሖዋ የሌላውን ችግር እንደ ራሱ የሚያይ አዛኝ አምላክ ነው። የሕዝቡን ሥቃይ እንደ ራሱ ሥቃይ አድርጎ መመልከቱ እንዲራራ አድርጎታል። ይሁንና የይሖዋ አዘኔታ በስሜት ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ እነሱን ለመርዳት እርምጃ ወስዷል። ኢሳይያስ 63:9 “በፍቅሩና በርኅራኄው ተቤዣቸው” ይላል። ይሖዋ እስራኤላውያንን “በብርቱ እጅ” ከግብፅ ነፃ አወጣቸው። (ዘዳግም 4:34) ከዚያም በተአምር እየመገበ ለም ወደሆነች ምድር አስገባቸው።

      9, 10. (ሀ) ይሖዋ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላም በተደጋጋሚ ከጠላቶቻቸው ያድናቸው የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) በዮፍታሔ ዘመን ይሖዋ እስራኤላውያንን ነፃ ያወጣቸው ከእነማን ጭቆና ነው? ይህን እርምጃ እንዲወስድ የገፋፋውስ ምንድን ነው?

      9 ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያሳየው ርኅራኄ በዚህ ብቻ አላበቃም። እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜያት በአምላክ ላይ በማመፃቸው ለችግር ይዳረጉ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ተጸጽተው ወደ እሱ በጮኹ ቁጥር ያድናቸው ነበር። ለምን? ‘ለሕዝቡ ስለራራ ነው።’—2 ዜና መዋዕል 36:15፤ መሳፍንት 2:11-16

      10 እስቲ በዮፍታሔ ዘመን የተፈጸመውን ሁኔታ ተመልከት። እስራኤላውያን የሐሰት አማልክትን ወደማምለክ ዘወር ብለው ስለነበረ ይሖዋ ለ18 ዓመታት አሞናውያን እንዲጨቁኗቸው ፈቀደ። በመጨረሻ እስራኤላውያን ንስሐ ገቡ። መጽሐፍ ቅዱስ “እነሱም ከመካከላቸው ባዕዳን አማልክትን አስወግደው ይሖዋን አገለገሉ፤ በመሆኑም በእስራኤል ላይ እየደረሰ የነበረውን መከራ ሊታገሥ አልቻለም” በማለት ይገልጻል። (መሳፍንት 10:6-16) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ከልብ ንስሐ ከገቡ በኋላ ሲሠቃዩ ማየት አላስቻለውም። በመሆኑም የርኅራኄ አምላክ የሆነው ይሖዋ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ እንዲያወጣ ለዮፍታሔ ኃይል ሰጠው።—መሳፍንት 11:30-33

      11. ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ካደረገው ነገር ስለ ርኅራኄ ምን እንማራለን?

      11 ይሖዋ የእስራኤልን ሕዝብ የያዘበት መንገድ ስለ ርኅራኄ ምን ያስተምረናል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ርኅራኄ የተቸገረን ሰው አይቶ እንዲሁ አዝኖ ከማለፍ የበለጠ ነገር እንደሚጠይቅ እንረዳለን። አንዲት እናት ልጇ ሲያለቅስ በርኅራኄ ተገፋፍታ የሚያስፈልገውን እንደምታደርግለት የሚገልጸውን ምሳሌ አስታውስ። በተመሳሳይም ይሖዋ የሕዝቦቹን ጩኸት እየሰማ ዝም አይልም። ከዚህ ይልቅ ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ ተገፋፍቶ ሕዝቦቹ እየደረሰባቸው ካለው ሥቃይ እፎይታ የሚያገኙበትን እርምጃ ይወስዳል። በተጨማሪም ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያደረገው ነገር ርኅራኄ የደካማነት ምልክት አለመሆኑን ያሳያል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማዳን ሲል ጠንከር ያለና ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ የገፋፋው ይህ ባሕርይ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ርኅራኄ የሚያሳየው በቡድን ደረጃ ብቻ ነው?

      ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚያሳየው ርኅራኄ

      12. ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች ያለውን ርኅራኄ የሚያሳየው እንዴት ነው?

      12 ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች እንደሚራራ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ለድሆች ያሳየውን አሳቢነት እንመልከት። ይሖዋ፣ የትኛውም እስራኤላዊ አጋጣሚዎች በሚፈጥሩት ሁኔታ ሳቢያ ለድህነት ሊዳረግ እንደሚችል ያውቅ ነበር። እስራኤላውያን ለድሆች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? ይሖዋ የሚከተለውን ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፦ “በድሃው ወንድምህ ላይ ልብህ አይጨክንበት ወይም እጅህን አትጠፍበት። በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠው ልብህ ቅር እያለው መሆን የለበትም፤ ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ በሥራህ ሁሉና በምታከናውነው በማንኛውም ነገር የሚባርክህ በዚህ የተነሳ ነው።” (ዘዳግም 15:7, 10) በተጨማሪም እስራኤላውያን የእርሻቸውን ዳርና ዳር ሙልጭ አድርገው እንዳያጭዱ እንዲሁም ቃርሚያውን እንዳይለቅሙ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ማሳውን የሚቃርሙት ችግረኞች ናቸው። (ዘሌዋውያን 23:22፤ ሩት 2:2-7) ሕዝቡ በመካከላቸው ላሉት ድሆች የወጣውን ይህን አሳቢነት የተንጸባረቀበት ሕግ ከታዘዙ ችግረኛ የሆኑ ግለሰቦች ለልመና አይዳረጉም። ይህ የይሖዋን ርኅራኄ የሚያሳይ አይደለም?

      13, 14. (ሀ) ዳዊት የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከልብ እንደሚያስብልን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ‘ልባቸው ለተሰበረና መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ ቅርብ መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

      13 አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ዛሬም ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል። የሚደርስብንን መከራና ሥቃይ ሁሉ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማሉ። ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።” (መዝሙር 34:15, 18) እዚህ ላይ የተገለጹትን ሰዎች በተመለከተ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “እነዚህ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ልባቸው የተሰበረ ከመሆኑም በላይ የጥፋተኝነት ስሜት አንገታቸውን አስደፍቷቸዋል። ራሳቸውን አዋርደውና ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ፤ እንዲሁም ምንም እንደማይረቡና ከንቱ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።” እንዲህ ያሉ ሰዎች ይሖዋ ከእነሱ የራቀ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ይሆናል፤ በፊቱ ከቁብ የማይቆጠሩ በመሆናቸው ስለ እነሱ ሊያስብ እንደማይችል ሆኖ ይሰማቸዋል። ሐቁ ግን ይህ አይደለም። የዳዊት ቃላት ይሖዋ ‘ምንም እንደማይረቡ የሚሰማቸውን’ ሰዎች በፍጹም እንደማይተዋቸው ያረጋግጡልናል። ሩኅሩኅ የሆነው አምላካችን ከምንጊዜውም ይበልጥ የእሱ ድጋፍ የሚያስፈልገን በዚህ ወቅት እንደሆነ ያውቃል፤ ስለሆነም ቅርባችን ይሆናል።

      14 እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ተመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ የምትገኝ አንዲት እናት የሁለት ዓመት ልጇ በመተንፈሻ አካል ላይ በሚከሰት ከባድ ሕመም እየተሠቃየ ስለነበረ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ይዛው ሄደች። ዶክተሮቹ ልጁን ከመረመሩት በኋላ እዚያው ሆስፒታል ማደር እንዳለበት ነገሯት። በዚህ ጊዜ እናቲቱ ምን አደረገች? በሆስፒታሉ መኝታ ክፍል ውስጥ ባለ አንድ ወንበር ላይ ልጇ አጠገብ ኩርምት ብላ አደረች! ልጇ ስለታመመ ከአጠገቡ መራቅ አልፈለገችም። አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ከዚህ የበለጠ እንደሚያደርግልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! ደግሞስ የተፈጠርነው በእሱ አምሳል አይደል? (ዘፍጥረት 1:26) በመዝሙር 34:18 ላይ የሚገኙት ልብ የሚነኩ ቃላት ‘ልባችን በሚሰበርበት’ ወይም ‘መንፈሳችን በሚደቆስበት’ ወቅት ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ‘ቅርባችን እንደሚሆን’ ይገልጹልናል። በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሚራራልን ከመሆኑም በላይ በሚያስፈልገን ሁሉ ይረዳናል።

      15. ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚረዳን እንዴት ነው?

      15 ታዲያ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚረዳን እንዴት ነው? ችግሩን ያስወግድልናል ማለት ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ወደ እሱ የሚጮኹትን ሰዎች የሚረዳባቸው ብዙ ዝግጅቶች አሉት። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን የሚችል እጅግ ጠቃሚ ምክር ይዟል። በጉባኤ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በሚረዱበት ጊዜ የእሱን ርኅራኄ ለማንጸባረቅ የሚጥሩ በመንፈሳዊ የጎለመሱ የበላይ ተመልካቾችን አዘጋጅቷል። (ያዕቆብ 5:14, 15) “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደመሆኑ መጠን “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” ይሰጣል። (መዝሙር 65:2፤ ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ መንግሥት መጥቶ ችግሮችን ሁሉ እስኪያስወግድልን ድረስ ለመጽናት የሚያስችለንን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ለእነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች አመስጋኞች አይደለንም? እነዚህ የይሖዋ ርኅራኄ መግለጫዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።

      16. ይሖዋ ርኅራኄውን ያሳየበት ከሁሉ የላቀ መንገድ ምንድን ነው? ይህስ በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው?

      16 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ርኅራኄውን ከሁሉ በላቀ መንገድ ያሳየው ከማንም በላይ የሚወደውን ልጁን ለእኛ ቤዛ አድርጎ በመስጠት ነው። ይህ መሥዋዕት የይሖዋን ፍቅር የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ መዳን የምናገኝበትን በር ከፍቶልናል። ይሖዋ የቤዛውን ዝግጅት ያደረገው ለእያንዳንዳችን መሆኑን አስታውስ። የአጥማቂው ዮሐንስ አባት የሆነው ዘካርያስ ይህ ስጦታ ‘አምላካችን ከአንጀት እንደራራልን’ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ መናገሩ የተገባ ነው።—ሉቃስ 1:78

      ይሖዋ ርኅራኄ ከማሳየት የሚቆጠብበት ጊዜ

      17-19. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ርኅራኄ ገደብ እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ርኅራኄ እንዲሟጠጥ ያደረገው ምንድን ነው?

      17 የይሖዋ ርኅራኄ ገደብ እንደሌለው አድርገን ልናስብ ይገባል? በፍጹም፤ ይሖዋ በእሱ ላይ ማመፃቸውን ለሚቀጥሉ ሰዎች ርኅራኄ እንደማያሳይ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዕብራውያን 10:28) እንዲህ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ የማያሳየው ለምን እንደሆነ ለመረዳት የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ መለስ ብለን እንመልከት።

      18 ምንም እንኳ ይሖዋ እስራኤላውያንን በተደጋጋሚ ጊዜ ከጠላቶቻቸው ያዳናቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ ርኅራኄው ተሟጥጦ ነበር። እነዚህ አንገተ ደንዳና ሰዎች ጣዖት ያመልኩ የነበረ ከመሆኑም በላይ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ እስከ ማስገባት ደርሰዋል! (ሕዝቅኤል 5:11፤ 8:17, 18) በተጨማሪም እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነድና ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣ ቃሉን ይንቁና በነቢያቱ ላይ ያፌዙ ነበር።” (2 ዜና መዋዕል 36:16) እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ለእነሱ ርኅራኄ ሊያሳይ የሚችልበት ምክንያት እስኪያጣ ድረስ በዓመፅ ድርጊታቸው ገፉበት፤ በመሆኑም ይሖዋ በእነሱ ላይ የጽድቅ ቁጣ መቆጣቱ ተገቢ ነበር። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስከተለ?

      19 ይሖዋ ለሕዝቡ ርኅራኄ ከማሳየት ለመታቀብ ተገድዷል። “ምንም ዓይነት ርኅራኄም ሆነ አዘኔታ አላሳይም፤ ምሕረትም አላደርግላቸውም፤ እነሱን ከማጥፋት ምንም ነገር አያግደኝም” ሲል ተናግሯል። (ኤርምያስ 13:14) በመሆኑም ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የጠፉ ሲሆን እስራኤላውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወስደዋል። ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የአምላክ ርኅራኄ እስኪሟጠጥ ድረስ እንዲህ ማመፃቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው!—ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:21

      20, 21. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ርኅራኄው ሲሟጠጥ ምን እርምጃ ይወስዳል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የይሖዋ ርኅራኄ የሚንጸባረቅበትን የትኛውን ዝግጅት እንመረምራለን?

      20 ዛሬስ ሁኔታው እንዴት ነው? ይሖዋ አልተለወጠም። ይሖዋ ለሰው ልጆች ካለው ርኅራኄ በመነሳት ምሥክሮቹ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመላው ምድር እንዲሰብኩ አዝዟል። (ማቴዎስ 24:14) አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ የመንግሥቱን መልእክት እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:14) ሆኖም ይህ የስብከት ሥራ ለዘላለም አይቀጥልም። ይሖዋ በመከራና በሥቃይ የተሞላው ይህ ክፉ ዓለም ለዘላለም እንዲቀጥል ቢፈቅድ በምንም ዓይነት የርኅራኄ መግለጫ ሊሆን አይችልም። ይሖዋ ርኅራኄው ሲሟጠጥ በዚህ ሥርዓት ላይ እርምጃ ይወስዳል። ይሁንና ይህንን እርምጃ እንዲወስድ የሚያነሳሳውም ርኅራኄ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ‘ለቅዱስ ስሙና’ ለታማኝ አገልጋዮቹ ስለሚያስብ ነው። (ሕዝቅኤል 36:20-23) ይሖዋ ክፋትን ጠራርጎ በማጥፋት ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያመጣል። ክፉዎችን አስመልክቶ ሲናገር “ዓይኔ አያዝንም፤ ደግሞም አልራራም። የተከተሉት መንገድ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳቸው ላይ አመጣባቸዋለሁ” ብሏል።—ሕዝቅኤል 9:10

      21 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ይሖዋ ጥፋት ለሚጠብቃቸው ሰዎችም እንኳ ሳይቀር ርኅራኄ ያሳያል። ከልብ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኛ ሰዎች ከይሖዋ የምሕረት ዝግጅት መጠቀም ይችላሉ፤ ይህ የይሖዋ ይቅር ባይነት ርኅራኄው ከሚገለጽባቸው እጅግ የላቁ መንገዶች አንዱ ነው። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ምሕረት እንደሚያደርግ የሚያሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ግሩም ምሳሌያዊ አገላለጾችን እንመለከታለን።

      a ይሁንና ራኻም የተባለው የዕብራይስጥ ግስ በመዝሙር 103:13 ላይ አባት ለልጆቹ የሚያሳየውን ምሕረት ወይም ርኅራኄ ለማመልከት ተሠርቶበታል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ኤርምያስ 31:20 ይሖዋ ለሕዝቡ ምን ዓይነት ስሜት አለው? ይህስ ስለ እሱ ምን እንዲሰማህ ያደርጋል?

      • ኢዩኤል 2:12-14, 17-19 የይሖዋ ሕዝቦች እሱ ርኅራኄ እንዲያሳያቸው ከፈለጉ ምን ማድረግ አለባቸው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?

      • ዮናስ 4:1-11 ርኅራኄ የማሳየትን አስፈላጊነት ይሖዋ ለዮናስ ጥሩ አድርጎ ያስተማረው እንዴት ነው?

      • ዕብራውያን 10:26-31 የይሖዋን ምሕረት ወይም ርኅራኄ አላግባብ መጠቀም የሌለብን ለምንድን ነው?

  • ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነ አምላክ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • እየጸለየ ያለ ሰው።

      ምዕራፍ 26

      ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነ አምላክ

      1-3. (ሀ) መዝሙራዊው ዳዊት ከባድ ሸክም ሆኖበት የነበረው ምንድን ነው? ማጽናኛ ያገኘውስ እንዴት ነው? (ለ) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ምን ነገር ሸክም ሊሆንብን ይችላል? ሆኖም ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?

      መዝሙራዊው ዳዊት “የፈጸምኳቸው ስህተቶች በራሴ ላይ ያንዣብባሉ፤ እንደ ከባድ ሸክም በጣም ከብደውኛል። ደነዘዝኩ፤ ፈጽሞም ደቀቅኩ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 38:4, 8) ዳዊት የሕሊና ወቀሳ ምን ያህል ከባድ ሸክም እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ የተረበሸውን ልቡን የሚያረጋጋ ማጽናኛ አግኝቷል። ይሖዋ ኃጢአትን የሚጠላ ቢሆንም እንኳ ንስሐ የገባንና መጥፎ ድርጊቱን እርግፍ አድርጎ የተወን ሰው እንደማይጠላ ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ይቅር ማለት እንደሚፈልግ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ‘ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ’ ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 86:5

      2 እኛም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የሕሊና ወቀሳ እረፍት ሊነሳንና ከባድ ሸክም ሊሆንብን ይችላል። በሠራነው ድርጊት መጸጸታችን ተገቢ ነው። የሠራነውን ስህተት ለማረም አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይችላል። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ በጥፋተኝነት ስሜት እንዳንዋጥ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ራሱን የመኮነን ዝንባሌ ያለው ልባችን፣ ምንም ያህል ንስሐ ብንገባ ይሖዋ ይቅር እንደማይለን ሆኖ እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። በመሆኑም “ከልክ በላይ በሐዘን [ልንዋጥ]” እንችላለን፤ ሰይጣን ደግሞ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በይሖዋ ፊት ዋጋ እንደሌለንና እሱን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንን ሆኖ እንዲሰማን በማድረግ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል።—2 ቆሮንቶስ 2:5-11

      3 ይሁንና ይሖዋ የሚመለከተን በዚህ መንገድ ነው? በፍጹም! ታላቅ የሆነው የይሖዋ ፍቅር አንዱ ገጽታ ይቅር ባይነት ነው። ከልብ የመነጨ እውነተኛ የንስሐ ፍሬ ካሳየን ይቅር እንደሚለን በቃሉ አማካኝነት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 28:13) በይሖዋ ይቅር ባይነት ሙሉ በሙሉ መተማመን እንድንችል እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ ለምንና እንዴት ይቅር እንደሚል እንመርምር።

      ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነው ለምንድን ነው?

      4. ይሖዋ አፈጣጠራችንን በተመለከተ የማይዘነጋው ነገር ምንድን ነው? ይህስ እኛን በሚይዝበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

      4 ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ በሚገባ ያውቃል። መዝሙር 103:14 “እሱ እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል” ይላል። ከአፈር እንደተሠራንና በአለፍጽምና ምክንያት ድክመት ወይም ጉድለት እንዳለብን ፈጽሞ አይዘነጋም። “እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃል” የሚለው አገላለጽ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ከሸክላ ሠሪ እኛን ደግሞ እሱ ከሚሠራቸው የሸክላ ዕቃዎች ጋር እንደሚያመሳስል እንድናስታውስ ያደርገናል። (ኤርምያስ 18:2-6) ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ያለብንን ድክመት ይረዳል፤ በመሆኑም ለእሱ አመራር የምንሰጠውን ምላሽ እያየ እኛን በሚይዝበት መንገድ ላይ በደግነት ማስተካከያ ያደርጋል።

      5. የሮም መጽሐፍ ኃጢአት ያለውን ኃይል የሚገልጸው እንዴት ነው?

      5 ይሖዋ ኃጢአት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያውቃል። ቃሉ እንደሚገልጸው ኃጢአት የሰውን ዘር አንቆ የያዘ ኃይል ነው። ኃጢአት ምን ያህል ኃይል አለው? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ ወታደሮች ለአዛዣቸው ሥልጣን እንደሚገዙ ሁሉ እኛም “የኃጢአት ተገዢዎች” ነን (ሮም 3:9)፤ ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ‘ነግሧል’ (ሮም 5:21)፤ በእኛ ውስጥ ‘ይኖራል’ (ሮም 7:17, 20)፤ የኃጢአት “ሕግ” ያለማቋረጥ በውስጣችን ይሠራል፤ በሌላ አነጋገር አኗኗራችንን ሊቆጣጠረው ይሞክራል። (ሮም 7:23, 25) በእርግጥም ኃጢአት ፍጽምና የጎደለውን ሥጋችንን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎታል!—ሮም 7:21, 24

      6, 7. (ሀ) ይሖዋ ከልባቸው ንስሐ ገብተው የእሱን ምሕረት ለሚሹ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አለው? (ለ) የአምላክን ምሕረት አላግባብ ልንጠቀምበት የማይገባው ለምንድን ነው?

      6 በመሆኑም ይሖዋ እሱን ለመታዘዝ የቱንም ያህል ልባዊ ፍላጎት ቢኖረን ፍጹም በሆነ ደረጃ ልንታዘዘው እንደማንችል ያውቃል። ከልብ ንስሐ ገብተን ይቅር እንዲለን ብንለምነው ምሕረት እንደሚያደርግልን ዋስትና ሰጥቶናል። መዝሙር 51:17 “አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም” ይላል። ይሖዋ ልቡ በጥፋተኝነት ስሜት “የተሰበረንና የተደቆሰን” ሰው መቼም ቢሆን ፊት አይነሳውም።

      7 ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል አለፍጽምናችንን ለኃጢአት ማሳበቢያ በማድረግ የአምላክን ምሕረት አላግባብ ልንጠቀምበት እንችላለን ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ እንዲሁ በስሜት የሚመራ አምላክ አይደለም። ምሕረቱ ገደብ አለው። ምንም ዓይነት የንስሐ መንፈስ የማያሳዩና ሆን ብለው በልበ ደንዳናነት ኃጢአት መሥራታቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችን ይቅር አይልም። (ዕብራውያን 10:26) በሌላ በኩል ግን ከልቡ የተጸጸተን ሰው ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። አስደናቂ የሆነውን ይህን የይሖዋ ፍቅር ገጽታ ሕያው አድርገው የሚገልጹ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫዎችን እስቲ እንመልከት።

      ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላል ሲባል ምን ማለት ነው?

      8. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሲል ምን ያደረገልን ያህል ነው? ይህስ ምን እምነት ያሳድርብናል?

      8 ዳዊት ንስሐ ከገባ በኋላ “በመጨረሻ ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ ስህተቴን አልሸፋፈንኩም። . . . አንተም ስህተቴንና ኃጢአቴን ይቅር አልክ” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 32:5) እዚህ ላይ “ይቅር አልክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ማንሳት” ወይም “መሸከም” የሚል ነው። ቃሉ እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት “በደልን፣ ኃጢአትንና መተላለፍን” አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ማራቅ የሚለውን ሐሳብ በሚያስተላልፍ መንገድ ነው። በመሆኑም ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአት ከላዩ አንስቶ ያራቀለት ያህል ነበር። ይህም ዳዊት እንደ ሸክም ሆኖበት የነበረውን የጥፋተኝነት ስሜት እንዳቀለለለት ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 32:3) እኛም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ምሕረቱን ለማግኘት ከለመንን አምላክ ኃጢአታችንን ከላያችን አንስቶ እንደሚያርቅልን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—ማቴዎስ 20:28

      9. ይሖዋ ኃጢአታችንን ከእኛ ምን ያህል ያርቀዋል?

      9 ዳዊት የይሖዋን ይቅር ባይነት ለመግለጽ ሌላ ሕያው የሆነ መግለጫም ተጠቅሟል፦ “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ።” (መዝሙር 103:12) ምሥራቅ ከምዕራብ ምን ያህል ይርቃል? ምሥራቅና ምዕራብ በተለያየ ጽንፍ የሚገኙ አቅጣጫዎች እንደ መሆናቸው መጠን ፈጽሞ ሊገናኙ አይችሉም። አንድ ምሁር እንዳሉት ይህ አገላለጽ “በጣም ሩቅ፣ ከምንገምተው በላይ ሩቅ” የሆነን ቦታ ያመለክታል። ዳዊት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን ከምንገምተው በላይ ከእኛ እንደሚያርቀው ይጠቁማሉ።

      በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮች።

      “ኃጢአታችሁ . . . እንደ በረዶ ይነጣል”

      10. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ኃጢአታችን ያስከተለብንን ኀፍረት ተሸክመን እንደምንኖር ሆኖ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?

      10 የመነቸከ ነጭ ልብስ ለማስለቀቅ ሞክረህ ታውቃለህ? የቱንም ያህል ብትፈትገው ቆሻሻው አልለቅ ይል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይቅር ባይነቱን እንዴት እንደገለጸው ልብ በል፦ “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደማቅ ቀይ ጨርቅ ቢቀላም እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ይሆናል።”a (ኢሳይያስ 1:18) በራሳችን ጥረት ኃጢአታችንን ልናጠራ ወይም ልናስወግድ አንችልም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደ ደም የቀላውን ወይም እንደ ደማቅ ቀይ የሆነውን ኃጢአታችንን እንደ በረዶ ወይም እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ነጭ ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም ይሖዋ ኃጢአታችንን አንዴ ይቅር ካለን በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ሁሉ ኃጢአታችን ያስከተለብንን ኀፍረት ተሸክመን እንደምንኖር ሆኖ ሊሰማን አይገባም።

      11. ይሖዋ ኃጢአታችንን ወደ ኋላው ይጥላል ሲባል ምን ማለት ነው?

      11 ሕዝቅያስ ታሞ ከሞት አፋፍ ከተረፈ በኋላ ባቀናበረው ስሜት የሚነካ የምስጋና መዝሙር ላይ ይሖዋን “ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ” ብሎታል። (ኢሳይያስ 38:17) ይህ ጥቅስ ይሖዋ፣ ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛ የሠራውን ኃጢአት ወደ ኋላው በመጣል ዳግመኛ እንደማያየውና ትኩረት እንደማይሰጠው የሚጠቁም አገላለጽ ይዟል። አንድ ጽሑፍ እንደሚለው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ “[ኃጢአቴን] ያልነበረ ያህል አደረግኸው” እንደ ማለት ነው። ይህ የሚያጽናና አይደለም?

      12. ነቢዩ ሚክያስ ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን ለዘለቄታው እንደሚያስወግደው ያመለከተው እንዴት ነው?

      12 ነቢዩ ሚክያስ፣ ተሃድሶን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ሕዝቦቹን ይቅር እንደሚል ያለውን ጠንካራ እምነት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የርስቱን ቀሪዎች [በደል] የሚያልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? . . . ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ ጥልቅ ባሕር ትጥላለህ።” (ሚክያስ 7:18, 19) እነዚህ ቃላት በጥንት ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው አስብ። በዚያ ዘመን “ወደ ጥልቅ ባሕር” የተጣለን ነገር መልሶ ማግኘት የሚቻልበት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበረም። በመሆኑም የሚክያስ ቃላት ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን ለዘለቄታው እንደሚያስወግድ የሚያመለክቱ ናቸው።

      13. “ዕዳችንን ይቅር በለን” የሚለው የኢየሱስ አነጋገር ምን ትርጉም አለው?

      13 ኢየሱስ የይሖዋን ይቅር ባይነት ለማስረዳት በአበዳሪና በተበዳሪ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። “በደላችንን [“ዕዳችንን፣” የግርጌ ማስታወሻ] ይቅር በለን” ብለን እንድንጸልይ መክሮናል። (ማቴዎስ 6:12) በመሆኑም ኢየሱስ ኃጢአትን ከዕዳ ጋር አመሳስሎ ገልጾታል። (ሉቃስ 11:4 የግርጌ ማስታወሻ) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የይሖዋ ‘ባለዕዳ’ እንሆናለን። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “ይቅር በለን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ “ዕዳን መተው፣ መሰረዝ ወይም አለማስከፈል” የሚል ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል። በመሆኑም ይሖዋ ይቅር ሲለን በእሱ ላይ ያለብንን ዕዳ የሰረዘልን ያህል ነው። ይህም ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን የሚያጽናና ነው። ይሖዋ ዕዳን አንዴ ከሰረዘ መልሶ አይጠይቅም።—መዝሙር 32:1, 2

      14. “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ” የሚለው ሐረግ የይሖዋን ምሕረት ግልጽ የሚያደርገው እንዴት ነው?

      14 በሐዋርያት ሥራ 3:19 ላይ ደግሞ የይሖዋ ይቅር ባይነት በዚህ መልኩ ተገልጿል፦ “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱ።” “እንዲደመሰስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ “ሙልጭ አድርጎ መጥረግን፣ . . . መሰረዝን ወይም ማጥፋትን” ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት እዚህ ላይ ያለው አገላለጽ አንድን የእጅ ጽሑፍ ማጥፋትን የሚጠቁም ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙበት የነበረው ቀለም ከካርቦን፣ ከሙጫና ከውኃ የተሠራ ነበር። አንድ ሰው በዚህ ቀለም ሲጽፍ ከቆየ በኋላ ጽሑፉን በእርጥብ ስፖንጅ ሙልጭ አድርጎ ሊያጠፋው ይችል ነበር። ይህ የይሖዋን ምሕረት የሚያሳይ ግሩም መግለጫ ነው። ኃጢአታችንን ይቅር በሚልበት ጊዜ በስፖንጅ ሙልጭ አድርጎ የማጥፋት ያህል ሙሉ በሙሉ ይደመስሰዋል።

      15. ይሖዋ ምን እንድናውቅ ይፈልጋል?

      15 እነዚህን የተለያዩ ዘይቤያዊ አገላለጾች ስንመረምር፣ ይሖዋ ከልባችን ንስሐ እስከገባን ድረስ እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን እንድናውቅ እንደሚፈልግ በግልጽ እንረዳለን። ኃጢአታችንን በሌላ ጊዜ እንደሚያነሳብን በማሰብ ስጋት ሊያድርብን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ታላቅ ምሕረት የሚነግረን ሌላው ነገር ይህን ያረጋግጥልናል፤ ይህም ይሖዋ ይቅር ሲል የሠራነውን ኃጢአት እንደሚረሳው የሚገልጸው ሐሳብ ነው።

      ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን እንድናውቅ ይፈልጋል

      “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም”

      16, 17. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ኃጢአታችንን እንደሚረሳው ሲናገር ምን ማለቱ ነው? አብራራ።

      16 ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉትን ሰዎች በተመለከተ “በደላቸውን ይቅር እላለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም” ሲል ቃል ገብቷል። (ኤርምያስ 31:34) እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ይቅር ሲል የሠራነውን ኃጢአት ማስታወስ ይሳነዋል ማለት ነው? በፍጹም፣ እንደዚያ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊትን ጨምሮ የይሖዋን ምሕረት ያገኙ በርካታ ሰዎች ስለሠሯቸው ኃጢአቶች ይናገራል። (2 ሳሙኤል 11:1-17፤ 12:13) ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ካላቸው በኋላም የፈጸሙትን ድርጊት እንደሚያውቅ ግልጽ ነው። የሠሩትን ኃጢአትም ሆነ ያሳዩትን የንስሐ ፍሬ እንዲሁም ይሖዋ ያደረገላቸውን ምሕረት የሚገልጸው ዘገባ ለትምህርታችን ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ እንዲቆይ ተደርጓል። (ሮም 15:4) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ይቅር ያላቸው ሰዎች የሠሩትን ኃጢአት ‘አያስታውስም’ ሲል ምን ማለቱ ነው?

      17 “ከእንግዲህ አላስታውስም” የሚለው ሐረግ ላይ ‘ማስታወስ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ የሚያመለክተው እንዲሁ ያለፈውን ነገር ወደ አእምሮ መልሶ ማምጣትን አይደለም። ቲኦሎጂካል ወርድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ቃሉ “ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የሚል መልእክትም ያስተላልፋል።” ከዚህ አንጻር ሲታይ ኃጢአትን ‘ማሰብ’ ወይም ‘ማስታወስ’ የሚለው አነጋገር በኃጢአተኞች ላይ እርምጃ መውሰድንም ያመለክታል። (ሆሴዕ 9:9) ሆኖም አምላክ “ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስታውስም” ብሎ ሲናገር ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን አንዴ ይቅር ካለ ወደፊት በዚያ ኃጢአት ምክንያት እንደማይቀጣቸው ማረጋገጫ መስጠቱ ነው። (ሕዝቅኤል 18:21, 22) በመሆኑም ይሖዋ ኃጢአታችንን ይረሳዋል ሲባል የፈጸምነውን ድርጊት በየጊዜው እያነሳ በተደጋጋሚ አይቀጣንም ማለት ነው። ይሖዋ ይቅር የሚልና ኃጢአታችንን የሚረሳ መሆኑ የሚያጽናና አይደለም?

      የፈጸምነው ኃጢአት የሚያስከትለው መዘዝስ?

      18. ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛ የይሖዋን ምሕረት አገኘ ማለት የፈጸመው ድርጊት ከሚያስከትልበት መዘዝ ሁሉ ነፃ ይሆናል ማለት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

      18 ይሖዋ ንስሐ የገባን አንድ ኃጢአተኛ ይቅር ሲለው ግለሰቡ ኃጢአቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ኃጢአት ከሠራን የፈጸምነው ድርጊት ከሚያስከትልብን መዘዝ ነፃ እንሆናለን ብለን ልንጠብቅ አንችልም። ጳውሎስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:7) በፈጸምነው ድርጊት ሳቢያ አንዳንድ ችግሮች ሊደርሱብን ይችላሉ። ይህ ማለት ግን ይሖዋ ይቅር ካለን በኋላ መከራ እንዲደርስብን ያደርጋል ማለት አይደለም። አንድ ክርስቲያን ችግር ሲገጥመው ‘ይሖዋ ቀደም ሲል ለሠራሁት ኃጢአት እየቀጣኝ ይሆናል’ ብሎ ማሰብ የለበትም። (ያዕቆብ 1:13) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ የፈጸምነው ድርጊት የሚያስከትልብንን መዘዝ እንዳንቀምስ አይከላከልልንም። ፍቺ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ በሰዎች ዘንድ የነበረንን አመኔታ ወይም ክብር ማጣት፤ እነዚህ ነገሮች በሠራነው ኃጢአት ምክንያት የሚመጡ ልናስወግዳቸው የማንችላቸው መዘዞች ናቸው። ይሖዋ ንጉሥ ዳዊትን ከቤርሳቤህና ከኦርዮ ጋር በተያያዘ ለፈጸመው ኃጢአት ይቅር ካለው በኋላም እንኳ ድርጊቱ ካስከተለበት ከባድ መዘዝ እንዳልታደገው አስታውስ።—2 ሳሙኤል 12:9-12

      19-21. (ሀ) በዘሌዋውያን 6:1-7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሕግ ተበዳዩንም ሆነ በዳዩን ወገን የሚጠቅመው እንዴት ነው? (ለ) በሠራነው ኃጢአት ምክንያት ሌሎች ተጎድተው ከሆነ ይሖዋ ምን እርምጃ እንድንወስድ ይፈልጋል?

      19 በፈጸምነው ድርጊት ሌሎች ሰዎችም ተጎድተው ከሆነ የሠራነው ኃጢአት ተጨማሪ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። በዚህ ምዕራፍ ላይ የሰፈረው የሙሴ ሕግ አንድ ሰው የሌላውን እስራኤላዊ ንብረት በመስረቅ፣ በመቀማት ወይም አጭበርብሮ በመውሰድ ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ ሊደረግ ስለሚገባው ነገር ይናገራል። ኃጢአተኛው ጥፋተኛ መሆኑን ሊክድ ብሎም በሐሰት እስከ መማል ሊደርስ ይችላል። በዚህ ጊዜ ድርጊቱ ሲፈጸም ያየ ምሥክር ላይኖር ይችላል። ይሁንና ከጊዜ በኋላ በደሉን የፈጸመው ሰው ሕሊናው ይወቅሰውና ኃጢአቱን ይናዘዛል። ይህ ሰው የአምላክን ምሕረት ማግኘት እንዲችል ኃጢአቱን ከመናዘዝ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ነገሮች ማድረግ ይጠበቅበታል፦ የወሰደውን መመለስ፣ የሰረቀውን ንብረት ዋጋ 20 በመቶ የሚሆን ካሳ መክፈልና የበደል መሥዋዕት እንዲሆን አውራ በግ ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር። ከዚያም ሕጉ እንደሚለው ካህኑ “በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ እሱም [በደሉ] ይቅር ይባልለታል።”—ዘሌዋውያን 6:1-7

      20 ይህ ሕግ የአምላክን ምሕረት የሚያንጸባርቅ ዝግጅት ነው። ተበዳዩን ወገን ይጠቅማል፤ ምክንያቱም የጠፋበትን ንብረት መልሶ ያገኛል፣ ጥፋተኛው ሰው የሠራውን ኃጢአት ያመነለት መሆኑም ደስ እንደሚያሰኘው የታወቀ ነው። በተጨማሪም ሕጉ፣ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ተገቢውን እርምጃ ለሚወስደው ግለሰብም ትልቅ ጥቅም አለው። ምክንያቱም ጥፋቱን አምኖ ለመስተካከል ፈቃደኛ ካልሆነ የአምላክን ምሕረት ማግኘት አይችልም።

      21 ምንም እንኳ እኛ በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ይህ ሕግ ይሖዋ ስለ ይቅር ባይነት ያለውን አመለካከት ጨምሮ የእሱን አስተሳሰብ ይበልጥ እንድንረዳ ያግዘናል። (ቆላስይስ 2:13, 14) እኛ በሠራነው ኃጢአት ሌሎች ተጎድተው ከሆነ አምላክ የበደልናቸውን ሰዎች ለመካስ የምንችለውን ሁሉ ጥረት ስናደርግ ሲያይ በጣም ይደሰታል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ይህም ጥፋታችንን አምነን መቀበልና የበደልነውን ሰው ይቅርታ መጠየቅን ሊጨምር ይችላል። ከዚያም በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመን እንችላለን፤ ይህን ስናደርግ ይሖዋ ምሕረቱን እንዳገኘን እንድንተማመን ያደርገናል።—ዕብራውያን 10:21, 22

      22. የይሖዋ ምሕረት ምን ነገርንም ሊያካትት ይችላል?

      22 እንደ ማንኛውም አፍቃሪ ወላጅ ሁሉ ይሖዋም ምሕረት በሚያደርግበት ጊዜ ተግሣጽ ሊሰጥም ይችላል። (ምሳሌ 3:11, 12) ንስሐ የገባ አንድ ክርስቲያን የሽምግልና፣ የጉባኤ አገልጋይነት ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት መብቱን ሊያጣ ይችላል። ከፍ አድርጎ ይመለከታቸው የነበሩትን መብቶች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ማጣቱ ከባድ ሐዘን ሊያስከትልበት ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ተግሣጽ ስለተሰጠው ይሖዋ ምሕረት አላደረገለትም ማለት አይደለም። ይሖዋ የሚገሥጸን ስለሚወደን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ተግሣጹን መቀበላችንና ተግባራዊ ማድረጋችን የሚጠቅመው እኛኑ ነው።—ዕብራውያን 12:5-11

      23. የይሖዋን ምሕረት ልናገኝ እንደማንችል ሆኖ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው? የእሱን የይቅር ባይነት ባሕርይ ለመኮረጅ ጥረት ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

      23 አምላካችን ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ምንም ያህል ከባድ ስህተት ብንሠራ የይሖዋን ምሕረት ልናገኝ እንደማንችል ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ከልብ ንስሐ ከገባን፣ የሠራነውን ስህተት ለማረም አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰድንና በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ምሕረት ለማግኘት አጥብቀን ከጸለይን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (1 ዮሐንስ 1:9) እንግዲያው እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ረገድ የይሖዋን የይቅር ባይነት ባሕርይ ለመኮረጅ ጥረት እናድርግ። ኃጢአት የማይሠራው አምላካችን ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ይቅር የሚለን ከሆነ ኃጢአተኛ የሆንነው እኛ የሰው ልጆች እርስ በርስ ይቅር ለመባባል የተቻለንን ጥረት ማድረግ አይገባንም?

      a አንድ ምሁር እንደገለጹት እዚህ ላይ “እንደ ደም” ተብሎ የተተረጎመው የቀለም ዓይነት “የማይለቅ ወይም የማይደበዝዝ ነው። እርጥበት፣ ዝናብ፣ እጥበት ወይም የረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊያስለቅቀው አይችልም።”

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • 2 ዜና መዋዕል 33:1-13 ይሖዋ ምናሴን ይቅር ያለው ለምንድን ነው? ይህስ ስለ ይሖዋ ምሕረት ምን ያስተምረናል?

      • ማቴዎስ 6:12, 14, 15 ሌሎችን ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እስካለ ድረስ ይቅር ባይ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

      • ሉቃስ 15:11-32 ይህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ያስተምረናል? ይህስ ምን እንዲሰማህ ያደርጋል?

      • 2 ቆሮንቶስ 7:8-11 የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

  • “ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • የበሰሉ የወይን ዘለላዎች።

      ምዕራፍ 27

      “ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”

      1, 2. የአምላክ ጥሩነት ምን ያህል ሰፊ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ባሕርይ ጎላ አድርጎ የሚገልጸውስ እንዴት ነው?

      በመጥለቅ ላይ ያለችው ፀሐይ የፈጠረችው ውብ እይታ አካባቢውን ግርማ ሞገስ አላብሶታል፤ በጣም የሚቀራረቡ ጥቂት ጓደኛሞች ይህን የተፈጥሮ ውበት እያደነቁና እርስ በርስ እየተጨዋወቱ ደጅ ላይ ቁጭ ብለው እየተመገቡ ነው። በሌላ ቦታ የሚገኝ አንድ ገበሬ ጥቁር ደመና ያዘለው ሰማይ ማንጠባጠብ በመጀመሩ እርሻው ዝናብ ሊያገኝ እንደሆነ በማሰብ እጅግ ተደስቷል። አንድ ባልና ሚስት ደግሞ ሕፃን ልጃቸው እየተውተረተረ ለመራመድ ሲሞክር በማየታቸው በጣም ተደስተዋል።

      2 እነዚህ ሰዎች አወቁትም አላወቁት ይህን ደስታ ሊያጣጥሙ የቻሉት በይሖዋ አምላክ ጥሩነት ነው። የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ጊዜ “እግዚአብሔር መልካም ነው” ብለው ሲናገሩ እንሰማለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የአምላክ ባሕርይ የሚገልጽበት መንገድ ግን የበለጠ ኃይል አለው፤ “ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!” ይላል። (ዘካርያስ 9:17) ሆኖም በዛሬው ጊዜ ይህ አባባል ምን ትርጉም እንዳለው የሚያስተውሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል። ለመሆኑ የይሖዋ አምላክ ጥሩነት ምን ነገሮችን ይጨምራል? ይህ የአምላክ ባሕርይ እያንዳንዳችንን የሚነካንስ እንዴት ነው?

      የአምላክ ፍቅር አቢይ ገጽታ

      3, 4. ጥሩነት ምንድን ነው? ጥሩነት የይሖዋ ፍቅር መግለጫ ነው ቢባል ይበልጥ ተስማሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

      3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው ጥሩነት በዋነኝነት የሚያመለክተው ቀናነትን እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባርን ነው። በመሆኑም ጥሩነት የማይነካው የይሖዋ ማንነት ገጽታ የለም ማለት ይችላል። ኃይሉን፣ ፍትሑንና ጥበቡን ጨምሮ የይሖዋ ባሕርያት በሙሉ ጥሩነቱን የሚያሳዩ ናቸው። ከሁሉ ይበልጥ ግን ጥሩነት የይሖዋ ፍቅር መግለጫ ነው ቢባል ይበልጥ ተስማሚ ነው። ለምን?

      4 ጥሩነት በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከጽድቅ ይልቅ ጥሩነት በሰዎች ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ባሕርይ እንደሆነ ገልጿል። (ሮም 5:7) ጻድቅ ሰው ሕጉ የሚጠይቅበትን ምንም ሳያጓድል ሊያደርግ ይችላል፤ ጥሩ ሰው ግን ከዚያ አልፎ ይሄዳል። በራሱ ተነሳስቶ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ይጥራል። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ከዚህ አንጻር ይሖዋ በእርግጥም ጥሩ ነው። ይህ ጥሩነቱ ወደር ከማይገኝለት ፍቅሩ የሚመነጭ እንደሆነ ግልጽ ነው።

      5-7. ኢየሱስ “ጥሩ መምህር” ተብሎ መጠራት ያልፈለገው ለምንድን ነው? እግረ መንገዱን ምን መሠረታዊ እውነት ማስገንዘብ ፈልጎ ነበር?

      5 ይሖዋ በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የለውም። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ አንድ ሰው “ጥሩ መምህር ሆይ” ብሎ በመጥራት አንድ ጥያቄ አቀረበለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” በማለት መለሰለት። (ማርቆስ 10:17, 18) ይህ የኢየሱስ መልስ ግር ሊልህ ይችል ይሆናል። ኢየሱስ ሰውየውን ያረመው ለምንድን ነው? ደግሞስ ኢየሱስ “ጥሩ መምህር” አይደለም እንዴ?

      6 ይህ ሰው “ጥሩ መምህር” የሚለውን መግለጫ የተጠቀመው እንዲሁ ኢየሱስን ለመካብ ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስ ራሱን ዝቅ በማድረግ ይህን ክብር ማግኘት ያለበት በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሰማያዊ አባቱ እንደሆነ አመልክቷል። (ምሳሌ 11:2) ሆኖም ኢየሱስ እግረ መንገዱንም አንድ መሠረታዊ እውነት ማስገንዘብ ፈልጎ ነበር። የመጨረሻው የጥሩነት መሥፈርት ይሖዋ ራሱ ነው። የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ጥሩና መጥፎ የሆነውን የመወሰን መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። አዳምና ሔዋን መልካምና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ በመብላት በአምላክ ትእዛዝ ላይ ባመፁበት ወቅት ይህን መብት ለራሳቸው መውሰድ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ ግን ይህን መሥፈርት የማውጣት መብት የአባቱ መሆኑን በትሕትና አምኖ ተቀብሏል።

      7 ደግሞም ኢየሱስ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ያውቅ ነበር። “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ከእሱ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ በልግስና በመስጠት ጥሩ አምላክ መሆኑን ያሳየባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

      ማለቂያ የሌለውን የይሖዋ ጥሩነት የሚያሳይ ማስረጃ

      8. ይሖዋ ለሰው ዘር በሙሉ ጥሩነቱን ያሳየው እንዴት ነው?

      8 የይሖዋን ጥሩነት ያልቀመሰ አንድም ፍጡር የለም። መዝሙር 145:9 “ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው” ይላል። ሁሉን አቀፍ የሆነውን የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 14:17) ጥሩ ምግብ በልተህ የተደሰትክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ይሖዋ በጥሩነቱ ተገፋፍቶ በምድር ላይ የማያቋርጥ የውኃ ዑደት እንዲኖርና የተትረፈረፈ እህል የሚመረትባቸው “ፍሬያማ ወቅቶች” እንዲፈራረቁ ባያደርግ ኖሮ እንዲህ ያለ ምግብ ማግኘት አትችልም ነበር። ይሖዋ ይህን ጥሩነት ያሳየው ለሚወዱት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው። ኢየሱስ “እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:45

      9. ፖም የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

      9 ብዙዎች ፀሐዩንም ሆነ ዝናቡን እንደ ልብ ስለሚያገኙ፣ ወቅቶችም ጊዜያቸውን ጠብቀው ስለሚፈራረቁ ይሖዋ ለሰው ልጆች ያደረገውን የተትረፈረፈ ልግስና አቅልለው ሊመለከቱት ይችላሉ። እስቲ ፖምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በወይና ደጋ አካባቢዎች በብዛት የሚገኝ ፍሬ ነው። ፖም ሲያዩት የሚማርክ፣ ሲገምጡት ጣፋጭና ውኃው የሚያረካ፣ ደግሞም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች የሞሉበት ፍሬ ነው። ለመሆኑ በዓለም ዙሪያ 7,500 ገደማ የሚሆኑ የተለያዩ የፖም ዓይነቶች እንዳሉ ታውቃለህ? ቀይ፣ ወርቃማ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴና ሌሎች የተለያዩ ቀለማት አሉት፤ መጠኑም ቢሆን ከወይን ፍሬ ትንሽ ከፍ ከምትለዋ አነስተኛ ፖም አንስቶ ትልቅ ብርቱካን እስከሚያህለው ድረስ የተለያየ ነው። አንዲት የፖም ዘር እንዲሁ ስትታይ ብዙ የሚያስደንቅ ነገር የላትም። ሆኖም በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት የዛፍ ዓይነቶች አንዱ የሚበቅለው ከዚህች አነስተኛ ዘር ነው። (መኃልየ መኃልይ 2:3) የፖም ዛፍ በጸደይ ወቅት በሚያማምሩ አበቦች የሚያሸበርቅ ሲሆን በመከር ወቅት ደግሞ ብዙ ፍሬ ያፈራል። እያንዳንዱ ዛፍ ለ75 ዓመታት ያህል በየዓመቱ 400 ኪሎ ገደማ ፍሬ ይሰጣል!

      ይሖዋ ‘ከሰማይ ዝናብ ያዘንባል፤ ፍሬያማ ወቅቶችንም ይሰጠናል’

      የበሰሉ የፖም ፍሬዎች ያሉበት የፍራፍሬ እርሻ። የውስጠኛው ፎቶግራፍ፦ ትንሽ የፖም ዘር በጣቶቹ የያዘ ሰው።

      ከዚህች አነስተኛ ዘር የሚበቅለው ዛፍ ሰዎችን ለብዙ ዓመታት የሚመግብና የሚያረካ ፍሬ ይሰጣል

      10, 11. የስሜት ሕዋሶቻችን የአምላክን ጥሩነት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

      10 ይሖዋ ማለቂያ በሌለው ጥሩነቱ ተገፋፍቶ “ድንቅ” አካል ሰጥቶናል፤ አካላችን በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ለመደሰት የሚያስችሉ የስሜት ሕዋሳት አሉት። (መዝሙር 139:14) በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተገለጹትን ትዕይንቶች መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። በደስታ የሚፍለቀለቀው ሕፃን፤ ማሳው ላይ ሿ እያለ የሚወርደው ዝናብ፤ ፀሐይ ስትጠልቅ በቀይ፣ በወርቃማና በሐምራዊ ቀለማት የሚያጌጠው ሰማይ። እነዚህን ነገሮች ማየት ልብን በሐሴት የሚሞላ አይደለም? የሰው ዓይን በመቶ ሺዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀለማትን መለየት ይችላል! የመስማት የስሜት ሕዋሳችን የተለያዩ የድምፅ ቃናዎችን፣ በዛፎች መካከል የሚሰማውን የነፋስ ሽውታና የሕፃን ልጅን ሳቅ መለየት ይችላል። እንዲህ ባሉ እይታዎችና ድምፆች መደሰት የቻልነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፣ ሁለቱንም የሠራው ይሖዋ ነው” ይላል። (ምሳሌ 20:12) ይሁንና እነዚህ ከስሜት ሕዋሶቻችን መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው።

      11 የማሽተት የስሜት ሕዋሳችን ሌላው የይሖዋ ጥሩነት ማስረጃ ነው። የሰው አፍንጫ እጅግ በጣም ብዙ ሽታዎችን መለየት ይችላል፤ አንዳንዶች በሺዎች አልፎ ተርፎም በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ሽታዎችን መለየት እንደሚችል ይገምታሉ። ለአብነት ያህል እስቲ እነዚህን አስብ፦ ሽታው ምራቅ የሚያስውጥ ምግብ፣ የአበቦች መዓዛ፣ የእርጥብ አፈር ሽታ፣ በክረምት ከብበን ከምንሞቀው እሳት የሚወጣው ጭስ። በተጨማሪም የመዳሰስ የስሜት ሕዋስ ባይኖርህ ኖሮ አንድ ሰው ሲስምህም ሆነ አቅፎ ሲያበረታታህ ልዩ የሆነ ስሜት ሊሰማህ አይችልም ነበር፤ አንድን ፍሬ በእጅህ በመዳበስ ልስላሴውን ማወቅ የምትችለውም ይህ የስሜት ሕዋስ ስላለህ ነው። ፍሬውን ገምጠህ ማጣጣም የምትችለው ደግሞ የመቅመስ የስሜት ሕዋስ ስላለህ ነው። በምላሳችን ላይ የሚገኙት ሕዋሳት በፍሬው ውስጥ በሚገኙ ኬሚካሎች የረቀቀ ውህደት የተፈጠሩትን ልዩ ልዩ ጣዕሞች መለየት ይችላሉ። በእርግጥም “ጥሩነትህ ምንኛ ብዙ ነው! አንተን ለሚፈሩ ጠብቀህ አቆይተኸዋል” ብለን እንድንናገር የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። (መዝሙር 31:19) ይሁንና ይሖዋ ለሚፈሩት ሰዎች ጥሩነቱን ጠብቆ ያቆየው እንዴት ነው?

      ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ጥሩነት

      12. ይሖዋ ካደረገልን ዝግጅቶች መካከል ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው ነው? ለምንስ?

      12 ኢየሱስ “‘ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) በእርግጥም ይሖዋ ያደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኙልን በመሆናቸው እሱ ከሰጠን ሰብዓዊ ምግብም ይበልጥ ጠቃሚ ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ ይሖዋ ለማደስ በሚጠቀምበት ኃይሉ አማካኝነት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት መንፈሳዊ ገነት እውን እንዲሆን እንዳደረገ ተመልክተናል። የዚህ መንፈሳዊ ገነት አንዱ ቁልፍ ገጽታ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ነው።

      13, 14. (ሀ) ነቢዩ ሕዝቅኤል በራእይ ምን ተመልክቷል? ይህስ ራእይ ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ያደረገው ሕይወት ሰጪ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት ምንድን ነው?

      13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ የተሃድሶ ትንቢቶች አንዱ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል ዳግም የተገነባና ክብር የተጎናጸፈ ቤተ መቅደስ በራእይ እንደተመለከተ የሚገልጸው ነው። ከዚህ ቤተ መቅደስ ውኃ ይፈስ የነበረ ሲሆን ውኃው እየሰፋና ጥልቀቱ እየጨመረ ሄዶ ወንዝ ይሆናል። ወንዙ በሚፈስበት አቅጣጫ ሁሉ መልካም ነገር ያስገኛል። በወንዙ ዳርና ዳርም ለምግብነትና ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ብዙ ዛፎች በቅለዋል። ይህ ወንዝ ጨዋማና ሕይወት አልባ የሆነው የሙት ባሕር እንኳ ሕይወት እንዲገኝበት አድርጓል! (ሕዝቅኤል 47:1-12) ሆኖም የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?

      14 ስለ ቤተ መቅደሱ የሚገልጸው ራእይ ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ መልሶ እንደሚያቋቁም የሚያመለክት ነው። ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ እንደገና የእሱን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚያሟላ ይሆናል። በራእዩ ላይ እንደታየው ወንዝ ሁሉ፣ አምላክ ለዘላለም ሕይወት ያደረገው ዝግጅትም በየጊዜው እየጨመረ ነው። ንጹሕ አምልኮ መልሶ ከተቋቋመበት ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ ሕይወት ሰጪ በሆኑ ዝግጅቶች ሕዝቦቹን መባረኩን ቀጥሏል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱሶች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች እንዲሁም የጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲደርሱ እያደረጉ ነው። ይሖዋ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት ከሁሉ ስለላቀው ስጦታው ማለት ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሰዎች በማስተማር ላይ ነው። ይሖዋን ከልብ የሚወዱና የሚፈሩ ሰዎች በፊቱ ንጹሕ አቋም እንዲያገኙና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ያስቻለው ይህ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው።a በመሆኑም ዓለም በመንፈሳዊ ጠኔ እየተሠቃየ ባለበት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ሕዝቦች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ ላይ ናቸው።—ኢሳይያስ 65:13

      15. በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የይሖዋ ጥሩነት ለታማኝ የሰው ልጆች የሚፈሰው በምን መንገድ ነው?

      15 ሆኖም ይህ አሮጌ ሥርዓት ሲያከትም ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝም መፍሰሱን ያቆማል ማለት አይደለም። እንዲያውም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በይበልጥ መፍሰሱን ይቀጥላል። በዚያ ወቅት ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት የኢየሱስ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል፤ በመሆኑም ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ በይሖዋ ጥሩነት ምን ያህል እንደምንፈነድቅ አስበው!

      የይሖዋ ጥሩነት የተንጸባረቀባቸው ሌሎች መንገዶች

      16. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ጥሩነት ሌሎች ባሕርያትንም ያቀፈ እንደሆነ የሚገልጸው እንዴት ነው? ከእነዚህስ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

      16 ይሖዋ ጥሩ ነው ሲባል ለጋስ ነው ማለት ብቻ አይደለም። አምላክ ለሙሴ “እኔ ራሴ ጥሩነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሜን በፊትህ አውጃለሁ” ብሎት ነበር። በተጨማሪም ዘገባው እንደሚከተለው ይላል፦ “ይሖዋም በፊቱ እያለፈ እንዲህ ሲል አወጀ፦ ‘ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ቸር የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ።’” (ዘፀአት 33:19፤ 34:6 የግርጌ ማስታወሻ) ስለዚህ የይሖዋ ጥሩነት ሌሎች ግሩም ባሕርያትንም ያቀፈ ነው። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እስቲ እንመልከት።

      17. ይሖዋ ፍጽምና ለጎደላቸው የሰው ልጆች ደግነትና ትሕትና የሚያሳየው እንዴት ነው?

      17 “ቸር።” እዚህ ጥቅስ ላይ “ቸር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ሩኅሩኅ” ተብሎም የሚተረጎምበት ጊዜ አለ። ቃሉ የሚያመለክተው ባሕርይ፣ ይሖዋ ፍጥረታቱን ስለሚይዝበት መንገድ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ። ይሖዋ በሥልጣን ላይ እንዳሉ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ትሕትናና ፍቅራዊ ስሜት የጎደለው ወይም ጨቋኝ ሳይሆን ገርና ደግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አብርሃምን “እባክህ ካለህበት ቦታ ሆነህ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 13:14) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “እባክህ” የሚለውን ቃል ይተዉታል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚሉት በበኩረ ጽሑፉ ላይ ዓረፍተ ነገሩ ቀጥተኛ ትእዛዝ የሚያስተላልፍ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በትሕትና የቀረበ ጥያቄ እንደሆነ የሚጠቁም ማያያዣ ቃል ጥቅሱ ላይ ይገኛል። ተመሳሳይ አገላለጽ የሚገኝባቸው ሌሎች ጥቅሶችም አሉ። (ዘፍጥረት 31:12፤ ሕዝቅኤል 8:5) የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እዚህ ግባ የማይባለውን የሰውን ልጅ “እባክህ” ብሎ በትሕትና ሲያናግር እስቲ አስበው! ኃይለኝነት በነገሠበትና ለሰው አክብሮት በጠፋበት በዚህ ዓለም ውስጥ የአምላካችንን የይሖዋን መልካምነት ወይም ደግነት ማሰብ የሚያጽናና አይደለም?

      18. ይሖዋ “እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? እነዚህ ቃላት የሚያጽናኑ የሆኑትስ ለምንድን ነው?

      18 “እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ።” ዛሬ ሐቀኝነት ከምድር ላይ ጠፍቷል ሊባል ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ እንደ ሰው አይዋሽም” ይላል። (ዘኁልቁ 23:19) እንዲያውም ቲቶ 1:2 ‘አምላክ ሊዋሽ እንደማይችል’ ይገልጻል። ይሖዋ እጅግ ጥሩ አምላክ ስለሆነ በምንም ተአምር ሊዋሽ አይችልም። በመሆኑም ተስፋዎቹ ፍጹም አስተማማኝ ናቸው፤ ቃሉ ምንጊዜም መሬት ጠብ አይልም። እንዲያውም “የእውነት አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። (መዝሙር 31:5) ሐሰትን ከመናገር መቆጠብ ብቻ ሳይሆን እውነትን አትረፍርፎ ይሰጣል። እውነትን ሚስጥር አድርጎ የሚይዝ ወይም ትክክለኛውን መረጃ የሚደብቅ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከማይነጥፈው የጥበብ ምንጩ ለታማኝ አገልጋዮቹ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቅላቸዋል።b አልፎ ተርፎም በዚህ እውነት በመመራት ‘በእውነት ውስጥ መመላለስ’ እንዴት እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። (3 ዮሐንስ 3) ታዲያ የይሖዋ ጥሩነት በግለሰብ ደረጃ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

      “በይሖዋ ጥሩነት . . . ፊታቸው ይፈካል”

      19, 20. (ሀ) ሰይጣን፣ ሔዋን በይሖዋ ጥሩነት ላይ ያላት እምነት እንዲሸረሸር ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? (ለ) የይሖዋ ጥሩነት በእኛ ላይ ምን ስሜት ሊያሳድርብን ይገባል? ለምንስ?

      19 ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ሔዋንን ሲፈትናት መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ በይሖዋ ጥሩነት ላይ ያላት እምነት እንዲሸረሸር ማድረግ ነበር። ይሖዋ ለአዳም “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ” ብሎት ነበር። ይሖዋ፣ በገነት ውስጥ ከነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ የሚያማምሩ ዛፎች መካከል ማዕቀብ ያደረገው በአንዷ ላይ ብቻ ነው። ሆኖም ሰይጣን ለሔዋን ያቀረበላት የመጀመሪያ ጥያቄ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” (ዘፍጥረት 2:9, 16፤ 3:1) ሔዋን አምላክ ያስቀረባቸው አንድ መልካም ነገር እንዳለ እንዲሰማት ለማድረግ ሲል ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ በረቀቀ መንገድ አጣምሞ አቅርቦታል። የሚያሳዝነው ሰይጣን የተንኮል ዘዴው ሰምሮለታል። ሔዋን ዛሬ እንዳሉት እንደ ብዙዎቹ የሰው ልጆች፣ ሁሉን ነገር የሰጣትን አምላክ ጥሩነት መጠራጠር ጀመረች።

      20 ይህ ጥርጣሬ ምን ያህል ሥቃይና መከራ እንዳስከተለ እናውቃለን። ስለሆነም በኤርምያስ 31:12 ላይ የሚገኙትን “በይሖዋ ጥሩነት . . . ፊታቸው ይፈካል” የሚሉትን ቃላት ልብ እንበል። በእርግጥም በይሖዋ ጥሩነት መደሰት ይኖርብናል። በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለትን አምላካችንን በፍጹም ልንጠራጠረው አይገባም። ለሚወዱት ምንጊዜም በጎ ነገር የሚመኝ አምላክ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት እንችላለን።

      21, 22. (ሀ) የይሖዋ ጥሩነት ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ የትኛው ባሕርይ እንመለከታለን? ይህ ባሕርይ ከጥሩነት የሚለየውስ እንዴት ነው?

      21 በተጨማሪም ለሌሎች ስለ አምላክ ጥሩነት መናገር የምንችልበት አጋጣሚ ስናገኝ እንደሰታለን። መዝሙር 145:7 ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ሲገልጽ “የጥሩነትህን ብዛት ሲያስታውሱ በስሜት ያወራሉ” ይላል። የይሖዋን ጥሩነት ሳንቀምስ የምንውልበት አንድም ቀን የለም። በየዕለቱ ይሖዋ ያደረገልህን ጥሩ ነገር እየጠቀስክ ለምን አታመሰግነውም? ስለዚህ ባሕርይ ማሰላሰላችን፣ ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ በየዕለቱ ማመስገናችንና ስለዚህ ባሕርይው ለሌሎች መናገራችን ጥሩ የሆነውን አምላካችንን እንድንኮርጅ ይረዳናል። እንደ ይሖዋ ለሌሎች መልካም ለማድረግ ስንጥር ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን። አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጄ ሆይ፣ መጥፎ የሆነውን አትከተል፤ ይልቁንም ጥሩ የሆነውን ተከተል። መልካም የሚያደርግ የአምላክ ወገን ነው” ሲል ጽፏል።—3 ዮሐንስ 11

      22 የይሖዋ ጥሩነት ከሌሎች ባሕርያትም ጋር ዝምድና አለው። ለምሳሌ “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፀአት 34:6) ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ጥሩነቱን የሚያሳይ ቢሆንም ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ግን ታዛዥ ለሆኑ አገልጋዮቹ ብቻ መሆኑ ይህን ባሕርይ ልዩ ያደርገዋል። ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።

      a ከቤዛው ዝግጅት የበለጠ የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳይ ነገር ሊኖር አይችልም። ይሖዋ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት መካከል ለእኛ ሲል እንዲሞት የመረጠው የሚወደውን አንድያ ልጁን ነው።

      b መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ብዙ ጊዜ ከብርሃን ጋር ያዛምደዋል። መዝሙራዊው “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 43:3) ይሖዋ ከእሱ ለመማር ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ መንፈሳዊ ብርሃኑን ቦግ አድርጎ ያበራላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:6፤ 1 ዮሐንስ 1:5

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • 1 ነገሥት 8:54-61, 66 ሰለሞን ለይሖዋ ጥሩነት ያለውን አድናቆት የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ እስራኤላውያን ምን እንዲሰማቸው አድርጓል?

      • መዝሙር 119:68 ጸሎታችን የይሖዋን ጥሩነት መኮረጅ እንደምንፈልግ ሊያንጸባርቅ የሚችለው እንዴት ነው?

      • ሉቃስ 6:32-38 የይሖዋን የልግስና መንፈስ እንድንኮርጅ ሊያነሳሳን የሚችለው ምንድን ነው?

      • ሮም 12:2, 9, 17-21 በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጥሩነትን ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

  • “አንተ ብቻ ታማኝ ነህ”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ምሽት ላይ ደምቃ የምትታየው ጨረቃ።

      ምዕራፍ 28

      “አንተ ብቻ ታማኝ ነህ”

      1, 2. ክህደት ለንጉሥ ዳዊት እንግዳ ነገር አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?

      ክህደት ለንጉሥ ዳዊት እንግዳ ነገር አልነበረም። በነውጥ የተሞላው የግዛት ዘመኑ በአንድ ወቅት የገዛ ብሔሩ አባላት በጠነሰሱት ሴራ ቀውስ ገጥሞት ነበር። በተጨማሪም ዳዊት የቅርቤ ናቸው የሚላቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ከድተውታል። የዳዊት የመጀመሪያ ሚስት የሆነችውን ሜልኮልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጀመሪያ ላይ “ዳዊትን ትወደው ነበር”፤ የንግሥና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትረዳውና ትደግፈው እንደነበረም ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ “በልቧ ናቀችው”፤ እንዲያውም ዳዊትን “እንደ አንድ ተራ ሰው” በመቁጠር ንቀቷን አሳይታለች።—1 ሳሙኤል 18:20፤ 2 ሳሙኤል 6:16, 20

      2 የዳዊት የቅርብ አማካሪ የነበረው አኪጦፌልም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። ምክሩ መሬት ጠብ የማይል ከመሆኑ የተነሳ በቀጥታ ከይሖዋ እንደመጣ ቃል ተደርጎ ይታይ ነበር። (2 ሳሙኤል 16:23) ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ እምነት የተጣለበት የዳዊት ሚስጥረኛ ከጊዜ በኋላ በዳዊት ላይ ካመፁ ሰዎች ጋር በማበር ከሃዲ ሆነ። ይህን ሴራ የጠነሰሰውስ ማን ነበር? የራሱ የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ነው! ይህ ሴረኛ አሳቢ መስሎ በመቅረብና “የእስራኤልን ሰዎች ልብ [በመስረቅ]” የዳዊትን ሥልጣን መቀናቀን ጀመረ። አቢሴሎም ያቀነባበረው ዓመፅ እያየለና እየተጠናከረ በመምጣቱ ንጉሥ ዳዊት ነፍሱን ለማዳን መሸሽ ግድ ሆኖበታል።—2 ሳሙኤል 15:1-6, 12-17

      3. ዳዊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

      3 ከዳዊት ጎን በታማኝነት የቆመ ማንም አልነበረም ማለት ነው? ዳዊት በመከራው ዘመን ሁሉ ከጎኑ የማይለይ ታማኝ ወዳጅ እንዳለው ያውቅ ነበር። ይህ ታማኝ ወዳጁ ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ዳዊት ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ” ብሏል። (2 ሳሙኤል 22:26) ታማኝነት ምንድን ነው? ይሖዋ ይህን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ አርዓያ የሆነውስ እንዴት ነው?

      ታማኝነት ምንድን ነው?

      4, 5. (ሀ) “ታማኝነት” ምንድን ነው? (ለ) ታማኝነት እንዲሁ እምነት የሚጣልበት ወይም አስተማማኝ ከመሆን የሚለየው እንዴት ነው?

      4 “ታማኝነት” የሚለውን ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ካለው አገባብ አንጻር ስንመለከተው አንድን አካል በፍቅር የሙጥኝ በማለትና ከዚህ አካል ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ ዳር እስኪደርስ ድረስ ከእሱ ጎን በመቆም የሚገለጽ ደግነት ነው። ታማኝ ሰው ይህን የሚያደርገው እንዲሁ ግዴታን ለመወጣት ያህል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ነው።a በመሆኑም ታማኝ መሆን እምነት የሚጣልበት ወይም አስተማማኝ ሆኖ ከመገኘት የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው ጨረቃ ሁልጊዜ በምሽት የምትወጣ በመሆኗ “በሰማያት ታማኝ ምሥክር” ሆና እንደምትኖር ተናግሯል። (መዝሙር 89:37) እዚህ ላይ ጨረቃ ታማኝ ተብላ የተጠራችው አስተማማኝ በመሆኗ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ማሰብ የሚችሉ አካላት ከሚያሳዩት ታማኝነት የተለየ ነው። ለምን? ምክንያቱም ታማኝነት የፍቅር መገለጫ ነው፤ ግዑዝ ፍጥረታት ደግሞ ፍቅር ማሳየት አይችሉም።

      ጨረቃ ታማኝ ምሥክር ተብላ ተጠርታለች፤ የይሖዋን ዓይነት ታማኝነት ሊያንጸባርቁ የሚችሉት ግን የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ብቻ ናቸው

      5 ታማኝነት የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባለው አገባብ መሠረት ወዳጃዊ መንፈስ የሚንጸባረቅበት ባሕርይ ነው። አንድ ሰው ለሌላው ታማኝ የሚሆነው በሁለቱ መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ታማኝነት ጊዜያዊ አይደለም። በነፋስ እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ተለዋዋጭ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታማኝነት ወይም ታማኝ ፍቅር በጣም አስቸጋሪ የሆኑ መሰናክሎችን ሁሉ ማለፍ የሚያስችል ጥንካሬና ጽናት ያለው ባሕርይ ነው።

      6. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ታማኝነት እየጠፋ ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስስ ይህን የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ታማኝነት ምን እንደሚጠይቅ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? ለምንስ?

      6 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለው ታማኝነት እየጠፋ ነው ሊባል ይችላል። “እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች” በዝተዋል። የትዳር ጓደኛቸውን ጥለው የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። (ምሳሌ 18:24፤ ሚልክያስ 2:14-16) ታማኝነት ማጉደል በጣም እየተለመደ በመምጣቱ እኛም እንደ ነቢዩ ሚክያስ “ታማኝ ሰው ከምድሪቱ ጠፍቷል” ብለን ለመናገር እንገፋፋለን። (ሚክያስ 7:2) ምንም እንኳ የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ ታማኝነታቸውን የሚያጎድሉ ቢሆንም ይሖዋ ይህን ተወዳጅ ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ የላቀ ምሳሌ ነው። እንዲያውም ታማኝነት ምን እንደሚጠይቅ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይሖዋ የፍቅሩ ታላቅ መግለጫ የሆነውን ይህን ባሕርይ እንዴት እንዳንጸባረቀ መመርመር ነው።

      አቻ የማይገኝለት የይሖዋ ታማኝነት

      7, 8. ‘ይሖዋ ብቻ ታማኝ ነው’ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

      7 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “አንተ ብቻ ታማኝ ነህ” ይላል። (ራእይ 15:4) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አስደናቂ የሆነ የታማኝነት አቋም ያሳዩ ሰዎችና መላእክት አሉ አይደለም እንዴ? (ኢዮብ 1:1፤ ራእይ 4:8) ኢየሱስ ክርስቶስስ ቢሆን ግንባር ቀደሙ የይሖዋ “ታማኝ አገልጋይ” አይደለም? (መዝሙር 16:10) ታዲያ ‘ይሖዋ ብቻ ታማኝ ነው’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

      8 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ታማኝነት የፍቅር አንዱ ገጽታ እንደሆነ አስታውስ። “አምላክ ፍቅር ነው”፤ በሌላ አነጋገር የዚህ ባሕርይ ዋነኛ መገለጫ እሱ ነው። ታዲያ ከይሖዋ በተሻለ ሁኔታ ታማኝ ሊሆን የሚችል ማን ይኖራል? (1 ዮሐንስ 4:8) መላእክትም ሆኑ ሰዎች የአምላክን ባሕርያት ሊያንጸባርቁ ቢችሉም ከሁሉ በላቀ ደረጃ ታማኝ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። “ከዘመናት በፊት የነበረ” እንደመሆኑ መጠን ከየትኛውም ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ፍጡር ይበልጥ ለረጅም ዘመን ታማኝነት ሲያሳይ ኖሯል። (ዳንኤል 7:9) በመሆኑም ይሖዋ የታማኝነት ዋነኛ ተምሳሌት ነው። ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቀው ከማንኛውም ፍጡር በላቀ ደረጃ ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።

      9. ይሖዋ ‘በሥራው ሁሉ ታማኝ’ የሆነው እንዴት ነው?

      9 ይሖዋ ‘በሥራው ሁሉ ታማኝ ነው።’ (መዝሙር 145:17) እንዴት? መዝሙር 136 ለዚህ መልስ ይሰጠናል። መዝሙሩ እስራኤላውያን በተአምራዊ መንገድ ቀይ ባሕርን የተሻገሩበትን ሁኔታ ጨምሮ ይሖዋ የወሰዳቸውን የተለያዩ የማዳን እርምጃዎች ይጠቅሳል። በዚህ መዝሙር ላይ የሚገኘው እያንዳንዱ ቁጥር “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በሚል ዓረፍተ ነገር እንደሚቋጭ ልብ በል። ይህ መዝሙር በገጽ 289 ላይ በሚገኘው “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” በሚለው ሣጥን ውስጥ ተካትቷል። በዚህ መዝሙር ላይ የተገለጹትን ይሖዋ ለሕዝቡ ታማኝ ፍቅር ያሳየባቸውን የተለያዩ መንገዶች ስትመለከት መደነቅህ አይቀርም። አዎን፣ ይሖዋ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮቹ የእሱን እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና በመስማትና ራሱ በወሰነው ጊዜ እርምጃ በመውሰድ ታማኝነቱን ያሳያቸዋል። (መዝሙር 34:6) አገልጋዮቹ ለእሱ ታማኝ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ይሖዋ ለእነሱ ያለው ታማኝ ፍቅር ፈጽሞ አይቀንስም።

      10. ይሖዋ ከመሥፈርቶቹ ጋር በተያያዘ ታማኝ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

      10 በተጨማሪም ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ምንጊዜም በመጠበቅ ለአገልጋዮቹ ታማኝነት ያሳያል። ይሖዋ በስሜትና በግብታዊነት እንደሚመሩ ወላዋይ ሰዎች፣ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ያለውን አመለካከት በየጊዜው አይለዋውጥም። ባለፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች፣ ስለ ጣዖት አምልኮና ስለ ነፍስ ግድያ ያለው አመለካከት ፈጽሞ አልተለወጠም። “እስከ እርጅናችሁ ዘመን ድረስ እኔ ያው ነኝ” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:4) በመሆኑም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ግልጽ የሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ጥቅም እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 48:17-19

      11. ይሖዋ የገባውን ቃል በመፈጸም ረገድ ታማኝ እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።

      11 ይሖዋ የገባውን ቃል በመጠበቅም ታማኝ መሆኑን ያሳያል። አስቀድሞ የሚናገረው ነገር ሁሉ ፍጻሜውን ማግኘቱ አይቀርም። ስለሆነም ይሖዋ “ከአፌ [የሚወጣው] ቃሌ . . . ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ያደርጋል፣ የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂ ያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም” ሲል ገልጿል። (ኢሳይያስ 55:11) ይሖዋ ቃሉን በመጠበቅ ለሕዝቡ ያለውን ታማኝነት ያሳያል። የማይፈጽምላቸውን ነገር በጉጉት እንዲጠብቁ አያደርግም። ይሖዋ ቃሉን በመጠበቅ ረገድ ያተረፈው ስም ምንም እንከን የማይወጣለት በመሆኑ አገልጋዩ ኢያሱ “ይሖዋ ለእስራኤል ቤት ከገባው መልካም ቃል ሁሉ ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም፤ ሁሉም ተፈጽሟል” ብሎ መናገር ችሏል። (ኢያሱ 21:45) እንግዲያው ይሖዋ የገባውን ቃል ሳይፈጽም ቀርቶ ለሐዘን ይዳርገናል ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት የለም።—ኢሳይያስ 49:23፤ ሮም 5:5

      12, 13. የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

      12 ቀደም ሲል እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ታማኝ ፍቅር “ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል። (መዝሙር 136:1) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ኃጢአትን ይቅር የሚለው ለዘለቄታው ነው። በምዕራፍ 26 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ አንድን ሰው አንዴ ይቅር ካለው በኋላ ጥፋቱን መልሶ አያነሳበትም። ‘ሁላችንም ኃጢአት ሠርተናል እንዲሁ የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ ተስኖናል’፤ በመሆኑም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል።—ሮም 3:23

      13 ይሁን እንጂ የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ የሚኖርበት ሌላም አቅጣጫ አለ። የአምላክ ቃል፣ ጻድቅ ሰው “በጅረቶች ዳር እንደተተከለ፣ ፍሬውን በወቅቱ እንደሚሰጥ፣ ቅጠሉም እንደማይጠወልግ ዛፍ ይሆናል። የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 1:3) ቅጠሉ የማይደርቅ የለመለመ ዛፍ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር! እኛም የአምላክን ቃል በማንበብ ከልብ የምንደሰት ከሆነ ረጅም፣ ሰላማዊና ፍሬያማ ሕይወት ይኖረናል። ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያፈስስላቸው በረከቶች ዘላለማዊ ናቸው። በእርግጥም ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ለዘላለም የማጣጣም አጋጣሚ ያገኛሉ።—ራእይ 21:3, 4

      ይሖዋ ‘ታማኝ አገልጋዮቹን አይተዋቸውም’

      14. ይሖዋ አገልጋዮቹ ስለሚያሳዩት ታማኝነት ምን ይሰማዋል?

      14 ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታማኝነቱን አሳይቷል። ፈጽሞ የማይለዋወጥ አምላክ በመሆኑ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያሳየው ታማኝነት መቼም ቢሆን አይቀንስም። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤ ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም። ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም።” (መዝሙር 37:25, 28) ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ልናመልከው እንደሚገባ የታወቀ ነው። (ራእይ 4:11) ይሁንና ይሖዋ ታማኝ ስለሆነ በታማኝነት የምናከናውነውን መልካም ተግባር ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ሚልክያስ 3:16, 17

      15. ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያደረገው ነገር ታማኝነቱን እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚያሳይ ግለጽ።

      15 ይሖዋ ሕዝቡ ችግር ላይ ሲወድቁ በተደጋጋሚ ጊዜያት በታማኝ ፍቅሩ ተገፋፍቶ አስፈላጊውን እርዳታ አድርጎላቸዋል። መዝሙራዊው “እሱ የታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት ይጠብቃል፤ ከክፉዎች እጅ ይታደጋቸዋል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 97:10) ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር ተመልከት። እስራኤላውያን፣ በቀይ ባሕር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባዳናቸው ጊዜ “የታደግካቸውን ሕዝቦች በታማኝ ፍቅርህ መራሃቸው” በማለት ይሖዋን በመዝሙር አወድሰዋል። (ዘፀአት 15:13) በእርግጥም ይሖዋ በቀይ ባሕር ያከናወነው ታላቅ የማዳን ሥራ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ይሖዋ እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ቁጥራችሁ ስለበዛ አይደለም፤ ቁጥራችሁማ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ አነስተኛ ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እናንተን ከባርነት ቤት ይኸውም ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ ይታደጋችሁ ዘንድ ይሖዋ በብርቱ እጅ ያወጣችሁ ስለወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለጠበቀ ነው።”—ዘዳግም 7:7, 8

      16, 17. (ሀ) እስራኤላውያን አድናቆት ጎድሏቸው እንደነበረ ያሳዩት እንዴት ነው? ሆኖም ይሖዋ ርኅራኄ ያሳያቸው እንዴት ነው? (ለ) አብዛኞቹ እስራኤላውያን ‘ፈውስ የማይገኝላቸው’ ደረጃ ላይ የደረሱት እንዴት ነው? ይህስ ለእኛ ማስጠንቀቂያ የሚሆነን እንዴት ነው?

      16 እርግጥ ነው፣ እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ይሖዋ ላሳያቸው ታማኝ ፍቅር አድናቆት ሳያሳዩ ቀርተዋል። ነፃ ካወጣቸው በኋላ “በልዑሉ አምላክ ላይ በማመፅ በእሱ ላይ ኃጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ።” (መዝሙር 78:17) በቀጣዮቹ መቶ ዘመናትም ይሖዋን በመተው፣ የሐሰት አማልክትን በማምለክና የሚያረክሱ አረማዊ ድርጊቶችን በመፈጸም በተደጋጋሚ ጊዜያት ዓምፀውበታል። ያም ሆኖ ይሖዋ ቃል ኪዳኑን አላፈረሰም። ከዚህ ይልቅ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል “ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፣ ተመለሽ . . . እኔ ታማኝ ስለሆንኩ እናንተን በቁጣ አልመለከትም” ሲል ሕዝቡን ተማጽኗል። (ኤርምያስ 3:12) ይሁን እንጂ ምዕራፍ 25 ላይ እንደተገለጸው አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለመስተካከል ያደረጉት ጥረት የለም። እንዲያውም “በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣ ቃሉን ይንቁና በነቢያቱ ላይ ያፌዙ ነበር።” ይህ ምን ውጤት አስከተለ? በመጨረሻ ‘ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ።’—2 ዜና መዋዕል 36:15, 16

      17 ከዚህ ምን እንማራለን? ይሖዋ ታማኝ ነው ሲባል ሰዎች የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት እንዲሁ ችላ ይላል ወይም በቀላሉ ይታለላል ማለት አይደለም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ ነው። ደግሞም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል በቂ ምክንያት ሲኖር ምሕረት ማድረግ ያስደስተዋል። ይሁን እንጂ አንድ ኃጢአተኛ ለመታረም ፈቃደኛ በማይሆንበት ጊዜስ ምን ያደርጋል? በዚህ ጊዜ ይሖዋ የራሱን የጽድቅ መሥፈርቶች በመጠበቅ በግለሰቡ ላይ የቅጣት እርምጃ ይወስድበታል። ለሙሴ እንደገለጸለት “ጥፋተኛውን . . . በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ” አምላክ ነው።—ዘፀአት 34:6, 7

      18, 19. (ሀ) ይሖዋ በክፉዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ ራሱ ታማኝነቱን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በደረሰባቸው ከባድ ስደት ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡ አገልጋዮቹ ታማኝነቱን የሚያሳየው በምን መንገድ ነው?

      18 አምላክ በክፉዎች ላይ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ራሱ ታማኝነቱን የሚያሳይ ነው። እንዴት? በራእይ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው፣ ይሖዋ ለሰባቱ መላእክት የሰጠው ትእዛዝ ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው። ይሖዋ ሰባቱን መላእክት “ሂዱና የአምላክን ቁጣ የያዙትን ሰባቱን ሳህኖች በምድር ላይ አፍስሱ” ሲል አዟቸዋል። ሦስተኛው መልአክ “በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ወንዞችና ወደ ውኃ ምንጮች” ባፈሰሰ ጊዜ ውኃው ወደ ደም ተለወጠ። ከዚያም መልአኩ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “ያለህና የነበርክ ታማኝ አምላካችን፣ እነዚህን የፍርድ ውሳኔዎች ስላስተላለፍክ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ምክንያቱም የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም አፍስሰዋል፤ አንተም ደም እንዲጠጡ ሰጥተሃቸዋል፤ ደግሞም ይገባቸዋል።”—ራእይ 16:1-6

      19 መልአኩ የፍርድ መልእክቱን በሚያስተላልፍበት ጊዜ ይሖዋን “ታማኝ አምላካችን” ብሎ እንደጠራው ልብ በል። ይህን ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ክፉዎችን ማጥፋቱ ለአገልጋዮቹ ታማኝ መሆኑን ስለሚያሳይ ነው፤ ከእነዚህ አገልጋዮቹ መካከል ብዙዎች በደረሰባቸው ከባድ ስደት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን አገልጋዮቹን መቼም አይረሳቸውም። በሞት የተለዩትን እነዚህን ታማኝ አገልጋዮቹን ዳግመኛ ሊያያቸው ይናፍቃል፤ በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከሞት በማስነሳት ወሮታ የመክፈል ዓላማ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። (ኢዮብ 14:14, 15) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ስለሞቱ ብቻ አይረሳቸውም። እንዲያውም “በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው።” (ሉቃስ 20:37, 38) ይሖዋ በአእምሮው ማኅደር ያኖራቸውን ሰዎች ዳግም ሕያው ለማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑ ታማኝነቱን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

      ይሖዋ ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው በመስጠት ታማኝ መሆናቸውን ያስመሠከሩትን አገልጋዮቹን በማስታወስና ከሞት በማስነሳት ታማኝ መሆኑን ያሳያል

      ቤርናርት ሉዪምስ (በስተ ግራ) እና ዎልፍጋንግ ኩሰሮ (መሃል) በናዚዎች ተገድለዋል

      ሞሰስ ንያሙሱዋ (በስተ ቀኝ) በአንድ የፖለቲካ አንጃ በጦር ተገድሏል

      የይሖዋ ታማኝ ፍቅር መዳን ያስገኛል

      20. “የምሕረት ዕቃዎች” የተባሉት እነማን ናቸው? ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ታማኝነት ያሳየውስ እንዴት ነው?

      20 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ለታማኝ ሰዎች በጣም የሚያስደንቅ ታማኝነት አሳይቷል። እንዲያውም ይሖዋ “ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች” በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት “በብዙ ትዕግሥት [ችሏቸዋል]።” ለምን? “ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች ላይ ለመግለጥ” ነው። (ሮም 9:22, 23) እነዚህ “የምሕረት ዕቃዎች” ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ገዢዎች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ናቸው። (ማቴዎስ 19:28) ይሖዋ እነዚህ የምሕረት ዕቃዎች መዳን የሚችሉበትን አጋጣሚ በመክፈት ለአብርሃም ያለውን ታማኝነት አሳይቷል፤ ምክንያቱም ይሖዋ “ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ” ሲል ለአብርሃም ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበር።—ዘፍጥረት 22:18

      የተለያየ ዕድሜና ዘር ያላቸው ደስተኛ ወንድሞችና እህቶች።

      ይሖዋ ታማኝ በመሆኑ ታማኝ አገልጋዮቹ ሁሉ አስተማማኝ ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል

      21. (ሀ) ይሖዋ “ታላቁን መከራ” የማለፍ ተስፋ ላላቸው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ታማኝነቱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ታማኝነት ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

      21 ይሖዋ “ታላቁን መከራ” አልፈው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ‘እጅግ ብዙ ሕዝብም’ ተመሳሳይ የሆነ ታማኝነት አሳይቷል። (ራእይ 7:9, 10, 14) አገልጋዮቹ ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ በታማኝ ፍቅሩ ተነሳስቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? የይሖዋ ታማኝነት ከሁሉ በላቀ ደረጃ የተንጸባረቀበትን የቤዛውን ዝግጅት በመጠቀም ነው። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 5:8) የይሖዋ ታማኝነት ጽድቅን የተራቡ ሰዎች ወደ እሱ እንዲሳቡ እያደረገ ነው። (ኤርምያስ 31:3) ይሖዋ እስካሁን ያሳየውም ሆነ ወደፊት የሚያሳየው ታማኝነት ይበልጥ ወደ እሱ እንድትቀርብ አይገፋፋህም? የዘወትር ምኞታችን ይበልጥ ወደ አምላክ መቅረብ እንደመሆኑ መጠን፣ እሱን በታማኝነት ለማገልገል ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ በመጽናት ላሳየን ፍቅር አዎንታዊ ምላሽ እንስጥ።

      a በ2 ሳሙኤል 22:26 ላይ “ታማኝ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በሌሎች ቦታዎች ላይ “ታማኝ ፍቅር” ተብሎ ተተርጉሟል።

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • 1 ሳሙኤል 24:1-22 ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ጋር በነበረው ግንኙነት ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ዓይነት የታማኝነት ባሕርይ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?

      • አስቴር 3:7-9፤ 4:6–5:1 አስቴር ሕይወቷን ጭምር አደጋ ላይ ጥላ ከሕዝቧ ጎን በመቆም አምላካዊ ታማኝነት ያሳየችው እንዴት ነው?

      • መዝሙር 136:1-26 ይህ መዝሙር ስለ ይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምን ያስተምረናል?

      • አብድዩ 1-4, 10-16 ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ታማኝነት ከዳተኛ የሆኑትን ኤዶማውያን እንዲቀጣ የገፋፋው እንዴት ነው?

  • ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • ኢየሱስ ለአንድ ሰው ርኅራኄ ሲያሳይ።

      ምዕራፍ 29

      ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’

      1-3. (ሀ) ኢየሱስ አባቱን እንዲኮርጅ ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ፍቅሩን ያንጸባረቀባቸውን የትኞቹን ሦስት መንገዶች እንመረምራለን?

      አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን ለመምሰል ሲጥር አይተህ ታውቃለህ? የአባቱን አረማመድ፣ አነጋገር ወይም ድርጊት ይኮርጅ ይሆናል። እያደገ ሲሄድ ደግሞ አባቱ የሚመራባቸውን ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ እሴቶች መከተል ሊጀምር ይችላል። አዎን፣ አንድ ልጅ አፍቃሪ ለሆነው አባቱ ያለው አድናቆትና ፍቅር እሱን ለመምሰል እንዲጣጣር ይገፋፋዋል።

      2 በኢየሱስና በአባቱ መካከል ስላለው ግንኙነትስ ምን ማለት ይቻላል? በአንድ ወቅት ኢየሱስ ‘አብን እወደዋለሁ’ ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:31) ከሌላ ከማንኛውም ፍጡር ይበልጥ ረጅም ዘመን ከይሖዋ ጋር የኖረው ልጁ ኢየሱስ ነው፤ በመሆኑም ከእሱ ይበልጥ ይሖዋን የሚወድ ሊኖር አይችልም። ይህ ልጅ አባቱን እንዲኮርጅ ያነሳሳው ይህ ጥልቅ ፍቅር ነው።—ዮሐንስ 14:9

      3 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ ኢየሱስ የይሖዋን ኃይል፣ ፍትሕና ጥበብ ፍጹም በሆነ መልኩ እንደኮረጀ ተመልክተናል። ሆኖም የአባቱን ፍቅር ያንጸባረቀውስ እንዴት ነው? ኢየሱስ ፍቅሩን ያንጸባረቀባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት፤ እነሱም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ፣ ርኅራኄ ማሳየትና ይቅር ባይነት ናቸው።

      ከዚህ “የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም”

      4. ኢየሱስ ከማንኛውም ሰው በላቀ መንገድ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

      4 ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ሲባል ከራስ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎትና ጥቅም ማስቀደም ማለት ነው። ኢየሱስ ይህን ዓይነቱን ፍቅር ያንጸባረቀው እንዴት ነው? “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ሲል እሱ ራሱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:13) ኢየሱስ ለእኛ ሲል ፍጹም ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሰጥቷል። አንድ ሰው ፍቅሩን ሊገልጽበት የሚችል ከዚህ የላቀ መንገድ ሊኖር አይችልም። ሆኖም ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅሩን ያሳየው በዚህ ብቻ አይደለም።

      5. የአምላክ አንድያ ልጅ ከሰማይ ወደ ምድር መምጣቱ ትልቅ መሥዋዕትነት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

      5 የአምላክ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ የተከበረ ቦታና ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ከይሖዋም ሆነ እጅግ ብዙ ከሆኑት መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። ይህ የተወደደ የአምላክ ልጅ በዚህ ሁኔታ በሰማይ ይኖር የነበረ ቢሆንም “ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ፤ ደግሞም ሰው ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:7) “በክፉው ቁጥጥር ሥር” በሆነው ዓለም ውስጥ ከኃጢአተኛ ሰዎች ጋር ለመኖር በፈቃደኝነት ወደ ምድር መጣ። (1 ዮሐንስ 5:19) በእርግጥም የአምላክ ልጅ በፍቅር ተገፋፍቶ ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍሏል!

      6, 7. (ሀ) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) በዮሐንስ 19:25-27 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

      6 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ታላቅ ፍቅር እንዳለው በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። ኢየሱስ ራሱን አይቆጥብም ነበር። በአገልግሎቱ በጣም ከመጠመዱ የተነሳ የሰው ልጆች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንኳ ሳይቀር መሥዋዕት አድርጓል። “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 8:20) ጎበዝ አናጺ እንደመሆኑ መጠን ለራሱ ልዩ የሆነ ቤት መሥራት ወይም ውብ የሆኑ የቤት ዕቃዎችን እየሠራ በመሸጥ ገንዘብ ማጠራቀም ይችል ነበር። ሆኖም ችሎታውን ቁሳዊ ሀብት ለመሰብሰብ አልተጠቀመበትም።

      7 ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ጥልቅ ፍቅር እንደነበረው የሚያሳይ ልብ የሚነካ ዘገባ በዮሐንስ 19:25-27 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ብዙ ሐሳብ በአእምሮው ይጉላላ እንደነበር መገመት አያዳግትም። በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እየተሠቃየ ሳለ ስለ ደቀ መዛሙርቱ፣ ስለ ስብከቱ ሥራ በተለይ ደግሞ የእሱ ታማኝ መሆን አለመሆን በአባቱ ስም ላይ ስለሚያስከትለው ነገር ያወጣ ያወርድ ነበር። የሰው ዘር የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ በእሱ ጫንቃ ላይ ወድቆ ነበር! ይህ ሁሉ ጭንቀት እያለበትም እንኳ ለእናቱ ለማርያም በጣም ያስብ እንደነበረ አሳይቷል፤ ማርያም በወቅቱ መበለት ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ፣ እንደገዛ እናቱ አድርጎ እንዲደግፋትና እንዲንከባከባት ለሐዋርያው ዮሐንስ አደራ ሰጠው፤ ዮሐንስም አደራውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ይዟት ሄደ። ኢየሱስ በዚህ መንገድ እናቱ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ እንክብካቤ እንዲደረግላት ሁኔታዎችን አመቻቸ። በእርግጥም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ታላቅ ፍቅር አሳይቷል!

      “በጣም አዘነላቸው”

      8. መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ርኅራኄ ለመግለጽ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል ትርጉም ምንድን ነው?

      8 እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ሩኅሩኅ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚገልጹት ኢየሱስ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች በጣም ስለሚያዝን እነሱን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ርኅራኄ ለመግለጽ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል “በጣም አዘነላቸው” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ቃል . . . አንድ ሰው አንጀቱ በሐዘን እንዲንሰፈሰፍ የሚያደርገውን ጥልቅ ስሜት ያመለክታል። የርኅራኄን ስሜት ለመግለጽ ከሚያገለግሉት የግሪክኛ ቃላት ሁሉ የበለጠ ኃይል አለው።” ኢየሱስ ከአንጀቱ ራርቶ እርምጃ የወሰደባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እስቲ ተመልከት።

      9, 10. (ሀ) ኢየሱስና ሐዋርያቱ ገለል ወዳለ ስፍራ መሄድ የፈለጉት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ፣ ሕዝቡ በሄደበት ሁሉ ሲከተሉት ምን ተሰማው? ለምንስ?

      9 ርኅራኄ የሰዎችን መንፈሳዊ ረሃብ እንዲያስታግሥ አነሳስቶታል። በማርቆስ 6:30-34 ላይ የሚገኘው ዘገባ ኢየሱስ ለሰዎች እንዲያዝንና እንዲረዳቸው ያደረገውን ዋነኛ ምክንያት ይገልጻል። እስቲ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ሐዋርያቱ ያደረጉትን መጠነ ሰፊ የስብከት ዘመቻ መጨረሳቸው ስለነበር በጣም ተደስተዋል። ወደ ኢየሱስ ተመልሰው ያጋጠማቸውን ሁሉ ለኢየሱስ በስሜት እየነገሩት ነው። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ገና እህል እንኳ በአፋቸው ሳይዞር ብዙ ሕዝብ በአንዴ አጠገባቸው ስብስብ አለ። ኢየሱስ ሁሌም አስተዋይ ስለሆነ ሐዋርያቱ እንደደከማቸው ተገነዘበ። ስለዚህ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው። ከዚያም ጀልባ ተሳፍረው በገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ጫፍ ወደሚገኝ ጸጥ ያለ ስፍራ ሄዱ። ሆኖም ሕዝቡ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወዴት እንደሄዱ ስላወቁ ወዲያውኑ ወደ ሰሜናዊው የባሕር ዳርቻ ጫፍ በመገስገስ ከጀልባዋ ቀድመው ደረሱ!

      10 ኢየሱስ ሕዝቡ መፈናፈኛ እንዳሳጣው ተሰምቶት ተበሳጨ? በፍጹም! ተሰብስቦ እየጠበቀው ያለውን በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ሲመለከት ከልቡ አዘነ። ማርቆስ እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል፦ “እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው። ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።” ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ እጅግ ተርበው እንደነበር ተገንዝቧል። የሚመራቸው ወይም የሚጠብቃቸው እረኛ አጥተው እንደሚቅበዘበዙ በጎች ነበሩ። ኢየሱስ አፍቃሪ እረኞች መሆን ይጠበቅባቸው የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ለሕዝቡ ግድ እንደሌላቸውና ችላ ብለዋቸው እንደነበር አስተውሏል። (ዮሐንስ 7:47-49) የሕዝቡ ሁኔታ አንጀቱን ስለበላው “ስለ አምላክ መንግሥት” ያስተምራቸው ጀመር። (ሉቃስ 9:11) ኢየሱስ ለሕዝቡ ያዘነው ላስተማራቸው ነገር የሰጡትን ምላሽ ካየ በኋላ አለመሆኑን ልብ በል። በሌላ አነጋገር የኢየሱስ ርኅራኄ የሕዝቡን ምላሽ በማየት የመጣ ውጤት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከመጀመሪያውም ሕዝቡን እንዲያስተምራቸው የገፋፋው ምክንያት ርኅራኄ ነው።

      ኢየሱስ የሥጋ ደዌ የያዘውን አንድ ሰው እጁን ዘርግቶ በመዳሰስ ርኅራኄ ሲያሳየው። በአካባቢው ያሉ ሰዎች ሰውየውን ተጸይፈውታል።

      “እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው”

      11, 12. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለሥጋ ደዌ በሽተኞች የነበረው አመለካከት ምን ይመስል ነበር? ሆኖም ኢየሱስ “የሥጋ ደዌ የወረሰው” አንድ ሰው ወደ እሱ ሲቀርብ ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽተኛውን መዳሰሱ በሰውየው ላይ ምን ስሜት አሳድሮ ሊሆን ይችላል? የአንድ ሐኪም ገጠመኝ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውስ እንዴት ነው?

      11 ርኅራኄ ሥቃያቸውን እንዲያስታግሥ አነሳስቶታል። የተለያየ ሕመም የነበራቸው ሰዎች ኢየሱስ ሩኅሩኅ እንደሆነ ስላወቁ ወደ እሱ ይቀርቡ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሳለ የተፈጸመው ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። “መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ የወረሰው ሰው” ወደ ኢየሱስ መጣ። (ሉቃስ 5:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሥጋ ደዌ በሽታ የያዛቸው ሰዎች በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያዛምቱ ሲባል ተገልለው እንዲቆዩ ይደረግ ነበር። (ዘኁልቁ 5:1-4) ከጊዜ በኋላ ግን ረቢዎች የሥጋ ደዌ በሽታን በተመለከተ ርኅራኄ የጎደለው አመለካከት እንዲስፋፋ ያደረጉ ከመሆኑም በላይ የራሳቸውን ጨቋኝ የሆኑ ደንቦች አውጥተው ነበር።a ሆኖም ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽታ ያለበትን ይህን ሰው እንዴት እንደያዘው ልብ በል፤ ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰውም ወደ እሱ ቀርቦ ‘ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ’ በማለት ተንበርክኮ ተማጸነው። በዚህ ጊዜ በጣም አዘነለትና እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፤ ከዚያም ‘እፈልጋለሁ! ንጻ’ አለው። ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።” (ማርቆስ 1:40-42) ኢየሱስ ይህ ሰው ከሕዝቡ ጋር መቀላቀሉ ተገቢ እንዳልነበር ያውቃል። ሆኖም በጣም ስላሳዘነው ወደ እሱ እንዳይቀርብ ከመከልከል ይልቅ ጭራሽ የማይታሰብ ነገር አደረገ። ሰውየውን በእጁ ዳሰሰው!

      12 የሥጋ ደዌ በሽተኛው ኢየሱስ ሲዳስሰው ምን እንደተሰማው ልትገምት ትችላለህ? ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ገጠመኝ ተመልከት። ዶክተር ፖል ብራንድ የተባሉ የሥጋ ደዌ ስፔሻሊስት በሕንድ አገር ስላከሙት አንድ የሥጋ ደዌ በሽተኛ የሚነግሩን ነገር አለ። ምርመራ እያደረጉለት ባሉበት ወቅት እጃቸውን ትከሻው ላይ ጣል አድርገው ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚደረግለት በአስተርጓሚ አማካኝነት ነገሩት። በሽተኛው ድንገት ማልቀስ ጀመረ። ዶክተሩ “የሚያስከፋ ነገር ተናገርኩ እንዴ?” ሲሉ ጠየቁ። አስተርጓሚዋ ታካሚውን ምን እንዳስለቀሰው በቋንቋው ከጠየቀችው በኋላ እንዲህ ስትል ለዶክተሩ መለሰችላቸው፦ “አይ አልተናገሩም። ‘ያለቀስኩት እጅዎን ትከሻዬ ላይ በማሳረፍዎ ነው’ እያለ ነው። እዚህ እስኪመጣ ድረስ ለብዙ ዓመታት ማንም በእጁ ነክቶት አያውቅም።” ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽተኛውን መዳሰሱ ከዚህም የላቀ ጥቅም ነበረው። ከሰዎች እንዲገለል አድርጎት የነበረው በሽታ በዚያው ቅጽበት ተወገደ!

      13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ናይን ከተማ አቅራቢያ ሲደርስ ምን አጋጠመው? ሁኔታውን ይበልጥ አሳዛኝ ያደረገውስ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በርኅራኄ ተነሳስቶ በናይን ላገኛት መበለት ምን አደረገላት?

      13 ርኅራኄ ከሐዘናቸው እንዲላቀቁ ለማድረግ አነሳስቶታል። ኢየሱስ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ሲመለከት አንጀቱ ይንሰፈሰፍ ነበር። ለምሳሌ በሉቃስ 7:11-15 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። ጊዜው በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት አጋማሽ አካባቢ ነው፤ ኢየሱስ ናይን ወደምትባለው የገሊላ ከተማ እየተጠጋ ነበር። ወደ ከተማዋ በር ሲቃረብ ወደ ቀብር የሚሄዱ ሰዎች ተመለከተ። ሁኔታው በጣም የሚያሳዝን ነበር። የሞተው ወጣት የአንዲት መበለት አንድያ ልጅ ነው። ይህች ሴት ከዚህ ቀደም ባሏን ቀብራለች። አሁን ደግሞ አንድ ልጇን አጣች፤ ምናልባትም የምትተዳደረው ይህ ልጅ በሚያደርግላት ድጋፍ ብቻ ሊሆን ይችላል። ለቀብር ይጓዙ ከነበሩት ሰዎች መካከል አልቃሾች፣ ሙሾ የሚያወርዱ ሰዎችና የሐዘን ዜማ የሚጫወቱ ዋሽንት ነፊዎችም ሳይኖሩ አይቀሩም። (ኤርምያስ 9:17, 18፤ ማቴዎስ 9:23) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ትኩረቱ ያረፈው በእናቲቱ ላይ ነው፤ ምናልባትም የልጇን አስከሬን በያዘው ቃሬዛ አጠገብ እየሄደች ምርር ብላ እያለቀሰች ይሆናል።

      14 ኢየሱስ በሐዘን ለተደቆሰችው ለዚህች እናት “በጣም አዘነላት።” ከዚያም በሚያረጋጋ ድምፅ “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ። ቃሬዛውን የተሸከሙት ሰዎች ምናልባትም ለቀስተኞቹ በሙሉ ቆሙ። ኢየሱስ “አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!” በማለት ለአስከሬኑ ተናገረ። ከዚያስ ምን ተከሰተ? “የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ”፤ ጭልጥ ካለ እንቅልፍ እንደነቃ ሰው ማለት ነው! ቀጥሎ ኢየሱስ ልጁን “ለእናቱ ሰጣት” የሚል ልብ የሚነካ ዘገባ እናነባለን።

      15. (ሀ) ኢየሱስ ለሰዎች እንዳዘነ የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በርኅራኄና በድርጊት መካከል ምን ዝምድና እንዳለ ያሳያሉ? (ለ) በዚህ ረገድ ኢየሱስን ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?

      15 ከእነዚህ ዘገባዎች ምን እንማራለን? በእያንዳንዱ ታሪክ ላይ በርኅራኄና እርምጃ በመውሰድ መካከል ያለውን ዝምድና ልብ በል። ኢየሱስ የሌሎችን መከራና ሥቃይ ሲያይ ሁሌም ይራራል፤ ርኅራኄው ደግሞ እነሱን ለመርዳት እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግዴታ አለብን። ይህን እንድናደርግ የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ሆኖም ይህ ሥራ የርኅራኄ መግለጫ መሆኑንም መዘንጋት የለብንም። እንደ ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ የምናዝን ከሆነ ልባችን ምሥራቹን ለእነሱ ለመንገር የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ማቴዎስ 22:37-39) ችግር ላይ ለወደቁ ወይም ላዘኑ የእምነት አጋሮቻችን ርኅራኄ ስለ ማሳየትስ ምን ማለት ይቻላል? ሰዎችን በተአምር ከበሽታ መፈወስ ወይም ከሞት ማስነሳት እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም አሳቢነታችንን በመግለጽ ወይም አቅማችን በፈቀደ መጠን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን።—ኤፌሶን 4:32

      “አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው”

      16. ኢየሱስ ተሰቅሎ እያለም እንኳ ይቅር ባይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

      16 ኢየሱስ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ በመሆንም የአባቱን ፍቅር ፍጹም በሆነ ሁኔታ አንጸባርቋል። (መዝሙር 86:5) ተሰቅሎ እያለም እንኳ ይቅር ባይ መሆኑን አሳይቷል። እጆቹና እግሮቹ በሚስማር ተቸንክረው ክብርን በሚነካ ሁኔታ እንዲሞት በተደረገበት ወቅት የተናገረው ቃል ምን ነበር? ይሖዋ፣ የሰቀሉትን ሰዎች እንዲቀስፍለት ተማጽኗል? በፍጹም፤ እንዲያውም “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ሲል አባቱን ለምኗል።—ሉቃስ 23:34b

      17-19. ኢየሱስ ሦስት ጊዜ የካደውን ሐዋርያው ጴጥሮስን ይቅር እንዳለው ያሳየው በምን መንገዶች ነው?

      17 ስለ ይቅር ባይነቱ ከዚህም በላይ ልብ የሚነካ ምሳሌ የምናገኘው ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ስላሳየው ምሕረት በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ከልብ ይወደው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ኒሳን 14 በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የመጨረሻ ምሽት ላይ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ወደ ወህኒ ለመውረድም ሆነ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጴጥሮስ ኢየሱስን ጨርሶ እንደማያውቀው በመናገር ሦስት ጊዜ ካደው! መጽሐፍ ቅዱስ ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስን በካደበት ወቅት የሆነውን ሁኔታ ሲገልጽ “ጌታ ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው” ይላል። ጴጥሮስ በሠራው ከባድ ኃጢአት ቅስሙ በመሰበሩ “ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።” በዚያው ዕለት ኢየሱስ ሲሞት ሐዋርያው ‘ጌታዬ ይቅር ብሎኝ ይሆን?’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 22:33, 61, 62

      18 ጴጥሮስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ረጅም ጊዜ መጠበቅ አላስፈለገውም። ኢየሱስ ኒሳን 16 ጠዋት ላይ ከሞት ተነሳ፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው በዚያኑ ዕለት ለጴጥሮስ በግል ተገለጠለት። (ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮንቶስ 15:4-8) ኢየሱስ ሽምጥጥ አድርጎ ለካደው ሐዋርያ እንዲህ ለየት ያለ ትኩረት የሰጠው ለምንድን ነው? ንስሐ ለገባው ለጴጥሮስ ያለው ፍቅርና ከፍ ያለ ግምት እንዳልቀነሰ ሊያረጋግጥለት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ የእሱን ይቅርታ እንዳገኘ እርግጠኛ እንዲሆን ሲል ሌላም ያደረገው ነገር አለ።

      19 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። በዚህ ወቅት ኢየሱስ፣ ሦስት ጊዜ የካደውን ጴጥሮስን ይወደው እንደሆነ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ጠየቀው። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ሲጠየቅ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰ። እርግጥ ነው፣ ልብን ማንበብ የሚችለው ኢየሱስ ጴጥሮስ ምን ያህል እንደሚወደው አሳምሮ ያውቃል። ሆኖም ለእሱ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት አጋጣሚ ለጴጥሮስ መስጠት ፈልጎ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የእሱን ‘ግልገሎች የመመገብ’ እና ‘የመጠበቅ’ ተልእኮ ሰጠው። (ዮሐንስ 21:15-17) ጴጥሮስ ቀደም ሲል የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር። (ሉቃስ 5:10) ሆኖም በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን እንዲጠብቅ በማሳሰብ በጴጥሮስ ላይ ምን ያህል እምነት እንዳለው የሚያሳይ ከባድ ኃላፊነት ሰጠው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሚያከናውኑት ሥራ ረገድ የጎላ ሚና የመጫወት ኃላፊነት ለጴጥሮስ ሰጥቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-41) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ይቅር እንዳለውና በእሱ ላይ ያለው እምነት እንዳልቀነሰ ሲያውቅ እንዴት እፎይ ብሎ ይሆን!

      ‘የክርስቶስን ፍቅር ታውቃለህ?’

      20, 21. በተሟላ ሁኔታ ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’ የምንችለው እንዴት ነው?

      20 በእርግጥም፣ የይሖዋ ቃል የክርስቶስን ፍቅር ግሩም በሆነ መንገድ ይገልጸዋል። ሆኖም እኛ ለኢየሱስ ፍቅር ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ “ከእውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር [ለማወቅ]” እንድንጥር አጥብቆ ይመክረናል። (ኤፌሶን 3:19) ከላይ እንደተመለከትነው ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች ስለ ክርስቶስ ፍቅር ብዙ የሚያስተምሩን ነገር አለ። ሆኖም በተሟላ ሁኔታ ‘የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ’ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ የሚናገረውን መማር ብቻውን በቂ አይደለም።

      21 ‘ማወቅ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በተግባር፣ በተሞክሮ” ማወቅ የሚል ፍቺ አለው። የኢየሱስን ስሜት በትክክል መረዳት የምንችለው ፍቅር በማሳየት ረገድ ስንመስለው ነው፤ ራሳችንን ሳንቆጥብ ለሌሎች በመስጠት፣ በርኅራኄ ተነሳስተን ለችግራቸው በመድረስና ከልብ ይቅር በማለት ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። በዚህ መንገድ “ከእውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር” እንዲሁ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ‘ማወቅ’ እንችላለን። ደግሞም ኢየሱስ የይሖዋ ፍጹም ነጸብራቅ በመሆኑ እሱን እየመሰልን በሄድን መጠን አፍቃሪ ወደሆነው አምላካችን ይበልጥ እየቀረብን እንደምንሄድ መዘንጋት የለብንም።

      a የረቢዎች ሕግ ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ሁለት ሜትር ገደማ መራቅ እንዳለበት ያዝዛል። ነፋስ የሚነፍስ ከሆነ ደግሞ ሕመምተኛው ቢያንስ 45 ሜትር ገደማ መራቅ ነበረበት። ሚድራሽ ራባ የተባለው የአይሁዶች መጽሐፍ አንድ ረቢ ከሥጋ ደዌ በሽተኞች ይሸሸግ እንደነበረ፣ ሌላው ረቢ ደግሞ እንዳይጠጉት ሲል ድንጋይ ይወረውርባቸው እንደነበር ይገልጻል። የሥጋ ደዌ በሽተኞች ሕዝቡ በጣም ያገልላቸውና ይጸየፋቸው የነበረ በመሆኑ ስሜታቸው ይጎዳ ነበር።

      b የሉቃስ 23:34 የመጀመሪያ ክፍል በአንዳንድ የጥንት ቅጂዎች ላይ አይገኝም። ሆኖም ተአማኒነት ባላቸው በሌሎች ብዙ ቅጂዎች ላይ ስለሚገኝ በአዲስ ዓለም ትርጉም እና በሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ተካትቷል። እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለሰቀሉት የሮም ወታደሮች እየተናገረ ሳይሆን አይቀርም። ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ማንነት የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ የሚያደርጉትን አያውቁም ሊባሉ ይችላሉ። በተጨማሪም እንዲገደል የጠየቁትን በኋላ ግን በእሱ ያመኑትን አይሁዳውያን አስቦም ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 2:36-38) እርግጥ ነው፣ ሞት እንዲፈረድበት ያደረጉት የሃይማኖት መሪዎች ይህን ተግባር የፈጸሙት የኢየሱስን ማንነት አውቀውና በክፋት ተነሳስተው በመሆኑ በምንም ዓይነት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ ይቅር ሊባሉ አይችሉም።—ዮሐንስ 11:45-53

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • ማቴዎስ 9:35-38 ኢየሱስ በምን ጉልህ መንገድ ርኅራኄውን አሳይቷል? ይህስ እኛን ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?

      • ዮሐንስ 13:34, 35 የክርስቶስን ፍቅር ማንጸባረቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      • ሮም 15:1-6 ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነውን የክርስቶስ አስተሳሰብ ልናንጸባርቅ የምንችለው እንዴት ነው?

      • 2 ቆሮንቶስ 5:14, 15 ለቤዛው ያለን አድናቆት በአመለካከታችን፣ በግባችንና በአኗኗራችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

  • “በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
    • በጉባኤ ስብሰባ ላይ ወንድሞችና እህቶች ደስ እያላቸው ሲጨዋወቱ።

      ምዕራፍ 30

      “በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”

      1-3. ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋ የተወልንን ምሳሌ መኮረጃችን ምን ውጤት ያስገኛል?

      “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት የሚከተለውን እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ፦ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር መልሶ ይክሳል። ፍቅርን መቀበል ደስታ የሚያስገኝ ቢሆንም ፍቅርን ለሌሎች መስጠት ወይም ማሳየት የሚያስገኘው ደስታ ግን እጅግ የላቀ ነው።

      2 ይህን እውነታ በሰማይ ካለው አባታችን ይበልጥ የሚያውቅ የለም። በዚህ ክፍል ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ከሁሉ የላቀ የፍቅር ተምሳሌት ነው። ከይሖዋ በላቀ ደረጃ ፍቅርን ያሳየ ማንም የለም፤ ይህን ባሕርይ ለረጅም ዘመን በማንጸባረቅ ረገድም ቢሆን ተወዳዳሪ አይገኝለትም። ታዲያ ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ሊያስደንቀን ይገባል?—1 ጢሞቴዎስ 1:11

      3 አፍቃሪ የሆነው አምላካችን በተለይ ፍቅርን በማሳየት ረገድ እሱን ለመምሰል እንድንጥር ይፈልጋል። ኤፌሶን 5:1, 2 “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤ . . . በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” ይላል። ፍቅርን በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ ከኮረጅን፣ በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ መቅመስ እንችላለን። በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ’ የሚሰጠንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ በማድረጋችን ይሖዋን እናስደስተዋለን፤ ይህ ደግሞ ትልቅ እርካታ ያስገኝልናል። (ሮም 13:8) ይሁን እንጂ ‘በፍቅር መመላለሳችንን መቀጠላችን’ አስፈላጊ የሆነባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።

      ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት

      አንድ ወንድም በዕድሜ ከእሱ የሚያንስ ወንድም ትከሻ ላይ እጁን ጣል አድርጎ ሲያበረታታው፤ ፊቱ ላይ ፈገግታ ይነበባል።

      ፍቅር ወንድሞቻችንን እንደምንተማመንባቸው እንድንገልጽላቸው ይገፋፋናል

      4, 5. ለእምነት ባልንጀሮቻችን የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      4 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ፍቅር ለእውነተኛ ክርስትና መሠረታዊ የሆነ ባሕርይ ነው። ፍቅር ከሌለን ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አንችልም። ከሁሉ የከፋው ደግሞ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት የሚያሳጣን መሆኑ ነው። የአምላክ ቃል እነዚህን እውነታዎች እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚያሳይ ተመልከት።

      5 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34, 35) “እኔ እንደወደድኳችሁ” ማለቱን ልብ በል፤ አዎን፣ ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት ፍቅር እንድናሳይ ታዝዘናል። በምዕራፍ 29 ላይ ኢየሱስ የሌሎችን ጥቅምና ፍላጎት በማስቀደም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ የላቀ ምሳሌ እንደተወልን ተመልክተናል። እኛም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት ይጠበቅብናል፤ ደግሞም ፍቅራችን ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች እንኳ ሳይቀር በግልጽ መታየት ይኖርበታል። በእርግጥም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀው ይህ የወንድማማች ፍቅር የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን የሚያሳውቅ መለያ ምልክት ነው።

      6, 7. (ሀ) የይሖዋ ቃል ለፍቅር የላቀ ግምት እንደሚሰጥ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የተናገረው ስለ የትኛው ፍቅር ነው?

      6 ፍቅር የሚጎድለን ቢሆንስ? ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር . . . ከሌለኝ በኃይል እንደሚጮኽ ደወል ወይም ሲምባል ሆኛለሁ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:1) የሚጮኽ ደወልም ሆነ ሲምባል የሚያወጡት ድምፅ የሚረብሽ ነው። እንዴት ተስማሚ ምሳሌ ነው! ፍቅር የሌለው ሰው፣ የሚረብሽና ጆሮ የሚያደነቁር ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ሊሰሙት እንደማይፈልጉት ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ ነው። እንዲህ ያለ ሰው ከሌሎች ጋር እንዴት ጥሩ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል? በተጨማሪም ጳውሎስ “ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:2) እስቲ አስበው፣ አንድ ሰው የቱንም ያህል ትልቅ ነገር ማከናወን ቢችል ፍቅር ግን ከሌለው “ጥቅሙ ምንድን ነው?” (ሕያው ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) የይሖዋ ቃል ለፍቅር ምን ያህል የላቀ ግምት እንደሚሰጥ ከዚህ መረዳት አይቻልም?

      7 ይሁንና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የሚገኙትን ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት እንመርምር። በዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ የሚገልጸው አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ወይም እኛ ለአምላክ ያለንን ፍቅር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ የተናገረው አንዳችን ለሌላው ልናሳየው ስለሚገባው ፍቅር ነው። ፍቅር የሚያደርጋቸውንና የማያደርጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝሯል።

      ፍቅር የሚያደርገው ነገር

      8. ታጋሽ መሆናችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

      8 “ፍቅር ታጋሽ . . . ነው።” ስለዚህ ፍቅር ለማሳየት ሌሎችን በትዕግሥት መቻል አለብን ማለት ነው። (ቆላስይስ 3:13) እንዲህ ዓይነት ትዕግሥት ማሳየት እንደሚያስፈልገን ጥያቄ የለውም። እኛም ሆንን አብረውን የሚያገለግሉት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም አንዳችን ሌላውን የምናበሳጭበት ጊዜ እንደሚኖር የታወቀ ነው። ታጋሾችና ቻዮች መሆናችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የሚፈጠሩ ቀላል ቅሬታዎችን እንዲሁ ማለፍ እንድንችል ይረዳናል፤ ይህም የጉባኤው ሰላም እንዳይደፈርስ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

      9. ለሌሎች ደግነት ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

      9 “ፍቅር . . . ደግ ነው።” ደግነት ሌሎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን በማድረግና አሳቢነት የሚንጸባረቅባቸውን ቃላት በመናገር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ፍቅር፣ ደግነት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች እንድንፈልግ ያነሳሳናል፤ በተለይ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች። ለምሳሌ ብቸኝነት የሚሰማቸውና ጠያቂ የሚያስፈልጋቸው አረጋዊ ወንድም ሊኖሩ ይችላሉ። ብቻዋን ሆና ልጆቿን የምታሳድግ ወይም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላት እህት እገዛ ወይም ማበረታቻ ያስፈልጋት ይሆናል። ወይም ደግሞ የሚያጽናናው ወዳጅ የሚፈልግ የታመመ ወይም ችግር ላይ የወደቀ ወንድም ሊኖር ይችላል። (ምሳሌ 12:25፤ 17:17) እነዚህ ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት ደግነት ለማሳየት የምንጥር ከሆነ የፍቅራችን እውነተኝነት በግልጽ ይታያል።—2 ቆሮንቶስ 8:8

      10. ሐቁን መቀበል አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ፍቅር ከእውነት ጎን እንድንቆምና እውነትን እንድንናገር የሚረዳን እንዴት ነው?

      10 “ፍቅር . . . ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ፍቅር . . . ከእውነት ጎን በደስታ ይቆማል” ይላል። ፍቅር እውነት ለሆነው ነገር እንድንቆምና ‘እርስ በርሳችን እውነትን እንድንነጋገር’ ይገፋፋናል። (ዘካርያስ 8:16) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የምንወደው ሰው ከባድ ኃጢአት ሠራ እንበል፤ ለይሖዋ እንዲሁም ስህተቱን ለሠራው ሰው ያለን ፍቅር ኃጢአቱን ለመሸፋፈን፣ ለማቃለል ይባስ ብሎም ስለ ጉዳዩ ለመዋሸት ከመሞከር ይልቅ አምላክ ያወጣው መሥፈርት የሚጠይቀውን ነገር እንድናደርግ ኃይል ይሰጠናል። እርግጥ ነው፣ እውነታውን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ሆኖም ለዚህ ወዳጃችን ከልብ የምናስብ ከሆነ የአምላክን ፍቅራዊ ተግሣጽ እንዲያገኝና እንዲስተካከል እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ምሳሌ 3:11, 12) በተጨማሪም በፍቅር የምንመራ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

      11. ፍቅር ‘ሁሉን ችሎ የሚያልፍ’ በመሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚሠሯቸውን ስህተቶች በተመለከተ ምን ማድረግ አይኖርብንም?

      11 “ፍቅር . . . ሁሉን ችሎ ያልፋል።” ይህ አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ፍቅር ሁሉን ይሸፍናል” ማለት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) አንደኛ ጴጥሮስ 4:8 “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” በማለት ይገልጻል። አዎን፣ በፍቅር የሚመራ አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልንጀሮቹን ድክመትና ገመና ሁሉ አይገልጥም። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችን የሚሠሯቸው ስህተቶች ቀላል ናቸው፤ በመሆኑም በፍቅር ልንሸፍንላቸው ይገባል።—ምሳሌ 10:12፤ 17:9

      12. ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልሞና ላይ እምነት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ ከጳውሎስ ምን ልንማር እንችላለን?

      12 “ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል።” የሞፋት ትርጉም ፍቅር “ምንጊዜም ጥሩ ጥሩውን ማመን ይቀናዋል” ይላል። የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር በጥርጣሬ ዓይን አንመለከትም። ፍቅር ስለ ወንድሞቻችን ‘ጥሩ ጥሩውን እንድናምን’ እና እንዳንጠረጥራቸው ይረዳናል።a ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው ፊልሞና፣ ትቶት ሄዶ የነበረውንና ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን የሆነውን አገልጋዩን አናሲሞስን በቀና መንፈስ እንዲቀበለው ለማበረታታት ነው። ጳውሎስ ፊልሞናን ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ በፍቅር ተማጽኖታል። ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ ያለውን መተማመን ሲገልጽ “ይህን የምጽፍልህ በዚህ እንደምትስማማ በመተማመንና ከምጠይቅህም በላይ እንደምታደርግ በማወቅ ነው” ብሏል። (ቁጥር 21) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እምነት እንደምንጥልባቸው እንድንነግራቸው ይገፋፋናል፤ ይህ ደግሞ መልካም ባሕርያቸው እንዲወጣ ያደርጋል።

      13. ለወንድሞቻችን መልካም እንደምንመኝ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      13 “ፍቅር . . . ሁሉን ተስፋ ያደርጋል።” ፍቅር ሁሉን ማመን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ተስፋ ያደርጋል። ወንድሞቻችንን ስለምንወዳቸው መልካም የሆነውን ነገር እንመኝላቸዋለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም “ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል” የሚሰጠውን ፍቅራዊ እርዳታ ተቀብሎ ይስተካከላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። (ገላትያ 6:1) እምነታቸው የተዳከመባቸው ወንድሞቻችንም ቢሆኑ ዳግመኛ በመንፈሳዊ እንደሚበረቱ ተስፋ እናደርጋለን። እምነታቸው እንዲጠነክር ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ ጥረት በማድረግ በትዕግሥት እንይዛቸዋለን። (ሮም 15:1፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) አንድ የምንወደው ሰው ከእውነት መንገድ ቢወጣ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ልጅ አንድ ቀን ልብ እንደሚገዛና ወደ ይሖዋ እንደሚመለስ ተስፋ እናደርጋለን።—ሉቃስ 15:17, 18

      14. በጉባኤ ውስጥ ጽናታችንን የሚፈታተን ሁኔታ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ፍቅር ሊረዳን የሚችለውስ እንዴት ነው?

      14 “ፍቅር . . . ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።” ጽናት፣ የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ወይም ችግር ሲያጋጥመን ተስፋ ቆርጠን ወደኋላ እንዳንል ይረዳናል። ጽናታችንን የሚፈታተን ነገር የሚመጣው ከጉባኤ ውጭ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎችም ፈተና ሊሆኑብን ይችላሉ። ወንድሞቻችን ፍጹማን ባለመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኙን ይሆናል። አሳቢነት የጎደለው አነጋገር ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ወይም አንድ የጉባኤ ጉዳይ እኛ ባሰብነው መንገድ እልባት አላገኘ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በጉባኤ ውስጥ የተከበረ አንድ ወንድም የሚያደርገው ነገር ሊያበሳጨንና ‘እንዴት አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያደርጋል?’ በሚል ስሜት ቅሬታ ሊያድርብን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ራሳችንን ከጉባኤው በማግለል ይሖዋን ማገልገላችንን እናቆማለን? ፍቅር ካለን እንዲህ እንደማናደርግ የታወቀ ነው! አዎን፣ ፍቅር ካለን አንድ ወንድም ያለበት ድክመት እሱም ሆነ መላው ጉባኤ ያለውን መልካም ጎን ማየት እንዲሳነን ሊያደርገን አይችልም። ፍቅር፣ ፍጽምና የጎደለው አንድ ሰው የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ነገር ምንም ይሁን ምን ለአምላክ ታማኝ እንድንሆንና ከጉባኤው ጎን እንድንቆም ይረዳናል።—መዝሙር 119:165

      ፍቅር የማያደርገው ነገር

      15. ተገቢ ያልሆነን ቅናት ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው? ፍቅር ይህን ጎጂ ስሜት እንድናስወግድ የሚረዳንስ እንዴት ነው?

      15 “ፍቅር አይቀናም።” ተገቢ ያልሆነ ቅናት በሌሎች ንብረት፣ መብት ወይም ችሎታ እንድንመቀኝ ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ቅናት ከራስ ወዳድነት የመነጨ ጎጂ ስሜት ሲሆን ይህን ስሜት ማስወገድ ካልተቻለ የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርስ ይችላል። የቅናት መንፈስ እንዳያድርብን ምን ሊረዳን ይችላል? (ያዕቆብ 4:5) በአጭር አነጋገር ፍቅር ነው። ይህ ውድ ባሕርይ ሌሎች ከእኛ የተሻለ ነገር ቢያገኙ ወይም ቢኖራቸው ከመቅናት ይልቅ አብረናቸው እንድንደሰት ያደርገናል። (ሮም 12:15) በተጨማሪም ፍቅር አንድ ሰው ባለው ልዩ ችሎታ ወይም ባከናወነው ላቅ ያለ ነገር ቢመሰገን ቅር እንዳንሰኝ ይረዳናል።

      16. ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወድ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት እያከናወንን ስላለው ነገር ጉራ ከመንዛት የምንታቀበው ለምንድን ነው?

      16 “ፍቅር . . . ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም።” ፍቅር ስለ ችሎታችን ወይም ስላከናወንነው ነገር ጉራ ከመንዛት እንድንቆጠብ ያደርገናል። ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ በአገልግሎት ስላገኘነው ስኬት ወይም በጉባኤ ውስጥ ስላገኘናቸው መብቶች ነጋ ጠባ እናወራለን? እንዲህ ያለው ጉራ የሌሎችን ቅስም ሊሰብርና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱ ሊያደርግ ይችላል። ፍቅር፣ አምላክ በሰጠን የአገልግሎት መብት ስላከናወንናቸው ነገሮች ጉራ ከመንዛት እንድንታቀብ ያደርገናል። (1 ቆሮንቶስ 3:5-9) ጳውሎስ እንዳለው ፍቅር “አይታበይም” ወይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚለው “ራሱን ከልክ በላይ ከፍ አድርጎ አይመለከትም።” ፍቅር ስለ ራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዳያድርብን ይረዳናል።—ሮም 12:3

      17. ፍቅር ለሌሎች እንዴት ያለ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል? ምን ዓይነት ምግባር ከማሳየትስ እንድንቆጠብ ያደርገናል?

      17 “ፍቅር . . . ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም።” ጨዋነት የጎደለው ምግባር ያለው ሰው ከሥርዓት ውጭ የሆነ ወይም ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ያደርጋል። እንዲህ ያለው ምግባር ለሌሎች ስሜት ደንታ ቢስ መሆንን የሚያሳይ ስለሆነ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው። በአንጻሩ ግን ፍቅር ሥርዓታማ እንድንሆንና ለሌሎች አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። ፍቅር ጨዋ እንድንሆን፣ አምላካዊ ምግባር እንዲኖረንና ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት እንድናሳይ ያደርገናል። በመሆኑም ፍቅር “አሳፋሪ ምግባር” ማለትም ክርስቲያን ወንድሞቻችንን የሚያሸማቅቅ ወይም ቅር የሚያሰኝ ጠባይ ከማሳየት እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ኤፌሶን 5:3, 4

      18. አፍቃሪ የሆነ ሰው ሁሉ ነገር እኔ ባልኩት መንገድ ካልሆነ ብሎ ድርቅ የማይለው ለምንድን ነው?

      18 “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን አገላለጽ “ፍቅር እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ አይልም” ሲል ተርጉሞታል። አፍቃሪ የሆነ ሰው ሁልጊዜ የእሱ ሐሳብ ብቻ ትክክል የሆነ ይመስል ሁሉም ነገር በእኔ መንገድ ካልተከናወነ አይልም። ከእሱ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በማግባባትና በማሳመን የእሱን አመለካከት እንዲደግፉ ለመጫን አይሞክርም። እንዲህ ያለው ግትርነት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከኩራት የመነጨ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “ኩራት ጥፋትን . . . ይቀድማል” ይላል። (ምሳሌ 16:18) ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ አመለካከታቸውን የምናከብር ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእኛን አመለካከት ለመለወጥ ፈቃደኞች እንሆናለን። ይህም ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ” ሲል የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል።—1 ቆሮንቶስ 10:24

      19. ፍቅር ካለን ሌሎች ሲያስቀይሙን ምን እናደርጋለን?

      19 “ፍቅር . . . በቀላሉ አይበሳጭም። . . . የበደል መዝገብ የለውም።” ፍቅር ሌሎች በሚናገሩትም ሆነ በሚያደርጉት ነገር ቶሎ አይበሳጭም። እርግጥ ነው፣ ሌሎች ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲፈጽሙብን እንደምናዝን የታወቀ ነው። ሆኖም እንድንቆጣ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ቢኖረንም እንኳ ፍቅር ካለን ቁጣችን ቶሎ ይበርዳል። (ኤፌሶን 4:26, 27) ቅር ያሰኘንን አነጋገር ወይም ድርጊት በመዝገብ ጽፈን የመያዝ ያህል ሁልጊዜ በውስጣችን ይዘን አንኖርም። ከዚህ ይልቅ ፍቅር ካለን አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል እንገፋፋለን። በምዕራፍ 26 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እስካለ ድረስ ይቅር ይላል። አንዴ ይቅር ካለ ደግሞ የሠራነውን በደል ዳግመኛ አያስበውም፤ ወይም ያንኑ ጥፋት መልሶ መላልሶ እየጠቀሰ አይወነጅለንም። ይሖዋ የበደል መዝገብ የማይዝ አምላክ በመሆኑ አመስጋኞች መሆን አይገባንም?

      20. አንድ የእምነት ባልንጀራችን በኃጢአት ወጥመድ ቢወድቅና መጥፎ ነገር ቢደርስበት ምን ሊሰማን አይገባም?

      20 “ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ፍቅር . . . ሌሎች ሰዎች በኃጢአት ሲወድቁ በማየት አይፈነድቅም” ይላል። የሞፋት ትርጉም ደግሞ “ፍቅር ሌሎች ሲሳሳቱ አይደሰትም” ይላል። ፍቅር በዓመፅ የማይደሰት በመሆኑ ማንኛውንም የሥነ ምግባር ብልግና አቅልለን አንመለከትም። አንድ የእምነት ባልንጀራችን በኃጢአት ወጥመድ ቢወድቅና መጥፎ ነገር ቢደርስበት ምን ይሰማናል? ፍቅር ካለን ‘ጎሽ፣ ዋጋውን አገኘ!’ ብለን አንደሰትም። (ምሳሌ 17:5) ከዚህ ይልቅ ኃጢአት የሠራ አንድ ወንድም አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ ከደረሰበት መንፈሳዊ ውድቀት ሲያገግም ስንመለከት ደስ ይለናል።

      ‘ከሁሉ የላቀው መንገድ’

      21-23. (ሀ) ጳውሎስ “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ለ) በዚህ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?

      21 “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።” ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ለጥንት ክርስቲያኖች ስለተሰጡት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ነው። እነዚህ ስጦታዎች አምላክ፣ በወቅቱ በተቋቋመው አዲስ ጉባኤ እየተጠቀመ መሆኑን የሚያመለክቱ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች መፈወስ፣ መተንበይ ወይም በልሳን መናገር ይችሉ ነበር ማለት አይደለም። ሆኖም አንድ ክርስቲያን እነዚህ ስጦታዎች ኖሩት አልኖሩት የሚያመጣው ለውጥ አልነበረም፤ ምክንያቱም እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎች ለሁልጊዜው የሚቀጥሉ አልነበሩም። ይሁንና ማንኛውም ክርስቲያን ሊያዳብረው የሚችል ለዘላለም የሚቀጥል አንድ ነገር አለ። ይህ ነገር ከየትኛውም ተአምራዊ ስጦታ የላቀና ለዘላለም የሚጸና ነው። እንዲያውም ጳውሎስ ‘ከሁሉ የላቀው መንገድ’ ሲል ጠርቶታል። (1 ቆሮንቶስ 12:31) ይህ ‘ከሁሉ የላቀ መንገድ’ ምንድን ነው? የፍቅር መንገድ ነው።

      22 በእርግጥም ጳውሎስ የገለጸው ክርስቲያናዊ ፍቅር “ለዘላለም ይኖራል”፤ በሌላ አነጋገር የሚያከትምበት ጊዜ አይኖርም። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀው የወንድማማች ፍቅር እስከዛሬም ድረስ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መለያ ምልክት ነው። በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ይህ ፍቅር እየታየ አይደለም? ይሖዋ ታማኝ ለሆኑት አገልጋዮቹ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጥ ቃል የገባ በመሆኑ ይህ ፍቅር ዘላለማዊ ነው። (መዝሙር 37:9-11, 29) እንግዲያው ‘በፍቅር መመላለሳችንን ለመቀጠል’ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ ማጣጣም እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ አፍቃሪ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በመምሰል ለዘላለም ፍቅርን እያንጸባረቅን መኖር እንችላለን።

      የይሖዋ ሕዝቦች መለያ ምልክት እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር ነው

      23 ስለ ፍቅር የሚያብራራው ክፍል መደምደሚያ በሆነው በዚህ ምዕራፍ ላይ አንዳችን ለሌላው ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። ይሁንና ከይሖዋ ፍቅር ብሎም ኃይል፣ ፍትሕና ጥበብ በእጅጉ የምንጠቀም ከመሆኑ አንጻር ‘ይሖዋን ከልብ እንደምወደው ላሳየው የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ይህ ጥያቄ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

      a እርግጥ ይህ ሲባል ክርስቲያናዊ ፍቅር በቀላሉ ይታለላል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፍፍል ከሚፈጥሩና ለእንቅፋት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን ከሚያመጡ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ . . . ይህን ከሚያደርጉ ሰዎች ራቁ” ሲል ያሳስበናል።—ሮም 16:17

      ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች

      • 2 ቆሮንቶስ 6:11-13 ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት ሲባል ምን ማለት ነው? ይህን ምክር ልንሠራበት የምንችለውስ እንዴት ነው?

      • 1 ጴጥሮስ 1:22 በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኙት ቃላት ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ልባዊ፣ እውነተኛና ሞቅ ያለ መሆን እንዳለበት የሚያሳዩት እንዴት ነው?

      • 1 ዮሐንስ 3:16-18 “የአምላክ ፍቅር” በውስጣችን እንዳለ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

      • 1 ዮሐንስ 4:7-11 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር እንድናሳይ የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ